ጥያቄ፡- ዮሐ 6፡53-54 እንብብ። ሀ) ጌታ ኢየሱስ፥ አንድ ሰው ሕይወትን ማግኘት ከፈለገ ምን ያድርግ ይላል? ለ) ጌታ ኢየሱስ አንድ ሰው ሥጋውን ቢበላና ደሙን ቢጠጣ ምንን ያገኛል አለ?
ጥያቄ ዮሐ. 6፡35 አንብብ። ጌታ ኢየሱስ አንድ ሰው እንዳይራብ ወይም እንዳይጠማ ምን ያድር አለ?
ብዙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ጸጋ ተቀብለው ለመዳን ሲሉ ቅዱስ ቁርባንን መቀበል ይፈልጋሉ። ሌሎች ደግሞ ካልቀረቡ በስተቀር ሊድኑ እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። የተቀሩት ሰዎች ደግሞ፥ የቅዱስ ቁርባን ተካፋዮች በመሆን የእግዚአብሔርን ጸጋ በመቀበል መዳናቸውን እንደሚያረጋግጡ ያምናሉ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እነዚህ ሰዎች በቅዱስ ቁርባን ላይ መሳተፍ በዮሐንስ 6፡53-54 ውስጥ እንደተጻፈው የእግዚአብሔርን የማዳን ጸጋ የሚያሰጣቸው መሆኑን ለአሳባቸው ድጋፍ አድርገው ያቀርባሉ፡ በዚህ ክፍል ኢየሱስ የሚናገረው፥ ሰዎች «ሥጋውን በልተው፥ ደሙን የሚጠጡት» ሕይወትን ለማግኘት ስለሆነ፥ ማንም ሰው ሥጋውን የሚበላና ደሙን የሚጠጣ ሁሉ የዘላለም ሕይወትን ያገኛል። ለአንዳንድ ሰዎች ጌታ ኢየሱስ ስለ ቅዱስ ቁርባን የተናገረ ይመስላቸዋል። በመጀመሪያ ጊዜ፥ ኢየሱስ ቅዱስ ቁርባንን ለደቀ መዛሙርቱ በሰጠ ጊዜ፥ «ይህ ለእናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነው። ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ የሚፈጸም አዲስ ኪዳን ነው» አላለምን? (1ኛ ቆሮንቶስ 11፡24-25። እነዚህ ሰዎች በቅዱስ ቁርባን ጊዜ ኅብስቱን መብላትና ከጽዋው መጠጣት የዘላለምን ሕይወት የሚሰጣቸው አድርጎ ኢየሱስ የተናገረ አድርገው ያምናሉ።
ሆኖም፤ ደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን እንዲበሉና ደሙንም እንዲጠጡ ኢየሱስ ሲነግራቸው ምን ማለቱ እንደሆነ በጣም የተሻለ ማብራሪያ አለ። በዮሐንስ 6፡53-54 ውስጥ ኢየሱስ ስለ ኅብስት ከአይሁዶች ጋር ያደረገው ረጅም ውይይት ከፊሉ ይገኛል። የመጽሐፍ ቅዱስን አንድ ክፍለ ምንባብ ትርጉም የመተንተን የመጀመሪያውና እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆነው መመሪያ፥ የክፍለ ምንባቡን ጭብጥና ይዘት ማጥናት ነው። ኢየሱስ በዮሐንስ 6፡52-53 ውስጥ ስለተናገረው ጥቅል ትርጉም ለመተንተን የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 6 መላውን ክፍል ማጥናት ይገባናል። በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 6 በመጀመሪያዎቹ ጥቅሶች ላይ ኢየሱስ አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣዎችን ለአምስት ሺህ ሰዎች እንደ መገበ እንነዘባለን። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሕዝቡን ተለይቶ ሄደ። ወዲያው ቀን አገኙት (ዮሐንስ 6፡25)። ሕዝቡ ኢየሱስን ባገኙት ጊዜ፥ እንጀራ ስላበላቸው የፈለጉት መሆናቸውን ነገራቸው። ቀጥሎም፥ ለሚጠፋ ምግብ አትሥሩ፥ የዘላለም ለሚሆን ምግብ ሥሩ አላቸው (ዮሐንስ 26፡27)። ነገር ግን አይሁዶቹ በሥጋዊ ምግብ ፍላጎት ስላየለባቸው፥ ኢየሱስ እነርሱን ለመመገብ ሌላ ተአምር እንዲፈጽም ጠየቁት (ዮሐ 6፡31-32)። ከዘላለም ሕይወት ይልቅ ምግብን አስበልጠው ስላዩ፥ እርሱ ከሰጣቸው ሥጋዊ ምግብ ይልቅ እርሱን እንዲች አሳሰባቸው። እውነተኛ የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የመጣው መሆኑን ነገራቸው (ዮሐ. 6፡33)። ሰዎቹ ግን አሁንም ኢየሱስ ስለ ዓለማዊ እንጀራ የሚናገር መሰላቸው። ይህን እንጀራ እንዲሰጣቸው ጠየቁት (ዮሐ 6፡34)። በጣም ጠቃሚ በሆነ ጥቅስ አማካይነት ኢየሱስ ስለሚናገረው በትክክል ያስገነዝባቸዋል። በዮሐንስ 6፡35 ውስጥ ኢየሱስ ራሱ ከሰማይ የመጣ እንጀራ መሆኑንና ወደ እርሱ የሚመጣ ጨርሶ እንደማይራብ፥ የሚያምንበትም የማይጠማ መሆኑን ይነግራቸዋል። ኢየሱስ የመንፈስን ምግብና መጠጥ የማግኘቱ መንገድ ወደ እርሱ ዘንድ መምጣትና በእርሱ ማመን መሆኑን በማስረዳት፥ ወደ እርሱ ዘንድ ቢመጡ እርሱ ከሰማይ የመጣ እንጀራ ስለሆነ በፍጹም የማይራቡና በመንፈስም የማይጠሙ መሆናቸውን አስገንዝቦአቸዋል። ኢየሱስ ከሰማይ ስለ መምጣቱ በተናገረ ጊዜ አይሁዶች አጉረመረሙ (ቁጥር 41-42)። ምክንያቱም እርሱ የተናገረው ቃል አልገባቸውም ነበር። ኢየሱስ በመመገብ ሥጋዊ ፍላጎታቸውን የፈጸመላቸው፥ መንፈሳዊ ትምህርትን ሊያስተምራቸው እንደነበረ አልገባቸውም ነበር። ኢየሱስም አያይዞ፥ ሰዎች ሊመጡበት የሚገባ ከሰማይ የመጣ እንጀራ መሆኑን ስለ ራሱ ተናገረ (ዮሐ 6፡50-51)። ሰዎች ሥጋውን እንዲበሉና ደሙን እንዲጠጡ ሲናገራቸው (ዮሐ 6፡53-54)፥ በቁጥር 32 ውስጥ በተናገረው ስልት ዓይነት ነበር አሳቡን የገለጸው። ኢየሱስ ሊናገር የፈለገውን የአነጋገር ስልትና ምሥጢር ቁጥር 35 ውስጥ ትርጉሙን አብራርቶታል። ሥጋውን መብላትና ደሙን የመጠጣት ምሥጢር ወደ ኢየሱስ የመምጣትና በእርሱ የማመን ምሥጢር ነው። ኢየሱስ ለአይሁዶች ሲናገር፥ የዘላለም ሕይወትን ለማግኘት ቢሹ ወደ እርሱ ዘንድ መጥተው በእርሱ ማመን እንዳለባቸው አሳስቦአቸዋል።
ቅዱስ ቁርባን በእያንዳንዱ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆነ ሥነ ሥርዓት ነው። ቅዱስ የሆነ የአምልኮ ጊዜ ነው። በዚህን ጊዜ አማኙ ኃጢአቱን ይናዘዛል፥ የክርስቶስን ሞት ያስባል፥ ከእግዚአብሔርና ከሌሎች ምእመናን ጋር ይገናኛል። ደግሞም ኢየሱስ ደኅነትን ሊሰጠው ስለ ፈጸመው ሁሉ ምሥጋና ያቀርባል፥ እርሱንም ያመልካል። ሆኖም ቅዱስ ቁርባንን መቀበል ማንንም ሊያድን ወይም የዘላለም ሕይወትን ሊሰጥ አይችልም። የዘላለምን ሕይወት የምናገኘው፥ ወደ ኢየሱስ ዘንድ በእምነት በመምጣት ነው። ይህንንም ራሱ በዮሐንስ 6፡35 ውስጥ ተናግሮአል።
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ