የሕይወት እንጀራ

“የኢየሱስ ነቢይነት ለእስራኤላውያን ብቻ ነው፡፡”

የኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት ክርስቲያኖች እንደሚያምኑት ለሰው ዘር ሁሉ ሳይሆን ለእስራኤላውያን ብቻ ነው ሲሉ አንዳንድ ሙስሊሞች ይሟገታሉ፡፡ ከዚህ የመከራከሪያ ነጥብ ላይ በመነሳትም ክርስቲያኖች (እንደ እነሱ እምነት ‹‹ዘመን የማይሽረውና የአለሙ ሁሉ ነቢይ›› የሆነውን) ሙሐመድን እንዲከተሉ ለማሳመን ይጥራሉ፡፡ ይህንን መከራከሪያቸውን በማስረጃ ለማስደገፍም በፍጥነት ከአዲስ ኪዳን የሚከተለውን ጥቅስ ያነሳሉ፡፡

  • እነዚህን አሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው፣ አዘዛቸውም፣ እንዲህም አለ። በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ፣ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤ ይልቅስ የእሥራኤል ቤት ወደሚሆኑ ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ እንጂ። 

ማቴዎስ 10፡5፣6

  • እርሱም [ኢየሱስም] መልሶ። ከእሥራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም አለ።

ማቴዎስ 15፡24

በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስ በአብርሃም፣ ይስሃቅና ያዕቆብ ዘር ውስጥ እንደ ተወለደ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ኢየሱስ፣ ከብዙ ምእተ ዓመታት በኃላ የተፈፀመውና እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባለት ቃል ኪዳን ፍፃሜ ነው፡፡ አብርሃም ለእግዚአብሔር ፈቃድ ባሳየው መታዘዝና ፍፁም መገዛት እግዚአብሔር ሁለት ዘርፍ ያለው ቃል ኪዳን ገብቶለት ነበር፡፡ የቃል ኪዳኑ የመጀመሪያ ዘርፍ፣ እግዚአብሔር የአብርሃምን ዘር ማለትም ይስሃቅን፣ ያዕቆብን (እሥራኤል) እና የእሥራኤልን ዘሮች ሁሉ ለመባረክ ቃል ኪዳን መግባቱ ሲሆን የቃል ኪዳኑ ሁለተኛ ዘርፍ ደግሞ ከዚህ ዘር (ማለትም ከአብርሃም ይስሃቅና ያዕቆብ ዘር) መካከል ለአሕዛብ ሁሉ የሚሆን በረከት እንደሚገኝ ማለትም በዘሩ አሕዛብ ሁሉ እንደሚባረኩ ቃል ኪዳን መግባቱ ነበር (የሐዋሪያት ሥራ 3፡25፣ 26 እና ገላቲያ 3፡8፣14 ይመልከቱ)፡፡

ለአብርሃም በተገባለት ቃል ኪዳን መሠረት የእሥራኤል ዘርና አሕዛብ (እሥራኤላዊ ያልሆነ የሰው ዘር በሞላ) እንደሚባረኩ ማወቅ ይቻላል፡፡ የዚህ ቃል ኪዳን መፈፀም ከብዙ ምዕተ አመት በኃላ በኢየሱስ መወለድ ተረጋግጧል፡፡ ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ በእስራኤላውያን ልማድ መሠረት ቤተሰቡ ሃይማኖታዊ የሆነውን ስርአት ለመፈፀም ወደ መቅደስ ይዘውት ሄዱ፡፡ በመቅደስ ይፀልይ የነበረ አንድ ሽማግሌ ሰው በመንፈስ በመረዳት ሕፃኑን በእጆቹ በመያዝ በፀሎቱ ውስጥ የሚከተለውን ለእግዚአብሔር ተናገረ፡-

  • ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእሥራኤል ክብር ነው። 

ሉቃስ 2፡30-32

ከላይ በተመለከትነው ምንባብ መሠረት ኢየሱስ ሁለት ፈርጅ ያለው አገልግሎት እንደ ነበረው መገንዘብ እንችላለን፡፡ በመጀመሪያ፣ እነደ እሥራኤላዊ ሆኖ ስለ ተወለደ የመጀመሪያ ተልዕኮው ራሱንና እግዚአብሔርን ለእስራኤላውያን መግለጥ ነበር፡፡ የአብርሃም፣ ይስሃቅና ያዕቆብ ዘሮች በእግዚአብሔር የተመረጡ ሕዝቦች ነበሩና፡፡ ቁርአን ሳይቀር ስለዚህ ጉዳይ ምስክርነቱን አይሸሽግም፡፡

  • ባሮቻችንንም ኢብራሂምን [አብርሃምን]፣ ኢስሐቅንና [ይስሃቅን] ያዕቆብንም የኀይልና የማስተዋል ባለ ቤቶች የኾኑትን አዉሳላቸዉ፡፡ እኛ ጥሩ በኾነች ጠባይ መረጥናቸዉ፤ (እርሷም) የመጨረሻይቱን አገር ማስታወስ ናት፡፡

ሱረቱ ሷድ (38)፡45፣46

And commemorate Our servants Abraham, Isaac, and Jacob, possessors of power and vision. Verily, we did chose them for a special (purpose)– proclaiming the message of the hereafter.

  • የእሥራኤል ልጆች ሆይ! ያችን በናንተ ላይ የለገስኳትን ጸጋየንና እኔም በዓለማት ላይ ያበለጥኳችሁ መኾኔን አስታውሱ፡፡

ሱረቱ አል-በቀራህ (2)፡47

Children of Israel, call to mind the (special) favour which I bestowed upon you, and that I preferred you to all others (for My message).

እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን እንዲህ አይነቱን ልዩ ምርጫና ጥሪ ያደረገ ቢሆንም፣ በሚያሳዝን ሁኔታ እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ጥሪ እልኸኞችና ግዴለሾች ሆኑ፡፡ በዚህም ምክንያት ኢየሱስ በእግዚአብሔር የተመረጠውን ሕዝብ ለመቤዠት፣ በእግዚአብሔር የተቀባና የተባረከ፣ እሥራኤልም ለረጅም ዘመናት ይጠብቀው የነበረ መሲህ መሆኑን ለማረጋገጥ በመካከላቸው ድንቅንና ምልክቶችን እያደረገ እንዲያገለግል ግድ ሆነበት፡፡ ይህን የመጀመሪያ ተልዕከኮውን ለመወጣት፣ ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሥራኤል ልጆች ብቻ እንዲሄዱ አዘዛቸው፡፡ እስራኤላውያን መልዕክቱን በመጀመሪያ መስማት የተገባቸው ነበሩና፡፡ በእግዚአብሔር የበረከት ተስፋ የተገባላቸው የቃል ኪዳን ሕዝቦች ስለ ነበሩ ይህን ልዩ መብትና ጥቅም በመጀመሪያ ሊያጣጥሙ ተገብቷቸዋል፡፡ ከኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ በኃላ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዱ ለእስራኤላውያን እንዲህ ሲል ንግግር አደረገ፡-

  • እናንተ የነቢያት ልጆችና እግዚአብሔር ለአብርሃም፡- በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ ብሎ፣ ከአባቶቻችን ጋር ያደረገው የኪዳን ልጆች ናችሁ። ለእናንተ አስቀድሞ እግዚአብሔር ብላቴናውን አስነሥቶ፣ እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ እየመለሰ ይባርካችሁ ዘንድ፣ ሰደደው። 

የሐዋሪያት ሥራ 3፡25፣26

የኢየሱስ ተልዕኮ ሁለተኛ ክፍል ከፍተኛ ትርጉም እንዳለው አፅንኦት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ይህ ተልዕኮ ነፍሱን ለሰው ዘር ኃጢአት ቤዛ አድርጎ የሰጠበት ነው (1ጢሞቴዎስ 2፡4-6)፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ለሰው ልጆች ሁሉ የሆነው የበረከት የምሥራች፡፡ የምሥራቹም፣ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደምና በተቀበለው ስቃይ በሰዎች ላይ የነበረውን የኃጢአት ቅጣት ማስወገዱ ነው፡፡ ማንም ይህንን የድኅነት/የመዳን በረከት ቢቀበል ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም የመኖር ዋስትና ያገኛል!

  • እንዲህም አላቸው። ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፣ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል። 

ሉቃስ 24፡46፣47

በመሲሁ ኢየሱስ በኩል የሆነው ይህ ድኅነት/መዳን ለአይሁድና ለመላው የዓለም ሕዝብ ሁሉ የተሰጠ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልፅ ይናገራል፡፡ ያስተውሉ፣ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረው አገልግሎቱ ወቅት ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሥራኤላውያን ዘንድ ብቻ እንዲሄዱ አዟቸው ነበር፡፡ ነገር ግን በሁለተኛ የአገልግሎት ክፍሉ (መስቀል ላይ ሞት ከተቀበለ በኃላ) ደቀ መዛሙርቱን ምን ብሎ እነዳዘዛቸው ከዚህ በታች በቀረቡ ጥቅሶች ያስተዉሉ፡-

  • ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።

የሐዋሪያት ሥራ1፡8 

  • እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።

ማቴዎስ 28፡19-20 

  • ደግሞም ኢየሱስ፡- እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው።

ዮሐንስ 8፡12

ቁርአን ሳይቀር የኢየሱስን አለማቀፋዊ አገልግሎት በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ እስቲ የሚከተሉትን ክፍሎች እንመልከት፡-

  • (በጋብቻ) ሰው ያልነካኝ ኾኜ አመንዝራም ሳልኾን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል! አለች፡፡ አላት፡- (ነገሩ) እንደዚህ ነዉ፣ ጌታሽ፡- እርሱ በእኔ ላይ ገር ነዉ፣ ለሰዎችም ታምር ከኛም ችሮታ ልናደርገዉ (ይህንን ሠራን) የተፈረደም ነገር ነው አለ፣ (ነፋባትም)፡፡

ሱረቱ- መርየም (19)፡20፣21

And (We wish) to appoint him (Jeses) as a sign unto men (ayat-al linnasi), and a mercy from Us.

አንዳንድ ሙስሊሞች እንድናምን እንደሚፈልጉት ይህ ክፍል ‹‹ለእስራኤላውያን ብቻ የሆነ ምልክት›› እንደማይል አንባቢ ያስተውል፡፡ እንደውም አረቢኛው ‹‹ለሰው ዘር ሁሉ ምልክት!›› ነው የሚለው፡፡

የጌታ ጸጋ ከእርስዎ ጋር ይሁን፤ ሀሳብዎን ለመስማት ዝግጁ ነን።

Discover more from የሕይወት እንጀራ

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading