የመጽሐፈ ሩት ዋና ዋና ትምህርቶች 

በመጽሐፈ ሩት ውስጥ በተደጋጋሚ የተጠቀሱ ሁለት ቁልፍ ቃላት ይገኛሉ። እነርሱም የመጽሐፉን ዋና ዋና ትምህርቶች የያዙ ናቸው።

 1. መዋጀት፡- በዚህ ታሪክ መዋጀት የሚለውን ትርጉም የሚሰጠውን የዕብራይስጥ ቃል በተለያየ መልኩ 23 ጊዜ እናገኘዋለን። በመጽሐፈ ሩት «መዋጀት» የሚለው ቃል በተለይ ያገለገለው የአይሁድን የመቤዥት ባሕል ለመግለጥ ነው። ተቤዢው ለሟች ዘመዱ ወራሽ የሆነ ልጅ ለማሳደግ፥ ወይም ለችግረኛ ዘመዱ በችግር ምክንያት የሸጠውን መሬቱን ከፍሉ ለማስመለስ፥ ወይም በባርነት ሊወድቅ ላለ ዘመዱ ዋጋ ከፍሉ ከባርነቱ ለማስቀረት ወዘተ ፈቃደኛ የሆነ ነው። ቦዔዝ ለሩትና ለኑኃሚን ተቤዢ ሆነ።

ቦዔዝ የእግዚአብሔርና የሕዝቡ የእስራኤል ግንኙነት ተምሳሌት ነበር። ቦዔዝ ኑኃሚንና ሩትን በድህነት ምክንያት ከነበረባቸው ባርነት ዋጃቸው (ተቤዣቸው)። ፍላጎታቸውን አሟላ። ልክ እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ነፃ እንዳደረገ ዓይነት ማለት ነው። እርሱ የእስራኤላውያንን ፍላጎት ሁሉ ያሟላ አምላክ ነው።

ቦዔዝ የክርስቶስ ኢየሱስ ተምሳሌት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆነ፥ በመሆኑም የእኛ ዘመድ ሆነ። እንደ ዘውድነቱ በመስቀል ላይ በመሞቱ፥ እያንዳንዳችንን ከኃጢአት ባርነት ዋጀን፤ (የሐዋ. 20፡28)፤ በዚህም የተቤዢነቱን ዓላማ አሟላ። ተቤዢያችን ክርስቶስን እኛን ከባርነት፥ ከመንፈሳዊ ጉስቁልና ለመዋጀት የሚከፈለውን ዋጋ ከፈለ። በዚህም የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት አደረገን።

የትኩረት ነጥብ፥ የተቤዠህን ክርስቶስን ለማመስገን ጊዜ ይኑርህ።

 1. በፍቅር የተሞላ ቸርነት፡- አይሁድ «ሂሴድ» የሚል ልዩ ቃል ነበራቸው። ይህ ቃል በብዙ ልዩ ልዩ መንገዶች ሊተረጎም ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ለቃል ኪዳኑ ታማኝነት፥ አንዳንድ ጊዜ ርኅራኄ፥ ሌላ ጊዜ ፍቅር መሆን ይችላል።

የሩት ታሪክ እንዲህ ዓይነቱን በፍቅር የተሞላ ርኅራኄ ይገልጣል። ሩት እውነተኛ ተስፋ ባይኖርም እንኳ በፍቅር የተሞላ ርኅራኄና ቸርነት ለኑኃሚን ገለጠች። የኑኃሚንን ጉስቁልና በመካፈል በታማኝነት ለኑኃሚን የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ከእርሷ ላለመለየት መቁረጧን ገለጠች (2፡11-12)። ቦዔዝ ሩትን በእርሻ ስፍራው በመርዳት፥ ወራሾቹን አደጋ ላይ የሚጥል ቢሆንም እንኳ፥ እርሷን ለማግባት በመፍቀድ እንዲህ ዓይነቱን በፍቅር የተሞላ ቸርነትና ርኅራኄ ለሩትና ለኑኃሚን ገለጠ።

ከሁሉም በላይ ግን በታሪኩ ውስጥ የእግዚአብሔርን በፍቅር የተሞላ ቸርነትና ርኅራኄ እንመለከታለን (2፡20)። ከዚህ ታሪክ የምንመለከተው፥ እግዚአብሔር በእርሱ የሚታመኑትን ፍቅርን በተሞላ ቸርነትና ርኅራኄ እንደሚመለከታቸው ነው። በመጽሐፈ ሩት ውስጥ እግዚአብሔር በተለያዩ ስውር መንገዶች ለሕዝቡ ጥቅም ሲሠራ እንመለከታለን። ሩትን ወደ ቦዔዝ እርሻ መራት፤ ቦዔዝም እንዲራራላት አደረገ፤ ቦዔዝና ሩት እንዲጋቡም አደረገ። ቦዔዝ፥ ሩትንና ኑኃሚንን የታላቁ የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት አያት በሆነ ልጅ ባረካቸው።

ምንም እንኳ የእግዚአብሔርን እጅ ሁልጊዜ በሥራ ላይ ባናየውም፥ እግዚአብሔር በማይታይ መንገድ ለእርሱ ታማኝ የሆኑ ሕዝቦችን ሁልጊዜ እንደሚረዳ እንመለከታለን። የሩት ታሪክ ሮሜ 8፡28ን ይገልጣል። «እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን።»

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነህ መከራን በምትቀበልበት ጊዜ፥ ይህ እውነት እንዴት ያጽናናሃል? ለ) ለእግዚአብሔርና ለሌሎች ባለህ ግንኙነት ታማኝ ስለመሆን አስፈላጊነት ይህ ታሪክ ምን ያስተምርሃል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

መጽሐፈ ሩት (1-4)

 1. የሩት ታሪክ የተፈጸመበት ጊዜና ቦታ (ሩት 1)

መጽሐፈ ሩት የሚጀምረው ታሪኩ በዘመነ መሳፍንት ወቅት የተፈጸመ መሆኑን በመናገር ነው። በይሁዳ ግዛት ራብ እንደተነሣ ይናገራል። የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ራብን የተጠቀመበት በአቤሜሌክ ቤተሰብ ላይ ስለመጣው ችግር ለመናገር ብቻ ሳይሆን፥ ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ስለመሆናቸውም ለማጋለጥ ነበር። ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው የራብን መርገም ጭምር እንደሚያመጣባቸው እግዚአብሔር አስቀድሞ ተናግሮአል (ዘዳ. 28፡23-24)።

የአቤሜሌክ ቤተሰብ ራቡን በመሸሽ ወደ ሞዓብ ሄደ። በዚያም ለብዙ ዓመታት ስለኖሩ፥ ሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸው ሞዓባውያን የሆኑ ሴቶችን አገቡ፤ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ አቤሜሌክና ሁለቱ ልጆቹ ሞቱ።

የታሪኩ ዋና ትኩረት ኑኃሚን እንዴት ባዶና ድሀ እንደሆነች ለማሳየት ነው። ባልዋን እና ልጆችዋን አጣች። በእርጅናዋ ወራት እንክብካቤ የሚያደርግላት አንዳችም ወራሽ፥ ወይም ራሷን የምትደግፍበት መሬት አልነበራትም፤ ስለሆነም እጅግ ተማርራ ወደ ይሁዳ ለመመለስ ወሰነች። አንደኛዋ ምራቷ በሞዓብ ስትቀር፥ ሌላኛዋ ግን ማለትም ሩት አማትዋን ለመከተል አማልክትዋን፥ ቤተሰብዋንና አገሯን ሁሉ ተወች። ሩት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገለጥ የታማኝ ፍቅር ምሳሌ ናት። ወደ እስራኤል ምድር እንደ እንግዳ ከመሄድ ይልቅ በአገሯ መቅረት፥ ከገዛ ሕዝቧ ጋር መኖር በቀለላትም ነበር።

 1. ለኑኃሚንና ለሩት እንክብካቤ ለማድረግ እግዚአብሔር የሠራው ሥራ (ሩት 2-3)

በዚህ ታሪክ ውስጥ እግዚአብሔር የተጠቀሰበት ቦታ ብዙ ባይሆንም፥ በታሪኩ ሁሉ የእግዚአብሔርን እጅ እንድናይ ለማድረግ ጽሐፊው እንደሞከረ ግልጥ ነው። ሩት እንዴት ወደ አማቷ ዘመድ የእርሻ ቦታ እንደሄደች ተመልከት። የኑኃሚን ዘመድ የሆነው ቦዔዝ ለሩት ልዩ የሆነ ትኩረትና ጥንቃቄ እንዴት እንዳደረገ እንመለከታለን። እግዚአብሔር ቦዔዝ የቤተሰብ ግዴታውን ለመፈጸም ብሎ አሕዛብ የሆነች ሴት እንዲያገባ እንዴት እንደገፋፋው ተመልከት።

ታሪኩ የሚያተኩረው በሁለት ዋና ዋና ገጸ-ባሕርያት ታማኝነት በተሞላ ፍቅር ላይ ነው። በመጀመሪያ፥ ሩት ለኑኃሚን የነበራት በታማኝት የተሞላ ፍቅር ነው። በሁለተኛው ደግሞ፥ ቦዔዝ ለሩትና ለኑኃሚን ያሳየው በታማኝነት የተሞላ ፍቅር ነው።

ነገር ግን ከሰው የታማኝነት ፍቅር ምሳሌነት ሁሉ በላይ እግዚአብሔር ለሁለት ድሀና ምስኪን ሴቶች የነበረውን ፍቅርና እንክብካቤ እናያለን።

 1. እግዚአብሔር የሩትንና የቦዔዝን ታማኝነት በማክበርና ለእርሱ ዋጋ በመስጠት ለኑኃሚን በረከቱን መለሰላት (ሩት 4)

ከሩት ታሪክ በስተጀርባ የአይሁድ ባሕል የሆነ «የመዋጀት» ተግባር እናያለን። መመሪያው በዘዳግ. 25፡5-10 ይገኛል። በዚህ ስፍራ የእግዚአብሔር ሕግ የሚለው አንድ ሰው ልጅ ሳይኖረው ቢሞት፥ ወንድሙ የሞተውን ሰው ሚስት በመውሰድ ከሴቲቱ ልጅ መውለድ እንደነበረበት ነው። በዚህ መንገድ የሚገኘው ልጅ የሟች ወንድሙ ወራሽ ይሆን ነበር፤ ደግሞም በዘሌ. 25፡25-31፥ 41-55 ሕጉ በተጨማሪ ድሀ የሆነ ሰው በድህነት ምክንያት መሬቱን ቢሸጠው፥ የዚህ ድሀ ሰው ዘመድ ገንዘቡን በመክፈል መሬቱን ሊያስመልስና በባዕድ እጅ እንዳይገባ ሊከላከል ይገባ ነበር። የእነዚህ ሁለት ሕግጋት ዓላማ የአንድን ሰው የቤተሰብና የመሬት ወራሽነት ለመጠበቅ ነበር። 

በመጽሐፈ ሩት፥ ይህ ሕግ በቅርብ ዘመድ ብቻ ሳይወሰን፥ በሩቅ ዘመድም ላይ የሚሠራ ሆነ። የመዋጀት ግዴታ የወደቀው በቅርብ ዘመድ ላይ ነበር። ይህ የቅርብ ዘመድ ግዴታውን ለመወጣት ፈቃደኛ ያልሆነ ወይም የማይችል ከሆነ ብቻ ኃላፊነቱ ወደ ሌላ ዘመድ ይተላለፍ ነበር። በዚሁ መሠረት ቦዔዝ ሩትን አገባና የአቤሜሌክና የልጆቹ ወራሽ የሚሆን ልጅ አስገኘ። ልጁ የአቤሜሌክ ምድር ወራሽ ሆነ፥ ቦዔዝ ደግሞ የአቤሜሌክ ምድር የተያዘበትን ዕዳ ሁሉ የመክፈል ግዴታ ነበረበት። 

ይህ ከሩት ምዕራፍ 4 ታሪክ በስተኋላ የሚገኝ ባሕላዊ ልማድ ክፍል ነው። ቦዔዝ የኑኃሚን የቅርብ ዘመድ የሆነውን ሰው ይፋ ፍርድ ወደሚሰጥበት ስፍራ አመጣው። በጥንት ዘመን የጎሣ ሽማግሌዎች በከተማይቱ በር ላይ ይገናኙና በጉዳዮች ላይ ውሳኔ በመስጠት ይፈርዱ ነበር። ወደዚህ የፍርድ ስፍራ የመጣው የቅርብ ዘመድ ለሩት ያለበትን ግዴታ ለመወጣት ፈቃደኛ አለመሆኑን ገለጠ። ይህንን ለማድረግ ያልፈለገው፥ የራሱ ልጆች ቢሞቱ ቀሪው ወራሽ ከሩት የሚወለደው ልጁ ስለሚሆን፥ የራሱንም ንብረት ለመቆጠብ ሳይሆን አይቀርም። ይህ ዘመድ ከቦዔዝ የሚለይበት ነገር ቢኖር ስለራሱ ብቻ የሚያስብ ስስታም ስለ ነበር ነው።

ቦዔዝ ሩትን የማግባት ግዴታውን ተወጣ። በዚህም ኢዮቤድ የተባለ ልጅ አገኙ። በኃዘኗ ምክንያት በብቸኝነት ተቆራምዳ የነበረችው ኑኃሚን፥ የተባረከች ኑኃሚን ሆነች። የልጅ ልጅ ማግኘቷ ብቻ ሳይሆን ምድሪቱ ለእርሷ ተመለሰችላት፤ በእርጅናዋ ወራት የሚጦራትንም አገኘች። 

በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ጥበብ፥ የሩትና የቦዔዝ ልጅ የእስራኤል ታላቅ ንጉሥ የሆነው የዳዊት አያት ሆነ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ እግዚአብሔርና ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ስላለው ግንኙነት ከዚህ ታሪክ የተማርካቸው ዋና ዋና ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመጽሐፈ ሩት ዓላማ 

የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔር መጽሐፈ ሩት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲካተት ያደረገው ለምን ይመስልሃል?

መጽሐፈ ሩት ለምን እንደተጻፈና በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እንደተካተተ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ይከራከራሉ። ስለዚህ ጉዳይ ሦስት ዋና ዋና አመለካከቶች አሉ፡-

መጽሐፈ ሩት የተጻፈው የዳዊትን አያቶችና ቅድመ አያቶች በመናገር፥ እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ የዳዊትን የዘር ግንድ እንዴት እንደጠበቀ ለማሳየት ነው። አንዳንዶች የሩትና የቦዔዝ ታሪክ ዳዊት ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሳየት የተጻፈ ነው ይላሉ። ኑኃሚን ከባዶነት ወደ ሙላት (1፡2)። ከከፍተኛ ራብና ችግር (1፡1-5)፥ ወደ ደኅንነትና ተስፋ (4፡13-17) እንደተመለሰች ሁሉ፥ ራስ ወዳድ ባልሆነው በዳዊት አመራር የእስራኤል ሕዝብ ከብሔራዊ አደጋ ወደ ሰላምና ብልጥግና ተመልሰዋል። በዚህ ዓይነት ዳዊት እውነተኛው የሩትና የቦዔዝ ልጅ መሆኑ ታየ። ይህ የመጽሐፉ ዓላማ ሊሆን የሚችል ነው ቢባልም ዋናው የመጽሐፉ ዓላማ ግን አይደለም።

 1. መጽሐፈ ሩት የተጻፈው አይሁድ አሕዛብን ወደ ይሁዲነት እምነት ለመለወጥ መሞከር እንዳለባቸው ለማስተማርና አሕዛብም እግዚአብሔርን በእውነተኛ እምነት ሊያመልኩ እንደሚችሉ ለማስተማር ነበር። ይህም ቢሆን የመጽሐፉ ዋና ዓላማ መሆን የሚያጠራጥር ነው።
 2. መጽሐፈ ሩት የሚያስተምረው፥ አጠቃላይ የሆነ ክሕደት ባለበት ዘንድ በእግዚአብሔር ላይ እውነተኛ እምነት ያላቸው ጥቂት ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ለማሳየት ነው። ብዙ ክፋት ባለበት ስፍራ እምነት ሊኖር ይችላል። እግዚአብሔር የእነዚህን ጥቂት ሰዎች እምነት ስለሚያከብር፥ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታም ውስጥ ጠበቃቸው። ከሦስቱ አመለካከቶች መካከል የመጽሐፈ ሩት ዋና ዓላማ ይህ ሳይሆን አይቀርም። 

መጽሐፈ ሩትን ለመረዳት፥ ከመጽሐፈ መሳፍንት ቀጥሎ መምጣቱንና ዘመነ መሳፍንት ደግሞ ከፍተኛ ክፋትና የሥነ – ምግባር ብልሽት የታየበት ዘመን መሆኑን ማስታወስ እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህ መጽሐፍ ንጉሥ ያልነበረበትን የዚህ ዘመን አጠቃላይ ገጽታ የሚያሳይ ነው።

መጽሐፈ ሩት፥ አብዛኛው የእግዚአብሔር ሕዝብ ከነበረበት አሳዛኝ ክሕደት ጋር በተነጻጻሪነት የቀረበ ታሪክ ነው። የመጽሐፈ ሩት ጸሐፊ በታላቅ ክፋት መካከል ጨርሶ ባልተጠበቀ ስፍራ፣ ባልታሰቡ ሰዎች ልብ ውስጥ እምነት ሊኖር እንደሚችል በብዙ ንጽጽር ያሳየናል። ጸሐፊው በርካታ የተለያዩ ምሳሌዎችን በመጠቀም እውነተኛ እምነት በጥቂት ታማኝ ሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚያመጣውን ለውጥ ያሳያል። የሚከተሉትን ተመልከት፡

 1. የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑት አይሁድ የእግዚአብሐርን ንጉሥነት እምቢ ብለው ጣዖታትን አመለኩ። (ዘመነ መሳፍንት)
 2. የተናቀችው የአሕዛብ ወገን እውነተኛውን እግዚአብሔርን ለመከተል የጣዖት አምልኮን ተወች፡፡ (መጽሐፈ ሩት) 
 3. ዘመነ መሳፍንት ትኩረቱ በሕዝቡ ሕይወት በሚታየው ታላቅ ክፋት ላይ ነው።
 4. መጽሐፈ ሩት ትኩረቱ እንደ ሩትና ቦዔዝ ባሉት ጥቂት ግለሰቦች እምነት ላይ ነው። 
 5. ዘመነ መሳፍንት ትኩረቱ በወንዶችና በኃጢአተኛነታቸው ላይ ነው፡፡
 6. መጽሐፈ ሩት ትኩረቱ በሴቶችና በእግዚአብሔር ባላቸው እምነት ላይ ነው። 
 7. ዘመነ መሳፍንት እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደሚቀጣ ያሳያል፡፡
 8. መጽሐፈ ሩት እግዚአብሔር፥ እምነታቸውን በእርሱ ላይ ለሚያደርጉ ሰዎች ታማኝ መሆኑን ያሳያል። 

መጽሐፈ ሩት የሚመደበው «አጭር ታሪክ» ተብሎ ከሚጠራ የሥነ-ጽሑፍ ዓይነት ነው። የታሪኩ ዓላማ ትልቅ የሃይማኖት መሠረታዊ ትምህርት ለማስተማር አይደለም፤ ነገር ግን በክፋት መካከል ሰዎች ሊኖራቸው የሚችለውን እምነትና በመታዘዝ ለሚከተሉት እግዚአብሔር ያለውን ታማኝነት ለማሳየት ነው። ታሪኩ፥ እውነተኛ እምነት ተራ በሆኑ በታማኝ የእግዚአብሔር ሰዎች ሕይወት ውስጥ ምን እንደሚመስል ይገልጣል።

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ቆሮ. 1፡18-31 አንብብ። ሀ) እነዚህ ጥቅሶች ተራ ሰዎችን በመጠቀም ውስጥ የእግዚአብሔር ዓላማ ምንድን ነው ይላሉ? ለ) እግዚአብሔር ይህንን የሚያደርገው ለምን ይመስልሃል? ሐ) ይህ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ሲፈጸም የምታየው እንዴት ነው? መ) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሀብታሞች ወይም በተማሩ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ስለማድረግ ይህ ምን ያስተምረናል? ሠ) ብዙ ጊዜ ተራ ሰዎች እውነተኛ እምነትና ታላቅ መንፈሳዊነት ለጥቂት የተማሩ ሰዎች ብቻ ነው ብለው የሚያስቡት በምን መንገድ ነው? ረ) እግዚአብሔር የተራ ሰዎችን እምነት እንደሚያከብር መጽሐፈ ሩት ምን ያስተምረናል? 

የውይይት ጥያቄ፥ ሩት 1-4 አንብብ። ሀ) የአቤሜሌክ ቤተሰብ ወደ ሞዓብ የሄደው ለምን ነበር? ለ) የሩትን እምነት ከዖርፋ እምነት ጋር አወዳድር። የሩት እምነት ታላቅ የሆነው እንዴት ነው? ሐ) ሩት ለኑኃሚን ታማኝ መሆኗን ያሳየችው እንዴት ነበር? መ) እግዚአብሔር ሩት ለኑኃሚን ያሳየችውን ታማኝነት ያከበረውና ዋጋ የሰጠው እንዴት ነበር? ሠ) ከዚህ ታሪክ በእግዚአብሔር ላይ ሊኖረን ስለሚገባ ታማኝነትና እግዚአብሔር ለልጆቹ ስላለው ታማኝነት ልንማር የምንችለው ነገር ምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

መጽሐፈ ሩት መግቢያ

በየትኛውም ዘመን፥ ምንም ያህል ጊዜው ጨለማ ቢሆን፥ እግዚአብሔር የራሱ የሆኑ የተመረጡ ሕዝቦች አሉት። አብዛኛው ሕዝብ የሚኖረውን ኑሮ እየተቃወሙ፥ እግዚአብሔርን የሚያስከብርና ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሕይወት የሚኖሩ ጥቂት ታማኞች አሉ፤ በመጽሐፈ ሩት ውስጥ የምናየው ነገር ይህ ነው። ዘመነ መሳፍንት በአጠቃላይ ሲታይ እጅግ የከፋ ቢሆንም፥ በእስራኤል ውስጥ እግዚአብሔርን ያከበሩ ጥቂት ሰዎች ነበሩ። መጽሐፈ ሩት የእነዚህን ጥቂት ሰዎች እምነትና እግዚአብሔር እንዴት ለእነርሱ መልካም እንዳደረገላቸው የሚያሳይ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ በማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለእግዚአብሔር የሆኑ ቅሬታዎች ወይም ጥቂት ታማኞች የመኖራቸውን እውነትነት በሕይወትህ እንዴት አየኸው? 

የውይይት ጥያቄ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ መጽሐፈ ሩትን ተመልከት፤ ስለዚህ መጽሐፍ የሚናገራቸውን ዋና ዋና ነገሮች ዘርዝር። 

የመጽሐፈ ሩት ስያሜ

መጽሐፈ ሩት የተሰየመው በመጽሐፉ ታሪክ ዋና ገጸ ባሕርይ በሆነችው በሩት ነው። አስቴርን ጨምሮ በሴት ስም ከተሰየሙ ሁለት መጻሕፍት መካከል መጽሐፈ ሩት አንዱ ነው። 

የመጽሐፈ ሩት ጸሐፊ

የመጽሐፈ ሩት ጸሐፊ ማን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኘው ምንም መረጃ የለም። የአይሁድ ትውፊት መጽሐፉን የጻፈው ሳሙኤል ነው ይላል። የመጽሐፉ የመጨረሻ ትኩረት በዳዊት ላይ ስለሆነ፣ ጸሐፊው ሳሙኤል አይመስልም። ስለዚህ በዳዊት ዘመነ መንግሥት፥ ወይም ከዚያ ጥቂት ራቅ ብሎ፥ እግዚአብሔር የዳዊትን የዘር ግንድ ለመጠበቅ እንዴት እንደሠራ ለመግለጽ የሚፈልግ አንድ ሰው እንደጻፈው ይገመታል። ሩት 1፡1 የዘመነ መሳፍንት ፍጻሜን የሚያሳይ ይመስላል። የዳዊት ስም በመጽሐፉ መጨረሻ መጠቀሱ ሕዝቡ ዳዊትን ያውቁት እንደነበር ያሳያል። 

የመጽሐፈ ሩት ታሪክ የተፈጸመበት ጊዜ

የመጽሐፈ ሩት ታሪክ የተፈጸመው በዘመነ መሳፍንት ነው። በዘመነ መሳፍንት በየትኛው ጊዜ እንደተፈጸመ የምናውቀው ነገር የለም። አንዳንድ ምሁራን ዮፍታሔ በነበረበት ዘመን አካባቢ የተፈጸመ ነው ብለው ይገምታሉ። 

የመጽሐፈ ሩት አስተዋጽኦ

 1. በአቤሜሌክ ቤተሰብ ላይ የደረሰው መከራና ኃዘን (1፡1-5) 
 2. ኑኃሚንና ሩት ወደ ቤተልሔም ተመለሱ (1፡6-22) 
 3. ሩት ቦዔዝን በመከር መሰብሰቢያ ስፍራ አገኘችው (2) 
 4. ሩት ወደ ቦዔዝ የአውድማ ስፍራ በመሄድ እንዲያገባት ጠየቀችው (3) 
 5. ቦዔዝ ሩትን አገባ፤ ወንድ ልጅም ወለዱ (4፡1-17) 
 6. የዳዊት የዘር ሐረግ (4፡18-22)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)