የጳውሎስ የማጠቃለያ ማበረታቻ እና የስንብት ሰላምታ (2ኛ ጢሞ. 4፡1-22)

ጳውሎስ ጢሞቴዎስ የእግዚአብሔር ታማኝ አገልጋይ ሆኖ ሊኖር ስለሚችልበት መንገድ የማጠቃለያ ማበረታቻ ይሰጠዋል (2ኛ ጢሞ. 4፡1-5)።

ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን መሪ ተግባር ምን መሆን እንዳለበት ጠቅለል አድርጎ በመግለጽ ለጢሞቴዎስ ያቀረበውን ምክር ይደመድማል። ጢሞቴዎስ እግዚአብሔር ሕይወቱን እየተመለከተ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልገው ነበር። አንድ ቀን ደግሞ በሕያዋንና በሙታን ላይ በሚፈርድ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ይቀርባል። አንድ መሪ ምን ማድረግ እንዳለበት፥ እንዴት መምራት እንዳለበት ወይም የስኬታማ አመራር ምሥጢሮች ምን ምን እንደሆኑ የሚያብራሩ ብዙ ሊቆች አሉ። ምንም እንኳ የእነዚህ ሊቃውንት ምክር ጠቃሚ ቢሆንም፥ ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ እጅግ ጠቃሚ እውነቶችን ዘርዝሯል።

ሀ) መሪ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት። ጊዜው አመቺ ሆኖ ሰዎች ስብከቱን በሚሰሙበት ጊዜ (በጊዜውም) ወይም ጊዜው አስቸጋሪ ሲሆንና ሰዎች ስብከቱን በማይቀበሉበት ጊዜ (አለጊዜውም)፥ ሕዝቡን የማረም፥ የመገሠጽና የማበረታታት ተግባሩን ማከናወን አለበት። ዘለቄታዊ ውጤት የሚያመጣው የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው። ከዘመኑ የአመራር ሊቃውንት የሚመጡ ምክሮች ወይም ፈውሶችና ተአምራት የእግዚአብሔርን ቃል ያህል ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ አይችሉም። የእግዚአብሔርን ቃል ማስተማር አስፈላጊ ከሚሆንባቸው ምክንያቶች አንዱ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት እየቀረበ በሚመጣበት ጊዜ፥ ብዙ ሰዎች እውነትን ለመስማት የማይፈልጉ መሆናቸው ነው። ሰዎች የሚሰሙት የሚፈልጉትን ስብከት ብቻ ይሆናል። እነዚህም ሰባኪዎች ሕዝቡ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉ ሳይሆን ጊዜያዊ ስሜታቸውን በሚኮረኩሩ ነገሮች ላይ ያተኩራሉ።

ለ) መሪ በተለዋዋጭ ጊዜያትና ሁኔታዎች ግር መሰኘት ወይም መፍራት የለበትም። ሁሉንም ተቋቁሞ በርጋታ መመላለስ ይኖርበታል።

ሐ) መሪ እግዚአብሔር እንዲያልፍ በሚጠይቀው መከራ ሁሉ ውስጥ ማለፍ አለበት። የመሪነት ጎዳና ቀላል አይደለም። ከቤተ ክርስቲያንም ሆነ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ችግሮች ይገጥሙታል። ነገር ግን በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ እግዚአብሔር ሁልጊዜም ከልጆቹ ጋር ነው።

መ) መሪ ዓይኖቹን ከእግዚአብሔር በተቀበላቸው ኃላፊነት ላይ ማኖር አለበት። መሪ በቀላሉ ዓላማውን ሊስትና እግዚአብሔር ያልጠራውን አገልግሎት ለማከናወን ሊሯሯጥ ይችላል። ነገር ግን መሪ እግዚአብሔር የሰጠውን ስጦታ ተጠቅሞ ዓላማውን ማከናወኑ ወሳኝ ነው። ጢሞቴዎስ ለጠፉት ወንጌልን እየሰበከና የወንጌላዊነት ተግባሩን እየተወጣ ቤተ ክርስቲያንን የመገንባት ተግባሩን ማከናወን ነበረበት። ጢሞቴዎስ በአንድ ቦታ መቀመጥ የሚገባው መጋቢ ሳይሆን፥ ለጠፉት የመመስከርና የተዳከሙትን አብያተ ክርስቲያናት የማጠንከር ጸጋ የተሰጠው አገልጋይ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር ምን ዓይነት ስጦታዎች ወይም ጥሪ የሰጠህ ይመስልሃል? ለ) ይህንኑ ተግባር እንዴት እያከናወንህ ነው? ሐ) እግዚአብሔር የሰጠህን ስጦታና ጥሪ ትቶ ወደ ሌላ አገልግሎት መግባት የሚያስከትላቸው ፈተናዎች ምን ምንድን ናቸው? መ) ጳውሎስ ከላይ ያቀረባቸው ትእዛዛት እግዚአብሔር ከእያንዳንዱ መሪ ሕይወት የሚፈልገውን አገልግሎት የሚገልጹት እንዴት ነው?

ጳውሎስ እየቀረበ ስላለው ሞቱ በመግለጽ ጢሞቴዎስ ወደ እርሱ እንዲመጣ ይጠይቃል። ለወዳጆቹም ሰላምታ ይልካል (2ኛ ጢሞ. 4፡6-22)።

ጳውሎስ ይህንን ደብዳቤ ያጠቃለለው የቅርብ ጓደኛውና መንፈሳዊ ልጁ ለነበረው ጢሞቴዎስ የሚሞትበት ጊዜ እንደቀረበ በመግለጽ ነው። ቀደም ሲል ከፍርድ ችሎቱ ሲቀርብ ወዳጆቹ ሁሉ ትተውት ራቁ። ፍርዱም በጳውሎስ ላይ እየጠነከረ መጣ። ነገር ግን ጳውሎስ መራር ከመሆን ይልቅ፥ እግዚአብሔር በቅርብ እንደረዳውና ወንጌሉን ለማሰራጨት እንዳስቻለው ገልጾል። ጳውሎስ ለጊዜው ከአንበሳ አፍ ድኖ ነበር። ይህ ተምሳሌታዊ አገላለጽ የሚያመለክተው ጳውሎስ በቅርቡ እንደሚገደል ነው። ምክንያቱም የሮም ዜግነት ያላቸው ሰዎች በአንበሶች ተበልተው እንዲሞቱ አይደረግም ነበር።

አሁን ግን ጳውሎስ የሞትን ፍርድ ወደሚቀበልበት ችሎት እየቀረበ ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ የራሱን ሕይወት ይገመግማል። ጳውሎስ ራሱን የተመለከተው እንደ ሰማዕት ወይም አሳዛኝ ሁኔታ እንደሚደርስበት ሰው አልነበረም። ይልቁንም ራሱን እንደ መጠጥ መሥዋዕት ይቆጥረዋል። በብሉይ ኪዳን ዘመን ከእንስሳት መሥዋዕት ጋር ከመሠዊያው ሥር የሚፈስ የወይን መሥዋዕት ይቀርብ ነበር። ይህም አይሁዶች እግዚአብሔር ለሰጣቸው በረከት ምሥጋና የሚያቀርቡበት መንገድ ነበር (ዘኁል. 15፡1-12፥ 28፡7፥ 24)። ጳውሎስ ሕይወቱ ለሚወደው ክርስቶስ የቀረበ መሥዋዕት መሆኑን ተመለከተ። ክርስቶስ ደግሞ ለሰዎች ሕይወቱን የሰጠ ዋንኛው መሥዋዕት ነበር። ጳውሎስ በሕይወት ቢኖር ኖሮ ሕይወቱ ሕያው መሥዋዕት ይሆን ነበር (ሮሜ 12፡1-2)። ሲሞት ደግሞ ሕይወቱን ለክርስቶስ በፍቅርና በምስጋና መልሶ ያስረክበዋል። እናም የመሥዋዕትነት ሞት ይሞታል። ጳውሎስ ሕይወቱንና መንፈሳዊ ሩጫውን መለስ ብሎ ሲመለከት፥ ለክርስቶስ ታማኝ ሆኖ መልካሙን ሩጫ ስለሮጠ እግዚአብሔርን ያመሰግናል። ጳውሎስ ወደፊት አሻግሮ በሚመለከትበት ጊዜ ክርስቶስ የጽድቅን አክሊል እንደሚሸልመው ያውቅ ነበር። በጥንት ዘመን አትሌቶች በስፖርት አሸናፊ በሚሆኑበት ጊዜ ከወይንና ከአበባ የተሠራ አክሊል በራሳቸው ላይ ይደረግላቸው ነበር። ነገር ግን መንፈሳዊ ሩጫ ለሚሮጡ ሰዎች ጳውሎስ የተሻለ ሽልማት እንደሚሰጣቸው ይናገራል። ይህም የጽድቅ አክሊል ነው። ጳውሎስ በችሎት ፊት ቀርቦ ሞት እንደሚፈረድበት ቢያውቅም፥ ሞቱ ሽንፈት ሳይሆን እግዚአብሔር ወደ መንግሥተ ሰማይ ሊወስደው የተጠቀመበት መንገድ መሆኑን ተረድቷል። ጳውሎስ ከመሞቱ በፊት ጢሞቴዎስና ዮሐንስ ማርቆስ ወደ ሮም መጥተው ከእርሱና ከሉቃስ ጋር እንዲገናኙ ይፈልጋል። ጢሞቴዎስ በርኖሱን ይዞላት እንዲመጣ ጠይቋል። ይህም ከእስር ቤቱ ብርድ ይከላከለው ነበር። በተጨማሪም የብራና መጽሐፉን (ምናልባትም መጽሐፍ ቅዱሱን እንዲያመጣለትም ጠይቆታል።)

ጳውሎስ ስለ አንዳንድ የሥራ ጓደኞቹም ጽፎአል። ከጳውሎስና ጢሞቴዎስ ጋር ሲሠራ የቆየው (ቆላ. 4፡14) ዴማስ ከፍርሃት ወይም ከክፉ እሳብ የተነሣ ጳውሎስን ትቶ ወደ ቤቱ ተመልሷል። ቲቶና ቄርቂስን እንዲሁ ወደ ሌላ ስፍራ ሄደዋል። እነርሱ የሄዱት ምናልባት ለአገልግሎት ይሆናል። ኤርስጦስ ጳውሎስ ወዳለበት ወደ ሮም ሊመጣ አልቻለም። ነገር ግን በቆሮንቶስ ማገልገሉን ቀጠለ። ሌላው የእነጳውሎስ የአገልግሎት ጓደኛ ጥሮፊሞስን ታሞ በሚሊጢን ቀረ።

ጳውሎስ በጢሞቴዎስ በኩል ለአንዳንድ ልዩ ጓደኞቹ ሰላምታ በመላክ ይህንን መልእክት ይፈጽማል። እነዚህም አቂላ፥ ጵርስቅላና የሄኔሲፎሩ ቤተሰቦች ናቸው። እንዲሁም ጳውሎስ ከእርሱ ጋር የነበሩት ጥቂት ክርስቲያኖች ለጢሞቴዎስ ያስተላለፉትን ሰላምታ አቅርቧል።

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) የመጨረሻዎቹ የጳውሎስ ቀናት የምንሞትበት ጊዜ በሚቃረብበት ወቅት ሊኖረን ስለሚገባው አመለካከት መልካም ምሳሌዎች የሚሆኑት እንዴት ነው። ለ) የጳውሎስ የመጨረሻው መልእክት ከሆነው የ2ኛ ጢሞቴዎስ ውስጥ ለመንፈሳዊ ሩጫ መሠረታዊ የሆኑትን ትምህርቶች ዘርዝር። ሐ) ከዚህ መልእክት የተፈተነ አገልጋይ ስለመሆን ምን እንማራለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚኖረው ክሕደት እና ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠው ዐደራ (2ኛ ጢሞ. 3፡1-17)

ጳውሎስ በመጨረሻው ዘመን የሰዎች ባሕሪ ምን እንደሚመስል ይገልጻል (2ኛ ጢሞ. 3፡1-9)

ብዙውን ጊዜ ነገሮች ከዓመት ዓመት እየተሻሻሉ ይሄዳሉ ብለን እናስባለን። ብዙ ሰዎች ትምህርት የተከታተሉ አዳዲስ ሥራዎችን በመፍጠር ብዙ ገንዘብ ያገኛሉ፥ ከግብርና ቦታቸው ራቅ ባሉ አካባቢዎች የተሻሉ ቤቶችን ይሠራሉ፥ የራሳቸውን ቴሌቪዥን፥ መኪና ወዘተ… ይገዛሉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በመሳሰሉ ተቋማት አማካኝነት በዓለም ላይ ብዙ ገንዘብና ብዙ ሥራም ማግኘት ይቻላል። ይሁንና ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ዓለምን ሲመለከት ሰዎች ወደ መጨረሻው ዓለም እየቀረቡ በሚመጡበት ጊዜ ዓለም የበለጠ በክፋት እንደምትሞላ ተገንዝቧል። ትምህርትና ሥልጣኔ በመጨረሻው ዘመን ላይ አዎንታዊ ገጽታ ከማሳየት ይልቅ አሉታዊ ጥላ ያጠላል። ጳውሎስ በዚህ ክፍል ውስጥ በመጨረሻው ዘመን የሚለወጡትን አንዳንድ ነገሮች ጠቃቅሷል።

ሀ) ሰዎች ከመጠን በላይ ራስ ወዳድ በመሆን ደስ ያሰኛቸውን እያደረጉ ለራሳቸው ብቻ ይኖራሉ። እግዚአብሔር ስለሚፈልገው ነገር ግድ አይኖራቸውም። ሃይማኖተኞችና መንፈሳውያን ቢመስሉም፥ ከእግዚአብሔር ጋር እውነተኛ ግንኙነት አይኖራቸውም። (የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል።)

ለ) ሰዎች ሌሎችን ለራሳቸው ፍላጎት በማገልገል እውነት እንዳይስፋፋ ያደርጋሉ። ጳውሎስ ሙሴን የተቃወሙትን ሁለት ሰዎች ማለትም አያኔስንና ኢያንበሬስን ይጠቅሳል። እነዚህ ሁለት ሰዎች በብሉይ ኪዳን ውስጥ አልተጠቀሱም። ነገር ግን በአይሁድ ትውፊቶች ውስጥ ሙሴን የተቃወሙ የግብጻውያን የችሎት አስማተኞች መሆናቸው ተገልጾአል (ዘጸ. 7፡11)።

የውይይት ጥያቄ፡– በወላጆችህ ዘመን የነበረውን የሥነ ምግባር መመዘኛ ዛሬ ከብዙ ወጣቶች (ክርስቲያኖችን ጨምሮ) ከምንመለከተው የሥነ ምግባር መመዘኛ ጋር አነጻጽር። ተቀባይነት ያላቸው ልምምዶች ጳውሎስ ከገለጻቸው ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው? ይህ ክርስቶስ ወደሚመለስበት የመጨረሻው ዘመን እየቀረብን መሄዳችንን የሚያመለክተው እንዴት ነው?

ጳውሎስ ከተቃውሞና ፈተናዎች ባሻገር እግዚአብሔርን እንዴት በታማኝነት ማገልገል እንደሚያሻ የራሱን ምሳሌነት ጠቅሶ ያብራራል። ጢሞቴዎስ ሐሰትን ለመዋጋት የጳውሎስን ሕይወት መከተልና ቅዱሳት መጻሕፍትን መጠቀም ያስፈልገው ነበር (2ኛ ጢሞ. 3፡10-17)።

ጳውሎስ ስለ መጨረሻው ዘመን ሲያስብ፥ ሁለት የሕይወት መንገዶችን ያነጻጽራል። አጠቃላዩ ማኅበረሰብ አንዱ ሌላውን ለማታለል ሲሞክር ሰይጣን ደግሞ የበለጠ ያታልላቸዋል። እነዚህ ሰዎች ከፈሪሃ እግዚአብሔር ርቀው የተሳካ ሕይወት ለመኖር የቻሉ ቢመስላቸውም፥ የኋላ ኋላ ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል።

ከዚህ በተቃራኒ ጳውሎስ ጢሞቴዎስ የእርሱን ምሳሌነት እንዲከተል ያበረታታዋል። ምንም እንኳን ጳውሎስ ለጊዜው ስደት ቢደርስበትም፥ ሕይወቱን የኖረው ዓላማ ባለው መልኩ ነበር። ይኸውም ወንጌልን በዓለም ሁሉ ማድረስ ነበር። በስደት ጊዜ ታጋሽ፥ ለሰዎች ፍቅርን የሚገልጽና ክርስቶስ በሁኔታዎች ሁሉ እንደሚረዳው የሚተማመን አገልጋይ ሆኖ ተመላልሷል። እያደር እየተናደ በሚሄድ የሕይወት ጠርዝ ላይ ሆኖ ጢሞቴዎስ በእግዚአብሔር ቃል ላይ አጽንኦት እንዲሰጥ ጳውሎስ ያደፋፍረዋል። የእግዚአብሔርን ፍጹማዊ እውነት የሚያገኘው ከቃሉ ነውና። ጳውሎስ የእግዚአብሔር ቃል ሰዎች የፈጠሩት አለመሆኑን ይገልጻል። ነገር ግን እግዚአብሔር አጽናፈ ዓለሙን በቃሉ ትእዛዝ እንደፈጠረ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ሁሉ የመነጨው ከእርሱ ነው። ጢሞቴዎስ ሐሰተኛ ትምህርትን ለመከላከል መጽሐፍ ቅዱስን በዋናነት መጠቀም ያስፈልገው ነበር። ጢሞቴዎስ እውነትን ለማስተማር፥ እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ የማይመላለሱትን ሰዎች ለመገሠጽ፥ ግራ የተጋቡትን ለማረምና ሰዎችን በጽድቅ ጎዳና ለማሠልጠን የእግዚአብሔርን ቃል መጠቀም ነበረበት።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ቆራጥ ወታደር ሆኖ ለክርስቶስ እንዲሠራ ያደፋፍረዋል (2ኛ ጢሞ. 2፡1-26)

ስደት ሲጠናከርና አማኞች ለእምነታቸው የመሞታቸው ጉዳይ ቁርጥ ሲሆን፥ አማኞች በተለይም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሊያስታውሷቸው የሚገቧቸው ወሳኝ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ስለመመላለስ የሚያስተምሩ ቁልፍ እውነቶች ምን ምንድን ናቸው? እምነታችን ለቀጣዩ ትውልድ በጥንቃቄ መተላለፉን እንዴት ልናረጋግጥ እንችላለን? ጳውሎስ የእግዚአብሔር ሕዝብ ታማኝ መሪ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለጢሞቴዎስ ያብራራል።

ሀ) ታማኝ የቤተ ክርስቲያን መሪ የወንጌሉን እውነት ብቃት ላላቸው ሰዎች በጥንቃቄ ያስተምራል። ይህም እምነቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይቋረጥ እንዲተላለፍ ያስችላል። ጳውሎስ የወንጌሉን ወሳኝ እውነቶች ወዳጁና ሠልጣኙ ለነበረው ጢሞቴዎስ አስተላልፎአል። አሁንም ጢሞቴዎስ ታማኝ ሰዎችን ፈልጎ እነዚህን እውነቶች እንዲያስተምር ይመክረዋል። ጳውሎስ ሠልጣኞቹን የሚመርጠው በሁለት ዐበይት ብቃቶች ላይ በመመርኮዝ ነበር። በመጀመሪያ፥ ሠልጣኞቹ ለእግዚአብሔርና ለወንጌል እውነቶች ታማኞች መሆን ነበረባቸው። ሁለተኛ፥ የሚመረጡት ሰዎች ሌሎችን የማስተማር ብቃት ያላቸው መሆን ነበረባቸው። ሠልጣኞቹ የተማሩትን እውነት ወስደው ለቤተ ክርስቲያን አባላት ማስተላለፍ ያስፈልጋቸው ነበር። በመጨረሻም፥ እነዚህ ጢሞቴዎስ ያሠለጠናቸው ሰዎች ሌሎችን ሰዎች ማሠልጠን ይኖርባቸዋል። በዚህ ዓይነት መንገድ የወንጌል እውነታዎች ከስሕተት ተጠብቀው ወደ እያንዳንዱ አዲስ ትውልድ ይደርሱ ነበር።

ጳውሎስ ጢሞቴዎስ የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላት በሙሉ ከሚያሠለጥናቸው ሰዎች ጋር እኩል በሆነ ደረጃ እንዲያስተምር አለመናገሩ ልብ ሊባል የሚገባው ነው። ጳውሎስ የሚያሠለጥናችውን ሰዎች በጥንቃቄ እንዲመረጥ ለጢሞቴዎስ ነግሮታል። የሠለጠኑት ሰዎች ደግሞ ቤተ ክርስቲያን በማስተማር የክርስቲያን እምነት ይጠብቃሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሌሎችን በጥንቃቄ መምረጥና ማሠልጠን አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) አብዛኞቹ የቤተ ከርስቲያን መሪዎች ሌሎችን በጥንቃቄ የሚያሠለጥኑ ይመስልሃል? ካልሆነ፥ ለምን? ሐ) የወንጌሉን መሠረታዊ እውነቶች ያስተማረ ማን ነው? መ) አንተስ እነዚህኑ መሠረታዊ እውነቶች ለማን ለማስተማር እየሞከርህ ነው? አንድን ሰው እያስተማርክ ካልሆነ፥ እየተማርክ ባላኸው እውነት እስከ አምስት የሚደርሱትን ክርስቲያን ወጣቶች እንድታስተምር እግዚአብሔር እነዚህን ሰዎች በልብህ ውስጥ እንዲያስቀምጥ በጸሎት ጠይቀው። ሠ) ከሌሎች ሽማግሌዎች ጋር በመመካከር፥ እነዚህን ግለሰቦች ለማስተማርና ደቀ መዝሙር ለማድረግ ፈቃድ ጠይቅ። በየሳምንቱ እነዚህን ወጣቶች የምታስተምርበት ጊዜ ወስን። ረ) ለእነዚህ የአዲስ ትውልድ መሪዎች ምን እውነቶችን ማስተማር ያስፈልጋል?

ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪ እንደ ስደት፥ ሞትና አጠቃላይ የአመራር ችግሮች ያሉትን በትዕግሥት መጋፈጥ ይኖርበታል። የቤተ ክርስቲያን መሪ ከሰይጣንና ከመንግሥቱ ጋር እንደሚዋጋ ወታደር ነው። ስለሆነም፥ በጦር ሜዳ ላይ የሚዋጉ ወታደሮች ጉዳት እንደሚደርስባቸውና ሊሞቱም እንደሚችሉ መገንዘብ ይኖርበታል።

ሐ) መሪ በግል ጉዳዮች ሳቢያ ከአገልግሎቱ መደናቀፍ የለበትም። ማለትም፥ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያጠላልፍም። «የጦር አዛዥ » የሆነውን ክርስቶስን በሚያስከብር መንገድ ይመላለስ ዘንድ የገንዘብን ፍቅር፥ ምቹ አኗኗር፥ የትምህርት ፍቅርና ግላዊ ክብር ወደ ጎን መተው ይኖርበታል።

መ) በውድድሩ የተደነገገውን ሕግ ተከትሎ ኦሎምፒክ ላይ እንደሚሮጥ አትሌት፥ የቤተ ክርስቲያን መሪ ክርስቶስ መንፈሳዊ ሩጫውን እንዲሮጥ በሰጠው ሕግጋት መሠረት ሩጫውን መቀጠል ይኖርበታል። ስለሆነም እንደ የገንዘብ ፍቅር፥ የግል ክብርና ጥቅማ ጥቅም ለማግኘት ማገልገል፥ ወሲባዊ ኃጢአት የመሳሰሉት ነገሮች ከሩጫው ሕግ ውጪ ናቸው። መንፈሳዊ ውድድራችንን አሽንፈን ከክርስቶስ መልካም አደረግህ የሚል የሙገሳ ቃል እንድንሰማ ከተፈለገ፥ ክርስቶስ በሰጠን ደንብ መሠረት መሮጥ ያኖርብናል።

ሠ) የቤተ ክርስቲያን መሪ የወደፊቱን ሽልማት እያስታወሰ እንደ ትጉሕ ገበሬ ጠንክሮ መሥራት ይኖርበታል። ገበሬ መሬቱን ለማለስለስ ጠንክሮ ሲሠራ ይቆይና በመጨረሻው ዘሩን ይዘራል። ከዚያም ሲጠባበቅ ቆይቶ የመከር ጊዜ ሲደርስ አዝመራውን ይሰበስባል። በተመሳሳይ መንገድ፥ የቤተ ክርስቲያን መሪ የወንጌሉን እውነቶች በመትከል ከእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት ጋር በጥንቃቄ ተግባሩን ያከናውናል። ብዙውን ጊዜ ሽልማቱ የሚመጣው በምድር ላይ ሳለህ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን በሰማይ ለክርስቶስ በታማኝነት በማገልገልህ ትሸለማለህ። ስለሆነም፥ በምድር ላይ ፈጣን ሽልማቶችን ከመጠበቅ ይልቅ የቤተ ክርስቲያን መሪ የመንግሥተ ሰማይን በረከቶች በጉጉት መጠበቅ ይኖርበታል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ስለ ወታደር፥ አትሌትና ገበሬ ከተሰጠው ምሳሌ ስለ ቤተ ክርስቲያን እመራር ሌሎች ምን እውነቶችን ልትገነዘብ ትችላለህ? ለ) ሕይወትህን ገምግም፡፡ ምን ዓይነት ወታደር አትሌትና ገበሬ እንደሆንክ ራስህን መለስ ብለህ መርምር። የጦር አዛዥህ ከሆነው ከክርስቶስ ሽልማት ታገኝ ዘንድ ከሕይወትህ ሊለወጡ የሚገባቸው ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?

ረ) ሁልጊዜም የቤተ ክርስቲያን መሪ ሕይወቱና አገልግሎቱን በክርስቶስ ላይ ማተኮር አለበት። ሰዎች ስጦታዎቹን፥ ችሎታዎቹን ወይም ሥልጣኑን እንዲያደንቁለት አይፈልግም። ዋናው ነገር የክርስቶስ ወንጌል እንጂ የመሪው ሁኔታ አይደለም። ምንም እንኳን የቤተ ክርስቲያን መሪ እንደ ጳውሎስ ሊታሰርና ሊገደል ቢችልም፥ ማንም ሰው ሕይወት ለዋጩን የወንጌል መልእክት ሊያስር ወይም ሊገድል አይችልም። የቤተ ክርስቲያን መሪ መልእክቱ ሳይደናቀፍ ወደ ፊት ይገሰግስ ዘንድ የሚገጥመውን ችግር ሁሉ ለመቋቋም መቁረጥ ይኖርበታል።

በ2ኛ ጢሞ. 2፡11-13፥ ጳውሎስ ምናልባትም የቀድሞይቱን ቤተ ክርስቲያን መዝሙር እየጠቀሰ ይሆናል። መዝሙር በታማኝነት መመላለስ ሽልማትን እንደሚያስከትልና ክርስቶስን መካድ ደግሞ ቅጣትን እንደሚያመጣ የሚያመለክት ነው። ከክርስቶስ ጋር ከሞትን (ለኃጢአት ባሕሪያችን ስንሞትና እስከምንሞትበት ጊዜ ድረስ ለክርስቶስ በታማኝነት ስንኖር)፥ ለዘላለም ከእርሱ ጋር እንኖራለን። አሁን ስደትንና መከራን ከታገስን፥ በኋላ በእርሱ ተሸልመኝ የንግሥናው ተካፋዮች እንሆናለን። ነገር ግን ክርስቶስን ከካድን፥ ወደ መንግሥተ ሰማይ ስንደርስ በሆነ መንገድ እርሱም እኛን ይክደናል (ማቴ. 10፡33 አንብብ)። ጳውሎስ የሚናገረው ዓይነት ክህደት አንደኛውን ክርስቶስን ትቶ የሐሰት ጣዖታትን መከተልን የሚያመለክት ይመስላል። እንደ እውነቱ ከሆነ፥ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ለጊዜው ታማኝነት ማጉደላችን የማይቀር ነው። ነገር ግን የሚወድደን ክርስቶስ ምን ጊዜም ታማኝነቱን ስለማያጓድልብን ልንበረታታ ይገባናል።

ሰ. የቤተ ክርስቲያን መሪ በመጨረሻ ለኃፍረት እንዳይጋለጥና ዳሩ ግን ከጌታ ዘንድ ሙገሳ እንዲሰጠው መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ማጥናትና ተግባራዊ ማድረግ ይኖርበታል። ይህም በሐሰተኛ ትምህርት እንዳይወሰድ ወይም ፊሊጦስና ሄሜኔዎስ እንዳደረጉት ሰይጣን የውሸት እውነቶችን ለማሰራጨት በመሣሪያነት እንዳይጠቀምበት ይረዳዋል። ብዙውን ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የጠለቀ ግንኙነት የላቸውም። አንዳንዶች እንዲያውም ጊዜ ወስደው አያነቡትም። አብያተ ክርስቲያናት ወንጌሉን በማያውቁና ከዚህም የተነሣ ከሐሰት ሊጠብቋቸው በማይችሉ መሪዎች ተሞልተዋል። ያልሠለጠነና ያልተማረ የቤተ ክርስቲያን መሪ (ሽማግሌ) በቀላሉ የሰይጣን መሣሪያ ሊሆን ስለሚችል አደገኛ ነው። እንደ ፊሊጦስና ሄሜኔዎስ ሐሰተኛ ነገር አስተምረን የሰዎችን እምነት ልናናጋ እንችላለን። ብዙውን ጊዜ በእግዚአብሔር እውነት የሠለጠኑ ሰዎችም መልካም ስብከት አያቀርቡም። እግዚአብሔር ሕዝቡ ሊሰማ ወደሚገባው እውነት እንዲመራቸው በጸሎት አይጠይቁትም። ሰባኪዎች እግዚአብሔር ቃሉ በተጻፈበት ጊዜ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት ምን እንደሆነ ለመረዳት ይችሉ ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ አያጠኑትም። ስለዚህም ጥቅሶችን ከዐውደ ምንባቡ ውጭ በመጠቀም ጸሐፊው ሊያስተላልፍ የፈለገውን መልእክት ሳይረዱ ይሰብካሉ። አንዳንዶች እንዲያውም፥ መንፈስ ቅዱስ መናገር ያለብኝን ስለሚነግረኝ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የለብኝም ይላሉ። ይህ ጳውሎስ እግዚአብሔር ስለሚያመሰግነው አገልጋይ ከተናገረው ውጪ ነው። ይህ የዝግጅት ጉድለት አደገኛ በመሆኑ ሰይጣን ሐሰተኛ ትምህርቶችን ለማስፋፋት ወይም ሕዝቡ በእምነት እንዳያድግ ለመከላከል ሊጠቀምበት ይችላል።

የእውነትን ቃል በትክክል ለመያዝ ሁለት ዐበይት ነጥቦች ያስፈልጋሉ። በመጀመሪያ፥ «መንፈስ ቅዱስ መጀመሪያ ለአማኞች በሰጠው ጊዜ የዚህ ጥቅስ ወይም ምንባብ መልእክት ምን ነበር?» የሚል ጥያቄ ማንሣት ያስፈልጋል። ይህ ጥያቄ ተፈትኖ የጠራው አገልጋይ እውነቶችን በተገለጹበት ምንባብና በጠቅላላው የመጽሐፍ ቅዱስ ዐውድ እንዲገነዘብ ይረዳዋል። ሐሰተኛ ወይም ሚዛናዊነቱን ያልጠበቀ ትምህርት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሰርጎ ከሚገባባቸው መንገዶች አንዱ ሰዎች አንድን ጥቅስ ወይም እውነት ከዐውዱ ገንጥለው በማውጣት ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስለአነሡት ርእሰ ጉዳይ ምን እንደሚል ሳያገናዝቡ መጠቀማቸው ነው። ሁለተኛው ዐቢይ ነጥብ፥ «ይህ መልእክት ለዛሬው ዘመን ምን ትምህርት ያስተላልፋል? መንፈስ ቅዱስ በዚህ ጥቅስና ምንባብ ውስጥ ያሉትን እውነቶች እንድንጠቀም የሚፈልገው እንዴት ነው?» የሚል ነው። መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል የሰጠው ለዘመናትና ትውልዶች ሁሉ ነው። ነገር ግን ዛሬ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ በመቁጠር በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ የምናደርገው እውነት መንፈስ ቅዱስ መጀመሪያ ለአማኞች የሰጠው መሆን አለበት። ለአንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ የእግዚአብሔር ሕዝብ ለሚጋፈጧቸው ሁነኛ ችግሮች ተዛማጅነት የሌሏቸውን እውነቶች ማስተማሩ አደገኛ ነው። እንዲሁም ደግሞ የቤተ ክርስቲያን መሪ የእግዚአብሔርን ቃል መንፈስ ቅዱስ መጀመሪያ ከገለጠበት መንገድ ውጪ መጠቀሙ አደገኛ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያንህ አገልጋዮች የእውነትን ቃል የሚይዙበት መንገድ ጳውሎስ የተፈተኑ አገልጋዮች እንዲላቸው የሚያደርግ ይመስልሃል? መልስህን አብራራ። ለ) ባለፈው ወር ውስጥ የሰማሃቸውን ስብከቶች አብራራ። ሰባኪው መንፈስ ቅዱስ ምንባቡን መጀመሪያ በገለጠ ጊዜ ሊያስተላልፍ ስለፈለገው መልእከት ትክክለኛ ግንዛቤ ያለው ይመስልሃል? ሰባኪው መንፈስ ቅዱስ መጀመሪያ የገለጠውን እውነት በቀጥታና በግልጽ ለዛሬው ዘመን ክርስቲያናዊ ሕይወት አዛምዷልን? ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት መንፈስ ቅዱስ መጀመሪያ ለገለጠው እውነት ታማኝነት እንዲኖረውና ዛሬ መንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያንህ ሊያስተላልፍ ከሚፈልገው መልእክት ጋር ተዛማጅነት እንዲኖረው ምን ማድረግ ያሻል?

ሸ) የቤተ ክርስቲያን መሪ እግዚአብሔር ሊጠቀምበት ከፈለገ የእግዚአብሔር ንጹሕ መሣሪያ ለመሆን መወሰን አለበት። ይህም «የተቀደሰ ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ» እንዲሆን ያስችለዋል። ጳውሎስ ይህን እውነት ሁለት የሸክላ ዕቃዎችን በምሳሌነት በመጠቀም ያብራራል። ሰዎች እጃቸውን ለመታጠብ የሚጠቀሙት ዓይነት ተራ ሳህንና ለእንግዶች ምርጥ ምግብ ለማቅረብ የሚያስችል የሸክላ ዕቃ አለ። የቤተ ክርስቲያን መሪ በሕይወቱ ውስጥ ንስሐ ያልተገባበት ኃጢአት እንዲኖር ሲፈቅድ፥ ክርስቶስ እንደ ልዩ የሸክላ ዕቃ ሊጠቀምበት እይችልም። በመሆኑም ተራ ዕቃ ይሆናል። ጳውሎስ አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ክርስቶስ የሚጠቀመው ልዩ የሸክላ ዕቃ ለመሆን ሁለት ነገሮችን ማድረግ እንዳለበት ገልጾአል። በመጀመሪያ፥ «ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት መራቅ» አለበት። ሕይወቱንና አገልግሎቱን ከሚያቆሽሹት ኃጢአቶች (የወሲብ ኃጢአቶች፥ የገንዘብና የሥልጣን ፍቅር) መራቅ አለበት። ሁለተኛ፥ የኃጢአት ባሕሪውን እግዚአብሔርን በሚያስከብሩ ነገሮች መተካት አለበት። እነዚህም እንደ ጽድቅ፥ እምነት፥ ፍቅርና ሰላም ያሉ ናቸው።

ቀ) የቤተ ክርስቲያን መሪ ከቤተ ክርስቲያን ምእመናን ጋር ያለውን ግንኙነት መጠበቅ አለበት። በትናንሽ ጉዳዮች ሐሳቡን ከማይቀበሉት ሰዎች ጋር መጣላት የለበትም። ሰዎች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ሲታገሉ በትዕግሥት እያስተማረ ሊረዳቸው ይገባል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ታማኝ ስለ መሆን የተሰጠ ማበረታቻ (2ኛ ጢሞ 1፡1-18)

ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ለወንጌሉ በቆራጥነት እንዲቆም ያበረታታዋል (2ኛ ጢሞ 1፡1-14)

ከአርባ ለሚበልጡ ዓመታት ገብረ እግዚአብሔር እግዚአብሔርን በታማኝነት ሲከተል ቆይቷል። በግል ሕይወቱ፥ እግዚአብሔርን በሙሉ ልቡ ለመውደድና በመንፈሳዊ ሕይወቱ ለማደግ ሲሻ ቆይቷል። በአደባባይ ሕይወቱም እንዲሁ፥ ገብረ እግዚአብሔር በምስክርነትና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተለያዩ እርዳታዎችን በማድረግ እግዚአብሔርን ለማገልገል ጥሯል። ምንም እንኳን የቤተ ክርስቲያኒቱ ሽማግሌ ሆኖ ባይመረጥም፥ በየሳምንቱ በማለዳ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣል። ይህንንም የሚያደርገው ቤተ ክርስቲያኒቱን ለአምልኮ ለማሰናዳት ነበር። የቤተ ክርስቲያን የሥራ ቀን በሚታወጅበት ጊዜ፥ ሁልጊዜም ገብሬ ከሰዎች ቀድሞ ይመጣና ዘግይቶ ከቦታው ይሄዳል። በየቀኑ ሰፊ ጊዜ በጸሎት ያሳልፋል። በተለይም ደግሞ ለቤተ ክርስቲያኒቱና ለመጋቢው አጥብቆ ይጸልያል። የጥበቃ ሠራተኛ የሆነው ገብረ እግዚአብሔር በታማኝነቱ የታወቀ ነበር። በጊዜ ወደ ሥራው በመምጣት፥ ሳያንቀላፋ ተግቶ በመቆየትና ተግባሩን በሚገባ በማከናወን አገልግሎቱን ያበረክታል። ገብሬ ከእርጅናው የተነሣ ሥራውን ለማከናወን ባልቻለ ጊዜ በጡረታ ተገለለ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በጠና ታሞ ሊሞት መቃረቡን ተገነዘበ። በዚህም ጊዜ የቤተ ክርስቲያኒቱ መጋቢ መጥቶ እንዲጠይቀው መልእክተኛ ላከበት። ወጣቱ መጋቢ ሊጸልይለት በመጣ ጊዜ፥ ገበሬ ምን ዓይነት ጸሎት ሊደረግለት እንደሚፈልግ ጠየቀው። ገብሬ ለዚህ ወጣት፥ «በጥሩ ሁኔታ ለመሞት እፈልጋለሁ። እስከ መጨረሻው ድረስ ለክርስቶስ ታማኝ መሆን አለብኝ። እርሱም መልካም አደረግህ ታማኝ ባሪያዬ እንዲለኝ እፈልጋለሁ (ማቴ. 25፡14-30)። ክርስቶስ እንደማያሳፍር መልካም ሠራተኛ እንዲያየኝ እፈልጋለሁ (2ኛ ጢሞ. 2፡15)። በክርስቶስ ካመንኩበት ዕለት ጀምሮ እርሱን በታማኝነት ለማገልገል ስሻ ኖሬአለሁ። ከፍተኛ ስጦታ አልነበረኝም፥ ትምህርት ቤት የመግባትም ዕድል አላገኘሁም። ነገር ግን እግዚአብሔር ያለኝን ሁሉ ለክብሩ እንዲጠቀምበት ፈልጌአለሁ። አሁን ሩጫዬን በመልካም ሁኔታ እንድፈጽም ጸልይልኝ።» ሲል ተናገረ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የገብረ እግዚአብሔር ባሕሪ እግዚአብሔር ከሁላችን የሚጠብቀው አመለካከት መሆኑን ግለጽ። ለ) ይህ ፍላጎት የገብሬን የዕለት ተዕለት ሕይወት እንዴት እንደ መራው አብራራ። ሐ) ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆን በዓለም ከሚታወቀው ስኬት፥ ማለትም እንደ ትምህርት፥ ሀብት፥ ጥሩ ርስት፥ ወዘተ… ካሉት ነገሮች በላይ ለእግዚአብሔር አስፈላጊ የሚሆነው እንዴት ነው? መ) የራስህን ሕይወት ለመገምገም ጊዜ ውሰድ። አሁን ወደ መንግሥተ ሰማይ ብትሄድ እግዚአብሔር ታማኝ አገልጋይ ነበርህ የሚልህ ይመስልሃል? ካልሆነ ታማኝ አገልጋይ እንድትሆንና መንግሥተ ሰማይ በደረስህ ጊዜ መልካም አደረግህ እንድትባል ከባሕሪህና ከተግባርህ ሊለወጥ የሚገባው ምንድን ነው?

የ2ኛ ጢሞቴዎስ መጽሐፍ የተጻፈው ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሕይወቱ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ነበር። ሕይወቱን መለስ ብሎ በተመለከተ ጊዜ፥ ጳውሎስ ሕሊናው ንጹህ እንደነበረ ለመመስከር ችሏል (2ኛ ጢሞ. 1፡3)። መንፈሳዊ ሕይወቱንም በጥሩ ሁኔታ እንዳከናወነ ተረድቷል (2ኛ ጢሞ. 4፡6-8)። ያለምንም ጸጸት ከሚወደው ጌታው መልካም አደረግህ የሚሉትን ቃላት ለመስማት ወደ መንሥተ ሰማይ እየገሰገሰ ነበር። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ፥ ጳውሎስ በሚሞትበት ጊዜ መልካም አደረግህ የሚሉትን እነዚሁኑ ቃላት ለመስማት የሚያስችሉትን ወሳኝ መንፈሳዊ እውነቶች ያብራራል። በዚህ አዛውንቱ ጳውሎስ ለወጣት መንፈሳዊ ልጁ በጻፈው መልእክቱ፥ እግዚአብሔርን አስከብሮ ስለመኖር የሚናገሩ ጠቃሚ እውነቶችን ዘርዝሯል።

ስደት በሚነሣበት ጊዜ ብዙ ክርስቲያኖች በፍርሃት ይናጣሉ። በመሆኑም ብዙዎቹ መመስከር ያቆማሉ። አማኞች መሆናቸውም እንዳይታወቅ ጥረት ያደርጋሉ። አንዳንድ ፈሪ እማኞች አካባቢውን ለቅቀው ሰዎች ወደማያውቋቸው አካባቢዎች ይፈልሳሉ። ሌሎች ግን በሚታሰሩበት ጊዜ እምነታቸውን ይክዳሉ። ይህ ፍርሃት ተፈጥሯዊ ነው። እንደውም ስደትን መፍራት ወይም ሌሎች መሪዎች ምን ይሉኝ ይሆን የሚለው አስተሳሰብ ከጳውሎስ ጋር ከ15 ዓመታት ለሚበዙ ጊዜያት ያገለገለውን ጢሞቴዎስን እየተፈታተነው ነበር። ይህም የጢሞቴዎስን አገልግሎት አደናቅፎታል። ስለሆነም ሐዋርያው ጳውሎስ የ2ኛ ጢሞቴዎስ መልእክቱን የጀመረው ወጣት የሥራ ጓደኛው ፍርሃቱን ተቋቁሞ እግዚአብሔርን በድፍረት እንዲያገለግል በማበረታታት ነበር። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ምክር የሚከተሉትን ነጥቦች ይጠቅሳል፡-

ሀ) ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የነበረውን ጥልቅ ፍቅር በመግለጽ እንደሚጸልይለትና እንደገና ሊያየው እንደሚናፍቅ ይገልጽለታል።

ለ) ጳውሎስ የጢሞቴዎስን የቤተሰባዊ ውርስ፥ እንዲሁም የእናቱንና የአያቱን ጠንካራ እምነት ያስገነዝበዋል። በተጨማሪም ጢሞቴዎስ ከእግዚአብሔር ስለተቀበለው ስጦታና ጥሪ ያሳስበዋል። ምናልባትም ከሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው በኋላ፥ ጳውሎስ ለወጣቱ ጢሞቴዎስ በሚጸልይበት ጊዜ እግዚአብሔር እንደ ጢሞቴዎስ ልዩ መንፈሳዊ ስጦታ የሰጠው ይመስላል። ጳውሎስ የሚናገረው ስለምን ዓይነቱ ስጦታ እንደሆነ አልተጠቀሰም። ምናልባትም በ1ኛ ጢሞ. 4፡14 ላይ የተጠቀሰው የትንቢት ስጦታ ሳይሆን አይቀርም። ምናልባትም ጢሞቴዎስ ሰዎችንና ሐሰተኛ አስተማሪዎችን በመፍራቱ ምክንያት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ለሌሎች የማካፈሉን ስጦታ ከመጠቀም ሳይቆጠብ አልቀረም። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ፍርሃት ከእግዚአብሔር እንዳልሆነ ነግሮታል። ምንም እንኳን ጢሞቴዎስ ዓይናፋርና ፈሪ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ስጦታውን በሰዎች ፊት እንዲጠቀም ኃይልን ይሰጠዋል። እንዲሁም እግዚአብሔር ሰዎችን በሚያስፈርስ ሳይሆን በሚያንጽ መንገድ ስጦታውን እንዲጠቀም ፍቅርን ይሞላበታል። በተጨማሪም የራሳችንን መንፈሳዊ ሕይወት ከመገንባቱ በተጨማሪ፣ ጥራት ያለውን አገልግሎት የምንሰጥባትን ራስን የመግዛት ችሎታ ያላብሰናል። ይህም አገልግሎታችን በተከፈለ ልብ እንዳናከናውን ይረዳናል። ይህ ጥቅስ እያንዳንዱ ክርስቲያን መንፈሳዊ ስጦታውን በማሳደግ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛ ውጤት ማምጣት እንዳለበት ያሳያል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) መንፈሳዊ ስጦታዎችህ ምን ምንድን ናቸው? ለ) እነዚህን ስጦታዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለመጠቀም ምን እያደረግህ ነው? ሐ) በበለጠ ውጤታማነት ትገለገልባቸው ዘንድ እነዚህን ስጦታዎች እያሳደግህ ያለኸው እንዴት ነው?

ሐ) ጳውሎስ ጢሞቴዎስ የስደትና የሥቃይ ፍርሃቱን እንዲያሸንፍ ይነግረዋል። ሀ) በማያምኑ ሰዎች ፊት ስለ ክርስቶስ በድፍረት ለመመስከር፥ ለ) በእስር ቤት ውስጥ በሚገኘው ጳውሎስ ምክንያት ኀፍረት እንዳይሰማው ያስጠነቅቀዋል። ጢሞቴዎስ ስደትን ከመፍራቱ የተነሣ ከጳውሎስ የራቀ ይመስላል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ መከራንና ስደትን ከእግዚአብሔር የተቀበለው ጥሪ አካል አድርጎ እንዲቀበል ያሳስበዋል። ጳውሎስ ስለ ወንጌሉ የነበረው ግንዛቤ ስደትን፥ መከራንና ሞትን ያለ ፍርሃት እንዲቀበል አስችሎታል። ወንጌል የጳውሎስን አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ሞትን የሚጋፈጥበት መንገድ ጭምር የሚለውጥ ነበር። ክርስቶስ ሞትን እንዳሸነፈውና በወንጌሉ አማካኝነት ሕይወትንና ዘላለማዊነትን እንዳመጣ ማመኑ ሞትን እንዳይፈራ እድርጎታል። ጳውሎስ፥ «ያመንሁትን አቃለሁና የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ለመጠበቅ እንዲችል ተረድቻለሁ» ሲል ተናግሯል። ክርስቶስ ሞትን እንዳሸነፈና የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንደሰጠን ካመንን፥ ያ የተስፋ ቃል እውነት እንዳልሆነ በመግለጽ ሞትን እየፈራን መኖር የለብንም።

መ) ጳውሎስ ጢሞቴዎስ የተሰጠውን መልካሙን አደራ እንዲጠብቅ አጽንኦት ሰጥቶ ይመክረዋል። ጳውሎስ እያረጀ ሲሄድ፥ ወንጌልን በጥንቃቄ በመጠበቁ ላይ ማለትም በጤናማ ትምህርት ላይ ሲያተኩር እንመለከተዋለን። ይህንንም ያደረገው የሐሰተኛ አስተማሪዎች እንዳይበርዙት በማሰብ ነው። ጳውሎስ ወንጌሉን፥ ማለትም የክርስቶስ ኢየሱስን ሕይወትና ሞት የሚያመለክተውን እውነት እንደ ማይለወጥ እውነት ይገልጸዋል። ይህ ለባንክ ቤት ብዙ ገንዘብ በአደራ እንደ ማስረከብ ነበር። ገንዘቡ ውድ ዋጋ ስላለው በጥንቃቄ መጠበቅ አለበት። ወንጌልንም በተመለከተ እንዲህ ዓይነት እርምጃ መውሰዱ ተገቢ ነው። ወንጌሉ እንዲለወጥ ማድረጉ ወይም ሐሰተኛ እውነቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ዘልቀው እንዲገቡ መፍቀድ ዘራፊ ባንክ ቤት ውስጥ ገብቶ የተከማቸውን ሁሉ ከሚዘርፍበት ሁኔታ የከፋ ነው። ጢሞቴዎስ እውነትን ብቻውን ሊጠብቅ አይችልም ነበር። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ እውነትን እንዲጠብቅ ሊያበረታታው ይገባ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች የማይለወጠውን የወንጌል እውነት ማወቅና በጥንቃቄ መጠበቅ የሚያስፈልገው ለምን ይመስልሃል?

እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እውነትን እንዲያውቁና እንዲጠብቁ ይፈልጋል። ወንጌሉ በሐሰተኛ ትምህርት እንዲበረዝና እንዲለወጥ ከፈቀዱ፣ መሪዎቹ የሰዎችን ሕይወት ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታ ለአደጋ አጋልጠዋል ማለት ነው። ዋናው ነገር ክርስቲያን የሚለወጥ ስም እንደ ታፔላ ለጥፎ መዞሩ አይደለም። ድነት (ደኅንነት) እና የዘላለም ሕይወት የሚገኙት አንድ ሰው ስለ ክርስቶስና ስለ ሞቱ ትክክለኛ እውነቶችን ሲያውቅና ክርስቶስ የሞተው በእርሱ ምትክ መሆኑን በግሉ አምኖ ሲቀበል ብቻ ነው። በዘመናችን አንድነትን ለማምጣት ስንል እውነትን እንዳንሠዋ መጠንቀቅ ይኖርብናል።

በተጨማሪም ጳውሎስ ልንከላከል እንደሚገባንና እንደማይገባን ስለሚናገራቸው ነገሮች መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። ጳውሎስ የተወሰነ የአምልኮ ስልትን ጠብቀን ለማቆየት እንድንሞክር አላዘዘንም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ያልተቀመጠውን እውነትም እንድንጠብቅ አላስተማረም። አንዱን ቤተ እምነት በመደገፍ ሌላውን እንድንቃወምም አላዘዘንም። ይልቁንም ጤናማውን ትምህርት ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተቀመጡትን መሠረታዊ የአስተምህሮ እውነቶች እንድንጠብቅ አዞናል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ የቤተ እምነታችን አጽንኦት የሆነውንና የምንመርጠውን የአምልኮ ወይም የአኗኗር ስልት ከወንጌሉ አስኳል ለይተን መመልከት መቻል አለብን። ንጹህን ወንጌል ጠብቀን ለማቆየት መጣር አለብን። ነገር ግን እርስ በርሳችን ክርስቲያናዊ ፍቅርና መቻቻልን በማዳበር ቤተ እምነታዊ ልዩነቶችን ከመራገብ መቆጠብ ይኖርብናል። እነዚህ ቤተ እምነታዊ ልዩነቶች የአምልኮ ስልትን ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ያልተቀመጡትን እውነቶች የሚመለከቱ ናቸው። (ስለ መጨረሻው ዘመን ያለን አመለካከት ለዚህ ለቤተ እምነታዊ ልዩነቶች እንደ አብነት የሚጠቀስ ነው።)

ጳውሎስ ከሄኔሲፎሩ በስተቀር ሁሉም እንደተዉት ይናገራል (2ኛ ጢሞ. 1፡15-18)

የስደቱ ውጥረት በሮም ግዛት ሁሉ በተለይም በሮም ከተማ ያየለ ይመስላል። ኔሮ የክርስቶስ ተከታይ ነን የሚሉትን ብዙ ሰዎች ገድሎ ነበር። ሮማውያን የክርስትና መሪዎች ናቸው ብለው የሚያስቧቸው ጴጥሮስና ጳውሎስ ወኅኒ ቤት ታስረው ለእምነታቸው ሊሠዉ ተዘጋጅተው ነበር። ይህ ለክርስቲያኖች ፈታኝ ጊዜ ነበር። እንደ አለመታደል ሆኖ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ጨምሮ ብዙ ክርስቲያኖች ለእምነታቸው ለመሞት ዝግጁ አልነበሩም። በመሆኑም እምነታቸውን በመደበቅ፥ ወይም እንደ ጳውሎስ ካሉት ሰዎች ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ለሰዎች ላለማሳወቅ ጥረት አድርገዋል። ጳውሎስ ከዚሁ የስደት ፍርሃት የተነሣ በእስያ ከሚገኙት አማኞች ብዙዎቹ ከእርሱ ጋር ለመተባበር እንዳልፈለጉ ገልጾአል። እስያ ኤፌሶንና በራእይ ውስጥ የተጠቀሱት ሰባቱ አብያተ ክርስቲያን የሚገኙባት የሮም አውራጃ ነበረች። ጳውሎስ በዚህ መልእክት መጨረሻ ላይ ከጻፈው አሳብ ለመረዳት እንደሚቻለው፥ በእምነታቸው ጸንተው የቆሙ አንዳንድ ክርስቲያኖች ነበሩ። ነገር ግን ከስደት ፍርሐት የተነሣ ብዙዎቹ እምነታቸውን ደብቀዋል።

ጳውሎስ የፊሎጎስንና የሄርዋጌኔስን ፍርሃት ከሄኔሲፎሩ ድፍረት ጋር ያነጻጽራል። እነዚህ ሰዎች በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የታወቁ መሪዎች ነበሩ። ሄኔሲፎሩ ምናልባትም የኤፌሶን ክርስቲያን ሳይሆን አይቀርም። እርሱና ቤተሰቦቹ እምነታቸውን ወይም ከጳውሎስ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ለመደበቅ አልፈለጉም። እንዲያውም ጳውሎስን ለማበረታታት ሲል ሄኔሲፎሩ ወደ ሮም ተጉዟል። በዚያም ጳውሎስን እስኪያገኝ ድረስ ከተማ ለከተማ እየዞረ ፈልጎታል።

ጳውሎስ ይህን ሁኔታ በመጠቀም ሞትም የሚያስከትልብን ቢሆንም እንኳን፥ በስደት ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብን ያስረዳል። በክርስቶስ ያለንን እምነት መደበቅ የለብንም። እንዲሁም ለእምነታቸው የታሰሩትን ሰዎች ከመርዳትና ከእነርሱ ጋር ከመተባበር ወደ ኋላ ማለት የለብንም። ለወንጌሉና ለእርስ በርሳችን ሕይወታችንን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባል። ምክንያቱም ለወንጌል መሞት አማኝን ከክርስቶስ ጋር ወደሚኖርበት ዘላለማዊ ቤት የሚያደርስ በር እንደሆነ ያስተምራል። ፍርሃት ሕይወታችንን እንዲቆጣጠር መፍቀድ የለብንም።

የውይይት ጥያቄ፡- በኮሚኒዝም ዘመን ለእምነቱ የታሰረ አማኝ አነጋግር። ሀ) እምነቱንና ከሌሎች ጋር የነበረውን ግንኙነት ለመደበቅ የተፈተነበት ሁኔታ እንዳለ ጠይቀው። ለ) ከዚህ ይልቅ ምን ለማድረግ መረጠ? ሐ) እግዚአብሔር በዚያ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ እንዴት እንዳበረታታው አብራራ። መ) በእስር ቤት ውስጥ ለክርስቶስ ያላቸውን ምስክርነት መጠበቃቸው፥ በእስር ቤት ውስጥ ከአማኞች ጋር ኅብረት ማድረጋቸው አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሠ) ይህ እውነተኛ እምነት ያላቸውን ሰዎች እምነት የሚያጸናው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የ2ኛ ጢሞቴዎስ መዋቅር እና አስተዋጽኦ

የ2ኛ ጢሞቴዎስ መዋቅር

2ኛ ጢሞቴዎስ እንደ መጽሐፍ ሳይሆን ጳውሎስ ከመሞቱ በፊት የእምነት ልጁ ለሆነው ጢሞቴዎስ የሰጠውን ግላዊ ምክር የሚያስተላልፍ ሆኖ ስለቀረበ፥ ይህንንም መልእክት በአስተዋጽኦ መልክ ማቅረቡ አስቸጋሪ ነው። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ በስደት ውስጥ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንዴት መመላለስ እንዳለበት አስተዋይነት የተሞላበትን ምክር ይለግሰዋል። ይህ መጽሐፍ በአራት ክፍሎች ሊከፈል ይችላል።

 1. ጳውሎስ ጢሞቴዎስ እንዴት እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ለመመላለስ እንደሚችል ይመክረዋል (2ኛ ጢሞ. 1፡2)። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ከፍርሃትና ዓይን አፋርነት ተላቅቆ ለእግዚአብሔር በጽናት እንዲቆምና የክርስቶስ ተከታይ በመሆኑ እንዳያፍር ያስጠነቅቀዋል። በጦርነት ውስጥ መከራ እንደሚቋቋም ብርቱ ወታደር፥ ሕይወቱን ለክርስቶስ በንጽሕና እንደሚጠብቅና ሐሰትን ለመዋጋት የእግዚአብሔርን ቃል በጥንቃቄ እንደሚጠቀም አገልጋይ ሆኖ መመላለስ ያስፈልገው ነበር።
 2. ጳውሎስ የሐሰት ትምህርቶች እየተስፋፉ መሄዳቸውን በመግለጽ ጢሞቴዎስ እንዴት ለእውነት ታማኝ ሆኖ ሊመላለስ እንደሚገባ ያሳስበዋል (2ኛ ጢሞ. 3)። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ የተጠናከረ የሐሰተኛ አስተማሪዎች ተቃውሞ እንደሚደርስበት በመግለጽ፥ ይህንኑ ለመጋፈጥ ራሱን እንዲያዘጋጅ ያሳስበዋል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ የእርሱን ምሳሌነት እንዲከተልና በተቃውሞ ፊት መንፈሳዊ ሕይወቱን እንዲጠብቅ፥ እንደዚሁም ሐሰትን ለመከላከል የእግዚአብሔርን ቃል በጥንቃቄ እንዲያጠናና እንዲጠቀም ያበረታታዋል።
 3. ጳውሎስ ጢሞቴዎስ እንዴት ታማኝ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሆኖ መኖር እንደሚችል የመጨረሻ ማደፋፈሪያ ያቀርብለታል (2ኛ ጢሞ. 4፡1-5)። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ሰዎች ለመስማት ባይፈልጉ እንኳን የእግዚአብሔርን ቃል በማሰራጨት የወንጌል መልእክተኛ ሆኖ አገልግሎቱን በታማኝነት እንዲፈጽም ያበረታታዋል።
 4. ጳውሎስ እየቀረበ ስላለው ሞቱ በመግለጽ፥ ጢሞቴዎስ ወደ እርሱ እንዲመጣ ይጠይቀዋል። በተጨማሪም ለወዳጆቹ ሰላምታ ያስተላልፋል (2ኛ ጢሞ. 4፡6-22)። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በቅርቡ እንደሚሞትና በሰማይ ግን እንደሚከብር ይነግረዋል። ጢሞቴዎስ ዮሐንስ የተባለውን ማርቆስን ይዞ እንዲመጣና ሳይሞት በፊት በቶሎ ወደ ሮም እንዲደርስ ያሳስበዋል። ጳውሎስ በችግሩ ጊዜ ትተውት የተለዩትን ሰዎች ከዘረዘረ በኋላ፥ ድጋፍ ለሰጡት ታማኝ ሰዎች ሰላምታ ይሰጣል።

የ2ኛ ጢሞቴዎስ አስተዋጽኦ

 1. ጳውሎስ ጢሞቴዎስ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንዴት መመላለስ እንደሚገባው ይመክረዋል (2ኛ ጢሞ. 1-2)።

ሀ) ጳውሎስ ጢሞቴዎስ በቆራጥነት ለወንጌሉ እንዲቆም ያበረታታዋል (2ኛ ጢሞ. 1፡1-14)።

ለ) ጳውሎስ ከሄኔሲፎሩ በስተቀር ሁሉም እንደተዉት ይናገራል (2ኛ ጢ ሞ . 1፡15-18)።

ሐ) ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ታማኝ ወታደር ሆኖ ለክርስቶስ እንዲሠራ ያደፋፍረዋል (2ኛ ጢሞ. 2)።

 1. ጳውሎስ የሐሰት ትምህርት እየተስፋፋ እንደሚሄድ በመግለጽ ጢሞቴዎስ ለዚህ የሐሰት ትምህርት እንዴት ምላሽ እንደሚሰጥና በታማኝነት እንደሚቆም ያስገነዝበዋል (2ኛ ጢሞ. 3)።

ሀ. ጳውሎስ በመጨረሻው ዘመን የሰዎች ባሕሪ ምን እንደሚመስል ያብራራል (2ኛ ጢሞ. 3፡1-9)።

ለ. ጳውሎስ በተቃውሞና በፈተናዎች ሳይረቱ እግዚአብሔርን እንዴት በታማኝነት ማገልገል እንደሚቻል የራሱን የሕይወት ምሳሌነት ጠቅሶ ያስረዳል። ጢሞቴዎስ እርሱን በመምሰልና በመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ላይ በመደገፍ ሐሰትን እንዲከላከል ይመክረዋል (2ኛ ጢሞ.3፡10-17)።

 1. ጳውሎስ ጢሞቴዎስ እንዴት ታማኝ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሆኖ እንደሚኖር የማጠቃለያ ማበረታቻ ይሰጠዋል (2ኛ ጢሞ. 4፡1-5)።
 2. ጳውሎስ እየቀረበ ስላለው ሞቱ በመግለጽ፥ ጢሞቴዎስ ወደ እርሱ እንዲመጣ ይጠይቀዋል፥ ለወዳጆቹም ሰላምታ ይልካል (2ኛ ጢሞ. 4፡6-22)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የ2ኛ ጢሞቴዎስ ዓላማ እና ልዩ ባሕሪያት

የ2ኛ ጢሞቴዎስ ዓላማ

የመጀመሪያው ዓላማ፡- ጢሞቴዎስ ከሚጋፈጠው ስደት ባሻገር በእምነቱ እንዲበረታ ለማሳሰብ። በመጨረሻዎቹ ጥቂት ወራት ጳውሎስ ብቸኝነት ተጫጭኖት ነበር። ከጽሑፎቹ እንደምንመለከተው፥ ጳውሎስም እንደኛ ሰው በመሆኑ በአንዳንድ አማኞች ተግባራት ጥልቅ ስሜት ጉዳት ደርሶበት ነበር። ስደትን ከመፍራታቸው የተነሣ ይመስላል ብዙዎቹ የጳውሎስ የግል ጓደኞችና የአገልግሎት ተባባሪዎች ብቻውን ጥለውት ወደየቤቶቻቸው ገቡ። ጳውሎስ ከእስያ አውራጃ ሁሉም ሰው እንደ ተወው ይናገራል። ይህም በኤፌሶን አካባቢ የሚገኝ ስፍራ ሲሆን፥ ጳውሎስ ለረጅም ጊዜያት ያገለገለበት ቦታ ነበር (2ኛ ጢሞ. 1፡15)። አብሮት ያገለግል የነበረው ዴማስ ትቶት ሄደ (2ኛ ጢሞ. 4፡10)። እነዚህ ሰዎች በክርስቶስ ማመናቸውን ይተዉ አይተዉ የታወቀ ነገር የለም። ነገር ግን ጳውሎስ እጅግ በሚፈልጋቸው ጊዜ ትተውት መሸሻቸው በጥልቀት ጎዳው። ነገር ኝ እንደ ሉቃስ ያሉ ጥቂቶች አብረውት እስከ መጨረሻው ቆይተዋል (2ኛ ጢሞ. 4፡11)። የቅርብ ወዳጁ ጢሞቴዎስ እንኳን ከጳውሎስ ጋር ለመተባበር በመፍራቱ ምክንያት እምነቱን ለመደበቅ የሞከረ ይመስላል። ስለሆነም ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ስደትን እንዳይፈራና በእስራቱ ወይም የእስራቱና የሞቱ ምክንያት በሆነው ወንጌል እንዳያፍር ይነግረዋል (2ኛ ጢሞ. 1፡8)።

ሁለተኛ ዓላማ፡- ጳውሎስ በኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለነበሩት ችግሮች ከሰማ በኋላ፥ ኔሮ ስደቱን እያጠናከረ ሲሄድና የሐሰት ትምህርቶች ሲስፋፉ ብዙ ሰዎች በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት እንዳይተዉ ሰግቷል። በመሆኑም ጳውሎስ ጢሞቴዎስ የወንጌልን እውነት እንዲጠብቅ (2ኛ ጢሞ. 1፡14)፣ ተጨማሪ ስደት የሚያስከትልባቸው ቢሆንም (2ኛ ጢሞ. 1፡8፤ 2፡3) በአስቸጋሪ ጊዜያት ወንጌሉን መመስከራቸውን እንዲቀጥሉ (2ኛ ጢሞ. 4፡2) ለማሳሰብ ይፈልጋል። ይህ መልእክት የተጻፈው ለጢሞቴዎስ ብቻ ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያን ሁሉ ነበር። ለዚህም ነው ጳውሎስ በ2ኛ ጢሞቴዎስ 4፡22 ላይ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን ያለው፤ ይህም የኤፌሶንን ቤተ ክርስቲያን የሚያመለክት ነው።

ሦስተኛ ዓላማ፡- ጢሞቴዎስ በጥንቃቄ ሊይዘው በሚገባው የእግዚአብሔር ቃል ላይ አገልግሎቱን በመመሥረት በእምነቱ እንዲጸና ለማበረታታት (2ኛ ጢሞ. 2፡15)።

4ኛ ጥያቄ፡- በዘመናችን ያሉት ክርስቲያኖች እነዚህን እውነቶች በማስታወስ ተግባራዊ ማድረጋቸው አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

የ2ኛ ጢሞቴዎስ መልእክት ልዩ ባሕርያት

 1. ጳውሎስ እውነትን ወይም ከሐዋርያት የተላለፈውን የእውነት አካል በመጠበቅ ላይ ያተኩራል። እዚህ ላይ አጽንኦት የተሰጠው አዲስን እውነት በማብራራት ወይም ሌሎች አስደሳች እውነቶችን በመፈለግ ላይ ሳይሆን፥ ጢሞቴዎስ ትክክል መሆኑን በሚያውቁት እውነት ላይ ነው። ብዙውን ጊዜ ከታላላቅ ሰባኪዎች የሚመጡትን አዳዲስና አስደሳች እውነቶች እንፈልጋለን ከታወቁ አብያተ ክርስቲያናት፥ ልዩ ስጦታ ያላቸውን ሰባኪዎች ወይም በምዕራቡ-ዓለም ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ የናኘ ዝና ያላቸውን አገልጋዮች ለመጋበዝ እንሽቀዳደማለን። ይህ ግን አደገኛ ነገር ነው። ምክንያቱም ጳውሎስ አስተምህሯዊ ግራ መጋባት በሚኖርበት ጊዜ ወሳኙ ነገር የእምነታችንን መሠረት መያዝና በእነዚያ እውነቶች ላይ መጽናት እንደሆነ ያስተምራል። ከጳውሎስ የተነሣው የእውነት መሥመር ለእኛና ከእኛም በኋላ ለሚመጡት ትውልዶች ይደርስ ዘንድ ተግተን ልንጠብቀው ይገባል።
 2. ይህ ደብዳቤ አንድ ሸምገል ያለ ሰው ሊሞት ሲል በዕድሜው ወጣት ለሆነ ሌላ ሰው የሚያስተላልፈውን የመጨረሻ ምስክርነት ወይም ምክር ይመስላል። ጳውሎስ በዚህች አጭር ደብዳቤ ውስጥ ከሕይወት የተማራቸውን ዐበይት እውነቶች ጠቅለል አድርጎ አስቀምጧል። ከሞት ጋር ፊት ለፊት በሚጋፈጡበት ጊዜ፥ ለክርስቲያኖች ጠቀሜታ የሌላቸው እውነቶች አስፈላጊዎች አይሆኑም። የሚያስፈልጓቸው እጅግ ወሳኝ የሆኑ እውነቶች ናቸው። ለዚህም ነው ጳውሎስ ይህንን በደብዳቤው ውስጥ ያካተተው።
 3. ጳውሎስ አለማፈር የሚለውን ቃል አጽንኦት ሰጥቶ ጠቅሷል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ሀ) ስለ እግዚአብሔር ለመመስከር፥ እስረኛ በሆነው በጳውሎስ (2ኛ ጢሞ. 1፡8)፥ ሐ) በወንጌል (2ኛ ጢሞ. 1፡12) እንዳያፍርና መ) ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ እንዳያፍር ታማኝ አገልጋይ ሆኖ እንዲሠራ ያስጠነቅቀዋል (2ኛ ጢሞ. 2፡15)። ጳውሎስ በኔሮ ፊት በተመረመረበት ወቅት ለእግዚአብሔር ታማኝ በመሆኑ ለኀፍረት እንደማይጋለጥ ይናገራል (2ኛ ጢሞ. 4፡16-17)።

4 ጳውሎስ አማኞችን ከተለያዩ ነገሮች ጋር በማነጻጸር የታማኝ አገልጋዮችን ሚና ያብራራል። አማኞች እንደ ልጅ (2ኛ ጢሞ. 2፡1)፣ እንደ ወታደር (2ኛ ጢሞ. 2፡3-4)፥ እንደ አትሌት (2ኛ ጢሞ. 2፡5)፥ እንደ ገበሬ (2ኛ ጢሞ. 2፡6)፥ እንደ ሠራተኛ (2ኛ ጢሞ. 2፡15)፥ እንደ ዕቃ (2ኛ ጢሞ. 2፡20-21) እና እንደ ባሪያ (2ኛ ጢሞ. 2፡24) ተገልጸዋል።

 1. ጳውሎስ አማኝ በክርስቶስ ኢየሱስ ላለው እምነቱ እስራትንና ሞትን እንዴት በእርጋታ እንደሚቀበል ያብራራል። ጳውሎስ ለወንጌሉ መከራን ስለ መቀበል በተደጋጋሚ ጠቅሷል። ይህም የክርስቲያኖች ተለምዷዊ አኗኗር መሆኑን በመግለጽ፥ ክርስቲያኖች መከራ በሚገጥማቸው ጊዜ ከመሸሽ ይልቅ በትዕግሥት እንዲወጡት አሳስቧል (2ኛ ጢሞ. 1፡8፥ 2፡3፥ 8-13)። ጳውሎስ ታላቅ ጀግና መሆኑን ለማሳየት አልፈለገም። ነገር ግን እግዚአብሔር ሁኔታዎችን በመቆጣጠር ላይ መሆኑንና ክርስቲያን የመንግሥተ ሰማይና የእግዚአብሔር ክብር የሚጠብቁት መሆኑን በእርጋታ ያስረዳል።

በዘመናችን፥ ስለ ስደትና ለክርስቶስ ስለ መሞት ለመነጋገር አንፈልግም። ነገር ግን በየዓመቱ 330,000 ሺህ ክርስቲያኖች ለእምነታቸው እንደሚሞቱ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ይህ በክርስቲያኖች ላይ የሚሰነዘር ጥላቻ እየጨመረ መሄዱን የሚያሳይ ሲሆን፥ እኛም አንድ ቀን ለእምነታችን ለመሞት እንገደድ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከገጠመን፥ እሥራትንና ሞትን ክርስቶስን በሚያስከብር መንገድ እንዴት መቀበል እንዳለብን የጳውሎስ ምሳሌነት ያስተምራል።

የውይይት ጥያቄ፡- ስደትና መከራ በሚገጥመን ጊዜ ስለ መንግሥተ ሰማይ የሚኖረን ግንዛቤና እውነት እንዴት ሊረዳን ይችላል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የ2ኛ ጢሞቴዎስ በማን ተጻፈ፣ ለማን ተጻፈ፣ መቼና የት ተጻፈ

የ2ኛ ጢሞቴዎስ ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፡– 2ኛ ጢሞ. 1፡1 አንብብ። ሀ) የመጽሐፉ ጸሐፊ ማን ነው? ለ) መጽሐፉ የተጻፈው ለማን ነው? ሐ) 2ኛ ጢሞቴዎስን በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገብ ቃላት ውስጥ በመመልከት ስለ ጸሐፊው፥ መልእክቱን ስለሚቀበሉት ሰዎችና ስለ መጽሐፉ የተገለጸውን ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።

ጳውሎስ የ2ኛ ጢሞቴዎስ መልእክቱን የጀመረው እንደተለመደው ራሱን፥ «በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነው ጳውሎስ» በማለት ነበር። ልክ እንደ 1ኛ ጢሞቴዎስ ሁሉ፥ ጳውሎስ ይህንንም መልእክት የጻፈው ለጢሞቴዎስ የራሱን ሐዋርያዊ ሥልጣን ለማስገንዘብ ብቻ አልነበረም። ነገር ግን ጢሞቴዎስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተግባራት ለማከናወን በሚፍጨረጨርበት ወቅት ይህንን ደብዳቤ የሥልጣኑ መሠረት አድርጎ እንዲጠቀምበት ይፈልጋል።

መልእክቱ የተጻፈው ለማን ነበር?

ጳውሎስ በዚህ ደብዳቤ መግቢያ ውስጥ ለተወደደው ልጄ ለጢሞቴዎስ ሲል ጽፎአል። ጳውሎስ ትዳር ስላልነበረው ከአብራኩ የወጣ ልጅ አልነበረውም። ጢሞቴዎስ ግን ከ15 ዓመታት በላይ አብሮት የሠራ ከመሆኑም በላይ እንደ ልጁ የሚያየው አገልጋይ ነበር። ስለሆነም ጳውሎስ በሰማዕትነት ከማለፉ ጥቂት ቀደም ብሎ ጥልቅ ፍቅሩን የገለጸበትን መልእክት ለጢሞቴዎስ ጽፎአል። ይህም የጳውሎስ የመጨረሻው መልእክት ነበር።

ጳውሎስ 2ኛ ጢሞቴዎስን የጻፈበት ጊዜና ስፍራ

ምሁራን በጳውሎስ ሕይወት መጨረሻ ምን እንደ ተፈጸመ ይከራከራሉ። አንዳንዶች የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከተጻፈ በኋላ ጳውሎስ በችሎት ፊት ተመርምሮ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በሮም ውስጥ እንደ ተገደለ ያስባሉ። ይህ እውነት ከሆነ 2ኛው የጢሞቴዎስ መልእክት የተጻፈው ከ63-65 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑ ነው። ይህም በሐዋርያት ሥራ ታሪክ መጨረሻ ላይ ጳውሎስ ሊሞት ጥቂት ወራት ሲቀሩት የተጻፈው መሆኑን ያሳያል።

ይሁንና ጳውሎስ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከተጻፈ በኋላ ከእስር ቤት የተፈታ ይመስላል። ከዚያ በኋላ ለቀጣይ አያሌ ዓመታት በምዕራባዊ የሮም ግዛት (ስፔን) ካገለገለ በኋላ ወደ ምሥራቅ ትንሹ እስያና ግሪክ የተጓዘ ይመስላል። በ66 ዓ.ም አካባቢ ጳውሎስ እንደገና ታስሮ ወደ ሮም ተወሰደ። ጳውሎስ ልብሶቹንና መጽሐፎቹን ለመያዝ ጊዜ አለማግኘቱና በኋላ ጢሞቴዎስ እንዲያመጣለት መጠየቁ (2ኛ ጢሞ. 4፡13)፥ በድንገት መታሰሩን የሚያመለክት ይመስላል። በዚህ ጊዜ የችሎቱ ምርመራ ተስፋ የሚጣልበት ባለመሆኑ፥ ጳውሎስ 2ኛ ጢሞቴዎስን በሚጽፍበት ጊዜ የሞት ፍርድ እንደሚፈረድበት ይጠባበቅ ነበር። በዚህ ጊዜ ቤት ተከራይቶ ለመቀመጥና ከጎብኚዎች ጋር ለመነጋገር አልቻለም ነበር። ነገር ግን በሰንሰለት ታስሮ በቀዝቃዛ እስር ቤት እንዲቀመጥ ተደርጓል (2ኛ ጢሞ. 2፡9)። በመሆኑም ጎብኚዎች ሊያገኙትና ሊጠይቁት አልቻሉም (2ኛ ጢሞ. 1፡16-17)። ፍጻሜው እንደ ቀረበ በማወቅ፥ ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ከኤፌሶን ወደ ሮም በመምጣት የሕይወቱን የመጨረሻ ጥቂት ወራት አብሮት እንዲያሳልፍ ጠይቆታል። ስለሆነም ይህ የ2ኛ ጢሞቴዎስ መልእክት የተጻፈው በሮም ከተማ ከ66-67 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ኤፌሶን ከተማ ለነበረው ጢሞቴዎስ ሳይሆን አይቀርም። 2ኛው የጢሞቴዎስ መልእክት ጳውሎስ በእምነቱ ከመሠዋቱ በፊት የጻፈው የመጨረሻ መልእክቱ ነበር።

በዚህ የጳውሎስ የሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ ይገዛ የነበረው ቄሳር ኔሮ በመባል የሚታወቅ ክፉ ሰው ነበር። ይህ ሰው ከ54-68 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የሮም ንጉሠ ነገሥት ነበር። ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ ታሪክ መጨረሻ ላይ ከኔሮ ፊት የቀረበ ሲሆን፥ በዚህ ጊዜ የተፈታ ይመስላል። በ64 ዓ.ም ግን፥ ኃይለኛ እሳት ተነሥቶ አብዛኛውን የሮም ክፍል አቃጠለ። ሕዝቡ ኔሮ እሳቱን እንዳቀጣጠለ በመግለጽ ይከስሰው ጀመር። ምናልባትም ኔሮ ይህን ያደረገው ክብሩን የሚገልጽበትን ሕንጻ ለመገንባት የሚችልበትን ስፍራ ለማግኘት በመፈለጉ ይሆናል። ኔሮ ይህንን ክስ ለማስቀየስ ሲል በሮም ከተማ የነበሩትን ሌሎች የሕዝብ ቡድኖችን ይወቅስ ጀመር። እነዚህም የኔሮ የወቀሳ ማነጣጠሪያዎች ክርስቲያኖች ሲሆኑ፥ የተቀረው የሮም ማኅበረሰብ የእነዚህኑ ክርስቲያኖች እምነቶችና ተግባራት እንደ እንግዳ ነገር ይመለከት ነበር። በመሆኑም ሕዝቡ በክርስቲያኖችና በኔሮ ላይ ቁጣውን ይገልጽ ጀመር። በዚህም ጊዜ የኔሮ ወታደሮች በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን በመያዝ ወደ ስፖርት ስታዲዮሞች ወሰዷቸው። በዚያም ብዙዎቹ እስከነነፍሳቸው ሲቃጠሉ የተቀሩት ከአንበሶች ጋር እንዲፋለሙ ተደርገዋል። ይህ የፀረ ክርስቲያን ስሜት እያደገ በመሄዱ፥ ስደት እየተስፋፋ ይሄድ ጀመር (1ኛና 2ኛ ጴጥሮስ)። ኔሮን ለማክበርና ለእርሱ መሥዋዕት ለማቅረብ ያልፈለጉ ክርስቲያኖች በሙሉ ለከፍተኛ ስደት ተዳረጉ። ምናልባትም ጳውሎስ የክርስቲያኖች መሪ በመሆን ይታወቅ ስለነበር ሳይሆን አይቀርም፥ እርሱና ጴጥሮስ ታስረው ወደ ሮም ከተወሰዱ በኋላ፥ በዚያም ኔሮ ክርስቲያኖችን ማሳደዱን ሊያቆም በተቃረበበት ወቅት ጳውሎስ አንገቱ ተቀልቶ ወደ ዘላለማዊ ቤቱ የተጓዘው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የሁለተኛ ጢሞቴዎስ መግቢያ

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወደሚካሄደው የቀብር ሥነ ሥርዓት እየሄድክ ነው እንበል፥ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ገብተህ ስትቀመጥ፥ ከቤተ ክርስቲያኒቱ መድረክ ላይ የተኛው አስከሬን ያንተው መሆኑን ትገነዘባለህ። የራስህን የቀብር ሥነ ሥርዓት እየተመለከትህ ነው እንበል። ፕሮግራሙን እየተከታተልህ እያለ፥ ከልጆችህ ታላቁ ብድግ ብሎ በልጅነቱ ከአንተ ጋር ስለነበረው ግንኙነትና ስለ አንተ የሚያስታውሳቸውን ነገሮች ለማኅበረ ምእመናኑ ይናገራል። ሁለተኛ፥ ባለቤትህም በበኩሏ ባሏ እንደ መሆንህ መጠን ስለ አንተ የምታስታውሰውን ትናገራለች። ሦስተኛ፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሽማግሌም ስለ አንተ የሚያውቀውንና የሚያስታውሰውን ይናገራል። አራተኛ፥ የሥራ ባልደረባህም እንዲሁ በሥራ ቦታ ምን ዓይነት ሰው እንደነበርክ ይመሰክራል። አምስተኛ፥ የማኅበረሰብህ አባል የሆነ ሰውም እንዲሁ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የነበረህን ድርሻ ያብራራል። ስድስተኛ በመንፈሳዊ ዓይንህ በክርስቶስ ፊት ቆመህ የእርሱን ግምገማ ትሰማለህ። እነዚህ ሰዎች ሁሉ እውነትን የሚናገሩ ሲሆን፥ የሚያሳዝኑህን ነገሮችንም እንዲሁ ይናገራሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ይህን ትዕይንት በአእምሮህ ስትስል፥ ሀ) እያንዳንዱ ሰው ስለ አንተ በእውነት ምን ሲናገር ደስ ይልሃል? ለ) በቀብር ሥነ ሥርዓትህ ላይ እንዲነገሩ የምትፈልጋቸው ምስክርነቶች ስለ ባሕሪህና ስለ ተግባሮችህ አስፈላጊ ነገሮችን ይናገራሉ። ሰዎች ስለ አንተ እንዲናገሩ የምትፈልገውን ከራስህ እውነተኛ ማንነትህ ጋር አነጻጽር። በምትሞትበት ጊዜ የምትፈልገው ነገር የሆንከውን ይሆን ዘንድ ልትለውጣቸው የሚገቡህ የሕይወትህ ክፍሎች ምን ምንድን ናቸው?

መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችንም እንደምንሞትና አንድ ቀን በክርስቶስ ፊት ቆመን ስለ ሕይወታችን የሚሰጠውን ግምገማ እንደምንከታተል ያስተምራል። ያም ግምገማ በክርስቶስ ማመን አለማመናችንን የሚመለከት አይሆንም። ሁሉም የሕይወታችን ክፍሎችና የነበሩን የግንኙነት ዓይነቶች በሙሉ ይገመገማሉ። ዛሬ በሕይወታችን አስፈላጊው ነገር ምን እንደሆነ ለይተን ካላወቅን፥ ክርስቶስ ወይም ሌሎች ሰዎች በምን ዓይነት ባሕርያት ወይ ተግባራት እንደሚያስታውሱን ካልወሰንን፥ አብዛኞቻችን በሕይወት ውስጥ ጠቃሚ በሆኑት ጉዳዮች ላይ እናተኩርም። በምንሞትበት ጊዜ፥ የቤተሰብ ውርሳችን፥ ጎሳችን፥ ትምህርታችን፥ ሀብታችን፥ ወይም ኃይላችን ወሳኝ ጠቀሜታ አይኖራቸውም። ይልቁንም የተሻልን ወላጆችና አፍቃሪ የትዳር ጓደኞች መሆናችን ወሳኝነት ይኖረዋል። እውነትን የምንወድና ለሌሎች የምናስብ፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፥ እውነተኛና ታማኝ ሠራተኞች፥ የማኅበረሰቡን ሕይወት ለማሻሻል የጣርንና ለእግዚአብሔር ክብር በታማኝነት የተመላለስን ሰዎች በሆንን ብለን እንመኛለን። እነዚህ በሰው ሕይወት ውስጥ ጉልህ ሚና ያላቸውና በክርስቶስም ፊት በምንቆምበት ጊዜ የምንገመገምባቸው ነጥቦች ናቸው (1ኛ ቆሮ. 3፡10-15)።

በ2ኛ ጢሞቴዎስ ውስጥ፥ ጳውሎስ በሰማዕትነት ከማለፉ ጥቂት ቀደም ብሎ የጻፈውን የመጨረሻ ደብዳቤ እናገኛለን። ጳውሎስ ሕይወቱን መለስ ብሎ ሲመለከትና ወደፊት እሻግሮ የዘላለምን ሕይወት ሲያይ፥ ስለ ሕይወት የነበረውን አመለካከት ይገልጻል። ጳውሎስ ወደ ኋላ ከዚያ ወደፊት ሲመለከት፥ «በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል፡፡ መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም» ይላል (2ኛ ጢሞ. 4፡6-8)። ጳውሎስ ሊሞት ሲቃረብ ያሳለፈውን ሕይወት የተመለከተው በጸጸት ሳይሆን በእርካታ ነበር። እንዲሁም የወደፊት ሕይወቱን ክርስቶስ ምን ይለኛል በሚል ፍርሃት ሳይሆን በልበ ሙሉነት ቃኝቶታል። ይህ የሆነው ጳውሎስ ሕይወቱን ለወንጌሉ እንደሚገባ አድርጎ እንደኖረ ያውቅ ስለነበር ነው። ከሥራ ጓደኞቹ፥ ከማኅበረሰቡ ጋር የነበረው ግንኙነት ፈሪሃ እግዚአብሔር የነገሠበት ነበር። ስለሆነም በእግዚአብሔር ፊት በሚቆምበት ጊዜ እንደማያፍር ያውቅ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለአንድ ሰው በሕይወቱ መጨረሻ የኋላውን ያለ ጸጸት፥ የፊቱን ደግሞ በልበ ሙሉነት መመልከት አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) አሁን ሞተህ በእግዚአብሔር ፊት ብትቀርብ የምትጸጸትባቸው አንዳንድ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? በክርስቶስ ፊት ብትቆም ምንን ትፈራለህ? በምትሞትበት ጊዜ ከጸጸት ወይም ከፍርሃት ነፃ ትሆን ዘንድ ቅድሚያ በምትሰጣቸው ነገሮች፥ በባሕሪህና በተግባርህ ውስጥ ሊለወጡ የሚገባቸው ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)