የክርስቶስ አምላክነት በቆላስይስ 1፡15-20 

በሚመጡት ሳምንታት ስለ ኢየሱስ ሥጋ መልበስ (ተሠግዎ) እናጠናለን። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን የሚናገሩ በርከት ያሉ ሌሎች ጥቅሶችን እንማራለን። ዛሬ ግን የኢየሱስን መለኮትነት የሚያጠናክረውንና ነገር ግን አንዳንድ የኑፋቄ ቡድኖች ለሐሰት ትምህርታቸው አላግባብ የሚጠቀሙበትን ጥቅስ ዘርዘር አድርገን እናጠናለን። ደግሞም እነዚህ አሳሳች ክፍሎች ኢየሱስን እግዚአብሔር ፈጠረው፥ እናም ኢየሱስ አምላክ አይደለም በማለት ለሐሰት ትምህርታቸው የሚጠቀሙበትን ሌላ ጥቅስ በአጭሩ እናጠናለን። 

ቆላስይስ 1፡5-20 

35ኛ ጥያቄ፡- ቆላስይስ 1፡15-20 አንብቡ። በምታነቡበትም ጊዜ ይህ ክፍለ ምንባብ ስለ ኢየሱስ አምላክነት የሚያስተምርባቸውን የተለያዩ መንገዶች ጻፉ። 36ኛ ጥያቄ፡- ቆላስይስ 1፡15-18 አንብቡ። ሀ) ኢየሱስ እግዚአብሔርን እንዴት አድርጎ ይገልጻል? ለ) ኢየሱስ አምላክ አይደለም ብለው ለማለት የሐሰት መምህራን ጥቅሱን እንዴት ይጠቀሙበታል? ልትለጧቸው ስለምትችሉት መልስ ማሰብ ትችላላችሁ? ሐ) ኢየሱስ ምንን ፈጠረ? እርሱ እግዚአብሔር መሆኑን ይህ እንዴት ያረጋግጣል? መ) ክርስቶስ ምን ያህል ኖረ? ሠ) ክርስቶስ በአሁኑ ጊዜ ለፍጥረተ ዓለም (ዩኒቨርስ) ምን እያደረገ ነው? ረ) ኢየሱስ የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው ሲባል ምን ማለት ይመስላችኋል? 

ቆላስይስ 1፡5-20 የኢየሱስን አምላክነት አጥብቆ የሚያረጋግጥ ክፍል ነው። ነገር ግን ይህ ክፍል የእርሱን አምላክነት የሚከዱ አንዳንድ ሃይማኖቶችም የሚጠቀሙበት ነው። ቆላስይስ 1፡15-16 ክርስቶስ የእግዚአብሔር ምሳሌ ነው በማለት ይጀምራል። ምሳሌ ለሚለው የገባው የግሪኩ ቃል ልጁ እግዚአብሔርን በትክክል እንደሚገልጸው ያስገነዝባል። ምሳሌ ሲባል እውነተኛ ያልሆነ ነገር ማለት አይደለም። ይልቅስ «ለአንድ ነገር የተወከለና የዚያንም ነገር መሠረታዊ ባሕርይ የሚገልጽ ምሳሌ ማለት ነው። እንዲያውም ያንኑ ነገር ሊሆንም ይችላል።» ላለዚህ ቆላስይስ 1፡5፥ «እግዚአብሔር አይታይም፤ ግን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ራሱን ገልጾአል፤ ራሱንም ወክሏል፥ ባሕርይውንም አሳይቷል» ይላል። ይህ ሐረግ ልጁ የእግዚአብሔርን መሠረታዊ ባሕርይ እንደሚገልጽ ይናገራል። እና ይህ የሚያመለክተው እርሱ አምላክ መሆኑን ነው። 

የሚቀጥለው ሐረግ ደግሞ ይበልጡኑ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን አጉልቶ ያመለክታል። እርሱ በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ እንደ ፈጠረ ይናገራል። ሌሎች ዙፋኖች፥ ጌቶች፥ ገዢዎችና ሥልጣናት በኢየሱስ የተፈጠሩና ለሥልጣኑ የሚገዙ ዝርዝሮች ናቸው። እዚህ ላይ ጳውሎስ የሚናገረው ስለ ሰብአዊ ሥልጣናትም ብቻ ሳይሆን ስለ መንፈሳዊ ሥልጣናት ነው። ወልድ ሁሉንም መላእክትንና በኋላ ወደ ኃጢአት ወድቀው አጋንንት የሆኑትን መናፍስትንም ጭምር ፈጥሮአል። ስለሆነም ኒየሱስ ሁሉንም በመፍጠሩ በላያቸው ላይ ሥልጣን አለው። ሊፈጥር የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው። በመናፍስት ዓለምም ላይ ሥልጣን ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለዚህ ይህ ጥቅስ በግልጽ ኢየሱስ አምላክ እንደሆነ ያስተምረናል። 

እንዲሁም ልጁ «የፍጥረታት ሁሉ በኩር ነው፡፡» አንዳንድ የኑፋቄ ክፍሎች “በኩር” የሚለውን ቃል ይመለከቱና እንዲህ ማለት ልጁ መጀመሪያ አለው ማለት ነው ብለው ያስባሉ። እነዚህ መናፍቃን አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ቃል ይለውጣሉ። ኢየሱስ ሁሉን ነገር» ፈጠረ በማለት ፈንታ ጥቅሱን ለውጠው «ሌሎች» የሚል ቃል ይጨምሩበታል። እርሱ «ሌሎችን ነገሮች ሁሉ ፈጠረ» ይላሉ። ነገር ግን «ሌሎች» የሚለው ቃል በመጀመሪያ በተጻፈው ግሪክ ውስጥ የለም። ኢየሱስ የተፈጠሩትን ነገሮች ሁሉ ፈጠረ። ይህ በግልጽ እንደሚያስረዳው እርሱ ራሱ አልተፈጠረም ማለት ነው። 

በተጨማሪም፥ «በኩር” የሚለው ቃል ልጁ ጅማሬ አለው ማለትም አይደለም። በኩር” የሚለው ቃል «በጊዜ ረገድ የመጀመሪያው» ማለትም አይደለም። በዚህ ፈንታ እገላለጹ አብዛኛውን ጊዜ «ዋነኛ» ማለት ነው። በአይሁድ ባሕል የበኩር ልጅ ሕጋዊ ወራሽ ነው። የበኩር መብትና ቡራከም የሚያገኘው እርሱ ነው (ዘፍጥረት 25፡24-34፤ 27፡1-4) እንዲሁም 48፡1 20 እንደ ምሳሌ ተመልከቱ።) ስለዚህ የበኩር ልጁ እጅግ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው፡ ነገር ግን የበኩር ልጅ መብት ለሌላ ሊተላለፍ ይችላል። በጊዜም ሁኔታ ከታየ ያዕቆብ የይስሐቅ የበኩር ልጅ አይደለም። ነገር ግን እንደ ስኩር ልጅ ታይቷል። በዘፀአት 422 ላይ እግዚአብሔር እስራኤልን የበኩር ልጄ ይለዋል። (እስራኤል የያዕቆብ ሌላው ስሙ ነው።) እንዲህ ማለት እስራኤል ልዩ በረከትና እንክብካቤ የሚያገኝ የእግዚአብሔር ሕዝብ ማለት ነው። በጊዜ ሁኔታ ከሄድን ኤፍሬም የዮሴፍ የበኩር ልጅ አይደለም። ነገር ግን እንደ በኩር ልጅ ተቀጠረ። እንዲያውም እግዚአብሔር የበኩር ልጄ ይለዋል (ኤርምያስ 31፡9)። በመዝሙር 89፡7 ላይ ምንም እንኳን ጻዊት ለቤተሰቡ የበኩር ልጅ ባይሆንም፥ እግዚአብሔር ዳዊትን «የበኩር» ንጉሥ ብሎ ይጠራዋል። ጻዊት ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ አልነበረም። ለእስራኤልም የመጀመሪያው ንጉሥ አልነበረም፡ ቢሆንም በልዩ ሁኔታ እግዚአብሔር የመረጠው ንጉሥ ነበር። በመጨረሻም፥ በዚሁ ክፍለ ምንባብ በቆላስይስ 18 ኢየሱስ ከሞት በመነሣት ፊተኛ» ነው ይላል። ኢየሱስ ከሞት በመነሣት የመጀመሪያው ሰው አልነበረም። ኤልሳዕ የመበለቷን ልጅ ከእርሱ በፊት ከሞት አስነሥቶታል (2ኛ ነገሥት 4፡2-37)። ኢየሱስም የኢያኢሮስን ለት ልጅ (ማርቆስ 5፡41-42) እና አልዓዛርን (ዮሐ 1፡43-44) ከራሱ ትንሣኤ በፊት ከሞት አስነሥቶአቸዋል። ከሞት በመነሣት ፊተኛውና መጀሪያው ሲባል ከሞት በመነሣት እርሱ በጣም በተለየ ሁኔታ ይታያል ለማለት እንጂ፥ እርሱ ከሞት በመነሣት በታሪክ የመጀመሪያው ሰው ነው ማለት አይደለም። 

በመሆኑም በኩር ወይም የመጀመሪያው ሲባል «እጅግ በጣም የታወቀና በተለየ ሁኔታ በእግዚአብሔር የተመረጠ» ማለት ነው። ኢየሱስ እግዚአብሔር የፈጠረው የመጀመሪያው ፍጡር ነው የሚልና እርሱ የፍጥረታት አካል ነው የሚል ትርጉም አይሰጥም። ይልቅስ ጥቅሱ የሚያስተምረው ኢየሱስ እጅግ በጣም የታወቀና ፍጥረታትን ሁሉ የሚገዛ መሆኑን ነው። 

በቆላስይስ 1፡17 ውስጥ ጳውሎስ ትርጉሙን ፍጹም ግልጽ ያደርገዋል። ክርስቶስ የተፈጠሩትን ሁሉ የፈጠረ በመሆኑ እርሱ ከፍጥረታት በፊት ቀድሞ እንደነበረ ግልጽ ነው። እርሱ ሁልጊዜም ነበረ። ነገር ግን ፈጣሪ ብቻም አልነበረም። በአሁኑ ጊዜ ፍጥረታትን በአንድነት የያዘም እርሱ ነው። ሳይንቲስቶች የደረሱበት እንደ ስበት ኃይል (ግራቪቲ) ያሉትን የተፈጥሮ ሕይወት በግዙፉ ዓለም ውስጥ በሥርዓት ያደረገና የሚቆጣጠር ክርስቶስ ነው። አንድ የግሪክ ፈላስፋ ሲናገር ፍጥረተ ዓለምን (ዩኒቨርስን) በአንድነት ያስተሳሰረው ሰንሰለት «ቃል» ነው ብሏል። ጳውሎስም በዚህ አገላለጽ ይስማማል። ነገር ግን እርሱ ጨመር አድርጎ ያ ሰንሰለት ዮሐንስ «ቃል» ብሎ የጠራው (ዮሐንስ 1፡1) ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ይላል። በእርግጥም ፍጥረተ ዓለምን (ዩኒቨርስን) በሙሉ በአንድነት ሊይዝ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ፍጠረተ ዓለምን (ዩኒቨርስን) በአንድነት መያዝ ስለሚችል ኢየሱስ እርሱ አምላክ መሆን አለበት። 

ጥያቄ፡- ቆላስይስ 1፡18 አንብቡ። ሀ) ክርስቶስ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያለው ንኙነት ምንድን ነው? ለ) ክርስቶስ ከፍጥረት ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? 

ክርስቶስ ከሞት በመነሣት ፊተኛና መጀመሪያ መሆኑን ቁጥር 18 ላይ ተመልክተናል። ነገር ግን በዚህ ጥቅስ ውስጥ ስለ ክርስቶስ ጌትነት የሚያመለክቱ ሁለት ጠቋሚ አሳቦችም አሉ። በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ እርሱ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው ይላል። ቀጥሎም፥ እርሱ የመጀመሪያ እንደሆነና ከሁሉ ነገር በፊት እርሱ ነበር ብሎ ይናገራል። ይህ ቁጥር ለየት አድርጎ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው አይልም። ነገር ግን እርሱ እግዚአብሔር በመረጠው ሕዝብ እና በፍጥረታት ሁሉ ላይ ጌታ ነው ይላል። ይህ ጥቅስ ክርስቶስን ከፍጥረታት ሁሉ በላይ አድርጎ ስላሚያቀርበው የእርሱን መለኮትነት ይገልጻል። 

ጥያቄ፡- ቆላስይስ 1፡19-20 አንብቡ። ሀ) ጳውሎስ በክርስቶስ ውስጥ ምን አለ ይላል? ለ) እንዲህ ማለትስ ምንድን ነው ብላችሁ ታስባላችሁ? 

በቆላስይስ 1፡19 ላይ ጳውሎስ፥ «የመለኮት ሙላት በልጁ ውስጥ ይኖራል» ይላል። እንዲህ ማለት ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኃይልና ባሕርያት ሁሉ አለው ማለት ነው። እግዚአብሔር የሚሆነውን ሁሉ ክርስቶስም ነው። የክርስቶስ ሕልውናዊ ባሕርይ ልክ እንደ እግዚአብሔር ሕልውናዊ ባሕርይ ነው። በመሆኑም ለሐዋርያው ጳውሎስ የእግዚአብሔር ሙላት በእርሱ ውስጥ ይኖራል ከማለት የተሻለ የክርስቶስን አምላክነት አጥብቆ የሚገልጽበት ቃል ሊኖረው አይችልም። 

ቆላስይስ 1፡15-20 ያለው ቃል ስለ ክርስቶስ መለኮታዊነት ግልጽና ጠንካራ የሆነ አገላለጽ ነው። ምንም እንኳን አንዳንድ መናፍቃን ልጁ ፍጡር ነው መጀመሪያም አለው ለማለት እንዲያመቻቸው በቁጥር 5 ላይ ወደ ተጻፈው «ሰኩር» ወደሚለው ቃል ቢያመለክቱም፥ ከጥቅሱ ጭብጥ እንደምንረዳው ከሆነ ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ እግዚአብሔር ነው። በዚህ ክፍል «በኩር» ማለት ክርስቶስ ወደር የሌለው ታላቅና ፍጥረታትን ሁሉ የሚገዛ ማለት ነው እንጂ እርሱ የእግዚአብሔር ፍጥረት አካል ነው ማለት አይደለም። 

ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቶስ ፈጣሪና የፍጥረታት ሁሉ ገዥ ከሆነ እኛ ለእርሱ ምላሽ መስጠት ያለብን እንዴት ነው? በዚህ ሳምንት ውስጥ ለክርስቶስ በመታዘዝ ልታከናውኑት በዕቅድ የያዛችሁትን አንድ የተወሰነ ተግባር ጻፉ። ለ) ክርስቶስ እግዚአብሔርን የሚያሳይ ከሆነ ክርስቶስን በማወቅ እንዴት እድርገን እግዚአብሔርን ልናውቀው እንችላለን? ስለዚህ በዚህ ሳምንት ውስጥ በተሻለ ሁኔታ ክርስቶስን በግል ለማወቅ የምታቅፍበትን አንድ መንገድ ጻፉ። 

ክርስቶስ የፍጥረት ሁሉ ጌታና የቤተ ክርስቲያን ራሱ ስለሆነ አማኞች ሁሉ እንደ ግል ጌታቸው አድርገው ሊቀበሉት ይገባል። የእርሱንም ፈቃድ ለመገንዘብ አማኛች ሁሉ ቃሉን ማጥናት ይኖርባቸዋል። ከዚያም ለቃሉ መታዘዝን ቀዳሚ ተግባራቸው ማድረግ አለባቸው። 

ክርስቶስ ፍጹም የሆነ የእግዚአብሔር መግለጫ ስለሆነ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ የሚያበቃው መንገድ ክርስቶስን ማወቅ ነው። ስለዚህ አማኞች ሁሉ እርሱን በቃሉ ውስጥ ፀጥ ብሎ ማድመጥን፥ 

መጸለይን፥ ቀኑን ሙሉ እርሱን ማሰብን፥ እንደዚሁም ቀን የሚያጋጥማቸውን ሁሉ ወደ እርሱ በማቅረብና «ኢየሱስ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምን ድርሻ አለው?» ብሎ መጠየቅን ቀዳሚ ተግባራቸው ሊያደርጉ ይገባል። በመሆኑም አማኞች ሁሉ እግዚአብሔር የተገለጠበትን ክርስቶስን የማወቁን ነገር ቀዳሚ ሥራቸው ሊያደርጉ ይገባል። 

ምሳሌ 8፡22 

ጥያቄ፡- ምሳሌ 8፡1 እና 12 አንብቡ። ሀ) በተዘረዘሩት ጥቅሶች ውስጥ የሚነገረው ስለ ምንድን ነው? ለ) ምሳሌ 8፡22 አንብቡ። በመጀመሪያው መልሳችሁ መሠረት ያልተደረገው ምንድን ነው? 

አንዳንድ መናፍቃን እግዚአብሔር አብ ቃልን ወይም ክርስቶስን ፈጠረ ይሉና ቃሉ ራሱ እግዚአብሔር አይደለም ይላሉ። እነዚህ መናፍቃን እንደሚሉት በምሳሌ 8፡22 ላይ የሚናገረው አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተበጀው ወይም የተፈጠረው ነው። የሚናገረው ቃሉ ወይም ክርስቶስ እንደሆነ አድርገው ስለሚገምቱና እግዚአብሔር ቃልን ፈጠረ ብለው ይገምታሉ። ቃሉ የተፈጠረ ከሆነ ደግሞ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር አይደለም ብለው ይክዳሉ። 

ሆኖም ግን፥ በምሳሌ 8፡12 ውስጥ ተናጋሪው ጥበብ ናት እንጂ ቃሉ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። የመጽሐፈ ምሳሌ አንዱና ዐቢይ ዓላማ ማንም ሰው ጥበብን በትጋት እንዲከተል ነው። ስለዚህ በዚህ ክፍለ ምንባብ ውስጥ የጥበብን ጠቃሚነት ለማሳወቅ ጥበብ ራሷ እንደ ሰው ትናገራለች። የመጽሐፈ ምሳሌ ይዘት ሥነ-ግጥማዊ ነው። በሥነ ግጥም ደግሞ ጥበብ እንደ ሰው ትናገራለች። ጥበብ የእሴቱንና የጠቃሚነቱን ትልቅነት ለመግለጽ፥ እንደ ሰው በመናገር፥ በመጀመሪያ እግዚአብሔር እንደ ፈጠራት ትገልጻለች። ነገር ግን እግዚአብሔር ከፍጥረት በፊት ጥበብ አልነበረውም? ያለጥርጥር ነበረው። ከዕብራይስጥ ወደ አማርኛ የተተረጎመው ቃል፡- «አደረገ ወይም ፈጠረ ይላል። «አደረገ» በአሮጌው ትርጉም ሲሆን፥ «ፈጠረ» ደግሞ በአዲሱ ትርጉም ነው። «የእርሱ የሆነውን እንዲፈጠር አደረገ» ማለት ነው። ምሳሌ 8፡22 እንደሚለው፥ «እግዚአብሔር ጥበብ ስለነበረው ጥበብን የሥራው መጀመሪያ አደረገው።» እግዚአብሔር ጥበብ ስለነበረው፥ እናት ልጅን እንደምትወልድ ሁሉ፥ እግዚአብሔር ጥበብን በፍጥረቱ መጀመሪያ ገልጾ አሳየ። ይህ ጥቅስ እግዚአብሔር ክርስቶስን ፈጠረ አይልም። ጥቅሱ የሚለው እግዚአብሔር ዓለምን በሚፈጥርበት ጊዜ ጥበብን የመጀመሪያው ነገር በማድረጉና በመግለጹ የጥበብ እሴት ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ታይቷል።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading