“በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ ቅዱሳት መጻሕፍት ተለውጠዋል፡፡”

ቁርአን፣ የታሀሪፍ መጽሐፍ ሰዎችን፣ – ‹እነዚህን መጻሕፍት በራሳቸው አፍ መፍቻ ቀይረዋል፣ ከፊል የመጽሐፍ ክፍሎችንም ደብቀዋል› – ብሎ ከመውቀስ በዘለለ በየትም ቦታ ላይ ክርስቲያኖች፣ የአይሁድን እና የክርስቲያኖችን ቅዱሳት መጻሕፍት ስለመቀየራቸው መረጃ አይሰጥም፡፡

  • ከነሱም እርሱ ከመጽሐፉ ያይደለ ሲሆን ከመጽሐፉ መሆኑን እንድታስቡ በመጽሐፉ ምላሶቻቸውን የሚያጣምሙ ክፍሎች [who distort the Book with their tongues] አሉ፡፡ …

ሱረቱ አሊ-ዒምራን (3)፡78 

There is among them a section who distort the Book with their tongues….

ቅዱሳት መጻሕፍቱ ተለውጠዋል የሚሉ ሰዎች ያልተለወጡትን ጽሑፎች በማስረጃነት በማቅረብ የተለወጠው ክፍል ምን እንደሆነ ማሳየት ይኖርባቸዋል፡፡ አሁን፣ አሁን፣ ከእዚህ ክርክር ጋር በተያያዘ በአንዳንድ ሙስሊሞች ዘንድ ‹‹የበርናባስ ወንጌል›› እየተባለ የሚጠራ መጽሐፍን እንደ ማስረጃነት ማቅረብ የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ ሆኖም ግን፣ መጽሐፉ እንኳንስ ይህንን ክርክር ሊያስረዳ ቀርቶ ከራሱ ከቁርአኑ ጋር ሳይቀር በርካታ ግጭቶችን በመፍጠሩ ምክንያት መጽሐፉን ጠቅሶ ‹ቅዱሳት መጻሕፍቱ ተለውጠዋል› የሚለውን ግምት ለማረጋገጥ የተደረገው ሙከራ ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ 

በመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ላይ መለስተኛ የንባብ ልዩነቶች ቢኖሩም፣ የቅዱሳት መጽሐፍቱን ዶክትሪኖች ሆን ብሎ ለመቀየር የተደረጉ ጥረቶች ስለመኖራቸው የሚጠቁሙ ምንም ማስረጃዎች የሉም፡፡ እንደ እዚህ አይነት መለስተኛ የንባብ ልዩነቶች ደግሞ ለቁርአኑም ቢሆን እንግዳ አይደሉም፡፡ ከ ቅዱስ ቁርአን መግቢያ፣ (ገጽ xxxvi፣ 2ኛ እትም፣ 1977) ላይ የተወሰደውና በ ኤ. ዩሱፍ አሊ የተፃፈውን የሚከተለውን ጽሑፍ እንመልከት፡፡

ከላይ ካሉት ታሪካዊ እውነታዎች አንጻር፣ የቁርአን ምንባቦች (ከጥቂት አነስተኛ ልዩነቶች በስተቀር) ከቅዱሱ ነቢይ ምግባሮችና ትምህርቶች ጋር ግቡብ እንደሆኑ ግልጽ ሊሆን በተገባ ነበር፡፡ ሁሉም ምሁራንና የቁርአን ቁራዎች QURRXX በሙሉ ድምጽ፣ በሚከተሉት መስፈርቶች መሠረት የቁርአኑ ምንባብ ትክክለኝነት እንዲረጋገጥ ወስነዋል፡- (ሀ) በሐድራት ኡትማን ከተሰራጩት ቅጂዎች ጋር የሚስማማ (ለ) ከአረብኛ ቋንቋ የቃላት ቅጥዎችና ምዕላዳዊ ሕጎች ጋር፣ ከቋንቋው አጠቃቀም፣ የአነጋጋር ዘይቤና ሰዋሰው ጋር የሚስማማ እና ከምንም በላይ ደግሞ (ሐ) ከራሱ ከቅዱሱ ነቢይ ጋር ካለ እውነተኛና የልተቋረጠ ግንኙነት ጋር የሚጣጣም፡፡ ለዚህ ነው በቅዱስ ቁርአን ውስጥ በጣም ጥቂት የሆኑ የንባብ ልዩነቶችን ብቻ የምናየው፡፡ እነዚህም ልዩነቶች ቢሆኑ በትርጉማቸው ይዘት አንጻር እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ ሳይሆኑ የምንባቦቹ አድማስ ይበልጥ እንዲሰፋና ግልጽ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ነው፡፡ ስለዚህ፣ ቅዱሱ ነቢይ እነዚህን ልዩነቶች ዛሬ ባሉበት ሁኔታ እንደ ተጠቀመባቸውና ልዩነቶቹም የይዘቱን ትርጉም ይበልጥ ግልጽ ያደርጉ እንደነበር ቅንጣት ጥርጣሬ የለንም፡፡

ለአብነት፣ ሁለት ምንባቦችን እንይ (ሀ) አል-ፋቲሐህ ቁጥር 3 እና (ለ) አል-ማ-ኢዳህ ቁጥር 6፡፡ አንድ የ I፡3 ምንባብ እንዲህ ይላል፡- ‹‹የፍርድ ቀን ጌታ›› – ሌላው ምንባብ ደግሞ ይህንን ምንባብ ‹‹የፍርድ ቀን ንጉሥ›› ይለዋል፡፡ እነዚህ ሁለት ምንባቦች የጥቅሱን አሳብ ይበልጥ ግልጽ ሲያደርጉት ማየት ይቻላል፡፡ (ሐ) በቁጥር V : 6፣ ላይ አንድ ምንባብ እንዲህ ይላል፡- በባዶ እግሮቻችሁ ለመንጻት በምትሆኑበት ጊዜ ‹‹ፊቶቻችሁን ታጠቡ– እግሮቻችሁንም (ታጠቡ)››፤ ሁለተኛው ምንባብ ደግሞ እንዲህ ይላል፡- ‹‹በእርጥብ እጆቻችሁ ፊቶቻችሁን ታጠቡ፣ ራሶቻችሁን አብሱ እግሮቻችሁንም (አንጹ)፡፡››

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተሰነዘረው – “ተለውጧል” – የሚለው ክስ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚከተሉት ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ሊያገኙ ይገባል፡፡

ጥያቄ 1፡ ቅዱሳት መጽሐፍቱን ማን ለወጣቸው?

ለእዚህ ጥያቄ ብዙ ጊዜ የሚሰጠው ምላሽ፣ የእስልምናን መስፋፋት ለመግታት ሲሉ አይሁድና ክርስቲያኖች ቀይሯቸዋል የሚል ነው፡፡ አይሁድና ክርስቲያኖች በአስተምህሯቸው በእጅጉ የሚለያዩ እምነቶች በመሆናቸው ይህንን ለውጥ ግንባር ፈጥረው ያደርጋሉ የሚለው ግምት ብዙ ርቀት የሚያስኬድ አይሆንም፡፡

  • እነርሱ መጽሐፉን የሚያነቡ ሲሆኑ አይሁዶች፡- ክርስቲያኖች በምንም ላይ አይደሉም አሉ፣  ክርስቲያኖችም፡-አይሁዶች በምንም ላይ አይደሉም አሉ፣ …

ሱረቱ አል-በቀራህ (2)፡113

The Jews say “The Christians have naught (to stand) upon;” and the Christians say, “The Jews have naught (to stand) upon.” Yet they (profess to) study the (same) book.

በአይሁድም ሆነ በክርስትና እምነት ውስጥ በርካታ ልዩ ልዩ የሃይማኖት ክፍሎች (sects) ስላሉ፣ ዶክትሪን ለመቀየር በሚል ሰበብ በእምነቶቹ ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የተለወጡ ክፍሎች ቢኖሩ፣ ከእነዚህ ልዩ የሃይማኖቶቹ ክፍሎች መካከል ይህን ለውጥ የሚቃወም ባልጠፋ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በቤተክርስቲያን ታሪክ እንዲህ አይነቱ ክስ ተሰምቶ አያውቅም፡፡ ተሰምቶ የሚያውቀው አቤቱታ፣ ቅዱሳት መጻሕፍቱ በተገቢው ሁኔታ አልተተረጎሙም የሚል እንጂ ተለውጠዋል ወይም ተቀይረዋል የሚል አይደለም፡፡

ኢየሱስ፣ በአገልግሎቱ ወቅት አይሁድ ቅዱሳት መጽሐፍቱን መለወጣቸውን ጠቅሶ የወቀሳቸው አጋጣሚ የለም፤ ወደ ቅዱሳት መጽሐፍቱ ፊታቸውን እንዲመልሱ ይሰብካቸው ነበር እንጂ፡፡ በቅዱሳት መጽሐፍቱ ውስጥ አይሁድ ይህን ለውጥ አድርገው ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ይህን ከመናገር አይመለስም ነበር፡፡ በሙሐመድ ዘመንም ቢሆን፣ ሙስሊሞች ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ወዳጅነታቸውን ያሳዩአቸው በአቢሲኒያ (በኢትዮጵያ) ይኖሩ የነበሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ በቅዱሳት መጽሐፍቱ ላይ የተደረገ ለውጥ ቢኖር ኖሮ ለእነዚያ እንግዳ ሙስሊሞች ይህንን ጉዳይ አንስተው ከመናገር አይቆጠቡም ነበር፡፡

  • …እነዚያንም ክርስቲያኖች ነን ያሉትን ለነዚያ ላመኑት [ለሙስሊሞች] በወዳጅነት በእርግጥ ይበልጥ የቀረቧቸው ሆነው ታገኛለህ፤ ይህ ከእነሱ ውስጥ ቀሳውስትና መነኮሳት በመኖራቸውና እነሱም የማይኮሩ በመሆናቸው ነው፡፡ 

ሱረቱ አል-ማዒዳህ (5)፡82 

Nearest among them in love to the believers wilt thou find those who say “We are Christians” because amongst these are men devoted to learning.

ጥያቄ 2፡ ቅዱሳት መጽሐፍቱ ተቀየሩ ከተባለ – መቼ?

የአይሁድ እና የክርስቲያኖች ቅዱሳት መጻሕፍትን ከሙሐመድ ሞት በፊት ተቀይረዋል ከተባለ፣ ሙሐመድ ከዚህ በታች በቁርአኑ ውስጥ የሰፈሩትን ጥቅሶች እንዲቀራ ባልተደረገ ነበረ፡-

  • … ከመጽሐፍ አላህ ባወረደው ሁሉ አመንኩ፤ … 

አል-ሹራ (42)፡15 

I believe in the Book (of the people of the Book)

  • በአላህና ወደኛ በተወረደው (ቁርአን) ወደ ኢብራሂምም [አብርሃም] ወደ ኢስማዒልና [እስማኤል] ወደ ኢስሐቅም [ይስሃቅ] ወደ ያዕቁብና [ያዕቆብ] ወደ ነገዶቹም በተወረደው በዚያም ሙሳና ዒሳ [ለሙሴና ለኢየሱስ] በተሰጡት በዚያም ነቢያት ሁሉ ከጌታቸዉ በተሰጡት ከነርሱ በአንዱም መካከል የማንለይ ስንኾን አመንን እኛም ለርሱ (ለአላህ) ታዛዦች ነን በሉ፡፡

ሱረቱ አል-በቀራህ (2)፡136

We believe in God, and the revelation given to us, and to Abraham, Isma’il, Isaac, Jacob, and the Tribes, and that given to Moses and Jesus, and that given to (all) prophets from their Lord. We make no difference between one and another of them.

  • እናንት የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! [አይሁድና ክርስቲያኖች] ተውራትንና [ኦሪትንና] ኢንጅልን [ወንጌልን] ከጌታችሁም ወደናንተ የተወረደውን እስከምታቆሙ (እስከምትሰሩባቸው) ድረስ በምንም ላይ አይደላችሁም በላቸው፤…

ሱረቱ አል-ማኢዳህ (5)፡68

O people of the Book, Ye have no ground to stand upon unless ye stand fast by the Law, the Gospel, and all the revelation that has come to you from your Lord.

  • የኢንጅልም [የወንጌልም] ባለቤቶች በውስጡ አላህ ባወረደው ሕግ ይፍረዱ፤ …

ሱረቱ አል-ማኢዳህ (5)፡47

Let the people of the Gospel judge by what God hath revealed therein.

  • በፈለጎቻቸውም (በነቢያቶቹ ፈለግ) ላይ የመሪየምን [የማሪያምን] ልጅ ዒሳን [ኢየሱስን] ከተውራት [ከኦሪት] በስተፊቱ ያለውን አረጋጋጭ ሲሆን አስከተልን፤ ኢንጂልንም [ወንጌልንም] በውስጡ ቀጥታና ብርሃን [guidance and light] ያለበት፣ በስተፊቱ ያለችውንም ተውራትንም የሚያረጋግጥ፣ ለጥንቁቆችም መሪና ገሳጭ ሲሆን ሰጠነው፡፡

ሱረቱ አል-ማኢዳህ (5)፡46

And in their footsteps We sent Jesus the son of Mary confirming the Law that had come before him. We sent him the Gospel: therein was guidance and light, and confirmation of the Law.

  • [ሙሐመድ] ወደ አንተም ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትኾን፣ እነዚያን ከአንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን [የመጽሐፉን ባለቤቶች] ጠይቅ፣ እውነቱ ከጌታህ ዘንድ በእርግጥ መጥቶልሃል፣ ከተጠራጣሪዎቹም አትኹን፡፡

ሱረቱ ዩኑስ (10)፡94

If thou (Muhammad) wert in doubt as to what We have revealed unto thee, then ask those who have been reading the Book from before thee (the people of the Book).

  • ከእነርሱም ጋር ያለውን (መጽሐፍ) አረጋጋጭ የሆነ መጽሐፍ [ቁርአን] ከአላህ ዘንድ በመጣላቸው ጊዜ … ያወቁት ነገር በመጣላቸው ጊዜ በእርሱ ካዱ፤ … አላህም ባወረደው ሁሉ እመኑ በተባሉ ጊዜ… እነርሱ ጋርም ላለው (መጽሐፍ) አረጋጋጭ የሆነ መልዕክተኛ ከአላህ ዘንድ በመጣላቸው ጊዜ፣… 

ሱረቱ አል-በቀራህ (2)፡89፣91፣101

And when there comes to them a Book (Qur’an) from God confirming what is with them…. Yet they reject all besides, even if it be truth confirming what is with them…. And when there came to them an Apostle from God confirming what was with them….

ከላይ በተገለጹት ጥቅሶችና በቁርአኑ ሌሎች ቦታዎች ላይ ሰፍረው ባሉ ጥቅሶች ላይ በተደጋጋሚ የተገለጸውን ‹‹ከእነርሱም ጋር ያለውን መጽሐፍ አረጋጋጭ ሆኖ›› የሚለውን ሐረግ ልብ ልንል ይገባል፡፡ በእነዚህ ጥቅሶች አሳብ መሠረት ቁርአን የወረደው ከእርሱ በፊት የነበሩትን የእይሁድና የክርስቲያኖች ቅዱሳት መጻሕፍን ለማረጋገጥ እንጂ ለማስተካከል ወይም እነሱን ለመተካት አይደለም! በርካታ ሙስሊሞች ግን ከእዚህ በተቃራኒው እንድናምን ይሻሉ፡፡ ሆኖም፣ በየትኛውም የቁርአን ገጽ ላይ ቁርአን የመጣው አማኙን ማሕበረሰብ ‹‹ከተበረዙት››፣ ‹‹ከተለወጡት›› ወይም ‹‹ከጠፉት›› የቶራ ቅዱሳት መጻሕፍት [የሙሴ መጻሕፍት] እና ኢንጂል [የአዲስ ኪዳን] ቅዱሳት መጻሕፍት ስህተት ለመታደግ መሆኑን አናነብም፡፡

እነዚህ የአይሁድና ክርስቲያኖች ቅዱሳት መጻሕፍት – ሙሐመድ ከሞተ በኃላ ተለውጠዋል – የሚለው ማስረጃ የሌለው ክስም ቢሆን በሚከተሉት ምክንያቶች ውድቅ መሆኑ ተረጋግጧል፡-

ከክርስቶስ ልደት በኃላ በ600 ዓ.ም. ክርስትና በእሲያ፣ አፍሪካና አውሮፓ በስፋት ተሰራጭቶ ነበረ፡፡ በእነዚህ አሕጉሮች የነበሩ ክርስቲያኖች አለማቀፍዊ ስብሰባ በመጥራት ቅዱሳት መጻሕፍቶቹን ለመቀየር ጥረት ማድረጋቸውን የሚጠቁም ምንም ማስረጃ የለም፡፡

ሙስሊሞች ቅዱሳት መጻሕፍትን በታላቅ አክብሮት የመጠበቅ ልማድ ስላላቸው፣ ተለውጠዋል የሚባሉት ቅዱሳት መጻሕፍት በእርግጥ ተለውጠው ቢሆን ኖሮ የአይሁድ ወይም የክርስትና እምነትን ትተው በሰለሙ አንዳንድ ሰዎች እጅ ውስጥ እነዚህ ተቀይረዋል የሚባሉት መጻሕፍት በተገኙ ነበር፡፡ በተግባር ግን አንዳች የተገኘ ነገር የለም፡፡

በ4ኛው እና 5ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ የተገኙ ቅዱሳት መጻሕፍት አሁንም ድረስ በዛው ይዞታቸው ይገኛሉ፤ (ልብ ይበሉ ሙሐመድ የተወለደው በ6ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ነው)፡፡ እነዚህ የጥንት ቅዱሳት መጻሕፍት አሁን ካሉት ትርጉሞችና ቅጂዎች ጋር አቻ ናቸው፡፡ 

ጥያቄ 3፡ እንዴት ተለወጠ? 

የአይሁድ እምነትና ክርስትና በዓለም ዙሪያ የተበተኑ እምነቶች በመሆናቸው፣ ማንም ሰው እነዚህን በዓለም ዙሪያ የተበተኑ መጽሐፍ ቅዱሶችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ማመዛገቢያና ማጣቀሻ የያዙ ቅዱሳት መጻሕፍትን፣ ረቂቆችን እና ፅሁፎችን ከሁሉም ቤተክርስቲያኖች፣ ምኩራቦች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ትምህርት ቤቶች እና ቤቶች በመሰብሰብ አስፈላጊ ለውጦች ከተካሄዱባቸው በኋላ መልሶ ማንም ሳያውቅ ማሰራጨት፣ ሊታሰብ የማይቻል ነገር ነው! ቁርአኑስ ቢሆን ማንም ሰው የእግዚአብሔርን ቃል ሊለወጥ እንደማይችል ይናገር የለምን?

  • የጌታህም ቃላት እውነተኛና ትክክለኛ ስትሆን ተፈጸመች፤ ለቃላቱ ለዋጭ የለም [None can change His Words] …

ሱረቱ አል-አንዓም (6)፡115

The Word of thy Lord doth find its fulfillment in truth and in justice. None can change His Words.

  • … የአላህ ቃላት መለወጥ የላትም …

ሱረቱ ዩኑስ (10)፡64

No change can there be in the Words of God. 

ሙስሊሞች ከላይ የቀረቡትን ጥቅሶች በማስረጃነት በማቅረብ፣ እግዚአብሔር ቁርአን እንዳይበረዝ ጠብቆታል ብለው የሚናገሩ ከሆነ እንግዲያውስ ይኸው አምላክ ከቁርአኑ በፊት የነበሩትንም ቅዱሳት መጻሕፍት ‹‹ከመበረዝ›› ሊያድናቸው ይችላል ብለው ሊያምኑ አይገባቸውምን?

__________________________________

 ‹ቅዱሳት መጻሕፍት› ተብለው የተጠቀሱት በብሉይ እና አዲስ ኪዲናት ውስጥ ተካተው ያሉትን 66 መጻሕፍት ነው፡፡

 ቁራዎች QURRXX = የዚህ ቃል አረብኛ ፍቺ ‹አንድን ጽሑፍ በቃል ብቻ ለሚወጡ (ለሚሸመድዱ/reciters) ሰዎች› በስያሜነት እንደሚውል ያሳያል፡፡ እንግዱህ ቁራ/ qurrāʾ የሚባሉት ሰዎች የእስልምናን ቅዱስ መጽሐፍ – ቁርአንን በቃላቸው የሚወጡትን ይወክላል ማለት ነው፡፡ ሙሐመድ ተከታዮቹ  የቁርአን ጥቅሶችን በቃላቸው በመያዝ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲያሸጋግሩ ያደርግ ነበር፡፡ ይህ የሽምደዳ ልማድ ከእስልምና በፊትም ግጥሞችን በቃል በመያዝ ለትውልድ ጠብቆ ለማቆየት በሥራ ላይ ይውል ነበር፡፡

 ሐድራት ኡትማን እ.ኤ.አ. በ573 ዓ.ም. በመካ ይኖሩ ከነበሩት የቁራይሽ (የነቢዩ ሙሐመድ ቤተሰቦች) መካከል የተገኘ የእስልምና ሶስተኛው ታላቅ ከሊፋ ነበር፡፡ በመካ ይኖሩ ከነበሩና ማንበብና መጻፍ ከሚችሉ ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ ሲሆን በሃብትም የበለጠገ ነበር፡፡ ሐድራት ኡትማን ወደ ኢትዮጽያ ተሰደው ከመጡ ሙስሊሞችም መካከሌ አንዱ ነበር፡፡ ሐድራት ከሙስሊም ጸሐፍት መካከል ስሙ በመጀመሪያ ረድፍ ላይ ከሚጠሩ ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡

 ከ ዩሱፍ አሊ፣ ‹‹ቅዱስ ቁርአን፡- ትርጉምና ማብራሪያ፣›› 2ኛ እትም፣ 1977 የተወሰደ፡፡

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading