ዳግም ልደት ማለት ምን ማለት ነው?

ዳግም ልደት ከክርስትና ዋነኛ ትምህርቶች መካከል አንዱ ነው። የሰው ልጅ ሁለት ልደቶች አሉት። አንደኛው ከስጋ ፈቃድ በሩካቤ ከአባት እና ከእናት የሚያገኘው ስጋዊ ልደት ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ኢየሱስን በማመን እና በመቀበል የሚያገኘው መንፈሳዊ ልደት ነው፣ ‘‘ለተቀበሉት ሁሉ ግንበስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም’’ (ዮሐንስ ወንጌል 1፡12-13)።

ያለዚህ ልደት ሰው የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርስ አይችልም። ሰው በስጋ ልደቱ የሰው ልጅ እንደሚባል፣ በመንፈስ ልደቱ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። ስጋ እና ደም የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርሱ አይችሉም፣ የእግዚአብሔር ልጆች ግን የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርሱ ይችላሉ። የመጀመሪያውን ልደት ብቻ ያገኙ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣቸው የለምና ስጋ እና ደም ብቻ ተብለው ይጠራሉ። እነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርሱ አይችሉም፣ ‘‘ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም’’ (1ቆሮንቶስ 15፥50)።

የመጀመሪያውን ልደት ብቻ ያገኙ ፍጥረታዊ ሰዎች ይባላሉ። አካላቸው ደግሞ ፍጥረታዊ አካል ይባላል (1ቆሮንቶስ15፡46)። እነዚህ ሰዎች መንፈሳዊ የሆነውን የእግዚአብሔርን ነገር ሊያስተውሉ አይችሉም ‘‘ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም’’ (1ቆሮንቶስ 2፡14)።

የመጀመሪያውን ልደት በመወለድ እንዳገኘነው፣ ሁለተኛውንም ልደት በመወለድ እናገኘዋለን። የመጀመሪያውን ስጋዊ ልደት ስጋዊ ከሆኑ ቤተሰቦቻችን እናዳገኘነው ሁለተኛውን ልደት ደግሞ መንፈሳዊ ከሆነው አባታችን በመወለድ የምናገኘው ይሆናል። የመጀመሪያውን ልደት መልካም ሰው በመሆን፣ ምጽዋት በመስጠት፣ በመፀለይ እና በመጾም እናዳላገኘነው፣ ሁለተኛውንም ልደት በእነዚህ መንገዶች አናገኘውም። የቤተሰቦቻችን ልጅ ለመሆን የከፈልነው ክፍያም ሆነ አስተዋጽዎ እንደሌለ ሁሉ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆንም የምናዋጣው መዋጮ የለም።

የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን ከእኛ የሚጠበቀው አንድ ነገር ብቻ ነው። ይኸውም፣ በኢየሱስ ማመን እና እርሱን መቀበል፣ ‘‘ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም’’ (ዮሐንስ ወንጌል 1፡12-13)። ‘‘በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና’’ (ገላቲያ 3፡26)።

የሰው ልጅ ሁለተኛውን ልደት ካላገኘ ወይም ዳግም ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርስ አይችልም፣ ‘‘ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው’’ (የዮሐንስ ወንጌል 3፡5-6)። ምንም ይስራ ምን፣ ከስጋ የተወለደ ስጋ ነው። ስጋ እና ደም ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርሱ አይችሉም። የተፈጥሯዊ ሰው መልካምነት እስከ አለም ዳርቻ ቢሰማም እንኳ፣ ከስጋ ከተወለደ ስጋ ብቻ ነው። ድርጊቱ ምንም ያህል የተከበረ፣ አንቱ የተባለ እና የተመሰከረለት ቢሆን፣ ተፈጥሮውን አይቀይርለትም። ሃይማኖተኛ ቢሆን፣ አዘውትሮ ረዥም ፀሎት ቢያደርግ (ማቴዎስ 23፡14) በሳምንት ሁለት ጊዜ ቢጾም ሳያጓድል ለእግዚአብሔር አስራት ቢያወጣ (ሉቃስ 18፡12)፣ ቀማኛ፣ ዓመፀኛ አመንዝራ ባይሆን (ሉቃስ 18፡11)፣ በሌላ አባባል በሰፈሩ የተመሰከረለት የሞራል ሰው ቢሆን፣ ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር ያው ስጋዊ፣ ያው ፍጥረታዊ ብቻ ነው። በእግዚአብሔር መንግስትም እድል ፈንታ የለውም። ዳግም ልደት የእግዚአብሔር ምህረት ውጤት እንጂ የእኛ መልካም ስራ ውጤት አይደለም። ‘‘እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም’’ (ቲቶ 3፡5)። በመልካም ስራ ተፈጥሯችን አይቀየርም። መልካም ስራችን በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት የሚኖረው ከአዲሱ ተፈጥሯችን ሲመነጭ ብቻ ነው።

ዳግም ልደት ሰው በእግዚአብሔር መንፈስ ዳግም ሲፈጠር ወይም ሲለወጥ የሚከናወን መንፈሳዊ ድርጊት ሲሆን ይህም ድርጊት ሰው ከእግዚአብሔር መለኮታዊ ባሕሪይ ተካፋይ እንዲሆን ያስችለዋል፣ ‘‘ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን’’ (2ጴጥሮስ 1፡4)።

ኢየሱስን በማመን እና በመቀበል የተገኘው ልጅነት (ዮሐንስ 1፡12)፣ እግዚአብሔርን አባት ብለን እንድንጠራው እና የእግዚአብሔር ወራሾች እንድንሆን መብትን አስገኝቶልናል፣ ‘‘በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፥ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን’’ (ሮሜ 8፡14-17)።

በመጀመሪያው ልደት ከቤተሰቦቻችን (ከፊተኛው አዳም)  የወረስነው ተፈጠሮ፣ አዳማዊ ተፈጥሮ ወይም አሮጌው ሰው ይባላል። በዳግም ልደት ኢየሱስን በማመን ከእግዚአብሔር ያገኘነው አዲሱ ተፈጥሮ ደግሞ አዲሱ ሰው ይባላል፣ ‘‘እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፥ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና፥ የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል’’ (ቆላሲያስ 3፡9-10)። ‘‘ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል’’ (2ቆሮንቶስ 5፡17)።

ኢየሱስን አምኖ የተቀበለ ሰው፣ በዳግም ልደት ሌላ አዲስ ተፈጥሮ ስለሚኖረው የሁለት ተፈጥሮዎች ባለቤት ይሆናል ማለት ነው። በዳግም ልደት አዲስ ተፈጥሮን እናገኛለን እንጂ የቀድሞውን አሮጌ ተፈጥሮ አናጣም። አሮጌው ተፈጥሮ እስከሞታችን ከእኛ ጋር ይኖራል። እነዚህ ሁለት ተፈጥሮዎች በባህሪይ ተቃራኒ በመሆናቸው እርስ በእርሳቸው ይቀዋወማሉ፣ ‘‘5፥17 ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ …’’ (ገላቲያ 5፡17)። ዳግም የተወለደ ሰው በፊተኛው እና እግዚአብሔርን በማያከብረው ስጋዊ ወይም አሮጌ ተፈጥሮ ቁጥጥር ስር እንዳይሆን በእግዚአብሔር ቃል እውቀት እለት እለት መታደስ ይኖርበታል። የአዲሱ ተፈጥሮ ምግብ የእግዚአብሔር ቃል ነው (ማቴዎስ 4፡4)። የአሮጌውን ተፈጥሮ ፍላጎት እንቢ እያልን የአዲሱን ተፈጥሮ ፈቃድ እየተቀበልን የምንጓዘው ጉዞ የቅድስና ጉዞ ይባላል፣ ‘‘ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።

ሰው በአሮጌው ተፈጥሮ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኝት ስለማይችል ዳግም ልደት ያስፈልገዋል፣ ‘‘እነሆ፥ በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ (መዝሙር 51፡5)። ‘‘የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው ማንስ ያውቀዋል? (ኤርሚያስ 17፡9።) ‘‘ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም’’ (ሮሜ 8፡16-17)። ‘‘በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን’’ (ኤፌሶን 2፡3)።

ዳግመኛ ልደት ያገኘ ሰው ምልክቶች ምንድን ናቸው? ዳግም የተወለደ ሰው ከሃጢአት ልምምድ ነፃ የወጣ ነው (ሮሜ 6፡14-23)። ዳግም የተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንፈስ ምሪት ለመቀበል እና ለመታዘዝ መሻት ይኖረዋል (ሮሜ 8፡13-14)። ዳግም የተወለደ ሰው የጽድቅ ሕይወት ይኖረዋል (1ዮሐንስ 2፡29)። ዳግም የተወለደ ሰው ሌሎችን ይወዳል (1ዮሐንስ 4፡7)። ዳግም የተወለደ ሰው ከሃጢአት ሕይወት ይርቃል (1ዮሐንስ 3፡9፤ 5፡18)። ዳግም የተወለደ ሰው አለምን መውደድ ይተዋል (1ዮሐንስ 2፡15-16)።

ኢየሱስን በማመን እና በመቀበል ይህን ዳግም ልደት ለማግኘት የሚሹ ከሆነ ይህን ሊንክ በመጫን፣ ኢየሱሰን መቀበል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይስ መናፍቃዊ የሚለውን ትምህርት እንዲያነቡ በትህትና እንጠይቆታለን። የመዳን ቀን አሁን ነው (2ቆሮንቶስ 6፡2)፣ ለነገ ቀጠሮ አይስጡ። ነገ የእርሶ አይደለምና።

መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትዎ ጌታ በማድረግ ቀሪው ዘመንዎን ለመኖር ወስነው ከሆነ፣ ይህንን ሊንክ በመጫን ስምዎንና የኢ-ሜይል አድናሻዎን ይላኩልንና፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገትዎ የሚቻለንን ሁሉ እገዛ እናደርግሎታለን።

Leave a Reply

%d bloggers like this: