በውኑ፣ ክርስቶስ ያማልዳልን?

1. መግቢያ፡- የሰው ልጅ ውድቀት

የዚህ ጽሁፍ አቢይ አላማ በየዕለቱ በሚገጥሙን ጉዳዮች ማለትም፣ ስለታመሙ ሰዎች፣ በእስር ስላሉ ሰዎች፣ ስለ መሪዎች፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ አገር፣ ስለ አገልግሎት፣ ወዘተ አንዱ ለሌላው ወደ ፈጣሪው የሚያደርሰው የምልጃ ጸሎት፣ ክርስቶስ ለእኛ ባደረገው የማማለድ ሥራ ላይ ጥላውን እንዳያጠላበት ጥንቃቄ እንድናደርግ ለማሳሰብ ነው፡፡ እነደነዚህ አይነቶቹ – አንዱ ስለ ሌላው የሚጸልየው ጸሎት – ክርስቶስ ለእኛ ከፈጸመው የምልጃ አገልግሎት ጋር ምንም ዝምድና እንደሌለው ማሳሰብና እነዚህ ሁለት ነገሮች ሊነጻጸሩም ጭምር እንደማይገባ ማሳየት፣ የማንም ሰው የጸሎት ምልጃ የክርስቶስን የመስቀል ላይ ምልጃ ሊተካው እንደማይችል መግለጽ፣ እንዳውም አንዳችን ለአንዳችን የመጸለይ (የመማለድ) ፈቃድን ያገኘነው በክርስቶስ የምልጃ ሥራ ከእግዚአብሔር ጋር ስለታረቅንና ከተቆጣን ፈጣሪ ጋር ሰላም ስለፈጠርን መሆኑን ማስገንዘብ የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ይህንን አሳብ ለመገንዘብ ይረዳን ዘንድ ከችግሩ መነሻ ማለትም ከሰው ልጅ የውድቀት ታሪክ እንነሳና ጉዳዩን በጥልቀት እንመልከት፡፡

የሰው ልጅ፣ አጽናፈ አለሙ፣ የምድር አራዊት፣ የሰማይ ወፎች፣ የባሕር ዓሶች ከተፈጠሩ በኋላ በፈጣሪው አምሳል በስድስተኛው ቀን የተፈጠረ ልዩ ፍጥረት ነው፡፡ ከእርሱ ቀድሞ የተፈጠሩትን ይገዛና ያስተዳድር ዘንድ ሃላፊነት ጭምር የተሰጠው ይህ ሰው፣ ይኖርበት ከነበረው ዔደን ገነት የአንዲቷን ዛፍ ፍሬ እንዳይበላ ከፈጣሪው ትእዛዝ ተሰጠው፡፡ በፈጣሪው ላይ መታመን ያልፈለገው የሰው ልጅ በትዕቢት ከፍሬዋ ቀጥፎ በላ፡፡ ከፍሬዋ በበላህ ጊዜ ሞትን ትሞታለህ ያለው አምላክም ጻድቅ ፈራጅ እንደ መሆኑ፣ የጽድቅ ብያኔውን በራሱ ላይ ተደግፎ ለመኖር በወሰነው በዚህ የሰው ልጅ ላይ አስተላለፈ፡፡ ከብያኔዎቹ መካከል አንዱ እንዲህ ይነበባል ፡- “… የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፣ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና፣ ምድር ካንተ የተነሳ የተረገመች ትሁን፤…” (ዘፍ. 3፡17)፡፡

የሰውና የፈጣሪ ጠብ እንግዲህ ከዚህ መጥፎ ጊዜ ይጀምራል፡፡ ከዚህች ቀንና ሰዓት ጀምሮ ሰውና ፈጣሪው ጥለኞች ሆኑ፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያዘጋጀውም መልካም ሃሳብ በሰይጣን ፈታኝነት፣ በሰው ልጅ ተባባሪነት እንቅፋት ገጠመው፡፡ አግዚአብሔር ሕግ ሰጠ፣ የሰው ልጅ ተላለፈው፣ ፈጣሪም የጽድቅ ፍርድ አስተላለፈ፡፡ ይህም ፍርድ ሞት ይባላል፡፡ የሰው ልጅ በሞት ፍርሃት ውስጥ እየማቀቀ ለበርካታ አመታት በምድር ላይ የስቃይ ኑሮ መግፋት ጀመረ፡፡

ይህን ፍርድ ያስተላለፈው አምላክ ጻድቅ ብቻ ሳይሆን የፍቅር አምላክ በመሆኑ፣ ከእስትንፋሱ የተካፈለው ሰው በምድር ላይ ሲሰቃይ ማየት አላስቻለውም፡፡ በዚህም ምክኒያት ጻድቅ ፈራጅነቱንና የፍቅር አምላክነቱን አዋህዶ የሚያሳይ የድነት (የደኅንነት) መንገድ ለሰው ልጅ አዘጋጀ፡፡ ይህ የድነት መንገድ፣ ጽንፍ የሚመስሉትን የአምላክ ሁለት ባሕሪያት (ፍርድና ምሕረት) በአንድ መስመር ያገናኘ አስገራሚ ክስተት ነበር፡፡ እግዚአብሔር በሰው ዘር ሁሉ ላይ ያሳለፈው ሊታጠፍ የማይችል የሞት ፍርድ ሳይቀለበስ፣ የሰው ልጅ ከተቆጣው አምላኩ ጋር ታረቀ፡፡ የአገራችን የእምነት ሊቃውንት ይህንን ሁኔታ ግሩም በሆነ መንገድ እንዲህ በማለት ይገልጹታል፡፡ «እግዚአብሔር ሰውን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ያዳነበት ጥበቡ ተጠበበች”፡፡ የዚህ አስገራሚ ትዓይንት ጀማሪ፣ ማእከሉ እና ፈጻሚው ደግሞ ምንም በደል ያልተገኘበት ኢየሱስ ነበር፡፡ እግዚአብሔር በሰው ልጅ ላይ የተቆጣውን ቁጣ በኢየሱስ ላይ አሳረፈው፤ ፍርዱን አሳየ፡፡ ኢየሱስ ስለ ኃጢአተኞቹ ስለ እኛ ሞተ፡፡ በእርሱም ምክኒያት የሰው ልጅ ምኅረትን ተቀበለ፡፡ ከፈጣሪውም የፍርድ ቁጣ ተረፈ (ሮሜ. 5፡9)፡፡

የብሉይና የሐዲስ ኪዳናት ቅዱሳት መጻሕፍት አስኳልና መሰረታዊ ጭብጥም ይኸው ታላቅ ሥራ ነው፡፡ ብሉይ ኪዳን የሐዲሱ ኪዳን ጥላ/ምሳሌ (ዕብ. 10፡1) እንደ መሆኑ፣ በዚህ ዘመን ውስጥ የሰው ልጅ የድነት መሰረት የሆነው (1ቆሮ. 3፡10-11) ክርስቶስ ዘመኑ ደርሶ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እስኪመጣ ድረስ፣ በታላቅ ምጥ ውስጥ ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን የሰው ልጅ ጥላ የነበረውንና ፍጹም ሊያደርገው የማይችለውን የእርቅ ሥርዓት (ዕብ. 9፡9፣10) እየፈጸመ ከአምላኩ ጋር ሊያስታርቀው የሚችለውን ፍጹሙን የድንነት ተስፋ መጠበቅ ጀመረ፡፡ አንዳንዶች ይህን ተስፋ በሩቅ ተሳለሙት (ዕብ. 11፡13፣ 11፡49፣40)፤ ሊሎች ደግሞ ይህን ተስፋ በአይናቸው አዩት (ሉቃስ 2፡29-32)፡፡ የዚህ ጽሑፍ አንባቢ እርሶ እና እኔ ደግሞ በዚህ የምሕረት ዘመን ውስጥ ለመገኘት የእግዚአብሔር መልካፍ ፈቃድ ሆነ፡፡

የሰው ልጆች ሁሉ ተስፋ የነበረው፣ የዓለሙን ሁሉ ኃጢአት የሚቤዠው፣ ሰውንና እግዚአብሔርን የሚያስታርቀው፣ የተዋረደውንና በውድቀት ከእግዚአብሔር ቁጣ ስር ለሞት የሚጠበቀውን የሰውን ዘር የሚታደገው ብቸኛ አዳኝ እስኪመጣ ድረስ፣ የሰው ልጅ የዚህን ፍጹም ተስፋ ጥላ እየተከተለ አካሉን ናፈቀ፡፡ ጥላው የነበረውን የብሉይ ሥርዓት እየፈጸመ የአካሉን መገለጥ ለግማሽ ምዕተ ዓመት በናፍቁት መጠበቅ ግድ ሆነበት፡፡ ከዚህ በታች ባሉት ጥቂት አንቀጾች ከሰው ውድቀት አንስቶ እስከ መሲሁ መምጣት ድረስ ባለው ግማሽ ምዕተ አመት፣ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር ተቀባይነት ያለውን ሕብረት ለማድረግ፣ የኃጢአት ሥርየትን ለማግኘትና የምስጋና መሥዋዕት ለማቅረብ ምን ነገሮችን ይፈጽም እንደነበረ አለፍ አለፍ እያልን እናያለን፡፡ ይህ የብሉይ ሥርዓት ሊመጣ ያለው እውነተኛ አካል ጥላ/ምሳሌ እንደሆነ አንባቢ ልብ ይበል (ቆላ. 2፡17)፡፡ በዚህ ስር የምናያቸው ቁም ነገሮች ግልጽ ከሆኑ፣ ኋላ ላይ የምናየው የሐዲስ ኪዳኑ አካል ፍሬ አሳብ ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡

2. የብሉይ ኪዳን ክህነት

የክህነት አገልግሎት የእስራኤል ሕዝብ በሙሴ መሪነት ከግብጽ ባርነት ከወጣ በኋላ የተጀመረና ለአንድ ሺህ አመታት የዘለቀ ታላቅ አገልግሎት ነው፡፡ እነዚህ የክህነት ሕግጋቶች ለእስራኤል የተሰጡት በሲና ተራራ ላይ ሲሆን (ዘሌ. 7፡38፣ 25፡1፣ 26፡46፣ 27፡34) የአገልግሎቱም አስፈላጊነት እስራኤል የኃጢአት ስርየትን በመቀበል ከርኩሰት ነጻ እንዲሆን ነበር (ዘሌ. 11፡45)፡፡ ይህ የአምልኮ ሥርዓት አንዳንዶች የብሉይ ኪዳን ወንጌል በሚሉት የዘሌዋዊያን መጽሐፍ ላይ በስፋት ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡

ካህን፣ የሰው እንደራሴ በመሆን መባና መሥዋዕት በማቅረብ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ አገልጋይ ነው፡፡ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል በመቆም የሚማልድ ነው፡፡ «ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማል” (ዘጸ. 28፡1፣ ዕብ. 5፡1-4) የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የካህናትን አጠራርና ተግባር በግልጽ ያሳያል፡፡ የዘሌዋዊያን መጽሐፍ ጭብጥ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የሚቻለው በመሥዋዕት አማካኝነት ብቻ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ ይህም ምሥዋዕት በእስራኤል የአምልኮ አገልግሎት ውስጥ ትልቅ ስፍራ እንዳለው ጨምሮ ያስገነዝባል፡፡ እስቲ አሁን በአጭሩ የአሮን ክህነት ባሕሪን እንመልከት፡፡

2.1 የአሮን ክህነት

የሰው ልጅ በኃጢአት ከወደቀ በኋላ በእግዚአብሔር ፊት ዳግም ተቀባይነት ያለውን ኑሮ ለመግፋትና እግዚአብሔርን ለማምለክ የክህነትን ሥራ ተጠቅሞበታል፡፡

እግዚአብሔር የነገድ ምርጫ ሳያደርግ የእስራኤልን ሕዝብ ባጠቃላይ የእርሱ ካህን የማድረግ ውጥን ቢኖረውም (ዘጸ. 19፡6) ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ሕግና ትዕዛዛት የድንጋይም ጽላት ለመቀበል አርባ ቀንና ለሊት ከእግዚአብሔር ጋር የቆየበትን አጋጣሚ በመጠቀም የወርቅ ጥጃ ሰርተው በማምለካቸው ምክንያት ለዚህ ክህነት አገልግሎት የሌዊን ነገድ ብቻ ለመምረጥ ተገደደ፡፡ ከዚህ ነገድ ደግሞ የመቅደሱን ውስጠኛ አገልግሎት ለመፈጸም የተፈቀደለት የአሮን ቤተሰብ ብቻ ነበር (ዘኁ. 3፡10)፡፡

ስለ መሥዋዕቶቹ ስንመልከት ደግሞ፣ በመጀመሪያዎቹ ሰባት የዘሌዋዊያን መጽሐፍ ሃሳብ መሰረት አራት ዋና ዋና መሥዋዕቶች እናያለን፡፡ እነዚህም የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የኃጢአት መሥዋዕት፣ የበደል መሥዋዕትና የደኅንነት መሥዋዕት በመባል ይታወቃሉ፡፡

ሊቀ ካህናት 4 ዋና ዋና ተግባራት ሲኖሩት እነዚህም በእግዚአብሔር ፊት የእስራኤል እንደራሴ መሆን (ዘጸ. 28፡17-29)፣ የነቢይነትን አገልግሎት በአግባቡ መወጣት (ዘጸ. 28፡30)፣ ለሕዝቡ ቡራኬ መስጠት (ዘኁ. 6፡22-27)፣ በማስተረያ ቀን ሥርዓቱን መፈጸም እና ለሕዝቡ መጸለይ (1ሳሙ. 12፡23) ናቸው፡፡ የመሥዋዕት አቀራረቡን በተመለከተ ደግሞ ካህናት በየዕለቱ የሚቀርቡ መሥዋዕቶችን የሚያሳርጉ ሲሆኑ፣ በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በመግባት መሥዋዕት ማቅረብ የሚፈቀድላቸው ግን ሊቀ ካህናት ብቻ ነበሩ፡፡

ሊቀ ካህኑ በአመት አንድ ጊዜ፣ የማስተስረያ ቀን በመባል በሚታወቀው ልዩ ዕለት፣ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ገብቶ የሚፈጽመው ስርዓት የሚከተለውን ይመስላል፡- አሮን ሊቀ ካህናት ሆኖ ለመሥዋዕትነት ከሚቀርቡት ከሁለቱ ፍየሎች አንዱን «ስለ ሕዝቡ ኃጢአት የሚሰዋውን … ፍየል ያርዳል፤ ደሙንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ያመጣዋል በወይፈንም ደም እንዳደረገ በፍየሉ ደም ያደርጋል፤ በመክደኛውም ላይና በመክደኛውም ፊት ይረጨዋል´፡፡ ይህንም ሥርዓት ከፈጸመ በኋላ «ሕያውን ፍየል ያቀርባል፤ አሮንም ሁለቱን እጆቹን በሕያው ፍየል ራስ ላይ የጭናል፤ በላዩም የእስራኤልን ልጆች በደል ሁሉ፣ መተላለፋቸውንም ሁሉ ኃጢአታቸውንም ሁሉ ይናዘዛል፤ በፍየሉም ራስ ላይ ያሸክመዋል፤ በተዘጋጀውም ሰውም እጅ ወደ ምድረ በዳ ይሰድደዋል፡፡ ፍየሉም ኃጢአታቸውን ሁሉ ወደ በረሃ ይሸከማል፤ ፍየሉንም በምድረ በዳ ውስጥ ይለቅቀዋለ” (ዘሌ. 16፡15-22)፡፡ እነዚህ ሁለቱም ፍየሎች በአንድነት በዚህ ቀን የሚሰዉ የኃጢአት መሥዋዕቶች ነበሩ (ዘሌ. 16፡5)፡፡ በመጀመሪያው ፍየል አማካኝነት የእስራኤል ሕዝብ የኃጢአት ቅጣት ሞት መሆኑን ሲገነዘቡ፣ በሁለተኛው ፍየል ደግሞ እንስሳው እነርሱን ተክቶ (ኃጢአታቸው ከእነርሱ ተወስዶ በፍየሉ ላይ እንደሆነ) የኃጢአታቸውን ቅጣት እንደተቀበለ በእርሱም ምክኒያት እነርሱ ከቅጣት ነጻ እንደሆኑ ይገነዘባሉ፡፡ ይህ ሥርዓት የክርስቶስ መሥዋዕትነት ጥላ ሲሆን፣ እኛም ክርስቶስ ኀጢአታችንን በመሸከሙና በመሞቱ ከኃጢአት ቅጣት ነጻ የወጣን መሆናችንን ያበስረናል (1ጴጥ. 2፡24፣ ዕብ. 9፡7፣ 15፡28)፡፡

 2.2 የመልከ ጼዴቅ ክህነት

የዚህ ሰው ክህነት ከአሮን ክህነት ፍጹም የተለየ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ካህን የሚናገረው እንግዳ ነገር የትርጓሜ ግርታን መፍጠሩ የተለመደ ስለሆነ እስቲ እነዚህን እንግዳ ቁም ነገሮች እንመልከት፡፡ ስለዚህ ካህን የትውልድ ቁጥር እና ዘመን የእብራዊያን ጸሐፊ ሲተርክ እንዲህ ይላል፡- «አባትና እናት የትውልድም ቁጥር የሉትም፣ ለዘመኑ ጥንት ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፣ ዳሩ ግን ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል፡፡” (ዕብ. 7፡3)፡፡ ይህን ገለጻ ሰውየው መልአክ ነው ወይስ የተለየ ፍጥረት እንድንል ይጋብዘን ይሆናል፡፡

«አባትና እናት የሉትም” ማለት እንዲሁም «ለዘመኑ ጥንት ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም” ሲባል ስለ እርሱ በቀረበው ጽሁፍ ወይም ታሪክ ውስጥ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ የተጻፈ ነገር የለም ማለት ነው እንጂ ፍጹም አባትና እናት የሌሉት እንግዳ ፍጥረት ነው ማለት አይደልም፡፡ እነዚህ ነገሮች ሳይጻፉ የቀሩበትም ምክኒያት መንፈስ ቅዱስ መልከ ጼዴቅ ክርስቶስን እንዲመስል በእርሱም የክርስቶስን ስዕል አግኝተን የክርስቶስ ክህነት ለዘላለም እንደሆነ እንድናስተውል ስለ ፈለገ ነው፡፡

በኦሪት ሕግ መሰረት ክህነት የተሰጠው ለአሮን ልጆች ብቻ መሆኑን ከላይ ተመልክተናል፡፡ ትውልዱ በትውልድ መጽሐፍ ያልተገኘ ማንኛውም ሰው እንደ ካህን ሊያገለግል አልቻለም (ዘኁ. 3፡10፣ 8፡19-22)፡፡ ይህ አባባል፣ ክህነት በዘር ተወስኖ የነበር አገልግሎት መሆኑን ያሳየናል፡፡ መልከ ጼድቅ ግን የትውልድ ቁጥር የለውም፡፡ ማለትም ትውልዱ በትውልድ በጽሐፍ አልተገኘም፡፡ ዘሩ ከየት እንደሆነም አልተጻፈም፡፡ በዚህ ምክኒያት ክህነቱ በዘር ላይ አለመመስረቱንና ይህም የእግዚአብሔር ልዩ ጥሪ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ስለሆነም የመልከ ጼዴክ ክህነት ከሌዊ ክህነት የተለየ መሆኑን እናያለን፡፡

“ለዘመኑ ጥንት ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፣ ዳሩ ግን ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል”፣ የሚለው አሳብ ደግሞ መልከ ጼዴቅ ስለ ኖረበት አመት ብቻ ሳይሆን ስለ ክህነቱም ዘመን ጭምር ያወራል፡፡ ሌዋዊያን ለአገልግሎታቸው የተወሰነ ዘመን ነበራቸው፡፡ ይህም ከ25 እስከ 50 አመት የሚዘልቅ ሲሆን (ዘኁ. 4፡46-47፣ 8፡24-26) የዚህ እድሜ ስሌት ክህነታቸው የሚጀመርበትና የሚያከትምበት የዘመን ቁጥር መኖሩን ያሳየናል፡፡ክህነታቸው “ለዘላለም” አልነበረም፡፡ መልከ ጼዴቅ ግን ለክህነቱ መጀመሪያና መጨረሻ ስለሌለው፣ “ለዘላለም” ተብሎለታል፡፡ ይህም ማለት ይህ ሰው በእድሜው ዘመን ሁሉ ካህን ሆኖ ኖሯል ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የሌዋዊያን ክህነት መጀመሪያና መጨረሻ የሚታወቅ ሲሆን የመልከ ጼዴቅ ክህነት ግን የሚጀምርበትና የሚጨርስበት ዘመን አልተቆጠረምና “ለዘላለም” ካህን ሆኖ ይኖራል ተብሎለታል፡፡ በነዚህ ምክኒያቶች ለኢየሱስ ክህነት ምሳሌነት የሚያገለግለው የአሮን ክህነት ሳይሆን የመልከ ጼዴቅ ክህነት ነው፡፡ ለምን ቢሉ ኢየሱስ ከይሁዳ ነገድ እንጂ ሌዋዊ አይደለምና፡፡ ክህነቱም ቢሆን እንደ አሮን ልጆች በሞት የተገደበ ሳይሆን ዘላለማዊ ነውና፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የዕብራዊያን ጸሃፊ ሲናገር “…አንተ (ክርስቶስ) እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ…” (ዕብ. 7፡17)፤ “እነርሱም (ካህናት) ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ (ኢየሱስ) ግን ለዘላለም የሚኖር ስለ ሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና…” (ዕብ. 7፡23-25) ይላል፡፡

3. የሐዲስ ኪዳን ክህነት

በብሉይ ይቀርቡ የነበሩት መሥዋዕቶች የራሳቸው የሆነ ትርጉም ነበራቸው፡፡ ይህ ትርጉም ደግሞ መሥዋዕቶቹ በራሳቸው ከሚኖራቸው ትርጉም በላቀ፣ ለሐዲስ ኪዳን ዘመን ያላቸው ፋይዳ ጉልህ ነበር፡፡ እነዚህ ጥላ ወይም ምሳሌ የሆኑት የመስዋዕት ሥርዓቶች አካሉ የሆነውን የኢየሱስ አገልግሎት በማሥረዳትና በመግለጥ ረገድ ያላቸው ሚና አስደናቂ ከመሆኑ በተጨማሪ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ለማዳን የተጓዘበትን የጥበብ ጎዳና የሚዘክሩ ናቸው፡፡

እስቲ አሁን የእነዚህን ጥላዊ መሥዋዕቶች ትርጉም ከሐዲስ ኪዳን አካላዊ ፈጻሜ አንጻር በጥቂቱ እንመልከት፡፡ በብሉይ ኪዳን ለመሥዋዕትነት ይቀርብ የነበረው እንስሳ ነውር የሌለበት መሆን ነበረበት (ዘሌ. 1፡3፣ 3፡1)፡፡ የዚህ ጥላ ሥርዓት አካል የሆነው ኢየሱስም እንዲህ እንደነበረ ሐዋሪያው ጴጥሮስ ሲመሰክር ፡- “… ነውርና እድፍ እንደሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ፡፡” ይላል (1ጴጥ. 1፡18-19)፡፡ ሌላው ደግሞ በመሥዋዕቱ ሥርዓት ወቅት የሰው ኃጢአት ወደ መሥዋዕቱ መተላለፍ ነበረበት (ዘሌ. 1፡4፣ 16፡21፣)፡፡ ይህም የሰው ሁሉ ኃጢአት በክርስቶስ ላይ የመሆኑ ምሳሌ ነበር (ኢሳ. 53፡6-12፣ 1ጴጥ. 2፡24፣ 3፡18፣ ዕብ. 9፡28)፡፡ መሥዋዕቱ ደግሞ ያን ኃጢአት በመሸከም ለኃጢአተኛው ምትክ ሆኖ መሞት ነበረበት (ዘፍ. 22፡7-8፣ ዘሌ. 16፡15)  የዚህ ምሳሌነቱ ደግሞ ክርስቶስ ለኃጢአተኞች ምትክ ሆኖ እንደሚሞት ለማመልከት ነበር (ኢሳ. 53፡5-6፣ ማር. 10፡45፣ ሮሜ 5፡8፣ 2ቆሮ. 5፡21፣ ገላ. 3፡13፣ ዕብ. 9፡28፣ 1ጴጥ. 3፡18፣ 1ዮሐ. 2፡2፣ 3፡16)፡፡ የዚህ ነገር መጨረሻው የሰውየው መንጻት ነውና፣ ከመሥዋዕቱ የተነሳ የሰውየው ኃጢአት ይደመሰሰ ነበር (ዘሌ. 4፡26፣ 31፡35፣ 16፡21-22፣ መዝ. 51፡1-9፣ ኢሳ. 44፡22፣ ሕዝ. 36፡25)፡፡ ምሳሌነቱም በክርስቶስ ሞት ምክኒያት የሰው በደል እንደሚደመሰስ ማሳየቱ ነው (1ቆሮ. 6፡11፣ ዕብ. 9፡14፣ 1ዮሐ. 1፡7፣ ራዕ. 1፡4-5፣ 7፡14)፡፡

በብሉይ ይቀርቡ በነበሩት የኃጢአት መሥዋዕትና የበደል መሥዋዕት አሳብ መሰረት እንስሳት ሰውን ተክተው ይሞቱ ነበር፡፡ ይህም ማለት የሰውየውን ሞት እነርሱ ሞተው፣ መሞት የሚገባውን ሰው ከኃጢአት ቅጣት ፍርድ ማለትም ሞት ያስመልጡ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህ አስደናቂ የመተካት መርህ የክርስቶስን የክርስቶስን የቤዛነት አገልግሎት ለማስረዳት ትልቅ ሥፍራ አለው፡፡ ሐዋሪያው ጴጥሮስ፣ ክርስቶስ በኃጢአታችን ምክኒያት መሞት በሚገባን ሰዎች ምትክ ሆኖ ኃጢአታችንን በመስቀሉ ላይ እንደተሸከመልንና ከሚጠብቀን የሞት ፍርድ እንዳዳነን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፡- “እርሱ (ክርስቶስ) ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ” (1ጴጥ. 2፡24)፡፡

በመቀጠል፣ ክቡር የሆነው ኢየሱስ ደም በሰው ልጆች መታረቅ ውስጥ ያለውን ታላቅ ሚና በሚከተሉት ሁለት ጥቅሶች ማሳያነት እንመልከት፡፡ የመጀመሪያው፣ “ደም ሳይፈስ ሥርየት የለም” (ዕብ. 9፡22) የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ፣ “የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና” (ዕብ. 10፡4) የሚለው ነው፡፡  የመጀመሪያው ጥቅስ ያለ ምትክ፣ እርቅ አይገኝም፤ ያለ ምትክ ከእግዚአብሔር ቁጣ መሸፈን መከለል አይቻልም የሚለውን ሲያስረዳ ሁለተኛው ደግሞ የብሉዩ ኪዳኑ መሥዋዕት የሐዲስ ኪዳኑ ጥላ ወይም ምሳሌ እንደነበረ ያስረዳል፡፡ በነገራችን ላይ ሥርየት ማለት መሸፈን ማለት እንደሆነ ልብ ይበሉ፡፡ እንግዲህ፣ እግዚአብሔርን የበደለው ሰው ነውና ፍጹም ምትኩም እንስሳ ሳይሆን ሰው ሊሆን ግድ ነው፡፡ ይህም ሰው ደግሞ ፍጹም መስዋዕት እንዲሆን ነውር የሌለበት ሊሆን የግድ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ሰው ደግሞ አምላክም ሰውም ከሆነው ከኢየሱስ በቀር ማን ሊሆን ይችላል? ስለዚህ ለሰው ደኅንነት ዋጋ የሚኖረው ክቡር የሆነው የክርስቶስ ደም ብቻ ነው፡፡ (1ጴጥ. 1፡18-19)፡፡ ያለ ነውር የሆነ ሰው በዚህ ምድር ላይ ተገኝቶ ቢሆን ኖሮ ይህን የመተካት ሥራ መስራት ስለሚችል አምላክ ሰው መሆን ባላስፈለገው ነበር፡፡ ነገር ግን፣ በምድር ላይ በአዳም ዘር ውስጥ አንድም ጻድቅ ሰው የለም (ሮሜ. 3፡11)፡፡ ከአዳም ውድቀት በኋላ በምድር ላይ ካለ የሰው ዘር ያለ ኃጢአት የተገኘ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡

ክርስቶስ ፋሲካችን ነው (1ቆሮ. 5፡6-7)፡፡ ከ400 አመታት በላይ በግብጽ ባርነት ውስጥ የነበረው የእስራኤል ሕዝብ ከዚህ ባርነት ሲወጣ እግዚአብሔር የተጠቀበመት የመጨረሻው ተአምር በግብጽ አገር ከሰው እስከ እንስሳ ድረስ በኩርን ሁሉ መግደል ነበር (ዘፀ.12፡12)፡፡ «ደሙንም በጉበኑና በሁለቱ መቃኖች ላይ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር በደጁ ላይ ያልፋል፣ አጥፊውም ይመታችሁ ዘንድ ወደ ቤታችሁ እንዲገባ አይተውም፡፡” (ዘፀ. 12፡23) «ደሙን ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ፤…” (ዘፀ. 12፡13)፡፡ ይህ ታሪክ ድነት በምትክነት የሚገኝ ስለመሆኑ ጥሩ አስረጅ ነው፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ የዳኑት ሰዎች ማንምና ምንም ስለሆኑ ሳይሆን የበግ ደም በቤቶቻቸው ላይ ስለ እነሱ ስለታየላቸው ነው፡፡ ይህም ዛሬ ከእግዚአብሔር ቁጣ ሰዎች የሚድኑት የክርስቶስ ደም በእነርሱ ፈንታ በሕይወታቸው ላይ የታየላቸው ሰዎች ብቻ ስለመሆናቸው ግልጽ ምሳሌ ነው፡፡ የበጉ ደም በበር ላይ መረጨት ነበረበት፡፡ እግዚአብሔር ከቁጣው እንዲያርፍ ደሙን ማየት ነበረበት፡፡ ይህ ትዕይንት የክርስቶስ ምሳሌው ስለሆነ (1ቆሮ. 5፡6-7) ለሐዲስ ኪዳን ሕዝቦች ያለው ፋይዳ እንደምን ይገለጣል ከተባለ  ምላሹ ዛሬም ለመዳን የሚፈልግ ሰው ሁሉ በክርስቶስ ደም መሸፈን አለበት (1ጴጥ. 1፡1-2፣ 1ዮሐ. 1፡7-9) የሚል ይሆናል፡፡

ክርስቶስ የብሉይ ኪዳን ክህነትና መሥዋዕት ፍጻሚ ነው፡፡ ይህም ለሐዋሪያቱ ምልጃን በማቅረብ (ሉቃስ 22፡31-32)፣ ለደቀ መዛሙርት ሌላ አጽናኝ እንደሚሰጣቸው አብን እንደሚለምን ቃል በመግባት (ዮሐ. 14፡16)፣ ከመያዙ በፊት በሰፊው ለተከታዮቹ በመጸለይ (ዮሐንስ 17) ተገልጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር “የማዕዛ ሽታ የሚሆን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ” ራሱን አሳልፎ በመስጠት (ኤፌ. 5፡2)፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ሆኖ ስለ እኛ በመማለድ (ሮሜ. 8፡34)፤ ጠበቃ በመሆን (1ዮሐ. 2፡1) እና መካከለኛ በመሆን (1ጢሞ. 2፡5) የመልከ ጼዴቅ ክህነት ፍጻሜ መሆኑን አሳይቷል፡፡ እርሱ በመስቀል ላይ ከፈጸመልን ሥራ የተነሳ አሁን ሁላችን በእርሱ ሥራ ወደ አብ “መግባት” አግኝተናል (ኤፌ 2፡18፤ 3፡12)፡፡ በሐዲስ ኪዳን አሳብ መሰረት ክርስቶስ ሊቀ ካህናችን በመሆኑ፣ እኛ ምእመኖቹ ሁላ ደግሞ የእርሱ ካህናት (አገልጋዮች) ሆነናል (ራዕ. 1፡5-6፣ 1ጴጥ. 2፡9)፡፡

4. የተሳሳቱ አመለካከቶች፡-

4.1 አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ያደረገውን ይህን የክርስቶስ የአማላጅነት አገልግሎት ትምህርት ለመቀበል ለምን ተቸገሩ?

መልካምም ይሁን ጎጂ፣ የሰው ልጅ አንዴ የያዘውን አስተሳሰቡን፣ ልማዱንና ወጉን መተው ይቸገራል፡፡ እነዚህ አስተሳሰቦች በአንድ ለሊት የተገነቡ ስላልሆኑ፣ በአንድ ለሊት ሊፈርሱ አይችሉም፡፡ ነጮች አሮጌ ልማዶችን የመሻር አስቸጋሪነትን “Old habits die hard!” በማለት ይገልጻሉ፡፡ ትርጓሜውም አሮጌ ልማዶች በቀላሉ አይሞቱም ማለት ነው፡፡ አንዴ ለዘላለም የሆነው የክርስቶስ ምልጃ፣ ምንም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በአገራችን የእምነት ትውፊቶች በግልጽ የተነገረ ሥራ ቢሆንም በእኛ አገር ክርስትና አሁንም ድረስ በቀላል ቁጥር በማይገመቱ ምእመናን ዘንድ ተቀባይነት ለማግኝት አልቻለም፤ ወይም ግልጽ አይደልም፡፡ የዚህ ዋነኛ ምክኒያቱ ደግሞ ስለ ጉዳዩ ለማሰብ፣ መጽሐፍ ቅዱስን አስረጅ አድርጎ ከማቅረብ ይልቅ ለሰው አመክንዮ (logic) እና ልማድ ትልቅ ሥፍራ መስጠት እደሆነ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ያምናል፡፡ ለምሳሌ “እንዴት አምላክ የሆነው ኢየሱስ ያማልዳል?” “ምልጃ የፍጡራን ሥራ መሆን አለበት፡፡” “ከማለደልንም፣ ሊማልድልን የሚችለው በምድር ላይ ሳለ ብቻ መሆን አለበት፡፡” የሚሉቱ ሎጂኮች ለፍጥረታዊ ሰው አስተሳሰብ ተቀባይነት ለማግኘት ቀሊሎች መስለው ሊታዩ ቢችሉም ማራኪ የሆኑ ተፈጥሮአዊ ፕሬሚሶች (መነሻ አሳቦች) ሁሉ ፍጹም ወደሆነው መንፈሳዊ ማጠቃለያ ላይ ሊያደርሱን እንደማይችሉ ልንገነዘብ ይገባል፡፡ እንዳውም ብዙዎቹ የእግዚአብሔር ሥራዎች -መዳናችንን ጨምሮ- ለእኛ ፍጥረታዊ አመክንዮ ግራና ሊቀበሏቸው የሚያስቸግሩ ናቸው (1ቆሮ. 1፡18-21)፡፡ ለዚህ ነው የእግዚአብሔርን ነገር መረዳት ለፍጥረታዊ ሰው ሞኝነት የሚሆው፡፡ “ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቀው አይችልም” (1ቆሮ. 2፡14)፡፡ ስለዚህ በመንፈስ የሚመረመረውን የእግዚአብሔርን አሳብ በራሱ ቃል መሰረት ለማረጋገጥ ከማጥናት ውጪ ከራሳችን አመክንዮና ሐይማኖታዊ ቅናቶች በመነሳት ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የምናረገው ማንኛውም ጥረት ውጤቱ አደገኛ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የሰማሁትን አንድ የእምነት ንግግር ላካፍላችሁና ይህን ሃሳብ ልቋጭ፡፡ አንድ የእግዚአብሔርን መኖር የማያምን ሰው አንዱን አማኝ እንዲህ ሲል ይጠይቀዋል፡- “እንዴት ዮናስ በታላቅ ዓሳ ሆድ ውስጥ ለ3 ቀንና ለሊት ቆየ ብለህ ማመን ትችላለህ፤ ይህ ከሣይንስ መርሆች አኳያስ እንዴት ያስኬዳል?” ብሎ ቢጠይቀው፣ “ወዳጄ፣ አንተ የቸገረህ ይህን ማመን ቢሆንም እኔ ግን ዓሣ አንበሪው በዮናስ ሆድ ውስጥ ለዚህን ያህል ቀናት ተቀመጠ የሚለው ሃሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ ባገኘው እንኳ ለማመን አልቸገርም፡፡” አለውና ውይይቱ በዚያው ተጠናቀቀ፡፡ የቱንም ያህል ለአእምሮአችንና ልማዶቻችን ይክበደው እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩትን ግልጽ አሳቦች መቃወም ፈጽሞ አይገባንም፡፡

4.2 የክርስቶስ የምልጃ አገልግሎት ከአብና መንፈስ ቅዱስ እንዲያንስ ያደርገዋል ወይ?

ኢየሱስ በመለኮቱ (በአምላክነቱ) ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል ስለመሆኑ የሚናገሩ በርካታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች ቢኖሩም ለአብነት የሚከተሉትን ይመልከቱ፡- “… ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ፡- እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፣ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት … ይፈልጉ ነበር” (ዮሐ. 5፡18)፡፡ “እኔና አብ አንድ ነን” (ዮሐ. 10፡30)፡፡ “… እኔን ያየ አብን አይቷል” (ዮሐ. 14፡9)፡፡ “ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው” (ዮሐ. 16፡15)፡፡ “በመጀመሪያ ቃል ነበር፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር፣ ቃልም እግዚአብሔር ነበር” (ዮሐ. 1፡1)፡፡ “… እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው” (1ዮሐ. 5፡20)፡፡

ኢየሱስ ይህን የምልጃ ሥራ በመስራቱ ከአባቱም ሆነ ከመንፈስ ቅዱስ አያንስም፡፡ ለነገሩ፣ በተግባራት ላይ ተመስርተን የተግባሩን ባለቤት ስታተስ (ክብር ወይም ሥልጣን) መመዘንና ደረጃ ማውጣት የሰው ሥርዓት ስለ ሆነ ይህንን እርኩሰት የተሞላበትን ባህላችንንና አስተሳሰባችንን ለፈጣሪ ፍጹም ሥራ ምዘና ሥናውለው ከፍተኛ ጥንቃቂ ማድረግ እንዳለብን መዘንጋት የለብንም፡፡ በዚህም ምክኒያት ነው እግዚአብሔር ወልድ ያለማንም አስገዳጅነት በፈቃዱ በፈጸመው የምልጃ ሥራ ከአባቱ አብ ወይም ከመንፈስ ቅዱስ እንደሚያንስ እንድናስብ የምንገደደው፡፡ እንግዲያው ሥላሴ በስልጣን፣ በገዢነት፣ በአምላክነት፣ ወዘተ አንድ ሲሆኑ በግብር (በስራ) ግን እንደሚለያዩ የሚተርከው የቤተ ክርስቲያን የእምነት አቋም ትርጉሙ ምኑ ላይ ነው? በግብር አንጻር፡- አብ በመውለዱ፣ ወልድ ደግሞ በመወለዱ ምክኒያት አብ ወላጅ ስለሆነ የሚበልጥ፣ ወልድ ደግሞ ልጅ ስለሆነ የሚያንስ እንዳልሆነ መቀበል ካልከበደን፣ ለምን በመስቀሉ ሥራ ላይ በግብር፡- አብ ተማላጅ ወልድ ደግሞ ማላጅ መሆኑን መቀበል ከበደን?

4.3 ክርስቶስ ያማለደው በሥጋው ወራት (በምድር ሳለ) ብቻ ነውን?

ኢየሱስ በምድር ላይ በሰነበተበት የ3አመት ተኩል ጊዚያት፣ በተለያየ ሁኔታ የምልጃ ሥራን ሰርቷል፡- ሉቃስ 22፡31-32፣ ዮሐ 17፡21፣ ሉቃስ 23፡34፣ ዕብ. 5፡7 – ነገር ግን አሁን በአባቱ ቀኝ በተቀመጠበት ጊዜ ይህ ቆሟል የሚሉ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ ይህ አስተያየት የክርስቶስን የክህነት ባሕሪ ጠንቅቆ ካለመረዳት ወይም ከባዶ ቅንዓት የሚመነጭ ነው የሚሆነው፡፡ የክርስቶስ ክህነት እንደ አሮን ሞት የሚከለክለውና የሚቋረጥ አይደለም (ዕብ. 7፡17)፡፡ ሞት ያላስቀረው ሊቀ ካህናችን ስለ ሆነ ስለ እኛ “…ሲያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል፡ ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል” (ዕብ. 7፡25)፡፡ የኢሱስ ክህነት/ምልጃ ዘላለማዊና የማይለወጥ ክህነት/ምልጃ ነው “… እርሱ (ኢየሱስ) ግን የማይለወጥ ክህነት አለው፤…”፡፡ “… የሞተው ይልቁንም ከሙታን የተነሳው በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” (ሮሜ. 8፡34)፡፡ ይህ ጥቅስ የክርስቶስ ምልጃ/ክህነት በመሞቱ ምክኒያት ያልተቋረጠ መሆኑን በግልጽ ያሳያል፡፡ ይህ ክህነት በምድር ላይ እያለ ብቻ ሳይሆን ከትንሳኤው በኋላ በአባቱ ቀኝ ተቀምጦም ሳለ አብሮት ያለ የዘላለም ሹመት እንደሆነ ያሳየናል፡፡ “አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ” (ዕብ. 5፡6) ያለውን ትንቢት መዘንጋት የለብንም፡፡

“ልጆቼ ሆይ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህንን እጽፍላችኋለሁ፤ ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቅ የሆነ ክርስቶስ ነው” (1ዮሐ. 2፡1) የሚለው ጥቅስ የኢየሱስን የጥብቅና ማዕረግ በጉልህ ያሳያል፡፡ ይህም ጥብቅና ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ሰዓት ብቻ ሳይሆን አሁንም ድረስ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብም ሆነ የኃጢአት ይቅርታን ለመቀበል ትምክህት ሊሆነን የሚችል ጠበቃ እርሱ ብቻ እንደሆነ የበስረናል፡፡ ጠበቃ አለን እንጂ ጠበቃ ነበረን አለማለቱን አንባቢ ልብ ይበል፡፡

“እርሱ (ክርስቶስ) … ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ …” (ዕብ. 10፡12) ስለ ተቀመጠ ምልጃውም አንዴ ለዘለዓለም የቀረበ የምልጃ/የክህነት ሥራ ስለሆነ ክርስቶስ ዛሬ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት እንደነበረው ሥርዓትና እንደ አሮን ክህነት በየአመቱ ወደ ቅድስት መስዋዕት ይዞ መግባት አያስፈልገውም (ዕብ. 9፡25)፡፡ በእግዚአብሔር ቀኝ ሆኖ ስለ እኛ ይማልዳል ማለት በመስቀል ላይ የፈጸመውን ሥራ ይደጋግማል ማለት ሳይሆን በኢየሱስ በኩል ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ እርሱ ስለ እኛ ይታያል ማለት ነው እንጂ፡፡

4.4 ኢየሱስ ካረገ በኋላም እንደሚማልድ የትውፊት መጽሐፍት ይናገራሉ፡-

“ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ የእኔ ስለ ሆኑት ምህረትን ወደ ምለምንበት ወደ ሰማይ ወደ አባቴ አርጋለሁ አላቸው፡፡” (መጽሐፈ ዚቅ ዘሰኔ ሚካኤል፣ ገጽ 189)

“አብ ሆይ ስለ ኢየሱስ እርዳን፤ ክርስቶስ ወደ ቸር አባትህ አማጽነን/አማልደን የአብና የወለድ መንፈስ አጽናናን፡፡” (ሰዓታት ዘሌሊት ወዘንግህ፣ ገጽ 222)

4.5 መዳናችንን/መጽደቃችንን/መታረቃችንን ከዚህ የክርስቶስ የምልጃ አገልግሎት በተለየ መንገድ የምናገኘው ነው ወይ?

መዳናችንን/መጽደቃችንን/መታረቃችንን ከዚህ የክርስቶስ የክህነት ሥራ በተለየ መንገድ እንደምናገኝ ማሰብ ወይም ለማግኘት መሞከር የእግዚአብሔርን የማዳን መንገድ ለማሻሻል ከመሞከር ሌላ የተለየ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡ ጽድቅ በሕግ በኩል ከሆነ፣ መዳን በሰው ምልጃ በኩል የሚገኝ ከሆነ፣ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ሌላ የተሻለ መንገድ ካለ፣ እንግዲያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ (ገላ. 2፡21)፡፡

4.6 “እኔ ኃጢአተኛ ስለ ሆንኩ፣ በእግዚአብሔር ፊት ልቀርብ ስለማልችል፤ ሌሎች መካከለኛ ሰዎች አያስፈልጉኝም ወይ?”

ከአዳም ውድቀት በኋላ፣ ሰውን ከሰው ሳይለይ ሁሉ (ሮሜ. 3፡9-11) በእግዚአብሔር ፊት መቅረብ አይችልም ነበር፡፡ እግዚአብሔር ጻድቅ ስለ ሆነ እርሱ ፊት ሊቀርብ የሚችለው ልክ እንደርሱ ቅዱስ የሆነ ሰው ብቻ ነው፡፡(ማቴ. 5፡48)፡፡  “እንግዲያስ ከሰው ዘር እንደ እርሱ ቅዱስ የሆነ ማን ሊገኝ ይችላል?” የሚል ጥያቄ ያነሱ ይሆናል፡፡ መልሱ በእርግጥ ተችሏል የሚል ነው! ይህም ሰው ኢየሱስ ይባላል፡፡ «የኢየሱስስ እሺ፣ የእኛ ዕጣ ፈንታስ?” የሚሉ ከሆነ የዛም ምላሽ ተገኝቷል፡፡ “እኛ በእርሱ ሆነን (በክርስቶስ ሆነን) የእግዚአብሔር ጸድቅ እንባል ዘንድ ኀጢአት ያላወቀውን እርሱን (ክርስቶስን) ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው” (2ቆሮ. 5፡21)፡፡ ይህ አስደናቂ የልውውጥ ሥራ ኃጢአተኞቹን እኛን ጻድቅ፣ ጻድቁን ጌታ ደግሞ ኃጢአት ያደረገ መለኮታዊ ሥራ ነው፡፡ በዚህ ሥራ አመካኝነት (በእርሱ በኩል) ሁላችን እንደ ጻድቅ ወደ እግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ድፍረት አግኝተናል (ዕብ. 10፡19-20፣ ኤፌ. 2፡13፣ 2፡16)፡፡ እንግዲህ ከአዳም ዘር የሆንን ሁላችን ማንንም ከማንም ሳይለይ ኃጢአተኞችና በእግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ የማንችል ብነሆንም በክርስቶስ በተደረገልን ቤዛነት፣ በእርሱ ፍጹም ሥራ በኩል ወደ እግዚአብሔር መቅረብም ሆነ መጸለይ እንችላለን፡፡ ወደ እግዚአብሔር የመቅረቢያ ድፍረታችን የለበስነው የኢየሱስ ጽድቅ እንጂ የእኛ መልካም ነገር አይደለም፡፡ በራሴ መልካም ሥራ በኩል ወይም ከእኔ በተሻሉ በምላቸው ሌሎች ሰዎች በኩል ወደ እግዚአብሔር መድረስ እችላለው የምትል ነፍስ ራሷን ከቅዱሱ ኢየሱስ ጋር እያወዳደረች መሆኗን ልትገነዘብና ንስሀ ልትገባ ይገባታል፡፡ ስለዚህ ከእርሱ ሌላ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብባቸው ሌሎች መካከለኞች፣ ሌሎች አማላጆች ፈጽሞ አያስፈልጉንም፡፡

4.7 “ልክ እንደ ብሉይ ኪዳን በሐዲስ ኪዳንም ለክህንነት የተመረጡ ጥቂት ግለሰቦች የሉም እንዴ?”

በሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያንን የመምራት፣ የማስተዳደርና ምእመኑን የመመገብ ኃላፊነት የተሰጣቸው መጋቢዎች፣ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት፣ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች፣ ዲያቆናት (ሐዋ. 20፡28፣ 14፡23፣ ፊሊ. 1፡1) ተብለው ስያሜን ከማግኘት ውጪ ከምእመናን በተለየ መልኩ ካህን ወይም ሊቀ ካህን የሚል ሹመት አልተሰጣቸውም፡፡ መጽሐፉ እንደሚል የሐዲስ ኪዳን ብቸኛ ሊቀ ካህን ኢየሱስ ብቻ ሲሆን (ዕብ. 2፡17፣ 9፡6-11) በእርሱ ያመኑ ምእመናን ሁሉ ዘር፣ ቀለም፣ ጾታ፣ የትምህርት ደረጃ ሳይለይ የእርሱ ካህናት ተብለዋል (1ጴጥ. 2፡5-9፣ ራዕ. 5፡10)፡፡ ዛሪም የብሉይ ኪዳን ክህነት ይሰራል ብለው የሚከራከሩ ካሉ፣ እንግዳው ይህም ክህነት ቢሆን ለአሮን ቤተሰብ ብቻ የተሰጠ መሆኑን ማስታወስ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለ ክህነት እግዚአብሔር የማያውቀው ክህነት ስለሆነ ፈጥነን ልንነቃ ይገባናል፡፡

5. ማጠቃለያና የንስሃ ጥሪ፡-

የጸሎት ምልጃን በተመለከተ ማንም ሰው ለማንም መጸለይ ይችላል (ያዕ. 5፡14፣ ቆላ. 4፡2-4፣ 12)፡፡ እርግጥ ነው እግዚአብሔር የሚፈሩትን ሰዎች ጸሎት ይሰማል (ምሳሌ 15፡29)፡፡ ይህ ማለት ግን የእግዚአብሔር ጆሮዎች በቁጥር ከ 50 ለማይበልጡ እኛ ለምናውቃቸው ቅዱሳን ብቻ የተከፈተ ነው ማለት አይደለም፡፡ ማናችንም ብንሆን እግዚአብሔርን በመውደድና በእምነት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ጸሎታችንን በኢየሱስ ስም ብንጸልይ እግዚአብሔር የሁላችንን ጸሎት ያለ ልዩነት ይሰማል፡፡ የማናችንም ሥራ በእርሱ ፊት ብቃትን ሊሰጠን አይችልም፡፡ ከክርስቶስ ውጪ ስንታይ፣ እንኳን አመጻችን ጽድቃችን እንኳ የመርገም ጨርቅ ነው (ቆሻሻ ነው) ኢሳ. 64፡6፡፡ ዛሬ ገና የምስራቹን ቃል (ወንጌልን) የተቀበለ አዲስ ክርስቲያን ቢሆን፣ የሰነበተ ዲያቆን፣ ጀማሪ ቄስ ይሁን፣ የበቃ ጳጳስ፣ የአንድ አመት መጋቢ ይሁን የቆየ ሽማግሌ፣ … በእግዚአብሔር ፊት ለመጸለይና ወደ ፊቱ ለመቅረብ የምንችለው በክርስቶስ ሥራ ብቻ ነው፡፡

ይህን ለራሳችንም ሆነ ለሌላ ሰው የምናደርሰው ጸሎት፣ ጸሎትን ወደ ሚሰማና ወደ ሚመልስ እግዚአብሔር ሊደርስ የሚችለው በአንድ መንገድ ብቻ ነው (ዮሐ. 14፡6)፡፡ ሊሎች አማራጮች የሉንም፤ አያስፈልጉንምም፡፡ ይህም መንገድ ኢየሱስ ነው፡፡ በስሙ (በኢየሱስ ሰም) የምንለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰማና እንደሚመልስ መጽሐፍ ቅዱሳችን በግልጽ ይነግረናል (ዮሐ. 14፡13-14፣ 16፡23-24)፡፡

ይህ ሁኔታ በአገራችን የትውፊት መዛግብት ላይ ሳይቀር እንግዳ አለመሆኑን ከድርሳነ ማኅየዊ የተወሰደውን የሚከተለውን ክፍል ይመልከቱ “አቤቱ ጌታችን ተቀዳሚ ተከታይ ስለ ሌለው ስለ ልጅህ ስለ ወዳጅህ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አማኑኤል ብለህ ይቅርታህን ከእኛ አታርቅ፤ መሀላህንም አታፍርስ” (ድርሳነ ማኅየዊ፣ ምዕራፍ 1 ቁጥር 13፣ ገጽ 5)፡፡

በመጨረሻም፣ በዚህ ጽሁፍ የቀረቡትን አሳቦች በመጠቅለል መቋጫ እናበጅና እንለያይ፡፡ የሰው ዘር ከውድቀት በኋላ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሆኖ መቅረብ ባለመቻሉ፣ ክርስቶስ ለዚህ ተስፋ ቢስ የሰው ዘር ወኪል በመሆንና በመታዘዝ ጻድቅ ሕይወቱን በሰው ልጅ ፈንታ ለእግዚአብሔር አቀረበ፡፡ የሰው ልጅ ሊሸከማት ያልቻለውን የኃጢአት ቅጣት በእርሱ ፈንታ በመሸከም የኃጢአት ስርየትን አስገኘለት፡፡ ከዚህም የተነሳ ሰው በእግዚአብሔር ፊት እንደ ጻድቅ ተቆጠረ፤ ክርስቶስ ግን ስለ እኛ ሃጢአት ሆነ፡፡ ሐዋሪያው ይህን ታላቅና አስደናቂ ልውውጥ “እኛ በእርሱ (በክርስቶስ) ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን (ክርስቶስን) ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው” በማለት ገልጦታል (2ቆሮ. 5፡21)፡፡ በአንድ በኩል ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር እርቅና ሰላም የሚኖረው ክርስቶስ በእርሱ ስፍራ የሕግን ቅጣትና እርግማን በመሸከሙ ሲሆን (ገላ. 3፡13) በሌላ በኩል ደግሞ በክርስቶስ ጽድቅ ውስጥ በመቆሙ ነው (1ቆሮ. 1፡30-31)፡፡

የክርስቶስ ሞት የእኛ ምትክ መሆኑ የሚያስገነዝበን ነገር ቢኖር እርሱ በእኛ ምትክ መሞቱን፣ የእኛን ህማም መታመሙን፣ የእኛን በደል መሸከሙን (ኢሳይያስ 53) ነው፡፡ ኢየሱስ ስለ እኛ ቆሰለ፣ ስለ እኛ ተዋደረ የማይገባውን ያውም የመስቀል ሞት ለመሞት የታዘዘ ሆነ (ፊሊ. 2፡8)፡፡ ጤነኛ የሆነ አእምሮ ሁሉ ይህን ካነበበ በኋላ “ግን ለምን?” ብሎ ሊጠይቅ ይገባዋል፡፡ መልሱም ሊያድነን፣ ከአብ ጋር ሊያስታርቀን፣ ቅዱስ ሕዝብ ሊያደርገን፣ ቀድሞ ወደ ነበርንበቱ ክብር መልሶ ሊያመጣን የሚል ይሆናል፡፡ ይህ የመዳን መንገድ ብቸኛው የመዳን መንገድ ነው (ዮሐ. 14፡ 6)፣ ከዚህ የተሻለ የመዳን መንገድ ለመፈለግ ማሰብም ሆነ ማድረግ ከእግዚአብሔር ይልቅ ጥበበኛ ነኝ ከሚል ትእቢተኛ ልብ የሚመነጭ ከመሆኑ ባሻገር የኢየሱስን ደም ማክፋፋትና (ዕብ. 10:29) ሞቱንም ከንቱ ማድረግ ይሆናል (ገላ. 2፡21)፡፡

ኢየሱስ ይህን ሁሉ ከፈጸመልኝ የእኔ ድርሻ  ምንድር ነው? እርስዎን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ የሚቀር ሌላ መሥዋዕት እንደሌለ ይወቁ፣ የኢየሱስ መሥዋዕት ፍጹም፣ ንጹህ፣ ቅዱስ፣ በቂ በመሆኑ እርስዎን ለማዳን የሚችል እንደሆነ ይመኑ፡፡ ይህንን የማዳን መንገድ ሙሉ ለማድረግ ከእምነት ውጪ ከእርስዎ ምንም እንደማይጠበቅ ይወቁ፡፡ ከዚህ ውጪ ምንም ነገር ለማድረግ በሚንቀሳቀሱበት ቅስበት የኢየሱስ የመስቀል ሥራ ጎዶሎና ያለእኔ እርዳታ በራሱ ሊቆም የማይችል ደካማ ሥራ ነው እያሉ እንደሆነ ይረዱ፡፡ “ለመዳን (ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ) ከማመን ውጪ ከኔ የሚጠበቅ እኔ የማዋጣው ነገር የለም ነው የምትለኝ?” የሚሉኝ ከሆነ፣ እኔ ደግሞ በተራዬ አንድ ጥያቄ እንድጠይቆ ይፍቀዱልኝ፡- “ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ እርሶ ሊያደርጉት የሚችሉት አንዳች ነገር ቢኖር ኖሮ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ለዚህ ሥቃይ አሳልፎ የሚሰጠው ይምስሎታል?”

ኢየሱስ በመሥቀሉ ላይ ሞትዎን እንደሞተልዎ ሥቃይዎን እንደ ተሰቃየልዎ ብያምኑ፣ ለነፍስዎም ቤዛ አድርጎ ሕይወቱን አሳልፎ እንደ ሰጠ ቢያምኑ፣ እግዚአብሔር በእርስዎ ላይ የተቆጣውን ቁጣ በእርስዎ ምትክ ሆኖ ሁለት እጆቾን ዘርግቶ እርቃኑ በቀራንዮ ኮረብታ ላይ በተገኘልዎ አዳኝ ላይ ማሳረፉና እርስዎም በዚህ ምክኒያት ከዚያ አስፈሪ ቁጣ ማምለጥዎን ቢያምኑ፣ ከተጣላዎ ፈጣሪዎ ጋር እርቅ ፈጥረዋልና በእርግጥም የዘላላም ሕይወት አሎት!! በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ምክኒያት (እርሱን ለብሰው) ስለሚታዩ ጻድቅና ቅዱስ ለርሰቱም የሚመጥኑ ሆነው በፊቱ መቆም ይችላሉ፡፡ ጸሎት መጸለይ፣ ጦም መጦም፣ ችግረኛ መርዳት፣ በቅድስና ለመኖር ራስን መግዛትና የመሳሰሉት ነገሮች ሁሉ ከአምላኩ ጋር ከታረቀና የዘላለም ሕይወት እንዳለው ከሚያምን አማኝ ሁሉ የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት እያንዳንዱ ሰው ሽልማት የሚቀበልበት መመዘኛዎች ናቸውና የሚናቁ ነገሮች አይደሉም (ራዕ. 22፡12)፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ነገሮች በአንድ ላይ ሆነው እንደተራራ ቢቆለሉ ክርስቶስ ለእርሷ ካደረገልዎ የመስቀል ሥራ አንጻር የኢምንት መጠን እንኳ ሊቸራቸው አይችልም፤ ፈጽሞም ከእግዚአብሔር ጋር ሊያስታርቋ አይችሉም፡፡

የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔርም ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስም ሕብረት ከእርሶ ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡

ዋቢ መጻሕፍት

የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ፣ በ ዳ.እ

የአዲስ ኪዳን መካከለኛ

ኀይማኖተ አበው

ትምሕርተ ክርስቶስ፣ በቄስ ኮሊን ማንስል

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading