ምዕራፍ 11 – የጊዜ አጠቃቀም

ጸሎት፡

‹‹አባት ሆይ፣ መንግስትህን በምድር ላይ ለማስፋት፣ ኃላፊነቶቼን በአግባቡ ለመወጣት፣ ሌሎችን ለማገልገልና አንተን ለማክበር ሰአቶቼንና ቀናቶቼን በተሻለ መንገድ መጠቀም እንድችል አይኖቼን ክፈት፡፡ አንተንና የፈጠርከውን ለማድነቅ የጥሞና እና የእረፍት ጊዜዎችን እሻለሁ፡፡ በሌሎች ጊዜያቶቼ ደግሞ ትጉህ እና ዉጤታማ አድርገኝ! አሜን፡፡››

ስለ ጊዜ አጠቃቀም ማወቅ ለምን ያስፈልጋል?

የትምህርታዊው ጉባኤ መሪ፣ ድራማዊ በሆነ አካሄድ በረጅሙ እየተራመደ ወደ ክፍሉ ገባ፡፡ በእጁ አንድ የወረቀት ከረጢት እና አንድ ጋሎን የሚይዝ የመስታወት ገንቦ ይዟል፡፡ ታዳሚው ሁሉ ምን እንደሚሆን በጉጉት ይጠባበቅ ነበር፡፡

የጉባኤው መሪ ፈገግ ብሎ፣ ‹‹ዛሬ እዚህ የተሰበሰብነው ስለ ጊዜ አጠቃቀም ለመነጋገር ነው፡፡ እናም ይሄ የመስተዋት ገንቦ ዛሬ ለሕይወታችሁ እጅግ ጠቃሚ ትምህርት ያስተምራችኋል፡፡››

አሁን ታዳሚው በሙሉ በፍፁም ጉጉትና መመሰጥ መከታተል ጀምሯል፡፡

“ልብ ብላችሁ ይህን የመስታዋት ገንቦ ተመለከቱ፡፡ ይህ ገንቦ በአየር የተሞላ እንደሆነ ሁላችሁም ታውቃላችሁ ብዬ አስባልሁ። አየሩን ለጌዜው እንተውና፣ ይህ ገንቦ ባዶ ነው ወይስ ሙሉ?” ሲል ጉባኤውን ጠየቀ።

‹‹ባዶ፣›› ሲሉ በርካቶቹ መለሱ፡፡

‹‹ትክክል፡፡ ስለዚህ አሁን መሙላት እንጀምር፡፡›› ከኦትሮንሱ ጀርባ በመሄድ የተለያየ መጠን ያላቸውን ኮረቶች የያዘ ሳጥን አወጣ፡፡ ከዛም ኮረቱን በመስታዋት ገንቦ ውስጥ በጥንቃቄ መጨመር ጀመረ፣ አስተካከለ፣ ደግሞ አስተካከለ፣ እያወጣ ደግሞ አስገባ፡፡ ይህን አድርጎ ሲያበቃ፣ ወደ ታዳሚው ተመልክቶ፣ ‹‹በቃ! አሁን ገንቦው ሞልቷል አይደል?›› ሲል ጠየቀ፡፡

ከ ታዳሚዎቹ መካከል አንዱ፣ ‹‹በትልልቆቹ ኮረቶች መሃል መሰግሰግ የሚችሉ ሌሎች አነስ ያሉ ኮረቶች ካሉህ ገንቦው አሁንም ክፍት ቦታዎች አሉት፡፡›› ሲል መለሰ፡፡

‹‹እጅግ በጣም ጥሩ ነገር ብለሃል!›› ሲል የትምህርታዊው ጉባኤ መሪ ተናገረ፡፡ ከዛም ከአትሮንሱ ስር ያስቀመጠውን አነስ ያሉ ኮረቶች የያዘ ከረጢት አውጥሮ በመስታወት ገንቦ ውስጥ መጨመር ጀመረ፡፡ አነስተኛ ኮረቶቹ መጀመሪያ በገቡት ትልልቅ ኮረቶች መካከል የነበሩትን ክፍት ቦታዎች ሞሉ፡፡

‹‹አሁን ገንቦውን ሞላነው፣ አይደል?›› ሲል ከመናገሩ፣ አንዲት ወጣት ሴት ብድግ ብላ፣ ‹‹ገንቦው አሁንም ጥቂት አሸዋ የሚይዝ ቦታ ይኖረዋል ብዬ አስባለው —›› አለች፡፡

‹‹ጥሩ ሃሳብ ነው!›› የጉባኤው መሪ እንደ ቀድሞው ከአትሮኑስ ስር ያስቀመጠውን ከመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ያነሱ መጠን ያላቸውን ኮረት የያዘ ከረጢት አወጣ፣ የአሁኑ ከረጢትደቃቅ አሸዋ የያዘ ነበር፡፡ አሸዎውን በገንቦው ውስጥ ሲጨምር በኮረቶቹ መካከል የነበረውን ቦታ ያዘ፡፡

‹‹እሺ! አሁን በቃን፤አይደል? ሁሉም ስፍራ በኮረቶች ተይዟል!›› አለ የጉባኤው መሪ ወደ ታዳሚው እየተመለከተ። ‹‹ቆይ አንድ ጊዜ፣ አለ ከታዳሚዎቹ መካከል አንዱ፡፡ ‹‹ጥቂት ውሃ ብንጨምርበትስ?››

‹‹ይህን ሃሳብ ታመጣለህ ብዬ አልገመተኩም ነበር፣›› አለ የጉባኤው መሪ ፈገግ ብሎ፡፡ በጆግ ውሃ ካዘጋጀ በኋላ ቀስ ብሎ በመስተዋቱ ገንቦ ውስጥ መጨመር ጀመረ፡፡ ውሃው ቀስ በቀስ በኮረቶቹ መሃል አልፎ ገንቦው ስር ደረሰ፡፡ በመጨረሻም እስከ አፉ ጢም አለ፡፡

‹‹አሁንስ ልንሞላው የምንችለው ክፍት ቦታ አለ?›› ሲል የጉባኤው መሪ ለታዳሚዎቹ ጥያቄ አቀረበ፡፡ ማንም ምላሽ አልሰጠም፡፡ ‹‹እንግዳው፣ ከዚህ ገለጻ ስለ ጊዜ አጠቃቀም ምን ተማራችሁ?››

ከታዳሚው መካከል አንድ ሰው ልክ እንደ ተማሪ እጆቹን ወደላይ አውጥቶ በጉጉት፣ ‹‹አጥብቀህ የምታስብ እና ፈጠራ ያለህ ከሆንክ፣ የጊዜ ሰሌዳህ እንደሚይዝልህ ከምታስበው በላይ ሌሎች ልታደርጋቸው የሚገቡህን ነገሮች ሊይዝልህ እንደሚችል ተምሬአልው!›› ሲል መለሰ፡፡

‹‹ፈፅሞ!›› ሲል የጉባኤው መሪ መለሰ፣ ‹‹የዚህ ገለጻ ዋነኛ ነጥብ ይህ አይደለም፡፡ ያልከውን ሃሳብ ከገለጻው መገንዘብ ይቻል ይሆናል ግን ከዚህ የተሻለ ነጥብ አለ፡፡››

ሁሉም በማሰብ ፀጥ አሉ፡፡ በመጨረሻም የጉባኤው መሪ፣ ‹‹የገለጻው ዋና ነጥብ ይህ ነው፡- ‹‹ትልልቁን ኮረት ለመጨመር ከፈለጋችሁ፣ መጨመር ያለባችሁ መጀመሪያ ላይ ነው!››

ይህ ትምህርት በሕይወትህ ያሉ ‹‹ትላልቅ ኮረቶችን›› እንድትለይ እና መጀመሪያ ላይ መግባታቸው እንድታረጋግጥ ይረዳሃል፡፡ ከዛም አነስ ያሉት ጠጠሮች፣ አሸዋውና ውሃው ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት እንደሚከተሉ ከገለጻው እንረዳለን።

‹‹ሰአትን በአግባቡ ለመጠቀም መጀመሪያ ማድረግ ያለብህ፣ ጠቃሚ የሆነውን ካልሆነው መለየት ነው፡፡ ልንቀበለው የሚከብደን ነገር ቢሆንም ሁሉን ማድረግ እንደማንችል ማወቅ አንዳንድ ጊዜ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡›› – ሮን ፍራይ

እንዴት ይህ ርዕስ ‹‹ቅዱስ›› ከሆኑት እንደ ጸሎት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እና በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ከሚሉት ርዕሶች ተርታ ሊሰለፍ ቻለ? ምላሹ ቀላል ነው፡፡ እንደ ክርስቲያን ከኢየሱስ ጋር መጓዝ ጊዜ እንደሚጠይቅ ሳታስተውል የቀረህ አይመስለኝም፡፡ ኢየሱስን በተቀበልህ ጊዜ፣ በተለያዩ ነገሮች በተጣበበው የጊዜ ሰሌዳህ ውስጥ – ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ለመገኘት፣ ለመማር፣ ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት ለማድረግ- የሚሆን ተጨማሪ ጊዜ መፈለግ ነበረብህ፡፡ ስለ አንተ ባላውቅም በዚህ በ 21ኛው ክፍለ ዘመን የሚኖሩ በርካታ ሰዎች የየዕለት የጊዜ ሰሌዳቸው በፕሮግራሞች ተጣቧል፡፡

ዴቪድ ዳውሰን፣ የ ‘Equipping The saints’ አገልግሎት መስራች እንዲህ አለ፡- ‹‹አስቸጋሪው ነገር የጊዜ እጦት ሳይሆን ባለን ጊዜ የምንሰራው ነገር ነው፡፡ ጊዜን ማጠራቀም፣ መግዛት፣ መለዋወጥ ሆነ ወደ ኃላ መመለስ ስለማንችል መቆጣጣር መማር ይኖርብናል፡፡ ጊዜን በአግባቡ ማስተዳደር ካልቻልን ውጤታማ ሕይወት ልንመራ አንችልም፡፡

የሃላፊነት ሹመት (ታማኝ መጋቢነት)

የ ‹‹መጋቢ›› ብያኔ (ትርጉም)፡- በሃላፊነት የተሰጠን ነገር፣ በጥንቃቄና በሃላፊነት መንፈስ ማስተዳደርን ያመለክታል፡፡ 1ቆሮንቶስ 3፡11-15 አንብብ፡፡ ይህ ክፍል ወደፊት ስለሚመጣው ‹‹የክርስቶስ የፍርድ ወንበር›› ትዕይንት ያወራል፡፡ ይህ ጊዜና ቦታ የእግዚአብሔር ወንድና ሴት ልጆች በምድር ላይ ስላደረጉት ሥራና አኗኗራቸው በእግዚአብሔር ፊት የሚጠየቁበት ነው፡፡ በዚህ የፍርድ ወቅት የእያንዳንዱ ‹‹ስራህ›› ዋጋ ‹‹ይፈተናል››፡፡

ማስታወሻ፡- ይህ ስፍራ መንግስተ ሰማይ ወይም ገሃነም ለመግባት ውሳኔ የሚሰጥበት አይደለም፡፡ ይህ ውሳኔ አስቀድሞ ሆኗል፡፡ በክርስቶ ኢየሱስ ላይ ባለህ እምነት ምክንያት የዘላለም ሕይወትን አግኝተሃል፡፡ የዚህ ቀን ፍርድ በእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግስት ውስጥ የሚኖርህን የሽልማት መጠን፣ መብትና ሃላፊነት ይወስናል፡፡

  1. በ1ቆሮንቶስ 3፡11-15 መሠረት በሕይወትህ ያለው መሠረት ማን ነው?
  2. በዛ መሠረት ላይ፣ ከሁለት የተለያዩ ነገሮች ሥራ ትሰራለህ፡፡ ‹‹ወርቅ፣ ብር እና የከበረ ድንጋይ›› ምን የሚያመለክቱ ይመስልሃል?
  3. ‹‹እንጨት፣ ሣር፣ ወይም አገዳ›› ምን የሚያመለክቱ ይመስልሃል?
  4. የጊዜ አጠቃቀምህን በተመለከተ ራስህን የትኛው ደረጃ ላይ ታስቀምጣል?
  5. ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት መካከል በሰአት አስተዳደርህ ውስጥ በጣም አስቸጋሪ የሆነብህ የቱ ነው? [3 ብቻ ምረጥ!]
  • አስቀድሞ ማቀድ
  • ነገሮችን እንደ አስፈላጊነታቸው በቅድመ ተከተል ማስቀመጥ
  • የትኩረት መበታተን
  • በእቅዴ አለመጽናት
  • የትጋት ማነስ
  • ማዘግየት (ማርፈድ)
  • ብኩንነት
  • እግዚአብሔርን ከእቅዴ ማስወጣት
  • ሌሎች? ————————-

ውሱን የሆነ ጊዜ በሃላፊነት (በአደራ) ተሰጥቶሃል፡፡ ይህንን ውሱን ጊዜህን -በወርቅ፣ ብር እና የከበረ ድንጋይ- አልያም -በእንጨት፣ሣር እና አገዳ- መለወጥ አለመለወጥ የአንተ ድርሻ ነው!

‹‹ትላልቆቹ ኮረቶች›› – በሕይወታችን ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ያመለክታሉ

እነዚህን ትላልቅ ኮረቶች በሕይወትህ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ሊደረደሩ እንደሚገባቸው ታምን ይሆናል፤ ነገር ግን ብዙ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ትላልቅ ኮረቶች ምን እንደሆኑ ለማወቅ ግራ ሲጋቡ ይስተዋላል፡፡ እንደ ክርስቲያን የእኛ ቅድሚያዎች በእግዚአብሔር ቅድሚያዎች እንዲዋጡ እንሻለን። በመሆኑም ይህንን ግራ መጋባት ለመፍታት መጀመሪያ የእግዚአብሔር ቅድሚያዎችን ልናውቅ ይገባል፡፡

  • እግዚአብሔር ቅድሚያ እንድትሰጣቸው የሚፈልጋቸው ነገሮች ምን ይመስሉሃል?

የአንተና የእግዚአብሔር ቅድሚያዎች ንፅፅር

የጊዜ አጠቃቀማችንን ከእግዚአብሔር ቅድሚያዎች አንጻር ማየት ተገቢ ነው፡፡ እያንዳንዳችን በሣምንት 168 ሰአቶች ተሰጥተውናል፡፤ እንዴት ነው የምንጠቀማቸው? ሳምንታዊ ተግባሮችህን በመገምገም ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት ተግባራት በሣምንት ምን ያህል ሰአት እንደምትፈጅ በመመዝገብ አስላ፡፡

የቅድሚያዎች መገምገሚያ መልመጃ፡

– ለመተኛት

– ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት (ለመዘጋጀትና ለመሰባሰብ)

– ለመብላት

– የቤት ውስጥ ሥራዎችን ለመስራት

– ለመልበስ፣ ጢም ለመላጨት፣ ለመታጠብ ለመስከታከል፣ ወዘተ

– ከቤተሰብ ጋር ለማሳለፍ

– ከቤት ወደ ሥራ ለመጓዝ

– ሌሎችን ሰዎች ለመጎብኘት

– የክፍል እና የቤት ሥራ ለመስራት

– ለመዝናናት፤ የግል ጊዜ

– የግልና የጋራ ጸሎት ለማድረግ

– ለሰውነት ማጎልመሻ ስፖርት

– ከቅዱሳን ጋር ሕብረት ለማድረግ

– የመስሪያ ቤት ሥራ ለመስራት

– ለማገልገል

– ቤት ለመጠገን፣ ለማስተካከል

– ለማንበብ (መጻሕፍት፣መፅሔቶች)

በሣምንት ውስጥ ያለህ አጠቃላይ ሰአት (168) – የተጠቀምክበት ሰአት (—–) = ‹‹የባከነ ጊዜ›› (————–)

ምዘናውን መስራት፡-

እዚህ ላይ ሁለት ልታጤናቸው የሚገቡ ቁም ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው – ‹‹የባከኑ ጊዜያቶችህ›› ነው፡፡ ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ – ከላይ የዘረዘርካቸውን ተግባራት አስቀድሞ ከዘረዘርካቸው ‹የእግዚአብሔር ቅድሚያዎች ጋር ማነጻጸር ነው፡፡ ምን ያህሎቹ የአንተ ቅድሚያዎች ናቸው ከእግዚአብሔር ቅድሚያዎች ጋር አብረው የሚሄዱት? (በአንዱ ምላሽህ ላይ አክብብ) 0% 10% 20% 30% 40% 50% 60% 70% 80% 90% 100%።

ማንኛውም ክርስቲያን በመጀመሪያ፣ ህጸፅ ከሚበዛበት የቅድሚያ ዝርዝር እንደሚነሳ ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ለእኛ ከሰጠበት ምክንያቶች አንዱ የእኛ ቅድሚያዎ ከእግዚአብሔር ቅድሚያዎች ጋር በሂደት እንዲገጥሙ ለመረዳት ነው፡፡ ይህ በአንድ ለሊት ሊተገበር የሚችልና ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር የምንተባበር ከሆነ ግን መሆኑ በሂደት መሆኑ አይቀርም፡፡

ከዚህ በላይ በተማርናቸው ትምህርቶች መሠረት የሕይወትህ ‹ትላልቆቹ ኮረቶች› ምንድን ናቸው? ወይም ምን መሆን አለባቸው? በማስታወሻ ደብተርህ ላይ፣ ከ5 እስከ 8 የሚሆኑ፣ በሕይወትህ ቀድመው ሊተገበሩ የሚገባቸውና ከፍተኛ ትኩረት ልትሰጣቸው የምትፈልጋቸውን ነገሮች ዘርዝር፡፡

ለውጤታማ የሰአት አጠቃቀም የሚረዱ አምስት ደረጃዎች

በየዕለቱ ባለህ የጊዜ ሰሌዳ ትላልቆቹ ኮረቶች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው በአግባቡ መደርደራቸውን ለማረጋገጥ አምስት ደረጃ ባላቸው ሂደቶች ውስጥ ማለፍህን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው፡፡ የሚከተለው ጥናት በእነዚህ አምስት ደረጃዎች ውስጥ እንድታልፍ ይረዳሃል፡፡

ደረጃ 1፡ ቅድሚያዎችህን በተልዕኮ መግለጫ ቅረፅ

የተልዕኮ መግለጫ – በሕይወትህ በአሁኑ ሰአት እየፈጸምክ ያለኸውን ወይም ልትፈፅም የምትሻውን ጉዳይ የሚገልጽ ነው፡፡ ግልፅ የሆነ የተልዕኮ መግለጫ ካለህ ከፊትህ ያሉትን ጊዜያት ለማቀድ ያግዝሃል፡፡ ምክንያቱም የአሁን ጊዜህን ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ለመጠቀም ይህ መግለጫ፣ ተጨባጭ መመዘኛ በመሆን ወደ ሕይወትህ የሚመጡትን አጋጣሚዎች ‹እሺ› ወይም ‹እምቢ› የማለት መሠረት ይጥልልሃልና፡፡ ይህ መግለጫ፣ አንድን ነገር ለመፈጸም የሚያስችል አቅጣጫ ይሰጥሃል። የምትሰራውን ነገር ሁሉ በማካተት እንደ ዣንጥላ ያገለግልሃል። ከዚህ በተጨማሪ ሊለወጥ የማይገባውንና ሙሉ በሙሉ ተከናውኖ ማለፍ የሚገባውን የሕይወት ዘመን ጉዞና ተግባርህን ያመለክታል፡፡

ደረጃ 2፡ የተልዕኮ መግለጫህን እውን ለማድረግ የሚያስችሉህን ዋና ግቦች ለይተህ አስቀምጥ፡፡

እነዚህ ግቦች ቢያንስ ለረጅም ጊዜ የማይለወጡ መሆን ይኖባቸዋል፡፡ እነዚህ ግቦች ሰፊ እና የረጅም ጊዜ ህልሞች (እቅዶች) በመሆናቸው ተግባራዊ ለመሆን ወራት፣ አመታት ወይም አስርት አመታት የሚጠይቁ ይሆናሉ፡፡ እነዚህ ግቦች ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ሁሉንም ወይም የተወሰኑትን የሕይወትህን ክፍሎች ይዳስሳሉ፡፡

  • መንፈሳዊ
  • አካላዊ
  • ግላዊ
  • ስራ ነክ
  • ገንዘብ ነክ
  • ቤተሰብ
  • ማህበራዊ ጉዳዮች
  • ፖለቲካ

ግቦችን ስትቀርፅ ግቦችህ – የተወሰነ፣ የሚለካ፣ ሊደረስበት የሚቻል፣ ተግባራዊ፣ ተጨባጭ መሆናቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው፡፡

በመጪዎቹ ሀያ ሰላሳ አመታት ምን ሆነህ ማየት ትፈልጋለህ? ምን ብትሆን ነው በሕይወትህ መጨረሻ ዘመን፣ ‹‹ምንም የምፀፀትበት ነገር የለኝም›› ብለህ ልትናገር የምትችለው? ቤተሰብ ብትመሠርት? የንግድ አውሮፕላን አብራሪ ብትሆን? ወደ ውጪ አገር ብትሄድ? አንድ ሚሊዮን ብር ብታገኝ? በኦሎምፒክ ውድድር ላይ ብትወዳደር?

በማስታወሻ ደብተርህ ላይ በሕይወትህ ዘመን አጠናቀህ ልታያቸው የምትፈልጋቸውን የመጀመሪዎቹን አምስት ዋና ግቦችህን ፃፍ፡፡ ‹‹ደስተኛ መሆን›› የሚሉ አይነት ግልፅ ያልሆኑ ዐረፍተ ነገሮች እና ‹‹ኃጢአት የሌለበት ፍፁም ሰው መሆኑ›› ወይም ‹‹አንድ ማይል በሦስት ደቂቃ መሮጥ›› የሚሉ አይነት ተጨባጭ ያልሆኑ ዐረፍተ ነገሮችን ከግቦችህ መካከል አስወግድ፡፡

ደረጃ 3፡ ዋነኛ ግቦችህ ላይ ለመድረስ የሚረዱህን መካከለኛ ግቦች ቅርፅ

መካከለኛ ግቦች ወደ ዋነኛው ግብህ የሚያፈናጥሩህ ስፕሪንጎች ናቸው፡፡ በርካታ መካከለኛ ግቦች በአንድ ላይ ሆነው አንድ ዋነኛ ግብ ተግባራዊ እንዲሆን ይረዳሉ፡፡ ለአብነት፡- ከዋነኛ ግቦችኅ መካከል አንዱ ‹‹የአእምሮ ቀዶ ጥገና ባለሞያ መሆን›› ይሆናል፡፡ እናም የመጀመሪያው መካከለኛ ግብህ ‹‹የኮሌጅ ትምህርትህን በ 3.8 አጠቃላይ ውጤት ማጠናቀቅ ይሆናል፡፡ ቀጣዩ ደግሞ፣ በ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕክምና ትምህርት ቤት ተቀባይነት ማግኘት›› ይሆናል፡፡ ከዛም፣ ‹‹የሕክምና ትምህርቱን ማጠናቀቅ››፣ ወዘተ፡፡

በሌላ ወረቀት ላይ፣ በደረጃ 2 ስር የጻፍካቸውን ዋነኛ ግቦች ከእያንዳንዱ ስር ግማሽ ወረቀት ክፍት ቦታ እየተውክ ጻፋቻ፡፡ ከዛም በእያንዳንዱ ዋነኛ ግቦች ስር ልትዘረዝራቸው የምትችላቸውን ወደዚህ ግብ እንድትደርስ የሚረዱህን መካከለኛ ግቦች ፃፍ፡፡

ከዚህ በታች በተሰጠህ ክፍት ቦታ፣ በሌላ ወረቀት ላይ ከዘረዘርካቸው መካከለኛ ግቦች መካከል ለእያንዳንዱ ዋነኛ ግቦችህ የፃፍከውን የመጀመሪያ መካከለኛ ግብ ፃፍ፡፡

የመጀመሪያ መካከለኛ ግብ፡-

ለዋነኛ ግብ # 1 —- 1. ——————

ለዋነኛ ግብ # 2 —- 2. —————–

ለዋነኛ ግብ # 3 —- 3.——————-

ለዋነኛ ግብ # 4 —- 4. ——————

ለዋነኛ ግብ # 5 —- 5. ——————

ደረጃ 4፡ መካከለኛ ግቦችህ ላይ ሊያደርሱህ የሚችሉ የአጭር ጊዜ ግቦችን ቅረፅ

እዚህ ደረጃ ላይ ራስህ የምትጠይቀው ጥያቄ፣ ‹‹የመጀመሪያውን መካከለኛ ግቤን ተግባራዊ ለማድረግ በአሁን ሰአት መውሰድ ያለብኝ እርምጃ ምንድን ነው? የሚል ነው፡፡ ምላሽህ፣ የአጭር ጊዜ ግቦች ዝርዝር ይሆናል፡፡

ዶክተር ሪቻርድ ፋርማን የቀዶ ጥገና ባለሞያ ለመሆን ኮሌጅ ገብቶ ለመሰልጠን የነበረውን ህልም ለማሳካት የነበረው አጠቃላይ ግብ ውጤታማ የሆነው አንድ ቀን ሌሊት በሰራው የኬሚስትሪ የቤት ስራ ምክንያት እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ያችን ሌሊት በስንፍና አሳልፏት ቢሆን ኖሮ፣ ፈተናውን ይወድቅ ነበር፡፡ ፈተናወን ቢወድቅ ኖሮ ደግሞ ኮርሱን አነስተኛ በሆነ ውጤት ያጠናቅቅ ነበር፡፡ ይህ ውጤት አነስተኛ ከሆነ ደግሞ፣ ወደ ሕክምና ኮሌጅ መግባት የማይታሰብ ይሆናል፡፡ የሕክምና ኮሌጅ ካልገባ ደግሞ የቀዶ ጥገና ባለሞያ መሆን የማይታሰብ ይሆናል፡፡ እሱ ግን፣ በዛች ሌሊት በትጋት በመስራት ቆንጆ ውጤት ስላመጣ፣ የቀዶ ጥገና ባለሞያ ለመሆን የሚያደርገው ጉዞ ቀና እና በሮቹም የተከፈቱ ሆኑለት፡፡ ሁሉ ነገር አሁን ያለችሁን ሰአት በአግባቡ በመጠቀም ላይ የተወሰነ ነው፡፡

በደረጃ 3 ላይ የዘረዘርካቸውን አምስቱንም መካከለኛ ግቦች መልሰህ ካጤንክ በኃላ በሌላ ወረቀት ላይ በእያንዳንዱ ስር ያቀድካቸውንና እነዚህን ግቦች ለማሳካት የሚረዱህን የአጭር ግዜ ግቦች ጻፍ፡፡ ከዚህ በታች በተሰጠህ ክፍት ቦታ የመጀመሪያው መካከለኛ ግብህን የሚመለከቱ የአጭር ጊዜ ግቦችህን ፃፍ፡፡

ለመጀመሪያ መካከለኛ ግብ፡-

1ኛ የአጭር ጊዜ ግብ —- 1. ———————

2ኛ የአጭር ጊዜ ግብ —- 2. ——————–

3ኛ የአጭር ጊዜ ግብ —- 3. ———————

4ኛ የአጭር ጊዜ ግብ —- 4. ———————

5ኛ የአጭር ጊዜ ግብ —- 5. ———————

ደረጃ 5፡ የአጭር ጊዜ ግቦችህን የምታጠናቅቅበት የጊዜ ሰሌዳ አውጣ፣ አላስፈላጊ ተግባራትን ለይ።

የዚህ ጉዞ መጨረሻ የሚሆነው፣ የአጭር ጊዜ ግቦችህ በጊዜ ሰሌዳህ ላይ ሰፍረው ሲጠናቀቁ ነው፡፡ እያንዳንዱ የአጭር ጊዜ ግቦች በጊዜ ሰሌዳው መሠረት ሲጠናቀቁ ነገሩ አበቃ ማለት ነው፡፡ ‹‹የተፈጸመች ፈቃድ ሰውነትን ደስ ታሰኛለች!›› (ምሳሌ 13፡19) ፡፡ ፈቃዶችህን በጊዜ ሰሌዳ ላይ አስፍረህ ፍፃሜያቸውን ካልተከታተልክ በቀር ይህንን ደስታ ማጣጣም አስቸጋሪ ነው!

የጊዜ ሰሌዳህን አዘጋጅ፡፡ በደረጃ 4 ስር ያሰፈርካቸውን የአጭር ጊዜ ግቦች አጢናቸው፡፡ በርካቶቹ በጊዜ ገደብ የታጠሩ ናቸው – እነዚህን ግቦች በጊዜህ ሰሌዳህ ላይ አስፍራቸው!

ጊዜህ ቅድሚያ በምትሰጣቸው ነገሮች አስይዘህ ከሆነ፣ አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ‹‹እምቢ›› ስለምትል፣ ሰዎች የአንተን ጊዜዎች በማትፈልጋቸው ነገሮች ሊሞሉ አይችሉም፡፡ ቀናቶችህን የማታቅድባቸው ከሆነ፣ ሌላ ሰው ላንተ ያቅድልሃል – ምናልባትም በዚህ እቅድ አትደሰት ይሆናል!

ብቻህን ከጌታ ጋር በመምከር፣ በገንቦው ውስጥ የትኛቹ ትላልቅ ኮረቶች መጀመሪያ ላይ መግባት እንዳለባቸው፣ ከዛም መቼና እንዴት ጠጠሮቹ፣ አሸዋውና ውሃው መግባት እንዳለበት መወሰን አለብህ፡፡

ተግባራዊ የሰአት አጠቃቀም መርሆዎች

የዚህን ምዕራፍ ጥናት፣ እግዚአብሔር የሰጠህን ጊዜ በኃላፊነት መንፈስ ለመጠቀም የሚያስችልህን ተግባራዊ የሆኑ አምስት አጠቃላይ መርሆዎች በማየት እናጠናቅቃለን፡፡

  1. አስቀድመህ እግዚአብሔርን አማክር

ኢየሱስ ጌታህ እንዲሆን በጠየቅኸው መሰረት እንደዛው ስትመላልስ ሊያይህ ይፈልጋል፡፡ አስቀድመህ ምን ሊያደርግልህ እንደምትፈልግ ልትጠይቀው ይገባሃል፡፡ ይህንን ፓሊሲ የማትከተል ከሆነ የጉዞህ መጨረሻ በውጪያ ወደሌላቸው መንገዶች መጓዝ እና ጊዜ ማጥፋት ይሆናል። ይህ ደግሞ እግዚአብሔር ላንተ ካዘጋጀው አላማ ጋር የሚቃረን ነው፡፡

የሐዋሪያት ሥራ 22፡6-10 አንብብና ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ለተሰበሰቡ ሰዎች የመሰከረውን ምስክርነትን ተመልከት፡፡ ኢየሱስ ለጳውሎስ በተገለጠለት ጊዜ የጳውሎስ የመጀመሪያ ጥያቄ፣ ‹‹ጌታ ሆይ አንተ ማነህ?›› የሚል ነበር፡፡ አንተም ተመሳሳይ ጥያቄ ጠይቀህ ምላሽ አግኝተህ ይሆናል፡፡ የጳውሎስ 2ኛ ጥያቄ ምን ነበር? ይህን ጥያቄ በየቀኑ ደጋግመን ልንጠይቅ ይገባል!

በዮሐንስ 17፡4 የቀረበው ጥቅስ ኢየሱስ ከስቅለቱ በፊት በነበረችው ለሊት የጸለየው ጸሎት ነው፡፡ ኢየሱስ የሦስት አመት የአገልግሎት ጊዜ ብቻ ቢኖረውም በዚህ ጊዜ ውስጥ ስራውን መፈጸም መቻሉን ልብ ልትል ይገባል፡፡ እዚህ ክፍል ልብ ልትለው የሚገባህ ቁልፍ ነጥብ ኢየሱስ ምን አይነት ሥራ እንደሰራ ነው፡፡ በጥቅሱ ውስጥ፣ ኢየሱስ የፈጸመው ስራ ምን አይነት እንደሆነ ነው የተገለጸው?

የምትሰራው ስራ (ማንኛውም ጊዜ የሚወስድ ነገር ሁሉ) ራስህ ለመስራት የወሰንከው ወይም ሰዎች በአንተ ላይ የጫኑት ሳይሆን እግዚአብሔር እንድትሰራው የሰጠህ ስራ መሆኑ የምትለይበት መንገድ ምንድ ነው? – ጥቂቶቹን ግለጽ፡፡

ሕይወትህን በእርሱ ትዕዛዝ ስር ለማስገዛትህ እውቅና እስከሰጠህ ድረስ ጊዜህን በምን ሁኔታ መጠቀም እንዳለብህ በምታደርገው ምርጫ ውስጥ እግዚአብሔር ይረዳሃል፡፡ በሚመራህ መንገድ ለመጓዝ ፈቃደኛነትህን እስከገለፅክ ድረስ በእግዚአብሔር እጅ ጊዜህ አይባክንም፡፡

ዛሬ ላይ ሆነህ ስትመለከት፣ ጥቁር ወይም ሰማያዊ ካልሲ ማድረግ ወይም ወደ መሳሪያ ቤት ለመሄድ ይሄኛውን አልያም ያኛውን መንገድ መምረጥህ እግዚአብሔርን ብዙ የማያሳስበው ጉዳይ እንደሆነ ታስብ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች በቀላሉ የማይታዩ መሆናቸውን ማወቅ ይኖብሃል፡፡ ለዚህ ነው በማንኛውም ሁኔታ በተገዢነት ልብ ከእግዚአብሔር ጋር መጓዝ የሚኖርብህ፡፡

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ጥቅሶች ጊዜአችንን በመጠቀም ረገድ እግዚአብሔርን ምን ማማከር እንዳለብን ጠቃሚ ነጥቦችን ያሳዩናል፡፡ የተመለከትከውን ሃሳብ ፃፍ፡፡

  • ምሳሌ 3፡5-6
  • ምሳሌ 16፡3
  • ምሳሌ 20፡24
  • ኤርሚያስ 10፡23
  • ኤርሚያስ 29፡11
  1. ለማቀድ ጊዜ ይኑርህ

አንዳንድ ሰዎች ሁሉን ነገር በጥድፊያ ማድረግ ይወዳሉ፡፡ መስራት ያለባቸውን ነገር የሚያውቁት በሩጫ ላያ ሳሉ ነው፡፡ ትኩረት የማጣት ችግር አለባቸው፣ በዚህም ምክንያት በጥቂቱ ብቻ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድመን እንድናቅድ በግልጽ ይመክረናል፡፡ ያለህን ግብአቶች፣ ጊዜ፣ እና ከንዘብህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ምክንያታዊ እና ሊጨበጥ የሚችል እቅድ ንደፍ፡፡ አስቀድመህ ቀናቶችህን፣ ሳምንታቶችህን፣ ወራቶችህንና አመታቶችህን አቅዳቸው! ወደ እንተ ለሚመጡት ሁኔታዎች ምላሽ እየሰጠህ ከመኖር ይልቅ ሁኔታዎቹ ያንተን እቅዶች እንዲያገለገሉ አድርጋቸው!

  1. ታታሪ ሁን

የዌብስተር መዝገበ ቃላት ‹‹ታታሪ›› የሚለውን ቃል ሲፈታ፣ ‹‹ፅናትን፣ ብርቱ ጥረትን፣ ሀሞተ ኮስታራነትን፣ ስራ ወዳድነትን አጣምሮ የያዘ ማንነትን›› ያመለክታል፡፡ አንድ ሰው የሚፈልገውን እቅድ ሁሉ ሊያወጣ ይችላል ነገር ግን ይህን ለማስፈጸም ታታሪነት ከጎደለው ነገሩ ሁሉ እርባና ቢስ ይሆናል፡፡ በቆላሲያስ 3፡23-24 መሠረት በምንሰራው ስራ ሁሉ ታታሪ መሆን ካለብን ምክንያቶ መካከል አንዱ ምንድን ነው?

‹‹ታማኝነት›› ከ ‹‹ታታሪነት›› ጋር አብሮ ይሄዳል፡፡ በሉቃስ 16፡10 መሠረት እግዚአብሔር በሚሰጠን ጥቂቷ ነገር ሳይቀር ታማኝና ታታሪ የምንሆንበት ምክንያት ምንድን ነው?

ጥቂት ስለዚህ ጉዳይ አስብ፡- እንዴት ነው በአመት ውስጥ 11 ቀን ከግማሽ ያህል የስራ ቀናት በሕይወትህ ላይ መጨመር የምትችለው? ማድረግ የሚኖርብህ ከዚህ በፊት ከምትነሳበት ሰአት 15 ደቂቃ ብቻ ቀደም ብለህ መነሳት ነው! ይህንን ማስላት ትችላለህ፡፡ 30 ደቂቃ ቀደም ብለህ ብትነሳ ደግሞ በአመት ውስጥ ከሦስት ሳምንት በላይ ተጨማሪ የስራ ቀናት ማትረፍ ትችላለህ!

ምሳሌ 21፡5 አንብብና የትጉሃን ሃሳብ ወደ ምን እንደሚያደርስ ተናገር፡፡ ‹‹ችኩሎችስ›› ፍፃሜያቸው ምንድን ነው?

  1. ውጤታማነትን አጥብቀህ ተከታተል

ልብ ልትላቸው የሚገቡ ነጥቦች፡- እንዴት አድርጌ ነው ከዚህ በተሻለ ይህን ነገር የምሰራው? በተሻለ ፍጥነት እንዴት አድርጌ ነው የምሰራው? የተሻለ ውጤት እንዲኖረው ማድረግ የምችለው እንዴት ነው? ሁለት ነገሮችን በአንድ ጊዜ በመስራት ጊዜዬን እንዴት መቆጠብ እችላለሁ? አንዳንድ ነገሮችን ሌሎች እንዲሰሩት በመስጠት ጊዜዬን እንዴት መቆጠብ እችላለሁ?

  • በኤፌሶን 5፡15-16 መሠረት በጊዜዎቻችን በጥንቃቄ መጓዝ ያለብን ምክንያት ምንድን ነው?
  • ‹‹የቀናት ክፋት›› ከዚህ ጉዳይ ጋር ምን ግንኙነት አላቸው?
  • በ1 ቆሮንቶስ 14፡33፣40 መሠረት ነገሮችን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንጂ ስርአት በጎደለው መንገድ መስራት የሌለብን ምክንያት ምንድን ነው?
  1. እስኪዝሉ መስራትን አስወግድ፡- ጥቂት እረፍት አድርግ!

እያንዳንዱን ሰአት ‹‹ውጤታማ›› ለመሆን በማቀድ ከመጠን በላይ ታታሪ መሆን ይቻላል፡፡ ነገር ግን እረፍት በሕይወታችን ልንዘነጋው የማይገባ ትልቅ ጠጠር እንደሆነ እግዚአብሔር ግልጽ አድርጎልናል! የእረፍትን ጠቃሚነት እግዚአብሔር ግልጽ በሆነ መንገድ በአስሩ ትዕዛዛት ውስጥ አስፍሮልናል! ዘጸአት 20፡8-11 አንብብ፡፡ ከትዕዛዛቶቹ ይልቅ ይህ ትዕዛዝ ሰፋ ብሎ መገለጹን ልብ በል፡፡ ይህ ምን ያስገነዝብሃል? የዚህ ትዕዛዝ ዋነኛ አጀንዳ ሰንበትን ‹‹መቀደስ›› ቢሆንም ስለ ስራ ሃሳብም ይናገራል፡፡ ምን እንድናደርግ ነው የሚያዘን?

ማርቆስ 6፡30-31 አንብብ፡፡ ቁጥር 7 ላይ ማንበብ እንደምትችለው – ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ሁለት ሁለት አድርጎ እንዲያገለግሉ ላካቸው፡፡ ከአገልግሎታቸው ሲመለሱ ስላደረጉት ነገር ሪፖርት አቀረቡ፤ በቀጣይ ስለሚያገለግሏቸው በርካታ ሰዎችም መደነቅ ይዟቸው ነበር፡፡ ኢየሱስ ግን ከዚህ የተለየ ሃሳብ ነበረው፡፡ የኢየሱስ ቀጣይ አቅጣጫ ምን ነበር (ቁጥር 31)?

‹‹ወሰን›› አስምር፡፡ ‹‹ወሰን በእኛና በገደቦቻችን መካከል ያለ ክፍተት ነው፡፡ ለመጠባበቂያ እና ላልተጠበቁ ነገሮች የተቀመጠ ጊዜ ልንለው እንችላለን፡፡ በእድገትና ብልጽግና ውስጥ በተሸሸገ የስግብግብነት ባህሪ ምክንያት ይህ ወሰን በብዙ ሰዎች ተጥሷል፡፡ ይህ ክርስቲያኖችንም ይጨምራል። ይህ እረፍት የጎደለው ኑሮ በዚህ ዘመን የሚኖሩ ሰዎችን ጭንቀት፣ ሁከት እና ዝለት ምክንያት ይጠቁመናል! አንዳንድ ጊዜ ነገ ብዙ ለመስራት ዛሬ ጥቂት ነገር ብቻ መስራት ይኖርብህ ይሆናል፡፡

የጊዜ ሰሌዳህን በምታቅድበት ጊዜ ራስህን ዘና የምታደርግበት ጥቂት ጊዜ ማሰብን አትርሳ፡፡ በየቀኑ ለጥቂት ደቂቃዎች ራስህን ዘና አድርግ፡፡ ዊንስተን ቸርችል፣ ቤን ፍራንክሊን፣ ቶማስ ኤድሰን እና የመሳሰሉ በርካታ ውጤታማ ሰዎች ከቀትር በኃላ ጥቂት ጊዜ ለሸለብታ ያጠፋ ነበር፡፡ እሁድን ቀለል አርገህ ለማሳለፍ ሞክር፡፡ በወር አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ ገለል ባለ ስፍራ ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ ለማሳለፍ አቅድ፡፡ ከቤተሰቦችህም ጋር አብረህ ዘና የምትልበትን ጊዜ አቅድ፡፡ ከባለቤትህ ጋር ብቻ የምትገናኝበት የቀጠሮ ጊዜ ይኑርህ፡፡ በጫካ ውስጥ የእግር ጉዞ አድርግ፡፡ ቆም ብለህ የአበቦችን ሽታ ለማድነቅ ጊዜ ይኑርህ፡፡ እረፍት ለማድረግ ታታሪ ሁን!

የቃል ጥናት ጥቅስ፡

ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፥ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት፥ ከጌታ የርስትን ብድራት እንድትቀበሉ ታውቃላችሁና። የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስ ነውና።-ቆላሲያስ 3፡23-24

ማጠቃለያ፡-

‹‹ምርጡ ጊዜህን ለእኔ ትሰጣለህ?›› ሲል ኢየሱስ ይጠይቅሃል፡፡

የደቀ መዝሙር ትምህርቱ ጥናት እዚህ ላይ ያበቃል። የእርስዎ መንፋሳዊ ጉዞ ግን ይቀጥላል። በመቀጠል መጽሐፍ ቅዱስን በርዕስ በጥልቀት እንዲያጠኑ እንጋብዞታለን። ይህንን ጥናት ለማድረግ መጀመሪያ ወደ ድረ ገጹ ዋና ገጽ (Home page) ይመለሱና “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት” በሚለው ርዕስ ስር ያሉትን ይመልከቱ።

ሌሎች ተጨማሪ የደቀ መዝሙር ትምሕርቶችን ለማጥናት ያሚሹ ከሆነ ደግሞ፣ የሚከተለውን ሊንክ በመጫን ጥናትዎን ይቀጥሉ። ግለሰብ ተኮር የደቀ መዝሙር ማሰልጠኛ ማኑዋል

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading