“የሙሐመድ ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተሰርዟል፡፡”

በርካታ ሙስሊሞች፣ የሙሐመድ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድም ቦታ ላይ ባለመጠቀሱ ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት ለመጠራጠር እንደ ምክንያት ሲያቀርቡ ይስተዋላል፡፡ በቅዱስ መጽሐፋቸው፣ ቁርአን ውስጥ በተጠቀሱ ሁለት ጥቅሶች ምክንያት የሙሐመድን ስም በአይሁድና ክርስቲያኖች ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ለማየት ይሻሉ፡፡ ለመሆኑ እነዚህ ጥቅሶች ምን ይላሉ፡-

  • የመርየም [የማሪያም] ልጅ ዒሳም [ኢየሱስም] ፡- የእሥራኤል ልጆች ሆይ እኔ ከተውራት [ከኦሪት] በፊት ያለውን የማረጋግጥና ከኔ በኋላ በሚመጣው መልዕክተኛ ስሙ አሕመድ በሆነው የማበስር ስሆን ወደናንተ (የተላክሁ) የአላህ መልዕክተኛ ነኝ፤…

አል-ሶፍ (61)፡6 

And remember Jesus, the son of Mary, said: “O Children of Israel! I am the apostle of God (sent) to you confirming the Law (which came) before me, and giving glad tidings of an apostle to come after me, whose name shall be Ahmad.

  • ለነዚያ ያንን እርሱ ዘንድ በተውራትና [በኦሪትና] በኢንጂል [በወንጌል] ተጽፎ የሚያገኙትን የማይጽፍና የማያነብ ነቢይ [ሙሐመድ] የሆነውን መልዕክተኛ የሚከተሉ ለሆኑት (በእርግጥ እጽፋታለሁ)፤ በበጎ ሥራ ያዛቸዋል፤ ከክፉም ነገር ይከለክላቸዋል፤ መልካም ነገሮችንም ለነርሱ ይፈቅድላቸዋል፤ መጥፎ ነገሮችንም በእነርሱ ላይ እርም ያደርግባቸዋል፡፡

አል-አዕራፍ (7)፡157

Those who follow the apostle, the unlettered prophet (Muhammad) whom they find mentioned in their own (Scriptures), — in the Law and the Gospel; –For he commands them what is just and forbids them what is evil.

በቅጡ የተማሩ የሙስሊም ምሁራን ካደረጓቸው ምርምሮች የተነሳ ከሙሐመድ ዘመን በፊት ጥንት የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ከሙሐመድ ዘመን በኃላ ካሉቱ ጋር ፍፁም አንድ እንደሆኑ ያውቃሉ፡፡ በዚህ ምክንያት የሙሐመድን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማውጣት ሲባል መጽሐፍ ቅዱስ ተለውጧል የሚለው ክስ መሠረተ ቢስ ይሆናል፡፡ ክሱ ግን በዚህ አያበቃም፡፡ መዚህ መንገድ ስኬት ያላገኘው ክስ መልኩን ይለውጥና ምንም እንኳን የሙሐመድ ስም በቀጥታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸ ባይሆንም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ፣ ግን በግልጽ፣ ተቀምጧል ይላሉ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሙሐመድ የተገጸው ሃሳብ ሙሐመድ ለሰው ልጅ ሁሉ የተሰጠውን አገልግሎትና ነቢይነት ያረጋግጣል በማለትም ክርስቲያኖች ሙሐመድንና እስልምናን እንዲከተሉ ያግባባሉ፡፡

ከላይ ባየናቸው የቁርአን ጥቅሶች ላይ በመንተራስ፣ የሙሐመድን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማግኘት ፍለጋ ያደረጉ በርካታ የሙስሊም ምሁራን በዮሐንስ ወንጌል ሰፍረው የሚገኙትንና ስለ መንፈስ ቅዱስ የሚያወሩትን ጥቅሶች በመውሰድ ስለ ሙሐመድ የተነገሩ ትንቢቶች ናቸው በማለት ለማጠቃለል ይሞክራሉ፡፡ ከእነዚህም ጥቅሶች መካከል ለአብነት ዮሐንስ 14፡16 ፣ 15፡26 እና 16፡7 ይገኙባቸዋል፡፡ በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የሚገኘው ፓራክሊቶስ (parakletos) የሚለው ቃል የግሪክ ቃል ሲሆን ወደ እንግሊዘኛ ቋንቋ ሲመለስ ደግሞ ‹‹አፅናኝ››፣ ‹‹ጠበቃ››፣ ወይም ‹‹አማካሪ›› የሚሉ የአማርኛ ፍቺዎች ተሰጥተውት እናነባለን፡፡ አንዳንድ የሙስሊም ምሁራን የመጀመሪያው የግሪክ ቃል ከመነሻው በስህተት ተፅፎ ነው እንጂ ሊጻፍ ይገባ የነበረው ፔሪክሉቶስ (periklutos) በሚል መንገድ ነበር በማለት ይከራከራሉ፡፡ የዚህ ቃል ትርጉም ‹‹ምስጋና የተገባው›› ማለት ሲሆን አህመድ ከሚለው ስም ጋር የተቀራረበ ትርጉም ይሰጣል፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ አህመድና ሙሐመድ የሚሉት ቃላት አንድ አይነት አለመሆናቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡ ‹‹ሙሐመድ›› የተጽኦ ስም ሲሆን ትርጉሙም ‹‹ሊመሰገን የሚገባው ሰው›› ማለት ነው፡፡ አህመድ ደግሞ ቅፅል ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹ምስጋና የተገባው›› ማለት ነው፡፡ ከሙሐመድ ዘመን በፊት አህመድ የሚለው ቃል በተጽኦ ስምነት ውሎ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው የእስልምና ሃይማኖት ነቢይ የሆነው ሙሐመድ በቁርአን የትም ቦታ ላይ አህመድ በመባል ያልተጠራው፡፡

በዮሐንስ ወንጌል ላይ የተጠቀሰው ፓራክሊቶስ (አፅናኝ፣ ጠበቃ፣ አማካሪ) ቃሉ የተጠቀሰባቸው አውዶች – ዓለም ሊያየው የማይችል ‹‹የእውነት መንፈስ››፣ በአማኞች ልብ ውስጥ የሚኖር እና ስለ ኢየሱስ የሚመሰክር – እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ስለዚሁ ስለ መንፈስ ቅዱስ አንስቶ ሲያስጠነቅቃቸው እንዲህ ብሏቸው ነበር፡-

  • ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።

የሐዋሪያት ሥራ 1፡8

ስለ መንፈስ ቅዱስ የተነገረው ይህ ትንቢት ክርስቶስ ከሞተ ከ 50 ቀናት በኃላ በጰንጠቆስጤ ቀን በታላቅ ተአምራት በደቀ መዛሙርቱ ሕይወት ተፈፅሟል፡፡ ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ የሆነው ጴጥሮስ ይህን አስገራሚ ትዕይንት ሲገልጥ እንዲህ አለ፡- 

  • ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው።

የሐዋሪያት ሥራ 2፡32፣33

ከላይ ባየናቸው ጥቅሶች መሰረት ይህ ፓራክሊቶስ፣ መንፈስ ቅዱስ እንጂ ፈፅሞ ሰው ሊሆን እንደማይችል ግልፅ ሊሆን ይገባል! በተጨማሪም፣ ኢየሱስ ከአባቱ ዘንድ እንደሚመጣ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረለት ይህ ፓራክሊቶስ በእርግጥም በእነዚህ ሰዎች ሕይወት ላይ መጥቷል፡፡ እዚህ ላይ ሙሐመድ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከሞቱ ከ 500 አመታት በኃላ የመጣ ሰው መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

ከእነዚህ ጥቅሶች በተጨማሪ ስለ ሙሐመድ የተነገረ ነገር ቢኖር በማለት ሙስሊሞች ብሉይ ኪዳንን በተለይ ቶራን (የሙሴ መጻሕፍትን) መርምረዋል፡፡ ስለ ሙሐመድ የሚያወሩ ናቸው በሚል ከዚህ የብሉይ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በተደጋጋሚ የሚጠቀሱ ጥቅሶች ዘዳግም 18፡15-16 እና ዘዳግም 18 ቁጥር 18 ናችው፡-

  • አምላክህን እግዚአብሔርን በኮሬብ ስብሰባ ተደርጎ በነበረበት ቀን። እንዳልሞት የአምላኬን የእግዚአብሔርን ድምፅ ደግሞ አልስማ፣ ይህችን ታላቅ እሳት ደግሞ አልይ ብለህ እንደ ለመንኸው ሁሉ፣ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል፤ እርሱንም ታደምጣለህ።… ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሳላቸዋለው፤ ቃሌንም በአፉ አደርጋለው፤ ያዘዝሁትን ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል፡፡

ዘዳግም 18፡15-16፣ 18፡18

በርካታ ሙስሊሞች ከሙሴ በኃላ ይነሳል የተባለው ይህ እንደ ሙሴ አይነቱ ነቢይ፣ ሙሐመድ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ጉዳይ፣ በቀጣዩ ክፍል ላይ የሚዳሰስ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading