እግዚአብሔር ልጆቹን ከሰይጣን ጥቃቶች ለማዳንና ድል-ነሺዎች እንዲሆኑ ለማገዝ መንፈሳዊ የጦር ዕቃዎችን ሰጥቷቸዋል (ኤፌ. 6፡10-24)

ጳውሎስ አማኞች የሰይጣንን ጥቃቶች እንዴት ሊያሸንፉ እንደሚችሉ መመሪያዎችን በመስጠት የትምህርቱን ክፍል ያጠቃልላል። ሰይጣን የክርስቲያኖች ኃይለኛ ስውር ጠላት ነው። ሰይጣን እግዚአብሔርን ይጠላል። ብዙውን ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር የሚዋጋው ልጆቹን በማጥቃት ነው። ጳውሎስ ከኃጢአት ባሕሪያችን ጋር፥ ከሌሎች አማኞች ወይም ከማያምኑ ሰዎች ጋር፥ በአጠቃላይም በዚህ ምድር ላይ እስካለን ድረስ በሚገጥሙን ትግሎች ሁሉ ውስጥ የሰይጣን እጅ እንዳለበት ገልጾአል። ጳውሎስ ከሰይጣንና ከብዙ ረዳቶቹ (አጋንንት ወይም ከፉ መናፍስት) ጋር የምናደርገውን ውጊያ አስመልክቶ፥ «መጋደላችን. . . ከእለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር ነው እንጂ » ብሏል። ይህም የሰይጣን ሠራዊት ሰዎች እንደሚያደራጁት የጦር ኃይል የተደራጀ መሆኑን ያሳያል።

ሰይጣን ማንነት ያለው ጠላት ቢሆንም በዓይን አይታይም። እንግዲህ ክርስቲያኖች ከዚህ ጠላት ጋር የሚዋጉት እንዴት ነው? ዛሬ ድምፅን ከፍ አድርጎ በመጸለይና በመገሠጽ ሰይጣንን መዋጋት እንደሚቻል ይታመናል። አንዳንዶች ወደ ጥልቁ ውረድ! እያሉ የተሳሳተ ጸሎት ይጸልያሉ። እግዚአብሔር ሰይጣንን ወደ ጥልቁ የማውረድ ሥልጣን አልሰጠንም። አንድ ቀን እግዚአብሔር ሰይጣንን ወደ ጥልቁ ከዚያም ወደ ሲኦል እንደሚያወርደው ቢታወቅም (ራእይ 20፡1-10)፥ ይህ የሚሆነው ግን በእኛ ወይም በጸሎታችን አማካኝነት አይደለም። ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ ውጊያ ሲያስተምር፥ ሰይጣንን ለመቋቋምና ለማጥቃት መዘጋጀት እንዳለብን አጽንኦት ሰጥቶ ገልጾአል። ጳውሎስ ጸንተን እንድንቆም ያሳስበናል። ጳውሎስ ሰይጣንን እንድናጠቃ ሳይሆን፥ በሕይወታችንም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ወደ ፈተና እንድንገባና እንድንታለል የሚጠቀምባቸውን በሮች መዝጋት እንዳለብን አስረድቷል። [ማስታወሻ:- (ሰይጣን ኃጢአት እንድንፈጽም የመፈተን እንጂ በግድ ኃጢአት የማሠራት አቅም የለውም። ኃጢአትን የምንፈጽመው በእውነት ከመጽናት ይልቅ ሰይጣን የሚናገረውን ውሸት በማመን ነው። ይህ የእኛ ውሳኔ ስለሆነ፥ ለኃጢአታችን ኃላፊነት የምንወስደው ራሳችን ነን። (ያዕ. 1፡13-15 አንብብ።)]

ጳውሎስ ይህን መልእክት የጻፈው ሮም ታስሮ በነበረበት ወቅት ነበር። በዚህ ጊዜ ምናልባትም ከእርሱ ጋር በሰንሰለት የታሰሩ ወይም እንዳያመልጥ ወኅኒ ቤቱን የሚጠብቁ የሮም ወታደሮች ነበሩ። ጳውሎስ ከእነዚህ ወታደሮች የተመለከተውን የጦር መሣሪያ በመጠቀም ከሰይጣን ጥቃት ራሳችንን እንዴት እንደምንከላከል የሚያስረዳ መልእክት ጽፎአል።

ሀ. የእውነት መቀነት (ቀበቶ)፡፡ ቀበቶ የጦር መሣሪያ ጠቃሚ አካል ባይመስልም፥ ለሮማውያን ከፍተኛ ጠቀሜታ ነበረው። መቀነቱ በሚዋጉበት ጊዜ ልብሳቸው እንዳይወልቅ ከመካከሉም በላይ፥ አብዛኛዎቹ የጦር መሣሪያዎች ከመቀነታቸው ጋር የተያያዙ ነበሩ። ያለ መቀነቱ መከላከያዎቻቸው ሰውነታቸውን ሊሸፍኑ አይችሉም ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ከሰይጣን ጥቃቶች ራሳችንን ለመከላከል ከምናደርጋቸው ነገሮች አንዱ እውነትን በማወቅ እንደሆነ ያስረዳል። ሰይጣን የውሸት አባት ስለሆነ ( ዮሐ 8፡44)፥ ክርስቲያኖች ውሸትን እንዲያምኑ በማድረግ በከፍተኛ ደረጃ ያጠቃቸዋል። የምንፈጽመው ኃጢአት ሁሉ ምንም ጉዳት እንደማያገኘን በማረጋገጥ ውሸት ላይ የተመሠረተ ነው። የምንከተለው የተሳሳተ ትምህርት ሁሉ የሰይጣን ውሸት ነው። የመከላከያ መሣሪያዎቻችን ሁሉ ከእውነት ጋር ካልተያያዙ፥ ሰይጣንንና የውሸት ፍላጻዎቹን ለመመከት የሚያስችል ኃይል ሊኖረን አይችልም። ይሁንና አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ለእውነት ግድ የላቸውም። ብዙ ክርስቲያኖች ወደ አምልኮ ወይም የፈውስ ፕሮግራም እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ወደሚረዱበት የሰንበት ትምህርት ቤት ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመሄድ አይፈልጉም። በእውነት ካልተሸፈንን ሰይጣን በቀላሉ ሊያሸንፈን ይችላል።

ለ. የጽድቅ ጥሩር። ጳውሎስ የገለጸው ሁለተኛው የጦር መሣሪያ ከከብት ቆዳ፥ ከነሐስ ወይም ከብረት ተሠርቶ የወታደሮችን ደረት የሚሸፍነው ጥሩር ነው። ይህ መሣሪያ እንደ ልብ ያሉትን ወሳኝ የሰውነት ክፍሎች ከአደጋ ይጠብቃል። ጳውሎስ ጽድቅ ሰይጣን ከሚወረውራቸው ውሸቶችና ጥርጣሬዎች እንደሚጠብቀን አስረድቷል። ይህ ጽድቅ በሁለት አቅጣጫዎች ይታያል። በመጀመሪያ፥ በክርስቶስ የተገኘውን የስፍራ ጽድቅ መገንዘብ ያሻል። ሰይጣን ከሳሽ ስለሆነ ብዙውን ጊዜ ለድነት (ደኅንነት) ብቁዎች እንዳልሆንን በመግለጽ ይከሰናል። ነገር ግን በክርስቶስ ባመንን ጊዜ እግዚአብሔር «ጥፋተኞች እንዳልሆንን» ወይም የእርሱን ጽድቅ እንደተቀበልን ተናግሯል። ስለሆነም በክርስቶስ ደም የተሸፈንንና የእርሱ ጽድቅ ስላለን፥ ሰይጣን እኛን ለመክሰስ ሥልጣን የለውም። ሁለተኛ፥ ይህ አዎንታዊ፥ ተግባራዊ ጽድቅንም ያመለክታል። እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ስንኖር፥ ኃጢአትን ከሕይወታችን ስናስወግድ፥ እግዚአብሔርን የሚያስከብሩትን መልካም ነገሮች ስናደርግና ስናስብ፥ ሰይጣን እኛን ለማጥቃትና ለማሽነፍ ይቸገራል። የሰይጣን ፍላጻዎች ወደ ሕይወታችን ሊገቡና ሊያሸንፉን የሚችሉት በኃጢአታችን ምክንያት ክፍተቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ ብቻ ነው።

ሐ. የሰላም ወንጌል፡፡ አንድ ወታደር ትክክለኛውን ጫማ ሳያደርግ በድንጋይ እግሩ እየተጎዳ ለመዋጋት መቸገሩ የማይቀር ነው። ትክክለኛውን ዓይነት ጫማ ካደረገ ግን ደኅንነቱ ተጠብቆለት በብቃት ሊዋጋ ይችላል። የሮም ወታደሮች በጭቃና በአቧራ ውስጥ አዳልጧቸው እንዳይወድቁ ብዙውን ጊዜ በጫማቸው ሶል ላይ እንደ ሚስማር ያሉ ጉጠታማ ነገሮች ይሠሩ ነበር። ለእኛ ግን መጫሚያችን ወንጌሉ ነው። ወንጌሉን አውቀን ለሌሎች በምናካፍልበት ጊዜ ከሰይጣን ጥቃቶች ልናመልጥ እንችላለን። ነገር ግን እምነቱን በንቃት የማያካፍል ዝምተኛ ክርስቲያን ብዙውን ጊዜ ለሰይጣን ጥቃቶች ይጋለጣል።

መ. የእምነት ጋሻ፡፡ ጥንታውያን ወታደሮች ሁለት ዓይነት ጋሻዎችን ይጠቀሙ ነበር። እግረኛ ጦር በተጋጋለ ጦርነት ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ የሚጠቀምበት አነስተኛ ጋሻ ነበር። በተጨማሪም፥ ከተሞችን በሚወሩበት ጊዜ የከተማይቱ ዜጎች ከሚወረውሩባቸው ፍላጻዎች ራሳቸውን ለመከላከል መላ አካላቸውን የሚሸፍኑበት ትልቅ ጋሻም ነበር። ጳውሎስ የእምነት ጋሻ የሚለውን ቃል የተጠቀመው ትልቁን ጋሻ ለማመልከት ነው። ብዙውን ጊዜ ሰይጣን የሚወረውራቸው ፍላጻዎች ስለ እግዚአብሔር፥ ስለ ደኅንነታችን፥ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር፥ ወዘተ… እንድንጠራጠር የሚያደርጉ ናቸው። እነዚህን ጥርጣሬዎች የምናሸንፈው በእምነት ነው። የዕብራውያን መልእክት፥ እምነት ያልታዩትን ነገሮች በእርግጠኝነት መረዳት እንደሆነ ያስረዳል (ዕብ. 11፡1)። ስለሆነም፥ ሰይጣን የጥርጣሬን ፍላጻ ወይም የኃጢአትን ፈተና ወደ ሕይወታችን በሚልክበት ጊዜ ጥርጣሬን አስወግደን በእርግጠኝነት በመሞላት በእግዚአብሔር፥ በመልካምነቱ፥ በፍጹም መንገዱና በማዳኑ ማመን አለብን። ይህ ትልቅ ጋሻ ጎን ለጎን የሚቆሙ ወታደሮች፥ ፍላጻዎችን የሚከላከል ግድግዳ ለመፍጠር እንዲችሉ የሚያያይዟቸው መንጠቆዎች ያሉት መሆኑ አስገራሚ ነው። ይህም እምነታችንን ለመጠበቅ ከሁሉም የሚሻለው መንገድ ከሚያውቁን፥ ከሚጸልዩልንና ሰይጣን በሚያጠቃን ጊዜ በእምነታችን እንድንጸና ከሚያግዙን የክርስቶስ አካላት ጋር መተሳሰር መሆኑን ያስረዳል። የሰይጣንን ጥቃት ልናሸንፍ የምንችለው በጠንካራ እምነት በመጽናት ነው። ጠንካራ እምነት እንዲኖረን ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር የቅርብ ግንኙነት ሊኖረንና ልንተማመንበት ይገባል። በተጨማሪም፥ በእምነታችን እንድንጸና ከሚረዱን አማኞች ጋር የቅርብ ኅብረት ልንመሠርት ይገባል።

ሠ. የመዳን ቁር። ውጊያው የሚካሄደው በሰይፍ ስለነበርና ጠላትን ለመግደል ከሁሉም የሚሻለው ጭንቅላቱን በሰይፍ መውጋት ስላነበር፥ የሮም ወታደሮች በራሳቸው ላይ ቁር ይደፉ ነበር። ይህ የወታደሩን ጭንቅላት ለመጠበቅ ይረዳ ነበር። እኛም ክርስቲያኖች አእምሯችንን መጠበቅ አለብን። የሚጠብቀን ደግሞ ድነት (ደኅንነት) ነው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ «ድነት (ደኅንነት)» የሚለው ቃል በሁለት መንገዶች ይታያል። በመጀመሪያ፥ በክርስቶስ የሚያምን ክርስቲያን ሁሉ ድነትን ተቀብሏል። ሰይጣን ይህንን ድነት (ደኅንነት) ማግኘታችንን እንድንጠራጠር ይሞክራል። ነገር ግን እግዚአብሔር በቃሉ ውስጥ በሰጠው የተስፋ ቃል ምክንያት ክርስቲያኖች መዳናቸውን ያውቃሉ። ሁለተኛው ዓይነት ድነት (ደኅንነት) በየዕለቱ በድል ነሺነትና ክርስቶስን በመምሰል መመላለሳችንን ያመለክታል። ለእግዚአብሔር እየታዘዝን ስንመላለስ፥ በባሕሪያችንና በድነት (ደኅንነት) ዋስትናችን በማደግ ክርስቶስን እንመስላለን። ይህም ሰይጣን የአስተሳሰባችንና የተግባራችን ምንጭ በሆነው አእምሯችን ላይ የሚሰነዝረውን ጥቃት ይወስነዋል።

ረ. የመንፈስ ሰይፍ፡ የጥንት ወታደሮች ሁለት ዓይነት ሰይፎችን ይጠቀሙ ነበር። አንደኛው ጠላትን ለማጥቃት በሁለት እጆቻቸው የሚሰነዝሩት ነበር። በዚህ ስፍራ ጳውሎስ በሁለቱም በኩል ስለታም ስለሆነው አጠር ያለ ሰይፍ ይናገራል። ጳውሎስ የማጥቂያ መሣሪያችን መንፈስ ቅዱስ ሰይጣንን ለማሸነፍ የሚጠቀምበት መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን አስረድቷል። ሰይጣን ክርስቶስን በፈተነውና በተዋጋው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን በመጥቀስ ምላሽ ሰጥቷል። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ጠላትን ለማሸነፍ እግዚአብሔር የሚሰጠንና መንፈስ ቅዱስ ድልን ለመንሣት የሚጠቀምበት መሣሪያ የእግዚአብሔር ቃል ነው። አሁንም ሰይጣንን ለማሸነፍ መጽሐፍ ቅዱስን ማወቅ ጠቃሚ መሆኑን እንመለከታለን።

ነገር ግን ውጊያውን በአጥጋቢ ሁኔታ ለማካሄድ ሌላም አንድ አስፈላጊ ነገር አለ። ወታደሩ ከጦር አዛዥ ጋር የቀረበ ግንኙነት ሊኖረው ይገባል። ግንኙነት ከሌለ ወታደሩ ወደ ግራ፥ ወደ ቀኝ መዞር ወይም ባለበት መጠበቅ እንዳለበት አያውቅም። ልንዋጋ የሚገባንና ሰይጣን በእኛ ላይ የሚሰነዝረውን ጥቃት በማሸነፍ የመንግሥቱን ግዛት ልንወስድ የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ አዛዣችን ከሆነው ከክርስቶስ ጋር የቅርብ ግንኙነት ሊኖረን እንደሚገባ አስረድቷል። ይህንን የምናደርገው በጸሎት ነው። ስለሆነም፥ ጳውሎስ የኤፌሶን ክርስቲያኖች በማያቋርጥ ጸሎት መንፈሳዊ ሕይወታቸውን እንዲያረሰርሱ ያሳስባቸዋል። እንደ ግለሰቦችና የቤተ ክርስቲያን አካል ለራሳቸውና ለእርስ በርሳቸው በሚጸልዩበት ጊዜ ድል ነሺዎች ይሆናሉ። ለጳውሎስ በሚጸልዩበት ጊዜ ደግሞ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን በመጠቀም ጳውሎስ ሰዎችን ከሰይጣን መንግሥት እየነጠቀ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲያመጣ ያደርጋል። እጅግ ውጤታማዎች ጸሎቶች ብዙውን ጊዜ ለእርስ በርሳችን የምናቀርባቸው የራስ ወዳድነት ጸሎቶች (ለምሳሌ፥ የፈውስ፥ የሥራ፥ ወዘተ) ሳይሆኑ፥ ቀደም ሲል ጳውሎስ በኤፌሶን ውስጥ የጸለያቸው ዓይነት ናቸው። እነዚህ ስለ እግዚአብሔር ፍቅርና ጥልቅ የእውነት ግንዛቤ ያላቸው ጸሎቶች ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰይጣን አንተን ያጠቃበትን የግል ሁኔታ ግለጽ። ጥቃቱ (ፍላጻው) ምን ነበር? እነዚህ የጦር መሣሪያዎች ሰይጣንን ለማሸነፍ እንዴት ይረዱሃል? ከእነዚህ መሣሪያዎች የአንዱ መጉደል ሽንፈትን የሚያስከትለው እንዴት ነው? ለ) ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንህን የሚያጠቃበትንና የሚያሸንፍበትን ሁኔታ ግለጽ። ከእነዚህ የጥበቃ መሣሪያዎች የጎደሉት የትኞቹ ናቸው? በውጊያው የበኩልህን እገዛ ለማድረግ ምን ልትሠራ ትችላለህ? ሐ) ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ ውጊያ ያቀረበው ገለጻ ብዙውን ጊዜ ከምንረዳውና ተግባራዊ ከምናደርገው እንዴት ይለያል?

የማጠቃለያ ሰላምታ (ኤፌ. 6፡21-24)

ጳውሎስ ቲኪቆስን ከኤፌሶን ሰዎች ጋር ያስተዋውቀዋል። ምናልባትም ይህን መልእክት ከሮም ወደ ኤፌሶን ያመጣውና ወደ ሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት ያደረሰው ቲኪቆስ ሳይሆን አይቀርም። ቲኪቆስ ለቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን (ቆላ. 4፡7) እና ምናልባትም ለፊልሞናም የጳውሎስን መልእክቶች አድርሷል። ጳውሎስ የኤፌሶን አማኞች የእግዚአብሔር ጸጋ፥ ሰላምና ፍቅር እንዲበዛላቸው በመጸለይ መልእክቱን ደምድሟል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

እግዚአብሔር የቤተሰብ አባላት እንዴት እንደሚዛመዱ ያብራራል (ኤፌ. 5፡21-6፡9)።

የውይይት ጥያቄ፡– ኤፌ. 5፡21-6፡9 አንብብ። ሀ) በዚህ ክፍል ስለ ቤተሰብና የሥራ ቦታ ግንኙነቶች የቀረቡት ጠቃሚ ትምህርቶች ምን ምንድን ናቸው? ለ) እግዚአብሔር ቤተሰቦች እርሱን በሚያስከብር መንገድ እንዲኖሩ የሚፈልገው እንዴት ነው? ሐ) በኢትዮጵያ በቅርበት የሚፋቀሩና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኙ ቤተሰቦች እንዳይኖሩ ችግር የሚፈጥሩት ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? መ) የቤተ ክርስቲያንህ መሪዎች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ቤተሰባዊ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ምን እያደረጉ ናቸው?

ማኅበረሰብ የተለያዩ የሰው ቡድኖች የሚካተቱበት ተቋም ነው። ትንሹ ቡድን ግለሰቦችን የያዘ ሲሆን፥ የሚቀጥለው ደረጃ ደግሞ ቤተሰብ ነው። ከዚያም ጎሳና አገር ይከተላሉ። እግዚአብሔርን የምታስከብር ጠንካራ አገር ለመገንባት ከታች የሚገኙት ደረጃዎች መጠናከር አለባቸው። ይህም ግለሰቦች እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ መኖር እንዳለባቸው ያሳያል። ጳውሎስ ግለሰቦች ለወንጌሉ እንደሚገባ ስለሚኖሩበት ሁኔታ እያብራራ ነበር። አሁን ጳውሎስ ወደ ቀጣዩ ደረጃ በመሸጋገር ስለ ጠንካራ መንፈሳዊ ቤተሰቦች ይናገራል። ግለሰቦችና ቤተሰቦች እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ በሚኖሩበት ጊዜ በማኅበረሰቡና በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ጳውሎስ በአያሌ የተለያዩ የቤተሰብ ግንኙነቶችና በሚዛመዱባቸው መርሆች ላይ አጽንኦት አድርጓል።

ሀ. የሁሉም መንፈሳዊ ግንኙነቶች መሠረታዊ መርሆ፡- «ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ።» ወንዶች ሚስቶቻቸው እንዲገዙላቸው ሲያዙ መስማቱ የተለመደ ነገር ነው። ነገር ግን ጳውሎስ ባሎችና ሚስቶች እንዴት መዛመድ እንደሚገባቸው ከመናገሩ በፊት፥ ሁሉም ክርስቲያኖች ለእያንዳንዳቸው እንዲገዙ መክሯል። ጳውሎስ ይህን ሲል እርስ በርሳችን በምናደርገው ግንኙነት ከራሳችን መንገድ ይልቅ ሌሎችን እንድናከብርና የእነርሱን ጥቅም እንድንሻ ማሳሰቡ ነው። ሰዎች ለእኛ ጥሩዎች ባይሆኑስ? አንድ ሰው ቢነዳንስ፣ ለሰዎች የምንገዛላቸው መገዛት የሚገባቸው በመሆናቸው ሳይሆን ክርስቶስን ለመታዘዝ ስንል ነው። የሚወደንን ክርስቶስን ለማክበርና ለመታዘዝ ስንል የራሳችንን ፈቃድ ትተን ሌሎች የራሳቸውን መንገድ እንዲከተሉ እንፈቅድላቸዋለን። የሚገርመው ሌሎች ይህንን ወይም ያንን እንዲያደርጉ መፈለጋችንን ስንተው ብዙውን ጊዜ የምንመርጠውን እንድናደርግ ይፈቅዱልናል። ነገር ግን በፍላጎታችን ላይ በምናተኩርበት ጊዜ ከፍላጎታቸው ላለመመለስ ይጥራሉ።

ለ. ሚስቶች ለባሎቻቸው መገዛት አለባቸው። ብዙውን ጊዜ ወንዶች ይህን አሳብ አላግባብ ሲጠቀሙ፥ ሴቶች ደግሞ ይቃወሙታል። ብዙውን ጊዜ ሚስቶች፥ «ለባለቤቴ ለምን መገዛት ያስፈልገኛል?» ይላሉ። ባሎች ደግሞ፥ «ከአለቅነቴ ሥር ልትታዘዝ ይገባል» ይላሉ። ነገር ግን ጳውሎስ ስለ መገዛት የሚናገረው ብዙውን ጊዜ እኛ ከምናስበው በተለየ መንገድ ነው። ጳውሎስ መገዛት እግዚአብሔር በፍጥረት ውስጥ ባስቀመጠው ሥርዓት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያስረዳል። መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበት ጊዜ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ክርስቶስ ወደ ምድር ለላከው ለእግዚአብሔር አብ እንደ ተገዛ እንመለከታለን። ይህ መገዛት ግን በፍቅር ላይ የተመሠረተ እንጂ ጭቆናን የሚያስከትል አይደለም። ክርስቶስ ከቤተ ክርስቲያን የሚጠብቀውም ይህንኑ ዓይነት መገዛት ነው።

ከእነዚህ አሳቦች ስለ መገዛት ሁለት ጠቃሚ እውነቶችን እንማራለን። በመጀመሪያ፥ መገዛት ለሚገዙለት ሰው የበታች መሆንን አያሳይም። አብና ወልድ እኩል አምላክ ናቸው። በሥልጣን ግን ወልድ ለአብ ይገዛል። ወንዶችና ሴቶች በእግዚአብሔር ዓይን ፊት እኩል ናቸው። ለዚህ ነው ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወንድ የለም ሴት የለም ያለው (ገላ. 3፡28)። ነገር ግን እግዚአብሔር በመሠረተው ሥርዓት ወንዶች ከሴቶች በላይ ተሰይመዋል። ሁለተኛ፥ የተጠበቀው መገዛት አብ ከወልድ የጠየቀውና ወልድም ከቤተ ክርስቲያን የጠየቀው ዓይነት ነው። አብም ሆነ ወልድ ከሥራቸው ያሉትን ለመጨቆን ወይም ለመግደል ኃይላቸውን አይጠቀሙም። ነገር ግን ከሥራቸው ያሉትን ይወዳሉ ያከብራሉ። በመሠረቱ በዚህ ክፍል ውስጥ የቀረበው መገዛት የአሳብ ልዩነት በሚከሰትበት ጊዜ ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ነው። ከክርስቶስ ጋር በነበረው ግንኙነት ውስጥ እንደታየው እግዚአብሔር የሚጠብቀው በጉዳዮች ላይ በጋራ መወያየት፥ ማን ምን እንደሚሠራ መወሰንን፥ የሁለቱንም ወገኖችን ፍላጎት መጣጣምን ነው። ነገር ግን እኛ ሰዎች ስለሆንን በአሳብ የምንለያይባቸው ጊዜያት አሉ። በእነዚያ ጊዜያት ሚስት ባትስማማ እንኳ ለባሏ ውሳኔ መገዛት ይጠበቅባት ነበር።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለአንድ ሰው ሥልጣን በሚሰጥበት ጊዜ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል ባሎች ማስታወስ ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ፥ ንጉሥ ሥልጣን ቢኖረውም ከሥሩ ላሉት ሰዎች በጎነት የመሥራት ኃላፊነት አለበት። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ባል በቤተሰቡ ላይ ሥልጣን አለው። ይህ ግን በቀዳሚነት ፍላጎታቸውን የማሟላት ኃላፊነት እንዳለበት ያሳያል።

የውይይት ጥያቄ፡- መንፈሳዊ የቤተሰብ አገዛዝንና ሥልጣንን ብዙ ክርስቲያኖች ከሚይዙት ግንዛቤ ጋር አነጻጽር። ሚስት መንፈሳዊ መገዛትን፥ እንዴት ልታሳይ እንደሚገባ ምሳሌዎችን ስጥ። አምላካዊ ሥልጣን እንዴት በባል በኩል ሊታይ እንደሚችል በምሳሌ አስረዳ።

ሐ. ባል ሚስቱን እንዲያፈቅር ታዟል። ፍቅር የሚለው ቃል ራስን ለሌሎች ጥቅም አሳልፎ መስጠትን ያመለክታል። ስለሆነም፥ ባል ሊጠይቅ የሚገባው ዐቢይ ጥያቄ፡- «ሚስቴን ለመርዳት ምን ላደርግ እችላላሁ? ለቤት ሥራዋና ለልጆች እንክብካቤ ምን ባደርግላት ይበጃል? ሌሎች እንደ ትምህርት የመሳሰሉ የምትፈልጋቸው ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?» የሚል መሆን አለበት። ጳውሎስ ይህን አሳብ ለማብራራት እንደገና የክርስቶስንና የቤተ ክርስቲያንን ግንኙነት በምሳሌነት ጠቅሷል። ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ ወይም ጌታ ስለሆነ፥ ቤተ ክርስቲያን ልትገዛለት ይገባል። ክርስቶስ ግን ከፍቅሩ የተነሣ ለቤተ ክርስቲያን ለመሞት ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል። ባልም እንዲሁ ራሱን በፍቅር ለሚስቱ እሳልፎ ሊሰጥ ይገባል። ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ለባል ጠቃሚ መሆኑን ለማሳየት ሌላም ምሳሌ ሰጥቷል። ባልና ሚስት አንድ አካል ስለሆኑ፥ ባል ሚስቱን በሚበድልበት ጊዜ ሁሉ ራሱን ይጎዳል። በፍቅር በሚረዳት ጊዜ ደግሞ ራሱን ይረዳል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከሚስት መገዛትና ከባል የክርስቶስን የሚመስል የመሥዋዕትነት ፍቅር ከማሳየት የትኛው የሚከብድ ይመስልሃል? መልስህን አብራራ። ለ) ባል ለሚስቱ በተግባራዊ መንገድ ፍቅሩን ሊያሳይ የሚችልባቸውን አንዳንድ ምሳሌዎች ዘርዝር። ሐ) አብዛኞቹ ክርስቲያን ባሎች ከሚስቶቻቸው ጋር በዚህ መንገድ የሚዛመዱ ይመስልሃል? ይህ በቤተሰብ ውስጥ የሚረጋገጠው እንዴት ነው?

መ. ልጆች ለወላጆቻቸው መታዘዝ አለባቸው። በዚህ በምንኖርበት ዘመን ልጆች ለወላጆቻቸው በአጥጋቢ ሁኔታ አይታዘዙም። ወላጆቻቸው ብዙም የተማሩ ባለመሆናቸው ይንቋቸዋል። ይህ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው መንፈሳዊ ግንኙነት ይቃረናል። ጳውሎስ ከአሥርቱ ትእዛዛት አንዱን ለዚህ ትምህርት መሠረት አድርጎ ይጠቅሰዋል። እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ወላጆቻቸውን ከታዘዙ መልካም ሕይወት እንደሚኖራቸው ገልጾላቸው ነበር። ዛሬም ይህ እውነት ነው። ልጆች ከወላጆቻቸው የበለጠ ሊማሩና ገቢ ሊያመጡ ቢችሉም፥ ወላጆቻቸውን ከማክበር ሊቆጠቡ አይገባም። ብዙውን ጊዜ በሰው ሕይወት ውስጥ ከፍተኛውን ጠቀሜታ የሚያስገኙት፥ ከወላጆች የተገኙ መርሆችና እውነቶች ናቸው። በወላጆች ላይ ማመፅ በሥልጣናት ሁሉ ላይ ወደ ማመፅ ስለሚመራ ልጆች መታዘዝንና መገዛትን ካልተማሩ የተሳካ ሕይወት ሊኖራቸው አይችልም።

ሠ. አባቶች ልጆቻቸውን ማሠልጠንና ማስተማር እንጂ ማስቆጣት የለባቸውም። አባት የቤቱ ራስ ስለሆነ ልጆች አባታቸውንና እናታቸውን ማክበር አለባቸው። ይህ ሥልጣን ግን ኃላፊነትን የሚያስከትል ነው። እግዚአብሔር ለቤተሰብ ልጆችን የሰጠው ለምንድን ነው? የቤተሰቡን ስም ከትውልድ ትውልድ ለማስተላለፍ ብቻ ነው? አይደለም። ነገር ግን ወላጆች ለልጆቻቸው ሥጋዊና መንፈሳዊ ዕድገት የግል ኃላፊነትን እንዲወስዱ ነው። ጳውሎስ ይህ በቀዳሚነት የአባት ኃላፊነት እንደሆነ አስረድቷል። ብዙውን ጊዜ ግን ወላጆች በተለይም አባቶች ለዚህ ኃላፊነት አጽንኦት አይሰጡም። ሥልጠናው በሰንበት ትምህርት ቤት ወይም በመንግሥት ትምህርት ቤት እንደሚካሄድ ያስባሉ። እግዚአብሔር ግን ለልጆቻቸው ሥልጠና ወላጆችን በተለይም አባቶችን ተጠያቂ ያደርጋቸዋል። ሳንይቲስቶች ወላጆች በመጀመሪያዎቹ 5 ወይም 6 ዓመታት ውስጥ በልጆቻቸው ላይ ከሁሉም የላቀ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ያስተምራሉ። ልጆች እሴቶቻቸውን የሚማሩት በእነዚህ የሕፃንነት ጊዜያት ነው። እግዚአብሔርን መውደድ ወይም መጥላት የሚማሩትም በዚሁ ጊዜ ነው። በዓለም ሁሉ ከ80% የሚበልጠ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ላይ እምነታቸውን የጣሉት ከ15 ዓመታቸው በፊት ነው። ስለሆነም፥ ለልጆቻችን በጌታ መንገድ ስለመመላለስ የምናስተምረው እውነት በልጁ ማመንና ወደ መንግሥተ ሰማይ መሄድ ላይ ዐቢይ ሚና ይጫወታል። (ማስታወሻ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆች ክርስቲያኖች መሆናቸው ልጆችን ክርስቲያን እንደሚያደርጋቸው አያስተምርም። እያንዳንዱ ግለሰብ ክርስቶስን ለመከተል የመምረጥ ኃላፊነት አለው። ወላጆች ልጆቻቸው በክርስቶስ እንዲያምኑ ሊጸልዩና ከሦስት ወይም አራት ዓመት ዕድሜያቸው ጀምሮ ሊያስተምሯቸው ይገባል።)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች ወላጆች ያሏቸው አብዛኞቹ የክርስቲያን ወላጆች ልጆች ወላጆቻቸውን የሚታዘዙ ይመስልሃል? ለ) ልጆቻቸውን በጥንቃቄ ሲያስተምሩና ሲያሠለጥኑ ያየሃቸውን ወላጆች ምሳሌዎች ዘርዝር። ሐ) ጥቂት ወላጆች ብቻ ልጆቻቸውን በጥንቃቄ የሚያስተምሩት ለምን ይመስልሃል? መ) ወላጆቹን የሚታዘዝ ሰው ምን በረከት ሲያገኝ ተመልክተሃል? ሠ) ወላጆቹን የማይታዘዝ ሰው ምን ችግሮች ሲገጥሙት አይተሃል?

ረ. ባሮች ጌቶቻቸውን መታዘዝ፥ ማክበርና መፍራት ይኖርባቸዋል። በጥንቱ ዓለም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ባሮች ነበሩ። ከእነዚህ ባሪያዎች አብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች ሆነዋል። አማኝ ባሮች ለገዟቸው፥ እንደ ዕቃ ለሚቆጥሯቸውና ለሚበድሏቸው ሰዎች ምን ዓይነት ምላሽ ሊሰጡ ይገባል ? ማመፅ ነበረባቸው? በጌቶቻቸው ኑሮ ላይ ችግር መፍጠር ነበረባቸው? ምንም እንኳ ጳውሎስ ከተቻለ ባሮች ነጻነታቸውን ሊቀዳጁ እንደሚገባ ቢገልጽም (1ኛ ቆሮ. 7፡20-22)፥ ፊት ለፊት ባርነትን ሲቃወም አንመለከትም። ጳውሎስ ባሮች እግዚአብሔር የሰጣቸውን ደረጃ ላለመቀበል እንዳይፍጨረጨሩና ምድራዊ ጌቶቻቸውን በሚገባ እንዲያገለግሉ መክሯቸዋል። ይህን የሚያደርጉት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ለጌቶቻቸው ሲገዙ እግዚአብሔርን ማገልገላቸው ስለሆነ ነው። ስለሆነም፥ ለጌቶቻቸው የሚሰጡት አገልግሎት ለክርስቶስ እንደሆነው ሁሉ በትጋት የሚካሄድ ሊሆን ይገባል። እግዚአብሔር ለምድራዊ ጌቶቻቸው ለሚያሳዩት አመለካከትና ተግባር በኃላፊነት ይጠይቃቸዋል። በአሁኑ ዘመን የድሮ ትውልዶች ዓይነት ባርነት የለም። ነገር ግን የዘመናችን የሥራ ግንኙነት ቀጣሪና ተቀጣሪ  በመባል ይታወቃል፡፡ አብዛኞቻችን የመንግሥት፥ የንግድ ኅብረተሰብ፥ የቤተ ክርስቲያን፥ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት፥ ወዘተ… ተቀጣሪዎች ነን። ለአሠሪዎቻችን ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? እንዳያባርሩን ብቻ ነው መሥራት ያለብን? ጳውሎስ የምንችለውን ያህል ከፍተኛ ተግባር ማከናወን እንዳለብን ይመክራል። በጊዜ ከሥራ ገበታችን ላይ ልንገኝ፥ በትጋት ልንሠራ፥ ታማኝ ልንሆን፥ በሰዓቱ ከሥራ ገበታችን ልንወጣ፥ ወዘተ… ይገባል። ክርስቶስ አሠሪያችን ቢሆን ምን እናደርግ ነበር ብለን በማሰብ ተግባራችንን ማከናወን አለብን። ለወንጌሉ እንደሚገባ መመላለስ ማለት ለአንድ አሠሪ በምንሠራበት ጊዜ በተቻለ ትጋት መሥራት አለብን ማለት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ለአሠሪዎቻቸው እንዲህ ዓይነት አመለካካት አላቸው? ካልሆነ፥ ለምን? ለ) ክርስቲያን ሠራተኞች በአመለካከታቸው፣ በጊዜ አጠቃቀማቸው፥ በትጋታቸው፥ ወዘተ. . አሠሪዎቻቸውን እንዴት እንደሚያታልሉ ግለጽ። ክርስቶስ በዚህ ዓይነቱ አመለካከት የሚደሰት ይመስልሃል? ሐ) አሠሪህ ማን ነው? ከእርሱ ጋር ያለህን ግንኙነትና ሥራህን መርምር። ክርስቶስ በዚህ መንገድ ስትሠራ ሲያይህ ይደሰታል ወይስ አንተው በዚህ ሥራህ የምታፍርበት ይመስልሃል? ለአሠሪህ በምታበረክተው አገልግሎት ታከብረው ዘንድ ክርስቶስ ምን ዓይነት ለውጦችን እንድታደርግ የሚፈልግ ይመስልሃል? መ) ወደ ቤተ ክርስቲያን አምልኮ ለመሄድ ስትል ሰዓቱ ሳይደርስ ከሥራ ቦታህ በመነሣትህ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝብህ ይመስልሃል? ለምን?

ይህ ትምህርት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሆነን ለምናገለግልም ይሁን ተቀጥረን ለምንሠራ ሰዎች ጠንካራ ማስጠንቀቂያ የሚሰጠን ነው። ብዙውን ጊዜ ሌላ ሥራ ያላቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ስብሰባ ለመሄድ ሲሉ ከሥራ ገበታቸው ላይ ቀደም ብለው ይነሣሉ ወይም አርፍደው ይደርሳሉ። ይህ በእግዚአብሔር ፊት ስሕተት ነው። የአንድ ሰው ወይም ድርጅት ሠራተኛ ለመሆን በተስማማህ ጊዜ፥ ጊዜህንና ሥራህን የመጠቀም መብት ሰጥተኸዋል። አሁን በሥራ ሰዓት ጉልበትህንና ጊዜህን ለእነርሱ መስጠት አለብህ። ስለሆነም፥ አርፍደህ ስትመጣ፥ ቀደም ብለህ ስትሄድ፥ የስንፍና ተግባር ስታከናውን ወይም ለቤተ ክርስቲያን ስብሰባ ብለህ ከሰዓቱ በፊት ስትሄድ እየሰረቅሃቸው ነው። እግዚአብሔር ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ የአሠሪህን ጊዜ መስረቅህን እንደ ጥሩ ማመኻኛ አይቀበለውም። «መንፈሳዊ» ሥራ ለመሥራት ከሰዎች «መስረቅህን» አይደግፍም።

ሰ. ጌቶች ባሮቻቸውን በፍትሐዊ መንገድ ማስተዳደር ይኖርባቸዋል። አንዳንድ ሀብታም ባሪያ እስተዳዳሪዎችም በክርስቶስ አምነው ነበር። ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች ባሮቻቸውን ነፃ እንዲያወጡ ባይነግራቸውም፥ በአግባቡ እንዲያስተዳድሯቸው አስጠንቅቋቸዋል። ጳውሎስ ባሪያ ፈንጋይነትን በቀጥታ ባይቃወምም ለክርስቲያኖች ይህንን ተቋም አጣጥሎባቸዋል። ጳውሎስ በእግዚአብሔር ፊት ሰዎች ሁሉ እኩል መሆናቸውን አስተምሯል። እግዚአብሔር ባሮችንና ነፃ ሰዎችን እኩል አድርጎ ይመለከታቸዋል። ሁለቱም በእርሱ አምሳል የተፈጠሩ ፍጥረቶች ናቸው። በክርስቶስ ካመኑ በኋላም ሁለቱም የእርሱ ልጆች ናቸው። ባሪያዎችም ለሥራ አፈጻጸማቸው፥ ጌቶች ደግሞ ባሮቻቸውን ላስተዳደሩበት ሁኔታ በእግዚአብሔር ይጠየቃሉ።

ክርስቲያን አሠሪዎች፥ «ሠራተኞቼን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እያስተዳደርሁ ነኝ? ሊያስተዳድራቸው የሚችል በቂ ደመወዝ እከፍላቸዋለሁ? ወይስ ትርፉን ሁሉ ለራሴ ለመሰብሰብ እየሞከርኩ ነኝ? አፍቃሪና ቸር ነኝ ወይስ ጨካኝ?» ብለው ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው። እግዚአብሔር ከድርጅትህ ውስጥ የሚሠሩትን ሰዎች ስለምታስተዳድርበት ሁኔታ በኃላፊነት እንደሚጠይቅህ አስታውስ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

እግዚአብሔር ልጆቹ በቅድስና በመመላለስ እርሱን እንዲመስሉ ይፈልጋል (ኤፌ. 4፡17-5፡20)።

የተቀደሰ ሕይወት ሳይኖሩ ለወንጌሉ እንደሚገባ መመላለስ አይቻልም። መቀደስ ማለት መለየት ማለት ነው። ስለሆነም፥ እኛ ከዓለም አሠራር ወይም አስተሳሰብ የተለየን ነን። ከኃጢአት የተለየን ነን። እንዲሁም ለእግዚአብሔር የተለየን ነን። ይህ ማለት በምናደርገው ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ማክበር አለብን። ጳውሎስ በዚህ የኤፌሶን ክፍል በቅድስና ላይ በማተኮር የሚከተሉትን እውነቶች ገልጾአል።

ሀ. መቀደስ ማለት ከዓለማውያን በተለየ መንገድ ማሰብ ነው። ቅድስና የሚጀምረው ከአስተሳሰባችን ነው። አእምሯችን የሕይወታችን፥ የባሕርያችንና የተግባራችን ምንጭ ነው። ያልታደሰ አእምሮ ዓለም የምታተኩርባቸውን ነገሮች በአስፈላጊነት ይገነዘባል። ስለሆነም፥ ዓለማዊ አእምሮ ስለ ወሲባዊ እርኩሰት፥ ጎሰኝነት፥ በትምህርት መኩራራት፥ ራስ ወዳድነትና የመሳሰሉት ያስባል። እግዚአብሔርን የሚያስደስት አእምሮ በቤተ ክርስቲያን በአንድነት ስለ መኖር፥ ስለ ምስክርነት፥ የተቸገሩትን ስለ መርዳትና ስለ ሌሎችም እግዚአብሔርን ደስ ስለሚያሰኙ ነገሮች ያስባል።

ለ. መቀደስ ማለት እግዚአብሔርን የማያስከብሩትን ነገሮች ለማስወገድና የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን የሚያንጸባርቁትን ነገሮች ለመልበስ መቁረጥ ነው። ጳውሎስ ይህንን ምርጫ ከልብስ ጋር ያነጻጽረዋል። የአንድ ሰው ልብስ በሚያድፍበት ጊዜ ያወልቅና ንጹሑን ይለብሳል። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ተግባራችን፥ አስተሳሰባችንና አመለካከታችን በኃጢአት በሚጎድፍበት ጊዜ አውጥተን በመጣል የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን በሚያሳዩ አዳዲስና ንጹሕ ባሕርያት እንለውጣቸዋለን። እነዚህ ልንለብሳቸው የሚገቡን ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?

 1. ውሸትንና በሌሎች የመጠቀምን ሁኔታ አስወግደን እውነትን እንናገራለን። እውነተኛ ተግባራትንም እናከናውናለን።
 2. ከሰዎች ጋር መልካም ግንኙነቶች ይኖሩናል። በሰዎች ላይ በምንቆጣበት ጊዜ በፍጥነት ቁጣችንን አስወግደን በኑዛዜና ይቅርታን በመጠየቅ ነገሮችን እናስተካክላለን።
 3. ከመስረቅና ከትጉሕ ሠራተኝነት ከመሸሽ ይልቅ በታማኝነትና በትጋት እንሠራለን። (መስረቅ የተለያዩ መልኮች አሉት። ከሥራ ቦታ እስክሪብቶ እንሥተን ስንጠቀም፥ በሰዓት ከሥራ ገበታችን ላይ ሳንገኝ ስንቀር ወይም ሰዓቱ ሳይደርስ ስንሄድና ሙሉ ክፍያ ስንቀበል እንሰርቃለን።) ግን ለምን እንሠራለን? ሀብታም ለመሆን ነው? ጳውሎስ ለሌላቸው ሰዎች የምናካፍለው እንዲኖረን መሥራት አለብን ብሏል።
 4. ሌሎችን ሰዎች ማማትና ስለ ወሲባዊ ርኩሰቶች መነጋገር ትተን ሰዎችን ስለሚያንጹና ስለሚያከብሩ ነገሮች ብቻ እንነጋገራለን። ለራሱ ለግለሰቡ የማንናገረውን ነገር ለሌሎች ልንናገርበት አይገባም። ስለ ሌላ ሰው ምንም ባንናገር መልካም ነው። ያውም ለምናማው ሰው ልንናገር የማንችለውን። የምንናገረው ሰሚውን የማያንጽ ከሆነም አለመናገሩ ይመረጣል።
 5. ከመራርነት፥ ቁጣ፥ ጠብ ወይም ስድብ የራቁ መንፈሳዊ ባሕርያት ይኖሩናል። ቸሮችና ርኅሩኆች በመሆን የሚጎዱንን ይቅር እንላለን። የይቅርታ ምሳሌያችን በክርስቶስ በኩል ኃጢአታችንን እግዚአብሔር ይቅር ማለቱ ነው።
 6. ከወሲባዊ ኃጢአቶች ሁሉ እንርቃለን። መጽሐፍ ቅዱስ ከትዳር ጓደኛችን ጋር ብቻ ወሲብን እንድንፈጽም ያስተምረናል። ያላገቡ ሰዎች ከማግባታቸው በፊት ወሲብን መፈጸም የለባቸውም። ያገቡትም ከትዳር ጓደኞቻቸው ውጭ መሄድ የለባቸውም። እግዚአብሔር ከወሲብ ኃጢአት የማይመለሱትን ሰዎች እንደሚቀጣ ተናግሯል።

ሐ. እንቀደስ ዘንድ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ግንኙነት ሊኖረን ይገባል። ጳውሎስ ክርስቲያኖች እምነታቸውን የሚያንጸባርቅ የተቀደሰ ሕይወት መምራት እንዳለባቸው ካስተማረ በኋላ፥ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ባላቸው ግንኙነት ሊያደርጓቸው የሚገቧቸውን አያሌ ነገሮች ጠቅሷል። እግዚአብሔርን የሚያስከብር የተቀደሰ ሕይወት የምንኖርበትን ኃይል የሚሰጠን መንፈስ ቅዱስ ከሆነ፥ በቀረበ መንፈሳዊ መንገድ ከእርሱ ጋር መዛመዳችን እጅግ አስፈላጊ ነው። (እነዚህ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ስለሚኖረን ግንኙነት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከተሰጡን ጥቂት ትእዛዛት ሁለቱ ናቸው። ብዙውን ጊዜ አዲስ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ ስለሚፈጽመው ተግባር እንጂ ከእርሱ ጋር በአግባቡ ለመዛመድ ምን ማድረግ እንዳለብን አይናገርም።)

አንደኛ፥ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን መንፈስ ቅዱስ እንዳናሳዝን ይናገራል (ኤፌ. 4፡30)። መንፈስ ቅዱስን የምናሳዝነው እንዴት ነው? በቀዳሚነት መንፈስ ቅዱስን የምናሳዝነው ባልተናዘዝንባቸው ኃጢአቶች እንደሆነ ከዓውደ ንባቡ እንረዳለን። ጳውሎስ ከላይ የዘረዘራቸው ዓይነት የተሳሳቱ ተግባራትና አመለካከቶች በሕይወታችን ውስጥ በሚኖሩበት ጊዜ በውስጣችን የሚኖረውን መንፈስ ቅዱስ እናሳዝናለን። መንፈስ ቅዱስን ካሳዘንነው፤ ኃጢአትን የምናሸንፍበትንና የተቀደሰ ሕይወት ለመኖር የምንችልበትን ኃይል አይሰጠንም።

ሁለተኛ፥ ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ እንድንሞላ አዞናል (ኤፌ. 5፡18)። ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ እንዴት እንደምንሞላ ወይም በመንፈስ ቅዱስ መሞላት በሕይወታችን ምንን ሊያመጣ እንደሚችል አልተናገረም። ጳውሎስ በዚህ ስፍራ ስለምን ዓይነት መሞላት እንደሚናገር ለመረዳት ዓውደ ንባቡ ሳይረዳን አይቀርም። ጳውሎስ አጽንኦት የሰጠው እንደ ልሳን ወይም ተአምራት ባሉት አስደናቂ ነገሮች ላይ ሳይሆን፥ የተቀደሰ ሕይወት በመኖርና እግዚአብሔርን በማምለክ ላይ ነው። በቅድስና ስንመላለስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንኖራለን። እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ልንኖር የምንችለው መንፈስ ቅዱስ ከረዳን፥ ከሞላን፥ ብሎም የኃጢአትን ተፈጥሮ የምናሸንፍበትን ኃይል ከሰጠን ብቻ ነው። በመንፈስ ቅዱስ በምንሞላበት ጊዜ በቅድስና መመላለስ ብቻ ሳይሆን፥ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድም እናመልካለን። እነዚህ ሁለቱ በዚህ ስፍራ በሚያስገርም ሁኔታ ተያይዘዋል። የተቀደሰ ሕይወት እስካልኖርን ድረስ እግዚአብሔርን የሚያስደስት አምልኮ ልናካሂድ አንችልም። በመንፈስ ቅዱስ መሞላት አምልኳችንንም ሆነ አኗኗራችንን ያግዘዋል። አኗኗራችን ወይም አምልኳችን ከወንጌሉ ጋር ካልተጣጣመ፥ በልሳን ብንናገር ወይም ተአምራት ብንሠራም በመንፈስ ቅዱስ አልተሞላንም። ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት ምን ማድረግ እንዳለብን ያልተናገረው ምናልባትም በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት የሚያስፈልገው ብቸኛው ቅድመ-ሁኔታ ለእግዚአብሔር የተገዛና በቅድስና የተሞላ ሕይወት ስለሆነ ይሆናል። ለመንፈስ ቅዱስ ሙላት እንድንጸልይ እልተነገረንም። ነገር ግን ኃጢአታችንን ከተናዘዝን፥ ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር ከተገዛንና መንፈስ ቅዱስን ከታዘዝን፥ ይሞላናል፥ ይቆጣጠረናል፥ ኃጢአትን እንድናሸንፍና እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንድንኖር ኃይልን ይሰጠናል። ኃጢአትን በምንሠራበት ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ አልተሞላንም ማለት ነው። በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት ከተሰጡት ገለጻዎች አንዱ «በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ክርስቲያኑ በተግባርና በባሕርይ ክርስቶስን ይመስል ዘንድ በሕይወቱ ውስጥ ለሚሠራው ለመንፈስ ቅዱስ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥበት ልምምድ ነው» የሚል ነው።

ማስታወሻ፡— በአዲስ ኪዳን ውስጥ፥ ሦስት የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ዓይነቶች የሚታዩ ይመስላል። በመጀመሪያ፥ በመንፈስ ቅዱስ መሞላት መንፈሳዊ ብስለት ላለው ሰው የተሰጠ አገላለጽ ይመስላል። ለዚህም ምክንያቱ ግለሰቡ አብዛኛውን ጊዜ ለመንፈስ ቅዱስ በመታዘዝ መኖሩ ነው ( የሐዋ. 6፡3)። ምንም እንኳ ሁሉም ክርስቲያኖች በዚህ ዓይነት ሕይወት ባይኖሩም፥ እግዚአብሔር ከሁላችንም ይህንኑ ይጠብቃል። ጳውሎስ በኤፌሶን 5፡18 ስለ መንፈስ ቅዱስ ሙላት የተናገረው ከዚህ አንጻር ነው። ሁለተኛ፥ አዲስ ኪዳን አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ለአንድ ሰው የሚሰጠውን የተለየ የሕይወት ዘመን አገልግሎት ለማመልከት በመንፈስ ቅዱስ መሞላትን ይጠቅሳል። መጥምቁ ዮሐንስ ለነቢይነት አገልግሎቱ ከተወለደ ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ እንደ ተሞላ ተነግሮለታል (ሉቃስ 1፡15-17)። ጳውሎስ የአሕዛብ ሐዋርያ ይሆን ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ እንደ ተሞላ ተገልጾአል (የሐዋ. 9፡17)። ሦስተኛ፥ በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ማለት አንድ ሰው ድንገተኛ ሁኔታን ለመቋቋም እንዲችል መንፈስ ቅዱስ ሲያስታጥቀው ማለት ሊሆንም ይችላል። ተግባሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ይሄ ማስታጠቅ ይወሰዳል። በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት በአብዛኛው ያገለገለው በዚህ መልኩ ነው። ጴጥሮስ በሃይማኖት መሪዎች ፊት በቆመ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ነበር። እስጢፋኖስ ቀደም ሲል በመንፈስ ቅዱስ እንደተሞላ የተገለጸ ሲሆን፥ ሊሠዋ ሲልም እንደገና ተሞልቷል። ጳውሎስ በምትሐተኛው ላይ የተግሣጽ ቃል በተናገረ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ እንደ ተሞላ ተገልጾአል (የሐዋ. 4፡8፥ 31፤ 7፡55፤ 13፡9)።]

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ብዙ ክርስቲያኖች በቅድስና ለመኖር ከላይ ከተጠቀሱት ነገሮች የሚቸገሩት በየትኞቹ አካባቢ ነው? ለ) አንተስ? ሐ) መንፈስ ቅዱስ በሕይወትህ እርሱን የሚያሳዝን ነገር ካላ እንዲያሳይህ ጠይቀው። መንፈስ ቅዱስ ይቅር እንዲልህና በሕይወትህ የሚገኙትን መጥፎ ልማዶች፥ ጥሩ ያልሆኑ አስተሳሰቦችና ኃጢአቶች የምታሸንፍበትን ኃይል እንዲሰጥህ ጠይቅ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

በክርስቶስ አካል ያለ አንድነት (ኤፌ. 4፡1-16)

ጳውሎስ የኤፌሶን ክርስቲያኖች ለወንጌሉ እንደሚገባ ይመላለሱ ዘንድ ጠየቀ (ኤፌ. 4-6)።

ጳውሎስ የእግዚአብሔርን አስደናቂ ጸጋ፥ ለእኛ ያለውን ፍቅር፥ የማይገባን ሆነን ሳለ የሰጠንን የድነት (ደኅንነት) እና ያጎናጸፈንን ሰማያዊ ስጦታዎች በትክክል ከተረዳን፥ አኗኗራችንን ለመለወጥ እንደምንሻ ገልጾአል። ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር እንድንለወጥ ያደርገናል።

የኤፌሶን መልእክት የመጨረሻው ክፍል (ምዕ. 4-6) በክርስቶስ ላይ ያለን እምነት የሚያስከትላቸውን ነገሮች ያስረዳል። ጳውሎስ እንደሚለው፥ እነዚህ እግዚአብሔር ለሰጠን ታላቅ ድነት (ደኅንነት) እንደሚገባ እንድንመላለስ የሚረዱን ነገሮች ናቸው። በክርስቶስ ላይ ያለን እምነት አኗኗራችንን እንዴት ሊለውጥ እንደሚገባ ለማሳየት የሚያግዙ ብዙ የሕይወት ክፍሎች ቀርበዋል። ጳውሎስ ብዙዎቻችን ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ውስጥ ወሳኞች ናቸው ብለን በምናስባቸው አምልኮና ተአምራት ላይ ብዙም ትኩረት አለማድረጉ አስገራሚ ነው። ነገር ግን ጳውሎስ በሚያስቸግሩን ተግባራዊ የሕይወት ክፍሎች ላይ ያተኩራል። እምነታችን አኗኗራችንን እስካልለወጠ ድረስ ለወንጌሉ እንደሚገባ አልተመላለስንም ማለት ነው። እምነታችን ከሌሎች ክርስቲያኖች፥ ከዓለማውያን፥ ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎታችንና ከቤተሰቦቻችን ጋር በምናደርገው ግንኙነት ላይ ለውጥ ማምጣት አለበት። እምነታችንም የሰይጣንን ውጊያ ለማሸነፍ ኃይል ይሆነናል።

ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ሁሉ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በተከፋፈለችበት ዘመን ውስጥ እንኖራለን። በሁሉም የኢትዮጵያ ቤተ እምነቶች ማለት ይቻላል፥ ዐበይት ውስጣዊ አለመስማማቶች አሉ። እነዚህ አለመግባባቶች ከተለያዩ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አለመግባባት የመነጩ ናቸው። በተጨማሪም፥ ብዙ ቤተ እምነቶች ከሌሎች ቤተ እምነቶች ጋር በመጣላት ላይ ናቸው። በዚሁ መሠረት የተጋጋለ አምልኮ ስለምናካሂድና ብዙ ተአምራቶች ስለሚታዩ ከበፊቱ የበለጠ መንፈሳውያን ነን ብለን እናስባለን። ጳውሎስ እውነተኛው የመንፈሳዊነትና የመነቃቃት መፈተኛ አኗኗራችን እንደሆነ አስረድቷል። እምነታችንን እንዲያንጸባርቅ ለማድረግ ከሚያዳግቱን ነገሮች አንዱ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ነው። ጳውሎስ እርስ በርሳችን የምናደርገው ግንኙነት እግዚአብሔርን ወደሚያስከብሩ ግንኙነቶች የሚመራ ትክክለኛ አመለካከትና ግልጽ ግንዛቤ ሊኖረው እንደሚገባ አስረድቷል።

ሀ. ግንኙነቶች የሚጀምሩት በጋራ እምነታችን ውስጥ እውነት የሆነውን ነገር በመገንዘብ ነው። አማኞች ሁሉ በጋራ እምነታቸው በአንድነት መተሳሰር አለባቸው። ጳውሎስ እምነታችን እንደ «ሙጫ» ሊያያይዘን እንደሚገባ ለማሳየት «አንድ» የምትለውን ቃል ደጋግሟል። አማኞች ሁሉ በአንድ «አካል» ማለትም የክርስቶስ አካል የሆነች ቤተ ክርስቲያን እንዳለች ያምናሉ። በምድር ላይ ብዙ የተለያዩ ቤተ እምነቶች ሊኖሩን ቢችሉም፥ በሰማይና በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት በእውነተኛ አማኞች የተገነባች አንዲት አካል ብቻ አለች። በእያንዳንዱ ክርስቲያን ልብ ውስጥ የሚያድር አንድ መንፈስ ቅዱስ ብቻ አለ። በሙሉ ወንጌል የሚሠራውና በመካነ ኢየሱስ የሚሠራው መንፈስ ቅዱስ አንድ ነው። አንዳንዶች መንፈስ ቅዱስ እንዳላቸውና ሌሎች እንደሌላቸው ወደሚያስረዳው ትምህርት የሚመራው ሐሰተኛ እምነት ነው።

አንድ «ተስፋ» አለ። ይኸውም አንድ ቀን ሁላችንም በመንግሥተ ሰማይ እንደምንሰባሰብ የሚያሳይ ነው። አንድ «ጌታ» አለ። እርሱም ለኃጢአታችን የሞተውና የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነው ክርስቶስ ነው። በክርስቶስ አምነን የምንድንበት አንድ «እምነት»፥ አማኞች ሁሉ ሊከተሉት የሚገባ አንድ «ጥምቀት»፥ ብሎም ነገሮችን ሁሉ የሚቆጣጠር አንድ መንፈሳዊ የጋራ «አባት» አለን። ጳውሎስ በክርስቶስ የምናምን ሁላችን እነዚህን እውነቶች ሁሉ ከያዝን፥ ላለመጣላትና እርስ በርሳችን ለመተባበር በቂ ምክንያት እንዳለን አመልክቷል።

ነገር ግን ይህ ትምህርት አሉታዊ ገጽታም አለው። ጳውሎስ ይህ የአንድነት መሠረት የሌላቸው ሰዎች መቼም ከእኛ ጋር ሙሉ በሙሉ አንድ ሊሆኑ እንደማይችሉ አመልክቷል። በሥላሴ ካላመኑ፥ ወይም በኢየሱስ ክርስቶስ ካላመኑ፥ ወይም ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት እምነታቸውን በኢየሱስ ላይ ካላኖሩ፤ የአንድነት መሠረት የላቸውም ማለት ነው። በዘመናችን ሁሉም መንገዶች ወደ እግዚአብሔር እንደሚመሩና ሁሉም ሃይማኖቶች ተቀባይነት እንዳላቸው አንዳንድ አስተማሪዎች ያስተምራሉ። ጳውሎስ ግን አንድነታችን በመሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እምነቶች ላይ የተመሠረተ መሆኑን በመግለጽ ይህንኑ አመላካከት ይቃወማል። በእነዚህ ነገሮች የማያምኑ ሰዎች ከእኛ ጋር አንድነት ሊኖራቸው አይችልም።

ለ. አንድ መሠረታዊ እምነት ያለን የአንድ ቤተሰብ አካል ስለሆንን፥ አመለካከታችን ይህንኑ ማንጸባረቅ አለበት። ከሌሎች ምእመናን የተሻልን ነን ብለን ከምናስብ ይልቅ «ትሑታን» ልንሆን ይገባል። ዋነኛ ባልሆኑ ጉዳዮች ከእኛ የተለየ ቀኖናዊ አቋም ያላቸውን ሰዎች «መታገሥ» አለብን። ፍቅርን ማሳየት አለብን።

ሐ. ሁላችንም አንድ እምነት ያለን የክርስቶስ አካል ክፍሎች ስለሆንን፥ በአንድነትና በሰላም በመመላለስ አንድነታችንንና ፍቅራችንን መግለጽ አለብን። በጸጋው እንደሚገባ እንደምንመላለስና በክርስቶስ ባገኘነው ይቅርታ ደስ መሰኘታችንን የምናሳየው በዚህ መንገድ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- በክርስቲያኖች መካከል መከፋፈል በሚኖርበት ጊዜ ከላይ ከተጠቀሱት ሦስት ነገሮች አንዱ ይጓደላል። ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚከሰቱትን ክፍፍሎች ዘርዝር። ከላይ ከተጠቀሱት ሦስት ነገሮች የጎደለውና ክፍፍልን የሚያስከትለው ምንድን ነው? ለ) በክርስቲያኖች መካከል መልካም ግንኙነቶች ባልኖረበት ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መነቃቃት ሊኖር ይችላል ብለህ ታስባለህ? መልስህን አብራራ።

ክርስቶስ የአካሉ ክፍሎች ለእርስ በርሳቸው አገልግሎት እንዲሰጣጡና በብስለት እንዲያድጉ የተለያዩ ስጦታዎችን ሰጥቷቸዋል (ኤፌ. 4፡7-16)።

ጳውሎስ ሁሉም አማኞች የአንድ አካል ክፍሎች እንደ መሆናቸው ተስማምተው ሊኖሩ እንደሚገባ ካሳየ በኋላ፥ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ያስተምራል። መንፈሳዊ ስጦታ አንድ አማኝ በክርስቶስ አካል ውስጥ እንዲያገለግል መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠው የአገልግሎት ችሎታ ነው። ጳውሎስ በዚህ መልእክቱ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ዝርዝር ጉዳዮችን አላቀረበም። በ1ኛ ቆሮንቶስ 12-14 ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች በስፋት አስተምሯል። በኤፌሶን 4፡7 ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች አንዳንድ ጠቃሚ አሳቦችን ጠቃቅሷል።

በመጀመሪያ፥ መንፈሳዊ ስጦታን «ጸጋ» ይለዋል። ይህም እግዚአብሔር የሚሰጠን ችሎታ ወይም አገልግሎት በጥረታችን ወይም ከሌሎች ተሽለን በመገኘታችን ሳይሆን፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠን የማይገባ ጸጋ እንደሆነ ሊያስገነዘበን ይገባል።

ሁለተኛ፥ ጳውሎስ ለእያንዳንዳችን መንፈሳዊ ስጦታ እንደ ተሰጠን አብራርቷል። ይህም እያንዳንዱ ክርስቲያን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ቢያንስ አንድ ስጦታ እንዳለው ያሳያል። ስለሆነም፥ እያንዳንዱ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚጫወተው እግዚአብሔር የሰጠው ሚና ስላለው ተመልካች ብቻ ሊሆን አይገባም።

ሦስተኛ፥ ጳውሎስ እነዚህ የጸጋ ስጦታዎች እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን እንደ ተሰጡን ያስረዳል። መንፈሳዊ ስጦታዎች ከእግዚአብሔር የሚመነጩ እንጂ የተፈጥሮ ችሎታዎች ወይም የቅጥር ሥራዎች አይደሉም። ነገር ግን ምንጫቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ልዩ ስጦታና ድርሻ በመስጠት ስጦታችንን አውቀን እንድናገለግለው ይፈልጋል።

ጳውሎስ ሁሉም ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ስጦታዎችን እንደ ተቀበሉ ቢናገርም፥ በኤፌሶን መልእክቱ የመሪነት ስጦታዎችን በተመለከተ ብቻ በብዛት ጽፎአል። (ለምእመናን የተሰጡትን ሌሎች መንፈሳዊ ስጦታዎች ዝርዝር ከ1ኛ ቆሮንቶስ 12፡28-30 አንብብ።) ጳውሎስ ለቤተ ክርስቲያን የተሰጡትን አምስት ዐበይት የአመራር ስጦታዎች ገልጾአል። የአመራር ስጦታዎች ሰዎች በምርጫ ጊዜ የሚወስኗቸው አይደሉም። ነገር ግን እነዚህ ስጦታዎች እግዚአብሔር የሚሰጣቸውና እኛም ለይተን ለቤተ ክርስቲያን የምንጠቀምባቸው ናቸው። እግዚአብሔር የመሪነት ስጦታ የሰጣቸውን ሰዎች ለዚሁ አገልግሎት መምረጥ አለብን። ነገር ግን ስጦታ የሌለውን ሰው ልንመርጥና ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ስጦታውን ይሰጠዋል ብለን ልንጠብቅ አይገባም። በመጀመሪያ፥ ሐዋርያት ተጠቅሰዋል። እዚህ ላይ ጳውሎስ ክርስቶስ ስለ ሾማቸው በኢየሱስ ስለተመረጡት 12ቱና ስለ ራሱ እያሰበ መሆኑ አይጠረጠርም። ነገር ግን እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ለመመሥረት ስለተጠቀመባቸው አገልጋዮችም እያሰበ ሊሆን ይችላል። ሁለተኛ፥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለክርስቶስ አካል የማስተላለፍ ኃላፊነት የተሰጣቸው ነቢያት አሉ። ይህ የመሪነት ተግባር አዲስ ኪዳን ከመጻፉ በፊት ለቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን የተለየ ጠቀሜታ ነበረው። ሦስተኛ፥ ወንጌሉን ለዓለማውያን የማካፈል ስጦታ የተሰጣቸው ወንጌላውያን ነበሩ። አራተኛ፥ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን ምእመናን መንፈሳዊ ፍላጎቶች የማሟላት ኃላፊነት የተሰጣቸው መጋቢያን ነበሩ። አምስተኛ፥ ሰዎች እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ እንዲመላለሱ በሚያበረታታ መልኩ የእግዚአብሔርን ቃል የማስተላለፍ ስጦታ የተሰጣቸው መምህራን ነበሩ። (ከግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ የመጋቢነትና የአስተማሪነት ስጦታ አንድ ይሁን ወይም ሁለት የተለያዩ ስጦታዎች መሆናቸውን መረዳቱ አስቸጋሪ ነው።) ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን እነዚህን የመሪነት ስጦታዎች የሰጠው የክርስቶስ አካል መንፈሳዊ አመራር እንዲኖራት ነው። የአመራር ስጦታዎች ቤተ ክርስቲያንን ለመትከል፥ ለማሳደግና ለጠፉት ወንጌሉን እንድትሰብክ ለማገዝ ይረዳሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከላይ የተጠቀሱት አምስት መንፈሳዊ ስጦታዎች እንዳሏቸው የምታውቋቸውን ሰዎች በምሳሌነት ጥቀስ። ለ) ሰዎቹ መንፈሳዊ ስጦታዎቹ እንዳሏቸው እንዴት ታውቃለህ?

የአመራር ስጦታዎች ዓላማ ምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ መሪዎች አገልግሎታቸውን በውል ስለማያውቁ ግራ ይጋባሉ። ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር የሚፈልገውን ከማድረግ ይልቅ የዓለምን የአመራር ስልት ይኮርጃሉ። ብዙ ሽማግሌዎች ወይም መጋቢዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሥራቸው የሚናገረውን አያውቁም። በኤፌሶን 4፡12-13 ጳውሎስ አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ እግዚአብሔር በሰጠው የመሪነት ስጦታ አማካኝነት ምን ማድረግ እንዳለበት አብራርቷል።

ሀ. መንፈሳዊ መሪዎች «ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራት ለክርስቶስ አካል ሕንፃ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ» ማዘጋጀት አለባቸው። ብዙውን ጊዜ መሪዎች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሥራት እንዳለባቸው ያስባሉ። ጳውሎስ ግን ምእመናን የቤተ ክርስቲያኒቱን አገልግሎት ያካሂዱ ዘንድ መሪዎች ሊያሠለጥኗቸው እንደሚገባ አስረድቷል። መሪዎች ምእመናን ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን ስጦታ ለይተው እንዲያውቁ ሊረዷቸው ይገባል። ከዚያም በስጦታዎቻቸው አማካኝነት የክርስቶስን አካል ይገነቡ ዘንድ የአገልግሎትን ስፍራዎች ሊሰጧቸው ይገባል።

ለ. መንፈሳዊ መሪዎች ምእመኖቻቸውን በሚያሠለጥኑበት ጊዜ ሕዝቡ ወደ ክርስቶስ ፍጹም ሙላት ይደርሳሉ። በሌላ አገላለጽ፥ በእምነታቸው በመብሰል፥ ስለ ክርስቶስ የጠለቀ እውቀት በማግኘትና በአንድነት በመመላለስ ያድጋሉ። እግዚአብሔር እንደሚፈልግባቸው በመኖር ለወንጌሉ እንደሚገባ ይመላለሳሉ።

አንድ ክርስቲያን በብስለት ማደጉን እንዴት እናውቃለን? ያ ብስለት እንዴት ራሱን ይገልጻል? ጳውሎስ አያሌ ነገሮችን ዘርዝሯል።

 1. በሳል ሰው በእምነቱ ይረጋል። አዳዲስ የሐሰት ትምህርቶች ሲመጡ አይናወጥም።
 2. በሳል ሰው እውነትን በፍቅር ይናገራል። ይህ ከባድ ስለሆነ፥ ብዙውን ጊዜ ወደ አንደኛው አጽናፍ እናደላለን። አንዳንድ ክርስቲያኖች ብዙም ፍቅር ሳይኖራቸው እውነት ነው ብለው የሚያስቡትን በድፍረት ይናገራሉ። ይህ ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የስሜት መጎዳትንና ክፍፍልን ያስከትላል። ሌሎች ክርስቲያኖች በፍቅር ላይ ከማተኮራቸው የተነሣ የሰዎችን ስሜት እንዳይጎዱ በመፍራት እውነትን አይናገሩም። ይህም ሰዎች በተሳሳቱ መንገዶች እንዲመላለሱና የቤተ ክርስቲያን ምስክርነት እንዲጎድፍ ያደርጋል። እግዚአብሔር ስለ እውነት እንድንገደድና በክርስቶስ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ለሆኑት ወገኖቻችን እንድንናገር ይፈልጋል። ነገር ግን ሌላውን ሰው በሚረዳና በሚያሳድግ መልኩ እውነትን በፍቅር እንድንናገርም ይፈልጋል።
 3. በሳል ሰው ከክርስቶስ ጋር የጠለቀ ግንኙነት አለው። ክርስቶስ በነገሮች ሁሉ ንጉሣችን እንደሆነ ተቀብለን በቅርብ ግንኙነት እንመላለሳለን። ክርስቲያኖች ሁሉ ከክርስቶስ ጋር እንዲህ ዓይነት ግንኙነት ሲኖራቸው ሁሉም ክርስቲያን በክርስቶስ አካል ውስጥ የራሱን ድርሻ ያሟላል። የዚህች ዓይነት ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ኃይል አላት።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አብዛኛዎቹ የቤተ ክርስቲያንህ አባላት መንፈሳዊ ስጦታዎችን የሚያውቁ ይመስልሃል? ካልሆነ፥ ለምን? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ የሚገኘው አብዛኛው ሕዝብ በመንፈሳዊ ሕይወቱ የበሰለ ይመስልሃል? ካልሆነ ለምን? ሐ) አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ የቤተ ክርስቲያኑ ምእመናን መንፈሳዊ ስጦታዎቻቸውን እንደሚያውቁ፥ እንደሚጠቀሙና ምእመናን ሁሉ በመንፈሳዊ ብስለት እንደሚያድጉ ለማረጋገጥ ምን ሊያደርግ ይችላል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ጳውሎስ ለአሕዛብ የተመረጠ ሐዋሪያ መሆኑ እና ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የተደረገ ጸሎት (ኤፌ. 3፡1-21)

፩) ጳውሎስ ተሰውሮ የኖረውን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገረውን የወንጌል ምሥጢር ለማስተማር በእግዚአብሔር የተመረጠ አገልጋይ ነበር (ኤፌ. 3፡1-13)።

ጳውሎስ ለአማኞቹ ሌላ ጸሎት ለመጀመር ፈልጎ ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ታላቁን ምሥጢር በመግለጽ ረገድ ስለሰጠው ድርሻ አሰበ። ጳውሎስ እግዚአብሔር ስለ ቤተ ክርስቲያን ምሥጢሩን እንዲገልጽ የመረጠው በታላቅነቱ፥ የተማረ በመሆኑ፥ ወይም አይሁዳዊ በመሆኑ ሳይሆን በጸጋው እንደሆነ ያውቅ ነበር። ጳውሎስ ስለዚህ ምሥጢሩን፥ «በወንጌል መስበክ በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነ የተስፋ ቃል አብረው እንዲካፈሉ፥ ለቅዱሳን ሐዋርያትና ለነቢያት በመንፈስ አሁን እንደተገለጠ በሌሎቹ ትውልዶች ዘንድ ለሰው ልጆች አልታወቀም» ብሏል። ስለሆነም፥ ምሥጢሩ በብሉይ ኪዳን ዘመን ያልተገለጠውና እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን ዘመን የገለጠው እውነት ነው። ለክርስቲያኖች ይህን ልዩነት ማወቁ ጠቃሚ ነው። አንዳንድ ጊዜ በብሉይ ኪዳን ለእስራኤላውያን የተሰጡትን የተስፋ ቃሎች በቀጥታ ከራሳችን ጋር በማዛመድ ስሕተት እንሠራለን። ምንም እንኳን ከሕይወታችን ጋር የሚዛመዱ መርሆች ቢኖሩም፥ ብዙ ትእዛዛት፥ ሕግጋትና የተስፋ ቃሎች በብሉይ ኪዳን ዘመን የእስራኤልን ሕዝብ የሚመለከቱ ናቸው። እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ዘመን አዲሱ ሕዝብ የሚገኝባትን ቤተ ክርስቲያን የመፍጠር ዓላማዎቹን ይፋ አላወጣም ነበር። የቤተ ክርስቲያን ዓላማዎቹን በጳውሎስና በሌሎችም አገልጋዮቹ በኩል የገለጸው ከክርስቶስ ሞት በኋላ ነበር። እንግዲህ የተገለጠው ምሥጢር ምንድን ነው? በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እግዚአብሔር አሕዛብ በክርስቶስ አማካኝነት ከአይሁዶች ጋር እኩል እንዲወርሱ አድርጓል። ከእንግዲህ በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት በአይሁዶችና በአሕዛብ መካከል ልዩነት የለም።

እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን የጀመረው ለምን ዓላማ ነበር? እግዚአብሔር የክርስቶስ አካል በሆነችው ቤተ ክርስቲያን በኩል በገዥዎችና በሰማያዊ ስፍራ ባሉት ባለሥልጣናት ፊት ታላቅ ጥበቡን ለማሳየት ፈልጓል። ይህም መላእክትን፥ ሰይጣንንና አጋንንትን የሚመለከት ነው። እግዚአብሔር የጎሳና የምጣኔ ሀብት ልዩነቶችን ያስወገደበት የቤተ ክርስቲያን (የአዲስ ሕዝብ) መፈጠር ለጥበቡ ታላቅ ምስክር ነው። ምንም እንኳ ቤተ ክርስቲያን ከኃጢአትና ከሐሰት ትምህርቶች ጋር የሚታገሉ ደካማ ሰብአዊ ፍጡራን የሚገኙባት ብትሆንም፥ ለፍጥረት ሁሉ ማለትም ለሰዎችም ሆነ ለመንፈሳውያን ፍጥረታት ታላቅ ጥበቡን የሚያሳይባት የእግዚአብሔር ዋነኛ መሣሪያው ነች።

፪) ጳውሎስ አማኞች የክርስቶስንና ከእርሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ታላቅነት እንዲገነዘቡ እግዚአብሔር እንዲያጠነክራቸው ይጸልያል (ኤፌ. 3፡14-21)።

በኤፌሶን 3፡1 ጳውሎስ ወደ እግዚአብሔር መጸለይ ከጀመረ በኋላ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን ስላለው አስደናቂ ዕቅድና እርሱም ይህን ታላቅ ምሥጢር በማብራራቱ በኩል የእግዚአብሔር አገልጋይ መሆኑን ገልጾአል። አሁን ጳውሎስ ወደ ጸሎቱ ይመለሳል። ጳውሎስ በዚህ መልእክት የመጀመሪያው ክፍል ባብራራቸው እውነቶች ላይ በመመሥረት፥ አማኞች እንዲማሩና አንዳንድ ጠቃሚ ነገሮችን ከሕይወታቸው ጋር እንዲያዛምዱ ይጸልያል።

ሀ. ክርስቶስ በልባቸው ውስጥ በእምነት ይኖር ዘንድ በውስጥ ሰውነታቸው እንዲጠነክሩ ይጠይቃቸዋል። ጳውሎስ እግዚአብሔር ከከበረው የጸጋው ባለጠግነት ለእነዚህ አማኞች ጸጋንና ኃይልን እንዲሰጣቸው ይጠይቃል። ትልቁ ፍላጎቱ ክርስቶስ በልባቸው ውስጥ በንጉሥነት እንዲኖር ነበር። ጳውሎስ ክርስቶስ ልባቸውን እንዲጎበኝ ብቻ ሳይሆን አብሯቸው በመኖር ከእነርሱ ጋር ኅብረትን እንዲያደርግ ይፈልጋል።

ለ. ጳውሎስ በፍቅር ሥር ሰድደው እንዲመሠረቱ ይጸልያል። ይህ ሥሩን ወደ መሬት አጥልቆ የሰደደን ትልቅ ዛፍ የሚያሳይ ምስል ነው። ጳውሎስ በእግዚአብሔር አስደናቂ ጸጋ ስለ ክርስቶስ ፍቅር የጠለቀ እውቀት እንዲኖረን ይፈልጋል። ሕይወታችንን ክርስቶስ እንደ ግለሰብና እንደ ቤተ ክርስቲያን ለእኛ ባለው ፍቅር በሚማርክበት ጊዜ እርሱን ደስ የሚያሰኝ ማንኛውንም ተግባር ከማከናወን ወደ ኋላ አንልም። እርሱን በመውደድ ለክብሩ እንኖራለን። በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር ክብር በብሉይ ኪዳን ዘመን ቤተ መቅደሱን እንደ ሞላ ሁሉ የእኛንም ሕይወት ይሞላዋል።

እግዚአብሔር ካለን ሕይወት የሚመነጨው ፍቅር እርስ በርሳችንም እንድንፋቀር ያደርገናል።

የውይይት ጥያቄ፡– የጳውሎስን ሁለት የጸሎት ጥያቄዎች ተመልክት። ሀ) እነዚህ ሁለት እውነቶች በሕይወታችን እውን ሊሆኑ የሚገባቸው ለምንድን ነው? ለ) የግልህንና የቤተ ክርስቲያንህን ችግሮች ዘርዝር። የእነዚህ ሁለት የጸሎት ጥያቄዎች መልሶች ለችግሮቻችን ሥሮች መፍትሔ የሚሰጡት እንዴት ነው? ሐ) በጳውሎስ ጸሎት መሠረት፥ እግዚአብሔር እንደሚፈልገው እንድንሆን ከሚያስፈልጉን ነገሮች እንደኛው ምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

በክርስቶስ አንድ መሆን (ኤፌ. 2፡11-22)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በዓለም ውስጥ የሚገኙትን አንዳንድ የጎሳ፥ የምጣኔ ሀብትና የጾታ ክፍፍሎች ዘርዝር። ለ) እነዚህ ልዩነቶች ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚንጸባረቁበትን ሁኔታ ግለጽ። ሐ) እነዚህ ልዩነቶች የሚያስከትሏቸው አሉታዊ ውጤቶች ምን ምንድን ናቸው?

በአይሁዶች አስተሳሰብ፥ ዓለም በሁለት ምድቦች የተከፈለች ነበረች። እነዚህም ሁለት ቡድኖች «የተገረዙት» ምርጥ የእግዚአብሔር ሕዝቦችና የቃል ኪዳን በረከቶችን ይጋሩ ዘንድ ያልተመረጡት (ያልተገረዙት) አሕዛብ ነበሩ። በእስያ ክፍለ ሐገራት አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት አሕዛብ እንጂ አይሁዳውያን አልነበሩም። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ከማመናቸው በፊት እንደ አሕዛብ ያሳለፉትን ሕይወት ያስገነዝባቸዋል። ጳውሎስ እግዚአብሔር በጸጋው ቤተ ክርስቲያንን በመሠረተ ጊዜ የነበረውን አስደናቂ ፍቅር ያብራራል። ከክርስቶስ ሞትና እግዚአብሔር፥ ቤተ ክርስቲያን በምትባለው አካል ውስጥ የሚገኙትን አዲስ ሕዝብ ከመፍጠሩ በፊት አሕዛብ ተስፋ በሌለው ሁኔታ ውስጥ ነበሩ።

ሀ. አሕዛብ የእግዚአብሔር ትኩረት የሆነው የታላቁ እስራኤል ሕዝብ አካል አልነበሩም። ሁልጊዜም ወደ ውጭ የተገለሉና የተናቁ ሰዎች ነበሩ።

ለ. ለተስፋው ቃል ኪዳን እንግዶች ነበሩ። አሕዛብ የአብርሃም ቃል ኪዳን፥ የሲና ተራራ ቃል ኪዳን፥ የአሮን ቤተሰብ ቃል ኪዳን፥ የከነዓን ምድር ቃል ኪዳንና የዳዊት ቃል ኪዳን ተካፋይ አልነበሩም። የነበራቸው ተስፋ ቢኖር እግዚአብሔር አንድ ቀን በአብርሃም በኩል እንደሚባርካቸው የሚያመለክት ፍንጭ ብቻ ነበር። ስለሆነም አሕዛብ ከእግዚአብሔር የብሉይ ኪዳን የቸርነት ምርጫና በረከት ውጭ ነበሩ።

ሐ. አሕዛብ ተስፋ አልነበራቸውም። ከክርስቶስ ሞት በፊት እነዚህ አሕዛብ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ስለሚዛመድበት ሁኔታ ከገለጸው ቃል ኪዳን ውጭ በመሆናቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን አግኝተው የሚድኑበት ተስፋ አልነበራቸውም።

መ. ያለ እግዚአብሔር ነበሩ። አሕዛብ በብዙ አማልክት ቢያምኑም፥ አንዱንና እውነተኛ የሆነውን አምላክ አያውቁም ነበር። እግዚአብሔር ማንነቱንና እንዴት ሊያመልኩት እንደሚገባ የገለጸበትን ብሉይ ኪዳን አልተሰጣቸውም ነበር። ስለሆነም፥ ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ።

እንግዲህ በአዲስ ኪዳን ምን ለውጥ ታየ? ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሲሞትና የአሕዛብን የበረከት በር ሲከፍት ምን ተከሰተ?

ሀ. እግዚአብሔር በክርስቶስ ሞት (በክርስቶስ ደም) አማካኝነት ከእርሱ ጋር የሚዛመዱበትን ዕድል ሰጣቸው። አሕዛብን ወደ ራሱ አስጠጋቸው።

ለ. ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን አይሁዶችንና አሕዛብን የከፋፈለውን የመለያየት ግድግዳ አስወገደ። በእነዚህ ሁለት ሕዝቦች መካከል የነበረውን የጥላቻ ግድግዳ አፈረሰ።

ሐ. ኢየሱስ «አዲሱ ሰው» ወይም «አንድ አካል» የተባለችውን ቤተ ክርስቲያን ፈጠረ። አሁን ቅርብ የነበሩት አይሁዶች ወደ እግዚአብሔር ለመምጣት በሚፈልጉበት ጊዜ፥ በክርስቶስ በኩል ወደ አይሁድ ሕዝብ ሳይሆን ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባት ይኖርባቸዋል። ርቀው የነበሩት አሕዛብ ስለ ክርስቶስ ሰምተው በሚያምኑበት ጊዜ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን አግኝተው ወደ ቤተ ክርስቲያን ይገባሉ። አይሁዶችና አሕዛብ እኩል ሆነዋል። አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ የሚድኑት በክርስቶስ በማመን ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥም ቢሆን ሁለቱም አንድ ናቸው።

መ. አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተመሳሳይ በረከቶችን ያገኛሉ። ሁለቱም፥

1) ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ባላገሮች ናቸው። ይህም በእኩል ደረጃ የእግዚአብሔር ሕዝብና የእግዚአብሔር መንግሥት አካል መሆናቸውን ያሳያል።

2) የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት ናቸው። ጳውሎስ የቤትን ምስያ በመጠቀም፥ በክርስቶስ በኩል አይሁዶችና አሕዛብ የአዲሱ ቤት አካል መሆናቸውን ገልጾአል። የጥንት ቤቶች በሚሠሩበት ጊዜ በወሳኝ ስፍራዎች ላይ ትላልቅ የመሠረት ድንጋዮች ይቆሙ ነበር። ከሁሉም የሚተልቅና የሚሻል የማዕዘን ድንጋይም ይጠቀሙ ነበር። በእግዚአብሔር መንፈሳዊ ቤት፥ ታላላቆቹ ድንጋዮች የቤተ ክርስቲያን መሥራቾችና መሪዎች የሆኑት ሐዋርያትና ነቢያት ናቸው። ነገር ግን በዚህ አዲስ የእግዚአብሔር ቤት ውስጥ እጅግ ጠቃሚ የሆነ አንድ ዓለት ነበር። እርሱም የማዕዘን ድንጋይ የሆነው ክርስቶስ ነበር። ይህ አዲሱ የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ በእግዚአብሔር ዓላማና ንድፍ መሠረት እንዲሠራ የሚያደርገው ክርስቶስ ነው።

3) ቅዱስ ቤተ መቅደስ። አይሁዶች በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ ልዩ የእግዚአብሔር ሕዝብ መሆናቸውን የሚያሳይ ልዩ ተምሳሌት እንደሆነ ያስቡ ነበር። የአይሁድ ክርስቲያኖችም በኢየሩሳሌሙ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያመልኩ ነበር። ይህን ልምምድ ያቋረጡት ጳውሎስ ይህን መልእክት ከጻፈ ከ10 ዓመታት ያህል በኋላ ነበር። በቤተ መቅደሱ ውስጥ አሕዛብ ወደ ውስጥ ሲገቡ እንደሚሞቱ የሚያስጠነቅቅ ውስብስብ ምልክት ነበር። ጳውሎስ ግን የእግዚአብሔር ንድፍ የሆነ የተሻለ፥ አዲስና «ቅዱስ» ቤተ መቅደስ እንደ ተሠራ ገልጾአል። ይህም የእግዚአብሔር ልጆች ኅብረት የሚያደርጉባትን ቤተ ክርስቲያን የሚያመለክት ነው።

4) እግዚአብሔር በመንፈስ የሚያድርበት መኖሪያ። የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃል፥ አይሁዶች የመገናኛውን ድንኳንና በኋላም ቤተ መቅደሱን በገነቡ ጊዜ እግዚአብሔር በዚያ ውስጥ እንደሚኖር ነበር (ዘጸ. 29፡45-46)። ይህንን በግልጽ ለማሳየት የመገናኛው ድንኳንና ቤተ መቅደሱ በተሠራ ጊዜ፥ የእግዚአብሔር ክብር ከሰማይ ወርዶ ቅድስተ ቅዱሳኑን ይሞላ ነበር (ዘጸ. 40፡34-38)። ነገር ግን ጳውሎስ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች መንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ መሆናቸውን ካብራራ በኋላ፥ እግዚአብሔር አይሁዶች በሚያከብሩት ቤተ መቅደስ ውስጥ እንዳደረ ሁሉ በእኛም ውስጥ እንዳደረ አመልክቷል። መንፈስ ቅዱስ በልባችን ውስጥ በማደር የሕያው፥ ዘላለማዊና ሁሉን ቻይ አምላክ የመኖሪያ ስፍራ ያደርገናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በሚቀጥለው ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያንህ ስትሄድ ዙሪያ ገባውን እየተመለከትህ ይህንኑ ስለ ቤተ ክርስቲያንና ስለ እግዚአብሔር ሕዝብ የተሰጠውን መግለጫ አስብ። እነዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ስላለን ግንኙነት የሚናገሩ በረከቶች ሊያበረታቱንና አኗኗራችንን ሊለውጡ የሚገባቸው እንዴት ነው? ለ) ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከዘር፥ ምጣኔ ሀብት ወይም ከትምህርት ጋር በተያያዘ ክፍፍሎች ይከሰታሉ። ይህ እግዚአብሔር ልጆቹን ሁሉ አንድ ለማድረግ ካለው ፍላጎት ጋር የሚቃረነው እንዴት ነው? እነዚህን የመለያየት ግድግዳዎች ለማስወገድ ምን ማድረግ ይቻላል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

በእግዚአብሔር ጸጋ፥ ሙታን የነበሩ የእግዚአብሔር ጠላቶች ሕያዋን ሆነው ድነትን (ደኅንነትን) አግኝተዋል (ኤፌ. 2፡1-10)።

እግዚአብሔርን እያስደሰትን እንድንኖር ከሚያነሣሡን እጅግ ጠንካራ ምክንያቶች አንዱ ቀደም ሲል የነበርንበትን ሁኔታ ከአሁኑ የእግዚአብሔር ልጅነት ሕይወታችን ጋር ማነጻጸር ነው። ከማመናችን በፊት ፈጽሞ ምስኪኖች እንደ ነበርንና የእግዚአብሔር ጸጋ ድነትን እንደ ሰጠን፥ እንዲሁም ስለ ዘላለማዊ በረከቶቻችን በተሻለ ሁኔታ ስንረዳ፥ በዚህ መንገድ የሚወደንን አምላክ ደስ ለማሰኘት እንሻለን።

የውይይት ጥያቄ፡– ኤፌ. 2፡1-3 አንብብ። ጳውሎስ ስላልዳኑት ሰዎች የገለጻቸው አምስት ነገሮች ከመዳንህ በፊት በሕይወትህ ውስጥ እንዴት እንደ ተንጸባረቁ አብራራ።

ሀ. ከመዳናችን በፊት የነበርንበት የምስኪንነት ሕይወት (ኤፌ. 2፡1-3)።

 1. በበደላችንና በኃጢአታችን ሙታን ነበርን። የሞተ ሰው ሕይወት ስለሌለው ለራሱ የሚጠቅሙትን ነገሮች ሊመርጥ አይችልም። ጳውሎስ በክርስቶስ ከማመናችን በፊት፥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ፍጹም ሙታን እንደ ነበርን ያስረዳል። ወንጌሉን ሰምተን ልንረዳ አንችልም ነበር። በክርስቶስ ለማመን ልንመርጥ አንችልም ነበር።
 2. ሙሉ በሙሉ በኃጢአት ቁጥጥር ሥር እንኖር ነበር። የኃጢአት ባሕርይ እስረኞች ነበርን።
 3. «በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ»፥ ማለትም በሰይጣን ቁጥጥር ሥር እንኖር ነበር።
 4. የኃጢአት ተፈጥሯችን የሚፈልገውን እየሠራን ለራሳችን ብቻ ደስ በመሰኘት እንኖር ነበር።
 5. የቁጣ ልጆች ነበርን። የእግዚአብሔር መለኮታዊ ቁጣና ፍርዱ በእኛ ላይ ነበር። የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው። ምንም ዓይነት ተስፋ ስላልነበረን የምንጠባበቀው ነገር ቢኖር እግዚአብሔር በዘላለማዊ ፍርዱ ወደ ሲኦል እንዲልክን ነበር።

ለ. ካመንን በኋላ ያገኘናቸው በረከቶች (ኤፌ. 2፡4-10)።

ጳውሎስ «ነገር ግን» በሚል ቃል ይህንን ክፍል ይጀምራል። መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት «ነገር ግን» እና «እንግዲህ» (ስለሆነም) የሚሉ ቃላት በጣም ጠቃሚዎች ናቸው። «እንግዲህ» የሚለው ቃል የአንድን አሳብ መደምደሚያ ያሳያል። ይህ አንድ ነገር እውነት በመሆኑ፥ እግዚአብሔር የተለየ ውጤት እንደሚመጣ ይናገራል። (ሮሜ 8፡1 አንብብ። ከ«እንግዲህ» በፊትና በኋላ የተከሰተው ልዩነት ምንድን ነው?) እዚህ በኤፌሶን 2፡4 ጳውሎስ «ነገር ግን» የሚለውን ቃል ተጠቅሟል። ይህም ከ «ነገር ግን» በፊትና በኋላ ያሉት ጉዳዮች ያላቸውን ከፍተኛ ልዩነት ያስረዳል። ጳውሎስ ሁላችንም ተስፋ በሌለው ሁኔታ ውስጥ እንደ ነበርን ካሳየ በኋላ፥ የእግዚአብሔር ጸጋና ፍቅር ያመጣውን ልዩነት ለማመልከት «ነገር ግን» የሚለውን ቃል ተጠቅሟል።

የልዩነቱ ምንጭ የእግዚአብሔር «ታላቅ ፍቅር» እና «የምሕረቱ ባለጸግነት» ነበር። ልዩነቱ የተገኘው ከእኛ መልካምነት ወይም እግዚአብሔር የሚወደውን ምርጫ ለመምረጥ በመቻላችን አይደለም። እኛ ሙታን በመሆናችን ይህን ልናደርግ እንችልም ነበር። ነገር ግን ያገኘናቸው በረከቶች ሁሉ ከእግዚአብሔር ምሕረትና ፍቅር የመነጩ ናቸው። ምሕረት ለማይገባው ሰው መልካምን ነገር ማድረግ ነው። ስሜት ብቻ ሳይሆን እርዳታ ለማይገባቸው ወገኖች እጅን መዘርጋት ነው።

ለመሆኑ ከእግዚአብሔር ፍቅርና ምሕረት የተነሣ ያገኘናቸው በረከቶች ምን ምንድን ናቸው?

 1. እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር አስነሣን። ክርስቶስ ከሞት እንደ ተነሣ ሁሉ እኛም ከመንፈሳዊ ሙትነታችን ተነሥተናል። ይህም ወንጌሉን እንድንሰማ፥ እንድንገነዘብና እንድናምን አስችሎናል።
 2. እግዚአብሔር በጸጋው አድኖናል። ይህ በመልካምነታችን፥ ከትክክለኛው ጎሳ በመወለዳችን ወይም በአኗኗራችን ለውጥ የምናገኘው አይደለም። ድነት (ደኅንነት) የእግዚአብሔር ነፃ ስጦታ ስለሆነ፥ ማንም በክርስትናው ሊመካ አይችልም። እንደ አልጄሪያ ክርስቲያኖች ከሌሉበት አገር ይልቅ ወንጌሉን ልንሰማ በምንችልበት አገር እንድንኖር ያደረገው የእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ነው። እግዚአብሔር እያመፅንበት ሳለ የመረጠንና ልጆቹ ያደረገን በማይገባን ምሕረቱ ብቻ ነው። እግዚአብሔር እኛን ፈለገን እንጂ እኛ እግዚአብሔርን አልፈለግነውም።
 3. በሰማያት ከክርስቶስ ጋር የተቀመጥን ስለሆነ፡ የታላቅ ቸርነቱን (የጸጋውን የማይነገር ባለጠግነት) ለዘላለም እናያለን። ጳውሎስ ይህን የሚለው ከክርስቶስ ጋር በሞቱ፥ በቀብሩ፥ በትንሣኤውና በዕርገቱ መተባበራችንን በምሳሌነት በመጠቀም ነው። አንድ ቀን ወደ ሰማይ እንደምንሄድና የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ጸጋና በረከቶች እንደምናገኝ ቢታወቅም፥ ጳውሎስ በእግዚአብሔር ዓይኖች ቀድሞውኑ ወደ ሰማይ ሄደን በረከቶቹን እየተቀበልን መሆናችንን ያስረዳል።
 4. እግዚአብሔር ቀደም ሲል ያዘጋጀውን «መልካሙን ሥራ» እናደርግ ዘንድ በጥንቃቄ ቀርጾናል። የጳውሎስ ገለጻ የሚያሳየው እንድን እንጨት በጥንቃቄ ቀርጾ ውብና ጠቃሚ ዕቃ የሚሠራውን ዋነኛ አናጺ ነው። እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ በጣም ግላዊ ተሳትፎ ያደርጋል። ለእያንዳንዳችን የተለየ ስብዕና፥ ስጦታ፥ ሥልጠና፥ ልምድ፥ ወዘተ… በመስጠት ይቀርጸናል። እነዚህ ሁሉ ዓላማ አላቸው። እግዚአብሔርን እንድናገለግል (መልካሙን ሥራ እንድንሠራ) ይረዱናል። የሚያስደንቀው ግን እግዚአብሔር ከፈጠረን ሁኔታ ጋር በሚጣጣም መልኩ እናገለግለው ዘንድ ነገሮችን ይመርጣል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር አንተን ስለፈጠረበት ሁኔታ አንዳንድ ልዩ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? ለ) እግዚአብሔርን ለማገልገል ይህንን እየተጠቀምህ ያለኸው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ጳውሎስ አማኞች እንደ እግዚአብሔር ልጆች ያላቸውን ስፍራ የበለጠ እንዲረዱ ጸለየ (ኤፌ. 1፡15-23)

የውይይት ጥያቄ፡- ጳውሎስ በኤፌሶን 1፡15-23 ያቀረበውን ጸሎት ብዙውን ጊዜ አንተ ለሰዎች ከምትጸልየው ጋር አነጻጽር። የጳውሎስን ጸሎት ከእኛ ጸሎት የሚለዩት ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?

የጳውሎስን ጸሎት እኛ ብዙውን ጊዜ ለሰዎች ከምንጸልየው ጸሎት ጋር ስናነጻጽር፥ ብዙ ልዩነቶችን ልንመለከት እንችላለን። ብዙውን ጊዜ ለሰዎች በምንጸልይበት ጊዜ እግዚአብሔር በሥጋ እንዲባርካቸው እንጠይቃለን። እግዚአብሔር ጤና እንዲሰጣቸው፥ በጉዞ ወቅት ከአደጋ እንዲጠብቃቸው፥ ምግብ እንዲሰጣቸው፥ ወዘተ… እንጠይቃለን። ጳውሎስ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከዚህ የጠለቀና የላቀ ፍላጎት እንዳለው አጢኗል። ይህም የመንፈሳዊ ዕድገት፥ በተለይም እግዚአብሔርን በሚያስከብር እውቀት ማደግ ነው። ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው በዚሁ የመጀመሪያው ጸሎት ውስጥ የሚከተሉትን ነገሮች ልንመለከት እንችላለን።

ሀ. ጳውሎስ «እርሱን በማወቅ የጥበብና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁና በእግዚአብሔር ዕውቀት እንድታድጉ» እያለ ይጸልያል። ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች መልእክት የጻፈበት ዓላማ እግዚአብሔር ልጆቹን ስለሚባርክበት ሁኔታ በማወቅ እንዲያድጉ ነበር። እግዚአብሔርን የበለጠ ስናውቅና ከእርሱ ጋር የቀረበ ግንኙነት ሊኖረን፥ ጸሎታችን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ይስማማል። እግዚአብሔርን በበለጠ ስናውቅ መንፈሳዊ ጉዟችን ጽኑ ይሆናል። እውቀት ለመንፈሳዊ ጤንነታችን መሠረት በመሆኑ፥ ምርጫ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም። የሚያሳዝነው ብዙ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር እውቀት ለማደግ አይፈልጉም። ስለ እግዚአብሔር፥ ስለ ባሕርያቱ፥ ስለ ተግባራቱ፣ ስለ ፈቃዱ፥ ወዘተ.. ጊዜ ወስደው አያጠኑም። ይህም ለሐሰት ትምህርት፥ ሚዛናዊ ላልሆነ አምልኮና ለኃጢአት ያጋልጣቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ስለ እግዚአብሔር ያለህ የጠለቀ እውቀት በመንፈሳዊ ጉዞህ እንዴት እንደረዳህ ግለጽ። ለ) የጸሎት ሕይወትህን እንዴት እንደረዳው አስረዳ። ሐ) ምእመናን ስለ እግዚአብሔር ባላቸው እውቀትና ግንኙነት እንዲያድጉ ለማገዝ ቤተ ክርስቲያንህ ምን እያደረገች ነው? መ) ይህ አጥጋቢ ውጤት እንዲያስገኝ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

ለ. ጳውሎስ አማኞች ስለ ወደፊት ሕይወታቸው፥ ስለ ብልጽግናቸውና የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ መንግሥት ስለ መውረሳቸው ግልጽ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ይጠይቃል። ዓለም እንደ በሽታ፥ ስደትና ሞት ባሉት ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች የተሞላች ነች። መፍትሔው ምንድን ነው? እንግዲህ ተስፋ የሚሰጠን ምንድን ነው? ጳውሎስ በዘላለማዊ ቤታችን የሚጠብቀንን በትክክል መረዳቱ ተስፋ እንደሚሰጠን ያውቅ ነበር። ስለሆነም፥ የወደፊቱን ታላቅ ስፍራና በረከት እንገነዘብ ዘንድ እግዚአብሔር እንዲረዳን ጸልዮአል።

ሐ. ጳውሎስ የኤፌሶን ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ለልጆቹ የሚሰጠውን ታላቅ ኃይል ተረድተው እንዲጠቀሙበት ጸልዮአል። እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ የተቀደሰ ሕይወት ልንኖር የምንችለው ይህንን ኃይል ስንጠቀም ነው። ይህ ምን ዓይነት ኃይል ነው? ጳውሎስ ይህ በክርስቶስ ሕይወት ውስጥ የነበረው ዓይነት ኃይል እንደሆነ ገልጾአል። ያ ኃይል፥ 1) ክርስቶስን ከሞት አስነሥቷል። 2) ክርስቶስን በሰማይ በእግዚአብሔር ቀኝ አስቀምጦታል። 3) ክርስቶስን በሰማይና በምድር የመጨረሻው ባለሥልጣን አድርጎታል። ጳውሎስ በምድር ላይ የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ይህንን አስደናቂ ኃይል ልትጠቀም እንደምትችል ገልጾአል።

የውይይት ጥያቄ፡- ስለ ጸሎቶችህ አስብ። ሀ) ለራሳችንና ለሌሎች የምናቀርባቸው ጸሎቶች በሥጋዊ በረከቶች የሚሞሉት እንዴት ነው? ለ) ጸሎቶችህን ከጳውሎስ ጸሎቶች ጋር ለማመሳሰል ምን ዓይነት ለውጦችን ማድረግ ትችላለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

በክርስቶስ የሚገኝ መንፈሳዊ በረከት (ኤፌ. 1፡1-14)

ሁሴን በሙስሊም ቤተሰብ ውስጥ ነበር ያደገው። ነገር ግን ትምህርቱን በመከታተል ላይ ሳለ ከሌላ ተማሪ ስለ ክርስቶስ ወንጌል ሰማ። ወንጌሉን አምኖ ስለተቀበለ ቤተሰቦቹ ወዲያውኑ ከቤት አባረሩት። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ በነበረባቸው ጊዜያት ከአንድ ክርስቲያን ቤት ወደ ሌላው እየተዘዋወረ ሲቸገር ኖረ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ሥራ ይዞ ራሱን እንደሚያስተዳድር ተስፋ ያደርግ ነበር። ነገር ግን ሥራ ባለማግኘቱ ኑሮው ትግል የበዛበት ሆነ። ቡቱቶ ልብሱን ለብሶ ወዲያ ወዲህ ማለት አሳፈረው። በዚህ ጊዜ ክርስቶስን ለመከተል መወሰኑ ትክክል ስለመሆኑ ያመነታ ጀመር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለክርስቲያኖች በድህነት ውስጥ በደስታ መኖር አስቸጋሪ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ኤፌ. 1፡3-14 አንብብ። ክርስቲያኖች በሰማያዊ ስፍራ የተባረኩባቸውን ነገሮች ዘርዝር። ሐ) የበለጠ ጠቀሜታ ያላቸው ምድራዊ በረከቶች ናቸው ወይስ መንፈሳዊ የሰማይ በረከቶች? ለምን? መ) ክርስቲያኖች ድህነት ወይም ስደት በሚደርስባቸው ጊዜ መንፈሳዊ በረከቶቻቸውን ማስታወስ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

ብዙዎቻችን እግዚአብሔር በብዙ ምድራዊ በረከቶች ይባርከናል ብለን እናስባለን። አንዳንድ ጊዜ እንደዚያ ያደርጋል። ብዙውን ጊዜ ግን አማኞች ከገንዘብ፥ ከበሽታና ከሌሎችም ሁኔታዎች ጋር የተያያዙ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክት እግዚአብሔር ድነትን (ደኅንነትን) ባገኘን ጊዜ ምን ዓይነት በረከቶችንና ዋስትና እንደሰጠን ግልጽ አድርጓል። ጳውሎስ በቁሳዊ በረከቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ እግዚአብሔር ለልጆቹ ሁሉ የሚሰጣቸውን መንፈሳዊ በረከቶች እንድናስታውስ አበረታቶናል። ማንም ሰው ሊወስድብን በማይችላቸው በእነዚህ ዘላለማዊ መንፈሳዊ በረከቶች ልንበረታታ ይገባል።

፩) መግቢያ (ኤፌ. 1፡1-2)

ጳውሎስ በመልእክቶቹ ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ «ሐዋርያ» ሊሆን መብቃቱን ይናገራል። የኤፌሶን ክርስቲያኖች የጳውሎስን ሐዋርያነትና ሥልጣን ስላልተጠራጠሩ፥ ጳውሎስ በዚህ ጉዳይ ላይ ለገላትያ ቤተ ክርስቲያን የጻፈውን ያህል አጽንኦት አላደረገም (ገላ. 1፡1)።

ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው «በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን» ነበር። «ኤፌሶን» የሚለው ቃል በመጀመሪያው የጳውሎስ መልእክት ውስጥ ስለመኖሩ ምሁራን የሚከራከሩ መሆኑን በአንደኛው ቀን ትምህርት ተመልክተናል። ይህ ለኤፌሶን ብቻ ሳይሆን በእስያ ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የተላከ ተዘዋዋሪ ደብዳቤ ሊሆን ይችላል። ኤፌሶን እጅግ አስፈላጊና በቀዳሚነት መልእክቱን የተቀበለች ቤተ ክርስቲያን በመሆኗ፥ ቀደምት ምሁራን «ኤፌሶን» የሚለውን ቃል ጨምረው ይሆናል።

እነዚህ ክርስቲያኖች ከዓለም የተለዩና ለክርስቶስ በታማኝነት የኖሩ ስለነበሩ፥ የወቀሳ አሳቦች አልተሰነዘሩም። ጳውሎስ እንዲለውጡ የጠየቃቸው አስተምህሮዎች ወይም ልምምዶች የሉም። ነገር ግን ጳውሎስ የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን የተለማመዳቸውን የጸጋና የሰላም ቡራኬ ሰጥቷል።

፪) የእግዚአብሔር ልጆች መንፈሳዊ በረከቶች (ኤፌ. 1፡3-14)

ዛሬ በምንኖርበት ዘመን ክርስቲያኖች በምድራዊ በረከቶች ላይ ያተኩራሉ። አንዳንድ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ካመንን ሀብታሞች እንሆናለን ብለው ያስባሉ። በክርስቶስ ካመንን፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች ከተከተልንና እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ከኖርን፥ እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ በቁሳዊ በረከቶች ይባርከናል ይላሉ። አንዳንድ ጊዜ ግን ይህንን አያደርግም። እግዚአብሔር ቢባርከንም እንኳን እነዚህ ምድራዊ በረከቶች ዋነኛ ነገሮች አለመሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል። ዋነኞቹ መንፈሳዊ በረከቶች ናቸው።

ጳውሎስ ለቅዱሳን ወይም በክርስቶስ ላሉት ከሁሉም የላቀ በረከት እንደ ተሰጠ አስረድቷል። እነዚህም ምድራዊ በረከቶች ሳይሆኑ፥ ጳውሎስ እንደሚለው በሰማያዊ ስፍራ የሚገኙ ናቸው። ጳውሎስ ብዙውን ጊዜ በምሥጢራዊ መንገድ ከክርስቶስ ሞት፥ ትንሣኤና ዕርገት ጋር መተባበራችንን ሲገልጽ መቆየቱን አንስተናል። በዚህ ስፍራ ጳውሎስ በክርስቶስ ዕርገት ላይ ያተኩራል። ክርስቶስ ወደ ሰማይ ስላረገና እኛም ከእርሱ ጋር ስለተባበርን፥ እግዚአብሔር የሚሰጠን በረከቶችም ያሉት በሰማይ ነው። ከክርስቶስ የተነሣ እነዚህ ሁሉ በረከቶች የእኛ ናቸው። እነዚህ በረከቶች ምን ምንድን ናቸው?

ሀ. እግዚአብሔር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን እንሆን ዘንድ መርጦናል። ስለ ድነት (ደኅንነት) ስናስብ ብዙውን ጊዜ በሰዎች ሚና ላይ እናተኩራለን፥ በክርስቶስ ስለማመናችንም እንናገራለን። ጳውሎስ ግን ድነት የሚመለከተው ከእግዚአብሔር እይታ አንጻር ነው። እግዚአብሔር በማንረዳው መንገድ በዓለም ውስጥ ከሚገኙ እጅግ ብዙ ዓለማውያን መካከል መርጦናል። ድነት (ደኅንነት) እግዚአብሔር አንተንና እኔን ልጆቹ አድርጎ ከመምረጡ ተግባር ነው የሚጀምረው። የበለጠ የሚገርመው ደግሞ ጳውሎስ ይህ ምርጫ የተካሄደው ከዓለም ፍጥረት በፊት እንደሆነ መናገሩ ነው። አዳምና ሔዋን ከመፈጠራቸው በፊት እግዚአብሔር አንተና እኔ የቤተሰቡ አካላት እንድንሆን መፈለጉን ያውቅ ነበር። ስለሆነም፥ መረጠን።

እግዚአብሔር የመረጠን ድነት እንድናገኝ ብቻ አልነበረም። እኛን የመረጠበት ዓላማ ኃጢአተኞች ብንሆንም እንኳ ተለውጠን እንድንቀደስና በፊቱ ነውር የሌለን እንሆን ዘንድ ነበር። ይህ በሁለት የተለያዩ መንገዶች ይከናወናል። በመጀመሪያ፥ ድነት ስናገኝ እግዚአብሔር ያጸድቀናል ወይም የኃጢአት በደለኞች አለመሆናችንን ያውጃል። የክርስቶስ ደም ኃጢአታችንን ስለሚሸፍን፣ እግዚአብሔር በፊቱ ንጹሐን እንደሆንን አድርጎ ያየናል። እንዲሁም የኢየሱስ ክርስቶስን ጽድቅ ይሰጠናል። የክርስቶስ ጽድቅና ፍጹማዊ ቅድስና የእኛ ጽድቅና ቅድስና ይሆናሉ። በዚህም መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ቅዱሳንና እንከን እንደሌለን ሆነን እንታያለን። ነገር ግን ጳውሎስ የሚለው ከዚህም ያለፈ ነው። ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር ኃጢአትን በማሸነፍና ክርስቶስን በመምሰል በቅድስና እንድናድግ ይፈልጋል።

ለ. እግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን ወስኗል። ሁለተኛው የድነት (ደኅንነት) እርምጃ እግዚአብሔር ከመረጠን በኋላ ልጆቹ ሊያደርገን መወሰኑ ነው። ይህ የእግዚአብሔር አሠራር እኛ ክርስቶስን ለመከተል ከመምረጣችን ወይም ካለመምረጣችን ጋር እንዴት እንደሚጣጣም ሙሉ ለሙሉ ለመገንዘብ አንችልም። ከእግዚአብሔር እይታ አንጻር ግን ደኅንነታችን የሚጀምረው ከእግዚአብሔር ምርጫ ነው። ከዚያም እግዚአብሔር ሁኔታዎችን በመቆጣጠር የመረጣቸውን ሰዎች ልጆቹ እንዲሆኑ ያደርጋል።

እግዚአብሔር እኛን ሲመርጥ ምን ነበር የፈለገው? ጳውሎስ እንደ ልጆቹ ሊያደርገን መፈለጉን ያስረዳል። ምናልባትም ጳውሎስ ስለ ሮም የማደጎ ልጅነት ልማድ እያሰበ ይሆናል። በሮምና በአይሁዶችም ዘንድ፥ አንድ ሰው አንድን ሕፃን በሕጋዊ መንገድ በማደጎነት ለማሳደግ በሚፈልግበት ጊዜ የሚከተለው የማደጎነት ሥርዓት ነበር። ልጁ ከባሪያዎቹ መካከል የአንዱ፥ የድሃ ጎረቤቱ ወይም የወዳጁ ሊሆን ይችላል። ልጁ ከወለዳቸው ልጆች እኩል የሆነ ሕጋዊ የልጅነትና የቤተሰቡ አባልነት መብት ይኖረዋል። ልጁ የማደጎ ልጅነትን መብት ካገኘበት ጊዜ አንሥቶ ከተወላጅ ልጆች ጋር እኩል መብትና የመውረስ ሕጋዊ መብት ይኖረዋል። እኛም ከእግዚአብሔር ቤተሰብ የራቅን የሰይጣን ልጆች ነበርን። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጸጋና ዘላለማዊ ፍቅር የተነሣ እግዚአብሔር ልጆቹ አድርጎናል። ስለሆነም፥ እኛም ከልጁ ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን (ሮሜ 8፡17)። ከመወለዳችን በፊት እንኳን እግዚአብሔር ልጆቹ፥ የመንግሥቱ ሕጋዊ ወራሾችና የመንግሥተ ሰማይ አባላት እንደምንሆን ወስኗል። በምድር ላይ ምንም ያህል ድሆች ብንሆንም፥ በሰማይ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ ልጆች ነን። ሰማያዊ ስፍራችን በምድር ላይ ካለው ከማንኛውም የንጉሥ ልጅ የላቀ ነው።

ጳውሎስ ለእግዚአብሔር ምርጫ ምን ያህል ትልቅ አጽንኦት እንደ ሰጠ ልብ በል። እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን ይህን ዕድል የሰጠን በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ ለጸጋው ክብር ምስጋና ነበር። እግዚአብሔር የመረጠን ልዩ ስለሆንን ወይም አንድን ታላቅ ተግባር ስላከናወንን አልነበረም። ይህ ምርጫ ከእግዚአብሔር ፈቃድ የመነጨ ነው። እግዚአብሔር የመረጠን ለእኛ ባለው ፍቅርና ለጸጋው ምስጋና ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የእግዚአብሔር ሕጋዊ ልጅ መሆን አስደናቂ የሚሆነው እንዴት ነው? ይህ ልጅነት የሚያስገኝልህን መልካም ዕድሎች ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር በቸርነቱ ልጁ እንድትሆን ስለመረጠህ አሁኑኑ አመስግነው።

ሐ. እግዚአብሔር በክርስቶስ ደም ዋጅቶናል፤ የኃጢአት ይቅርታም ሰጥቶናል። ቤዛ የሚለው ቃል ባሪያዎች ከሚሸጡበት ገበያ የተወሰደ ነው። በገበያ ላይ አንድ ሰው ለአንድ ባሪያ ካዘነለት ሊገዛውና ሰንሰለቱን ፈትቶ በነፃ ሊለቅቀው ይችል ነበር። ይህ ሰዎችን ነፃ ለማውጣት የሚካሄድ ግዥና ሽያጭ ቤዛነት ይባል ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ እኛም የኃጢአትና የሰይጣን ባሪያዎች እንደ ነበርን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ክርስቶስ ግን በሞቱ ለኃጢአታችን ዋጋ በመከፈል ሊገዛንና ነፃ ሊያወጣን ችሏል። በእግዚአብሔር ላይ የፈጸምነውን ኃጢአት ሁሉ ይቅር አለን። ይህ እግዚአብሔር በቸርነቱ በእኛ ላይ ያወረደው ጸጋ ምሳሌ ነው። ይህን ለምን አደረገ? ከፍቅሩ እንደ መነጨ ከመናገር በቀር ሌላ የምንረዳው ነገር የለም። ይህ የተደረገው የእግዚአብሔርን ታላቅ ጥበብና አሳቢነት በሚያሳይ መልኩ ነበር።

መ. እግዚአብሔር የፈቃዱን ምሥጢር አስታወቀን። በአዲስ ኪዳን «ምሥጢር» የሚለው ቃል የእግዚአብሔርን ስውር ምሥጢር ሳይሆን፥ ቀደም ሲል በከፊል ሳይገለጥ የቆየውንና አሁን ግን ለሰው ልጆች የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ነው። ጳውሎስ እግዚአብሔር እስከ አዲስ ኪዳን ዘመን ሳይገልጥ ያቆያቸውን ነገሮች ለመግለጽ በኤፌሶን ውስጥ ምሥጢር (ስውር) የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ ተጠቅሟል። በብሉይ ኪዳን ከተሰወሩትና አሁን ግን በጳውሎስ በኩል ከተገለጡት ምሥጢሮች አንዱ፥ እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ በክርስቶስ የመጠቅለሉ ጉዳይ ነው። ሰማይና ምድር ለእግዚአብሔር ክብር በሚሰጡበት መልክ ይዋሃዳሉ። ይሄ ሁሉ ግራ መጋባት፥ ኃጢአት፥ ዓመፅ ሁሉ ተወግዶ ሰማይና ምድር በኢየሱስ በኩል ለተፈጠሩበት ተግባር ይውላሉ።

ሠ. እግዚአብሔር በሉዓላዊ ምርጫው ለክብሩ ምስጋና መርጦናል። ከጥንቱ ዘመን የአዳዲስ ክርስቲያኖች ማስተማሪያ መጻሕፍት አንዱ፥ «የሰው የኋላ ኋላ መጨረሻው ምንድን ነው?» ሲል ይጠይቃል። መልሱ፥ «እግዚአብሔርን ማክበርና ለዘላለም በእርሱ ደስ መሰኘት» የሚል ነው። ድነት (ደኅንነት) ከእግዚአብሔር አንጻር ሲታይ ቀዳሚ ዓላማው እኛን ማዳን ሳይሆን፥ እግዚአብሔር እንዲመሰገን ነው። የዓመፀኛ ኃጢአተኞች መዳን በሆነ ምሥጢራዊ መንገድ ለእግዚአብሔር ታላቅ ክብርን ያመጣል። ሞት የሚገባን ኃጢአተኞች ሆነን ሳለ እግዚአብሔር እንዳዳነን ስንገነዘብ፥ እግዚአብሔርን ለአስደናቂ ሥራው እናመሰግነዋለን።

ረ. እግዚአብሔር ተስፋ በተገባው መንፈስ ቅዱስ አትሞናል። «እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለንን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ. . .»ጳውሎስ ስለ መጨረሻው መንፈሳዊ በረከት (ለእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ስለ መሰጠቱ) ከመናገሩ በፊት፥ ድነትን ከሰው እይታ አንጻር ይመለከታል። ስናምን ምን ይሆናል? ጳውሎስ በክርስቶስ ውስጥ እንደምንካተት ገልጾአል። በመንፈሳዊ ሁኔታ ከክርስቶስ ጋር እንዋሃዳለን። በክርስቶስ ውስጥ ሆነን እግዚአብሔር በሰማይ የሚሰጠንን በረከቶች ሁሉ እንቀበላለን። ጳውሎስ አስፈላጊው ነገር እምነት ብቻ ሳይሆን የምናምነው ነገር ጭምር መሆኑን አስረድቷል። እምነት ብቻውን አያድነንም። እምነታችን፥ በትክክለኛ ነገር ላይ ሊሆን ይገባል። ጳውሎስ «በእውነት ቃል» ማመን እንዳለብን ገልጾአል። የኤፌሶን ሰዎች አምነው የዳኑት በዚህ የወንጌል እውነት ነበር።

ጳውሎስ ማብራሪያውን እግዚአብሔር ከሚሰጠን እጅግ ጠቃሚ በረከቶች በአንዱ ይደመድማል። ይኸውም በእያንዳንዱ ክርስቲያን ልብ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ማደሩ ነው። ጳውሎስ ስለ መንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ያተኮረባቸውን ነገሮች አስተውል።

 1. ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ እንደ «ምልክት» ወይም እንደ ፊርማ መሆኑን አስረድቷል። በገዛነው መጽሐፍ ላይ ፊርማ ስናስቀምጥ መጽሐፉ የእኛ ንብረት እንደሆነና ማንም ሰው ያለ እኛ ፈቃድ ሊወስደው እንደማይችል መግለጻችን ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ እግዚአብሔርም መንፈስ ቅዱስን ሲሰጠን የእርሱ መሆናችንን ለሰዎች ሁሉ መናገሩ ነው።
 2. መንፈስ ቅዱስ ለውርሳችን ዋስትና የሚሰጥ መያዣ ነው። አንድ ሰው አንድን ነገር ለመግዛት ፈልጎ በቂ ገንዘብ በሚያጣበት ጊዜ ቀብድ ይከፍላል። ቀብዱ የቀረውን ገንዘብ አምጥቶ ዕቃውን እንደሚገዛ የሚያረጋግጥ የተስፋ ቃል ወይም መያዣ ሆኖ ያገለግላል። በሰዎች ዓቅም የቀረውን ገንዘብ ከፍሎ ዕቃውን መውሰዱ አስቸጋሪ የሚሆንበት ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እንደዚህ አይደለም። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ሲሰጠን አንድ ቀን ወደ መንግሥተ ሰማይ እንደሚያስገባን ተስፋ መግባቱ ነው። መዋጀታችንን የምናጠናቅቅበት ጊዜ ይሆንና በእግዚአብሔር መንግሥት ለእኛ የሚሰጠንን ርስት የምንወርስ ተካፋዮች እንሆናለን።

እግዚአብሔር ይህን ልዩ በረከት የሰጠን ለምንድን ነው? ጳውሎስ ለክብሩ ምስጋና እንደሆነ ይገልጻል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ ስለ መንፈስ ቅዱስ አገልግሎት የሰጠው ማብራሪያ ብዙውን ጊዜ እኛ ስለ መንፈስ ቅዱስ ከምናስበው እንዴት ይለያል? ለ) እግዚአብሔር ወደ ሰማይ እንደሚወስደን የሚያስረዳው የተስፋ ቃል በምድር ላይ ካሉን በረከቶች ሁሉ የሚልቀው እንዴት ነው፥

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የኤፌሶን መልእክት ዓላማ፣ ልዩ ባሕሪያት፣ መዋቅር እና አስተዋጽኦ

የኤፌሶን መልእክት ዓላማ

በድነት (ደኅንነት) ላይ ከሚያተኩረው የገላትያ መልእክት በተቃራኒ በኤፌሶን ውስጥ የቀረበ ዐቢይ የሐሰት ትምህርት ወይም ችግር አይታይም። የኤፌሶን መልእክት እግዚአብሔር ለአማኞች የሰጠውን በረከትና ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያብራራ የትምህርት መጽሐፍ ነው። በኤፌሶን ውስጥ ጳውሎስ ስለሚከተሉት ነገሮች ጽፎአል።

ሀ. ክርስቶስ በክፋት ኃይላት ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዳለውና ከሰይጣን ጥቃቶች የሚከላከሉ መንፈሳዊ የጦር መሣሪያዎች እንዳሉን (ኤፌ. 1፡20-22፤ 6፡10-18)። አንዳንድ ምሁራን ይህ የመንፈሳዊ ውጊያ ትምህርት የኤፌሶን ዋነኛ ርዕስ እንደሆነ ያስባሉ። የኤፌሶን አማኞች ቀደም ሲል ከፍተኛ የጣዖት አምልኮ ያካሂዱ ስለነበር የሰይጣንን ኃይል ይፈሩ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ የክርስቶስ ኃይል ከሁሉም ኃይላትና ሥልጣናት እንደሚበልጥ ገልጾላቸዋል። እንዲሁም ሁሉም ክርስቲያኖች ክርስቶስ የሰጣቸውን የጦር ዕቃዎች በመጠቀም ሰይጣንን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ያሳያቸዋል።

ለ. ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅድ እምብርት ነች። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን የክርስቶስ አካል (ኤፌ. 1፡23)፥ የእግዚአብሔር ቤተሰብ (ኤፌ. 3፡3)፤ ሕንፃ፤ ቅዱስ መቅደስ፥ የእግዚአብሔር ግዛት (ኤፌ. 2፡21-22)፥ ምሥጢር (ኤፌ. 3፡3)፥ ወዘተ. በማለት ይገልጻታል። ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር የመረጣቸው፤ የጠራቸውና በመንፈሳዊ ሁኔታ የባረካቸው ሰዎች ክምችት ነች። ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካልና (ኤፌ. 1፡22-23) ለታሪክ የወጠነው ዕቅድ መነሣሣት ናት። እግዚአብሔር ከቤተ ክርስቲያን በአይሁዶችና በአሕዛብ መካከል የነበሩትን ዓይነት የዘር ክፍፍሎች አስወግዷል። አማኞች የእግዚአብሔር ታላቅ ቤተሰብ አካል ናቸው። ሁሉን ቻዩ አምላክ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይኖራል (ኤፌ. 2፡19– 22)።

ሐ. እማኞች በክርስቶስ ያገኟቸው አስደናቂ በረከቶች። ከመዳናችን በፊት ተስፋ የሌለን፥ በኃጢአታችን የሞትንና ያለመታዘዝ ልጆች ነበርን (ኤፌ. 2፡1-4)። እግዚአብሔር ከጸጋው የተነሣ ክርስቶስን በመላኩ በእርሱ በማመን ከርኩሰትና ከቅጣት ነፃ ወጥተናል። አሁን፥ ለእግዚአብሔር ለመኖር የሚያስችል ኃይል እንዳለንና የበረከቶቹ ወራሾቹ እንደሆንን እናውቃለን (ኤፌ. 1፡3-12)። በክርስቶስ ስናምን የቀደመውን ኃጢአታችንን ለመሸፈን የሚያስፈልገንን ነገር፥ እግዚአብሔርን ለማስደሰትና ሰይጣንን ለማሸነፍ የሚያስችለንን ኃይል፥ እንዲሁም የወደፊቱን የበረከት ተስፋዎች እናገኛለን። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ስለሰጠን (ኤፌ. 1፡13)፥ ከኃጢአት መርገምና ከእስራት ወጥተን ወደ እግዚአብሔር ቀርበናል (ኤፌ. 2፡1-10)። አማኞች በአንድነትና በንጽሕና (ኤፌ. 4፡17-6፡9)፥ ወዘተ. ሊመላለሱ ይገባል።

መ. የእያንዳንዱ ክርስቲያንና ቤተ ክርስቲያን ዓላማ ለእግዚአብሔር ምስጋናና ክብር ማምጣት ነው (ኤፌ. 1፡6)።

ሠ. የእግዚአብሔር የመጨረሻ ግብ ክርስቶስን ማስከበርና በሰማይና በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ በእርሱ ሥልጣን ሥር ማዋል ነው (ኤፌ. 1፡10)።

ረ. አማኞች በሥራ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ዳኑ፥ የትኛውም ጎሳዊ ክፍፍል በክርስቶስ ሞት እንደ ተወገደና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስፍራ እንደሌለው ለማስታወስ (ኤፌ. 2፡11-22)።

ሰ. ሽማግሌዎች ክርስቲያኖች ሁሉ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉ በማገዙ በኩል የሚጫወቱት ሚና (ኤፌ. 4፡1-16)።

ሸ. የቤተሰቡ አባላት እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንዴት እርስ በርሳቸው ሊያያዙ እንደሚገባቸው ለማስተማር (ኤፌ. 4፡1፤ 5፡22-6፡9)።

የውይይት ጥያቄ፡– የቤተ ክርስቲያንህ አማኞች እነዚህን እውነቶች ማወቅና ተግባራዊ ማድረግ የሚያስፈልጋቸው እንዴት ነው?

የኤፌሶን መልእክት ልዩ ባሕርያት

 1. የኤፌሶን መልእክት ከቆላስይስ መልእክት ጋር በቅርብ የተዛመደ ነው። ሁለቱም በተመሳሳይ ጊዜ እንደ ተጻፉ ግልጽ ነው። የኤፌሶን ከ50 በመቶ የሚበልጡ ጥቅሶች በቆላስይስ ውስጥ ተደግመዋል። ቲኪቆስ የተባለ ግለሰብ ሳይሆን አይቀርም ሁለቱንም መልእክቶች ያደረሰው (ኤፌ. 6፡21፤ ቆላ. 4፡7-8)። የኤፌሶንም ሆነ የቆላስይስ መልእክቶች በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን ላይ ያተኩራሉ። የኤፌሶን መልእክት ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል መሆኗ ላይ ሲያተኩር፥ የቆላስይስ መልእክት ደግሞ ክርስቶስ የአካሉ ራስ በመሆኑ ላይ ያተኩራል።
 2. በዚህ መልእክት ውስጥ ስለ መንፈስ ቅዱስ እያሌ እውነቶች ተጠቅሰዋል። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፣ ቅዱስ (ኤፌ. 1፡13)፥ የጥበብ ምንጭና እውነትን ገላጭ ነው (ኤፌ. 1፡17፤ 3፡5)። መንፈስ ቅዱስ ሊያዝን (ኤፌ. 4፡30)፥ አማኞችንም ሊያትም (ኤፌ. 1፡13)፥ የአማኞች ውርስ መያዣ ሊሆን (ኤፌ. 1፡14)፥ ወደ እግዚአብሔር አብ የመቅረቢያ መንገድ ሊከፍት (ኤፌ. 2፡18)፥ ቤተ ከርስቲያንን ሊያንጽ (ኤፌ. 2፡22)፥ አማኞችን ሊሞላና ሊያበረታታ (ኤፌ. 3፡16፤ 5፡18)፥ ለአማኞች የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰጥ (ኤፌ. 6፡17) እና እንዲጸልዩ ሊረዳቸው ይችላል (ኤፌ. 6፡18)።
 3. ከሌሎች የጳውሎስ መልእክቶች በተቃራኒ፡ ይህንን መልእክት እንዲጽፍ ያነሣሣው ሁነኛ ምክንያት (የቤተ ክርስቲያን ወይም የአስተምህሮ ችግር) የለውም። ነገር ግን ለአማኞች ጠቃሚ መንፈሳዊ እውነቶችን ለማስተላለፍ የተጻፈ ነው።
 4. ጳውሎስ ከእነዚህ እውነቶች አብዛኞቹን በሁለት ታላላቅ ጸሎቶቹ አስተምሯል (ኤፌ. 1፡15-23፤ 3፡14-21)። እነዚህ ሁለት ጸሎቶች ለእርስ በርሳችን ለመጸለይ እንጠቀምባቸው ዘንድ የጸሎት ምሳሌዎች ሆነው ያገለግላሉ።

የኤፌሶን መልእክት መዋቅር

የኤፌሶን መልእክት እንደ አብዛኞቹ የጳውሎስ መልእክቶች በሁለት ክፍሎች የተከፈለ ነው። በመጀመሪያው ክፍል ጳውሎስ በእምነታችን ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድሩት መንፈሳዊ እውነቶች ላይ ትኩረት ሲያደርግ፥ በሁለተኛው ክፍል ደግሞ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንዴት መመላለስ እንዳለብን ያስተምራል።

 1. ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ጠቃሚ መንፈሳዊ እውነቶችን ያስተምራል (ኤፌ. 1-3)። እንደ አማኞች እኛ ማን ነን? ቤተ ክርስቲያን ምንድን ናት? እነዚህ በመጀመሪያዎቹ የኤፌሶን ሦስት ምዕራፎች ውስጥ መልስ የተሰጠባቸው ዐበይት ጥያቄዎች ናቸው። እንደ አማኞች፥ አስደናቂ መንፈሳዊ በረከቶች በሰማያዊ ስፍራ ተሰጥተውናል (ኤፌ. 1፡3)። እግዚአብሔር በሁሉም ዐበይት የሕይወታችን ክፍሎች በከፍተኛ ደረጃ ባርኮናል። ጠላቶቹ የነበርን ብንሆንም፥ ክርስቶስ እንዲሞትልን ልኮታል። በአስደናቂ ጸጋው አድኖናል።

ቤተ ክርስቲያን ምንድን ናት? ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ውስጥ የእግዚአብሔር ዋነኛ የትኩረት ስፍራ እንደሆነች አስረድቷል። እግዚአብሔር ታላቅ ክብር የሚያመጡለትን የአማኞች ማኅበረሰብ እየመሠረተ ነው። ይህም ማኅበረሰብ ከአይሁዶችና ከአሕዛብ ተውጣጥተው በክርስቶስ ያመኑ፥ ቅዱሳንና የተለዩ ሕዝብ የሚገኙበት ነበር። ይህ በፍቅር፥ አንድነትና ንጽሕና ተለይቶ የሚታወቅና ጎሳዊ እውቅና ከእንግዲህ ወዲህ የማይታይበት ማኅበረሰብ ነው።

 1. ጳውሎስ የኤፌሶን አማኞች እንደ የክርስቶስ አካል ክፍሎች እንዴት ሊመላለሱ እንደሚገባቸው ያስተምራል (ኤፌ. 4-6)። እግዚአብሔር የባረካቸው ሰዎች እንደ እግዚአብሔር ልጆች መኖር ይጠበቅባቸዋል። እኛ የአንድ አካል ወይም የአንድ ቤተስብ አባላት ስለሆንን፥ በፍቅርና በአንድነት ልንኖር ይገባል። እግዚአብሔር የአካሉን ክፍል በመንፈሳዊ ብስለት ለመገንባት ሲል ለመሪዎች ስጦታዎችን ይሰጣል። አማኞች ሰማያዊ አባታችንን የሚመስል የተቀደሰ ሕይወት መምራት ይኖርብናል። በዚህ ቤተሰብ ውስጥ በፍቅር፥ በሥርዓት፥ በአንድነትና በመቻቻል ልንኖር ይገባል። የክርስቶስንና የቤተ ክርስቲያንን ምሳሌ በመከተል ሚስቶች ለባሎቻቸው ሊገዙ፥ ባሎች ደግሞ ሚስቶቻቸውን ሊወዷቸው ይገባል። በሥራ ቦታ በሠራተኞች (ባሮችን) እና በቀጣሪዎች (ጌቶች) መካከል መከባበር ሊኖር ይገባል። በመንፈሳዊ ውጊያችን ደግሞ ክርስቶስ የሰጠንን የጦር መሣሪያ በመጠቀም ነቅተን ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባል።

የኤፌሶን መልእክት አስተዋጽኦ

 1. ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች፥ አማኞች በክርስቶስ ማን እንደሆኑና ቤተ ክርስቲያን ምን እንደሆነች ያስተምራል (ኤፌ. 1-3)፡፡

ሀ. መግቢያ (ኤፌ. 1፡1-2)

ለ. የእግዚአብሔር ልጆች መንፈሳዊ በረከቶች (ኤፌ. 1፡3-14)

ሐ. ጳውሎስ አማኞች እንደ እግዚአብሔር ልጆች ያላቸውን መንፈሳዊ ስፍራ እንዲረዱ ይጸልያል (ኤፌ. 1፡15-23)።

መ. ሙት የነበሩ የእግዚአብሔር ጠላቶች በጸጋው ሕያዋን ሆነው ድነዋል (ኤፌ. 2፡1-10)

ሠ. ሁሉም አማኞች ሰብአዊ ክፍፍሎች በማይታሰቡባት አንዲት ቤተ ክርስቲያን ተጠልለዋል (ኤፌ. 2፡11-22)

ረ. ጳውሎስ ስለ ክርስቶስና ቤተ ክርስቲያን የሚናገረውንና የእግዚአብሔር ምሥጢር የሆነውን ወንጌል ለማወጅ የተመረጠ አገልጋይ ነው (ኤፌ. 3፡1-13)

ሰ. ጳውሎስ አማኞች የክርስቶስንና ከእርሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነትና ታላቅነት ይረዱ ዘንድ እግዚአብሔር ጉልበት እንዲሰጣቸው ይጸልያል (ኤፌ. 3፡14-21)።

 1. ጳውሎስ የኤፌሶን አማኞች ለወንጌሉ እንደሚገባ ይመላለሱ ዘንድ ያደፋፍራቸዋል (ኤፌ. 4-6)።

ሀ. ለወንጌሉ እንደሚገባ መመላለስ ማለት እንደ አማኞች አንድነትን መፍጠርና እርስ በርሳችን መዋደድ ነው (ኤፌ. 4፡1-6)

ለ. እግዚአብሔር የአካሉ ክፍሎች እርስ በርሳቸው እንዲረዳዱና በብስለት እንዲያድጉ የተለያዩ ስጦታዎችን ሰጥቷቸዋል (ኤፌ. 4፡7-16)።

ሐ. እግዚአብሔር ልጆቹ በቅድስና በመመላለስ እርሱን እንዲመስሉ ይፈልጋል (ኤፌ. 4፡17-5፡20)

መ. እግዚአብሔር የቤተሰብ አባላቱ እርስ በርሳቸው እንዴት መዛመድ እንዳለባቸው አብራርቷል (ኤፌ. 5፡21–6፡9)።

ሠ. እግዚአብሔር ልጆቹ ራሳቸውን ከሰይጣን ጥቃቶች እንዲጠብቁና የድል ነሺነትን ሕይወት እንዲመሩ መንፈሳዊ የጦር ዕቃዎችን ሰጥቷቸዋል (ኤፌ. 6፡10-20)

ረ. የመጨረሻ ሰላምታ (ኤፌ. 6፡21-24)

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)