ምዕራፍ 1 – የእግዚአብሔር ቃል

ጸሎት፡-

‹‹አባት ሆይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ታላላቅ ነገሮች እመለከት ዘንድ አይኖቼን ክፈታቸው! ቃልህን ከእለት ምግቤ ይልቅ አስፈላጊዬ እንደሆነ አድርጌ እመለከት ዘንድ እርዳኝ፡፡ አሜን፡፡››

እግዚአብሔርን ማወቅ

ስለ እንግሊዝ ንግስት ለማወቅ ብትፈልግ ምንድን ነው የምታደርገው? ወደ ስፍራው በአውሮፕላን በመብረር የስብሰባ ጊዜ እንዲመቻችልህ በመጠየቅ፣ የምትፈልገውን ሁሉ ጥያቄ መጠየቅ አንዱ አማራጭ ነው፡፡ ሆኖም ብዙዎቻችን በረራው የሚጠይቀውን ዋጋ መክፈል አንችልም ወይም ከእርሷ ጋር ተገናኝቶ ማውራት ከቶ የማይቻል ይሆንብናል፡፡ በዚህ ምክንያት የሚቀረው አማራጭ ስለ እርሷ የተፃፉ መጻሕፍትን ማንበብ ብቻ ይሆናል፡፡ የትኛውን መጽሐፍ ማንበብ እንዳለብህስ በምን ታውቃለህ? አንዳንዶቹ ምንጮች ስለ ንግስቲቱ ትክክለኛ መረጃ የያዙ ሊሆኑ ቢችሉም ሌሎች ደግሞ በሃሰተኛ ጻሃፍት የተጻፉ የንግስቲቱን ክብር የሚያጎድሉ የሃሰት ሃሜቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

በመጀመሪያ የደራሲዎችን ተአማኒነት ማረጋገጥ ይኖርብሃል፡፡ ስለ ንግስቲቱ ታሪክ በጥልቀት ባጠኑ ደራሲያን የተጻፉ መጻሕፍትን ማጤን፣ በይበልጥ ደግሞ ንግስቲቱን በቅርበት በሚያውቃትና ከእርሷ ጋር በርካታ ሰአታት ባሳለፈ ሰው የተፃፈ መጽሐፍ ማጤኑ አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ‹‹ይህ መጽሐፍ በወዳጄ የተጻፈ ነው፣ በውስጡ ባለው ነገር ሁሉ እስማማለሁ፡፡›› የሚል የንግስቲቱ ማረጋገጫ የሰፈረበት መጽሐፍ ቢሆን ደግሞ ለማንበብና ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት ይበልጥ የተሻለ ይሆናል፡፡

ስለ እግዚአብሔር ማወቅ ስትፈልግስ? በቀጥታ እርሱን አግኝተህ ማነጋገር ስለማትችል የመጽሐፍ ማስረጃዎችን ለመመርመር ፊትህን ማቅናትህ አይቀሬ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ላንሳልህ? የትኛውን መጽሐፍ ለማንበብ ትወስናለህ?

እኛ ይህን እንመክርሃለን፡፡ ለዘመናት ስለ እግዚአብሔር ለተፃፉ መፃሕፍት ሁሉ ምንጭ እንደሆነ ወደተመሠከረለት መጽሐፍ – ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ዘወር እንድትል እንመክርሃለን፡፡ በእርግጥ በዚህ ጉዳይ ላይ ሙስሊሞች፣ ቡዲሂስቶች፣ ሂንዱዎችና የሌሎች እምነት ተከታዮች ላይስማሙን ይችላሉ፡፡ በክርስትና አንጻር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የእውነተኛ መረጃ ምንጭ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ለእግዚአብሔር ቅርብ በነበሩ ሰዎች የተጻፈ ነው። 2ጢሞቴዎስ 3፡16፣ እያንዳንዱ ጸሐፊ በቀጥታ በእግዚአብሔር ተመርቶ እንደጻፈ ይናገራል፡፡ በመሆኑም ስለ እግዚአብሔር ማወቅ ከፈለግህ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደተገለጠው መጽሐፍ ጎራ ማለት ይኖርብሃል፡፡

‹‹አንድ ቀን እምነት እንደ መብረቅ ካላይ መጥቶ በእኔ ላይ እንዲወርድ ስለ እምነት ጸለይኩ፡፡ የጠበኩት አልሆነም፡፡ አንድ ዕለት እንዲህ የሚለውን የሮሜ 10 መልዕክትን አነበብኩ፣ ‹እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው›፡፡ አስቀድሜ መጽሐፍ ቅዱሴን ከድኜ ስለ እምነት ጸለይኩ፡፡ አሁን መጽሐፍ ቅዱሴን ገልጬ ማጥናት ስጀምር ግን እምነት በውስጤ ማደግ ጀመረ፡፡›› -ዱዋይት ኤል. ሙዲ

የእግዚአብሔርን ቃል መመገብ

ባለፉት ምዕራፎች ውስጥ ማንነትህ ከሰውነት፣ ከነፍስና መንፈስ የተዋቀረ ባለ ሦስት ገጽ ፍጥረት እንደሆንክ ተረድተሃል፡፡ ሁላችንም ስጋችን መመገብ እንዳለበት እናውቃለን፣ ይህንንም በውስጣችን ባለው የረሃብ ስሜት እንረዳለን፡፡ ነፍሳችንና መንፈሳችንም ጭምር መመገብ እንዳለባቸው የምንረዳ ግን ጥቂቶች ነን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የመንፈስህ ምግብ ነው፡፡ ለአብነት ኢየሱስ በማቴዎስ 4፡4 ላይ፣ ‹‹ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም…›› ሲል ተናግሯል፡፡ ጴጥሮስ ደግሞ በ 1ጴጥሮስ 2፡2 ላይ እንዲህ ሲል ገልጿል፣ ‹‹…ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።››፡፡

የእግዚአብሔርን ቃል በመደበኛነት የማይመገብ ክርስቲያን መንፈስ የመነመነ፣ ደካማና በሽተኛ ይሆናል፡፡ ምናልባት በ 2ኛ የአለም ጦርነት ፍፃሜ ወቅት ከናዚ የጦር ካምፖች ነፃ የወጡ ሰዎችን ፎቶግራፍ ተመልክተህ ይሆናል፡፡ የአንዳንድ ክርስቲያኖችን መንፈስ ፎቶ ማንሳት ብንችል፣ ለረጅም ጊዜ እንግልት የደረሰባቸውን የእነዚህን ሰዎች አካላዊ ሁኔታ ይመስል ይሆናል፡፡ ይህ እንዲሆንብህ አትፍቀድ! የእግዚአብሔርን ምግብ እየተመገብክ ስለመሆንህ እርግጠኛ መሆን ይኖርብሃል!

መጽሐፍ ቅዱስ ምንድን ነው?

በግርድፉ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የታሪክ መጽሐፍ ነው ማለት እንችላለን፡፡ በእርግጥ ከታሪክ በላይ የሆነ ነገር የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ ግጥም፣ መዝሙሮች፣ ድራማ፣ ምሳሌዎች፣ ደብዳቤዎች፣ ትንቢቶች፣ ትዕዛዞች፣ ቀልድ፣ አሳዛኝ ነገር፣ ምስጢር፣ የፍቅር ታሪኮች፣ አስደንጋጭ ነገር፣ የሕግ ስምምነቶች፣ ፍልስፍና፣ የሕዝብ ቆጠራ ዳታ፣ የህይወት ታሪክ፣ ግለ ታሪክ እና ሌሎችንም ጉዳዮች በውስጡ ታገኝለህ፡፡ ጠቅለል አድርገን ስንወስደው የታሪክ መጽሐፍ ልንለው እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር ራሱን በሰዎች ታሪክ ውስጥ ያደረገበትና ከሰዎች ጋር ያደረገው ግንኙነት ትረካ መጽሐፍ ነው፡፡

ሰዎች፣ ‹‹እግዚአብሔር ራሱን ቢገልጥልን ኖሮ ማመን አይከብደንም ነበር፣›› ይላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ፍላጎት ሞልቷል፡፡ እግዚአብሔር ራሱን የገለጠላቸው የአይን ምስክሮች እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል፣ ምን ደስ እንደማያሰኘው፣ ከየት እንደመጣን፣ ወዴት እንደምንሄድ ለእኛ የቱ ጥሩ እንደሆነና የቱ ደግሞ መጥፎ እንደሆነ፣ ወዘተ ነግረውናል፡፡ እግዚአብሔር በዘመናት መካከል አስደናቂ ነገሮችን አድርጓል፡፡ ሰዎች ደግሞ እነዚህን ነገሮች እንዳንዘነጋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መዝግበውልናል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስን ማን ጻፈው? መቼ ተጻፈ?

‹‹ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ። ›› -2ጴጥሮስ 1፡20-21

 1. በጥቅሱ መሠረት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ ትንቢቶችን ምን አይነት ሰዎች ጻፏቸው?
 2. የመጽሐፍ ቅዱስ ይዘት ምንጭ ማን ነው?
 3. ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።›› -2ጢሞቴዎስ 3፡16 በጥቅሱ መሠረት፣ ‹‹በእግዚአብሔር እስትንፋስ›› ማለት ምን ማለት ይመስልሃል?

የሰው ደራሲያን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ 66 መጻሕፍትን አካቷል፡፡ 39ኙ በብሉይ ኪዳን የሚገኙ ሲሆኑ ቀሪዎቹ 27 ደግሞ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ይገኛሉ፡፡ መጻሕፍ ቅዱስ ቢያንስ 40 በሚሆኑ ጸሃፍት ተጽፏል፡፡ እያንዳንዱ በመንፈስ ቅዱስ እየተነዱ ነበር የጻፉት፡፡ እነዚህ ጸሐፊዎች የተለያየ መነሻና የሕይወት ታሪክ ያላቸው ነገስታት፣ ነቢያት፣ ፈላስፎች፣ ወታደሮች፣ ገበሬዎች፣ አሳ አጥማጆች፣ ሃኪም፣ ጠጅ አሳላፊ፣ ቀራጭ፣ አይሁድ መምህርና ሌሎች ናቸው፡፡ የኢዮብ መጽሐፍ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1850 ዓ.ዓ. የተፃፈና ከቅዱሳት መጻሕፍቱ ሁሉ ረጅም እድሜን ያስቆጠረ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በርካቶቹ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከ1500 ዓ.ዓ. በፊት የተፃፉ ናቸው፡፡ አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት (ዘፍጥረት፣ ዘጻአት፣ ዘሌዋዊያን እና ዘዳግም) በ 400 ዓ.ዓ. ገደማ ተፅፈዋል፡፡ ሁሉም የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ደግሞ በ57 ዓ.ም. እና በ96 ዓ.ም. መካከል ተፅፈዋል፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በሦስት የተለያዩ ቋንቋዎች ተፅፈዋል፡፡ እብራይስጥ የአይሁድ ቋንቋ ሲሆን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ዋነኛ ቋንቋ ነው፡፡ ግሪክኛ በክርስቶስ ዘመን ልክ እንደዛሬው እንግሊዘኛ ቋንቋ አለማቀፋዊ ቋንቋ የነበረ ሲሆን አብዛኛው የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ የተጻፉትም በዚሁ ቋንቋ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን ሁሉ የአራማይክ (አራማዊ) ቋንቋ ጥቅም ላይ የነበረ ቢሆንም ጥቂት የብሉይና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ብቻ ናቸው በዚህ ቋንቋ የተጻፉት፡፡

ጸሐፊዎቹ ከኢሲያ፣ አፍሪካና አውሮፓ አህጉሮች የተዉጣጡ ናቸው። ከጸሃፊዎቹ መካከል አንዳንዶቹ ጥልቅ ትምህርት የነበራቸው ምሁራን ሲሆኑ ሌሎች አልነበሩም፡፡ አንዳንዶቹ በተሰበረ ልብ ሲጽፉ ሌሎች ደግሞ በደስታ ጽፈውታል፡፡ አንዳንዶቹ በተድላ ይኖሩ የነበሩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በታላቅ ድህነትና ስደት ውስጥ ነበሩ፡፡ ከነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ እግዚአብሔር እየፈሩ የኖሩ ሲሆኑ ሉሎቹ ደግሞ ዘግይተው በጉልምስናቸው ለእግዚአብሔር እጅ የሰጡ ነበሩ፡፡

‹‹መጽሐፍ ቅዱስ የሁለት ወገኖች ድርሰት ሲሆን የሰው ልጅ ሁለተኛ ደረጃ ደራሲ ብቻ ነው፡፡ ዋነኛው ደራሲ እነዚህን ሰዎች ያነሳሳው፣ የመራው ያበራላቸውና የተቆጣጠራቸው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡›› – ጄ.አይ. ፓከር

የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍት አስደናቂ አንድነት

መጽሐፍ ቅዱስ ምንም እንኳ በተለያዩ ደራሲያን የተፃፈና በመጽሐፎቹ መካከልም የረጅም ጊዜ ልዩነት ቢኖርም፣ በቅዱሳት መጻሕፍቱ መካከል የሃሳብ፣ የርዕስ ጉዳይ፣ የእይታ፣ የፍልስፍና እና የአላማ አንድነት አለ፡፡ ሦስት የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ፣ ከሶስት የተለያዩ ክፍለ አለማት የመጡ፣ 40 የተለያዩ አርክቴክቶች ለ 2000 አመታት ያህል የኋይት ሃውስን ሕንፃ ሲገነቡ በአይነ ህሊናህ ለመሳል ሞክር፡፡ ምን አይነት ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችል አስብክ? መጽሐፍ ቅዱስ ግን አንድነቱን የጠበቀ መልዕክት የሚያቀርብ መጽሐፍ ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ መነሻው እግዚአብሔር መሆኑ ነው፡፡ ኤፌ.ኤፌ. ብሩስ እንደገለጸው፣ ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ደራሲያን ስራዎች መድብል አይደለም፡፡ በውስጡ መጽሐፍቱን አንድ አድርጎ የሚያስተሳስረ ውህደት አለ፡፡ መድብል መጻሕፍት ሊዋቀር ይችላል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ፈፅሞ፡፡››

የመጽሐፍ ቅዱስ መዋቅር

የመጽሐፍ ቅዱስህን ማውጫ ከፍተህ ተመልከት፡፡ 66ቱ መጻሕፍት በሁለት አብይ ክፍሎች ተከፍለው ትመለከታለህ፡፡ ምን ይባላሉ?

 1. ————
 2. ————

ብሉይ ኪዳን ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የነበረና በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የነበረውን አሮጌ ‹‹ኪዳን›› ወይም ‹‹ስምምነት›› የሚያመለክት ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን ማዕከላዊ ነገር ለመልካም ማሕበራዊ ሕይወት ቀጣይነት የሚበጁ እና በእግዚአብሔርና በሰው መካከል እንዲኖር ለሚፈለግ መልካም ግንኙነት የሚጠቅሙ ‹‹ሕጎች›› ናቸው፡፡ ሕጎቹን ይታዘዙ የነበሩ በምድር ላይ በረከትን ከማግኘት በተጨማሪ በዘላለም ሕይወት የሽልማት ባለቤቶች ይሆኑ ነበር፡፡

ከብሉይ ኪዳን ሕዝቅኤል 18፡4-9 አንብብ፡፡ ይህ ክፍል በብሉይ ኪዳን ‹‹ጻድቅ›› ማለት ምን ማለት እንደሆነ እና ጻድቅ ሰው ምን እንደሚገጥመው ነው የሚናገረው? ቁጥር 9 ላይ ‹‹— ፈፅሞ በሕይወት ይኖራል፡፡›› ይላል፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ አንድ ሰው ይህንን ‹‹ህይወት›› ይወርስ ዘንድ እንዲገልፅ የሚጠበቅበትን አምስት ወይም ስድስት ባሕሪያት ግለጽ፡፡

የብሉይ ኪዳን ሕጎችን በመታዘዝ መንግስተ ሰማይን ለመውረስ የምንችል ይመስልሃል? እስቲ ያዕቆብ 2፡10 አንብብና ምላሹን ፈልግ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ሃሳብ ጋር ይስማማል?

 1.  አንድ ሰው ሁሉንም ሕጎች ካልታዘዘ፣ የዘላለም ሕይወት አይኖረውም፡፡ በመጀመሪያው ጥቅስ መሠረት ኃጢአትን የሚሰራ ምን ይሆናል?
 2. በሁለተኛውና በሶስተኛውም ጥቅስ መሠረት ምን ያህል ሰው ኃጢአትን ሰርቷል?
 3. ይህ ቁጥር አንተን ይጨምራል?

የእግዚአብሔር የምሕረት እቅድ

እግዚአብሔር የሰው ልጅ በእርሱ የጽድቅ መለኪያ መጠን (መለኪያው ፍፁምነት እንደሆነ ልብ በል) ሊኖር እንደማይችል ስላየ የኃጥዑን ኃጢአት ‹‹የሚሸፍን›› የንፁ እንስሳ ደም እንዲሰዋ ስርዐትን አደረገ፡፡ ለብዙዎች ሁኔታው አሰቃቂ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ይህ ሁኔታ በፈጣሪያችን ላይ የሰራነው ኃጢአት አሰቃቂነትና ሰው ለሰራው ኃጢአት ሊከፍለው የሚገባውን የኃጢአት ዋጋ ግምትን ያስረዳል፡፡ የሰው ልጅ እነዚህን የሞራል ሕጎች መጠበቅ አቅቶት ሲተላለፍ ለበደሉ ሽፋን ለማግኘት መስዋዕት ያቀርብና በእርሱና በእግዚአብሔር መካከል ያለው ሕብረት ይታደስ ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን ሳይቀር ሰውየውን የሚያድነው ኃጢአትን ይቅር ሊል በሚወድ በእግዚአብሔር ላይ ያለው መታመን (እምነት) መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡

በኤርሚያስ 31፡31-34 ላይ እንደተገለፀው እግዚአብሔር አዲስ ኪዳንን ለማድረግ አስቀድሞ አቅዶ ነበር፡፡ ይህን ክፍል መጽሐፍ ቅዱስህን ክፈትና አንብበው፡፡ በቁጥር 33 መሰረት ሕጌን የት አኖርዋለሁ ነው የሚለው?

እዚህ እቅድ ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ድርሻ ምን ይመስልሃል?

‹‹አዲስ ኪዳን በብሉይ ኪዳን ውስጥ ተካቷል፣ ብሉይ ኪዳን ደግሞ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ተብራርቷል፡፡›› – ሜሪል ኤፍ. አንገር

አዲስ ኪዳን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞተና ከተነሳ በኋላ የተፃፈ ነው፡፡ የኢየሱስ ሞት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል አዲስ ስምምነትን በመፍጠሩ ምክንያት አዲስ ኪዳን ሊሰኝ በቅቷል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ፍፁምና ንፁህ መስዋዕት ነው፡፡ የእንስሳት መስዋዕት ኃጢአትን ከእግዚአብሔር አይን ይሸፍን የነበረ ሲሆን የኢየሱስ ደም ግን ኃጢአትን ያስወግዳል፤ እርሱ የኃጢአታችንን ዋጋ ከፍሏል፡፡ በዚህ አዲስ ስምምነት መሠረት አሁን ሙሉ በሙሉ ልንታዘዛቸው ከሚገቡን እነዚያ ሕጎች በታች መሆናችን ቀርቷል፡፡ አሁን በዚህ ፈንታ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በእኛ ውስጥ በማደር መልካምን እንድናደርግ ይረዳናል፡፡ አሁን በእግዚአብሔር ፊት ፃድቅ የሚያደርገን ሕግን ለመፈጸም የምናደርገው ጥረት ሳይሆን በክርስቶስ ላያ ያለን እምነት ነው፡፡

 1.  ሮሜ 8፡1-4 አንብብ፡፡ በክርስቶስ ነህ? ክርስቶስን ተቀብለህ ከሆነ በክርስቶስ ነህ፡፡ በክርስቶስ ከሆንህ ቁጥር 1 ምን የለብህም ይላል?
 2. በ ቁጥር 2 መሠረት፣ ምንድነው ‹‹ከኃጢአትና ሞት ሕግ›› ነፃ ያወጣህ?
 3. በ ቁጥር 3 ላይ ከሥጋ የተነሣ የብሉይ ኪዳን ሕግ ‹‹ደካማ›› እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ይህ ማለት ምን ማለት ነው?
 4. በ ቁጥር 4 መሠረት፣ ምን ስናደርግ ነው የሕግ ትእዛዝ የሚፈጸመው?

የብሉይ ኪዳን መዋቅር

ብሉይ ኪዳን ከ ‹‹ሕግና ትዕዛዛት›› ያለፈ ዛሬም ድረስ ልንጠቀምባቸው የምንችላቸውን በርካታ ነገሮች ይዟል፡፡ ከብሉይ ኪዳን ስለ እግዚአብሔር ማንነትና ባሕሪይ፣ ከሕዝቡ ምን እንደሚጠብቅ፣ ለወደፊት ምን እንዳሰበልን፣ እና እንዴት ልናመልከው እንደምንችል ልንማር እንችላለን፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ ማውጫህን ዳግመኛ ተመልከት፡፡ የብሉይ ኪዳንን 39 መጻሐፍ የመከፋፈያ በርካታ መንገዶች ቢኖሩም አንድ የተለመደ አከፋፈል አለ፡፡ ምን አልባት ይህን አከፋፈል በመጽሐፍ ቅዱስህ ማውጫ ላይ ልታኖረው ትችላለህ፡፡

የታሪክ መጻሐፍት

ዘፍጥረት፣ ዘጻአት፣ ዘሌዋዊያን፣ ዘኁልቁ፣ ዘዳግም፣ ኢያሱ፣ መሳፍንት፣ ሩት፣ 1ኛ እና 2ኛ ሳሙኤል፣ 1ኛ እና 2ኛ ነገስት፣ 1ኛ እና 2ኛ ዜና፣ ዕዝራ፣ ነህምያ፣ እና አስቴር

የግጥም መጻሐፍት 

ኢዮብ፣ መዝሙረ ዳዊት፣ ምሳሌ፣ መክብብ፣ እና ማኃልየ ማኅልየ ዘሰለሞን

የትንቢት መጻሐፍት

ኢሳይያስ፣ ኤርሚያስ፣ ሰቆቃው ኤርሚያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ዳንኤል፣ ሆሴዕ፣ ኢዩኤል፣ አሞጽ፣ አብድዩ፣ ዮናስ፣ ሚኪያስ፣ ናሆም፣ ዕንባቆም፣ ሶፎንያስ፣ ሐጌ፣ ዘካርያስ፣ እና ሚልክያስ

የታሪክ መጻሕፍቱ ሰለ ሰነ ፍጥረት፣ ሰለ ሰው ልጅ በምድር ገጽ ላይ መበተን እና ስለ የጥፋት ውሃ ይተርኩና የትኩረት አቅጣጫውን በአንድ አብርሃም በተባለ ታማኝ ሰው ላይ ያነጣጥራሉ፡፡ በመቀጠልም እነዚህ መጻሐፍት በደቡብ ባቢሎን (በአሁኑ ሰአት ኢራቅ እየተባለ) ከሚጠራው ስፍራ የአብርሃም ትንሽ ቤተሰብ ተነስቶ ለብዙ ዘመናት በግብጽ ባርነት መሰንበቱን፣ በሙሴ አማካኝነት በድንቅና ተአምራት ከግብጽ መውጣታቸውን፣ በኢያሱ አማካኝነት የፍልስጤም ምድርን መውረሳቸውን እና በመጨረሻም በንጉሥ ዳዊት አማካኝነት በምድር ላይ ታላቅ መንግስት በመሆን መጽናታቸውን ያወሳሉ፡፡ በመቀጠልም መሪዎቿ አምልኮተ እግዚአብሔርን ትተው እንግዳ አማልዕክት በማምለካቸው እና የገዛ ፈቃዳቸውን በመከተላቸው እስራኤል ጥቂት መቶ አመታት በእግዚአብሔር ፍርድ ስር እንደ ወደቀች እናነባለን፡፡

የግጥም መጻሕፍቱ በዋናነት በእስራኤል ‹‹ወርቃማ ዘመን›› የተፃፉ ሲሆኑ እግዚብሔርን በቅርበት የሚያውቁት ሰዎች ጥልቅ ጥበብ ነጸብራቅ ነው፡፤ አብዛኞቹ እነዚህ መጻሕፍትን በእግዚብሔር ዘንድ ‹‹እንደልቤ የሆነ ሰው›› (ሐዋሪያት ሥራ 13፡22) በተባለው ንጉሥ ዳዊት እና መጽሐፍ ቅዱስ፣ ‹‹ከሰውም ሁሉ ይልቅ…ጥበበኛ ነበር›› (1ነገሥት 4፡31) ባለው በዳዊት ልጅ በሰለሞን የተጻፉ ናቸው፡፡

የትንቢት መጻሕፍቱ በእስራኤል ‹‹የጨለማ ዘመን›› ማለትም የእስራኤል መንግስት በሰለሞን ልጅ በሮብአም ንግስና ወቅት ለሁለት በተከፈለችበት ዘመን የተፃፉ ናቸው፡፡ መንግስታቱም እስራኤልና ይሁዳ ተባሉ፡፡ ነቢያቱ ለእስራኤልና ለተቀረው አለም በቅርብና በሩቅ የሚፈጸሙ ትንቢቶችን ገለጡ፡፡ የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ላይ ማመጽ በመቀጠላቸው በእስራኤል መንግስት ይኖሩ የነበሩ አስሩ ነገዶች በአሶራዊያን ግዞት ስር በመውደቅ በዙሪያቸው ያለው ሕዝብ ባህል ሰለባዎች ሆኑ፡፡ በይሁዳ መንግስት የነበሩ ሁለቱ ነገዶች ደግሞ ኃላ ላይ በባቢሎን ቅኝ ስር በመውደቅ ልግዞትና ባርነት ወደ ባቢሎን ተጋዙ፡፡ አንዳንዶቹ የትንቢት መጻሐፍት ከግዞት በፊት ጥቂቶቹ ደግሞ በግዞቱ ወቅት ሌሎቹ ደግሞ ከ 70 አመት ግዞት በኃላ የተጻፉ ናቸው፡፡

የአዲስ ኪዳን መዋቅር

27ቱን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍ ለመከፋፈል ብዙ አማራጮች አሉ፡፡ የሚከተለው አከፋፈል በስፋት የሚታወቀው ነው፡፤ እነዚህ መጻሐፍት ታሪኮችን፣ ደብዳቤዎችንና ስለመጨረሻው ዘመን ሰፊ ዘገባን ያካትታሉ፡፡ እያንዳንዱ መጽሐፍ ስለ ክርስቶስና ስለ ዘላለማዊ መንግስቱ ያወሳሉ፡፡

 1. የታሪክ መጻሕፍት

ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ፣ ዮሐንስ፣ የሐዋሪያት ሥራ

 1. መልዕክቶች (ደብዳቤዎች)

ሮሜ፣ 1 እና 2ኛ ቆሮንቶስ፣ ገላቲያ፣ ኤፌሶን፣ ፊሊፕሲዮስ፣ ቆላሲያስ፣ 1ኛ እና 2ኛ ተሰሎንቄ፣ ዕብራዊያን፣ 1ኛ እና 2ኛ ጢሞቴዎስ፣ ቲቶ፣ ፊሊሞና፣ ያዕቆብ፣ 1ኛ እና 2ኛ ጴጥሮስ፣ 1ኛ፣2ኛ እና 3ኛ ዮሐንስ፣ ይሁዳ

 1. ራዕይ

የታሪክ መጻሕፍቱ ከኢየሱስ ጋር አብረው በነበሩ ሰዎች የተፃፈ ሲሆን ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅትና ከትንሳኤው በኋላ በነበሩ አመታቶች የሆነውን ሁኔታ ይተርካሉ፡፡ ማቴዎስ ከኢየሱስ 12 ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ ሲሆን ቀራጭ ነበር፡፡ ማርቆስና ጴጥሮስ ለብዙ አመታት የቅርብ ወዳጆች ስለነበሩ የማርቆስ ወንጌል፣ ጴጥሮስ ለማርቆስ በቃል ያጻፈው ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ ማርቆስ የበርናባስ የአጎት ልጅ ሲሆን በጳውሎስ የመጨረሻ የአገልግሎት ዘመን ወቅት አብሮት የሚያገለግል ሰው ነበር፡፡

ሉቃስ ሃኪም ሲሆን ከጳውሎስ ጋር አብሮ ያገለገለ እና የማርቆስ የልብ ወዳጅ ነበር፡፡ መጽሐፉን ሲፅፍ በጥንቃቄ ሁሉን ከመረመረና በርካታ የአይን ምስክሮችን ከጠየቀ በኋላ ነበር (ሉቃስ 1፡1-4)፡፡ ሉቃስ ከዚህ በተጨማሪ ስለ ቀደመቺቱ ቤተ ክርስቲያን ግብር (ሰራ) የሚያትተውን የሐዋሪያት ሥራን ፅፏል፡፡ ዮሐንስም ከ 12ቱ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ ነበር፡፡ ‹‹ኢየሱስ ይወደው የነበረው›› ደቀ መዝሙር ነበር፡፡ ይህ አባባል በመካከላቸው የነበረውን ቅርበት ይገልፃል፡፡

መልዕክቶች በቤተ ክርስቲያን ‹‹አእማዳት›› የተፃፉ ደብዳቤዎ ናቸው፡፡ እነዚህ ደብዳቤዎች ቤተ ክርስቲያን በከፍተኛ ፍጥነት በምታድግበት ወቅት፣ እነዚህ በመንፈስ ቅዱስ የሚነዱ መሪዎች ከክርስቶስ ተከታዮች ጋር ለመነጋገር የተጠቀሙባቸውን ጠቃሚ መረጃዎችን ይዘዋል – የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ኢ-ሜይል ልንላቸው እንችላለን፡፡ ጳውሎስ አክራሪ ፈሪሳዊ ነበር፡፡ ፈሪሳዊያን ክርስትናን ከ ‹‹ውጉዝ ዶክትሪኑ››ጋር ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ምለው የተገዘቱ አይሁድ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከሞት የተነሳውን ኢየሱስ ፊት ለፊት ከተገናኘው በኋላ ታላቅ ተፅእኖ የሚፈጥር የኢየሱስ ተከታይ ሆኖ አረፈው፡፡ ጴጥሮስና ዮሐንስ ሁለቱ የኢየሱስ የቅርብ ደቀ መዛሙርት ሲሆኑ ያዕቆብና ይሁዳ ደግሞ የማርያምና የዮሴፍ ልጆች የኢየሱስ ግማሽ ወንድሞች ናቸው፡፡

The Apocalypse፣ በአንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ላይ ‹‹የቅዱስ ዮሐንስ ዘመለኮት ራዕይ›› ወይም በሌሎች ‹‹የኢየሱስ ክርስቶ ራዕይ›› እየተባለ የሚጠራው መጽሐፍ በክፍፍሉ እራሱን የቻለ ስፍራ ይይዛል፡፡ ራዕይ ምናባዊ በሆነ ከባድ መልዕክቶች የተሞላ ምስጢራዊ መጽሐፍ ነው፡፡ ሰለ ምን የተፃፈ እንደሆነ በርካታ አስተያየቶች ቢሮሩም ስለ መጨረሻው ዘመንና ክርስቶስ በምድር ላይ ስለ ሚነግስበት ጊዜ በርካታ ትንቢት ምልከታዎችን መያዙ እርግጥ ነው፡፡ እነዚህ ትንቢቶች በሕዝቅኤል፣ ዳንኤል እና በሌሎች በርካታ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ እንዲሁም ኢየሱስ ራሱ በቃሉ በማቴዎስ 24 እና 25 ላይ ከተናገራቸው ትንቢቶች ጋር አብረው የሚሄዱ ናቸው፡፡ በሦስቱም የአዲስ ኪዳን ክፍፍል ስር ያሉ መጻሐፍቶችን ዮሐንስ መጻፉን ልብ ይሉዋል፡፡

ኢየሱስ ስለ ቅዱሳት መጻሕፍቱ የተናገረውን ከ ማቴዎስ 22፡29፣ ሉቃስ 24፡25 እና ዮሐንስ 5፡39 ካነበብክ በኃላ በራስህ አባባል ግለጽ፡፡

መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ጠቀሜታ

የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብና በሕይወት ላይ ተግባራዊ የማድረግ ጠቀሜታዎችን ይገልፃሉ፡፡ ከጥቅሶቹ የተገነዘብከውን አብራራ፡፡

 1. ኢያሱ 1፡8
 2. መዝሙር 19፡7-8
 3. መዝሙር 37፡31
 4. ዮሐንስ 15፡3፤17፡17
 5. 2 ጢሞቴዎስ 3፡16-17
 6. 1 ጴጥሮስ 2፡2-3
 1. መስማት

ሉቃስ 6፡45-49 አንብብ፡፡

 • በዚህ ክፍል ላይ ኢየሱስ አንድ ሰው የእግዚአብሔርን ቃል መስማት እንዳለበት አመልክቷል፡፡ ከመስማት በተጨማሪ ምን የተቀመጠ ነገር አለ?
 • እነዚህን ትዕዛዛት የሚተላለፍን ሰው ኢየሱስ ከምን ጋር ነው ያመሳሰለው?
 • በቋሚነት የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት እርግጠኛ የምትሆንባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው?
 1. ማንበብ

ዘዳግም 17፡18-20 አንብብ፡፡

 •  በእስራኤል ላይ የሚነግሱ ነገስታት ሊከተሉት የሚገባቸው ሕግ ነው፡፡ ንጉሱ ይህን ሕግ (የመጀመሪያዎቹ 5ቱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፎች) ምን ያህል ጊዜ እንዲያነብ ነው የሚናገረው?
 • ይህን ማድረጉ በንጉሡ ላይ ምን ያመጣል?
 • የእግዚአብሔርን ቃል ሳታቋርጥ ማንበብ በአንተ ሕይወት ላይ ምን አይነት ለውጥ የሚያመጣ ይመስልሃል?
 • መጽሐፍ ቅዱስን ሳታቋርጥ ለማንበብ ምን ማድረግ ያልብህ ይመስልሃል?
 1. ማጥናት

መጽሐፍ ቅዱስን ‹‹ማጥናት›› ከማንበብ የበለጠ ልዩ ትኩረትን የሚጠይቅ ድርጊት ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል በሕይወትህ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዱህ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ የማጥኛ ዘዴዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በታች ለመነሻ የሚሆንህ አንድ ዘዴ ቀርቧል፡፡ ይህ የማጥኛ አቀራረብ ያስገረመኝ፣ የወደድኩት፣ የማደርገው፣ የምጠይቀው በመባል ይታወቃል፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድ ክፍል መርጠህ ካነበብክ በኋላ እነዚህን አራት ነገሮች ራስህን ጠይቅ፡-

 1. ያስገረመኝ! – በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ያስደነቀኝ ነገር፡-
 2. የወደድኩት – በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የወደድኩት ጥቅስ፡-
 3. የማደርገው – ምዕራፉን ካነበብኩ በኋላ ልተገብረው የሚገባኝ ነገር፡-
 4. የምጠይቀው – ምዕራፉን ሳነብ ወደ አእምሮዬ የመጣ ጥያቄ፡-

መዝሙር 1 አንብብና ያስገረመኝ/የወደድኩት/የማደርገው/የምጠይቀው/ አጠና አቀራረብን ተግባራዊ አድርግ፡፡

 1. በቃል መያዝ

የምዘና ባለሙያዎች ምርምር እንደሚያሳየው፣ አንድ ሰው ከ 24 ሰአት በኋላ የሚያስታውሰው ነገር ከሰማው 5%፣ ካጠናው 35% ገደማ ሲሆን በቃል ከያዘው ውስጥ ግን 100% ነው፡፡ ካነበብከው የእግዚአብሔ ቃል ውስጥ የተወሰነውን ክፍል በቃል ይዘህ ‹‹በልብህ ስለ መሸሸግ ›› ይህ ምርምር ምን ያስተምርሃል?

መዝሙር 119:11 አንብብና የተገነዘበከውን አብራራ “አንተን እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ።”

 1. ማሰላሰል

መጽሐፍ ቅዱሳዊው ማሰላሰል፣ ‹‹በግል ጊዜ በመውሰድ የተወሰኑ መንፈሳዊ እውነታዎች ወይም ምስጢሮችን በጥልቀት ማሰብ፣ በውስጥ መጸለይና በወደፊት ባህሪና ድርጊት ላይ ለውጥ ለማምጣት ፈቃድን የማስገዛት ውሳኔ ውስጥ መግባትን የሚያካትት አምልኮ ነው፡፡›› (አንገር የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት)፡፡

አውራ ጣታችን ከቀሪዎቹ አራት ጣቶቻችን ጋር እርስ በእርስ እንደተያያዘ ሁሉ የምንሰማውን፣ የምናነበውን፣ የምናጠናውን እና በቃል የምንይዘውን የእግዚአብሔር ቃል ማሰላሰል ይኖርብናል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በወንፊት ውስጥ እንደሚያልፍ ውኃ በእኛ ውስ እንዲልፍ መፍቀድ የለብንም! የእግዚብሔርን ቃል ስናሰላስል እንይዘዋለን፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች እንመረምረዋለን፣ በጥልቀት እናስበዋለን። ይህም መንፈስ ቅዱስ ቃሉን በሕይወታችን ተግባራዊ እንዲያደርግ ሁኔታዎችን ያመቻችለታል፡፡

ከሕይወት ጋር ማዛመድ፡-

ከዛሬ ——– ቀን ጀምሮ፣ ለመጪዎቹ ———– ሣምንታት ያህል መጽሐፍ ቅዱስን በሣምንት ለ ————— ቀናት ያህል ከ ———— ደቂቃ ላላነሰ ጊዜ ለማጥናት ራሴን አዘጋጃለሁ፡፡ እንዲያበረታታኝና የሚረኖሩኝን ጥያቄዎች በመመለስ እንዲያግዘኝ ——— (እከሌን) እጠይቀዋለሁ፡፡

የቃል ጥናት ጥቅስ፡-

የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል። –2 ጢሞቴዎስ 3፡16-17

ማጠቃለያ፡-

‹‹ቃሌን ትመገባለህ?›› ሲል ኢየሱስ ጥያቄ ያቀርብልሃል፡፡

ምዕራፍ 8ትን ያጥኑ

2 thoughts on “ምዕራፍ 1 – የእግዚአብሔር ቃል”

Leave a Reply

%d