ኢየሱስን መቀበል – መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይስ መናፍቃዊ?

እስቲ ለአፍታ በቡድ ማሰብ ትተን በግላችን፣ ለግላችን እናስብ። ሰከን ባለ ስሜት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረንን ቃል እንመርምር። ለማሸነፍ ወይም ለመሸነፍ ሳይሆን ለማወቅ ቃሉን እንመርምር። ‘‘የትኛው ቡድን እንዲህ ያምናል?፣ የትኛውስ እንዲህ አያምንም?’’ የሚለውን ውጤት አልባ ክርክር ወደጎን ትተን ‘‘መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ያለው እውነት፣ የትኛው ነው?’’ በሚል መንፈስ ርዕሰ ጉዳዩን እንመርምር።

ለመሆኑ ኢየሱስን መቀበል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ወይ? መቀበል የሚለው ቃል – ይሁንልኝ፣ አሜን፣ እስማማለው፣ ይህንኑ አረጋግጣለው፣ የራሴ አድርጌዋለሁ፣ እወስዳለሁ፣ ወዘተ የሚሉ ትርጉሞች አሉት። እነዚህን ትርጉሞች ከሚከተሉት የእግዚአብሔር ቃል ላይ እንፈልግ፡-

ማቴዎስ 10፡14 ከማይቀበላችሁም ቃላችሁንም ከማይሰሙ ሁሉ፥ ከዚያ ቤት ወይም ከዚያች ከተማ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ።

ማቴዎስ 10፡41 ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል።

ማርቆስ 6፡11 ከማይቀበሉአችሁና ከማይሰሙአችሁ ስፍራ ሁሉ፥ ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ ከእግራችሁ በታች ያለውን ትቢያ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል አላቸው።

ሉቃስ 9፡5 ማናቸውም የማይቀበሉአችሁ ቢሆኑ፥ ከዚያ ከተማ ወጥታችሁ ምስክር እንዲሆንባቸው ከእግራችሁ ትቢያ አራግፉ።

ዮሐንስ 3፡11 እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም

ዮሐንስ 3፡32 ያየውንና የሰማውንም ይህን ይመሰክራል፥ ምስክሩንም የሚቀበለው የለም።

ዮሐንስ 3፡33 ምስክሩን የተቀበለ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ አተመ።

ከላይ በቀረቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ውስጥ፣ ‘መቀበል’ ማለት ምን ማለት እንደሆነ መጠነኛ ግንዛቤ ከማግኘታችን በተጨማሪ ቃሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ እንግዳ እንዳልሆነ የተረዳን ይመስለኛል። በመቀጠል ኢየሱስን መቀበል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆን አለመሆኑን ከመመርመራችን አስቀድሞ፣ መጽሐፍ ቅዱስ – የእግዚአብሔርን ቃል (መልዕክት) ስለ መቀበል እና መንፈስ ቅዱስን ስለ መቀበል የሚናገረውን በቅደም ተከተል እንመልከት፡-

የእግዚአብሔርን ቃል መቀበል

የሐዋርያት ሥራ 2፡41 ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፥ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ፤

የሐዋርያት ሥራ 8፡14 በኢየሩሳሌምም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደተቀበሉ ሰምተው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ሰደዱላቸው።

ዮሐንስ 17፡8 የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፥ ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ።

ዮሐንስ 12፡48 የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው እርሱ የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል።

የሐዋርያት ሥራ 11፡1 ሐዋርያትና በይሁዳም የነበሩት ወንድሞች አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ።

የሐዋርያት ሥራ 17፡11 እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና። ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ

1ቆሮንቶስ 15፡1 ወንድሞች ሆይ፥ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤

2ቆሮንቶስ 11፡4 የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ።

ገላቲያ 1፡9 አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።

1ተሰሎንቄ 1፡6 ደግሞ እናንተ ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀብላችሁ፥ እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ፤

1ተሰሎንቄ 2፡13 ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን።

ያዕቆብ 1፡21 ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ

የሐዋርያት ሥራ 22፡18 እርሱም፦ ፍጠን ከኢየሩሳሌምም ቶሎ ውጣ፥ ስለ እኔ የምትመሰክረውን አይቀበሉህምና ሲለኝ አየሁት።

2ዮሐንስ 1፡10 ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤

መንፈስ ቅዱስን መቀበል

ዮሐንስ 7፡39 ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና።

ዮሐንስ 14፡17 እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።

የሐዋርያት ሥራ 8፡15 እነርሱም በወረዱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ ጸለዩላቸው፤

የሐዋርያት ሥራ 8፡17 በዚያን ጊዜ እጃቸውን ጫኑባቸው መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ

የሐዋርያት ሥራ 8፡19 እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ስጡኝ አለ።

የሐዋርያት ሥራ 10፡47 በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፦ እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው? አለ።

የሐዋርያት ሥራ 19፡2 አንዳንድ ደቀ መዛሙርትንም አገኘ። ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን? አላቸው። እርሱም፦ አልተቀበልንም መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም አሉት።

ሮሜ 8፡15 አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና

1ቆሮንቶስ 2፡12 እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም

1ቆሮንቶስ 2፡14 ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም።

ገላቲያ 3፡14 የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ።

1ዮሐንስ 2፡27 እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ።

የሐዋርያት ሥራ 2፡38 ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ

የእግዚአብሔርን ቃል ወይም መልዕክት መቀበል እንዲሁም መንፈስ ቅዱስን መቀበል መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ እንደሆነ በበርካታ ማጣቀሻዎች ለማረጋገጥ የቻልን ይመስለኛል። መንፈስ ቅዱስ፣ ከስላሴ አንዱ መሆኑን እና አምላክነት የባሕሪዩ እንደሆነ በስላሴ ትምህረት ለሚያምኑ ሁሉ እንግዳ ሃሳብ አይደለም። ይህን አምላክ እያንዳንዳችን መቀበል እንዳለብን በማያወላዳ መልኩ ከጥቅሶቹ መገንዘብ ከቻልን፣ እግዚአብሔር ወልድን፣ ማለትም ኢየሱስን መቀበል እንዲሁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ልንገምት እንችል ይሆናል። ሆኖም ግን ግምታችንን ለጊዜው ወደጎን እናድርግና፣ እውነታውን ከቅዱሱ መጽሐፍ እንመርምር፡-

ኢየሱስን መቀበል

ቆላስያስ 2፡6 እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ።

ዮሐንስ 1፡11-12 የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትምለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤

ማቴዎስ 10፡40 እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላልእኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።

ማርቆስ 9፡37 እንደዚህ ካሉ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላልየሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን እንጂ እኔን አይቀበልም አላቸው።

ዮሐንስ 5፡43 እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ አልተቀበላችሁኝምም፤ ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ።

ዮሐንስ 13፡20 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ማናቸውን የምልከውን የሚቀበል እኔን ይቀበላልእኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።

ከላይ በቀረቡት ማስረጃዎች መሰረት ኢየሱስን መቀበል፣ መናፍቃዊ ሃሳብ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን የተገነዘብን ይመስለኛል። ‘‘እናም ኢየሱስን ተቀብያለሁ ወይ?’’ ‘‘መንፈስ ቅዱስንስ ተቀብያለሁ ወይ?’’ ‘‘እውነተኛ ወንጌል ተቀብያለሁ ወይ?’’ ብሎ ራስን መጠየቅ ተገቢ ከመሆኑ በላይ ራሳችንን ልንጠይቅ ከሚገቡን ጥያቄዎች መካከል ዋነኛዎቹ ናቸው። ክቡሩን አምላክ፣ መድሃኔዓለም ክርስቶስን ያልተቀበልን ማንን ልንቀበል ነው? ይህን የእግዚአብሔር ልጅ ያልተቀበሉት አይሁድ (ዮሐንስ 1፡11-12) ከእግዚአብሔር ፍርድ ስር ከሆኑ፣ ልጁን ያልተቀበልን እኛ ከዚህ ፍርድ እንዴት ልናመልጥ እንችላለን? የተቀበሉቱ ግን፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ስልጣን ተሰጧቸዋል። የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን ደግሞ የመንግስቱ ወራሾች ነን (ሮሜ 8፡17)። እናም፣ ፍርድን ከመቀበል ኢየሱስን ተቀብለን በእርሱ እንመላለስ (ቆላሲያስ 2፡6)። የአውሬውን ቁጥር ከመቀበል (ራዕይ 14፡9-10፤ ራዕይ 14፡ 11፤ ራዕይ 20፡4) ኢየሱስን ተቀብለን የእግዚአብሔር ልጆች እንሁን (ዮሐንስ 1፡11-12)።

መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትዎ ጌታ በማድረግ ቀሪው ዘመንዎን ለመኖር ወስነው ከሆነ፣ ይህንን ሊንክ በመጫን ስምዎንና የኢ-ሜይል አድናሻዎን ይላኩልንና፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገትዎ የሚቻለንን ሁሉ እገዛ እናደርግሎታለን።

 

1 thought on “ኢየሱስን መቀበል – መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይስ መናፍቃዊ?”

  1. Pingback: መንግስተ ሰማያትን ያውርስልን!!! – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading