አዲስ ሰማይና ምድር እና የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ተስፋ (ራእይ 21፡1–22፡21)

፩. አዲስ ሰማይና ምድር (ራእይ 21፡1–22፡6)

ስለ መንግሥተ ሰማይና በዚያ ሕይወት ምን እንደሚመስል የበለጠ ብናውቅ ደስ ባለን። ነገር ግን አብዛኛው ነገር ከእኛ የተሰወረ ነው። በዚህ ክፍል ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ መንግሥተ ሰማይ ምን እንደምትመስል በግልጽ ያሳየናል። እግዚአብሔር የተለያዩ ተምሳሌቶችን በመጠቀም የዘላለም ቤታችን ምን ያህል ውብ እንደሆነች እንድንገነዘብና ሕይወታችንን በሚገባ እያዘጋጀን እንድንኖር ያበረታታናል። ዮሐንስ የተለያዩ ምሳሌዎችን በመጠቀም ስለ ዘላለማዊ ቤታችን አንዳንድ ታላላቅ ነገሮችን ይነግረናል፡

ሀ. እግዚአብሔር አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርን ይፈጥራል። አሁን ያለ ነው በኃጢአት በተጨማለቀች ምድር ውስጥ ነው። ይሁንና አሁንም ለእኛ ውብ ናት። በኃጢአት ያልተበከሉ አዲስ ሰማይና ምድር ምን ያህል የበለጠ ያምሩ ይሆን!

ለ. እግዚአብሔርና ሰው ከመቼውም በበለጠ ቅርበት ኅብረት ያደርጋሉ። እግዚአብሔር ከሰው ጋር አብሮ ለመኖር ሲል ከሰማይ ወደ ምድር እንደሚመጣ በተምሳሌታዊ ቋንቋ ተገልጾአል። በዚህም እንደ ሃያ አራቱ ሽማግሌዎችና አራቱ እንስሳት እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ልናመልከው ስለምንችል፥ የቤተ መቅደስም ሆነ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ አያስፈልግም። ይህቺ እዲሲቱ ኢየሩሳሌም በዚህ ምድር ላይ ውድና ተፈላጊ ከሆኑት ነገሮች ሁሉ በላይ የደመቀች ናት። በመሆኑም በዚህ ምድር ላይ ውድ የሆኑት ነገሮች በዚያ ተራ ነገሮች ይሆናሉ። ጎዳናዎች በወርቅ ይነጠፋሉ። በሮች በከበሩ ማዕድናት ይሠራሉ።

ሐ. ለሐዘን ሊዳርገን የሚችል ምንም ዓይነት ነገር አይኖርም። እግዚአብሔር የጸጸትንና የሐዘንን እንባዎች ከዓይኖቻችንና ከአእምሮአችን በማበስ ለመቼውም እንዳናስታውሳቸው ያደርገናል። ኃጢአት፥ በሽታ፥ ሞት፥ ስደት፥ ማንኛውም ዛሬ ሥቃይን የሚያስከትልብን ነገር በዚያ አይኖርም።

መ. በእግዚአብሔር ላይ የሚያምጹ ሰዎች በዚያ አይኖሩም። ዮሐንስ ከእግዚአብሔር ዘላለማዊ ቤት ውጭ ያደርጉናል ብሎ የዘረዘራቸው ኃጢአቶች በዮሐንስ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ስደትን ለመሸሽ የሚፈተኑባቸው መሆናቸው አስገራሚ ነው። ለእምነታቸው ጸንተው ለመቆም ያልቻሉ ፈሪዎች፥ የከርስቶስን መሢሕነት ያልተቀበሉና ከእምነት የራቁ፥ የጠላትን ሐሰተኛ አምልኮ የተቀላቀሉ፥ እንዲሁም ወሲባዊ ኃጢአቶችን የፈጸሙና የጎደፉ ሰዎች ለቅጣት እንደሚጋለጡ ተገልጾአል።

ሠ. የክፋት ጨለማ ይወገድና የእግዚአብሔር ዘላለማዊ የመገኘቱ ብርሃን በሕዝቡ ላይ ያበራል።

ረ. ከተማይቱ ከማንኛውም አስጊ ነገር የጸዳች በመሆኗ በሮቿ አይዘጉም። ሌቦች ይመጡብናል ብሎ በር መዝጋቱ ያበቃል።

ሰ. ለእግዚአብሔር ንጹሕ አምልኮ ስለሚቀርብ በዘላለማዊ መንግሥት ውስጥ ያለ ሰው ሁሉ እግዚአብሔርን ለማምለክ ይመጣል። በኦሮጌዎቹ ሰማይና ምድር እንደነበረው ዐመፃ አይታሰብም።

ሸ. ከእግዚአብሔር አብና ወልድ በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለሚኖሩ አማኞች በረከቶች እንደማያቋርጥ የወንዝ ውኃ ይፈሱላቸዋል። እንዲሁም ከቶውንም የማይወድቅና እንደማይጠወልግ የሕይወት ዛፍ (ፈዋሽ ቅጠሎች ያሉት) የማያቋርጥ፥ ፈውስ ይመጣላቸዋል። ይህ ከበሽታ መፈወስን ሳይሆን፥ አሮጌዎቹ ሰማይና ምድር በሰዎች ላይ ዐመፀኛነቱን ከቀሰቀሱት ክፉ ነገሮች መፈወስን የሚያሳይ ነው።

ቀ. የእግዚአብሔር ቤተሰብ ለዘላለም ከእግዚአብሔር አብና ወልድ ጋር ይነግሣሉ። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ እስጨናቂ የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች መንግሥተ ሰማይን እንድትናፍቅ የሚያደርጉህ እንዴት ነው? ለ) እነዚህ የተስፋ ቃሎች ዛሬ ለኢየሱስ ክርስቶስ ታማኞች እንድንሆን የሚያበረታቱን እንዴት ነው?

፪. የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ተስፋ (ራእይ 22፡7-21)

የዮሐንስ ራእይ የመጽሐፉ መሠረት በሆኑት እውነቶች ይጠናቀቃል። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ በቶሎ እንደሚመለስ ለተከታዮቹ ያስገነዝባቸዋል (ራእይ 22፡7፥ 12)። ስለሆነም፥ ዳግም ምጽአቱን በናፍቆት መጠባበቅ ይኖርብናል። ዮሐንስ፥ መንፈስ ቅዱስና ሙሽራይቱ (ቤተ ክርስቲያን) ዳግም ምጽአቱን በመናፈቅ «ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ቶሎ ና» ሲሉ ይጸልያሉ። ማናችንም ክርስቶስ መቼ እንደሚመለስ አናውቅም። እስከ ዛሬ ሁለት ሺህ ዓመታት ቢቆጠሩም፥ ጌታ ገና አልተመለሰም። ነገር ግን ለእግዚአብሔር «በቶሎ» ማለት እኛ የምናስበው ዓይነቱ ቶሎ ላይሆን ይችላል። (2ኛ ጴጥ. 3፡8 አንብብ)። ነገር ግን እያንዳንዱ የአማኞች ትውልድ የክርስቶስን ምጽአት ሊጠባበቅና በቶሎ እንደሚደርስ ተስፋ ሊያደርግ ይገባል።

ሁለተኛ፥ ክርስቶስ ተከታዮቹ አኗኗራቸውን ከዳግም ምጽአቱ እውነታ አንጻር እንዲያስተካክሉ ያስጠነቅቃል። የዮሐንስ ራእይ የተሰጠው ወደፊት የሚሆነውን ብቻ ሳይሆን፥ በመጽሐፉ ውስጥ የተገለጹትን የትንቢት ቃሎች እንድንጠብቅ ጭምር ነው። እነዚህ በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ልናደርጋቸው የሚገቡ እውነቶች ናቸው። የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ልብሳችንን አጥበን ማንጻታችንን ማረጋገጥ አለብን። ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ማመናችንን የሚያመለክት ነው። እንዲሁም እምነታችንን ባለመደበቅ ወይም ባለመካድ፥ ሐሰተኛ አምልኮን ባለመከተልና የዓለማውያንን የተሳሳቱ ልምምዶች ተግባራዊ ባለማድረግ በቅድስና ልንመላለስ ይገባል። እነዚህ ዓለማውያን የእግዚአብሔር በረከቶች ተካፋይ እንደማይሆኑ ግልጽ ነው።

ሦስተኛ፥ ለማያምኑ ሰዎች የተሰጠ መልእክት። ክርስቶስ እስከሚመለስና ፍርድ እስከሚጀምር ድረስ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ጥማት ላደረባቸው ሰዎች ድነትን (ደኅንነትን) ይሰጣቸዋል። የዘላለም ሕይወት ውኃ ነፃ ነው። ይህን ለማግኘት ሰዎች ዋጋ መክፈል አያስፈልጋቸውም። አንድ ሰው ሊያደርግ የሚገባው ነገር ቢኖር ወደ ክርስቶስ ተመልሶ በእርሱ ማመን ነው። ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ ባላቸው ዐመፀኛነት ቢቀጥሉ፥ በዮሐንስ ራእይ ውስጥ ለተጠቀሱት መቅሰፍቶች ፍርድ ይጋለጣሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ሦስት መልእክቶች እግዚአብሔር የሰጠን እጅግ ጠቃሚ መልእክቶች የሚሆኑት ለምንድን ነው? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ እነዚህን ሦስት መልእክቶች ለአማኞችና ለማያምኑ ሰዎች እያደረሰች ያለችው እንዴት ነው? ሐ) ከዮሐንስ ራእይ ያገኘሃቸው ሌሎች ጠቃሚ ትምህርቶች ምን ምንድን ናቸው? 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የክርስቶስ የሺህ ዓመት ንግሥና (ራእይ 20፡1-15)

፩. የክርስቶስ የአንድ ሺህ ዓመት ንግሥና (ራእይ 20፡1-6)

ከክርስቶስ ጠላቶች መደምሰስ በኋላ የዮሐንስ ራእይ ስለ ዘላለማዊ መንግሥት አጀማመር ይነግረናል ብለን እንጠብቃለን። ነገር ግን በመጽሐፉ ውስጥ የምናገኘው ክርስቶስ ለአንድ ሺህ ዓመታት በምድር ላይ እንደሚነግሥ የሚያስረዳውን ክፍል ነው። የዮሐንስ ራእይ በተምሳሌቶች የተሞላ መጽሐፍ በመሆኑ፥ ብዙ አማኞች የሺህ ዓመቱ መንግሥት ክርስቶስ በምድር ላይ በአማኞች ልብ ውስጥ፥ በሰማይ ደግሞ በቅዱሳን ሕይወት መንገሡን የሚያመለክት ነው ይላሉ። ነገር ግን ይህ ክፍል መሢሑ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ለአንድ ሺህ ዓመታት በቀጥታ የሚነግሥ መሆኑን የሚያሳይ ይመስላል።

እግዚአብሔር የዘላለምን መንግሥት ከመጀመሩ በፊት ለሺህ ዓመታት በምድር ላይ ለመግዛት የፈለገበትን ምክንያት አናውቅም። ነገር ግን ሁለት ሊሆኑ የሚችሉ ምክንያቶች አሉ። በመጀመሪያ፥ በብሉይ ኪዳን ነቢያት የተነገሩና እንደ ዳዊት ካሉ ሰዎች ጋር የተደረጉ አብዛኞቹ ቃል ኪዳኖች ክርስቶስ በምድር ላይ የሚነግሥ መሆኑን ያሳይሉ። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር በተለይ ለአይሁዶችና በአጠቃላይ ለሰዎች ሁሉ እነዚህን የተስፋ ቃሎች ለማሟላት የክርስቶስን የምድር ላይ መንግሥት ይመሠርታል። ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር የሰዎችን ልብ ክፋት ለማሳየት ይፈልጋል። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ክፋትን የሚማሩት ከእነርሱ ውጭ የሆነ ነገር ወደ ከፋት ስለሚመራቸው ነው ብለን እናስባለን። ሰዎች ከወላጆቻቸው፥ ከባህላቸው፥ ወዘተ… ክፋትን ይማራሉ ብለን እናስባለን። ነገሮች ሁሉ መልካም ቢሆኑ፥ በምድር ላይ እውነተኛ ፍቅር ቢኖር፥ ሰዎች ሁሉ ቢማሩ፥ ሰዎች እግዚአብሔርን በማክበር በትክክለኛው መንገድ ይኖራሉ ብለን እናስባለን። ይህ ግን እውነት አይደለም። የሰው ልብ ክፉ ስለሆነ ሁልጊዜም የእግዚአብሔርን አገዛዝ ይቃወማል (ኤር. 17፡9)። ይህም በዚህ ክፍል ውስጥ በግልጽ ተመልክቷል። ምንም ዓይነት ባህላዊ፥ ወላጃዊ ወይም ማኅበራዊ ክፋቶች ለማማሃኛነት ሊጠቀሱ በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ (ክርስቶስ በጽድቅ ነግሦ ሳለ) ሰዎች አሁንም በእግዚአብሔር ላይ ያምጻሉ። ምናልባትም ታላቁን መከራ ካለፉት ክርስቲያኖች የተወለዱ ልጆች ከዚሁ የክርስቶስ የሺህ ዓመታት መንግሥት ፍጻሜ ላይ ማመጽ ይጀምራሉ። ወዲያውኑ ሰይጣን እንደ ተፈታ ከእርሱ ጋር በመተባበር ከእግዚአብሔር ጋር ይዋጋሉ። የሰው ልጅ ምንኛ ክፉ ነው! 

የውይይት ጥያቄ፡- የእግዚአብሔር ልጅ ብትሆንም እንኳን የልብህን ክፋት እንዴት እንደተመለከትህ ግለጽ። ይህ ስለ እግዚአብሔር ምሕረት ታላቅነት ምን ያስተምረናል?

ዮሐንስ የተለያዩ ቡድኖችንና ክርስቶስ በምድር ላይ ለመግዛት ከሰማይ በሚመለስበት ጊዜ በእነርሱ ላይ ስለሚሆኑት ነገሮች ያብራራል።

ሀ) ሰይጣንና ተከታዮቹ አጋንንት ሺህ ዓመታት ወደ ጥልቁ ወርደው ይታሰራሉ። ይህም ጥልቁ ጉድጓድ ክፉ መናፍስት የሚታሰሩበት ነው። በዚያም በእስር ቤት ሰዎች ኃጢአትን እንዲሠሩና በመሢሃቸው ላይ እንዲያምጹ ሊያደርጉ አይችሉም።

ለ) የተሠዉ አማኞችና በዘመናት ሁሉ የኖሩ ክርስቲያኖች ከሞት ተነሥተው የትንሣኤን አካል ይለብሳሉ። በታላቁ መከራ ጊዜ ያልሞቱና በሕይወት ያሉ አማኞችም ተለውጠው ከእነዚሁ ክርስቲያኖች ጋር ይሆናሉ (1ኛ ቆሮ. 15፡51-54)። አማኞቹ በእግዚአብሔር ተከብረው ከክርስቶስ ጋር በምድር ላይ ይነግሣሉ። (ማስታወሻ፡ በዮሐንስ ራእይ ውስጥ ሁሉ ዮሐንስ በሰማዕትነት ባለፉት አማኞች ላይ አጭር ማስታወሻ ይሰጣል። ይህንንም ያደረገው አማኞች በቆራጥነት ስደትን እንዲጋፈጡና ያለ ፍርሃት ለእምነታቸው እንዲሞቱ ለማበረታታት ነው። መከራን የሚቀበሉ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር እንደሚያከብራቸው ማስታወስ ይኖርባቸዋል። ምንም እንኳ ለጊዜው ክፉ ሰዎች ሁኔታዎችን በመቆጣጠር ላይ ቢሆኑም፥ እነዚህ መከራን የተቀበሉ አማኞች የሚነግሡበት ቀን ይመጣል። ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በግልጽ እንደሚታየው፥ አማኞች ሁሉ ከሞት ተነሥተው ከክርስቶስ ጋር ይነግሣሉ (1ኛ ተሰ. 4፡13-18፤ 2ኛ ጢሞ. 2፡12፥ ራእይ 5፡9-10)። ከክርስቶስ ትምህርት እንደምንመለከተው፥ በዚህ ምድራዊ ንግሥና እያንዳንዱ አማኝ የሚኖረው ሥልጣን አሁን እርሱን በምናገለግልበት ጊዜ ባለን ታማኝነት ላይ ይመሠረታል (ማቴ. 25፡14-30)። ዮሐንስ የአማኞችን ትንሣኤ የመጀመሪያው ትንሣኤ ሲል ይጠራዋል። ወደ ሲዖል መውረድን ደግሞ ሁለተኛው ሞት ሲል ይጠራዋል። ክርስቶስን በታማኝነት የሚከተሉ ሰዎች የዚህ የመጀመሪያው ትንሣኤ አካል ከመሆናቸው በተጨማሪ፥ በሁለተኛው ሞት ወደ ሲዖል እንደማይወርዱም ተገልጾአል።

ሐ) በሁሉም ዘመን የሞቱ ሰዎች ገና ከሞት አይነሡም።

፪. የሰይጣን መፈታትና የሰው ልጆች ዐመፅ (ራእይ 20፡7-15)

ሁላችንም የአዳምንና የሔዋንን ታሪክ እናውቃለን። በምርጥ ስፍራ ሲኖሩ ሳለ ሰይጣን በፈተናቸው ጊዜ ለማመጽ መርጠዋል። እኛ ግን ክርስቶስ በመካከላችን ቢኖር እንዲህ ዓይነት ኃጢአት እንፈጽምም ብለን ልናስብ እንችላለን። ይሁንና ኃጢአት መፈጸማችን የማይቀር ነው። ዮሐንስ የሰው ልጅ እንዴት ሁልጊዜም በእግዚአብሔር ላይ እንደሚያምጽ ያሳያል። ሰይጣን ከእስራቱ ከተፈታ በኋላ በቀላሉ የዓለም ሰዎች እንዲያምጹ ያደርጋል። እነዚህ ሰዎች ለሕይወት የሚያስፈልጉ ቁሳዊ በረከቶች ሁሉ በተሟሉባት የክርስቶስ የጽድቅ መንግሥት ውስጥ ይኖሩ ነበር። ይሁንና አሁንም ሰይጣንን ለመከተል መረጡ። ክርስቶስ የንግሥናው መዲና አድርጎ ወደ መረጣት ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ እየገሰገሰ ሳለ ክርስቶስ በራእይ 19 ጠላቶቹን እንዳሸነፈ ሁሉ በቀላሉ ያሸንፋቸዋል። የሚገርመው እነዚህ ሰዎች ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት ከተገለጸው የክርስቶስ ኃይል አለመማራቸው ነው። ዮሐንስ የዘላለም መንግሥት ከመጀመሩ በፊት ለእነዚህ የተለያዩ ቡድኖች ስለሚሆነው ሁኔታ ይገልጻል፡

ሀ) ሰይጣን ወደ እሳት ባህር ይወረወራል። እዚያም ለዘላለም ስለሚታሰር ከእንግዲህ ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ እንዲያምጹ የሚያደርግበትን ዕድል አያገኝም። ይህ የእሳት ባህር ወይም ሲዖል የእግዚአብሔር ጠላቶች ለዘላለም የሚቀጡበት ስፍራ ነው። ለሲዖል በመጽሐፍ ቅዱስ ከምንመለከታቸው ነገሮች ምን ያህሎቹ ተምሳሌታዊ ምን ያህሎቹ ደግሞ ቀጥተኛ እንደሆኑ እናውቅም። ነገር ግን አራት ነገሮችን እናውቃለን። 1. ሲዖል ለዘላለም የሚቀጥል ነው። ይህ ሰዎች ከኃጢአታቸው ጸድተው የሚወጡበት የመቆያ (ፐርጋቶሪ) ስፍራ አይደለም። 2. ሰዎች ወደ ምንምነት ወይም አዕምሮአቸውን ወደማያውቁበት ሁኔታ ውስጥ አይሆኑም። ሕይወት ያላቸውና ያሉበትን ሁኔታ የሚያውቁ ይሆናሉ። 3. ይህ ጥልቅ ሥቃይና መከራ የሚበዛበት ስፍራ ነው። እዛ ያሉት ሁሉ በጣም ይሠቃያሉ። 4. ሲዖል ምንም ዓይነት የእግዚአብሔር በረከት የሌለበት ስፍራ ነው። ከእግዚአብሔር ምሕረትና ፍቅር ደስታ የሚያመልጡልን ነገሮች ሁሉ በዚያ አይኖሩም።

ለ) ሙታን ከሞት ተነሥተው በታላቁ ነጭ ዙፋን ፊት ይቆማሉ። ምሁራን እነዚህ እነማን ናቸው በሚለው ጉዳይ ላይ ይከራከራሉ። የክርስቶስ የፍርድ ወንበርና ታላቁ ነጭ ዙፋን አንድ ናቸው ወይስ የተለያዩ? አንድ ከሆኑ፥ ይህ ታላቁ የነጭ ዙፋን ፍርድ ለአማኞችም ለማያምኑ ሰዎችም መሆኑ ነው። የተለያዩ ከሆኑ፥ ይህ ፍርድ የሚሰጠው ለማያምኑ ሰዎች ብቻ ይሆናል። በራእይ 20፡5 የተገለጸው ትንሣኤ (ሌሎች የአዲስ ኪዳን ክፍሎች የሚጠቅሱት) አማኞችን ሁሉ የሚያካትት ከሆነ፥ ሌሎችም የአዲስ ኪዳን ክፍሎች እንደሚጠቁሙን በነጭ ዙፋን ፊት የቆሙት ቀደም ሲል ለሕይወት ያልተነሡ ዓለማውያን ሊሆኑ ይችላሉ።

(ማስታወሻ፡ ይህ እውነት ከሆነ፥ ከዚህ ቀደም ብሎ የአማኞች የምድር ላይ ሕይወት የሚገመገምበትና ሰማያዊ ሽልማት የሚያገኙበት ጊዜ ይኖራል። ጳውሎስ ይህንን የክርስቶስ የፍርድ ወንበር ሲል ይጠራዋል። 1ኛ ቆሮ. 3፡11–15 አንብብ። ይህ ፍርድ ድነትን (ደኅንነትን) የሚመለከት አይደለም። ነገር ግን የአንድ አማኝ ሕይወት በማይጠቅሙ ነገሮች ለምሳሌ፡- ገለባ፥ እንጨት፥ ወይም በሚጠቅሙ ነገሮች ለምሳሌ፡- ወርቅ፥ ብር፥ የከበሩ ድንጋዮች መሟላቱን ለማረጋገጥ የተሰየመ ችሎት ነው። ለእግዚአብሔር የምናደርገው ነገር ጠቃሚ መሆን አለመሆኑ የሚወሰነው ክርስቶስን በምናገለግልበት ጊዜ ባለን ዓላማና አመለካከት ላይ ነው። በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው እጅግ ታላቅ፥ ኃያልና ቅዱስ በመሆኑ፥ በተምሳሌታዊ አገላለጽ ፍጥረት ሁሉ ከፊቱ ሊቆም አይችልም። ፈራጁ እግዚአብሔር አብና ወልድ ይመስላል (ራእይ 22፡1፥3)። የፍርዱ መሠረት ምንድን ነው? ፍርዱ የሚሰጠው በሁለት መጻሕፍት ላይ ተመሥርቶ ነው፡–

ሀ. የሕይወት መጽሐፍ፡ ይህ የሰማይ ዜጎችን ስም የሚዘረዝር መጽሐፍ ነው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው በዘመናት ሁሉ ያመኑት ሰዎች ስም ብቻ ነው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ስማቸው የተጻፈላቸው ሰዎች የመንግሥተ ሰማይ ነዋሪነትና የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ስማቸው ያልተጻፈላቸው ሰዎች ወደ ሲዖልና ዘላለማዊ ሞት ይላካሉ።

ለ. የሰዎችን ተግባራት የሚገልጹ መጻሕፍት፡ አንድ ሰው በምድር ላይ በኖረበት ሁኔታ ላይ ተመሥርቶ በሰማይ ለአማኞች የሚሰጡ ሽልማቶች በደረጃ እንደሚለያዩ ሁሉ፥ ለኃጢአተኞችም በምድር ላይ ሳሉ በፈጸሟቸው ተግባራት ላይ የተመሠረቱ የተለያዩ ፍርዶች የሚሰጡ ይመስላል። እንደ ሂትለር ሰይጣን የላቀ ክፋት ለመፈጸም የተጠቀመባቸው ሰዎች ክርስቶስን አልከተልም እያለ ዳሩ ግን መልካም ሕይወት ከመራ ሰው የባሰ ቅጣት ይጠብቃቸዋል። ነገር ግን መልካም ሕይወት መምራቱ ብቻ ሰውን ስሙ በመንግሥተ ሰማይ ዜጎች መዝገብ ውስጥ እንዲሰፍር አያስችለውም። የማያምኑ ሰዎች ሁሉ ሁለተኛው ሞት ለተባለው ዘላለማዊ የሲዖል ፍርድ ይጋለጣሉ። በዚህ ስፍራ ሞት የሚያመለክተው የሕልውናን ፍጻሜ ሳይሆን ከእግዚአብሔር መለየትን ነው። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት ለሚተዉ ሰዎች እንዴት ጠንካራ ማስጠንቀቂያ እንደሚሆን ግለጽ። ለ) ይህ ለማያምኑ ሰዎች ምን ማስጠንቀቂያ ይሰጣል? 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የክርስቶስ ምጽአት (ራእይ 19:1-21)

፩) በሰማይ ያሉት ለባቢሎን ውድመት የሰጡት ምላሽ (ራእይ 19፡1-10)

በራእይ 18 ዮሐንስ ዓለማውያን ለባቢሎን መደምሰስ የሰጡትን ምላሽ ገልጾል። ለእነርሱ ይህ የሐዘን ጊዜ ነበር። ምክንያቱም የወደዷቸው ነገሮች፥ ኃይልና ክብራቸው ሁሉ ወድሟልና ይህም ቁሳዊ ሀብት የሚያመጣው ነው። በራእይ 19፡1-10 ግን በሰማይ ለባቢሎን መደምሰስ የተሰጠው ምላሽ ተገልጾአል። ዮሐንስ በተለያዩ ሰዎች እግዚአብሔር በባቢሎን ተምሳሌትነት ለተገለጸው የዓለም ላይ ክፋት ፍርዱን ስለገለጸ ደስ ተሰኝተው ያመሰግኑታል።

ሀ) በሰማይ የታዩ እጅግ ብዙ ሕዝብ ቀደም ሲል በራእይ 7፡9-17 የተገለጹት አማኞች ናቸው። በእነዚህ ውስጥ ቀደም ሲል ታላቁ መከራ ተብሎ በሚጠራው የመከራ ጊዜ የሞቱ አማኞች ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች ለእምነታቸው በሰማዕትነት ያለፉ ናቸው። ለሞት አሳልፈው የሰጧቸው ክፉ ሥርዓቶች (ፖለቲካዊ፥ ሃይማኖታዊ፥ ኢኮኖሚያዊ) ሲወድሙ በማየታቸው አማኞቹ ደስ ተሰኝተው እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል። ይህ በተጨማሪም ራሳቸውን በንጽሕና የጠበቁና የዓለም ፍቅር እንዳይቆጣጠራቸው ያደረጉ እውነተኛ አማኞች ሁሉ የሚሰጡት ምላሽ ምልክት ነው። ፍትሕ ሊሰፍን ደስ ይሰኛሉ።

«ሃሌሉያ» የሚለው ቃል ከአይሁድ የአምልኮ ሥርዓት ተወስዶ ሳይተረጉም በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተቀመጠ ነው። የቃሉ ትርጉም «ጌታ ይመስገን» የሚል ነው። የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ያልተለመደ ደስታ ሲገጥማት ወይም በአምልኮ ጊዜ ይህንን ቃል ትጠቀም ነበር። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች ይህንን ቃል በተደጋጋሚ ይጠቀማሉ። ይህ ቃል የመንፈሳዊነት ወይም የልዩ ኃይል ምልክት የሆነ ይመስል ደጋግመን እንጠቀምበታለን። ምንም እንኳን ለአማኞች ትርጉሙን ካወቅነው ይህንን ቃል መጠቀሙ መልካም ቢሆንም፥ እነዚህ ቃላት የመንፈሳዊነት ምልክቶች ወይም በጸሎት ጊዜ ልንጠቀምባቸው የሚገቡ ምትሃታዊ ቃላት እንደሆኑ ማሰብ የለብንም። የደስታ ስሜታችን በተፈጥሯዊ መንገድ ሃሌሉያ ወይም እልል በማለት ራሱን ከገለጸ መልካም ነው። ይሁንና፥ ተራ አገላለጽ ተጠቅመው «ጌታ ይመስገን» ለማለት የሚመርጡትን ሌሎች አማኞች መኮነን የለብንም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንዳንድ ሰዎች በተደጋጋሚ ሃሌሉያ እያሉ የሚጮሁት እንዴት ነው? ለ) ሰዎች ይህንን ቃል የሚጠቀሙት ትርጉሙን ተረድተውና አግባብነትን ጠብቀው ነው ወይስ የበለጠ መንፈሳዊ ወይም ለጸሎታቸው ኃይል እንደሚሰጥ በማሰብ?

ለ) ሃያ አራቱ ሽማግሌዎችና አራቱ እንስሶችም እግዚአብሔርን ላከናወነው ተግባር ያመሰግኑታል።

ሐ) ሁለተኛው እጅግ ብዙ ሕዝብ። ይህ ሕዝብ ምናልባትም በዘመናት ሁሉ ድነትን (ደኅንነትን) ያገኙ ሰዎች ክምችት ሳይሆን አይቀርም። እነርሱም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል። የደስታቸውም ምንጭ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ መንገሡ ነው። ከእንግዲህ በሰማያት ያሉ ጠላቶች (ሰይጣን) አገዛዙን አይዋጉም። በምድር ላይም ያሉ ቢሆን አገዛዙን የሚቃወሙ (ለምሳሌ፥ መንግሥታት) ጠላቶች አይኖሩም። በሰማይና በምድር ያለው ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር አገዛዝ በመስገድ ትክክለኛ ሚናቸውን ይጫወታሉ። ይህ ሕዝብ የሚደሰትበት ሌላው ምክንያት ደግሞ የበጉ ሠርግ መቅረቡና ሙሽራይቱም ራሷን ማዘጋጀቷ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የነበሩትን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከሙሽራ ጋር ያነጻጽራል (ሆሴዕ 2፡19-20፤ 2ኛ ቆሮ. 11፡2)። አይሁዶች የመሢሑ መንግሥት የሚጀምረው በታላቅ ግብዣ እንደሆነ ያምኑ ነበር (ማቴ. 25፡1-13)። ዮሐንስ ይህንኑ ምሳሌ በዚህ ስፍራ ይጠቀማል። ነገር ግን ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ገና ለክርስቶስ እንደ ታጨች እንጂ እንዳገባችው አልገለጸም። ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከሞተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ጋብቻው አልተፈጸመም። ቤተ ክርስቲያን ለጋብቻ እየተዘጋጀች እንዳለች ሙሽራ ነች። ነገር ግን እግዚአብሔር ባቢሎንን ሲያጠፋና ክርስቶስም መግዛት ሲጀምር፥ በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ ንጹሕና የጠለቀ ይሆናል። በተምሳሌታዊ መልኩ ክርስቶስ ሙሽራ፥ ቤተ ክርስቲያን ሙሽራይቱ፥ እንዲሁም በመካከላቸው ያለው ግንኙነት እግዚአብሔር እንዳቀደው ንጹሕ ይሆናል። በሕይወታችን ውስጥ የኃጢአት መሰናክል ሳይኖር ክርስቶስን ፊት ለፊት እናየዋለን። ያ የጋብቻ ሥርዓት ጊዜ በምድር ላይ ከተደረጉት ከየትኞቹም የጋብቻ ባህሎች የላቀ ይሆናል።

ዮሐንስ አማኞች ዛሬ ለዚሁ ጋብቻ መዘጋጀት እንዳለባቸው ያስገነዝበናል። ቀጭንና ነጭ የተልባ እግር መልበስ ይኖርብናል። ይህ ተምሳሌት ሁለት ጠቃሚ እውነቶችን ያመለክታል። በመጀመሪያ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመናችን እግዚአብሔር ጻድቃን ናችሁ ብሎናል። ለዚህም ነው ሰዎች የተልባ እግሩን ራሳቸው ያላዘጋጁትና ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበሉት። ሁለተኛ፥ ዮሐንስ ድነንት (ደኅንነትን) እንዳገኙ ሰዎች እንዴት መመላለስ እንዳለብን ያስጠነቅቀናል። በሕይወታችን ውስጥ ካለው ክፋት ሁሉ ተላቅቀን ለእጮኛችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብርን የሚያመጡትን ነገሮች ማድረግ ይኖርብናል።

በዮሐንስ ራእይ መጨረሻ አካባቢ ዮሐንስ ሁለት ጊዜ መላእክትን ሊያመልክ ሲሰግድና ዳሩ ግን ይህንኑ እንዳያደርግ ሲከለክል እንመለከታለን (ራእይ 19፡10፤ 22፡8-9)። በቀድሞዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከተስፋፉት ሐሰተኛ ትምህርቶች አንዱ መላእክትን ማምለክ ነበር (ቆላ. 2፡18) አንብብ። ይህም ዛሬ በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚታይ ሁኔታ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር መላእክት ማን እንደሆኑና መላእክትን ማምለኩ ለምን ትክክለኛ ተግባር እንዳልሆነ እንድንገነዘብ ይፈልጋል። መላእክት በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ከእኛ የበለጡ አይደሉም። ነገር ግን መላእክት ከእኛ በተለየ መንገድ የተፈጠሩ ፍጥረታት ናቸው። መላእክትም ሆኑ ሰዎች ሁላችንም የእግዚአብሔር አገልጋዮች ነን። እንዲያውም እግዚአብሔር ለመላእክት ከሰጣቸው ዐበይት ተግባራት አንዱ የኢየሱስ ክርስቶስን ምስክርነት የሚጠብቁትን አማኞች እንዲረዱ ነው። ቅዱሳንን ማምለክ አያስፈልግም። ማርያምን ማምለክ አያስፈልግም። አያት ቅድመ አያቶቻችንንም ማምለክ የለብንም። ልናመልከውና ልንሰግድለት የሚገባው እግዚአብሔር ብቻ ናቸው። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች ለመላእክት፥ ለቅዱሳን፥ ለአያት ቅድመ እያቶቻቸው፥ ለማርያም፥ ወዘተ… የሚሰግዱት ለምንድን ነው? ለ) እነዚህ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ጋር ስላለን ግንኙነት ያልተገነዘቡት ነገር ምንድን ነው? ሐ) እነዚህ ሰዎች ስለ መላእክትና ታላላቅ ክርስቲያኖች የያዙት የተሳሳተ ግንዛቤ ምንድን ነው? 

፪) ባቢሎን የወደመችበትን ሁኔታ የሚያሳይ ገለጻ (ራእይ 19፡11-21)

ራእይ 16:17-18፡24 ባቢሎን በተለያዩ መልኮች እንደ ወደመች ያሳያል። ነገር ግን እነዚህ ራእዮች ክፋት እንዴት ሊጠፋ እንደ ቻለ በግልጽ አያሳዩም። ራእይ 19፡11-21 ክፉ ፖለቲካዊና መንግሥታዊ ሥርዓቶች እንዴት እንደ ወደሙ ያሳየናል። በዚህም ጊዜ ክርስቶስ የበላይ ሆኖ መንገሡን እንመለከታለን። ይህ ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ በቀጥታ የሚሳተፍበት ተግባር ነው። ዮሐንስ ታላቁ ሰማያዊ ተዋጊ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወደ ምድር ሲመጣ ያሳየናል። በዚህ ክፍል ውስጥ የተጠቀሱትን ነገሮች ከዚህ በታች ተመልከት፡-

ሀ) ተዋጊው ክርስቶስ የታመነና እውነተኛ ነው። እርሱ በተከታዮቹ የታመነ ሲሆን፥ በበቀል የገደሏቸውን ሰዎች ይቀጣል። እርሱ የሚናገራቸውን ነገሮች ሁልጊዜም ስለሚፈጽም እውነተኛ ነው። ለሰው ልጆች ስለ ዘላለማዊ ፍርድ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ደግሞ ይፈጸማል።

ለ) የእሳት ነበልባል የሆኑት ዓይኖቹ በጽድቅ ቁጣና በፍርድ የተሞሉ ናቸው።

ሐ) ማንም የማያውቀው ስሙ እርሱ ከማንም እንደሚበልጥ፥ ባሕሪውንና እንደ አምላክ ታላቅነቱን መረዳት ከሰዎች አእምሮ በላይ መሆኑን ያሳያል።

መ) ልብሱ በደም ተጨማልቋል። ምንም እንኳ ይህ ክርስቶስ ሰዎችን ለማዳንና በሰይጣን ላይ ለመፍረድ ሥልጣን ያገኘበትን የመስቀል ላይ ሞቱን ሊያመለክት ቢችልም፥ አማኞችን መቅጣቱን በበለጠ የሚያሳይ ይመስላል። ይህም የአንድ ተዋጊ ወታደር ልብሶች በጠላቶቹ ደም እንደሚበላሽ ማለት ነው።

ሠ) የሰማይ ሠራዊት ይከተሉታል። እነዚህ መላእክትና ከሰማይ ወደ ምድር ተከትለውት የሚመጡ አማኞች ናቸው። ከእርሱ ጋር የሚመጡት በውጊያው ለማገዝ ሳይሆን፥ ድሉን አብረውት ለማክበር ነው። ምክንያቱም ወደ ኋላ እንደምንመለከተው ክርስቶስ ጠላቶቹን ሁሉ በአንድ ትእዛዝ ቃል ብቻ ያጠፋቸዋል።

ረ) የጦርነቱ መሣሪያ የክርስቶስ የትእዛዝ ሰይፍ ነው። እርሱ እጅግ የሚበልጥ በመሆኑ ውጊያው በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አይደለም። (የኃይል ሚዛኑ አይመጣጠንም)። ክርስቶስ እርሱን ለመውጋት የተሰበሰቡትን ክፉ ገዢዎችም አይፈራም። ጦርነቱ የሚጠናቀቀው በሰይፍ በመጨፋጨፍና የኋላ ኋላም ጠላት ድልን በመንሣቱ ሳይሆን፥ በክርስቶስ ኃይለኛ የትእዛዝ ቃል ነው። የክርስቶስ ኃይል እንዲህ ነው።

ሰ) እርሱ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ ነው። ክርስቶስ ሁሉንም ነገሥታትና ጌቶች በሰማይም ሆነ በምድር ይቆጣጠራል። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከእነዚህ ጥቅሶች ስለ አዳኛችን ኃይል ምን እንማራለን? ለ) ይህ ከሰይጣን፥ ከክፋት፥ እንዲሁም በምድር ላይ ካሉት ክፉ ሰዎች ጋር በምናደርገው ጦርነት ውስጥ ማበረታቻን የሚሰጠን እንዴት ነው? 

ዮሐንስ ክርስቶስ ለተለያዩ የሕዝብ ቡድኖች የሰጠውን ትእዛዝ ውጤት ይገልጻል፡-

ሀ) ክርስቶስ በሕይወታቸው ውስጥ እንዲገዛ የማይፈቅዱትን ሰዎች ከመሪዎች እስከ ዝቅተኛ ባሪያዎች፥ ከታላላቆች እስከ ታናናሾች ድረስ በኃያል ትእዛዙ ይገድላቸዋል። ለዚህም ነው አሞራዎች የወደቁትን ሰዎች እንዲበሉ የተጠሩት። ይህ ክፉዎች አካላዊ ሞት እንደሚጠብቃቸውና የመቀበርም ዕድል እንደማያገኙ ያሳያል። ውድመታቸው ከፍጻሜ ይደርስና ለታላቅ ኃፍረት ይጋለጣሉ። ነገር ግን ሲዖል የሚወርዱበት ዘላለማዊ ሞት ገና አልደረሰባቸውም።

ለ) በምድር ላይ እጅግ ኃያላን የሆኑት ሰዎች ማለትም ሐሳዊ መሢሕና ረዳቱ በእሳት ባሕር ውስጥ ይጣላሉ። ይህም የዘላለም ፍርድ ስፍራ ነው። ከኃያሉ ክርስቶስ ጋር ሲነጻጸሩ እነዚህ ታላላቅ መሪዎች ደካማና ኃይል የሌላቸው ናቸው። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የባቢሎን ጥፋት (ራእይ 17:1-18:24)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዘፍጥ. 11፡1-9 አንብብ። ባቢሎን በመባል በምትታወቀው ሰናዖር ላይ ምን ተከሰተ? ለ) ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ስለ ባቢሎን የተጻፈውን አንብብና ስለ ባቢሎን ታሪክ በተለይም ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ስላላቸው ግንኙነት ማጠቃለያ ጻፍ። ሐ) ራእይ 17-18ን አንብብ። ስለ ባቢሎን የተጻፈውን ገለጻና እግዚአብሔር ባለው መሠረት የተፈጸመውን አሳብ ዘርዝር።

ራእይ 17-18 በባቢሎን ላይ ሊሆን ስላለው ነገር በሁለት አቅጣጫ ይጽፋል። ራእይ 17 ከሃይማኖታዊ እይታ አንጻር ስለጠፋችው ባቢሎን ይናገራል። ራእይ 18 ደግሞ የንግድ ማዕከል በነበረችው ባቢሎንና ለኑሮአቸውና ለብልጽግናቸው ሲሉ የተደገፏት ሕዝብ በሚሰጡት ምላሽ ላይ ያተኩራል። 

ባቢሎን ግን ማንን ትወክል ይሆን? ዮሐንስ በብሉይ ኪዳን ዘመን በኤፍራጥስ ወንዝ አካባቢ የጥንት ሥልጣኔ ማዕከል የነበረችውን ነባራዊዋን ባቢሎንን እየገለጸ ነው? ወይስ ተምሣሌታዊ ገጽታ ስላላው ሌላ ነገር እየተናገረ ነው? ተመራማሪዎች ሦስት የተለያዩ አመለካከቶች አሉአቸው? አንደኛ፥ ዮሐንስ ስለ ነባራዊዋ ባቢሎን እንደተናገረ የሚያምኑ ጥቂት ተመራማሪዎች አሉ። የባቢሎን ከተማ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት ናት። ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰችው በዘፍጥ. 11፡1-9 ሰናዖር በሚለው ስሟ ነው። ይህቺም ከተማ ከጥፋት ውኃ በኋላ ሰዎች ስማቸውን ለማስጠራት እስከ ሰማይ የሚደርስ ግንብ የገነቡባት ስፍራ ናት። በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ቋንቋቸውን በመለወጥ በምድር ዙሪያ ሁሉ በተናቸው። ወደ በኋላ ባቢሎን ኢየሩሳሌምንና መቅደሱን በማፍረስ ብዙ አይሁዶችን በ586 ዓ.ዓ ወደ ምርኮ በመውሰዷ የአይሁዶች ዋነኛ ጠላት ሆናለች። ከዚያም በኋላ ለአንድ መቶ ዓመታት ያህል አስፈላጊ ብትሆንም፥ በኋላ የሜዶንና የፋርስ መንግሥታት አሸንፈዋታል። በዚህም ምክንያት በኢሳይያስ በተነገረው ትንቢት መሠረት ፈራረሰች (ኢሳ. 13)። በአዲስ ኪዳን ዘመን ባቢሎን በአካባቢዋ ከሚኖሩ ጥቂት መንደርተኞች በስተቀር የፈራረሰች ከተማ ነበረች። የሆነ ሆኖ ግን፥ በመጨረሻው ዘመን የክርስቶስ ተቃዋሚ ከተማይቱን መልሶ በማቋቋም የግዛቱ ማዕከል እንደሚያደርጋት የሚያምኑ አንዳንዶች አሉ። ይህ እውነት ከሆነ ራእይ 17–18 የሚገልጸው የክርስቶስ ተቃዋሚን የግዛቱን ዋና ከተማ ጥፋት ነው ማለት ነው።

ሁለተኛ፥ ባቢሎን በአዲስ ኪዳን ዘመን የነበረችውን ሮምን በተምሳሌትነት የምታመለክት ናት ብለው የሚያምኑ ጥቂት ሰዎችም አሉ። በአዲስ ኪዳን ዘመን በነበሩት ሌሎች የአይሁዶችና የክርስቲያን ሥነ ጽሑፎችም ውስጥ ባቢሎን የሮም ተምሳሌት ነበረች። ሮም የአይሁዶች ጠላት ስትሆን፥ በ70 ዓ.ም ኢየሩሳሌምንና መቅደሱን አፍርሳለች፡፡ ይህም ባቢሎን በኢየሩሳሌምና በቤተ መቅደሱ ላይ ካደረገችው ጋር ተመሳሳይነት አለው። በተጨማሪም እርሷ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑትን አይሁድንና ክርስቲያኖችን ያሳደደች መንግሥት ናት። ከዚያም በኋላ በ1ኛ ጴጥሮስ 5፡13 ጴጥሮስ ባቢሎን የሚለውን ስም የተጠቀመው ሮምን ለማመልከት ሳይሆን አይቀርም። ስለሆነም፥ ብዙ ምሁራን ዮሐንስ የሮምን ውድመት እያመለከተ መሆኑን ይናገራሉ።

ሦስተኛ፥ በይበልጥ፥ ባቢሎን እግዚአብሔርን የሚቃወሙትን ሁሉ በተምሳሌትነት የምታመለከት ይመስላል። በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ውሎ ሰዎችን የሚያታልለውን የትኛውንም ሃይማኖት ትወክላለች። እውነትንና የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚቃወም መንግሥት የሚኖርባትን (እንደ ሮም ያለች) ከተማ ታመለክታለች። በዚህ መልኩ ሮም በአንድ በኩል ባቢሎን መሆኗን እንመለከታለን። ነገር ግን ከሁሉም የከፋችው ባቢሎን ዓለም በሙሉ እግዚአብሔርን እንዲዋጋ የሚያስተባብረው ሐሳዊ መሢሕ መንግሥት ትሆናለች። ስለሆነም ዮሐንስ ባቢሎን እንደምትወድቅ ሲገልጽ፥ በእግዚአብሔርና በመንገዶቹ ላይ የሚያምጹ ሁሉ እንደሚወድሙ መግለጹ ነው። ይህም ማለት የውሸት ሃይማኖቶች፥ ክፉ የመንግሥት ሥርዓቶች፥ ቁሳዊ ኢኮኖሚዎች፥ ወዘተ… ይጠፋሉ ማለት ነው። የሐሳዊ መሢሕ የመጨረሻው መንግሥት ዓለም እስከ አሁን አይቶት የማያውቀው ክፉ በመሆኑ፥ በዚህ ስፍራ በቀዳሚነት የተጠቀሰው ባቢሎን ይኸው ነው።

ብዙ ምሁራን ዮሐንስ ሁለት ተምሳሌታዊ ከተሞችን እያነጻጸረ ነው ይላሉ። አንደኛዋ የክፋት ተምሳሌት የሆነችው ባቢሎን ናት። ይህች ከተማ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ውላ ሁልጊዜም የእግዚአብሔርን መንገድ እየተቃወመች የሰዎችን መንገድ ከፍ ከፍ ታደርጋለች። ሌላዋ እግዚአብሔር የሚቆጣጠራቸውና እርሱን የሚያከብሩ ነገሮች ሁሉ ተምሳሌት የሆነችው አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ነች።

አዲሲቱ ኢየሩሳሌም እግዚአብሔር በንግሥና የሚገዛባትና ሰዎች እርሱን እየታዘዙ የሚያከብሩባት ከተማ ነች። ለዘላለም የምትኖረው ይህቺው ኢየሩሳሌም ናት።

ዮሐንስ ቀደም ሲል ስለ ባቢሎንና ስለሚደርስባት ፍርድ ሁለት ጊዜያት ጠቅሷል (ራእይ 14፡8፤ 16፡19)። የመጨረሻው የጽዋ ፍርድ ስለ መውደሟ ይናገራል። ራእይ 17–18 ስለ ታላቂቱ ባቢሎንና እግዚአብሔር ስለሚያመጣባት ውድመት ተጨማሪ ገለጻዎችን ያቀርባል። 

፩. ሃይማኖታዊዋ ባቢሎን፡ ከአውሬው ላይ የተቀመጠችው ሴት (ራእይ 17) 

የውይይት ጥያቄ፡- ሃይማኖትና መንግሥታት በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ስደት ለማምጣት እንዴት አብረው ሲሠሩ እንደተመለከትክ ግለጽ።

ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፥ ብዙውን ጊዜ ሐሰተኛ ሃይማኖትና ክፉ መንግሥታት እግዚአብሔርና ሕዝቡን ለመውጋት አብረው ይሠራሉ። ዮሐንስ ይህንን እውነት የአንዲትን ጋለሞታ ሴት ተምሳሌታዊ ራእይ በማቅረብ ያብራራል። ይህች ሴት ጋለሞታ የተባለችው ሰዎችን ከእውነተኛ ፍቅርና ለእግዚአብሔር ታማኝ ከመሆን ስለምትመልስ ነው። ይህቺ ሴት በብዙ ውሆች ላይ ትቀመጣለች። ይህም በሁሉም አገር ውስጥ እንደምትገኝ ያመለክታል። ሴቲቱ የተቀመጠችበት ቀይ አውሬ የስድብ ስሞች የሞሉበት፥ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች ያሉት ነው። ሃይማኖታዊዋ ባቢሎን ከፖለቲከኛዋ ባቢሎንና ከዘንዶው ጋር የጠበቀ ቁርኝት አላት። ሁሉም ተመሳሳዮች ናቸው። ይህቺ ጋለሞታ የሐሳዊ መሢሕን ያህል ሥልጣንና ኃይል አላት። ሴቲቱ እንደ ዘንዶው ማለትም እንደ ሰይጣን ናት። ዘንዶው ወይም ሰይጣን ከእግዚአብሔር ጋር በሚያደርገው ውጊያ እንድታግዘው ባሕሪውንና ኃይሉን ይሰጣታል። ይህቺ ሴት በሐምራዊ፥ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች አጊጣለች። ይህም ይህቺ ሴት የተከበረችና እንደ ንግሥት የምትታይ መሆኗን ያመለክታል። ከተከታዮቿ ባገኘችው ሀብት በልጽጋ ነበር። (አብዛኞቹ የሐሰተኛ ሃይማኖት መሪዎች ወደ ብልጽግናው ያደላሉ። ይህ ሐሰተኛ ሃይማኖት እንደ አብዛኞቹ ሐሰተኛ ሃይማኖቶች ሁሉ ውጭው ሲታይ የተከበረ ይመስላል። በውስጡ ግን ታላቅ ክፋት ተሰውሯል። ይህንን አክራሪ ሙስሊሞች እነርሱ የሚፈልጉትን ነገር የማያደርጉትን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሚገድሉበት ወይም ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖት በመሆን በመሪዎቹ አማካኝነት የተለየ አሳብ የሚይዙትን ሰዎች ከሚገድልበት (እንደ መስቀል ዘመቻ ዘመን) ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነው። ይህ ሃይማኖት ምንም ዓይነት ስም ይኑረው ለክርስቶስ ምስክርነት የሚሰጡትን ቅዱሳን ደም የሚያፈስ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላት ነው።

መልአኩ ጋለሞታይቱ ከተቀመጠችበት አውሬ ጀምሮ ራእዩን ያብራራል። ዮሐንስ ስለ አውሬው የሚናገረውን ሁሉ መረዳቱ አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ተምሳሌቱ መንግሥትንም ሰውንም ያመለክታልና ነው። እንዲሁም ተምሳሌቱ በዮሐንስ ዘመን የሮምን መንግሥት፥ እንዲሁም በሐሳዊ መሢሕ ፍጻሜውን ወደሚያገኝበት የመጨረሻው ዘመን የሚያመለክት ይመስላል። የዚህ ራእይ አያሌ ገጽታዎች ከዚህ በታች ቀርበዋል።

ሀ) “አስቀድሞ ነበር፥ አሁንም የለም፥ ከጥልቁም ይወጣ ዘንድ አለው። ወደ ጥፋትም ይሄዳል።” አንዳንድ ሰዎች ይህ ክፋት በሃይማኖትና በመንግሥታት ውስጥ የሚኖር መሆኑን ያሳያል ይላሉ። ሰዎች ምንም ያህል ክፋትን ለማጥፋት ቢታገሉም፥ ሁልጊዜም ተመልሶ ይመጣል። ክፋት ሙሉ በሙሉ የሚደመሰሰው በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ብቻ ነው። ይህ ምናልባትም በራእይ 13 እንደ ሞተና ከዚያም ነፍሰ እንደ ዘራ የተመለከትነውን ከባህር የወጣ አውሬ ወይም ሐሳዊ መሢሕን የሚያመለክት ይሆናል (ራእይ 13:3-4)።

ለ) ሰባቱ ራሶች ሰባት ኮረብቶችና ሰባት ነግሥታት ናቸው። ከሰባቱ ነገሥታት አምስቱ ቀደም ሲል ሞተዋል። አንዱ በሥልጣን ላይ ነው። ሌላኛው ደግሞ ገና ወደ ፊት ይመጣል። ከዚያም ከሰባተኛው ንጉሥ የሚመጣው ስምንተኛው ንጉሥ ሐሳዊ መሢሕ ይሆናል። የሮሜ ከተማ መጀመሪያ በሰባት ኮረብታዎች ላይ እንደ ተመሠረተች ከታሪክ እንረዳለን። ይህም በዚህ ስፍራ የተገለጸችው ሮም እንደሆነች የሚያመለክት ይመስላል። ይህ አስቸጋሪ ገለጻ ምሁራን የተለያዩ አመለካከቶችን እንዲይዙ አድርጓቸዋል። አንዳንዶቹ ዮሐንስ ከእርሱ በፊት ስለነበሩት አምስት ነገሥታት፥ በዘመኑ ስለነበረው አንድ ንጉሥና ከእርሱ በኋላ ስለሚመጡ ሁለት ነገሥታት፥ በአጠቃላይም ስምንት የሮም ነገሥታት እየተናገረ ነው ይላሉ። ሌሎች ሰባት ነገሥታት ከምድር የሚነሡ ዓለማዊ መንግሥታት መሆናቸውን ይናገራሉ። እነዚህም ከዮሐንስ ዘመን በፊት አምስቱ (እንደ ግብጽ፥ አሶር፥ ባቢሎን፥ ሜዶንና ፋርስ፥ ግሪክ)፥ የሮም መንግሥት እንዲሁም የሐሳዊ መሢሕ መንግሥት የሚመነጭበት ሌላ መንግሥት ናቸው። አሁንም ሌሎች ዮሐንስ በተምሳሌታዊ መልኩ የክፋትን ኃይል እያመለከተ ነው የሚሉ አሉ። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ የክፋትን ኃይል አሸንፎአል። አማኞችም ለክርስቶስ በመታዘዛቸው ምክንያት ነፍሳቸውን አሳልፈው እየሰጡ ክፋትን ያሸንፋሉ (ራእይ 12፡11)። በዮሐንስ ዘመን ግን ክፋት አሁንም በሮም መንግሥት ውስጥ ነግሦ አማኞችን በማሳደድ ላይ ነበር። ነገር ግን ወደፊት የሚኖረው አንድ የክፋት ራስ ብቻ ነበር። ይህም የሐሳዊ መሢሕ መንግሥት ነው። ነገር ግን ዮሐንስ ይኸው ክፋት በቅርቡ እንደሚጠፋ ለአማኞች ያረጋግጣል።

ሐ) ይህ የመጨረሻው የሐሳዊ መሢሕ መንግሥት ከሐሳዊ መሢሕ ጋር ቃል ኪዳን ከሚገቡ አሥር አገሮች የተመሠረተ ነው። የዮሐንስ ራእይ እግዚአብሔር ይህንንም ሁኔታ እንደሚቆጣጠር ያመለክታል። እነዚህ መንግሥታት ሥልጣን የሚይዙት ለአንድ ሰዓት ብቻ ነው። ይህ የጊዜውን አጭርነት ያመለክታል። እነዚህ የቃል ኪዳን አገሮች ተባብረው በጉን ይዋጋሉ። ነገር ግን በጉ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ በመሆኑ፥ ከቅዱሳኑ ጋር እነዚህን የዓለም መንግሥታት ያሸንፋቸዋል።

ለመሆኑ ጸረ እግዚአብሔር፥ ጸረ እውነት፥ በሆነችው የዓለም ሃይማኖት ላይ (ጋለሞታይቱ) ምን ይደርሳል? ለጊዜው በዓለም መንግሥታት ሁሉ ላይ ኃይል ይኖራታል። ከሐሳዊው መሢሕ ጋር በቅርብ አብራ ትሠራለች። ብዙም ሳይቆይ ግን የፖለቲካ መሪዎችና ሐሳዊው መሢሕ ያጠፉአታል። አንዳንዶች ምሁራን ይህ የመጨረሻው ዘመን ዓለም አቀፍ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ሐሳዊ መሢሕን በመደገፍ የሚጀምር መሆኑንና ሐሳዊው መሢሕ ግን በግሉ ለመመለክ በመፈለጉ ይህንን ሃይማኖት ለማክሰም እንደሚነሣሣ ያሳያል ይላሉ። ሌሎች ይህ ምንም እንኳን ብዙውን ጊዜ ሃይማኖትና ፖለቲካ አብረው ቢሠሩም፥ የኋላ ኋላ እርስ በርሳቸው የሚጣሉ መሆናቸውን ያሳያል ይላሉ። የሃይማኖት መሪዎች ሰዎች እንዲከተሏቸውና እንዲያከብሯቸው ይፈልጋሉ። የመንግሥታት መሪዎችም እንደዚሁ፥ ሁለቱም ዓይነት መሪዎች የሰዎችን ታማኝነት ለማግኘት ስለሚፈልጉ እርስ በርሳቸው ይዋጋሉ። በመጨረሻው ዘመን፥ ሐሳዊ መሢሕ ሰዎች እርሱን ብቻ እንጂ ሌሎችን እንዳያመልኩ ያስገድዳል። በመሆኑም ሃይማኖታዊቷን ባቢሎንን ያጠፋታል። (ማስታወሻ፡ አንዳንዶች በዚህ ውስጥ ብዙውን ጊዜ ክፋት ከራሱ ጋር የሚጣላና ራሱን የሚያጠፋ መሆኑን ይመለከታሉ።)

ምንም እንኳን ይህን ራእይ ለመረዳት አስቸጋሪ ቢሆንና፥ ምሁራን የተለያዩ አተረጓጎሞችን ቢያቀርቡም፥ እግዚአብሔር እርሱን የምትቃወመውን ባቢሎንን እንደሚያጠፋት ግልጽ ነው። ከተቃውሞው መካከል አንደኛው ሃይማኖታዊ ነው። ሰዎች አማራጭ የአምልኮ መንገዶች አድርገው የቀረጹአቸው ሐሰተኛ የሃይማኖት ሥርዓቶች ይከሰታሉ። በመጨረሻው ዘመን፥ ዓለም አቀፍ ሃይማኖት የሚመሠረት ይመስላል። ይህም ሐሳዊ መሢሕን የሚያመልክ ነው። የኋላ ኋላ ግን እግዚአብሔር ሐሰተኛ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን በሙሉ ያጠፋቸዋል። ሌላኛዋ ዓይነት ባቢሎን ፖለቲካኛዋ ባቢሎን ናት። ይህም በሐሳዊ መሢሕ የሚጠናቀቀውን የዓለም መንግሥት የሚያሳይ ነው። ይህም በራእይ 19 ውስጥ እንደምንመለከተው በእግዚአብሔር የሚጠፋ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር አንድ ቀን ሁሉንም ሐሰተኛ ሃይማኖቶችና በሰይጣን ኃይል የሚሠሩትን ፖለቲካዊ ሥርዓቶች ጨምሮ ባቢሎኖችን እንደሚያጠፋ ማወቃችን እንዴት ያበረታታናል? ለ) ይህ ለእግዚአብሔር ንጹሕ ሆኖ ከመቆየት ይልቅ ከባቢሎኖች ጋር ስለ መተባበር ምን ማስጠንቀቂያ ይሰጠናል?

፪. የነጋዴዋ ባቢሎን ውድመት (ራእይ 18)

የሰውን ልጅ የሚያጠፉ ሦስት ኃይላት አሉ። እነዚህም ሐሰተኛ ሃይማኖቶች፥ ክፉ መንግሥታትና በጥቂቶች ቁጥጥር ሥር ውሎ ፍትሕ አልበኝነትንና የእኩልነት መጓደልን የሚያስፋፋው በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረተ የኢኮኖሚ ሥርዓት ነው። ስርቆት፥ ግድያ፥ ጦርነት፥ ድህነት፥ ጉቦኛነት ሁሉ ሰዎች ከመንግሥተ ሰማይ ብልጽግና ይልቅ በገንዘብ ላይ የማተኮራቸው ውጤት ነው። እነዚህ ሁሉ ባቢሎን ተብለው ይጠራሉ። እነዚህ ሁሉ በታሪክ የተለየ የክፋት ገጽታ ያሳያሉ። ይህም እግዚአብሔር የወጠነው ዕቅድ የማይከተል ፀረ እግዚአብሔር ተግባር ነው። እነዚህ ሦስቱም የባቢሎን ዓይነቶች በሰይጣን ቁጥጥር ሥር የሚካሄዱ ናቸው። በማቴዎስ 6፡21 ክርስቶስ መዝገባችን ባለበት ልባችን በዚያ እንደሚሆን ተናግሯል።

በራእይ 18 ዮሐንስ ብዙውን ጊዜ ከመንግሥታት ጋር አብሮ የሚሠራው የዓለም ፍትሐዊ ያልሆነ የኢኮኖሚ ሥርዓት ተጠቃሚዎች ከነበሩት ወገኖች እይታ አንጻር የባቢሎንን ውድመት ገልጾአል። አብዛኞቹ መንግሥታት ሀብታሞችንና ነጋዴዎችን እንጂ ድሆችን እይደግፉም። የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሀብታሞች ሲሆኑ፥ በራስ ወዳድነት ሀብታቸውን ለማካበት ይጥራሉ። ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድም ይህንኑ ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም። ዮሐንስ የዓለምን ቁሳዊ የአኗኗር ዘይቤ እግዚአብሔር ከሚያጠፋት ከተማ ጋር ያነጻጽራል። የገንዘብ ፍቅር፥ ቁሳዊ ሀብትና የምቾት አኗኗር የምድርን ነገሥታት ያወደሙ የዝሙት ተግባራትም ሆነው ተገልጸዋል። እግዚአብሔርም የዓለምን የኢኮኖሚ ሥርዓት ለማጥፋት ተዘጋጅቷል። በመጀመሪያ ግን ለአማኞች ጥሪውን ያቀርባል። «ሕዝቤ ሆይ፥ በኃጢያቷ እንዳትተባበሩ ከመቅሰፍቷም እንዳትቀበሉ ከእርሷ ዘንድ ውጡ። ኃጢአቷ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሷልና።» እግዚአብሔር ይህን ሲል ክርስቲያኖች ዓለማውያን ከሚሠሩበትና ከሚኖሩበት አካባቢ እንዲርቁ መጠየቁ አይደለም። ክርስቲያኖች ወደሚኖሩበት አካባቢ በመሄዳችን ንጹሕ ሕይወት ልንኖር አንችልም። በዚህ ዓይነት በመራቅ ለዓለማውያን የምንመሰክርበትን ዕድል እናጣለን። እግዚአብሔር የሚለው ዓላማችን፥ አመለካከታችንና ተግባራችን የተለየ መሆን እንዳለበት ነው። የገንዘብ ፍቅር፥ ይበልጥ ተጨማሪ ቁሳዊ በረከቶችን ማግኘት ሕይወታችንን እንዳይቆጣጠር ይነግረናል። የእግዚአብሔርን መንግሥትና የዘላለምን ሕይወት አስቀድመን ልንሻ ይገባል። ይህ ዋንኛው ትኩረታችን ሊሆን ይገባል። በዚህ ዓይነት ንጹሐን ሆነን ከቆምን ከእግዚአብሔር ፍርድ እናመልጣለን። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች ለቁሳዊ ነገሮች፥ ለሀብት፥ ለምቾት፥ ወዘተ… ባላቸው አመለካከት የነጋዴዋ ባቢሎን ሥርዓት አባል ሲሆኑ የተመለከትከው እንዴት ነው? ለ) አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች የሚያደርጓቸውና የገንዘብ ፍቅር ሕይወታቸውን እንደ ተቆጣጠረ የሚያሳዩ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? ሐ) እግዚአብሔር በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ለሀብታም ክርስቲያኖች የሰጠው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው?

ዮሐንስ የነጋዴዋን ባቢሎንን መውደቅ በማሳየት ብዙውን ጊዜ የሌሎችን ሰዎች ጥረት ለራሳቸው መጠቀሚያ በማድረግ በራስ ወዳድነት ስለተመላለሱት የተለያዩ ሰዎች ያብራራል። ሥልጣናቸውን ለገንዘብ ማግኛ ስላዋሉት ነገሥታትና ገዢዎች ይናገራል። የኢኮኖሚ መዋቅራቸው በሚፈርስበት ጊዜ ጭንቀት ይውጣቸዋል። ከዚያም ቁሳቁሶችን በመግዛትና በመሽጥ ኑሯቸውን የሚገፉ ነጋዴዎች ተገልጸዋል። እነርሱም ሕይወታቸው ሲናጋና ባዶ እጃቸውን ሲቀሩ ያለቅሳሉ። በመጨረሻም፥ የውኃ ላይ መርከቦች ካፒቴኖች ተጠቅሰዋል። እነዚህም የዓለምን ቁሳዊ ሀብቶች የማጓጓዝ ኃላፊነት ያላቸውን ሁሉ የሚያመለክቱ ናቸው። የሚያጓጉዙት ነገር በማይኖርበት ጊዜ ኑሯቸው ይናጋል።

ዮሐንስ እግዚአብሔርን የሚቃወሙትን ማኅበረሰብ ሁሉ (ሃይማኖታዊ፥ ኢኮኖሚያዊ፥ ፖለቲካዊ) በተምሳሌትነት የምታመለክተው ባቢሎን የምትደመሰስ መሆኗን በመግለጽ ይህን ምዕራፍ ያጠናቅቃል። ሮማውያን ሙሉ በሙሉ እንዲደመስሷት ጥንታዊቷ የኢየሩሳሌም ከተማ፥ ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰይጣንን ከተማ በሚደመስስበት ጊዜ ሐሳዊ መሢሕ፡ ነቢዩ፥ እንዲሁም ከእግዚአብሔርና ከሕዝቡ ይልቅ ባቢሎንን የመረጡ ሁሉ ይደመሰሳሉ። በዚህም ጊዜ የእግዚአብሔር ፍትሕ ይከናወናል። እርሱ የነቢያቱንና የቅዱሳኑን ሞት ተበቅሏልና። 

የውይይት ጥያቄ፡- ራእይ 19-22 አንብብ። ሀ) በምድር ያሉት ዓለማውያን (ራእይ 18) ለባቢሎን መደምሰስ የሰጡትን ምላሽ በሰማይ ያሉት አማኞች ከሰጡት ጋር አነጻጽር። ለ) ክርስቶስ በጠላቶቹ ላይ ያለው ኃይልና ድል ነሺነት የተገለጸው እንዴት ነው? ሐ) በተለያዩ የእግዚአብሔር ጠላቶች ላይ ምን እንደሚከሰት ግለጽ። መ) የዘላለም ክብር የተገለጸው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ሰባቱ የጽዋ ፍርዶች (ራእይ 15:1-16:21)

የዘፍጥረት መጽሐፍ ትልቅ ውበትን በመግለጽ ይጀምራል። እግዚአብሔር በብርሃን፥ በእንስሳትና በሰዎች፥ እንዲሁም በአትክልት ስፍራ የተዋበች ዓለም ፈጥሯል። ከዚህም በላይ እግዚአብሔር በተደጋጋሚ የኤድን ገነት ነዋሪዎች ከሆኑት ወንድና ሴት ጋር እየተገናኘ ይወያያል። በመካከላቸውም ምንም ዓይነት መጋረጃም ሆነ ኃፍረት አልነበረም። ያ ሁሉ ውበት አዳምና ሔዋን እግዚአብሔር በሕይወታቸው ላይ የነበረውን ቁጥጥር በመቃወማቸው ከመቅጽበት ተናደ። በዚህም ጊዜ ያ ሁሉ ውበት በኃጢአት ቆሸሸ። ይህም እሾሆች፥ ላብ ጠብ የሚያደርግ ብርቱ ሥራ፥ የወሊድ ምጥና ሞት፥ ግድያ፥ ወሲባዊ ኃጢአት፥ ጦርነቶች፥ ወዘተ… እንዲስፋፉ አደረገ። በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙን ችግሮች ሁሉ የመነጩት በዘፍጥረት ውስጥ ከተከሰተው ዐመፅ ነው።

የዮሐንስ ራእይ የዘፍጥረት መጽሐፍ ከተጀመረበት ሁኔታ ጋር በሚቃረን መልኩ ይጠናቀቃል። ራእይ የሚጀምረው በኃጢአት፥ ዐመፅ፥ ጦርነቶች፥ የተፈጥሮ አደጋና በታሪክ በማንኛውም ስፍራ ከታየው ሁሉ በላቀ ክፋት ነው። ነገር ግን ያ ሁሉ ይወገዳል። እንዲሁም በድጋሚ አንድ ጊዜ፥ ውበትና ግልጽ የሆነ ግንኙነት ከአምላካችን ጋር እናደርጋለን። ማንኛውም የሥቃይ ስሜት የሚያመጣብን ምድራዊ ነገር ሁሉ ይወገዳል። ይህ አዲስ ሰማይና ምድር ምን እንደሚመስል ወይም የመጀመሪያዋን ምድር የምትመስል ትሁን ወይ ሌላ ሙሉ ለሙሉ አናውቅም። ነገር ግን እኛ ከምንገምተው ከማናቸውም ነገሮች በላይ ውብ እንደምትሆን እናውቃለን። አሁን የምንኖርባት ምድር እንኳን በኃጢአት ከተበከለችበት ሺህ ዓመታት በኋላ እንኳን ውብ ናት፥ ፈጽሞ የምትታደሰው አዲሲቱ ምድር ምን ልትመስል እንደምትችል እስኪ አስብ! ምንም ሥቃይ የሌለበት ዓለም ምን ይመስል ይሆን? ከሁሉ በላይ ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ያለ ምንም የኃጢአት ጋሬጣና ግድግዳ እንዲሁም ያለ አንዳች እፍረት ፊት ለፊት የምንገናኝበት ዓለም ምን ሊመስል እንደሚችል ገምት።

ወንድሞችና እኅቶች፥ ዮሐንስ ስለ አዲሲቱ ሰማይና ስለ አዲሲቱ ምድር እንድናስታውስ ይፈልጋል። ምክንያቱም ያ ቋሚ መኖሪያችን ነው። በዚህን ሰዓት በእምነት ጉዞ ላይ እንገኛለን። እውነት ነው በአሁኑ ዓለም ውስጥ በኃጢአትና በበሽታ ምክንያት እንቸገራለን። በተጨማሪም የክፉ መሪዎችና የአስጨናቂ ሃይማኖቶች ጊዜ ይሆናል። ነገር ግን በታማኝነት ክርስቶስን ብንከተልና ብንጸና፥ አንድ ቀን ይህ ሁሉ ችግር ልንገልጸው እስከማንችል ድረስ ወደ ክብር ይለወጣል። 

የውይይት ጥያቄ፡– ራእይ 15-16 አንብብ። እግዚአብሔር በምድር ላይ በመጨረሻው ጊዜ ላይ የሚያመጣውን የመጨረሻ ፍርድ ግለጽ። 

የመጨረሻው የፍርድ ጊዜ ፍጻሜ በደጅ ነው። ታላቁ መከራም በመጠናቀቅ ላይ ነው። ከዚህ በኋላ በምድር ላይ የሚመጣው አንድ ቀጣይነት ያለው ታላቅና መጥፎ የፍርድ ጊዜ ብቻ ነው። የዮሐንስ ራእይ የእግዚአብሔር ዙፋን ወዳለበት ሰማያዊ ክፍል ይመለሳል። በዚያም ሕዝብ በዙፋኑ ፊት ቆሞ ያያል። አማኞች አሸናፊዎች ናቸው። ሰይጣን ሐሰተኛው ነቢይና ሐሳዊው መሢሕ እምነታቸውን ለማስጣል ካመጡባቸው ፈተናዎች በተቃራኒ ታማኝ ሆነው በመቆማቸው ምክንያት አሸንፈዋል። ክርስቲያኖች ለማመቻመችና እንደ ምስል ላሉ ለማናቸውም ነገሮች ላለመስገድ ወስነዋል። የአውሬውን ምልክት በመቀበል የዓለም ሥርዓትን አስተናግደው ለዓለም ታማኝነታቸውን ለማሳየት አልፈለጉም። እነዚህ ቅዱሳን ስደትና የኑሮ ጉድለት አጎሣቁሏቸው ነበር። አሁን ግን በእረፍት ላይ ናቸው። ይህም እግዚአብሔር የሚበቀልበት፥ የክርስቶስን ጠላቶች የሚያጠፋበትና መንግሥቱን የሚመሠርትበት ጊዜ ነው። የእግዚአብሔር መንገዶች ትክክል በመሆናቸው ምክንያት አማኞች በታላቅ የውዳሴ ዝማሬ እግዚአብሔርን ያመልኩታል። ከዐመፅና ከመከራ ውስጥ ውበትን ማውጣት የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች አሁን እግዚአብሔር በሁሉም ዘንድ ክብርን እንደሚያገኝ ያውቃሉ። ዐመፅ ይቆማል። «የምስክሩ ማደሪያ» ከሚባለው ዙፋንም የመጨረሻዎቹ የእግዚአብሔር የቁጣ ጽዋዎች ፍርዶች ለሰባት መላእክት ተሰጡ። ከእነዚህ ፍርዶች መካከል አንዳንዶቹ ከመለከት ፍርዶችና በሙሴ ዘመን በግብጽ ምድር ላይ ከወረዱት መቅሠፍቶች ጋር ይመሳሰላሉ። እነዚህ ፍርዶች በቅደም ተከተል ደረጃ ከመምጣት ይልቅ ከመቅጽበት አንዱ በአንዱ ላይ እየተደራረበ ይመጣል።

 1. የመጀመሪያ ጽዋ፡- የአውሬው ምልክት ባለባቸው ሰዎች ላይ የሚመጣ ቁስል። እንደ ግብጹ መቅሠፍት ሁሉ (ዘጸ 7-11)፥ አንዳንዶቹ ፍርዶች ማኅተም ያለባቸውን የእግዚአብሔር ልጆችና የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትን ያላመኑ ሰዎች ለመለየት እንደሚያገለግሉ ዮሐንስ ያሳየናል። በዚህ ቁስል የሚመቱት የእግዚአብሔር ተቃዋሚዎችና የአውሬውን ምልክት የተቀበሉት የሰይጣን ግብረ አበሮች ብቻ ናቸው።
 2. ሁለተኛዋ ጽዋ፡- የባሕር ውኃ ሁሉ ወደ ደም መለወጥ። አስቀድመን የባሕር ሲሶ በፍርድ ውስጥ መመረዙን አይተናል። ይህም 2/3ኛው ለሰው ልጆች ተስማሚ እንደነበር ያሳየናል። አሁን ግን እግዚአብሔር በባሕር ውስጥ ያሉትን ፍጥረታት በሙሉ ያጠፋል። ከዚያ በኋላ በባሕር ላይ የመርከብ ላይ ጉዞ አይኖርም። በባሕር ዳርቻ ላይ ለሚኖሩም ከባሕር ውስጥ የሚገኝ ምግብ አይኖርም።
 3. ሦስተኛው ጽዋ፡- የማንኛውም ንጹሕ ውኃ ወደ ደም መቀየር። ይህም መቅሠፍት ልክ እንደ ሁለተኛው ጽዋ ሁሉ ከመለከት ፍርዶች የከፋ ነበር። ምክንያቱም መለከት ፍርድ ላይ 1/3ኛው ንጹሕ ውኃ ብቻ ሲበከል፥ አሁን ግን በጽዋው ፍርድ የውኃ ዘር የተባለ ሁሉ ይበከላል። መልአኩም ይህንን ፍርድ ተስማሚ ፍርድ ይለዋል። እርኩሳን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ደም አፍስሰዋል። አሁን ግን በእግዚአብሔር ፍርድ አማካኝነት ደሙን እንደ ውኃ ይጠጣሉ።
 4. አራተኛው ጽዋ፡- የፀሐይ ሰዎችን ማቃጠል። በአንድ በሆነ ምክንያት የፀሐይ ኃይል በብዛት ይጨምርና ሰዎችን ማቃጠል ይጀምራል። (ማስታወሻ፡- እነዚህ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሚሰጣቸው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያዎች ሲሆኑ ከመጨረሻው ጊዜ በፊት የሚሆን የንስሐ ዕድል ነው። ነገር ግን ሰዎች ምላሽ የሚሰጡት በምን መንገድ ይሆን? ከእርኩሰታቸው ተመልሰው እግዚአብሔርን ያመልኩት ይሆን? በጭራሽ፥ የተነገረን እነዚህ ፍርዶች የመጡት ከእግዚአብሔር ዘንድ መሆኑን እያወቁ እግዚአብሔርን እንደሚራገሙ ነው።)
 5. አምስተኛው ጽዋ፡- ጨለማና ሥቃይ። የክርስቶስ ተቃዋሚ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ ይኩራራል። ሰዎችም ያመልኩት ዘንድ ያስነግራል። የሁሉም ነገሮች ተቆጣጣሪ እንደሆነም ያውጃል። ሆኖም ግን የእግዚአብሔር ሰዓት ሲደርስ የእግዚአብሔር ፍርድ በክርስቶስ ተቃዋሚ፥ በቤተ መንግሥቱና በግዛቱ ሁሉ ላይ ይወድቃል። በመንግሥቱ ሁሉ ላይ ጨለማ ሲከብድ፥ በዚያ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የመጀመሪያው የጽዋ ፍርድ ቁስል ይሰማቸዋል። እንደገናም ሕዝቡ ንስሐ ገብቶ ወደ እግዚአብሔር እንደማይመለስ ተነግሮናል። የሰው ልብ ምንኛ ጠንካራ ነው!
 6. ስድስተኛ ጽዋ፡- ለአርማጌዶኑ ጦርነት የተደረገ የሕዝብ ስብሰባ። በእግዚአብሔር ትእዛዝ ክፉ መናፍስት ከዘንዶው፥ ከአውሬውና ከሐሰተኛው ነቢይ አፎች ውስጥ ይወጣሉ። እነርሱም ከእግዚአብሔር ጋር የሚዋጉበት ሰዓት እንደ ደረሰ ያውቃሉ። እነዚህም እንቁራሪት መሣይ ክፉ መናፍስት የምድር ነገሥታትና እርኩሳት መናፍስትን ሁሉ አርማጌዶን ለተባለው ጦርነት እንዲሰበሰቡ ያሳምናሉ። አንዳንድ ተመራማሪዎች አርማጌዶን፥ የእግዚአብሔርን ቀንና እግዚአብሔር ከጠላቶቹ ጋር የሚያደርገውን የመጨረሻ ጦርነት በተምሳሌትነት ብቻ እንደሚያሳይ ያምናሉ። ሌሎች ተመራማሪዎች ግን አርማጌዶን በሰሜን እስራኤል የሚገኝና የመጨረሻውም ጦርነት በትክክል የሚካሄድበት ስፍራ እንደሆነ ያስባሉ።
 7. ሰባተኛው ጽዋ፡- እግዚአብሔር በሰው ዘር ሁሉ ላይ ታላቅ የመሬት መንቀጥቀጥንና በረዶን ያመጣል። (ማስታወሻ፡- ይህ ሰባተኛው ፍርድ እንደ ፍርድ የተገለጠበት የመጀመሪያ ጊዜ ነው።) እግዚአብሔር «ተፈጸመ» ብሎ ሲናገር፥ ይህንን የታላቅ ፍርድ ጊዜ ወደ ፍጻሜው አመጣለሁ ማለቱ ነው። በዓለም ታሪክ የምናውቀው የሰዎች የበላይነት አሁን ፍጻሜውን አገኘ። አሁን ጊዜው፥ ኢየሱስ የሚመለስበትና መንግሥቱንም የሚመሠርትሰት ነው። አሕዛብ፥ ቅኝ ግዛቶችና «የታላቂቱ ባቢሎን» ተምሣሌቶች የሆኑት የዓለም ከተማዎች ሁሉ ጠፍተዋል። እስከ መጨረሻው ድረስ የሰው ዘር ለንስሐ ማመፅና በተስፋ ቢስ ቁጣ እግዚአብሔርን መራገምን ተያይዞታል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች ለመጨረሻው የእግዚአብሔር ፍርድ ከሚሰጡት ምላሽ በመነሣት ስለ ሰዎች የልብ ድንዳኔ ምን ልንማር እንችላለን? ለ) እግዚአብሔር ሰዎች ወደ እርሱ እንዲመለሱ በፍርዶች አማካኝነት ሲያስጠነቅቃቸው አብዛኛዎቹ ሰዎች ለምን ንስሐ እንደማይገቡ ግለጽ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

በመንፈሳዊ ውጊያ ውስጥ የሚሳተፉ ቁልፍ ግለሰቦች (ራእይ 12:1-14:20) 

የውይይት ጥያቄ፡– ራእይ 12-14 አንብብ። ሀ) በዚህ ክፍል በቀረቡት ራእዮች ውስጥ የተገለጹትን እያንዳንዳቸውን ገጸ ባሕርያት ዘርዝር። እያንዳንዳቸው እንዴት የተለዩና ከሌሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውን ግለጽ። ለ) ይህ ክፍል ስለ እግዚአብሔር አብና ወልድ ምን ያስተምረናል? ሐ) ስለ አማኞች ምን እንማራለን?

ዛሬ በምድር ላይ የሚፈጸሙትን ነገሮች ማለትም እንደ ስደት፥ ረሃብና ጦርነት የመሳሰሉትን እንዴት ልንረዳቸው ይገባል? ክርስቶስ ሊመለስ ሲል በዓለም ላይ የሚሆነው ሁኔታ ምን ይመስላል? ዮሐንስ እግዚአብሔር ወደ ምድር ስለሚልካቸው የመጨረሻዎቹ ተከታታይ ፍርዶች ከመግለጹ በፊት፥ ወደ ፊት ቁልፍ ሚና በሚጫወቱ ግለሰቦች ላይ ያተኩራል። ነገር ግን የእነዚህ ግለሰቦች ባሕርያት ሙሉ በሙሉ በመጨረሻው ዘመን የሚታይ ቢሆንም፥ አሁንም በመጠኑ እየታየ መሆኑ ግልጽ ነው።

፩. በሴቲቱና በዘንዶው መካከል የተደረገ ጦርነት (ራእይ 12)

ዮሐንስ ይህንን ራእይ «ታላቅ ምልክት» ሲል ይጠራዋል። ምልክት ከክስተት ወይም ከራእይ በስቲያ ያሉትን አስደናቂ ክስተት ወይም ራእይ ነው። ለምሳሌ ያህል፥ ብዙዎቹ የኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራት ምልክቶች ተብለው ይጠራሉ። ለዚህም ምክንያቱ እነዚህ ነገሮች ምን እንደ ተከሰተ የሚያሳዩ ታሪኮች ብቻ ሳይሆኑ፥ ክርስቶስ እንደ ሞት ባሉት ነገሮች ላይ መለኮታዊ ኃይል እንዳለው የሚያሳዩና መሢሕነቱን የሚገልጹ መሆናቸው ነው (ዮሐ 6፡30)። በዚህ የራእይ ምልክት ዮሐንስ ሴቲቱና ልጁ ከዘንዶው ጋር ያደረጉትን ትግል ያመለክታል።

ዮሐንስ በዚህ ራእይ ላይ ባለ 12 ከዋክበት አክሊል የደፋች እርጉዝ ሴት ይመለከታል። ይህች ዙፋን የሚወርስ ወንድ ልጅ ልትወልድ ያለች ሴት ማን ነበረች? ሦስት አመለካከቶች አሉ። መጀመሪያ፥ አንዳንዶች ይህቺ ሴት የክርስቶስ እናት የሆነችው ማርያም ናት ይላሉ። ሁለተኛ፥ ሌሎች ደግሞ የአማኞች ማኅበረሰብና መንፈሳዊት እስራኤል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ናት ይላሉ። ሦስተኛ፥ አሁንም ሴቲቱ መሢሑ የመጣባት እስራኤል ናት የሚሉ አሉ። ትክክለኛው አመለካከት ሁለተኛው ወይም ሦስተኛው ይመስላል።

ሴቲቱ ልትወልድ ስትል አንድ ታላቅ ቀይ ዘንዶ መጣባት። ይህ ዘንዶ የእግዚአብሔርና የልጆቹ ጠላት የሆነው ሰይጣን ነው። ዘንዶው ከከዋክብት ሲሶዎቹን ወደ ምድር ጣለ። ይህ ምናልባትም ሰይጣን በኃጢአት የወደቀበትን ሁኔታ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ሰይጣን ከመላእክቱ ሲሶዎቹን (አንድ ሦስተኛ) ይዞ ወድቋል። ሌሎች ደግሞ ይህ ሰይጣን ብዙ አማኞችን ለመግደል መሞከሩን ያሳያል ይላሉ። ዘንዶው ሰባት አክሊሎች ያሉባቸው ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች ነበሩት። ይህ ምናልባትም የዘንዶውን ታላቅ ኃይልና ሥልጣን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ዘንዶው ከሴቲቱ የሚወለደውን የመንግሥት ወራሽ የሆነ ልጅ ለመዋጥ ፈልጎ ከአጠገቧ ቆመ።

ወንዱ ልጅ ኢየሱስ ክርስርቶስን ያመለክታል። ሰይጣን ኢየሱስ ክርስቶስን በኃጢአት ፈተናና በመስቀል ላይ ሞት ሊያጠፋው ሞክሯል። ነገር ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ድል ነሺነቱን ያመለክታል። ከዚያም እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ከሰይጣን ጥቃት አርቆ ወደ መንግሥተ ሰማይ ወስዶታል። ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር መንግሥት ላይ እንዲገዛ የተሰጠውን መብት ማንም አይወስድበትም።

ዘንዶው ሴቲቱን ሊያጠፋት ሲፈልግ (ሴቲቱ እስራኤል ወይም ቤተ ክርስቲያን ትሆናለች) እግዚአብሔር ለአንድ ሺህ ሁለት መቶ ስልሳ ቀናት (ዘመን፥ ዘመናትና የዘመን እኩሌታ) በምድረ በዳ ውስጥ ይሸሽጋታል። (ማስታወሻ፡ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ስልሳ ቀናት፥ ሦስት ዓመት ተኩል ጊዜን ያመለክታሉ። ይህ ደግሞ ሁለቱ ምስክሮችና ይኼኛው ክስተት በእኩል የጊዜ ርዝመት የሚፈጸሙ መሆናቸውን ያመለክታል።) ዘንዶው ሴቲቱን ሊያጠፋ በሚፈልግበት ጊዜ የተፈጠረች ምድር እንኳን ከእግዚአብሔር ጋር ተባብራ ትረዳታለች። ይህ በሰይጣንና በእስራኤላውያን መካከል የሚካሄደውን ጦርነት የሚያመለክት ከሆነ፥ እግዚአብሔር በመጨረሻው የታላቁ መከራ ዘመን ሰይጣን የእስራኤልን ሕዝብ እንዳይጨርስ የሚከላከል መሆኑን ያሳያል። ሴቲቱ ቤተ ክርስቲያን ከሆነች፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን በምድር ላይ ሙሉ ለሙሉ ከመውደም የሚጠብቃቸው መሆኑን ያሳያል። ከሌሎች የዮሐንስ ራእይ ክፍሎች ለመረዳት እንደሚቻለው፥ አማኞች ለእምነታቸው የሚገደሉ መሆኑ ግልጽ ነው። ነገር ግን ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን በአጠቃላይ ሊያጠፋት አይችልም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ዛሬም ሆነ በታሪክ ሁሉ፥ እንዲሁም ሐሳዊ መሢሕ አማኞችን ለማጥፋት በሚፈልግበት በመጨረሻው ዘመን ሕዝቡን ይጠብቃል። ዘንዶው ሴቲቱን ለማጥፋት ባለመቻሉ ልጇን ለማጥፋት ይሞክራል። ይህ እስራኤላውያን ወይም የቤተ ክርስቲያን አማኞችን ሊያመለክት ይችላል፥ በአመዛኙ ሁሉንም አማኞች ይወክላል። ዮሐንስ እንዴት እንደሚገልጻቸው ልብ ብለህ ተመልከት። አማኞች የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚከተሉ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጆች ሁልጊዜም እግዚአብሔርን ለመታዘዝ እንደሚተጉ ያስባል። እነዚህ አማኞች የኢየሱስ ክርስቶስን ምስክርነት ይጠብቃሉ። አማኞች በወንጌሉ ላይ ያላችውን ንጹሕ እምነት በመጠበቅ ከስደት ሁሉ ባሻገር ስለ ክርስቶስ ይመሰክራሉ። ሰይጣን የሴቲቱን ልጅ ለማጥፋት የሞከረው እንዴት ነበር? በራእይ 13 ሰይጣን ሌሎች ሁለት ዓይነት ሰዎችን እንደሚጠቀም ተገልጾአል። ከባህር እንደሚወጣ አውሬ የተገለጸው የመንግሥት መሪ አለ። ይህም ሐሳዊ መሢሕ ነው። ከምድር እንደሚወጣ የተገለጸው ደግሞ ሃይማኖታዊ መሪ መሆኑን እንመለከታለን።

በምድር ላይ በሰይጣንና በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ከሚካሄደው ጦርነት በስተጀርባ ሌላ ታላቅ ጦርነት አለ። (በራእይ ምዕራፍ 13 እንደምንመለከተው፥ ሰይጣን የመንግሥትና የሃይማኖት መሪዎችን በመጠቀም ጦርነትን ያካሂዳል።) ይህ በሰይጣንና በኃይሎቹ፥ እንዲሁም በእግዚአብሔርና በኃይሎቹ መካከል የሚካሄድ ታላቅ ጦርነት ነው። የእግዚአብሔር ሠራዊት መሪ የሆነው ሊቀ መልአኩ ሚካኤል ሰይጣንና መላእክቱን ከሰማይ ወደ ምድር ይወረውራቸዋል። ይህ ራእይ መቼ እንደ ተፈጸመ አናውቅም። ነገር ግን ይህ በክርስቶስ መስቀል ላይ የተካሄደውን ጦርነት የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ሀ) ክርስቶስ በሞት ጊዜ የተካሄደ ጦርነት። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሚሞትበት ጊዜ ሰይጣን ድል ያገኘ መስሎት ነበር። ክርስቶስ ከሞት ሲነሣ ግን ሰይጣን በሰው ነፍሶች ላይ ያለውን ኃይል በማጥፋት ድል ነሥቶታል (ቆላ. 2፡15 አንብብ)። ለ) በአመዛኙ ይህ የመጨረሻው ዘመን እጅግ ክፉ የሚሆንበትንና የእግዚአብሔር ሕዝብ ለእምነታቸው የሚሞቱበትን ምክንያት የሚያስረዳ ይመስላል። ፍጻሜው እየተቃረበ በሚመጣበት ጊዜ እግዚአብሔር ሰይጣን ከመንግሥተ ሰማይ እንዲርቅ ያደርገዋል። (ሰይጣን በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት እንደሚቀርብ ለመመልከት ኢዮብ 1-2 አንብብ።) ስለዚህ በምድር ላይ ብቻ እንዲሠራ ይገደባል። ሰይጣን አጭር ጊዜ ብቻ እንደቀረው ስለሚገነዘብና እንቅስቃሴዎቹም በምድር ላይ ብቻ በመወሰናቸው፥ የእግዚአብሔርን ዕቅዶችና ሕዝብ ለማጥፋት የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል።

ነገር ግን የሰይጣን ወደ ምድር መምጣት የፍጻሜው መጀመሪያ ሊሆን፥ ክርስቶስ በሁሉም ላይ የሚነግሥስት ጊዜ መምጣቱን የሚያሳይ ነው። ዮሐንስ በራእይ 12፡10-12 ባቀረበው ታላቅ መዝሙር የሁሉም ዘመን አማኞች በሰይጣን ላይ ድል መቀዳጀት እንዳለባቸው ይናገራል። ይህ በተለይም ሰይጣን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማጥፋት ተግቶ በሚሠራበት በመጨረሻው ዘመን አስፈላጊ ነው። ለመሆኑ አማኞች ሰይጣንን የሚያሸንፉት እንዴት ነው? ድምጻቸውን ጮክ አድርገው በመጸለይ ይሆን? ወይስ ከአካባቢያቸው እንዲርቅ በመገሠጽ ነው? ወይስ ወደ ጥልቁ እንዲወርድ በማዘዝ? ዮሐንስ ድል የሚያስገኙትን ሦስት ነገሮች ይጠቅሳል።

ሀ) የበጉ ደም፡ ሰይጣንን የምናሸንፈው የእግዚአብሔር ልጆች፥ የመንግሥቱ አካሎች በመሆንና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም (በክርስቶስ ሞት) በመታመን ነው። በመልካም ሥራችን ድነትን (ደኅንነት) ልናገኝ አንችልም። ነገር ግን የድነትን ነፃ ስጦታ በእምነት እንቀበላለን። ይህም ከሰይጣን መንግሥት አውጥቶ በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት ውስጥ ያኖረናል። አማኞች ሆነን ኃጢአት ስንፈጽምና ሰይጣን ሲከስሰን፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ለኃጢአታችን እንደ ተከፈለና እግዚአብሔርም በነፃ እንዳሰናበተን ልንነግረው እንችላለን። ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ለማደስ ኃጢአታችንን እንናዘዛለን።

ለ) የምስክርነታችን ቃል፡ ስደት ክርስቲያኖች እምነታችንን እንድንደብቅ፥ አፋችንን እንድንዘጋና ምስክርነታችንን እንድናቆም ያደርገናል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ሰይጣን አሸናፊ ይሆናል። ዮሐንስ ሰይጣንን የምናሸንፍበት መንገድ የእግዚአብሔርን ቃል በማወቅና እምነታችንን ለዓለማውያን በማካፈል መሆኑን ይናገራል።

ሐ) ለእምነታችን ለመሞት በመፍቀድ፡ ሕይወታችንን በምንወድበት ጊዜ ሰይጣን በብዙ መንገዶች ሊያሸንፈን ይችላል። ገንዘብን በመጠቀም የዓለምን ነገሮች እንድንፈልግ ይማርከናል። የአመራር አገልግሎታችንን በተዛባ መልኩ እንድንጠቀም ያደርገናል። ፈርተን እምነታችንን እንድንደብቅ ስደትን ይጠቀማል። እነዚህ ሁሉ ራስን የመውደድ ምሳሌዎች ናቸው። ነገር ግን ድል የሚገኘው ለእግዚአብሔርና ለመንግሥቱ በመኖር ነው (ማቴ. 6፡33)። ለራሳችን የራስ ወዳድነትና የትዕቢት ፍላጎቶች በምንሞትበት ጊዜ ሰይጣን ሊያሸንፈን አይችልም። በስደት ጊዜ ጸንተን ስንቆምና ለእምነታችን ስንሞት ሰይጣን ሊያሸንፈን አይችልም። ነገር ግን ሊያገኘን ወደማይችልበት ሰማይ ይልከናል። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞትና በመነሣት ሰይጣንን እንዳሸነፈ ሁሉ፥ እኛም ሰይጣንን የምናሸንፈው ለክርስቶስ በታማኝነት እየኖርን በመሞትና ለዘላለም ከሞት በመነሣት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙውን ጊዜ እኛ ሰይጣንን እናሸንፋለን ብለን የምናስብባቸውን መንገዶች ዮሐንስ ከገለጻቸው ሰይጣንን የማሸነፊያ መንገዶች ጋር አነጻጽር። ለ) እነዚህ ሦስት ነገሮች ሰይጣንን ለማሸነፍ የምትጠቀምባቸው የመሣሪያዎች ክፍሎች የሆኑበትን ሁኔታ ግለጽ።   

፪. ከባህር የወጣው አውሬ (ራእይ 13፡1-10) ዘንዶው ሴቲቱን ለማሸነፍ ባለመቻሉ መንፈሳዊ ልጆቿን ለማጥፋት ይሻል። እነዚህም መንፈሳዊ ልጆቿ አማኞች ናቸው። ስለሆነም ዘንዶው ከባህር አጠገብ ቆሞ አንድ አውሬ ከእርሱ ሥልጣን ተቀብሎ በምድር ላይ እንዲገዛ ይጠራዋል። ሰይጣን የእግዚአብሔርን ልጆች ለማሸነፍ ከሚጠቀምባቸው ሁለት አውሬዎች በስተጀርባ የሚሠራ ኃይል መሆኑ ግልጽ ነው። የመጀመሪያው አውሬ ከባህር ይወጣል። ይህ አውሬ እንደ ዘንዶው ሰባት ራሶች፥ አሥር ቀንዶችና አሥር አክሊሎች ነበሩት። ይህ ምናልባትም ዘንዶው ኃይሉና ሥልጣኑ ለፖለቲካ መሪው እንዴት እንደሚሰጥና በእርሱ አማካኝነት እንዴት እንደሚገዛ የሚያመለክት ይሆናል። አንዳንዶች ራሶች፥ ቀንዶችና አክሊሎች ታላቅ ጥበቡንና ሥልጣኑን እንዲሁም በአገሮች ላይ ያለውን አገዛዝ የሚያሳዩ መሆናቸውን ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ይህ ፖለቲካዊ አውሬ በአሥር መንግሥታት ላይ የሚገዛ መሆኑን ይናገራሉ። ዮሐንስ የዳንኤል 7፡2-7ን ራእይ በመጥቀስ ይህ አውሬ በብሉይ ኪዳን ዘመን በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ የገዙትን የዓለም መንግሥታት ክፉ ባሕርያት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ያስረዳል።

አውሬው ማን ነው? ምንም እንኳን አንዳንዶች ዮሐንስ በሮም ስለነበረው ግዛት እየተናገረ ነው ብለው ቢያስቡም፥ ዮሐንስ በዚህ ስፍራ ለማመልከት የፈለገው ሐሳዊ መሢሕ ተብሎ በሚጠራ መሪ ሥር የሚተዳደረውን የመጨረሻ የዓለም መንግሥት ይመስላል። ዮሐንስ በዚሁ ታላቅ ገዢ ላይ በማተኮር አያሌ ነገሮችን ይነግረናል።

ሀ) የገዢው ኃይልና ሥልጣን የሚመጣው በቀጥታ ከሰይጣን ነው። ልብ ላንል ብንችልም ሰይጣን ዛሬም በተመሳሳይ መንገድ ሰዎችን (በተለይም የመንግሥትና የሃይማኖት መሪዎችን) በመሣሪያነት በመጠቀም የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማጥቃት ይሞክራል። ነገር ግን ይህ የመጨረሻው ገዢ በታሪክ ሁሉ ከታዩት መሪዎች በላይ በሰይጣን ኃይልና ክፋት የተሞላ ይሆናል።

ለ) ከራሶቹ አንደኛው ክፉኛ ይቆስላል። ምሁራን ይህን በሁለት መንገዶች ይተረጉማሉ። በመጀመሪያ፥ ይህ ሐሳዊ መሢሕ ሊገደልና በኋላ ግን ተአምርን በሚመስል መንገድ ከሞት እንደሚነሣ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። ይህም ሰዎች እንዲያመልኩትና ሰፊ ተቀባይነት እንዲያገኝ ይረዳዋል። ሰውዬው ሐሰተኛው ክርስቶስ መሆኑን አትዘንጉ። በመሆኑም የክርስቶስ የመስቀል ላይ ቁስል ድነትን (ደኅንነት) እንደሚያስገኝልን ሁሉ፥ ሐሰተኛው ክርስቶስ ለችግሮች ሁሉ መልስ እንደሆነና ቁስሎቹ እንደሚያሳዩት መለኮታዊ እንደሆነ በመግለጽ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመኮረጅ ይሞክራል። ሁለተኛ፥ ሌሎች ምሁራን ይህ ለሰይጣን የተለያዩ መንግሥታት (ሐሳዊ መሢሕንና መንግሥቱን ጨምሮ) ምን ያህል በቀላሉ የማይሞቱ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው ይላሉ። የሰይጣን መንግሥት የወደቀና የጠፋ ቢመስልም፥ የበለጠ ኃይልን ተላብሶ ይመለሳል።

ሐ) ሐሳዊው መሢሕ ፖለቲካዊ መሪ ብቻ ሳይሆን፥ ከሰዎች አምልኮ የሚፈልግም ጭምር ነው። ሐሰተኛው ክርስቶስ እንደ መሆኑ መጠን፥ የሰዎችን አምልኮ ከእውነተኛው ክርስቶስ ሰርቆ ለመውሰድ ይፈልጋል። በዮሐንስ ዘመን ዶሚቲያን ሰዎች እንዲያመልኩት እንደ ጠየቀ ሁሉ፥ በመጨረሻ ዘመንም ይኸው ሐሳዊ መሢሕ በዓለም ሁሉ የሚኖሩት ሰዎች ሁሉ እንዲያመልኩት ያዝዛቸዋል። ለበጉ በሆነው የሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ ያልተገኘ ማንኛውም ሰው ይህንን ታላቅ መሪ ያመልከዋል።

መ) ሐሳዊው መሢሕ አምላክ ነኝ በማለቱ የትዕቢትና የስድብ ባሕርያትን ያሳያል። እንደ እግዚአብሔር ለመሆን በመፈለጉ ምክንያት የወደቀውን የሰይጣን ባሕሪ ይላበሳል (ራእይ 14፡12-14) አንብብ)። በእግዚአብሔር ላይ በመመካትና በመሳለቅ እርሱን የሚያመልኩትን ያሳድዳቸዋል።

ሠ) ሐሳዊ መሢሕ በምድር ላይ ለአርባ ሁለት ወራት፥ ማለትም ለሦስት ዓመት ተኩል፥ ለአንድ ሺህ ሁለት መቶ ስልሳ ቀናት ወይም ለዘመን፥ ዘመናትና ለዘመን እኩሌታ ይገዛል። (ይህ ሁለቱ ምስክሮች የሚሠሩበትና የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወይም ሕዝብ የሚረገጥበት ጊዜ አውሬው ከሚገዛበት ዘመን ጋር ተመሳሳይ መሆኑን የሚያሳይ ይመስላል።) የሐሳዊው መሢሕ ሥልጣን በምድር ላይ ባሉት ሁሉ ላይ ይሰፋል። ሐሳዊው መሢሕ የመጀመሪያው ዓለም አቀፋዊ መሪ ይሆናል። ምንም እንኳን ሰይጣን ወኪሉ በሆነው ሐሳዊ መሢሕ አማካኝነት ለዘላለም ለመግዛት ቢፈልግም፥ እግዚአብሔር ሁሉንም የሚቆጣጠር አምላክ በመሆኑ የሰይጣንን ኃይል፥ ሥልጣንና የአገዛዝ ዘመን ይወስናል። እግዚአብሔር ለዚህ መሪ የሚገዛበትን ሥልጣን እንደ ሰጠው እናነባለን። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ሁልጊዜም ሰይጣንን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠር መሆኑን ይገልጻል።

ረ) ሐሳዊ መሢሕ አማኞችን በመዋጋት ያሸንፋቸዋል። ቀደም ሲል አማኞች በክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት፥ ታማኞች ሆነው በመጽናትና ለእምነታቸው በመሞት ሰይጣንን እንዳሸነፉ ተመልክተናል (ራእይ 12፡11)። አሁን ደግሞ እግዚአብሔር አውሬው (እና ሌሎች የፖለቲካ መሪዎች አማኞችን እንዲያሸንፉና) እንዲገድሉ ይፈቅድላቸዋል። ምንም እንኳን እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ አማኞችን በስደት ጊዜ ከሞት ቢታደጋቸውም፥ ብዙውን ጊዜ ለእምነታቸው እንዲሞቱ ይፈቅዳል። ዮሐንስ አንዳንድ ክርስቲያኖች ወደ ምርኮ ወይም ወኅኒ እንደሚወርዱ ይናገራል። ሌሎች ደግሞ ይገደላሉ። አማኞች ለሽንፈት በሚጋለጡባት በዚህ ጊዜ ሁለት ባሕርያትን መላበስ ይኖርባቸዋል። በመጀመሪያ፥ በትዕግሥት መጽናት ያስፈልጋቸዋል። ክርስቶስ ክፉ መሪዎችን አጥፍቶ ዘላለማዊ መንግሥቱን እንደሚመሠርት የገባላቸውን የተስፋ ቃል ተመልሶ እስከሚፈጽምበት ጊዜ ድረስ አማኞች በትዕግሥት ሊጠባበቁትና እስከ ሞት ድረስ ሊጸኑ ይገባል። ሁለተኛ፥ ታማኞች መሆን ያስፈልጋቸዋል። ሌላው ሰው በዓለም ውስጥ ምንም ቢያደርግ ወይም ምንም ዓይነት ስደት ቢመጣባቸው አማኞች በኢየሱስ ክርስቶስና በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት መጠበቅ ይኖርባቸዋል። 

የውይይት ጥያቄ፡- ከዚህ ክፍል አማኝ ከስደት ጋር ስላለው ግንኙነት ምን እንማራለን? 

፫. ከመሬት የወጣው አውሬ (ራእይ 13፡11-14) 

ብዙውን ጊዜ ሃይማኖትና መንግሥት አብረው ይሠራሉ። ይህ በዮሐንስ ዘመንም እውነት ነበረ። የሮም ንጉሠ ነገሥት ሕዝቡ እንዲያመልኩት ሲጠይቅ፥ የቤተ መቅደስ ካህናትና የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ይህንኑ ንጉሣዊ አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግና ያልታዘዙትን ሰዎች ለማሳደድ በጋራ ይሠሩ ነበር። ይህ በመጨረሻው ዘመንም የሚከናወን ተግባር ነው።

ሰዎችን ሁሉ ለመቆጣጠርና እንዲያመልኩት ለማድረግ በሚሻው ሐሳዊ መሢሕ የሚመራ ዓለም አቀፍ መንግሥት ከመኖሩ በተጨማሪ፥ በሌላ አውሬ የሚመራ ሃይማኖታዊ ሥርዓትም ይመሠረታል። አንዳንድ ምሁራን ይህ ከመሬት የሚወጣው አውሬ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር የሚሠራውን ፀረእግዚአብሔር ሃይማኖታዊ ሥርዓት በተምሳሌትነት ያሳያል ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ይህ የእግዚአብሔርን እውነት የሚዋጋ ሐሰተኛ ነቢይ ወይም ሃይማኖታዊ መሪ ነው ይላሉ። በመጨረሻው ዘመን ስለሚገለጠው ሁለተኛው ቁልፍ ግለሰብ የተጠቀሰውን ከዚህ በታች ተመልከት፡

ሀ) ከመሬት የሚወጣው አውሬ እንደ በግ ንጹሕና መንፈሳዊ መስሎ ይቀርባል። እንዲያውም በግ እንደሆነው እንደ ክርስቶስ ተመስሎ ሊታይ ይችላል። ነገር ግን እንደ ዘንዶ ይናገራል። ሰይጣን ለቃላቱ ኃይል ስለሚሰጥ ሰዎች እርሱ የተናገረውን ያምናሉ።

ለ) ይህ አውሬ ከባህር በወጣው አውሬ ወይም በሐሳዊ መሢሕ ሥልጣን ይሠራል።

ሐ) የሃይማኖታዊ መሪው ዐቢይ አገልግሎት በምድር ላይ ያሉት ሰዎች ሁሉ ከባህር የወጣውን አውሬና በእርሱም በኩል ሰይጣንን እንዲያመልኩ ማድረግ ነው። ከመሬት የወጣው አውሬ ሰዎች ያመልኩት ዘንድ የሐሳዊ መሢሕን ምስል ያኖራል። ኃይሉ እጅግ ታላቅ በመሆኑ ይህ ምስል ነፍስ ይዘራና ይናገራል።

መ) ሁለተኛው አውሬ እንደ ብሉይ ኪዳን ነቢይ ኃይልን ያገኝና በሰይጣን ኃይል ተአምራትን ይሠራል። ይህም ሰዎች ሐሳዊው መሢሕ አምላክ ነው ብለው እንዲቀበሉት ያደርጋል።

ሠ) ለምስሉ ወይም ለአውሬው የማይሰግዱትን ለመግደል ተግቶ ይሠራል።

ረ) ሃይማኖታዊ መሪው አውሬውን የሚያመልኩ ሰዎች ብቻ በግንባሮቻቸው ወይም በእጆቻቸው ላይ ምልክት የሚቀበሉበትን ሥርዓት ያዘጋጃል። በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች የጥበቃ ምልክት እንደሚደረግላቸው ሁሉ፥ ሰይጣንም የመንግሥቱ ተካፋዮች ለሆኑትና ሐሳዊ መሢሕን ለሚከተሉት ሰዎች ምልክትን ያዘጋጃል። ይህ ለሐሳዊ መሢሕ ታማኝነታቸውን የሚገልጹበት መንገድ ነው። ያለዚህ ምልክት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ አይችልም። ስለሆነም ለእግዚአብሔር ለሚታመኑና የሐሳዊ መሢሕን ምልክት ለመቀበል ለማይፈልጉ ሰዎች ሕይወት መራራ ትሆንባቸዋለች።

ሰ) ክርስቲያኖች ሐሳዊ መሢሕን ለይተው ያውቁታል። ይህም ሊሆን የሚችለው ስሙ ተሠልቶ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ስለሚመጣ ነው። በታሪክ ሁሉ ይህ ቁጥር አማኞች የተለያየ መላ እንዲመቱ አድርጓቸዋል። የተለያዩ ሥርዓቶችን በመከተል፥ እንደ ኔሮ፡ ሂትለር፥ እስታሊን፥ ኪሲንጀር፥ እንዲሁም የሮም ካቶሊክ ጳጳስ የመሳሰሉ ሰዎች ይህንን ቁጥር እንደሚያሟሉ በማሰብ፥ ብዙዎች ሐሳዊ መሢሕ ናቸው ሲሉ ደምድመዋል። ይህ የተለያዩ የቁጥር ቀመሮችን በመጠቀም እገሌ ሐሳዊ መሢሕ ነው እንዳንል ሊያስጠነቅቀን ይገባል። ምክንያቱም ዮሐንስ ቁጥሮችን በተምሳሌታዊ መንገድ ስለሚጠቀም ነው። (ለምሳሌ ያህል፥ ሰባት፥ አሥርንና አሥራ ሁለት ቁጥርን ለፍጹምነት! ይጠቀማል።) ብዙ ምሁራን ዮሐንስ የክርስቶስን ቅዱስነት ከሐሳዊ መሢሕ ኃጢአተኝነት ጋር እያነጻጸረ ነው ብለው ያስባሉ። ክርስቶስ ፍጹም ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ (ስለሆነም ቁጥሩ ሰባት ሰባት ሰባት ይሆናል)፤ ሐሳዊው መሢሕ ቅዱስ መስሎ ሊቃረብ ቢችልም በሰይጣን ኃይል የሚሠራ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ በክፋት የተሞላ ነው። ስለሆኑም ቁጥሩ ስድስት ስድስት ስድስት ይሆናል። የሰባት ቁጥር ፍጹምነት ይጎድለዋል። ዮሐንስ አማኞች ሐሳዊው መሢሕ አምላክና ለሰዎች ሁሉ ችግሮች መፍትሔ የሚሰጥ ነው የሚለውን ውሸት እንዳይቀበሉ ያስጠነቅቃቸዋል። ዮሐንስ ሐሳዊው መሢሕ ሰው ብቻ ሳይሆን፥ የሰይጣን መገለጫ መሆኑን ያስረዳል። ሰይጣን ሕይወቱን ተቆጣጥሮ ተግባሩን እያከናወነበት መሆኑን ያስረዳል። 

የውይይት ጥያቄ፡- በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ከተገለጹት ሦስት አውሬዎች በሰይጣን፥ በመንግሥታት፥ በሃይማኖቶችና በአማኞች መካከል ስላለው ግንኙነት ምን እንማራለን? 

፬. በጉና አንድ መቶ አርባ አራ ሺህዎቹ (ራእይ 14፡1-5)

ዮሐንስ በመጨረሻው ዘመን ውስጥ የሚታዩትን ሦስት ዐበይት ኃይላት ገልጾአል። እነዚህም ዘንዶው (ሰይጣን)፥ ፖለቲካዊ መሪ (ሐሳዊ መሢሕ)፥ እና ሃይማኖታዊ መሪ (ነቢይ) ናቸው። እነዚህ እንደ ውሸተኛ ሥላሴ ናቸው። አሁን ዮሐንስ፥ «በዚህ ጊዜ በአማኞች ላይ ምን ይከሰታል?» የሚለውን ጥያቄ ይመልሳል። ይህንንም የሚያደርገው ቀደም ሲል በጠቀሳቸው አንድ መቶ አርባ አራት ሺህዎቹ ላይ ምን እንደሚደርስ በመግለጽ ነው (ራእይ 7፡4)። እነዚህ ሰዎች እስራኤላውያን አማኞችን ወይም ቤተ ክርስቲያንን ሊያመለክቱ እንደሚችሉ አስተውል። ምሁራን ይህ በራእይ 14፡1-5 የተገለጸው ራእይ የሚፈጸመው በምድራዊቷ የጽዮን ተራራ (ኢየሩሳሌም) ወይም በሰማያዊቷ የጽዮን ተራራ ስለመሆኑ ይከራከራሉ። ነገር ግን ይህ ሰማያዊቷን ጽዮን የሚያመለክት ይመስላል።

ዮሐንስ በዚህ ራእይ ሊያስተላልፍ የፈለገውን መልእክት ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው በመጽናታቸው የዓለም ሥርዓት ለመከተል የማይፈልጉ፥ የዓለምን የተለያዩ አማልእክት እንዲያመልኩ የሚቀርብባቸውን ጫና የማይቀበሉና ካስፈለገም በእምነታቸው ለመሞት የሚፈቅዱ አማኞች፥ አንድ ቀን የላቀ ሽልማት እንደሚያገኙ ነው። ዮሐንስ ስለተባረኩት ሕዝቦች ምን እንደሚል ተመልከት፡-

ሀ) አንድ መቶ አርባ አራት ሺህዎቹ እነርሱ ብቻ የሚያውቁትን መዝሙር ይዘምራሉ። በእግዚአብሔር አብ ፊት ከዓለም መከራዎችና ስደት ሁሉ ነፃ ሆነው ቆመዋል። ወደ እግዚአብሔር ቀርበው የክብርን ስፍራ አግኝተዋል። ይህን መዝሙር ሊዘምሩ የሚችሉት እነርሱ ብቻ ናቸው። ምክንያቱም መዝሙሩ የወጣው ከስደት ባሻገር ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው በመቆየታቸው ነው።

ለ) አንድ መቶ አርባ አራት ሺህዎቹ ሰውነታቸውን በሴቶች ሳያቆሽሹ ንጹሐን ሆነው ኖረዋል። ይህ እነዚህ አማኞች በወሲባዊ ኃጢአት አለመርከሳቸውን ብቻ ሳይሆን፥ በዓለም ውስጥ ካለው ክፋትና ርኩሰት ሁሉ ራሳቸውን እንደ ጠበቁ የሚያሳይ ተምሳሌታዊ አገላለጽ ይመስላል። በሌላ አነጋገር የተቀደሰ ሕይወት ኖረዋል።

ሐ) ባለማቋረጥ በጉን ይከተሉታል። በምድር ላይ በእምነት ዓይኖቻቸው ክርስቶስን በመከተል፥ ትምህርቱን በማድመጥና ለእምነታቸው መሞት በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ሳይቀር ቃሉን በመታዘዝ ደቀ መዛሙርቶቹ ሆነው ተመላልሰዋል። አሁን በትንሣኤ አካላቸው ተከብረው በጉ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የቅርብ ግንኙነት (ኅብረት) እያደረጉ ይኖራሉ።

መ) እነዚህ አማኞች ውሸት ያልተገኘባቸውና እንከን የሌላቸው ነበሩ። በዮሐንስ ራእይ ውስጥ ብዙውን ጊዜ መዋሸት የእግዚአብሔርን ፍርድ የሚያስከትል ኃጢአት መሆኑ ተገልጾአል (ራእይ 21፡8)። ምናልባትም ይህ የሆነው ሰዎች፥ «ቄሳርን ወይም ሐሳዊውን መሢሕ አመልካለሁ» ብለው ከዋሹ በኋላ በልባቸው ክርስቶስን ለማምለክ ሊፈተኑ ስለሚችሉ ይሆናል። ወይም ደግሞ ክርስቲያኖች ነን እያሉ እንደ ዓለማውያን የሚኖሩ ሰዎች በመኖራቸው ምክንያት ይሆናል። እግዚአብሔር ያከበራቸው ሰዎች በክርስቶስ ስላላቸው እምነት እውነቱን ይናገራሉ። በክርስቶስ እናምናለን እያሉ እንደ ዓለማውያን በመመላለስ ሊዋሹም አይፈልጉም። 

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ዮሐንስ በዚህ ራእይ ውስጥ በምድር ላይ ስለምናሳልፈው ሕይወት ለአማኞች ምን ለማስተማር የሚፈልግ ይመስልሃል? ለ) እነዚህ እውነቶች በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ ስለመሆናቸው ግለጽ። 

፭. መላእክት ምድርን በፍርድ ያጭዳሉ (ራእይ 14፡6-20)

ዮሐንስ በዚህ ክፍል ውስጥ ሁለት የተለያዩ የመላእክት ቡድኖችን ይገልጻል። እነዚህም የእግዚአብሔርን ልብና የመጨረሻውን ዘመን ባሕሪ የሚያንጸባርቁትን ተግባራት የሚያከናውኑ ናቸው።

ሀ. ሦስቱ መላእክት (ራእይ 14፡6-13)። ሦስቱ መላእክት እግዚአብሔር፥ የሰው ልጆች ሁሉ ሊያስታውሷቸው የሚገቧቸውን መልእክቶች ያውጃሉ።

 1. የመጀመሪያው መልአክ እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ የሚኖሩ ሰዎች ወንጌልን እንዲሰሙ፥ ከሐሰተኛ አምልኮ እንዲመለሱና እውነተኛውን ፈጣሪ አምላክ እንዲያመልኩ የሚፈልግ መሆኑን ያስተምረናል። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ክርስቶስ ከመመለሱ በፊት እግዚአብሔር አስከፊ ፍርዱንና ዘላለማዊ ቅጣቱን ከማውረዱ በፊት ሰዎች አምነው የሚድኑበትን የመጨረሻ ዕድል ይሰጣቸዋል።
 2. ሁለተኛው መልአክ የባቢሎንን ውድመት ያውጃል። በራእይ 17-18 እንደምንመለከተው፥ ባቢሎን ክፉ የዓለም ሥርዓቶችን በተምሳሌትነት ታመለክታለች። እነዚህ ሥርዓቶች መንግሥታዊ፥ ኢኮኖሚያዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ናቸው። ሥርዓቶቹ ክፋትን ለማስፋፋትና የእግዚአብሔር ፍላጎቶችን ለመዋጋት የሚታገሉ ናቸው። እግዚአብሔር ሰዎች እርሱን የሚቃወም እርምጃ በመውሰድ የባቢሎን ተባባሪዎች እንዳይሆኑ፥ ይህን ካደረጉ ግን የሚፈረድባቸው መሆኑን ያስጠነቅቃል።
 3. ሦስተኛው መልአክ ሰዎች የአውሬውን ምልክት እንዳይቀበሉ ያስጠነቅቃል። ለእኛ ይህ የአውሬው ምልክት የእግዚአብሔርን ቃል የሚጻረር ማንኛውም የዓለም ሥርዓት፥ የሰዎች አስተሳሰብና ተግባር ይሆናል (1ኛ ዮሐ.)። በመጨረሻው ዘመን ግን ይህ ምልክት ሐሳዊው መሢሕን የመከተል መግለጫ ነው። ከእግዚአብሔር ይልቅ ሐሳዊ መሢሕን ለመከተል የሚመርጡ ሰዎች ዘላለማዊ ፍርድ ይጠብቃቸዋል። ይህ መመለሻ የሌለው ገደል ነው። ስለሆነም ሰዎች እግዚአብሔርንና የእርሱን ምልክት መምረጥ ይኖርባቸዋል። ከሰይጣን፥ ከሐሳዊ መሢሕና ከነቢዩ ጋር ከወገኑ፥ ከሰይጣንና ከአውሬዎቹ ጋር ወደ ሲዖል ይጣላሉ። አማኞች የዓለምን ምልክት ተቀብለው ከቅጣት ለማምለጥ እንዳይሞክሩ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። ነገር ግን በትዕግሥት ልንጸና፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ተግባራዊ ልናደርግና ታማኞች ሆነን ለክርስቶስ ልንቆም ይገባል። ከአስፈሪው የፍርድ ቀን የምንድነው ያኔ ብቻ ነው።

ለ) ዓለምን በፍርድ የሚያጭዱ ሁለት መላእክት (ራእይ 14፡14-20)። ዮሐንስ በመጨረሻው ዘመን የሚከሰቱትን የተለያዩ ግለሰቦች መመልከቱን አብቅቶ፥ እግዚአብሔር በምድር ላይ የሚያመጣውን የተሟላና የመጨረሻ ፍርድ ያሳየናል። ይህ ፍርድ እግዚአብሔር መንገዱን በማይቀበሉት ላይ የጽድቅ ቅጣቱን እንደሚያወርድ በሚያሳይ መልኩ ጠቅለል ብሎ ቀርቧል። በራእይ 15-18 ግን ከሰባቱ የጽዋ ፍርዶችና ከባቢሎን ጥፋት ጋር ዘርዘር ብሎ ተገልጾአል። ዮሐንስ በሚያምኑ ሰዎች ላይ ስለሚመጣው ፍርድ ለማብራራት ሁለት የመብል ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። በመጀመሪያ፥ በራእይ 14፡14-16 ዮሐንስ የአጨዳ ምሳሌ ያቀርባል። በዚህ ስፍራ የተጠቀሰው መልአክ ክርስቶስ ሳይሆን፥ ሌላ ታላቅ መልአክ ይመስላል። ይህ መልአክ በእግዚአብሔር ላይ በሚያምጹ ክፉ ኃይላት ሁሉ ላይ ፍርዱን ያመጣል። (ነገር ግን አንዳንዶች ይህ ራእይ አማኞች ከምድር ላይ ተነጥቀው እንደሚሄዱ ያሳያል ብለው ያምናሉ።) ሁለተኛ፥ በራእይ 14፡17-20 ዮሐንስ የወይን ዘለላዎችን ስለመቁረጥ የሚያወሳውን ምሳሌ ይጠቀማል። ይህ ፍርድ የሚመነጨው በሰማይ ካለ መሠዊያ ውስጥ ነው። ይህ ምናልባትም በራእይ 6፡9-11 እግዚአብሔር እስከ መቼ ፍርዱን እንደሚያዘገይ ስለጠየቁት ሰማዕታት ጸሎት ለማስታወስ የቀረበ ሊሆን ይችላል። አሁን እነዚህ ሰዎች የጸሎታቸውን መልስ ያገኛሉ። የፍርድና የበቀል ቀን ደርሷል።

አይሁዶች የወይን ዘለላዎችን በማጨድ ከቆረጡ በኋላ እነዚህኑ ዘለላዎች ከድንጋይ ተቆፍሮ በተዘጋጁት ጉድጓዶች ውስጥ ያኖሩ ነበር። ከዚያም በእግራቸው ይረግጡታል። በዚህ ጊዜ ጭማቂው ወደ አነስተኛ ጉድጓድ ይከማችና ሰዎች ይጠጡታል። አሁን የእግዚአብሔር መላእክት በዓለም ያሉት ክፉ ሰዎች እንዲታጨዱ አዝዟል። ይህ ፍርድ ምን ያህል ታላቅ እንደሚሆን ለመግለጽ ዮሐንስ ደማቸው ከ300 ኪሎ ሜትሮች የበለጠ ጥልቀት እንደሚኖረው (እስከ ፈረሶች ልጓም እንደሚደርስ) ይገልጻል። አንዳንዶች ይህ በዓለም ላይ የሚካሄደውን የመጨረሻ ጦርነት የሚያመለክት ነው ይላሉ (ራእይ 19)። ነገር ግን ዮሐንስ ይህንን ክፍል ያቀረበው የእግዚአብሔር የመጨረሻው ፍርድ ምን ያህል አስከፊ ሊሆን እንደሚችል ለማሳየት ይመስላል። 

ዮሐንስ እግዚአብሔር አፍቃሪ አምላክ ብቻ ላይሆን፥ ፈራጅም እንደሆነ ሊያስገነዝበን ይፈልጋል። እግዚአብሔር ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ፥ ወደ እርሱ እንዲመለሱና ልጆቹ እንዲሆኑ በትዕግሥትና በምሕረት ይጠባበቃል። ነገር ግን በትዕቢት እያመጹ ያሻቸውን ሲያደርጉና በእግዚአብሔርና በመንገዶቹ ላይ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ የፍርድ ቀን ይመጣባቸዋል። ሰይጣንና ክፉ መላእክት፥ የዓለም መንግሥትና የዓለም ሃይማኖቶች ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ተቃውሟቸውን ይገልጻሉ። የእነዚህ ሰዎች ተቃውሞ እርምጃ ለጊዜው የተሳካላቸው ይመስለናል። በመጨረሻው ግን አስከፊውን ፍርድ ከእግዚአብሔር ይቀበላሉ። እግዚአብሔር ጦርነትን፥ መላእክትን፥ ወይም በራእይ 15-16 እንደተጠቀሰው ሌሎች መቅሰፍቶችን ሊጠቀም ይችላል። መጨረሻው ግን ያው አንድ ነው። ይኸውም ኃጢአተኞች የሚቀጡ መሆናቸው ነው። 

የውይይት ጥያቄ፡- እነዚህ ጥቅሶች ከዓለም ጋር ለመወዳጀትና በተመሳሳይ ጊዜ ክርስቶስን ለመከተል ለሚፈልጉ አማኞች ምን ዓይነት ማስጠንቀቂያዎችን ይሰጣሉ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የእረፍት ጊዜ (ራእይ 10፡1-11፡14) እና የሰባተኛው መለከት ፍርድ (ዋይታ 3) ራእይ 11፡15-19

ከበደ ተወልዶ ያደገው በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ነው። ነገር ግን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ በነበረበት ወቅት ጀርባውን ለክርስቶስ ሰጥቶ እንደ እግዚአብሔር ሕጎች ላለመመላለስ ወሰነ። የዐመፀኝነት መንፈሱን ካሳየባቸው መንገዶች መካካል አንዱ ወሲባዊ ኃጢአቶችን መፈጸም ነበር። በትምህርት ቤት ከተለያዩ ሴት ተማሪዎች ጋር ያመነዝር ነበር። ገንዘብ ሲኖረው ደግሞ ወደ ሴተኛ አዳሪዎች ጎራ ማለቱን ተያያዘው። ብዙውን ጊዜ ይህ ባህሪው የጨብጥ በሽታ ያስከትልበት ነበር። ይህም ከተግባሩ እንዲታቀብ እግዚአብሔር ያስተላለፈለት ማስጠንቀቂያ ነበር። እርሱ ግን የእግዚአብሔርን ማስጠንቀቂያ ለመስማት አልፈለገም። ጊዜው እየገፋ ሲሄድ ከበደ የበሽታ ምልክቶች ይታዩበት ጀመር። መድኃኒት ሲወስድ ትንሽ ይቀልለዋል። ወዲያውኑ ደግሞ ይነሣበታል። ክብደትም መቀነስ ጀመረ። አንድ ጊዜ ሐኪም ቤት ሄዶ ሲመረመር የኤድስ ቫይረስ በደሙ ውስጥ እንዳለበትና በቅርብ ጊዜ እንደሚሞት ተነገረው። አሁንም እግዚአብሔር ለከበደ ስለፈጸማቸው ተግባራት ማስጠንቀቂያ በመስጠት ንስሐ የሚገባበትን ዕድል ሰጠው። እርሱ ግን ወደ እግዚአብሔር እንደ መመለስ የቁጣ ስሜት አደረበት። በእግዚአብሔር ላይ ስለ ተቆጣ ንስሐ ለመግባት አልፈለገም። እንዲሁም አኗኗሩን ለመለወጥ አልፈለገም። ይባስ ብሎ ከሌሎች ሰዎች ጋር ወሲባዊ ግንኙነቶችን በመፈጸም ይህንኑ መድኃኒት የሌለው በሽታ ወደ ተለያዩ ሴቶች ማስተላለፉን ተያያዘው። ከእርሱ ጋር የተኙት ሴቶች ደግሞ የበሽታውን ቫይረስ ለሌሎች ወንዶች ማስተላለፍ ጀመሩ። ከበደ እግዚአብሔር የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ለመስማት ቸል ብሎ ሕይወቱን አጥቷል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር ሰዎችን አለማመናቸውና ዐመፀኝነታቸው ስለሚያስከትሉባቸው ውጤቶች የሚያስጠነቅቅባቸውን ሌሎች መንገዶች ግላጽ። ለ) ብዙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ማስጠንቀቂያ ሰምተው ንስሐ የማይገቡት ለምንድን ነው? ሐ) እግዚአብሔር ሰዎችን ለማስጠንቀቅ አደጋን በመጠቀሙ ስለ ባሕሪው ምን እንማራለን? መ) አደጋ በሚመጣበት ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ካለመፈለጋቸው ስለ ሰዎች ልብ ምን እንማራለን?

ከዮሐንስ ራእይ አብዛኛው ክፍል እግዚአብሔር በተለይም በመጨረሻው ዘመን ወደ ምድር በሚልካቸው የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ፍርዶች ላይ አጽንኦት ይሰጣል። እነዚህ አደጋዎች ሰዎችን ለመቅጣት የታሰቡ ናቸው። እንዲሁም አደጋዎቹ ሰዎች ንስሐ ባይገቡ ዘላለማዊ ሞት እንደሚጠብቃቸው ለማስጠንቀቅ የታሰቡ ናቸው። እግዚአብሔር በምሕረቱ ሁልጊዜም ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ እንጂ እንዲሞቱ አይፈልግም (ሕዝ. 18፡21-23 አንብብ)። ነገር ግን የሰዎች ልብ እጅግ ክፉ ከመሆኑ የተነሣ ብዙ ሰዎች አደጋ በሚመጣበት ወቅት ወደ እግዚአብሔር አይመለሱም (ኤር 17፡9)። ነገር ግን ያለ እግዚአብሔር እርዳታ አደጋውን ለማሸነፍና በዐመፀኛነታቸው መንገዳቸው ለመቀጠል ይፈልጋሉ። ሞት በሚመጣበት ጊዜ ንስሐ የምንገባበትን ዕድል እናጣለን። ከዚህ በኋላ የሚጠብቀን ዘላለማዊ ሞትና ሲዖል ይሆናል። ሰዎች ሥራቸው ስለሚያስከትሏቸው ውጤቶች ልናስጠነቅቃቸው አይገባምን? ከዚህ ታላቅ መከራ ለማምለጥ ብቸኛ መንገድ ስለሆነው ክርስቶስ ለሰዎች ልንነግራቸው ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡– ራእይ 10–11 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ለዮሐንስ የሰጠው የመጽሐፍ ጥቅልሉ ጠቀሜታ ምንድን ነው? ለ) ስለ ሁለቱ ምስክሮችና በእነርሱ ላይ ስለተፈጸመው ሁኔታ ግለጽ።

፩. የእረፍት ጊዜ (ራእይ 10፡1-11፡14)  

በብዙ መንገዶች የዮሐንስ ራእይ የሠርግ ፎቶ ይመስላል። በአንድ ሰው ሠርግ ላይ ካልተገኘህ፥ በዚያን ጊዜ የተነሣቸው ፎቶግራፎች ስለ ሠርጉ ብዙ መረጃዎችን ይሰጡሃል። ነገር ግን የክስተቶቹን ቅደም ተከተል አያሳዩህም። የዮሐንስ ራእይ በተለይም መካከለኛው ክፍል (ራእይ 10-18)፣ በመጨረሻው ዘመን ታላላቅ ሚናዎች የሚጫወቱትን ሰዎች የሚገልጽ ይመስላል። ነገር ግን ራእዮቹ የድርጊቶቹን ቅደም ተከተል አያሳዩንም።

ዮሐንስ አሁንም ገለጻውን አቋርጦ የተለያዩ ነገሮችን ይመለከታል። ይህንንም ያደረገው ስለ መጨረሻው ዘመን የተሻለ ግንዛቤ ሊሰጠን ስለፈለገ ነው።

ሀ) መልአኩና ትንሿ መጽሐፍ (ራእይ 10)። በመጀመሪያ የተገለጸው ለዮሐንስ ትንሿን መጽሐፍ እንዲበላት የሰጠው መልአክ ነው። ይህ ዮሐንስ በእስትንፋሰ እግዚአብሔር ከተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ጋር ያለውን ግንኙነት ያመለክታል። በተጨማሪም፥ ዛሬ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ያለንን ግንኙነት ያሳያል። ዮሐንስ ወደ ምድር የተመለሰ ሲሆን፥ ወዲያውኑ አንድ ታላቅ መላእክ ከሰማይ ሲወርድ ያየዋል። መልአኩ በምድር ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዳለው ለማሳየት በባህርና በመሬት ላይ ይቆማል። በእጁ ትንሽ መጽሐፍ ይዟል። ክርስቶስ ከእግዚአብሔር አብ ከወሰዳት መጽሐፍ በተቃራኒ፥ ይህቺኛዋ መጽሐፍ በመጠን አነስ ያለች ስትሆን፥ በጽሑፍ መሞላቷም አልተገለጸም። ይህም እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ ከሚፈጸመው ተግባር ጥቂቱን ብቻ እንደገለጸልን ያሳያል። የተገለጸልን ግን የእግዚአብሔርን እውነት፥ የድነት (ደኅንነትን) መንገድ፥ እንዲሁም በመጨረሻው ዘመን ምን እንደሚከሰት ለመገንዘብ በቂያችን ነው።

መልአኩ ለዮሐንስ ትንሿን መጽሐፍ ከመስጠቱ በፊት በታላቅ ድምጽ ይጮሃል። በዚህም ጊዜ ሰባት ነጎድጓዶች ምላሽ ይሰጣሉ። ዮሐንስ እነዚያ ሰባት ነጎድጓዶች በፍርድ የተናገሩትን ሊጽፍልን ፈልጎ ሳለ መልአኩ ግን እንዳይጽፍ ከልክሎታል። ይህ ራእይ እግዚአብሔር በታሪክና በመጨረሻው ዘመን ስለሚፈጸመው ነገር ጥቂቱን ብቻ እንደገለጸልን ያሳያል። የሚከሰተውና የሚከሰትበትም ምክንያት በአብዛኛው በእግዚአብሔር ምሥጢራት ውስጥ የተደበቀ ነው። ይህም ለሰው ልጆች ያልተገለጸ መሆኑን እንመለከታለን። በታሪክ የመጨረሻዎቹ ቀናት የሚከሰተው ነገር አልተገለጸም። ነገር ግን እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ እንደሚቆጣጠር ለማወቅ የሚያስችል በቂ መረጃ ተሰጥቶናል። መጪዎቹ ጊዜያት ክፉዎችና አስቸጋሪዎች ቢሆኑም፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ጠላቶቹን ሁሉ (ሰዎችም ሆኑ ሰይጣን) ያሽንፋል።

ዮሐንስ የበላት ትንጂ መጽሐፍ እግዚአብሔር ለዮሐንስና በእርሱም በኩል ለእኛ የሰጠንን መለኮታዊ ቃል በተምሳሌትነት ታሳያለች። በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የዮሐንስ ራእይ ተጠቃልሎ እንመለከታለን። መለኮታዊው ትንቢት ኃጢአተኛ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር እንዴት ኅብረት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ስለሚናገር፥ ጣፋጭ ነው። እንዲሁም የኢየሱስን ዘላለማዊ መንግሥትን ክብር ይገልጻል። ይህም ብቻ አይደለም። ለማመን በማይፈልጉ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር የሚያመጣቸውን ፍርዶች ስለሚገልጽ መራራም ነው። ዛሬ ጣፋጩም ሆነ መራራው የእግዚአብሔር ቃል ለሰዎች ሁሉ መነገር አለበት። ዳቦ በምንበላበት ጊዜ በሰውነታችን ሁሉ ተሰራጭቶ ይገነባናል። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ መልአኩ ዮሐንስ ትንሿን መጽሐፍ እንዲበላት ነግሮታል። ይህም የእግዚአብሔርን ቃል ለሌሎቹ ከማጋራታችን በፊት በማጥናት፥ በማሰላሰልና በመታዘዝ የሕይወታችን አካል ልናደርገው እንደሚገባ ያሳያል። ብዙ ሰባኪዎችና አስተማሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከሕይወታቸው ጋር ሳያገናዝቡ ለምእመናን ያስተላልፋሉ። የቤተ ክርስቲያን አባላት ይህንን ግብዝነት በሚመለከቱበት ጊዜ ለአገልጋዮቻቸው አክብሮት ማጣት ብቻ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ ሳይሆን የእነዚህኑ መሪዎች ምሳሌነት ይከተላሉ። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የእግዚአብሔር ቃል በተለይም የዮሐንስ ራእይ እንዴት ጣፋጭም መራራም ሊሆን እንደቻለ ግለጽ። ለ) ዮሐንስ መጽሐፉን በተቀበለ ጊዜ እንዳደረገው ሁሉ እኛስ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ባለን ግንኙነት ምን ልናደርግ ይገባል? ሐ) ሰባኪዎችና አስተማሪዎች መጀመሪያ ከራሳቸው ሕይወት ጋር ሳይዋሃዱ የእግዚአብሔርን እውነት ለሰዎች ሲያስተላልፉ የተመለከትከው እንዴት ነው? ይህ በግላሰቡና በቤተ ከርስቲያን ላይ የሚያስከትለው አደጋ ምንድን ነው?

ለ) ሁለቱ ምስክሮች (ራእይ 11፡1-14)። ሁለተኛዎቹ ምድቦች ሁለት ምስክሮች ናቸው። ይህ በራእይ ውስጥ ለመተርጎም እጅግ ከሚያስቸግሩ ምንባቦች አንዱ ነው። በዚህ ምንባብ ላይ የምሁራኑ አስተሳሰብ በሁለት ዐበይት ቡድኖች የተከፈለ ነው። በመጀመሪያ፥ አንዳንዶች ይህ ትንቢት በታላቁ መከራ ጊዜ በእስራኤል ላይ የሚከሰተውን ሁኔታ ለመግለጽ በሚያስችል መልኩ በቀጥታ መተርጎም አለበት ይላሉ። እነዚህ ምሁራን በመጨረሻው ዘመን አይሁዶች ቤተ መቅደላቸውን እንደገና ገንብተው እዚያው ውስጥ እንደሚያመልኩ ይናገራሉ። ከዚያ በኋላ ግን ሐሳዊው መሢሕ ተነሥቶ ከአይሁዶች እግዚአብሔርን እንዳያመልኩ ይከለክላቸዋል። ብዙ አይሁዶችንም ይገድላል። ነገር ግን እግዚአብሔር ታማኝ አይሁዶች ሙሉ በሙሉ በሐሳዊ መሢሕ እንዳይደመሰሱ ይጠብቃቸዋል። እንዲሁም እግዚአብሔር ሁለት አይሁዶችን መርጦ ቃሉን እንዲናገሩና እንዲመሰክሩ ኃይልን ይሰጣቸዋል። ሁለተኛ፥ ራእዩ ቤተ ክርስቲያንን በተምሳሌትነት የሚያቀርብ ነው የሚሉ ምሁራን አሉ። እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የመመስከርና ሰዎችን የማስጠንቀቅ (ወንጌልን በመስበክ) ኃላፊነት እንደ ሰጣት ይገልጻሉ። እንዲሁም እግዚአብሔር እርሱን ለማምለክ እንዲያስችለንና በውስጣችን በኃይል እንዲሠራ መንፈስ ቅዱስን ሰጥቶናል። እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ከአጠቃላይ ውድመት ቢጠብቃትም፥ አንዳንድ አማኞች በስደት መጎዳታቸው የማይቀር ነው። ነገር ግን በትንሣኤ አማካኝነት ድሉ የራሳችን ስለሆነ ልንጨነቅ አይገባም። የዚህ ራእይ ቁልፍ ተምሳሌቶች የሚከተሉት ናቸው፡-

 1. የቤተ መቅደስ ውጫዊ ክፍል፥ የመሠዊያውና የማምለኪያዎቹ መለካት፡- በዚህ ራእይ ውስጥ ዮሐንስ አንድ መልአክ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሲለካ ተመልክቷል። በብሉይ ኪዳን ዘመን፥ መላእክት አንድን ነገር የሚለካበት ታላቅ በረከት (ኤር. 31፡38-40፤ ዘካ 1፡16) ወይም ጥፋት (አሞፅ 7፡7-9) እንደሚመጣ ለማሳየት ነው። የቤተ መቅደስ ውስጣዊ ክፍል መለካቱ እግዚአብሔር እውነት ተከታዮቹን ለማወቅና ሙሉ ለሙሉ እንዳይወድሙ ለመጠበቅ መፈለጉን የሚያሳይ ይመስላል። ለዚህ ራእይ የሚሰጡ ሁለት ዐበይት አተረጓጎሞች አሉ። ሀ) ይህ ራሳቸውን ለማቆሸሽ ባለመፈለግ ለእግዚአብሔር በታማኝነት ጸንተው የቆሙትን ሰዎች ያመለክታል። እግዚአብሔር እነዚህን ሰዎች ከአካላዊ ሞት ሳይሆን የመንግሥተ ሰማይን ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታ እንዳያጡ የጠበቀ ይመስላል። ለ) ወይም ደግሞ ይህ እግዚአብሔር ሐሳዊ መሢሕ አይሁዶችን ሙሉ ለሙሉ እንዳይጨርስ የሚጠብቃቸው መሆኑን የሚያሳይ ሊሆን ይችላል።
 2. የውጭው አደባባይ፡ መልአኩ አሕዛብ የሚያመልኩበትን ውጫዊ የቤተ መቅደስ አደባባይ አልለካም፡፡ ሀ) ይህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ላልሆኑት ሰዎች ጥበቃ እንደማይደረግላቸውና የኋላ ኋላም እንደሚደመሰሱ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። እሕዛብ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር አሳልፈው ለመስጠት ያልፈለጉትንና የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚያሳድዱትን ዓለማውያንን ይወክላሉ። ለ) ወይም ደግሞ ይህ እግዚአብሔር የሐሳዊ መሢሕ ሠራዊት የኢየሩሳሌምን ከተማ እንዲደመስስና አምልኮዋን ጨምሮ ሁሉንም ነገር እንዲቆጣጠር የሚፈቅድ መሆኑን የሚያመላክት ሊሆን ይችላል።
 3. ሁለቱ ምስክሮች፡– ቤተ ክርስቲያን ወይም እስራኤል ከፍተኛ ስደት በደረሰባቸውና ታላቅ ቀውስ በተከሰተበት በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ሁለት ልዩ ነቢያትን ያስነሣል። የእነዚህ ነቢያት አገልግሎት መመስከር ነው። እነዚህ ምስክሮች ሙሴንና ኤልያስን የሚመስሉ ሲሆን፥ የሚፈጽሟቸው ተአምራትም የእነዚህን አገልጋዮች ይመስላሉ። ለሦስት ዓመት ተኩል ጊዜያት ማንም እንዳይገድላቸው እግዚአብሔር ይጠብቃቸዋል። ከዚያ በኋላ ግን እግዚአብሔር የጥበቃ እጁን ያነሣና ሁለቱ ምስክሮች ከሰይጣን ኃይልን ባገኘው ሐሳዊ መሢሕ ይገደላሉ። ዓለም በእነዚህ ሰዎች መገደል ደስ ስትሰኝ፥ ከሦስት ተኩል ቀናት በኋላ ከሞት ተነሥተው ወደ ሰማይ ያርጋሉ። በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር ሰባ ሺህ ሰዎችን የሚገድል የመሬት መንቀጥቀጥ በመላክ ኃይሉን ይገልጻል። አንዳንዶች እነዚህ ሁለት ምስክሮች እንደ ዮሐንስ ያሉትን የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ለወንጌሉ በድፍረት መቆማቸውን ያመለክታል ይላሉ። ሌሎቹ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊመጣ ሲል እግዚአብሔር ሁለት ልዩ ነቢያትን በመላክ በቅርብ ጊዜ የሚከሰተውን የእግዚአብሔር ፍርድና የክርስቶስን ወንጌል እንዲያውጁ ያደርጋል ብለው ያስተምራሉ። 

ይህ የሁለቱ ምስክሮቹ ራእይ እውነትን በሁለት ደረጃ ዎች ይገልጻል። በመጀመሪያ፥ ሁለቱ ምስክሮች በስደት ጊዜም ሳይቀር ዛሬ ከአማኞች ምን እንደሚጠበቅ ያሳያሉ። እምነታችንን ከመደበቅ ይልቅ የተሰደድን አማኞች ስለ እምነታችን ማወጃችንን መቀጠል ይኖርብናል። የምናገለግለው በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው። ክርስቲያኖች ሕይወታችን በእግዚአብሔር የተጠበቀ መሆኑንና እርሱ የወሰነው ጊዜ ሳይደርስ ማንም እጁን በእኛ ላይ ሊጭን እንደማይችል መረዳት አለብን። ትንሣኤ ሞትን የሚከተል በመሆኑ፥ አማኞች አካላዊ ሞትን መፍራት የለብንም። ሁለተኛ፥ በመጨረሻው ዘመን እግዚአብሔር ሁለት ልዩና ኃይለኛ ነቢያትን የሚያስነሣ ይመስላል። እነዚህ ነቢያት ስለሚመጣው ፍርድ ሰዎችን ለማስጠንቀቅ፥ ንስሐ እንዲገቡ በመጠየቅና በሚፈጽሟቸው ተአምራቶች የእግዚአብሔር ነቢያት መሆናቸውን በማሳየት የእግዚአብሔርን ቃል ያስፋፋሉ። በእነዚህ ሁለት ምስክሮች አማካኝነት የእግዚአብሔር ቃል በዓለም ሁሉ ይሰራጫል። ነገር ግን እግዚአብሔር እነዚህ ምስክሮች እንዲገደሉ ይፈቅዳል። ይሁንና እግዚአብሔር በሁኔታው ላይ ያለውን ተቆጣጣሪነት በማሳየት ሁለቱን ምስክሮች ከሞት ያስነሣቸዋል፤ ያሳደዷቸውን ዓለማውያን ደግሞ ይቀጣል። 

የውይይት ጥያቄ፡– ከዚህ ራእይ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን መሪዎችና በሚያሳድዷቸው ሰዎች መካከል ስላለው ግንኙነት ምን እንማራለን?

፪. የሰባተኛው መለከት ፍርድ (ዋይታ 3) (ራእይ 11፡15-19)

እንደ ሰባተኛው ማኅተም ሁሉ ሦስተኛው ዋይታ የተባለው ሰባተኛው የመለከት ፍርድም በቀጥታ ከአንድ ፍርድ ጋር የተያያዘ አይደለም። ይልቁንም በዚህ ጊዜ የዓለም መንግሥታት ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት ኃይልና ሥልጣን ሥር መዋላቸው ታውጇል። ይህ ሰባተኛው የመለከት ፍርድ ሁለት አሳቦችን ያዋህዳል። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ ጠላቶቹን ለማሸነፍ እንደሚመጣና በራእይ 19 እንደተገለጸው በአገሮች ሁሉ ላይ እንደሚነግሥ ያሳያል። በራእይ 11፡17 ና 19፡11-16 ክርስቶስ ጠላቶቹን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንገሥ መጀመሩን እንመለከታለን። ሁለተኛ፥ ይህ ምናልባትም ሰባት የጽዋ ፍርዶችን የሚያካትት ይሆናል። እነዚህም ፍርዶች ተከታታይነት ያላቸውና የጠነከሩ ሲሆኑ፥ ፍጻሜ የሚያገኙት የክርስቶስ መንግሥት ሲመጣ ነው (ራእይ 15-16)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)