ጸሎት
‹‹አባት ሆይ፣ በመንፈሳዊ አለም ውስጥ ወልደኸኛል፡፡ በብዙ መንገድ ገና መንፈሳዊ ልጅ መሆኔ ይሰማኛል፣ እንዲህ ሆኜ መሰንበት አልፈልግም! በመንግስትህ ውስጥ እንግዳ ያለመሆን ስሜት እንዲሰማኝ እሻለሁ፡፡ ጌታ ሆይ፣ እንዳድግ እርዳኝ፡፡ እኔን በማብሰል ሂደትህ ውስጥ በምን መንገድ ካንተ ጋር መተባበር እንዳለብኝ አመልክተኝ፡፡ ለዚህ ጉዞ አስፈላጊ የሆኑትን ጥበብ፣ መገለጥና ትዕግስት ስጠኝ፡፡ አሜን፡፡››
መንፈሳዊ እድገትን የሚረዱ ተግባራትና ዝንባሌዎችን ማወቅ ለምን ያስፈልጋል?
ታላቁ የጣሊያን የቅርፃ ቅርፅ ባለሙያ ቤንቬኒቶ ሴሊኒ፣ አንድ ግዙፍ እብነበረድ ወደ ጣልያን፣ ፍሎረንስ የሚመጣበትን ቀን አበሰረ፡፡ እብነ በረዱ፣ በላዩ ላይ ከሚታይ አንድ ጉልህ ህፀፅ በስተቀር ምርጥ ድንጋይ ነበር፡፡ በዚህ ጉልህ ህፀፅ ምክንያት ከአንድ ባለሙያ በስተቀር እብነ በረዱን ቀርፆ ለማስዋብ ፋቃዱን ያሳየ የስነ ጥበብ ሰው አልነበረም፡፡
ፍሎረስ በሚገኝ በአንድ የሕዝብ አደባባይ እብነ በረዱ እንዲተከል ተደረገ፡፤ በእብነ በረዱ ዙሪያ አጥር ተሰራ፣ ለቀራፂው ማረፊያ የሚሆን እንደ ነገሩ የተሰራች ቤትም ተቀለሰ፡፡ ከዚህ በኃላ ቀራፂው ለሁለት አመታት ያህል ያን ግዙፍ እብነ በረድ ማበጀት ቀጠለ፡፡ ሥራው ሲጠናቀቅም በእብነ በረዱ ዙሪያ የነበረው አጥር ተነሳ፣ የቀራፂውም ቤት ፈረሰ፣ ስራውም ለፍሎረንስ ነዋሪ ለጉብኝት ግልጽ ሆነ፡፡ አስደናቂ ሥራ ነበር የታየው፡፡ ዛሬም ድረስ ይህ የቅርፅ ጥበብ አይን ካያቸው ታላላቅ የቅርፃ ቅርፅ ስራዎች መካከል አንዱ እንደሆነ በርካታ ሰዎች ይስማሙበታል፡፡ ይህ ስራ የሚቺላንጎ ‹‹ዴቪድ›› ነበር፡፡
ከዛ ግዙፍ ቅርፅ አልባ እብነበረድ ውስጥ አስደማሚ ሃውልት ወጣ፡፡ ሌሎች ቀራፂዎች አስቀድመው ይህ ቅርፅ አልባ እብነበረድ ያለውን ዋጋ ማየት አልቻሉም፤ ሚቼላንጎ ግን ማየት ችሎ ነበር፡፡ እነሱ እብነ በረዱ ባለው ጉልህ ህፀፅ ምክንያት እጃቸውን በላዩ ሊያሳርፉ አልፈለጉም፤ ሚቼላንጎ ግን ስራውን ከመጀመሩ በፊት የዚህ እብነ በረድ ፍፃሜ ምን ሊሆን እንደሚችል በአይነ ህሊናው አይቶት ነበር፡፡
እግዚአብሔር አንተን ማየት ከጀመረ ሰንብቷል፡፡ እናም አሁን ባለህበት ደረጃ እንኳን ባንተ ውስጥ አስደናቂ ያለቀ ሥራን ይመለከታል፡፡ በውስጥህ ያሉትን ህፀፆች ሁሉ ያውቃቸዋል። አንተን እንዴት አድርጎ መስራትና ህጸጾቹን ደግሞ እንዴት ማስወገድ እንዳለበትም ጭምር ያውቃል፡፡ የእግዚአብሔር ሃሳብ ልጁ ኢየሱስን እንድንመስል ማድረግ ነው፡፡ ኢየሱስን በተክለ ሰውነቱ እንድንመስለው ሳይሆን በዝንባሌአችን፣ ቅድሚያ በምንሰጣቸው ጉዳዮች አንፃር፣ በሕይወታችን ጭብጦች፣ እና በምርጫዎቻችን ጭምሮ ቁርጥ እርሱን እንድንመስል ነው የእግዚአብሔር ናፍቆት፡፡ እግዚአብሔር ከክርስቶስ መልክ ጋር የማይገጥሙትን ነገሮችህን በማለስለስ፣ በማፅዳት፣ በማረም እና በመጥረብ ሕይወትህን ከውስጥ ወደውጭ ማበጀት ይፈልጋል፡፡
እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባ ነጥብ አለ፡- አንተ ቀዝቃዛ፣ ሕይወት የሌለው የእብነበረድ ቁራጭ አይደለህም፡፡ ከድንጋዩ በተለየ መንገድ በቀራፂው መሮ ዙሪያ በሕያውነት መንቀሳቀስ ትችላለህ፡፡ አለመተባበርም ሆነ ስለ ሰሪው ስራ የግልህን አመለካከት ማራመድ ትችላለህ፡፡ በሰሪው ግቦች ላይ ፍላጎት ልታጣ ወይም በሥራው ሂደት መካከል ልትሰለች ወይም ትዕግስት ልታጣም ትችላለህ፡፡ ምናልባትም በግማሽ ደረጃ በተጠረቡ እግሮችህ ተነስተህ በመሄድ ለቀናት ወይም ለሳምንታት ተመልሰህ ወደቀራፂው ላትመጣ ትችላለህ፡፡ ከቀራፂው መዶሻ፣ በመሮው ላይ የሚያርፈው ጡጫ ደቃቅ የድንጋይ ጥራቢ እንኳን ከአንተ ላይ እንዳያንሳ አመጸኛ ልትሆንም ትችላልህ፡፡ በዚህ ምክንያት ከወራት ወራት፣ ከአመታት አመታት፣ ከአስርተ አመታት አስርት አመታት፣ በግማሽ የተጠናቀቀ ሥራ ብቻ ልትኖር ትችላልህ፡፡
የዚህ ጥናት አላማ ይህን ‹‹ያለመተባበር›› ዝንባሌ እንዴት ማስወገድ እንደምትችል በማሳየት መርዳት ነው፡፡ በልብህ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመምሰል መለወጥ እንዳለብህ ትረዳለህ፡፡ ሂደቱ ፈጣንና ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ወዳዘጋጀልህ ወደዚህ ረጅም ጉዞ ለመግባትና ሂደቱንም ለማፋጠን ልታደርጋቸው የሚገቡህ ነገሮች ይኖራሉ፡፡
ይህ ጥናት ከዚህ በኃላ ለሚቀርቡት አራት ተከታታይ ጥናቶች የመሠረት ድንጋይ ይጥላል፡፡ እነዚህን አምስት ጥናቶች ካጠናቀቅህ በኋላ የሕይወት ዘመን እድገትህንና ስኬትህን እውን የሚያደርጉ ተግባራዊ ምልከታዎች ልታገኝበት ይገባል፡፡
የመንፈሳዊ እድገት ንጥረ ነገሮች
በእድገት ላይ እንዳሉ እንደማንኛውም ነገሮች፣ አዲስ መንፈሳዊ ማንነትህ በእድገት ጎዳና ላይ ጉዞውን እንዲቀጥል አስተዋፅኦ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡ ስድስት ቁልፍ ንጥረ ነገሮች እነሆ፡-
- የክርስቶስ ጌትነት
- መጽሐፍ ቅዱስ
- ጸሎት
- ሕብረት
- ምስክርነት
- መታዘዝና ድርጊት
ቀልጣፋና ውጤታማ የእድገት ልምምድ የምትሻ ከሆነ እላይ ከተገለፁት ሁለቱ ወይም ሶስቱ ላይ ብቻ መደገፍ ሳይሆን ያለብህ ስድስቱንም በተመጣጣኝ ደረጃ መለማመድ ይኖርብሃል፡፡ እነዚህ ነገሮች በቅንጅት በመጠቀም እንዴት ‹‹የመብሰል ጉዞህን›› ስኬታማ ልታደርግ እንደምትችል ለማስረዳት፣ በዚህ ጥናት ውስጥና በተከታታያ በሚቀርቡት አራት ጥናቶች ውስጥ ‹‹የጎማ ምሳሌን›› እንጠቀማለን፡፡ እንዴት ከእግዚአብሔር እቅድ ጋር በመተባበር ማደግ እንደሚቻል በቀላሉ በማስረዳት ይህ ምሳሌ ጠቃሚ ነው ብለን እናምናለን፡፡
- የክርስቶስ ጌትነት
ኃይል፣ ከጎማው እምብርት (ማዕከል) ይነሳና በሽቦዎቹ መሃከል ከተሰራጨ በኃላ ለጎማው ጠርዝ ይደርሳል፡፡ በማናቸውም ጎማዎች ውስጥ የሚሆነው ነገር ይኸው ነው፡፡ የአንድ ክርስቲያን ማዕከላዊ የኃይል ምንጭ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህም በመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት በአማኙ ሕይወት ውስጥ ይገለጣል፡፡
በመጀመሪያ ከዚህ በታች የቀረቡትን ጥቅሶች አንብብ፡፡ ከዛም ጥቅሶቹ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወታቸው ማእከል ያደረጉ ሰዎች ምን እንደሚሆኑ ነው የሚከተሉት ጥቅሶች የሚናገሩት?
- ማቴዎስ 6፡33
- ዮሐንስ 12፡26
- ዮሐንስ 15፡4-7
ኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወትህ አዳኝ እንዲሆን መጋበዝ አንድ ነገር ነው፡፡ ይህ ብቻ ግን በቂ አይደለም። የሕይወትህ ጌታ እንዲሆንም ልትጋብዘው ይገባሃል። ይህን አድርገሃል? ካላደረግህ ለምን አሁን ጥቂት ጊዜ ወስደህ የሕይወትህ ጌታ እንዲሆን በጸሎት አትጋብዘውም?
- መጽሐፍ ቅዱስ
ባለፉት ክፍሎች እንደተማርከው አንተ ከሰውነት (አካል/ሥጋ)፣ ነፍስና መንፈስ የተዋቀርክ ፍጥረት ነህ፡፡ የግሮሰሪ ምግቦች ሰውነትህን እንደሚመግቡ ለአንተ እንግዳ እውቀት ሊሆን አይችልም፡፡ መልካም፣ ውብና እውነተኛ መረጃ ደግሞ ነፍስህን ይመግባል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር የምታዛመድህን መንፈስህንስ ምን ይሆን የሚመግባት? ምላሹ መጽሐፍ ቅዱስ ነው! የእግዚአብሔር ቃል ለአዲሱ ተፈጥሮህ መንፈሳዊ ምግቡ ነው፡፡
‹‹…አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ›› -1ጴጥሮስ 2፡2
አንድ ህፃን የሚፈልገው ወተት ካልተሰጠው (ከማልቀስ በተጨማሪ) ምን የሚሆን ይመስልሃል?
የእግዚአብሔር ቃል በሕይወትህ ላይ ያለው ተፅዕኖ
ከዚህ በታች የቀረቡትን እያንዳንዱን ጥቅሶች መርምር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ጊዜ ስትሰጥ፣ ስትወያየውና በሕይወትህ ላይ ተግባራዊ ስታደርገው ምን አይነት ጥቅሞች እንደምታገኝ እነዚህ ጥቅሶች ይነግሩሃል፡፡
- ‹‹የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፣ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም።›› -ኢያሱ 1፡8
- ‹‹የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው፣ በእርምጃውም አይሰናከልም።›› -መዝሙር 37፡31
- ‹‹ጕልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው። በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ፣ ከትእዛዝህ አታርቀኝ። አንተ እንዳልበድል፣ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ።›› -መዝሙር 119፡9-11
- ‹‹‹ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴ ብርሃን ነው።›› -መዝሙር 119፡105
- ‹‹በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል።›› -ዮሐንስ 15፡7
- ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።›› -2ጢሞቴዎስ 3፡16-17
ዮሐንስ 8፡31 አንብብ፡፡ ይህ ጥቅስ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ከሚሹት ዘንድ ምን እንደሚጠበቅባቸው ነው የሚናገረው? ይህን የሚጠበቅባቸውን ነገር አድርገው ቢገኙስ ምን ይሆንላቸዋል?
- ጸሎት
እግዚአብሔር ምን ያህል እንደሚያፈቅርህ ታውቃለህ? ሙሉ በሙሉ በአንተ ፍቅር ተነድፏል! በመኝታህ ሳለህ፣ ፊትህን ትክ ብሎ ይመለከታል፣ በራስህ ላይ ያሉትን ፀጉሮች ይቆጥራል፣ ላንተ የወጠነውን እቅድ ያስባል፣ ወዘተ! በእያንዳንዱ ቀን ስትነቃ ደግሞ ከአንተ ጋር ሕብረት ለማድረግ ይጓጓል፡፡ በሁለት በሚፋቀሩ ሰዎች መካከል እንደሚስተዋለው፣ ተግባቦት የሕብረቱ የደስታ ምክንያት ብቻ ሳይሆን ለሕብረቱ መኖርና እድገት ቁልፍ ነገር እንደሆነ ልብ ልትል ይገባል፡፡
እግዚአብሔር ድምጽህን መስማት ይሻል! ደስታህን፣ ተስፋዎችህን፣ ፍርሃቶችህን፣ ጥያቄዎችህን እና ምኞቶችህን እንድትገልጽለት ይፈልጋል፡፡ ካንተ ጋር ማውራት ይናፍቃል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ጸሎት ማለት – በሁለት በሚዋደዱ አካላት መካከል የሚደረግ ጭውውት!
የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብብ፡፡ እያንዳንዳቸው ጥቅሶች እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በጸሎት እንድታወራ የሚሻበትን ምክንያት ያቀርባሉ፡፡
- ማቴዎስ 7፡7-11
- ዮሐንስ 16፡24
- ፊሊፕሲዩስ 4፡6-7
ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር በእውነትና በግልጽ የምናወራበት፣ ችግሮች በሚያገጥሙን ጊዜ ደግሞ እርዳታውን የምንጠይቅበት ያልተወሳሰሰበ የግንኙነት መስመር ነው፡፡
‹‹ወደ እኔ ጩኽ፣ እኔም እመልስልሃለሁ፤ አንተም የማታውቀውን ታላቅና ኃይለኛ ነገርን አሳይሃለሁ።››-ኤርሚያስ 33፡3።
- ከላይ ያለው ጥቅስ፣ አንተ ወደ እርሱ ‹‹ብትጮህ›› እግዚአብሔር ምን ጥቅሞችን እንዳዘጋጀልህ ይናገራል?
- ይህ አንተ የምትፈልገው ጥቅም ነው? ከሆነ ለምን/ካልሆነ ለምን?
የጸሎት አይነቶች
አራት መሠረታዊ የጸሎት አይነቶች አሉ፡፡ ከዚህ በታች የቀረቡት አራት ጥቅሶች የእነዚህ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እያንዳንዱን ጥቅሶች ካነበብክ በኋላ የጸሎት አይነቶቹን ስለሚገልጹ ቃላት ወይም ሃረጋት ትኩረት ስጥ፡፡ ምሳሌ፡- ‹‹የንስሃ ጸሎት፡፡››
- ‹‹አምላኬ ንጉሤ ሆይ፣ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፣ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም እባርካለሁ። በየቀኑ ሁሉ እባርክሃለሁ፣ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም አመሰግናለሁ።›› -መዝሙር 145፡1-2
- ‹‹እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፣ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና። አንተን ብቻ በደልሁ፣ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፣ በነገርህም ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ።›› -መዝሙር 51፡3-4
- ‹‹አቤቱ፣ እናመሰግንሃለን እናመሰግንሃለን ስምህንም እንጠራለን፤ ተኣምራትህን ሁሉ እናገራለሁ።›› -መዝሙር 75፡1
- ‹‹እባክህ፣ መባረክን ባርከኝ፣ አገሬንም አስፋው፤ እጅህም ከእኔ ጋር ትሁን፤ እንዳያሳዝነኝም ከክፋት ጠብቀኝ ብሎ የእስራኤልን አምላክ ጠራ፤ እግዚአብሔርም የለመነውን ሰጠው።›› -ዜና 4፡10
እግዚአብሔርን ስለማንነቱ (ስለ ባሕሪው) አድንቀው።
እግዚአብሔርን ስላደረገው (ስለ ተግባሮቹ) አመስግነው።
- ሕብረት
እግዚአብሔር ስለመንግስቱ እኛን ለማስተማር የተጠቀመባቸው በርካታ ምሳሌቶች አሉ፡፡ በልጆቹ መካከል ስላለው ሕብረት ለማስተማር የተጠቀመበት የአካል ብልቶች፣ ምሳሌ አንዱ ነው፡፡
- ከመጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ1ቆሮንቶስ 12፡4-26 እውጥተህ አንብብ፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያን የአካልን ብልቶች የሚመስሉት እንዴት ነው?
- ከአካልህ አንዱ ብልት ሲታመም ወይም አካልህ አንድ ነገር ሲፈልግ ሌሎቹ የአካልህ ብልቶች ምን ይሆናሉ?
- ይህ ሃሳብ፣ በአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ አባላት እርስ በእርሳቸው ማድረግ ስላለባቸው ነገር ምን ትምህርት ያስተላልፍልሃል?
- ‹‹ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልከኛ እንዳይሆን፣ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፣ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ፤››-ዕብራዊያን 3፡13። በጥቅሱ መሰረት ኃጢአት ባንተ ላይ ሁለት ነገሮች ያደርጋል፡፡ መጀመሪያ_________ቀጥሎ ____________ ያደርግሃል፡፡
- ‹‹ብረት ብረትን ይስለዋል፣ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል።››-ምሳሌ 27፡17 በጥቅሱ መሠረት፣ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ጊዜ መውሰድ ምን ሌላ ጠቃሚ ነገር አለው?
- ‹‹ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።››-ማቴዎስ 18፡20። ጥቅሱ፣ ሕብረት ማለት ‹‹ሁለት ወይም ሦስት በመሆን በስሙ መሰብሰብ›› እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በዚህ ውኔታ ውስጥ ስንገኝ ምን ልዩ ነገር ይሆናል?
በምን መንገድ ሕብረት ማድረግ እችላልሁ?
- በእሁድ ጠዋት የአምልኮ አገልግሎት ላይ
- በእሁድ ምሽት የአምልኮ አገልግሎት ላይ
- ሣምንታዊ በሆኑ በሌሎች የቤተክርስቲያን ስብሰበዎች ላይ
- በአነስተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ቡድን ላይ
- በቤት የሕብረት ቡድን ላይ
- በጸሎት ስብሰባዎች ላይ
- በስፖርት ትዕይንቶች ጊዜ
- በጂምናዚየም ውስጥ
- ምግብ በምመገብበት ጊዜ
- በምሮጥበት ጊዜ
- በግብይት ጊዜ
- ሳይክል በምነዳበት ጊዜ
- በማገለግልበት ጊዜ
በዚህ ጉዳይ ላይ አሰላስል፡-
በቲቶ 1፡8 መሠረት ከቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ (ከቤተ ክርስቲያን መሪ) ከሚጠበቁ ዋነኛ አዎንታዊ ባሕሪያት መካከል አንዱ ‹‹እንግዳ ተቀባይነት›› ነው፡፡
ይህንን ልብ በል፡- እውነተኛ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ሕብረት፣ ተገናኝቶ ስለ አየር ንብረት አውርቶ ከመለያየት ይዘላል፡፡ ለመተናነፅ፣ ለመረዳዳት፣ የእግዚአብሔርን ቃል ለመከፋፈል፣ ገንቢ ግብረ-መልሶችን ለመለዋወጥ፣ ፍቅርን ለመገላለፅ እና ኢየሱስ ባልንጀራህን ለማበረታታት አንተን እንዲጠቀም ሕብረቱን ልትገለገልበት ይገባል፡፡
- መመስከር
በሕይወትህ የሆነልህ ታላቅ ነገር ምንድን ነው? ክርስቲያን ከሆንክ፣ ምናልባት ልትለው የምትችለው ነገር – ‹ክርስቶስን የተቀበልኩበትና የዘላለም ሕይወት ያገኘሁበት አጋጣሚ ነው› የሚል ይሆናል፡፡ ምላሽህ ይህ ከሆነ አንተስ ለሌላው ሰው ልታደርገው የምትችለው ትልቁ ነገር ምንድን ነው?
ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፣ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ። -ዳንኤል 12፡3
የምሳ ወቅት ምስክርነት…
ዮሐንስ 4፡1-34 አንብብ፡፡ ይህ ታሪክ ኢየሱስ በውኃ ጉድጓድ አቅራቢያ ለአንዲት ሰማሪያዊት ሴት ሲመሰክር ያስነብበናል፡፡ ይህ ታሪክ በተፈጸመበት ዘመን፣ ወንዶች ከሴቶች ጋር የስነ መለኮት ውይይት በማድረግ ራሳቸውን ዝቅ ማድረግ የማይሹበት፣ አይሁዳዊ ወንድ ደግሞ ከሰማሪያዊት ሴት ጋር በማውራት ራሱን ማርከስ የማይፈልግበት ጊዜ ነበር! ኢየሱስ ግን እነዚህን ማህበራዊ ‹ነውሮች› ጥሶ ለዚህች ሴት በግልጽና በፍቅር ወንጌልን ነገራት፡፡ ሴቲቱ፣ ኢየሱስ መሲሁ (ክርስቶስ) እንደሆነ አምና ይህንን ዜና ለመንደሯ ሰዎች ለመናገር ስትሄድ ደቀ መዛሙርቱ ለኢየሱስ ምሳ ይዘው ደረሱ፡፡ ምሳውንም በሰጡት ጊዜ፣ ኢየሱስ ከረሃቡ እንደረካ ሰው በትህትና ግብዣቸውን አልተቀበለም፡፡ በቁጥር 32-34 ላይ፣ ኢየሱስ ከምግብ በላይ የሚያረካው ነገር እንዳለ ገለጸላቸው፡፡ ይህ ነገር ምንድን ነው?
ሁለት የምስክርነት ዘዴዎች፡-
እነዚህ ዘዴዎች የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች በመሆናቸው አብረው የሚጓዙ ነገሮች ናቸው፡፡ አንዱን ከአንዱ ለይተህ አትጠቀም!
ሀ. ሕይወትህ /ኑሮህ
‹‹ሕይወትህ ሰዎች ሊያነቡት የሚችሉት ‹መጽሐፍ ቅዱስ› ነው፡፡›› ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ፣ ወይም የክርስቲያን ቴሌቭዥኖችን ለማየት፤ ወይም የወንጌል በራሪ ወረቀቶችን ለማንበብ ቸልተኛ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ሃይል የተሞላውን ሕይወትህን በትምህርት ቤት ውስጥ፣ ወይም በመስሪያ ቤት ውስጥ፣ ወይም በመንደርህ ውስጥ ሲመለከቱና በአንተ ውስጥ መንፈስ ቀዱስ ተፅእኖ ሲያሳድርባቸው ሲያዩ በምታድርገው ነገር መሳብ ይጀምራሉ፡፡ ለምን እንደ እዛ እንደምትኖር ለማወቅም ይፈልጋሉ!
መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። -ማቴዎስ 5፡16። ጥቅሱ ‹‹ብርሃናችን በሰው ፊት ሁሉ እንዲበራ›› ያዘናል፡፡ ለመሆኑ ይህንን እንዴት ነው ማድረግ የምንችለው?
መልካም ነገር ማድረግ ብቻ በቂ ይሆን? የሌላ እምነት ተከታዮች እና እምነት የለሾች ሳይቀሩ በጣም ጥሩ፣ በጥንቃቄ የተሞላና ለጋስ ኑሮ ሲኖሩ ይስተዋል የለምን? ምስክርነት ያለው መልካም ኑሮ ከመኖር በተጨማሪ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ይህ ጥያቄ፣ ወደ ሁለተኛው አስፈላጊ ነገር ያመራናል።
ለ. ቃሎችህ
ሰዎች በአንተ ውስጥ በሚገኘው የእግዚአብሔር ብርሃን ሊሳቡ ይገባል፡፡ ነገር ግን አንዴ ወደ እዚህ ደረጃ ከደረሱ በኋላ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ አንዳንድ ነገሮችን ማወቅ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የንግግር ምስክርነቱ የሚመጣው፡፡ ይህ ማለት ኢየሱስ በውኃ ጉድጓድ አጠገብ ከሰማሪያዊቷ ሴት ጋር ሲያደርገው የነበረው ነገር ማለት ነው፡፡
እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። -ሮሜ 10፡17። በጥቅሱ መሠረት እምነት በሰው ውስጥ ከመፈጠሩ በፊት ምን መደረግ አለበት?
- መታዘዝና ድርጊት
የእግዚአብሔር የማስቻል አቅም ከጎማው እምብርት (ከሕይወትህ ማዕከላዊ ክፍል ከክርስቶስ) ተነስቶ በሽቦዎቹ ውስጥ በማለፍ በመጨረሻ በጎማው ጠርዝ ላይ ይደርሳል፣ በዚህ ሰአት ጎማው ለመሽከርከር ዝግጁ ይሆናል፡፡ ሽቦዎቹ በአግባቡ ባይሰሩስ? መታዘዝ (-ፈቃዳችንን እና ድርጊታችንን ያካትታል) እና ድርጊት (-የፈቃድን ውሳኔ ተግባራዊ የሚያደርግ) በሌለበት፣ ጎማው የተቦረቦረ መንገድን የማለፍ አቅም አይኖረውም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ብትሆን፣ ወይም በአንድ ጊዜ ለረጅም ሰአታት የምትጸል ብትሆን፣ ወይም ያለማቋረጥ ቤተ ክርስቲያን የምትሄድ ብትሆን፣ አልያም ለሚንቀሳቀሰው ፍጥረት ሁሉ የምትመሰክር ሰው ብትሆንም፣ እግዚአብሔር በቃሉ እና በቅዱስ መንፈሱ በኩል እንድታደርግ ለሚጠቁምህ ነገር በመታዘዝ ምላሽ ካልሰጠህ፣ ወደ ብስለት የምታደርገው ጉዞ ብዙ ችግር ይገጥመዋል፡፡
ከዚህ በታች ባሉት ጥቅሶች ውስጥ ምን የጋር የሆነ ጭብጥ ታዘብክ?
- ‹‹ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ ቃሌንም ሰምቶ የሚያደርገው፣ ማንን እንዲመስል አሳያችኋለሁ።›› -ሉቃስ 6፡47
- ‹‹እናቴና ወንድሞቼስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት እነዚህ ናቸው አላቸው።›› -ሉቃስ 8፡21
- ‹‹አዎን፣ ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው አለ።›› -ሉቃስ 11፡28
- ‹‹በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉት ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ ጻድቃን አይደሉምና።›› -ሮሜ 2፡13
- ‹‹ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ።›› -ያዕቆብ 1፡22
- ሉቃስ 6፡46-49 አንብብ፡፡ ኢየሱስ ይህንን ምሳሌ ‹‹ጌታ ሆይ፣ ጌታሆይ›› ብለው ለሚጠሩት በርካታ ሰዎች ተናገረ፡፡ ኢየሱስ በዚህ ሁኔታቸው ደስተኛ አልነበረም፡፡ ችግሩ ምንድን ነበር?
- ‹‹ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ።›› -ዮሐንስ 14፡21 በጥቅሱ መሠረት፣ ለኢየሱስ ያለንን ፍቅር በምን አይነት መንገድ መግለጽ አለብን?
- ክርስቶስን ስንታዘዝ፣ የእግዚአብሔር አብ ምላሽ ምን ይሆናል? የእግዚአብሔር ወልድ ሁለት ፈርጅ ምላሾችስ ምንድን ናቸው፡፡
ስለ መንፈሳዊ እድገትን ልታውቃቸው የሚገቡ ሌሎች ሦስት ጠቃሚ ነገሮች…
ሀ) ጊዜ
በጥቂት ሳምንታት፣ ወሮች ወይም አመታት ውስጥ ‹‹ታላቅ ክርስቲያን›› ለመሆን አትጠብቅ፡፡ ለራስህ፣ ለእግዚአብሔርና እርሱ ላንተ ላለው እቅድ ታጋሽ ልትሆን ይገባል፡፡ አንዳንድ ጊዜ እድገትህ እስኪያምህ ድረስ ዝግ ያለ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት በመጠራጠር ብሕይወትህ እድገት ስለመኖሩም ራስህንንና እግዚአብሔርን ልትጠይቅ ትችላለህ፡፡ ጥራት የሚያሻው ሕይወትህ የእግዚአብሔርን በቂ ጊዜ ይሻል፡፡ እግዚአብሔር የበሉጥን ዛፍ ለማብቀል መቶ አመታትን ይወስዳል ስኳሽን ግን በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ያበጃታል፡፡
ለሁሉ ዘመን አለው፣ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። -መክብብ 3፡1
በእግዚአብሔር ሥራ ውስጥ አቋራጭ መንገዶችና የተዋከቡ ትምህርቶች የሉም! የማይለያይና ፍፁም የሆነ የፍጥነት ወሰን (pace) ያለው የእድገት ሂደትም የለም፡፡ እናም በአንድ መልኩ አስደሳች የእድገት እምቡጦች ስትለማመድና በሌላ ምልኩ ደግሞ ረጅም ጊዜ የሚጠይቁ እድገቶችን ስትለማመድ ሁለቱም የእድገትህ ሂደት አካሎች መሆናቸውን ልብ በል፡፡ ነገሩ ‹‹የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል›› እንደሚባለው የአገራችን ብሂል ነው፡፡
ለ) አስቸጋሪ ሁኔታዎች
አንዳንድ ክርስቲያኖች አስቸጋሪ ወቅቶች ሲገጥሟቸው እንዲህ በማለት ምክንያታዊ ለመሆን ይሞክራሉ፡- ‹‹የንጉሥ ልጅ ስለሆንኩ መንገዴ ለስላሳና ቀጥተኛ ሊሆን ይገባል!››
በማጉሊያ መነፅር የዛፍ ቀለበቶችን ተመልክተህ ታውቃለህ? ይህን አድርገህ የምታውቅ ከሆነ፣ ነጣ ያለ ቀለም ያላቸውን ህዋሶች/ሴሎች የሰሯቸው ቀለበቶች ትልልቅና ወፋፍራሞች መሆናቸውን ትመለከታለህ፡፡ ይህ ተክሎች በቂ ውኃ፣ ምግብና የፀሐይ ብርሃን እንድልብ በሚያገኙበት የክረምት ወራት በተክሉ ውስጥ የተካሄደ እድገት ነው፡፡ በርካታ ዛፎች በድምር በሌሎች ወራቶች ከሚጨምሩት በበለጠ በዚህ የሁለት ወር ተስማሚ ወቅት ብቻ ብዙ ክብ መቀነቶችን ይጨምራሉ፡፡ ነገር ግን አጉሊ መነፅርህን ወደ ተጠጋጉትና ጠቆር ወዳሉት ቀለበቶች ዘወር ብታደር፣ የምትመለከታቸው ህዋሶች/ሴሎች ትናንሽ፣ የተጨማደዱ እና የተጠቀጠቁ ግርግዳዎች ያሏቸው ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ምግብና ውኃ በሚያጥርበት እና ለተክሎቹ ተስማሚ የአየር ሁኔታ በማይኖርበት የበጋ ወራት በተክሉ ውስጥ የተካሄደ እድገት ነው፡፡ ለተክሉ አስቸጋሪ በሚሆንበት የበጋ ወራት በዛፉ ውስጥ ‹‹ሶሊድፊኬሽን›› የተባለ ሂደት ይካሄዳል፡፡ ዛፉ እነዚህን አስቸጋሪ ወቅቶ አሳልፎ ባይሆን ኖሮ ዘወትር በዙሪያው የሚያልፉትን ጎርፎች መቋቋም ባልቻለ ነበር፡፡
በመንፈሳዊ ሕይወታችንም የሚሆነው ነገር ይኸው ነው፡፡ እግዚአብሔር በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንድናልፍ ይፈቅዳል፣ ይህም የሚሆነው ሁኔታውን ለመከልከል ምንም ማድረግ ስለማይችል ሳይሆን ጠንካሮች እንደሚያደርገን ስለሚያውቅ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ማለፋችን ሊመጡ ላሉ ታላላቅ ነገሮች ያዘጋጀናል፡፡
እያንዳንዱ አትሌት ያለድካም ውጤታማ መሆን እንደማይችል ያውቃል! እግዚአብሔርን፣ አንተን ለመፈተሽ፣ ለመለጠጥ እና ለማጠንከር አስፈላጊ መጠን ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ወደ ሕይወትህ እንዲመጣ የሚፈቅድ ሰማያዊ አሰልጣኝህ አድርገህ ልትቆጥረው ትችላለህ፡፡
‹‹ወንድሞቼ ሆይ፣ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም።›› -ያዕቆብ 1፡2-4
ሐ) የእግዚአብሔር ልኡላዊነት
እግዚአብሔር ሕይወትህን እንዲቆጣጠር በመጠየቅህ፣ እርሱ ሕይወትህን እንደሚቆጣጠር ሁል ጊዜ ልታስታውስ ይገባል፡፡ የመንፈሳዊ እድገትህ ጉዳይ ካንተ በላይ እርሱን ያሳስበዋል! ለአንተ ፍፁም የሆነ እቅድ አለው (ኤርሚያስ 29፡11)፡፡ እናም አንዳንድ ጊዜ ነገሮች በተወሰነ መንገድ የተተረማመሱ ቢመስሉህም እንኳ፣ ወደ ሕይወትህ የሚመጡት ነገሮች ሁሉ በጥንቃቄ በእርሱ እየተጣሩ እንደሚመጡ ፈፅሞ እንዳትዘነጋ (ዮሐንስ 10፡28-30)፡፡
ወደ ጥርስ ሃኪም ዘንድ ስሄድ፣ ሃኪሙ በአፌ ውስጥ ምን እንደሚያደርግ የማውቀው ነገር የለም፡፡ በመሳሪያዎቹ አማካኝነት የሚያደርጋቸው ተግባራት ለኔ እንቆቅልሽ ናቸው፡፡ ነገር ግን ሃኪሙ ምን እየሆነ እንዳለ እንደሚያውቅ ስለምረዳ ዘና ብዬ ስራውን እንዲሰራ ምቹ ሁኔታን እፈጥርለታለሁ፡፡ እግዚአብሔርም በአንተ ሕይወት ውስጥ የሚሰራውን ያውቃልና ዘና በል!
ከሕይወትህ ጋር ማዛመድ፡-
በግል ‹‹ጎማህ›› ላይ ምርመራ አድርግ፡፡ ሕይወትህ በአሁኑ ሰአት ያለማቋረጥ ‹‹እየተንገጫገጨ›› ከሆነ እግዚአብሔር ላንተ ባዘጋጀው እና ጤናማ በሆነው በማጠንከሪያ ስልጠና ምክንያት ሊሆን ይችላል አልያም ጎማህ በተገቢው ሁኔታ እንዲሰራ የሚያግዙት አስፈላጊ ነገሮች ጎድለውት ሊሆን ይችላል፡፡ ክርስቶስ በሕይወትህ ‹‹ማዕከል›› ላይ ነውን? አራቱም ‹‹ሽቦዎች›› በቦታቸው አሉን? ይሰራሉስ? የጎማህ ጠርዝ ሙሉና ያልተጎዳ ስለመሆኑ በእርግጠኝነት መናገር ትችላልህ? – ይህም ማለት እግዚአብሔር እንድታደርገው ለሚያስታውስህ ነገር ታዛዥ ነህ? ይህንንስ በተግባር ትገልጣለህ?፡፡ ይህን የማታደርግ ከሆነ በጉዳዩ ላይ አንዳች እርምጃ መውሰድ እንድትችል እግዚአብሔርን በጸሎት ጠይቀው፡፡
የቃል ጥናት ጥቅስ፡-
‹‹ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።›› -ማቴዎስ 6፡33
ማጠቃለያ፡- ‹‹እንድታድግ እንድረዳህ ትፈቅድልኛለህ?›› ሲል ኢየሱስ ይጠይቅሀል፡፡