አጠቃላይ ምልከታ ስለእስልምና (በተርጓሚው)

እስልምና በ7ኛው ክፍለ ዘመን (እ.ኤ.አ. በ622 ዓ.ም.) በአንድ የአረብ ነጋዴ በመካ፣ ሳውዲ አረቢያ የተጀመረ ሐይማኖት ነው፡፡ ይህ ሰው ሙሐመድ (እ.ኤ.አ. 570) ይባላል፡፡ ይህ እምነት በይበልጥ ተስፋፍቶ የሚገኝባቸው አካባቢዎች መካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ሲሆኑ ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ተከታዮቹ እንዳሉት ይነገራል፡፡ በተከታዮች ብዛት ከክርስትና ቀጥሎ በአለም ሁለተኛ ሃይማኖት ሲሆን በስሩ ሶስት ዋና ዋና የእምነት ልይኑቶች (denominations) አሉት፤ እነሱም፡- ሱኒ፣ ሺአት፣ እና ሱፊ ይባላሉ፡፡ የእስልምና ቅዱስ መጽሐፍ ቁርአን ሲሆን የእምነቱ ዋና ቋንቋም አረብኛ ነው፡፡ እንደ ሙስሊሞች እምነት ቁርአን እግዚአብሔር ለመጨረሻውና (ተተኪ ለሌለው) ነብይ (ሙሐመድ) የገለጠው መፅሐፍ ነው፡፡ የእስልምና የእምነት አባቶች ሼክ፤ ኢማም (ሺአት) ሲባሉ የማምለኪያ ሥፍራው ደግሞ መስጂድ ይባላል፡፡

እስላም ማለት ‹‹ለፈጣሪ በመገዛት ውስጥ ያለ ሰላም›› ማለት ሲሆን ‹‹ማንኛውም ለፈጣሪ ፈቃድ ራሱን የሚያስገዛ ሰው ሁሉ ደግሞ ሙስሊም ይባላል፡፡

ሁሉም ሙስሊሞች አረቦች አይደሉም፡፡ እስልምና በተለያዩ ዘሮች ውስጥ ያለ ሃይማኖት ነው፡፡ ከአጠቃላይ የእስልምና ሃይማኖት ቁጥር አንጻር አረቦች 20% ብቻ ይይዛሉ፡፡ ከፍተኛ የእስልምና ተከታይ ቁጥር ያለባት አገር ኢንዶኔዢያ ስትሆን በዚህች አገር ያሉ የእስልምና ተከታዮቹም 120 ሚሊዮን ይደርሳሉ፡፡

አንድ ሰው ሙስሊም ለመሆን የሚጠበቅበት አንድና ዋነኛ ነገር ሻሃዳህን መፈጸም ነው፡፡ ይህም ማለት አንድ ፈጣሪ ብቻ እንዳለ እና ሙሐመድ ደግሞ የሰው ልጆች የመጨረሻ ነቢይ መሆኑን በአንደበቱ መናገር ማለት ነው፡፡ 

ሙስሊሞች በቁርአን ውስጥ አላህ እራሱን በ99 የተለያዩ ስሞች ገልጧል ብለው ያምናሉ፡፡ የሰው ልጅ ስለ ፈጣሪ ማንነት ሊያውቅ የሚችለውም በእነዚህ ስሞች አማካኝነት ነው ይላሉም፡፡ ከእነዚህ ስሞች ዝርዝር ውስጥ ለአብነት፡- መኃሪ፣ ሁሉን አዋቂ፣ ጠባቂ፣ ሰጪ፣ የቅርብ አምላክ፣ የመጀመሪያው፣ የመጨረሻው፣ የተሰወረ፣ እና የሰላም ምንጭ የሚሉት ይገኛሉ፡፡ 

ሙስሊሞች በቀደሙት ነቢያት ማለትም ከአዳም እስከ ኢየሱስ ድረስ ባሉት ያምናሉ (በአስተምህሮአቸው መሠረት ይህ ነቢይነት የሚጀምረው ከአዳም ሲሆን የሚጨርሰው ደግሞ ሙሐመድ ላይ ነው)፡፡ ሙስሊሞች እነዚህ ነቢያት ሳይቀሩ ለፈጣሪ ፈቃድ ራሳቸውን አዝገዝተዋልና ሙስሊሞች ናቸው ብለውም ይመሰክራሉ፡፡ 

የእስልምና ቅዱሳት መጻሕፍት (ቁርአን እና ሱናህ)

የሲራ (Sira) እና የሐዲት (Hadith) ቅዱሳት መጻሕፍት በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ከቁርአን በመቀጠል ልዩ ሥፍራ ያላቸው የእስልምና ቅዱሳት መጻሕፍት ናቸው፡፡ እስልምና በቁርአን፣ በሲራ (የሙሐመድ ባዮግራፊ/የሕይወት ታሪክ)፣ እና በሐዲት (የሙሐመድ ትራዲሽኖች/ልማዶች) ላይ የተመሰረተ ሃይማኖት ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ማለትም ሲራ እና ሐዲት የነቢዩ ሱናህ (Sunnah) በመባል ይታወቃሉ (ሱናህ የሙሐመድ ቃሎችና ተግባራት ማለት ነው)፡፡

ሱናህ Sunnah (سنة [ˈsunna], በብዙ ቁጥር سنن sunan [ˈsunan] የአረብኛ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም ልማድ/ልምድ ወይም ተዘውትሮ የሚደረግ ድርጊትን ያመለክታል፡፡ ይህ ቃል ከእስልምና ሃይማኖት አጠቃቀም አንጻር ሲታይ ደግሞ የእስልምና ነቢይ የሆነውን የሙሐመድን አባባሎች/ንግግሮች፣ ፈለጎች እና የአኗኗር ልምዶች ያመለክታል፡፡ 

ቁርአን ‹‹ሙሐመድ ከአላህ ዘንድ የተቀበለው የሙስሊሞች ቅዱስ መጽሐፍ›› ቢሆንም ብቻውን ስለ እስልምና የተሟል መረጃና መመሪያ አይሰጥም፡፡ ቁርአን በውስጡ በተደጋጋሚ የሰው ልጆች በሞላ የሙሐመድን ፈለግ (ቃሎችና ተግባራት) እንዲከተሉ ቢያዝም (ለአብነት 3:32) እነዚህን የሰው ልጅ እንዲከተላቸው የታዘዘውን የሙሐመድን ፈለጎች በስፋት ማግኘት የሚቻለው ግን በቁርአን ውስጥ ሳይሆን በሲራ እና በሐዲት ውስጥ ነው፡፡ 

የሙሐመድ ሱናህ – የሙሐመድን የራሱን ቃሎች፣ ልምዶች፣ የዘወትር ተግባራት፣ የጥሞና ይሁንታዎቹን (silent approvals) ከማካተታቸው በተጨማሪ እንዴት ከወዳጆች ጋር፣ ከቤተሰብ ጋር፣ እና ከመንግስት ጋር መስተጋብር መፍጠር እንደሚቻል ምልከታን የሚሰጥ ስለሆነ በእስልምና ውስጥ ትልቅ ስፍራ አለው፡፡ 

እንግዲህ ከላይ አንደተገለጸው፣ እነዚህ የሙሐመድ ሱናዎች (የሙሐመድ ቃሎችና ተግባራት) በጽሑፍ መልክ ሰፍረው የሚገኙት በሁለት የተለያዩ የሙስሊም ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ነው፡፡ አንደኛው ሲራ ሲባል ሁለተኛው ደግሞ ሐዲት ይባላል፡፡ (ሲራ + ሐዲት = ሱና)፤ (ቁርአን + ሱና = እስልምና)፤ በሚል የሂሳብ ስሌት በእስልምና ቅዱሳት መጽሐፍት መካከል ያለውን ግንኙነት መናገር ይቻላል፡፡

እስላማዊው ሊቅ ሃቢብ ኡር ራህማን አዛሚ ቁርአን በሐዲትና በሲራ ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑ እና ሸሪያም እንኳን ሙሉ የሚሆነው ከቁርአን እና ከሱናህ ጋር ከተረዳዳ ብቻ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ብዙዎቹ የእስልምና አስፈላጊ ልምምዶች እና እምነቶች የተቀዱት ከሱናህ ላይ ነው፡፡ እንግዲህ ሱናህ ለእስልምና በጣም ጠቃሚ የመንፈሳዊ እውቀት ምንጭ ቢሆንም ምንጩ ቁርአን ሳይሆን ሐዲት እና ሲራ መሆናቸውን አንባቢ ልብ ይሉዋል፡፡  

ስለ እነዚህ እስላማዊ ፅሑፎች ተአማኒነትና ህጋዊነት በተመለከተ የሙስሊም ምሁራን በቁርአን መግቢያ ሐዲትን አስመልክተው የፃፉትን እስቲ አብረን እንመልከት:- ‹‹ቁርአን እስልምናን ካቆሙ ሁለት እግሮች አንዱ ነው፡፡ ሁለተኛው እግር የነብዩ ሱናህ ነው፡፡ ቁርአንን ከሱናህ የሚለየው አፃፃፉ ነው፡፡ ቁርአን በቀጥታ የወረደ የአላህ ቃል ሲሆን’ የሐዲት ጥንቅር የሆነው ሱናህ ደግሞ በአላህ መንፈስ መነዳት (inspiration) የተፃፈ የነቢዩን ቃሎችና ድርጊቶች የሚተርክ ነው፡፡ ቁርአን በሰዎች ቃላት አልተገለፀም፡፡ ቃሎቹ’ ፊደል-በፊደል ከአላህ የተሰጡ (የተወረዱ/የወረዱ) ናቸው፡፡ ነብዩ ሙሐመድ ለሰው ልጆች ከአላህ የተላከ የመጨረሻ መልዕክተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ቁርአን አላህ ለኛ የላከው የመጨረሻ መልዕክት ነው፡፡ ከእርሱ በፊት የነበሩት እነ ኦሪት፣ መዝሙረ ዳዊትና ወንጌል ሁሉ በእርሱ ተውጠዋል፡፡›› 

የኢሻቅ (Ishaq) ግለ ታሪክና የታባሪ (Tabari) ታሪክ በሐዲት ውስጥ ይታቀፋሉ፤ ሱናህዎች በመሆናቸው እስላማዊ ጥቅሶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሱናህዎች ብቻቸውን የእስልምና ሃይማኖትን አፅመታሪክ፣ አውድና የታሪክ ቅደም ተከተል ይሰጡናል፡፡ ቁርአን እነዚህ ሱናህዎች በሚሰጡን ጊዜዎችና ቦታዎች ላይ ካልተደገፈ በቀር ግልጽ አይሆንም፡፡ የተቀረውም ሐዲት ቢሆን ዋጋው ዝቅ ይላል፡፡ ያለ ወንጌል ክርስትናን እንደማሰብ ማለት ነው፡፡ የታባሪ ተረጓሚዎች እንዲህ ይላሉ፣’ “ሙሐመድ ኢብን ኢሻቅ ለመጀመሪያ ጊዜ የነብዩን ግለ-ታሪክ የዘገበ ታዋቂ ሰው ነበር፡፡ የእርሱ ሲራ የሙሐመድን የህይወት ዘመን ታሪኮች በተገቢው ደረጃ ያስቀመጡ ናቸው፡፡”  

በርካታ ሐዲቶች ሲኖሩ ዋነኛዎቹ በቡካሪ የተጠናቀሩቱ ናቸው፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ማሱድ አል-ሐሰን ገለጣ ዋናዎቹ ስብስቦች፡-

የታወቁት (እውቅና) የተሰጣቸው የሐዲት ስብስቦች በ ‹ሙስናፍ› (1) ምሳሌ የሚከተሉት ስብስቦች ናቸው፡-

1. አል ቡካሪ (870 ሒጂራ) (የ7658 ሐዲቶች ስብስብ)

2. ሙስሊም (875 ሒጂራ) የ7748 ሐዲቶች ስብስብ)

3. አቡ ዳውድ (875 ሒጂራ) (የ5276 ሐዲቶች ስብስብ)

4. አል ቲርሚዚ (892 ሒጂራ) (የ4415 ሐዲቶች ስብስብ)

5. አል-ናሳይ (915 ሒጂራ) (የ5776 ሐዲቶች ስብስብ)

6. ኢብን ማጃ (886 ሒጂራ) (የ4485 ሐዲቶች ስብስብ)

የአል-ቡካሪና የአል-ሙስሊም ስብስቦች ከሌሎቹ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ነው ያሉት፡፡ ስልጣን ያላቸው መሆናቸውን ለማሳየትም ‹አል-ሳሂሃይን› ተብለው ይጠራሉ፡፡   

ሲራ የእስልምና ሕግን (ሸሪያ) ለመመስረት እና ቁርአንን ለማብራራት/ለመተርጎም ልዩ ስፍራ አለው፡፡ በጣም ተቀባይነት ያለውና ስልጣን ያለው የሙሐመድ ሲራ በኢብን ኢሻቅ የተዋቀረው ነው፡፡ ሁለቱ ጥንታዊ ሲራዎች የሚከተሉት ናቸው፡- (1) መሐመድ ኢብን ኢሻቅ (773) በኢብን ሂሻም በኩል (840 ሒጂራ) የክለሳ ስራ፣ Sirat Rasul Allah. (English translation 798 pages[3].) እና (2) መሐመድ ኢብን ሳዓድ (852 ሒጂራ) Kitab al-Tabaqat al-Kabir, (English translation, 1097 pages [4].)

ስድስቱ የእስልምና ሃይማኖት መግለጫዎች

እነዚህ ትምህርቶች የእስልምና መሠረታዊ እምነቶች ናቸው፡፡ ማንኛውም ሙስሊም እውነተኛ ሙስሊም ለመባል እነዚህን መሠረታዊ የእምነት አቋማት ሊከተላቸውና ሊፈጽማቸው ይገባል፡- (1) በአንድ ፈጣሪ ማመን (2) በሁሉም የፈጣሪ ነቢያት ማመን (3) ከአላህ ዘንድ ለነቢዩ ሙሴ፣ ለዳዊት፣ ለኢየሱስ እና ለሙሐመድ በተገለጡትን ቀደምት የቅዱሳት መጻሕፍት ቅጂዎች ማመን (4) በመላእክት ማመን (5) ስለ ፍርድ ቀን እና ከዛ በኋላ ስላለው ሕይወት ማመን (6) በመለኮታዊ አዋጅ (ወይም የፍጻሜ እጣ ፈንታ) ማመን፡፡  

አምስቱ የእስልምና አዕማዳት

(1) እምነትን መመስከር (ሻሃዳህ) ፈጣሪ አንድ መሆኑን እና ሙሐመድ የመጨረሻው የሰው ልጅ ነቢይ ነው ብሎ መናገር፡፡ (2) የየዕለት ጸሎት (ሶላት) በቀን አምስት ግዜ መጸለይ፡- በአምስቱ የዕለት ተዕለት ጸሎት አንድ ሙስሊም ፊቱን መካ ወደሚገኘው ካአባ አዙሮ መጸለይ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ባለ ስድስት ጎን ቅርጽ ያለው ድንጋይ (ካአባ) በሙስሊሞች ዘንድ መጀመሪያ በአዳም የተገነባ እና በመቀጠልም በአብርሃም የታደሰ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ሙስሊሞች ካአባ ለአንዱ አላህ በምድር ላይ የተሰራ የመጀመሪያ የማምለኪያ ሥፍራ እንደሆነም ያምናሉ፡፡ ሃጅ፣ ወደዚህ ሥፍራ በየአመቱ የሚደረግ መንፈሳዊ ጉዞ ነው፡፡ (3) ምጽዋት/ቀረጥ (ዘካ) በየአመቱ መጨረሻ ለችግረኞች የሚሰጥ ስጦታ፡፡ አንድ ሰው ከቆጠበው ሃብት ላይ 2.5 እጁን ለተቸገሩ የሚሰጥበት ሥርዓት ነው፡፡ (4) የሃይማኖት ጉዞ (ሀጅ) አካላዊ እና የገንዘብ ችግር ከሌለ በስተቀር ቢያንስ አንድ ግዜ ወደ መካ መሄድ፡፡ (5) የሮሞዳን ጾም (ሳውም)፡፡

የቁርአን ይዘት

ብዙዎቹን የተውራት/ኦሪት (አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት) እና የታልሙድ ( ታልሙድ፡- የአይሁድን የፍትሐ ብሔርና የሃይማኖት ሕግን የያዘ መጽሐፍ ስብስብ ነው) ታሪኮች በቁርአን ውስጥም ሰፍረው እናገኛቸዋለን፡፡ ምንም እንኳ በቁርአን ውስጥ ሰፍረው የምናገኛቸው በርካታዎቹ ገጸ-ባሕሪያት ከመጽሐፍ ቅዱስና ከታልሙዱ ጋር ተመሳሳይ ቢሆኑም የታሪኮቹ አውድ እና መቼት (ጊዜ እና ቦታ) ግን ልዩነት አላቸው፡፡ በቁርአን ውስጥ ቁርአን የጠቀሳቸውና በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይገኙ ገፀ-ባህሪያት 4 ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ሁለቱ በአፈታሪክ አገር የኖሩ አፈታሪክ ሰዎች ሲሆኑ 3ተኛው የሙሐመድ ትልቁ ነቃፊ (ተቺ) የነበረው አጎቱ አቡ ለሀብ ነው፡፡ አራተኛው ደግሞ በአላህ መሰረት የእስላሞች ነብይ የነበረው ታላቁ እስክንድር ነው፡፡

የተቀሩት ገፀ-ባህሪያት ማለትም፡- አዳም (አደም)፣ ኖህ (ኑሕ)፣ አብርሃም (ኢብራሂም)፣ ይስሀቅ (ኢስሓቅ)፣ እስማኤል፣ ያዕቆብ፣ ኢያሱ (አልየሰዕ)፣ ሎጥ፣ ሙሴ (ሙሳ)፣ አሮን (ሃሩን)፣ ዮናስ፣ ዳዊት (ዳውድ)፣ ሰለሞን (ሱለይማን)፣ ማርያም (መርየም)፣ ኢየሱስ (ዒሳ)፣ ሰይጣን፣ ገብርኤል (ጅብሪል) እና የመሳሰሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ታሪክ በቁርአኑ ላይ የሰፈረው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባለው መሠረት አይደለም፡፡ በቁርአን ውስጥ፣ በነዚህ ሰዎች ሕይወት ዙሪያ የቀረቡት ታሪኮች ወቅታቸውና አውዳቸው ከመጽሐፍ ቅዱሱ ወቅትና አውድ ጋር አይጣጣምም፡፡ 

 ምንጮች፡-

http://en.wikipedia.org/wiki/Sunnah

http://www.politicalislam.com/principles/pages/five-principles/

http://www.answering-islam.org/

Leave a Reply

%d bloggers like this: