ዘጸአት 25-40
ከዘጸአት 25-40 ባሉት ክፍሎች ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ቀርበዋል። 1) እግዚአብሔርን የማምለኪያ ስፍራ የሆነው የመገናኛው ድንኳን እንዴት መሠራት እንዳለበት የሚናገረው መመሪያ ሰፊውን ክፍል ይዟል። ቀጥሎም የእስራኤል ሕዝብ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ተቀብለው እግዚአብሔር የሚኖርበትን የመገናኛ ድንኳን እንዴት እንደሠሩ ይናገራል። 2) በሁለተኛ ደረጃ የካህናትና የሊቀ ካህኑ አልባሳት እንዴት እንደተሠሩ የሚናገር ክፍል እናገኛለን። 3) ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ የጥጃን ምስል ሠርተው እንዴት እንዳመለኩ የሚናገር ክፍል እናገኛለን። የውይይት ጥያቄ፥ ዕብ. 8፡1-6፤ 9፡1-14 አንብብ። የዕብራውያን ጸሐፊ የቀድሞውን የመገናኛ ድንኳን ከክርስቶስ ሥራ ጋር በማወዳደር ያቀረበው እንዴት ነው? የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 25-40 አንብብ። ሀ) በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚገኙትን የተለያዩ ዕቃዎች ዝርዝር። ለ) ለመገናኛው ድንኳን የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሁሉ የሰጠው ማን ነበር? ሐ) እግዚአብሔር የመገናኛው ድንኳን እንዲሠራ ያዘዘበትን የተለያዩ ምክንያቶች ዘርዝር። መ) ሙሴ በተራራው ላይ በቆየበት ጊዜ እስራኤላውያን ምን ኃጢአት ሠሩ? ሠ) በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የሙሴ ታላቅ መንፈሳዊ መሪነት የተገለጠው እንዴት ነው? ፩. የመገናኛው ድንኳን እስከዚህ ጊዜ ድረስ እስራኤላውያን በመሠዊያ ላይ ያመልኩ ነበር። የየቤተሰቡ ኃላፊም ለቤተሰቡ እንደ ካህን ያገለግል ነበር። መሠዊያ ሠርቶ፥ በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር የሚሆን እንስሳ ይሠዋ ነበር። በምድሪቱ ውስጥ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ፥ ሌሎች መሠዊያዎችን ይሠራ ነበር። አሁን ግን እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ስለ መረጠና ለሕዝቡ የሚሆን ሕግ ስለ ሰጠ፥ የአምልኮ መንገዳቸውን ለወጠው። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር እርሱን የሚያመልኩበት የመገናኛ ድንኳን እንዲሠሩ አዘዛቸው። ሁለተኛ፥ አምልኮውን ይመሩ ዘንድ ካህናትን ለዚህ ሥራ ለየ። በዚህ በዘጸአት ባለው የተወሰነ ክፍልና በኦሪት ዘሌዋውያን ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለማምለክ እንዴት መቅረብ እንዳለባቸው የተጻፉ ትእዛዛት አሉ። የእስራኤል ንጉሥ በሆነው በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን ከተደረገና የእግዚአብሔር አገልጋዮችም ካጸኑት በኋላ፥ ሕዝቡ እግዚአብሔርን የሚያመልኩበት የመገናኛ ስፍራ ይሆን ዘንድ የመገናኛ ድንኳንን እንዲሠሩ አዘዘ። የመገናኛው ድንኳን እግዚአብሔር ራሱንና ፈቃዱን ለሕዝቡ የሚገልጥበትም ስፍራ ነበር። እግዚአብሔር እንዳለው «በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ» (ዘጸ. 25፡8)። የመገናኛው ድንኳን ዛሬ እንዳሉት ቤተ ክርስቲያኖቻችን ቋሚ ሕንጻ አልነበረም። እስራኤላውያን በሚሄዱበት ስፍራ ሁሉ በውስጡ ካሉት ዕቃዎች ጋር ይዘው ለመሄድ እንዲችሉ ተደርጎ የተሠራ ነበር። ቤተ መቅደሱ ቋሚ የማምለኪያ ስፍራ ተደርጎ በሰሎሞን የተሠራው ከ400 ዓመታት በኋላ ነበር። ስለ መገናኛው ድንኳን የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡- የመገናኛው ድንኳን አንድ ብቻ ነበር እንጂ እንደ አሕዛብ የማምለኪያ ስፍራ ብዙ አልነበረም። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በመገናኛው ድንኳን ብቻ እንዲያመልኩ አዘዛቸው። ይህም እስራኤላውያንን ከመኮብለልና ሐሰተኞች አማልክትን ከማምለክ ለመጠበቅ ነበር። የእስራኤል ሕዝብ የመገናኛውን ድንኳን ለመሥራት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን የመስጠት ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር። የእስራኤል ሕዝብ የመገናኛውን ድንኳን ለመሥራት ምን ያህል ከፍተኛ ጉጉት እንደነበራቸው የምናየው ለመሥሪያ ከሚያስፈልጉ ነገሮች በላይ በመስጠታቸው ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ሙሴ ሕዝቡን ከመስጠት እንዲቆጠቡ ይነግራቸው ነበር (ዘጸ. 36፡2-7)። የመገናኛው ድንኳን የሚገኘው በእስራኤላውያን ሠፈር መሐል ነበር። ይህም እግዚአብሔርን ማምለክ በሕይወታቸው ከሁሉ በላይ አስፈላጊ ነገር መሆኑን የሚያሳይ ነበር (ዘኁል. 2፡17)። የእግዚአብሔር መገኘት የተቀደሰ መሆኑንና ከኃጢአትም መለየቱን ለማመልከት፥ ከሕዝቡ በሐር መጋረጃ ተለይቶ ነበር። ለመገናኛው ድንኳን አራት የተለያዩ ክፍሎች ነበሩት። የመጀመሪያው፥ ከመገናኛው ድንኳን ውጭ ያለው ስፍራ ነው። ሰዎች እግዚአብሔርን ስለማምለክ አንዳችም ትኩረት ሳያደርጉ ሊመላለሱና ሊሠሩ የሚችሉበት ስፍራ ነው። ይህም ሕዝቡ የሚኖሩበት ስፍራ ነው። ሕዝቡን ከመገናኛው ድንኳን የሚለየው መጋረጃ ነበር። የመገናኛው ድንኳን እግዚአብሔር የሚያድርበትና እርሱ ሊመለክበት የሚገባ ስፍራ መሆኑ በግልጽ ታውቆ መከበር የሚገባው ነበር። በሁለተኛ ደረጃ፥ ውጫዊው ክፍል ወይም «አምልኮ የሚፈጽሙ ሰዎች ያሉበት ክፍል» የሚባል ስፍራ ነበር። በዚህ ክልል ለአምልኮ የሚያገልግሉ ሁለት ዋና ዋና ዕቃዎች ነበሩ። እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡ 1) የነሐስ መሠዊያ፡- መሠዊያው 2.5 ካሬ ሜትር ስፋትና 1 ሜትር ከፍታ ነበረው። እርሱም መሥዋዕቶች ሁሉ የሚቀርቡበት ትልቅ መሠዊያ ነበር። ማንኛውም ተራ ሰው ወደ እግዚአብሔር በመምጣት አምልኮ ለመፈጸም የሚችልበት ስፍራ ነበር። ከዚህ የበለጠ ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ ግን አይችልም ነበር። ከዚህ የበለጠ በመቅረብና ወደ መገናኛው ድንኳን ውስጥ በመግባት ለማምለክ የሚችሉት ካህናት ብቻ ነበሩ። 2) የነሐስ መታጠቢያ፡- ይህም የተሠራው ከነሐስ ሲሆን፥ በውስጡ ውኃ ይደረግበት ነበር። ካህናት ወደ ቅድስት በመግባት እግዚአብሔርን ከማምላካቸውና ከማገልገላቸው በፊት፥ ንጽሕና ከጎደላቸው ከማናቸውም ነገሮች መንጻታቸውን ለማሳየት፥ እግሮቻቸውን የሚታጠቡት በዚህ ውኃ ነበር። የውይይት ጥያቄ፥ ይኸው መንፈሳዊ መንጻት በዚህ ዘመን ላሉ መሪዎች የሚያስፈልገው እንዴት ነው? በሦስተኛ ደረጃ፥ የሚገኘው ስፍራ ቅድስት ተብሎ የሚጠራው ነው። በዚያ በሰፊው የመገናኛ ድንኳን ክልል ውስጥ አነስተኛ ድንኳን ነበር። ይህ ድንኳን ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፥ ሰፊው ክፍል ቅድስት ይባል ነበር። ቅድስት የተባለው ስፍራ እግዚአብሔር ለማገልገል ኃላፊነት ያለባቸው ካህናት በየዕለቱ አገልግሎታቸውን የሚፈጽሙበት ስፍራ ነበር። ቅድስት በተባለው ስፍራ ሦስት የአምልኮ ዕቃዎች ነበሩ። 1) በስተሰሜን በኩል የኅብስቱ መቀመጫ ወርቃማ ጠረጴዛ ነበር። የተሠራው ከግራር እንጨት ሲሆን በወርቅ ተለብጦ ነበር። በጠረጴዛው ላይ እያንዳንዳቸው አንዳንድ የእስራኤል ነገድ የሚወክሉ እርሾ የሌለባቸው አሥራ ሁለት ቂጣዎች ነበሩ። እነዚህ በየሳምንቱ እየተቀየሩ ካህናቱ ይበሏቸው ነበር። 2) በደቡብ የቅድስት ክፍል ደግሞ የወርቅ መቅረዝ ነበር። መቅረዙ ሰባት ቅርንጫፎች ነበሩት። በየጠዋቱና በየምሽቱ የሚሆነውን ነገር ለማድረግ ካህናቱ ይከታተሉ ነበር። መቅረዞቹም ሌሊቱን በሙሉ ሲበሩ ያድሩ ነበር። 3) በምዕራብ በኩል ቅድስትን ከተከታዩ ክፍል ከሚለየው መጋረጃ አጠገብ፥ ከወርቅ የተሠራ የዕጣን መሠዊያ ነበር። ይህ መሠዊያ ከነሐስ መሠዊያው የሚያንስ ሲሆን፥ 1.2 ካሬ ሜትር ቁመት ነበረው። በዕጣን መሠዊያው ላይ ካህናቱ በየቀኑ ጥዋትና ማታ ዕጣን ያጥኑበት ነበር። በአራተኛ ደረጃ፥ ቅድስተ ቅዱሳን የሚባል ስፍራ ነበር። ይህ አነስተኛ ክፍል ሲሆን፥ የያዘውም ታቦት ብለን የምንጠራውን አንድ የአምልኮ ዕቃ ብቻ ነበር። ይህ የእግዚአብሔር ዙፋን ስለነበር፥ ከመገናኛው ድንኳን ዕቃዎች ሁሉ የሚበልጥና የተቀደሰ ነበር። ታቦቱም ከግራር እንጨት የተሠራ ሆኖ በወርቅ የተለበጠ ነበር። ከ1 ሜትር ትንሽ የሚበልጥ ርዝመት ሲኖረው፥ 0.75 ሜትር ቁመትና ጎን ነበረው። ታቦቱ ክዳን ያለው ሳጥን ይመስል ነበር። በክዳኑ ጫፍና ጫፍ ላይ ክንፎቻቸው የሚያንዣብቡ የሚመስሉ ከወርቅ የተሠሩ የሁለት ኪሩቦች ምስል ነበረበት። ከሁለቱ ኪሩቦች ክንፎች በታች ያለው የክዳኑ ክፍል «የሥርየት መክደኛ» በመባል ይታወቅ ነበር። ምክንያቱም በዓመት አንድ ጊዜ እግዚአብሔር የሕዝቡን ኃጢአት ይቅር ይል ዘንድ ደም የሚረጨው በዚህ ስፍራ ላይ ስለነበር ነው። የእግዚአብሔር ክብር የሚያድረውም በሥርየት መክደኛው ላይ ነበር። ይህም ዙፋኑ ነበር። ከቅድስተ ቅዱሳን ንጉሥ ሆኖ እስራኤልን ያስተዳድር ነበር። ይህ የመገናኛው ድንኳን ክፍል እጅግ የተቀደሰ ስፍራ ስለነበር በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ወደ እርሱ የመግባት ሥልጣን ያለው ሊቀ ካህኑ ነበር። በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ዓሥርቱ ትእዛዛት የተጻፈበት ጽላት (ዘጸ. 25፡21)፥ መና ያለበት ማድጋ (ዘጸ. 16፡32-34) እና ያቆጠቆጠች የአሮን በትር (ዘኁል. 17፡10) ነበሩበት። ኋላም የእግዚአብሔር ሕግ የተጻፈበት መጽሐፍ በታቦቱ አጠገብ እንዲቀመጥ ተደረገ (ዘዳ. 31፡26)። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የመገናኛውን ድንኳን በመሥራት ረገድ ከምናየው ከፍተኛ ጥንቃቄና ሰፊ ተግባር ውስጥ የምንማራቸው አንዳንድ መንፈሳዊ መመሪያዎች ምንድን ናቸው? ለ) ከአራቱ ክፍሎች ውስጥ እግዚአብሔርን ስለ ማምለክ የምንማረው ነገር ምንድን ነው? አንዳንድ ክርስቲያኖች እነዚህ የአምልኮ ዕቃዎች ወደ ክርስቶስ ያመለክታሉ ይላሉ። ለምሳሌ፡- ሀ) የነሐስ መሠዊያው፥ ክርስቶስ በእኛ ምትክ መሥዋዕት የመሆኑ ምልክት ነው (ሮሜ 5፡8)። ለ) የነሐስ መታጠቢያው፥ ክርስቶስ ከኃጢአታችን እንደሚያነጻን ያመለክታል (1ኛ ዮሐ. 1፡9)። ሐ) የኅብስቱ ጠረጴዛ፥ ክርስቶስ የሕይወት እንጀራ መሆኑን ያመለክታል (ዮሐ. 6፡51)። መ) የወርቅ መቅረዙ፥ ክርስቶስ የዓለም ብርሃን የመሆኑ ምልክት ነው (ዮሐ. 8፡12)። ሠ) የዕጣን መሠዊያው፥ ክርስቶስ አማላጃችን መሆኑን ያመለክታል (ዕብ. 7፡25)። ረ) የቃል ኪዳኑ ታቦት ክርስቶስ ንጉሣችን መሆኑን ያመለክታል (ራእ. 19፤ 16)። ስለዚህ ጉዳይ የበለጠ ለመረዳት «ክርስቶስ በማደሪያው ድንኳን» የሚለውን መጽሐፍ ማጥናት ትችላለህ። የመገናኛውን ድንኳን ለመሥራት እግዚአብሔር ሁለት ሰዎችን መርጦ ኃይል አስታጠቃቸው። እነዚህ ሰዎች