የሕይወት እንጀራ

August 2, 2018

የክርስቶስ ተከታዮች ለዓለም ብርሃንና ጨው መሆን አለባቸው (ማቴ. 5፡13-16)

ብዙ ክርስቲያኖች፥ «ዓለም ለእኛ በጣም መጥፎ ስለሆነች የመንግሥት ሥራ ትተን ወደ ክርስቲያናዊ ድርጅቶች ብንሄድ ይሻላል። ወይም ከማኅበረሰባችን ወጥተን ከሚመስሉን ሰዎች ጋር የምንሠራበትንና የምንኖርበትን ክርስቲያናዊ ማኅበረሰብ እንመሥርት» ይላሉ። ነገር ግን ይህ ክርስቶስ ያስተማረው የደቀ መዝሙርነት ዐይነት ነው ወይ? ከማኅበረሰቡ ወጥተው የራሳቸውን የቅዱሳን ማኅበረሰብ ከመሠረቱት ኢሴናውያን በተቃራኒ፥ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ በዓለም ውስጥ እንደ ጨውና ብርሃን እንዲያገለግሉ የሚፈልግ መሆኑን ገልጾአል። ኢየሱስ በዓለም ውስጥ ደቀ መዛሙርቱ ያደረጉትን አስተዋጽኦ ከሦስት ነገሮች ጋር በማነጻጸር አብራርቷል። በመጀመሪያ፥ ከጨው ጋር አነጻጽሯቸዋል። በጥንት ዘመን ጨው በጣም ጠቃሚ ነገር ነበር። እንደ ጥንታዊት ኢትዮጵያ በመሳሰሉት አገሮች፥ የመገበያያ ገንዘብ ሆኖ አገልግሏል። ጨው ለሁለት ነገሮች ያገለግል ነበር። ሀ ለጣዕም፥ ወጥ እንዲጣፍጥ፥ በገጠር በቡና ጭምር ጨው እንደሚጨመር ሁሉ፥ በክርስቶስ ዘመን ጨው ለጣዕም መስጫ ያገለግል ነበር። 2) ለማቆያ። ሥጋ እንዳይበላሽ በጨው ቀምመው ቋንጣ ያደረጉት ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ በቁጥር ቢያንሱም እንኳ እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ቢኖሩ ክርስቲያኖች በማኅበረሰቡ ውስጥ እነዚህን ሁለት ተግባራት መፈጸም ይችላሉ። መንፈሳዊ ምሳሌነት ያለው ሕይወት በመምራት በክፋት ለተሞላው ማኅበረሰብ መልካም መዓዛ ይጨምራሉ። በተጨማሪም እግዚኣብሔር ክፋት እንዳይጨምርና ማኅበረሰቡ የበለጠ ክፉ እንዳይሆን ለመከላከል፥ በውስጡ ያሉትን ክርስቲያኖች ይጠቀማል። እስራኤላውያን ጨው የሚያገኙት ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ ምሥራቅ ከሚገኘው ሙት ባሕር ነበር። ከመሬትም ቆፍረው ያወጡታል። ነገር ግን ይህ ንጹሕ ጨው ስላልሆነ፥ በፍጥነት ካልተጠቀሙበት ጨውነቱን እያጣ ይሄድ ነበር። ከዚያ በኋላ ሊያገለግል የሚችለው ወደ መሬት በመጣል፥ ወይም ጣሪያቸው እንዳያፈስ ከዚያው ላይ በማስቀመጥ ብቻ ይሆናል። ዛሬም እንኳ ብዙ የአይሁድ ቤቶች ውኃ የሚያስገቡ ጣሪያዎች አሏቸው። ዛሬም ድረስ ያረጀና የማይጠቅም ጨው በጣሪያቸው ላይ በማድረግ ዝናብ ይከላከላሉ።) በተመሳሳይ ሁኔታ የአንድ ክርስቲያን ባሕርይ የዓለምን ሲመስል፥ ለማኅበረሰቡ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ሊኖር አይችልም። ሁለተኛው ማብራሪያ ብርሃን ነበር። በጥንት ዘመን ኤሌክትሪክ ስላልነበረ፥ ሰዎች በወይራ ዘይት የተሞሉ ኩራዞችን ይጠቀሙ ነበር። ብርሃን አስደናቂ ነገር ነው። ትንሽ ብርሃን ብዙ ጨለማ ትገፋለች። የክርስቶስ ተከታዮች በቁጥር ቢያንሱም እንኳ፥ የክርስቶስን ባሕርያት በዓለም ውስጥ ማብራት አለባቸው። የሰዎችን ክፋት አብርተን በማሳየት፥ ሕይወታቸውንና ማኅበረሰባቸውን በሚለውጥ መንገድ እንዴት ሊኖሩ እንደሚችሉ እናሳያቸዋለን፡ ነገር ግን ሕይወታችን ዓለምን በመምሰል በኃጢአት ከጨለመ፥ ይህ በማሰሮ ውስጥ እንዳለ መብራት ይሆናል። ወይም ደግሞ ስደትን ፈርተን ብርሃናችንን ብንደብቅ፥ እግዚአብሔር ጽድቁን ለማብራት እኛን የተጠቀመበት ዓላማ ከግቡ ሳይደርስ ይቀራል፡፡ ሦስተኛው ምሳሌ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ናት። እንደተለኮሰ መብራት፥ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አትችልም። በተመሳሳይ ሁኔታ እነዚህን ክርስቶስ የጠቀሳቸውን ባሕርያት የያዙ ክርስቲያኖች ለሁሉም በግልጽ የሚለዩ ይሆናሉ። ምስክርነታችን የሚመጣው ከአፋችን ሳይሆን ከተግባራችን ነው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለእግዚአብሔር የሚኖሩ ጥቂት ክርስቲያኖች እንደ ብርሃንና ጨው ኅብረተሰቡን ሲለውጡ ያየህበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) እንደ ዓለማውያን በመኖራቸው ምክንያት የብርሃንነትና የጨውነት አገልግሎታቸው የጠፋበትን ሁኔታ ግለጽ። ሐ) ሕይወትህ እንደ ብርሃንና ጨው የሆነው እንዴት ነው? ብርሃንህና ጨውህ የበለጠ እያደገ በማኅበረሰቡ ላይ የበለጠ ለውጥ ለማስከተል ትችል ዘንድ ምን ታደርጋለህ? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

የክርስቶስ ተከታዮች ለዓለም ብርሃንና ጨው መሆን አለባቸው (ማቴ. 5፡13-16) Read More »

የተራራው ስብከት [እግዚአብሔር የባረከው ሰው ባሕርይ] (ማቴ. 5፡1-12)

የውይይት ጥያቄ፡- እራት ዓምዶች ያሉት ሠንጠረዥ በወረቀት ላይ ሣል። የመጀመሪያውን ዓምድ «ባሕርይ»፥ ሁለተኛውን «ያ ባሕርይ ምን ማለት እንደሆነ»፤ ሦስተኛውን ዓምድ «ክርስቶስ ተስፋ የሰጠው በረከት»፥ እንዲሁም አራተኛውን ዓምድ «ዓለም ሰዎች እንዴት እንዲኖሩ እንደምትፈልግ» በሚሉ ርእሶች ለይ። በማቴ. 5፡3-12 የሚገኙትን የብፅዕና ዓይነቶች በሠንጠረዥ ውስጥ ሙላ። ይህ የመጀመሪያው ክፍል በክርስቶስ ተከታዮች ባሕርይ ላይ ያተኩራል። እኛ ብዙውን ጊዜ ክርስቲያን ሊያደርገው ይገባል ወይም አይገባም በምንለው ውጫዊ ተግባር ላይ ስናተኩር፥ ክርስቶስ ግን የተገቢው ተግባር መሠረቱ፥ ባሕርይ መሆኑን ያመለክታል። ክርስቶስ የባሕርያችን መለወጥ የተግባራችንን መለውጥ እንደሚያስከትል ያውቃል። ከእነዚህ ባሕርያት ውስጥ አንዱን መርጠን ሌሎችን መተው አንችልም። እነዚህ ሁሉ የክርስቶስ ተከታዮችን መለያ ባሕርያት ለመመሥረት በአንድነት የሚታዩ ናቸው። አንድ ሰው እንደ ተናገረው፥ እነዚህ ባሕርያት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደር የሌላቸው የክርስቶስ መገለጫዎች ናቸው። እነዚህ ባሕርያት ዓለም አስፈላጊዎች ናቸው ብላ ከምታስተምረው ትምህርት ጋር የሚቃረኑ ናቸው። ሀ. በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ለአይሁዶች «ብፁዕ» የሚለው ቃል ደስተኛ ከመሆን የላቀ ፍች ነበረው። ይህ ቃል በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ማግኘትንና የበረከቱ ተቋዳሽ መሆንን ያሳያል። የመጀመሪያው በረከት የተሰጠው፥ በመንፈስ ድሆች ለሆኑት ሰዎች ነው። እዚህ ላይ ክርስቶስ የሚናገረው ስለ ሥጋዊ ድህነት ሳይሆን፥ ስለ መንፈሳዊ ድህነት ነው። ሥጋዊ ድህነት ያጠቃቸው ሰዎች ሙሉ በሙሉ በሰዎች ላይ ጥገኞች ሆነው የሚኖሩ ናቸው። የራሳቸው ሀብት ስለሌላቸው ለኑሮአቸው የሚደገፉት በሰዎችና በእግዚአብሔር ላይ ነው። በመንፈስ ድሀ መሆን ማለት፥ እግዚአብሔርን የሚያስደስትና ለእግዚአብሔር ለመኖር የሚያስችል መንፈሳዊ ሀብት እንደሌለን መገንዘብ ነው። ስለሆነም እርሱ ይረዳን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንመለከታለን። በመንፈስ ድሆች የሆኑ ሰዎች ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር ቢኖር፥ ወደ እግዚአብሔር ጸጋና ምሕረት ፊታቸውን መመለስ እንደሆነ ያውቃሉ። ወደ እርሱ ስለሚመለከቱ እግዚአብሔር ምሕረትን፥ ጸጋንና መዳን ይሰጣቸዋል። በመንፈስ ድሆች የሆኑ ሰዎች በራሳቸው ችሎታ ሳይመኩ ማንኛውም መፍትሔ ከእግዚአብሔር እንደሚመጣ ያምናሉ። ዓለም የምታስተምረው የዚህን እውነታ ተቃራኒ ነው። የኋላ ኋላ ዓለም በሌሎች ላይ በሚደገፍ ሰው ትቀልድበታለች። ዓለም በማንነታችንና በተግባራችን እንድንኮራ ታስተምረናለች። ስለዚህ በሃይማኖታዊ ውርሳችንና በመንፈሳዊነታችን እንኩራራለን። እንዲሁም ተነሣሽነት ያላቸውን፥ ብልሆችን፥ ሀብታሞችንና ኃይለኞችን እናደንቃለን። በራሳቸው ብርታት ሊሠሩ የሚችሉ ሰዎች የሥልጣን ስፍራ ይሰጣቸዋል። የሃይማኖት ሰዎች ሳይቀሩ መንፈሳውያን ለመሆንና ደኅንነትን ለማግኘት በመቻላቸው ይኩራራሉ። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ በመንፈሳዊ ባለጸግነታቸው በመመካታቸው ክርስቶስ ሊሰጣቸው የሚፈልገውን በረከት ያጣሉ። በመንፈስ የሚታበዩ ሰዎች የክርስቶስ መንግሥት አካል አለመሆናቸውን ያሳያሉ። በመንፈስ ድሆች የሆኑ መንግሥተ ሰማይን ከእግዚአብሔር ዘንድ በስጦታ ይቀበላሉ። ክርስቶስ እንደ አማኑኤል ከእነርሱ ጋር ይኖራል። እርሱ በሕይወታቸው ላይ ይነግሣል። ስለሆነም በመንፈስ ድሆች የሆኑ ሰዎች በምድር ላይ የእርሱ መንግሥት አካል ሲሆኑ፥ መንፈሳዊ በረከቶቹን ይቀበላሉ። ከዚህም በላይ የክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥት አካል ለመሆናቸው እርግጠኞች ናቸው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድ ክርስቲያን በመንፈስ ድሃ ከመሆን ይልቅ፥ በመንፈስ ሀብታም ሊሆን የሚችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) በመንፈስ ድሃ የሆነው ክርስቲያን፥ በመንፈስ ትዕቢተኛ ከሆነው ክርስቲያን በአኗኗሩ እንዴት እንደሚለይ ግለጽ። ለ. የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መጽናናትን ያገኛሉና። ክርስቶስ በምን ምክንያት እንደሚያለቅሱ አልገለጸም። ዐውደ ምንባቡ ግን መንፈሳዊ ባሕርይ ያለው ነው። በኃጢአተኛነታቸውና በልባቸው ድንዳኔ የሚያዝኑ፥ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያንና በአገራቸው ኃጢአት ምክንያት የሚያለቅሱ ወገኖች ይጽናናሉ [መዝ. (119)፡136 አንብብ። የሚያለቅሱት የራስ ወዳድነት ፍላጎቶቻቸው ስላልተሟሉላቸው ሳይሆን፥ ዓለምና ሰዎች እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ባለመጓዛቸው ምክንያት ነው። ይህም ዓለም ከምታስተምረው አሳብ ተቃራኒ ነው። ዓለም በሕይወታችን እንድንደሰት ታስተምረናለች። ስለዚህም «ሰው እስከሆንህ ድረስ ለኃጢአት መጨነቅ የለብህም፥ የቤተ ክርስቲያንም ሆነ የአገር ኃጢኣት ሊያስጨንቅህ አይገባም ልትለውጠው አትችልምና» ትለናለች። ክርስቶስ ስለ ኃጢአት የሚያለቅሱ ሰዎች እንደሚጽናኑ ተናግሯል። እነርሱም እግዚኣብሔር የሚሰጣቸውን ይቅርታ ስለሚያውቁ ይጽናናሉ። እግዚአብሔር በእነርሱና በጸሎታቸው አማካይነት የራሳቸውንንና የሌሎችንም ሕይወት እንደሚለውጥ ስለሚያውቁ ይጽናናሉ። በኀዘናቸው ጊዜ ራሱ ክርስቶስ አብሯቸው እንደሚሆን ስለሚያውቁ፥ ይጽናናሉ። ኣንድ ቀን ኀዘንም ሆነ ለቅሶ የሌለበት መንግሥት ቤተሰቦች ስለሚሆኑ ይጽናናሉ (ራእይ 7፡17፤ 21፡4)። የውይይት ጥያቄ፡- ለመጨረሻ ጊዜ በሕይወትህ ውስጥ ወይም በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ስለተከሰተው ኃጢአት ያለቀስኸው መቼ ነበር? አልቅሰህ ከሆንህ ይህ ስለ ልብህ ሁኔታ ምንን ያሳያል? ሐ የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና። የዋህ የሚለውን ቃል ለመተርጎም አስቸጋሪ ነው። ብዙውን ጊዜ የዋህነት ሰዎች ያሻቸውን ነገር ሲያደርጉ መልስ አለመስጠት ወይም ሞኝነት እንደሆነ እናስባለን። ይህ ግን ክርስቶስ ያስተማረው የዋህነት አይደለም። ክርስቶስ የዋህ የነበረ ቢሆንም፥ ይፋዊ ተቃውሞ ሳያሳይ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ ነገር እንዳይደረግ ተከላክሏል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የዋህነት የተለያዩ ጽንሰ አሳቦች አሉት። በሕይወታችን ውስጥ ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜ ቁጡና መራር ሳይሆኑ፥ በትዕግሥት መገዛት የዋህነት ነው። ወይም የዋህነት ነገሮችን በራሳችን መንገድ ከማከናወንና የምንፈልገውን የማያደርጉትን ከመቃወም ይልቅ፥ በገር መንፈስ መመላለስ ሊሆን ይችላል። የዋህ ሰው እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር እንደሚሠራና የኋላ ኋላም ለጥቅማችን እንደሚያውለው ይገነዘባል። ስለሆነም እግዚአብሔር በሁኔታዎች ሁሉ ውስጥ ፍጹም ፈቃዱን ተግባራዊ እንደሚያደርግ ይተማመናል። የዋህነት በራስ ጥረት ሳይመኩ ሕይወትን ከእግዚአብሔር እጅ እንደተቀበሉ አድርጎ ማስተናገድ ነው። የዋህነት ራሳችንን ወይም አሳባችንን ለመከላከል አለመሞከርና ስሕተታችንን መቀበል ነው። ከዚህ በተቃራኒው ዓለም ዐመፅን፥ ተቃውሞንና የግል ፍላጎትን ታከብራለች። አንድን ነገር ከፈለግህ ተጠቀምበት። አንድ ሰው ካበሳጨህ እርሱን የሚያበግን አንድ እርምጃ ውሰድ። በሕይወት ቀዳሚ ሆነህ ለመገኘት፥ ከሌሎች ተማሪዎች የተሻለ ውጤት ለማግኘት፥ የተሻለ ሥራ ለመያዝ፥ የቤተ ክርስቲያን መሪ ለመሆን፥ ጠልፈህ መጣል፥ ካስፈለገም ሰዎችን መገፍተርና ማጭበርበር ይኖርብሃል ትላለች። የዓለም ሥርዐት በሰዎች ላይ ኃይልን እንድንቀዳጅ ያበረታታል። በዚህ ሁኔታ ዓለም ሰዎች በማታለልና በማጭበርበር የቀዳሚነትን ስፍራ እንደሚይዙ ስታስተምር፥ ክርስቶስ ግን የዋሆች ምድርን እንደሚወርሱ አስተምሯል [መዝ. (37)፡9-11 አንብብ።] ይህ እንዴት ይሆናል? በመጀመሪያ፥ ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ዓለም ከምትጠብቀው ተገላቢጦሽ የሆነውን ይሠራል። የቀዳሚነትን ስፍራ ለመያዝ የሚፍጨረጨሩ ሰዎች ምንም እንኳ ለጊዜው መጠቀም ቢችሉም፥ የኋላ ኋላ ፍሬያማ አይሆኑም። እግዚአብሔር በራሱ ጊዜና በራሱ መንገድ እንደሚባርካቸው የሚተማመኑ ግን፥ ባልተጠበቅ መንገድ የእግዚአብሔርን በረከት ይቀበላሉ። ይህም ሆኖ በረከቶቹ ይገቡናል፥ በበጎ ሥራችን አገኘናቸው የሚል ስሜት የላቸውም። ማቴዎስ ያተኮረው ግን በወደፊቱ ጉዳይ ላይ ነው። ክርስቲያኖች ምድራዊ በረከት ልንቀበል ወይም ላንቀበል ብንችልም፥ ከክርስቶስ ጋር እንደምንነግሥ ግን ጥርጥር የለውም። ይህ አጭር ምድራዊ ቆይታ፥ በዘላለማዊ መንግሥት የሚተካ ሲሆን፥ ምድራዊ የዋህነታችን መንፈሳዊ በረከትን ያስገኝልናል (ሉቃስ 22፡29-30፤ ራእይ 20፡4)። የውይይት ጥያቄ፡- በቤተ ክርስቲያንህ የየዋህነት ጉድለት ችግር ያስከተላበትን አጋጣሚ ግለጽ። መ. ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና። በዓለም ውስጥ ከሚገኙ እጅግ ጠንካራ ስሜቶች ሁለቱ ረሃብና ጥማት ናቸው። ምግብና ውኃ ሳናገኝ ብንቀር፥ አሳባችን ሁሉ እነዚህን ሁለት ነገሮች በማግኘቱ ላይ ያተኩራል። ያለእነዚህ ነገሮች ለመኖር አንችልም። ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ መንፈሳዊ ፍላጎትን ከረሃብና ከጥማት ጋር ያነጻጽራል [መዝ (42)፡1-2 ኣንብብ።] ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በጊዜያዊ ነገሮች ከመወሰድ ይልቅ፥ ጽድቅን ሊራቡ እንደሚገባ አስተምሮአቸዋል። ጽድቅ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ማድረግ ወይም ሙሉ በሙሉ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መመላለስ ነው። በአሉታዊ ጎኑ፥ ከኃጢአትና እግዚአብሔርን ከማያስደስቱ ነገሮች መራቅ ነው። በአዎንታዊ ጎኑ፥ እግዚአብሔርን የሚያስደስቱትን ነገሮች ማድረግ ነው። እግዚአብሔርን በበለጠ ለማወቅና እርሱን ለማስከበር መፈለግ ነው። በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በዓለም ሰዎች ትክክለኛና የእግዚአብሔር ፈቃድ ያለበትን ሕይወት ሲመሩ ለማየት መፈለግ ነው። ዓለም ግን የምትራበው ሌሎች ነገሮችን ነው። ትምህርትን፥ ገንዘብን፥ ኃይልና ሥልጣንን፥ ሌሎችንም ነገሮች ትራባለች። ዓለማውያን እግዚኣብሔርን በሚያስደስት መንገድ የሚኖር ሰው ሞኝ እንደሆነ ያስባሉ። ኢየሱስ ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ እንደሚጠግቡ ተናግሯል። ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ግንኙነት እያደገ ሲሄድ ይመለከታሉ። ጽድቅን የሚሹ ሰዎች ባሕርያቸው ተለውጦ፥ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ሲስማማ ያያሉ። በእነርሱ አማካይነት በቤተ ክርስቲያናቸውና በማኅበረሰቡም መካከል ለውጦች ይከሰታሉ። ከሁሉም በላይ ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ሰዎች፥ ጽድቅ የሚገዛበት ዘላለማዊ መንግሥት ዜጎች በመሆናቸው ይጠግባሉ። 9ኛ ጥያቄ፡- ሕይወትህን መርምር። የምትራበውና የምትጠማው ለምንድን ነው? ጽድቅን የምትራብና

የተራራው ስብከት [እግዚአብሔር የባረከው ሰው ባሕርይ] (ማቴ. 5፡1-12) Read More »

ክርስቶስ ለተከታዮቹ ያቀረበው ግብረገባዊ ትምህርት ማጠቃለያ (ማቴ. 5-7)

ክርስቶስ በማቴ. 5-7 ላይ ያስተማራቸው ትምህርቶች፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ ዐበይት እውነቶች መካከል የሚመደቡ ናቸው። የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 5፡1-2 ኣንብብ። ሀ) ክርስቶስን ስለ መከተል የምንማራቸው ዐበይት ትምህርቶች ምንድን ናቸው? ለ) ከእነዚህ ባሕርያት መካከል ብዙውን ጊዜ ሰዎችን የሚታገሏቸው የትኞቹ ናቸው? አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ። ተመስገን በወንጌላዊነት የሚያገለግል ወንድም ሲሆን፥ ለሌላ ጎሳ ስለ ክርስቶስ እንዲመሰክር ቤተ ክርስቲያኑ ላከችው። እርሱ የተላከባቸው ሰዎች አርብቶ አደሮች ነበሩ። ምንም እንኳ ተመስገን ለእነዚህ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ቢመሰክርም፥ የወንጌል ትምህርቱን ያቀረበበት መንገድ ከእነርሱ አኗኗርና ባሕል የተለየ ነበር። በክርስቶስ በሚያምኑበት ጊዜ ሰውነታችውን እንዲታጠቡ፥ ልብስ እንዲለብሱ፥ መጠጥ እንዲያቆሙ፥ ሁለተኛ ሚስቶቻቸውን እንዲፈቱ አሳሰባቸው። ጌታሁን ለቤተ ክርስቲያን ቅድስና የሚያስብ መጋቢ ነበር። ስለሆነም በሚሰብክበት ጊዜ ሰዎች ከመጠጥ፥ ከዝሙትና ከጫት እንዲታቀቡ እስጠነቀቀ። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድ ሰባኪ ወይም ወንጌላዊ፥ ሰዎች ሊያደርጓቸው የሚገባቸውን ወይም የማይገባቸውን ነገሮች በመዘርዘር ወንጌልን ሲሰብክ የሰማኸው መቼ ነው? ለ) ከማቴ. 5፡1-12 ክርስቶስ ስለ መንግሥት ያቀረበው ስብከት፥ ብዙውን ጊዜ እኛ ወንጌሉን ከምንገልጽበትና ክርስቶስን ስለ መከተል ከምናስተምርበት መንገድ የሚለየው እንዴት ነው? ሐ) ሰዎች መንፈሳዊነትን እንዲማሩ ከመምከር ይልቅ፥ ውጫዊ ተግባራት ላይ በማተኮር ይህን አድርጉ፥ ያን አታድርጉ የሚሉ ዝርዝሮችን ሰጥቶ፥ አፈጻጸማቸውን መለካት የሚቀልለው እንዴት ነው? ማቴዎስ 5-7 ድረስ የተጻፈው ትምህርት ከየትኞቹም ወንጌላት በላይ ሰፋ ብሎ የቀረበ ሲሆን፥ ክርስቶስ ምን ትምህርት እንዳስተማረ ያብራራል። ምሑራን ይህ ትምህርት በኣንድ ስብከት ስለ መጠናቀቁ ይከራከራሉ። ምናልባትም ክርስቶስ ይህን ትምህርት በሁለትና ሦስት ቀናት ውስጥ ለሕዝቡ ያስተማረው ትምህርት አጠቃላይ አሳብ ሊሆን ይችላል። ክርስቶስ ከስፍራ ወደ ስፍራ እየተዘዋወረ ስለሚያስተምር፥ ከእነዚህ እውነቶች ብዙዎቹ በሌሎችም ስፍራዎች ላይደገሙ አልቀሩም። አንዳንድ ምሑራን ማቴዎስ መጽሐፉን በሚጽፍበት ወቅት፥ ክርስቶስ፥ ደቀ መዛሙርቱ ሊኖሩት የሚገባቸውን ሕይወት በአንድ ላይ እንዳሰባሰበ ይናገራሉ። ስለሆነም ምንም እንኳ ማቴዎስ ኢየሱስ ለረዥም ጊዜ በተራራ ላይ ሆኖ ማስተማሩን ቢገልጽም፥ ክርስቶስ በሦስት ዓመት ይፋዊ አገልግሎቱ ጊዜያት ያስተማራቸውን ሌሎች እውነቶችም ጨምሯል። ኢየሱስ በገሊላ በአገለለባቸው ጊዜያት ለደቀ መዛሙርቱ፥ የእርሱ ተከታይ መሆን፥ ፈሪሳውያን ብቁ አይሁዳዊ ስለ መሆን ከሚያስተምሩት ትምህርት የተለየ መሆኑን ኣሳይቷል። ምንም እንኳ ብዙ ሰዎች ትምህርቱን ቢከታተሉም፥ ማቴዎስ እንደሚነግረን፥ ክርስቶስ በተለይ ትምህርቱን ያተኮረው በደቀ መዛሙርቱ ላይ ነበር። ከማቴዎስ 5-7 ድረስ የተጠቀሱትን እውነቶች ክርስቶስ በደቀ መዛሙርቱ ሕይወት ውስጥ ሲተገበሩ ለመመልከት ፍላጎት ነበረው። በየዘመኑ ውስጥ የኖሩ ክርስቲያኖች እነዚህን እውነቶች ተግባራዊ ለማድረግ ታግለዋል። ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ መፈጸም አልተቻላቸውም። አንዳንድ ክርስቲያኖች የእነዚህ ምዕራፎች ትምህርት በተራ ክርስቲያኖች የማይሞከሩ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ብቻ ሊፈጽሟቸው የሚገቡ እንደሆነ አስተምረዋል። ሌሎች ደግሞ ክርስቶስ እነዚህን ትምህርቶች መፈጸም የማይቻል መሆኑን እያወቀ፥ ሰዎች ወደ ጸጋው እንዲመለሱ ለማበረታታት እንዳስተማረ አድርገው ገልጸዋል። የተቀሩት ደግሞ ክርስቶስ እነዚህን ትምህርቶች ለክርስቲያኖች እንዳልሰጠና፥ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ ለሺህ ዓመታት በሚነግሥበት ጊዜ ለሚኖሩት አይሁዶች የታቀዱ እንደሆነ አስረድተዋል። እነዚህ ሁሉ ክርስቶስ ከአስተማረው አስቸጋሪ ትምህርቶችና ደቀ መዛሙርቱ እንዲኖሩት ይፈልግ ከነበረው ሕይወት ለመሸሽ የተደረጉ ጥረቶች ነበሩ። ክርስቶስ እርሱን ለመከተል የሚፈልጉ ሁሉ ራሳቸውን ለእርሱ ሊያስገዙና በተለወጠ ሕይወት የመንግሥቱ አካል እንዲሆኑ ይሻል። ባሕርያቸው፥ ከሌሎች ጋር የሚዛመድበት መንገድና ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት አምልኮ ሁሉ መለወጥ አለበት። የክርስቶስ ተከታይ በሁሉም የሕይወት ዘርፍ ዐቢይ ለውጥ ማሳየት ይኖርበታል። ማቴዎስ 5-7 የተሰጠው ትምህርት ምናልባትም እንደ ክርስቶስ ተከታዮች እንዴት መኖር እንደሚገባን ከኣዲስ ኪዳን ምንባቦች ሁሉ ጥርት ባለ ሁኔታ የሚያስተምረን ክፍል ነው። ምንም እንኳ ይህ በራሳችን ኃይል የማይቻል ቢሆንምና ማናችንም ከመቅጽበት ለመለወጥ ባንችልም፥ ክርስቶስ እንድንኖር የሚፈልገው በዚህ መንገድ ነው። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)

ክርስቶስ ለተከታዮቹ ያቀረበው ግብረገባዊ ትምህርት ማጠቃለያ (ማቴ. 5-7) Read More »

የክርስቶስ የመጀመሪያ ዓመት አገልግሎት ማጠቃለያ (ማቴ. 4፡12-25)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ማቴ. 4፡12-25ን አንብብ። የክርስቶስ የመጀመሪያው አገልግሎት ዐበይት ባሕርያት ምንድን ናቸው? ለ) የክርስቶስ ትምህርት ከመጥምቁ ዮሐንስ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ከማቴ. 3፡2 ጋር አነጻጽር። የክርስቶስ የመጀመሪያ ዓመት አገልግሎት እንደ ቀጣዩ ሁለት ዓመት ጥድፊያ የበዛበት አልነበረም። ማቴዎስ የመጀመሪያውን ቀዳሚ ዓመት አገልግሎቱን አልጠቀሰም። ክርስቶስ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ እንደ ለወጠ ወይም በኢየሩሳሌም ከኒቆዲሞስ ጋር እንደ ተገናኘ ማቴዎስ አልገለጸም። ማቴዎስ ከመጀመሪያው ዓመት ብዙ ሥራዎችን አልፎ፥ ይፋዊ አገልግሎቱን ብቻ በማጠቃለያ መልክ ይጀምራል። ይህንንም ያደርገው መጥምቁ ዮሐንስ ከታሰረበት ዓመት በመጀመር ነው። ምናልባትም ማቴዎስ ታሪኩን በዚህ መልክ የጻፈው፥ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ የመጥምቁ ዮሐንስ «የመንገድ ጠራጊነት» ተግባር እንደ ተጠናቀቀ ለማሳየት ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ መሢሑ መጥቷል። ማቴዎስ ስለ ክርስቶስ የመጀመሪያ አገልግሎት ሲያጠቃልል በቀረው ማጠቃለያ ላይ በአራት ነገሮች ላይ ትኩረትን አድርጓል፡ ሀ. ክርስቶስ በቀዳሚነት በገሊላ ስለ ማገልገሉ በተከታዩ የአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ፥ ክርስቶስ በአብዛኛው ከናዝሬት 25 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኝ በገሊላ ባሕር ጫፍ ላይ በነበረችው የቅፍርናሆም ከተማ አገልግሏል። ከተማይቱ ጠቃሚ በሆነ የንግድ መስመር ላይ ትገኝ ስለነበር፥ በቅፍርናሆም የሚያልፉ ብዙ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ሰምተው ሊያምኑበት ችለዋል። በተጨማሪም ቅፍርናሆም ጴጥሮስንና ማቴዎስን ጨምሮ የብዙ ደቀ መዛሙርት መኖሪያ ነበረች። ማቴዎስን ያስደነቀው ነገር ቢኖር፥ ክርስቶስ በገሊላ የሰጠው አገልግሎት የትንቢት ፍጻሜ መሆኑ ነበር (ኢሳ. 9፡1-2)። ገሊላ በብሉይ ኪዳን ዘመን በዛብሎንና በንፍታሌም ነገዶች ግዛት ውስጥ ትገኝ ነበር። እነዚህ ሁለቱም አካባቢዎች በኢየሩሳሌም በሚኖሩ አይሁዶች ዘንድ የተናቁ ነበሩ። ለዚህም ምክንያት የነበረው፥ በእነዚህ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ አይሁዶች ከአሕዛብ ጋር ተጋብተው ጣዖታቸውንም ያመልኩ ስለነበር ነው። በ722 ዓ.ዓ እስራኤል በአሦር ከተማረከችበት ጊዜ አንሥቶ፥ ይህ የጳለስታይን ክፍል በኣሕዛብ ቅኝ ግዛት ሥር ውሎ ነበር። ከዚህ በኋላ አይሁዶች በመቃባውያን ዘመን በገሊላ ሰፈሩ። እነዚህ አነስተኛ የአይሁድ ቅኝ ግዛቶች እያደጉ የሄዱ ሲሆን፥ ብዙውን ጊዜ በይሁዳ ከሚኖሩ አይሁዶች በላይ ብሔራዊ ስሜት ይሰማቸው ነበር። ይህም ሆኖ፥ በይሁዳ የሚኖሩ አይሁዶች የገሊላ አይሁዶችን ይንቋቸው ነበር። እንኳን መሢሑ አብዛኛውን ጊዜውን በምድር ላይ ማሳለፉ ቀርቶ፥ ምንም መልካም የሆነ ነገር ከገሊላ ይመጣል ብሎ የጠበቀ ሰው አልነበረም። (ዮሐ1፡45-46፤ 1፡41፥ 52 አንብብ።) ምንም እንኳን ገሊላ በብዙ ሰዎች ብትናቅም፥ እንደ ሰው የአገርና የጎሣ ኩራት በማያጠቃው አምላክ ተከበረች። ለ. ኢየሱስ፥ «መንግሥተ ሰማይ ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» እያለ አስተማረ። ማቴዎስ፥ የክርስቶስ መሠረታዊ ትምህርት የመጥምቁ ዮሐንስ ዓይነት መሆኑን አሳይቷል። ይህም ለሰዎች መንግሥተ ሰማይ እንደ ቀረበችና ንስሐ መግባት እንዳለባቸው የሚያሳስብ ትእዛዝ ነበር። መሢሑ በመካከላቸው ስለነበረ፥ ሕዝቡ ሕይወታቸውን መለወጥ ነበረባቸው። ከአሮጌው ሕይወታቸው ተመልሰው ለመሢሑ መንግሥት መዘጋጀት ያስፈልጋቸው ነበር። ሐ ኢየሱስ ሰዎች ደቀ መዝሙሩ ሆነው እንዲከተሉት ጠርቷል። በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው፥ የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ስለ እግዚአብሔር ዐበይት እውነቶችን የሚያስተምሯቸው ደቀ መዛሙርት ነበሯቸው። እነዚህ ደቀ መዛሙርት መምህሮቻቸው ወደሚሄዱበት ሁሉ እየሄዱ ይረዷቸውና ትምህርት ይቀስሙ ነበር፡ ክርስቶስ ይህንን ትውፊት በመከተል ከመጀመሪያው ራሱን እንደ ሃይማኖት መሪ አስተዋውቋል። ክርስቶስ ሰዎች እስኪከተሉት ከመጠበቅ ይልቅ፥ ደቀ መዛሙርቱን ለመምረጥ የአስተዋይነት ምርጫ አድርጓል። ማቴዎስ ክርስቶስ ከመረጣቸው ደቀ መዛሙርት የመጀመሪያ አራቱን ጠቅሷል። የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ፥ ስምዖን ጴጥሮስና እንድርያስ የሚባሉ ወንድማማቾች ሲሆኑ፥ ሌሎቹ ሁለቱ ያዕቆብና ዮሐንስ የሚባሉ ወንድማማቾች ነበሩ። ክርስቶስ ከዚህ በፊት የነበራቸውን ሥራ ትተው እንዲከተሉት ጠራቸው። ዓሣ ማጥመዳቸውን እንዲተዉና የእርሱን ትምህርት ተቀብለው ሰዎችን እንዲያጠምዱ አሳሰባቸው። (ይህንን በዮሐንስ 1 ከሚገኘው ታሪክ ጋር በምናነጻጽርበት ጊዜ፥ አራቱም ደቀ መዛሙርት ለተወሰነ ጊዜ ክርስቶስን ከተከተሉ በኋላ ወደ ቀድሞ ሥራዎቻቸው በመመለሳቸው፥ ክርስቶስን ለመከተል እንደገና የተጠሩ ይመስላል።) በወንጌላት ውስጥ ብዙውን ጊዜ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ስለመሆን ያገለገለው ቃል፥ «መከተል» የሚል ነው። ክርስቶስ ይህን ቃል በመጠቀም በእርሱ የሚያምኑ ሰዎች በሕይወታቸው ላይ ላለው ሥልጣን እንዲገዙ እየጠየቃቸው ነበር። ዕቅዶቻቸውን ትተው የክርስቶስን ፈቃድ መፈጸም ያስፈልጋቸው ነበር። አኗኗሩን፥ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ቅርበት፥ ከሰዎች ጋር የነበረውን ቅርበትና ያገለገለበትን መንገድ መከተል ነበረባቸው። ተከታዮቹ እርስ በርሳቸው ኅብረት ነበራቸው። ይህም ኅብረት ቤተ ክርስቲያን ይባላል። አካሉ በሆነችው ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይሠራሉ። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለጴጥሮስ፥ እንድርያስ፥ ያዕቆብና ዮሐንስ ክርስቶስን የመከተሉ ምርጫ አስቸጋሪ ሊሆን የቻለው እንዴት ነበር? ለ) ከዚህ፣ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ስለ መሆን ምን እንማራለን? ሐ) የክርስቶስ «ተከታይ» መሆንህን እንዴት እያሳየህ እንደሆነ አብራራ። በማቴ 28፡19-20 ላይ፥ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ የራሱን አርአያ በመከተል ሌሎች ደቀ መዛሙርትን እንዲያፈሩ ነግሯቸዋል። በምድር ላይ ከሚገኙ ነገዶች ሁሉ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ማድረግ ይኖርባቸዋል። እያንዳንዱ ክርስቲያን የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን ተጠርቷል። ይህ ምን ማለት ነው? ማቴዎስ ደቀ መዝሙር የክርስቶስን አዲስ የሕይወት ልምምድ ለመቀበል ሲል፥ አሮጌ ሕይወቱን የሚተው ሰው እንደሆነ ይነግረናል። ይህ በቀዳሚነት ስለ ኢየሱስ በመመስከር፥ ደቀ መዛሙርት ይሆኑ ዘንድ «ሰዎችን ማጥመድ»ን ጭምር የሚያካትት ነው። ክርስቶስ እርሱን ለመከተል ሥራችንን እንድንተው አይጠይቀን ይሆናል፤ ይሁንና ሕይወታችንን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ እንድናስገዛ ይፈልጋል። ማቴዎስ ክርስቶስን መከተል ማለት እርሱን ለመከተል ሁሉንም ነገር መተው እንደሆነ አመልክቷል። ይህ ከፍተኛ ዋጋን የሚያስከፍለን እንጂ ቀላል ውሳኔ አይደለም። መ. ኢየሱስ ሲያስተምር፥ ሲሰብክና ሲፈውስ ዝናው እየገነነ መጣ። ማቴዎስ፥ ክርስቶስ ያደረጋቸውን ነገሮች ሁሉ ከመዘርዘር ይልቅ በማቴዎስ 5-7 ላይ በቀረበው የትምህርት አገልግሎቱ ላይ ያተኩራል። ነገር ግን የክርስቶስ ትምህርት የታላቁ አገልግሎት አካል እንደሆነ ለማሳየት ሲል፥ ማቴዎስ የክርስቶስን ተግባራትና የሕዝቡን ምላሽ ጠቅለል አድርጎ ገልጾአል። እንደ ተጻፈው ሁሉ ክርስቶስ በገሊላ ከተማ ውስጥ ከስፍራ ወደ ስፍራ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር። በምኩራብና በሜዳ ላይ ባለማቋረጥ ያስተምር፥ ይሰብክና ይፈውስ ነበር። አንድ ምሑር እንደ ገለጸው፥ «ማስተማር» ኢየሱስ ሰዎች እንዲያውቁ የፈለጋቸውን እውነቶች ማሳወቁን ያመለክታል። ስብከት ደግሞ ክርስቶስ ሰዎች እውነትን ተግባራዊ ለማድረግ ሕይወታቸውን እንዲለውጡ መፈለጉን ያሳያል። ፈውስ ደግሞ ክርስቶስ ለሕዝቡ የነበረውን ርኅራኄ ብቻ ሳይሆን፥ መሢሕ መሆኑንም በይፋ ያሳየበት አገልግሎት ነበር። ከፈውሱ ዓይነት ኣንዱ ከኣጋንንት ነፃ መውጣት ሲሆን፥ ይህም የክርስቶስ መንግሥት የሰይጣንን መንግሥት እያሸነፈ መሆኑን አሳይቷል። ክርስቶስ በዚህ ባሕሪው በሰዎች ዘንድ ተወዳጅነትን እያተረፈ ሊመጣ ችሏል። ከገሊላ በስተ ሰሜን ከምትገኘው ከሶሪያ እስከ ደቡባዊቷ ኢየሩሳሌምና በስተምሥራቅ እስከሚገኙት ዐሥሩ ከተሞች ድረስ ስለ እርሱ ሥራ በሰፊው ይወራ ነበር። ማቴዎስ ክርስቶስ የፈጸመውን ተግባር ጠቅለል ባለ ይዘት ካቀረበ በኋላ፥ በተቀረው የመጽሐፉ ክፍል ሁሉ በክርስቶስ ተአምራትና ዐበይት ትምህርቶች ላይ ያተኩራል። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)

የክርስቶስ የመጀመሪያ ዓመት አገልግሎት ማጠቃለያ (ማቴ. 4፡12-25) Read More »