የሕይወት እንጀራ

የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምሕርት ጥናት

መንግሥተ ሰማያትና የቅጣት ስፍራ

መንግሥተ ሰማያት  መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መንግሥተ ሰማያት ያወሳል (ዘፍጥ. 1፡1፤ ዕብ. 4፡14)፣ ሦስት ሰማያት ያሉ ይመስላል (2ኛ ቆሮ. 12፡2)። ሦስተኛው ሰማይ የጌታ መገኛ ነው። መንግሥተ ሰማያት እርግጠኛ ቦታ እንደሆንና፥ ወደዚያ ለመግባት የሚቻለውም በክርስቶስ በኩል ብቻ መሆኑን ጌታችን ራሱ ተናግሯል (ዮሐ. 14፡1-3)።  ከመንግሥተ ሰማይ ገጽታዎች አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፡- መኖሪያ ነው (ዕብ. 12፡22-24)፥ ውብ ስፍራ ነው (ራእይ 21፡1-22፡7)፥ በዚያ መዋለድ አይኖርም (ማር. 12፡25)፥ ቅዱስ ስፍራ ነው (ራእይ 21፡27)፥ እግዚአብሔርን እናመልክበታለን፥ እናገለግለዋለን፥ ከርሱም ጋር ኅብረት ይኖረናል (ራእይ 4-5)፥ መንግሥተ ሰማይ መግባታችን ስለ ማንኛውም ነገር አዲስ አመላካከት እንዲኖረን ያደርጋል (ኢሳ. 66፡24)።  የቅጣት ስፍራ  የቅጣቱ ቦታ በብሉይ ኪዳን በዕብራይስጥ “ሺኦል” ተብሏል። ትርጉሙም አንዳንዴ መቃብርን ሲያመለክት፥ በሌላ ጊዜ ደግሞ የሞቱ ሰዎች ሁኔታ ከሕያዋን ጋር ተነጻጽሮበታል። የስቃይ (መዝ. 30፡9፤ ዘኁል. 16፡33)፣ የልቅሶ (ኢሳ. 38፡3) እና የቅጣት (ኢዮብ 24:19) ስፍራ እንደሆነ ተቆጥሯል።  አዲስ ኪዳን ውስጥ የኃጢአተኞችን የቅጣት ቦታ የሚያመለክቱ ሦስት ቃላት አሉ፡-  1. “ሄዲስ” በብሉይ ኪዳን ሲኦል ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው። ይህም ያልዳኑ ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ የሚሄዱበትና ትንሣኤያቸውንና በታላቁ ነጭ ዙፋን የሚፈጸመውን ፍርድ የሚጠብቁበትን ቦታ ያመለክታል። “ሄዲስ” ጊዜያዊ ቦታ ነው። በመጨረሻው ቀን እዚያ ያሉ ሰዎች በሙሉ ወደ እሳት ባሕር (ገሃነም) ይጣላሉ።  2. “ታርታሮስ” የሚለው ሌላ ቃል (2ኛ ጴጥ. 2፡4) በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን፥ የወደቁ መላእክት የሚታሠሩበት ስፍራ ነው።  3. ገሃነም፥ “ገኸነም” ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የመጣ ሲሆን ቀደምት ትርጉሙም የሄኖም ሸለቆ ማለት ነው። ይህ ሸለቆ ከኢየሩሳሌም በስተደቡብ ነው የሚገኘው። በዚህ ቦታ ሕጻናት ሞሎክ ለተባለ የጣዖት አምላክ ለመሥዋዕትነት ይቀርቡ ነበር (2ኛ ቆሮ. 33፡6፤ ሐዋ. 7፡43)። በኋላም የከተማው ቆሻሻ የሚጣልበትና የሚቃጠልበት ቦታ ሆነ። በዚህ ምክንያት “ሄኖም” የሚለው ቃል ከዘላለም እሳት ቦታ ጋር ተመሳሳይ ሊሆን ችሏል፡፡ ገሃነም እንደ ጭለማ ስፍራ ይታወቃል (ማቴ. 8፡12)፤ ዘላለማዊ የቅጣትና የስቃይ ቦታ ነው (ራእይ 14፡10-11)።  ያልዳኑ ሰዎች የሚቀጡት እንዲጠፉ በመደረግ አይደለም፤ ወይም ከጥቂት ቅጣት በኋላ ይቅርታ አይደረግላቸውም። ያልዳኑ ሰዎች ቅጣት ዘላለማዊ ነው። በዘላለማዊ ፍርድ (ዕብ. 6፡2) ላይ የተጠቀሰው “ዘላለም” የሚለው ቃል ዘላለማዊውን አምላክ ለመግለጥ አገልግሏል (ራእይ 15፡7)፤ ዘላለማዊ ሕይወት (ዮሐ. 10፡28)፥ ዘላለማዊ ቅጣት (ራእይ 14፡11) ለሚሉ አገላለጦችም ጥቅም ላይ ውሏል። ከእነዚህ አንዱ ብቻ ጊዜያዊ ከሆነ፥ ሌሎችም ይሆናሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር ዘላለማዊ ነው ካልን፥ በእሳት ባሕር መቀጣትም ዘላለማዊ ነው። ጠፍቶ መቅረት፥ ወይም መታደስ የሚል አሳብ አይኖርም። አንዳንድ ሰዎች ሁሉም ያለ ምንም ዓይነት ቅጣት ይድናሉ ብለው ያምናሉ። የእምነታቸው መሠረትም በሐዋርያት ሥራ 3፡21፤ በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፡24-28 እና በቆላስያስ 1፡20 ላይ የተጠቀሰው የተዛባ ትርጉም ነው። እንዲሁም የጻድቃንንና የኃጥአንን ፍጻሜ የሚመለከተውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ችላ በማለት ያልፉታል (ማቴ. 25፡46፤ ዮሐ. 5፡29፤ ሮሜ 2፡8-10፤ ራእይ 20፡10፥ 15)። ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

መንግሥተ ሰማያትና የቅጣት ስፍራ Read More »

ትንሣኤዎች

አሳቡ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ቢያገኝም፥ አንድና አጠቃላይ የትንሣኤ ቀን አይኖርም። ከጊዜ ሳይሆን ከሰዎች አንጻር ሲታይ ሁለት ዓይነት ትንሣኤ እንደሚኖር ይታወቃል። ይህም የጻድቃንና የኃጥአን ትንሣኤ ነው (ሐዋ. 5፡28-29፤ ሉቃስ 14፡14)። በሞትና በትንሣኤ መካከል ባለው ጊዜ ጻድቃንም ሆን ኃጥአን “በነቃ ሕሊና” ይኖራሉ። አማኙ በዚህ ጊዜ ከጌታ ጋር ሲሆን (2ኛ ቆሮ. 5፡1-8፤ ፊልጵ. 1፡23)፣ የማያምኑት በስቃይ ይኖራሉ (ሉቃስ 16፡19-31)።  የጻድቃን ትንሣኤ  የጻድቃን ትንሣኤ የመጀመሪያው ትንሣኤ ሲባል፥ ይህም በተለያየ ደረጃ የሚሆን እንጂ፥ በአንድ ጊዜ የሚፈጸም አይደለም። በክርስቶስ የሞቱት ከቤተ ክርስቲያን ጋር አስቀድመው ይነጠቃሉ (1ኛ ተሰ. 4፡16)። በፍዳው ዘመን የሚዋጁትና በዚያው ዘመን የሚሞቱ ከሺህ ዓመቱ አገዛዝ በፊት ይነሳሉ (ራእይ 20፡4)። በብሉይ ኪዳን የተዋጁትም በጻድቃን ትንሣኤ የመካፈል ዕድል ይኖራቸዋል። እርግጥ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች፥ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን የሚነሱበትን ጊዜ በተመለከተ ያላቸው አሳብ የተለያየ ነው። አንዳንዶቹ በቤተ ክርስቲያን መነጠቅ ጊዜ ከቅዱሳን ጋር ይነሳሉ ሲሉ፥ ሌሎቹ ደግሞ ትንሣኤያቸው በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ይሆናል ይላሉ (ዳን. 12፡2)። ጸሐፊው ሁለተኛውን አመለካከት ይደግፋል።  የኃጥአን ትንሣኤ  ስለ ነጩ ዙፋን ፍርድ ስናጠና እንደተመለከትነው፥ ያልዳኑ ሰዎች ከሺህ ዓመቱ በኋላ ይነሱና ወዲያው ይፈረድባቸዋል፤ ከዚያም ለዘላለም ወደ እሳት ባሕር ይጣላሉ (ራእይ 20፡11-15)። በትንሣኤያቸውም የእሳት ባሕር ስቃይ ሊሰማው የሚችልና ለዘላለም የሚኖር ልዩ አካል ይሰጣቸዋል። ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

ትንሣኤዎች Read More »

የወደፊቱ ፍርድ

ፍርድ አማኞች ሥራ ላይ  ቤተ ክርስቲያን በመለውጥና በትንሣኤ ወደ ሰማይ ከተወሰደች በኋላ፥ እያንዳንዱ አማኝ በክርስቲያንነቱ ባከናወነው ሥራ መጠን ፍርድ ይሰጠዋል (1ኛ ቆሮ. 3፡11-15)። ፍርዱ ድነትን (ደኅነትን) እና የመንግሥተ ሰማያትን እርግጠኝነት የሚያመለከት ሳይሆን፣ ክርስቲያኑ መንግሥተ ሰማይ የሚገባው ከሽልማት ጋር፥ ወይም ያለ ሽልማት መሆኑን የሚመለከት ብቻ ይሆናል። አማኞች ፈተናውን ባለማለፋቸው ለስልክት ባይበቁም፥ ነፍሳቸው ግን እንደምትድን ጳውሎስ በጥቅሱ ውስጥ ግልጥ አድርጎታል (ቁ. 5)። እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ፥ ኃጢአቱ ይቅር የተባለለት ሰው እንዴት ለሥራው እንደገና በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ይቀርባል? የሚል ነው። ይቅርታ የመጽደቅን እርግጠኛነት ሲያሳይ፥ በሥራ መፈተኑ ግን ሽልማትን ያመለክታል። ከዚህ በኋላ ኅዘን ወይም ልቅሶ በመንግሥተ ሰማያት አይኖርም። ብዙ ጊዜ ሽልማቱ ምን እንደሚሆን ለማወቅ እንጓጓለን። መንግሥተ ሰማያት፣ መንግሥተ ሰማያት እስከሆነ ሽልማቱ ምን ልዩነት ያመጣል? በመጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ መልስ አልተሰጠም፤ ሽልማቶቹ ለክርስቲያን አገልግሎት ማነቃቂያ መሆናቸው ብቻ ነው የተገለጠው። ሽልማቱ ለምን ለምን አገልግሉት መሆኑ ግን ተጽፏል። ሰዎችን ወደ ክርስቶስ በማምጣት የደስታ አክሊል ይሰጣል (1ኛ ተሰ. 2፡19)፥ መገለጡን ለሚወዱ የጽድቅ አክሊል (2ኛ ጢሞ. 4:8)፥ ለጌታ ሲሉ መከራን ለሚታገሱ የሕይወት አክሊል (ያዕ. 1፡12)፥ እና በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ታማኝ ለሚሆኑ ሽማግሌዎች የከብር አክሊል ይሰጣቸዋል(1ኛ ጴጥ. 5፡4)።  በፍዳው ዘመን ውስጥ የሚያልፉ አሕዛብ የሚጠብቃቸው ፍርድ  አንዳንድ ሰዎች በፍዳው ዘመን በሕይወት የሚዘልቁ ሲሆን፥ እነርሱም የሺሁ ዓመት አገዛዝ ከመጀመሩ በፊት ይፈረድባቸዋል። የፍርድ ጊዜ መቼ መሆኑ ተጠቅሷል፡- “የሰው ልጅ በክብር በሚመጣበት ጊዜ” (ማቴ. 25፡31-46)። ፍርዱ በመሬት ላይ፥ ኢዮሳፍጥ ሸለቆ ውስጥ ይሆናል (ኢዩኤል 3፡2)። ይህ ሸለቆ ምናልባት በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ጊዜ በሚነሳ የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ በኢየሩሳሌም አካባቢ የሚፈጠር ይሆናል (ዘካ. 14፡4)። በብሉይ ኪዳን ምንባቦች ላይ “ጎይ” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ትርጉሙም “ሕዝብ”፥ “አረመኔ” “መንግሥታት”፣ እና ብዙ ጊዜም “አይሁድ ያልሆነ” ማለት ነው። የአዲስ ኪዳን ምንባቦች ደግሞ “ኤትኖስ” የሚለውን የግሪክ ቃል ተጠቅመዋል። ይህም ብዙውን ጊዜ “አይሁድ ያልሆነ” በሚል ይተረጎማል። (ለምሳሌ ያህል ሮሜ 11፡11-12፥ 25ን ይመልከቱ።) ጻድቅ መንግሥት እስከሌለ ድረስ፥ እዚህ ላይ የተጠቀሰው ፍርድ የግለሰቦች ፍርድ መሆን አለበት። ስለዚህ በዚህ ጥቅስ ላይ ቃሉ “አይሁድ ያልሆነ” በሚል ቢተረጎም የተሻለ ይሆናል።  የእነዚህ አሕዛብ ፍርድ የሚጀምረው ጌታ “ወንድሞቼ” ለሚላቸው ወገኖች ምን እንዳደረጉላቸው በመጠየቅ ይሆናል (ማቴ. 25፡40)። ማንነታቸው የሚወሰነውም እነሱን ደረጃ በደረጃ በማስወገድ ይሆናል። ክርስቶስ ዳኛ ከሆነ፥ ቤተ ክርስቲያን ከፍዳው ዘመን በፊት ከተነጠቀች፥ የሚፈረድባቸውም አሕዛብ ከሆኑ፥ በፍዳው ዘመን የሚቀሩት ሌሎች ወገኖች እይሁዳውያን ብቻ ይሆናሉ (በሥጋ “ወንድሞቹ”)። በዚያ ዘመን አይሁዳውያን በታላቅ ስደት ውስጥ ያልፋሉ። መልካም የሚያደርግላቸው፥ ጓደኛ የሚሆናቸው ሁሉም መጥፎ ይገጥመዋል። ከዚህ የተነሳ በሰብአዊነት የተነሳሱ ሰዎች አይሁዳውያኑን ማብላት፥ ማልበስ፥ ወይም መጎብኘት አይችሉም። ይህን የሚያደርጉ በከባድ ጥርጣሬ ይታያሉ፤ ከዚያም አልፎ እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት ይመጣባቸዋል። እነዚህን በጎ ድርጊቶች የሚፈጽም ሰው ካለ በዚያ ሕይወት አዲስ ለውጥ ለመኖሩ ማስረጃ ይሆናል። በሌላ አነጋገር እነዚህ አሕዛብ ለአይሁድና ለክርስቶስ ወንድሞች የሚያደርጉት መልካም ሥራ፥ የዳግም መወለዳቸው ምልክት ነው። ዳግም በመወለዳቸው ይድናሉ፤ መልካምም ተግባራቸው የመወለዳቸው ማረጋገጫ ይሆናል።  ሕይወታቸው ይህን የአዲስ ልደት ማረጋገጫ የሚያሳይ ሁሉ የመንግሥቱ ዜጎች ይሆናሉ (ማቴ. 25፡34)። ሥራቸው ለዘላለም ሕይወት የማያበቃቸው ደግሞ፥ ወደ እሳት ባሕር ይጣላሉ (ቁ. 41)። የመንግሥቱ ዜጎች የሚሆኑት ወደ መንግሥቱ የሚገቡት በሥጋዊ አካላቸው ስለሆነ ይጋባሉ፥ ይዋለዳሉ፥ በሺህ ዓመት መንግሥት ጊዜ ምድርን የሚሞሏት እነርሱ ናቸው።  የመከራውን ዘመን አልፈው የወጡ አይሁዳውያን ፍርድ  የመከራውን ዘመን አልፈው የወጡ አይሁዳውያንም ይፈረድባቸዋል (ሕዝ. 20፡34-38)። ጌታም ይህ ፍርድ እርሱ ከተመለሰ በኋላ እንደሚሆን በምሳሌ ተናግሯል (ማቴ. 25፡14-30)። ያልዳኑ አይሁዳውያንን ከሺህ ዓመቱ መንግሥትና ከዘላለም ሕይወት ማስወገድ ይሆናል፤ ማንኛውም ዓመፀኛ የሺህ ዓመቱ ተሳታፊ አይሆንምና (ሕዝ. 20፡37፤ ማቴ. 25፡30)።  የወደቁ መላእክት ፍርድ  ሰይጣንም በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ጊዜ ይፈረድበታል። በሺህ ዓመቱ አገዛዝ ወቅት፥ በጥልቁ ውስጥ በእሥር ቆይቶ በመጨረሻ ለጥቂት ጊዚ ዓመፅ ካካሄደ በኋላ፥ ለዘላለም ወደ እሳት ባሕር ይጣላል (ራእይ 20፡2-3፣ 7፥ 10)። መጀመሪያ በእግዚአብሔር ላይ ባመፀ ጊዜ የተከተሉት አጋንንትም ከሱ ጋር ይፈረድባቸዋል። ይህ ጊዜ ነው “ታላቁ ቀን” ተብሎ የሚጠራው (ይሁዳ 6)። ይህ ጊዚ ምናልባት በሺህ ዓመት ማብቂያ (የጌታ ቀን መጨረሻ) ሰይጣን ፍርዱን ለመጨረሻ የሚያገኝበት ይሆናል። አማኞችም ይህን ፍርድ በማስፈጸም ተግባር የሚሳተፉ ይመስላል (ኛ ቆሮ. 6፡3)።  ያልዳኑ ሙታን ፍርድ (በነጩ ዙፋን ፊት) (ራእይ 20፡11-15)  በሺህ ዓመቱ መጨረሻ የአሁኑ ከዋክብታማ ሰማይና ምድር ስለማይኖሩ፥ ህዋ ላይ ታላቅ ነጭ ዙፋን ይዘጋጃል። ከዚያ ላይ የሚቀመጠውም ክርስቶስ ይሆናል (ዮሐ. 5፡22)። የሚፈረድባቸው በዘመናት የሞቱ ኃጥአን ናቸው። የዳኑት ቀደም ሲል ከሞት ተነስተው ፍርድ ስላገኙ ያልዳኑት ብቻ ናቸው የቀሩት (ራእይ 20፡12)።  ሕዝቦች የሚፈረድባቸው እንደ ሥራቸው ነው (ቁ. 12-13)። ወደ ፍርድ የገቡት ባለመዳናቸው ነውና፥ እዚያ እስከሆኑ ድረስ በሥራቸው ይፈርድባቸዋል። የሕይወት መጽሐፍ ሲከፈት፥ በዙፋኑ ፊት ከሚቆሙት ያልዳኑ ሰዎች የአንዱም ስም አይገኝም። አዳኙን አለመቀበላቸው ከሕይወት መጽሐፍ ውጭ አድርጓቸዋል። በሕይወታቸው ዘመን የሠሯቸው ክፉ ሥራዎች ዘላለማዊ ቅጣት እንደሚገባቸው ያረጋግጣሉ።  ሆኖም እግዚአብሔር ለእነዚህ ሕዝቦች አንድ የመጨረሻ ዕድል በመስጠት ምሕረቱን ያሳየ ይመስላል። ምንም እንኳን ስማቸው በሕይወት መጽሐፉ ውስጥ ባይገኝም፥ በምድር ላይ በነበሩ ጊዜ የሠሩት ሥራ ወደ እሳት ባሕር የማያስጨምራቸው መሆኑን እንዲያሳዩ ዕድል ይሰጣቸዋል። ሁኔታው በገሃነም የተለያየ ደረጃ ያላቸው ቅጣቶች መኖራቸውን ያመለክታል (ሉቃስ 12፡47-48ን ይመልከቱ)። ለፍርድ የሚቀርቡ ሁሉ ተመሳሳይ ቅጣት ይጠብቃቸዋል፤ ያም ወደ እሳት ባሕር መጣል ነው። ይህ ሁለተኛ ሞት ሲባል፥ ለዘላለም ከእግዚአብሔር መለየትን ያመለክታል። ሞት (አካል የሚነጥቀው)፥ እና ሲኦል (ነፍስ የሚነጥቀው)፥ አገልግሎታቸው ስለሚያበቃ ወደ እሳት ባሕር ይጣላሉ። ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

የወደፊቱ ፍርድ Read More »

የዘመኑ መጨረሻ

ሰውና ሰይጣን በእግዚአብሔር ግዛት ላይ የሚያሳዩት ዓመፅ ሁሉ በሺህ ዓመት ማብቂያ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ይታያል። እግዚአብሔር በሺሁ ዓመታት ውስጥ መልካምን ነገር ሁሉ ለሰዎች በመስጠት ምድር በጌታ እውቀት እንድትሞላ ያደርጋል። ከዚህ ሁሉ በረከት በኋላ ሰዎች እግዚአብሔርን በግልጥ መቃወማቸው ስለሚከሰት፥ ውጫዊ ለውጥ የሰውን መሠረታዊ ፍላጎት የማያሟላ መሆኑ ይረጋገጣል። ሰው በዳግም ልደት የልብ ለውጥ እስካላደረገ ድረስ ውስጡ ዓመፀኛ እንደሆነ ይኖራል። በዘመኑ መጨረሻ ከሚወለዱት ልጆች ብዙዎቹ የንጉሡን (የክርስቶስን) ጸጋ ለመቀበል አይሹም። ውጫዊ ሁኔታቸው ሲታይ ግን ለክርስቶስ የሚገዙ ይመስላሉ። ነገር ግን በዘመናት ሁሉ እንደታየው፥ ሰዎች አዳኙን እንዲቀበሉ እግዚአብሔር አያስገድድም። ብዙ በሺህ ዓመቱ አገዛዝ ማብቂያ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ከርስቶስን እንደ መንግሥቱ ገዥ በማየት ቢታዘዙትም፥ ለደኅንነታቸው አልተቀበሉትም።  ሰይጣን ሲፈታ ነው በክርስቶስ ላይ የሚካሄደው ዓመፅ የሚጀምረው (ራእይ 20፡7-9)። ሰይጣን ሲፈታም መንግሥታትን ያስታል (ከመታሠሩ በፊት እንደነበረም)፤ በተጽዕኖውም ዓለምን ያዳርሳል። ዓመፀኞች ኃይላቸውን አስተባብረው የክርስቶስ አስተዳደር ማዕከል የሆነችውን ኢየሩሳሌም ለመውረር ሲዘጋጁ፤ ሰይጣንም ለዓመፅ ይጠናከራል። እነርሱም ቅድስቲቱን ከተማ ለማጥቃት ሲቃጡ፥ እግዚአብሔር ከሰማይ እሳት በመላክ ያጠፋቸዋል። የዓመፃው ተባባሪዎች ሁሉ በእሳት ይጠፋሉ። ይህም በጌታ ላይ የሚነሳውን ተቃውሞ ለዘላለም ያስወግዳል። ሰይጣንም ወደ እሳት ባሕር ይጣል (ራእይ 20፡10)። ይህ የመጨረሻው ዓመፅ ተሀድሶ ከዳግም ልደት፥ መሻሻልም ከመለወጥ ጋር አንድ አለመሆናቸውን ያመለክታል። የመለኮታዊ ጸጋ አሠራር የሚያስፈልገው የሰው ልጅ ልብ መሆኑን በድጋሚ ያረጋግጣል።  ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

የዘመኑ መጨረሻ Read More »

የሺህ ዓመት ግዛት

መለያዎቹ  የሺህ ዓመት ግዛት የሚባለው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ለ1000 ዓመት በጽድቅ የሚገዛበት እና የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃሎች ለአይሁድና ለዓለም ሁሉ የሚፈጸሙበት ጊዜ ነው። የዚህ የአገዛዝ ዘመን ርዝመት 1000 ዓመት መሆን፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው በአንድ ምዕራፍ ቢሆንም (ራእይ 20 በምዕራፉ ውስጥ 6 ጊዜ ተደጋግሞ ተጠቅሷል)፤ በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ስለዚህ መንግሥት የሚነግሩን ብዙ ጥቅሶች አሉ። ስለዚህ ይህ ትንቢት አንዳንዶች እንደሚሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፥ ለዚያውም ለመተርጎም በሚያስቸግር አንድ ምዕራፍ የተወሰነ አሳብ አይደለም።  መንግሥቱ በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ አኳኋን ተገልጧል። “በጌታ ጸሎት ውስጥ የሚመጣ መንግሥት” ተብሎ ተጠቅሷል (ማቴ. 6፡10)። “የእግዚአብሔር መንግሥት” (ሉቃስ 19፡1) “የከርስቶስ መንግሥት” (ራእይ 11፡15)፣ “ዳግም መወለድ” (ማቴ. 19፡28)፥ “የመጽናናት ዘመን” (ሐዋ. 3፡19)፥ “የሚመጣው ዓለም” (ዕብ. 2፡5) ተብሏል። ጌታችን በሉቃስ 19፡11-27 በጠቀሰው ምሳሌ፥ የሺህ ዘመኑ መንግሥት በፍጥነት እንደማይመሠረትና ከዚያ በፊት ሌላ ነገር (ማለት ቤተ ክርስቲያን) በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ቀዳሚ ድርሻ እንደሚኖራት ያመለክታል።  አስተዳደሩ  የሺህ ዓመት መንግሥት የሚመሠረተው በምድር ላይ ነው (ዘካ. 14፡9)። በፍዳ ዘመን ከሚከሰቱ አስከፊ ፍርዶች የተነሳ (የምድር መናወጥ፣ የአየር መለወጥ ወዘተ.) የዓለም ፊትና ገጽታ ይለወጣል። ኢየሩሳሌም የመንግሥቱ ማዕከል ትሆናለች (ኢሳ. 2፡3)። ከፍ ከፍ ትላለች (ዘካ. 14፥10)፤ ታላቅ የክብር ቦታ ትሆናለች (ኢሳ. 24፡23)፤ የመቅደሱ ስፍራ እዚያ ይሆናል (ኢሳ. 33፡20)፤ ለዓለም ሁሉ የደስታ ምንጭ ትሆናለች (መዝ. 48፡2)። ከተማይቱ አሁን የክርክርና የግጭት ስፍራ ብትሆንም፥ በሺህ ዓመቱ ግዛት ጊዜ ግን ለደኅንነቷ የማትሰጋ ትሆናለች (ኢሳ. 26፡1-4)። ከዚያች ከተማ ሕግ ይወጣል። ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድርም እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች (ኢሳ. 2፡3፥ 11፡9)።  የሺህ ዓመቱ መለኮታዊ አገዛዝ ንጉሥና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይሆናል። ምድርን ሁሉም ይገዛል (ዳን. 1፡14)፤ ፍጹምና ሙሉ ፍትህ ለሁሉም ያሰፍናል። ኃጢአትን ይቀጣል (ኢሳ. 11፡44 65፡20)፤ በፍጹም በጽድቅ ይፈርዳል (ኢሳ. 11፡3-5)። ይህ በምድር የሚከናወን የሰላም ምስጢር፥ ገዥው ሰላምን በጽድቅ የሚያሰፍንበት ይሆናል። ምናልባት ጌታ ከሞት የሚነሳውን ዳዊትን፥ ለመንግሥቱ እንደ አለቃ ይገለገልበት ይሆናል (ኤር. 30፡9፤ ሕዝ. 37፡24-25)። ከንጉሡ ሥልጣን ሥር ልዑል ይሆናል።  በአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ላይ የሚሾሙት አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ይሆናሉ (ማቴ. 19፡28)፤ ሌሎችም ልዑላንና መሳፍንት ሆነው በዚህ አገዛዝ ይካፈላሉ (ኤር. 30፡21፤ ኢሳ. 32፡1)። ሌሎችም ጻድቃን በዚህ የሺህ ዓመት ግዛት የተለያዩ ኃላፊነቶች ይቀበላሉ (ሉቃስ 19፡11-27)።  የዚህ ምድራዊ መንግሥት ተገዢ የሚሆኑት፥ የፍዳውን ዘመን አልፈው በምድራዊ አካላቸው የሚገኙ አይሁድና አሕዛብ ይሆናሉ። በመጀመሪያው ጊዜ በዚህ መንግሥት ውስጥ አንድም ያልዳነ ሰው ያለ አይመስልም። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆዩ አያሌ ሕፃናት ይወለዳሉ፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ይህ መንግሥት በብዙ ወጣቶች ይሞላል። ከእነዚህ መካከል ግማሾቹ ክርስቶስን እንደ አዳኛቸው ሲቀበሉ ሌሎች ግን አይቀበሉትም። እነዚህ ሁሉ፣ በክርስቶስ ዳግም የተወለዱትም ሆኑ ያልተወለዱት ለንጉሡ ፍጹም ታማኞች መሆን ግዴታቸው ነው። ቤተ ክርስቲያን የትንሣኤ አካል የሚኖራት ሲሆን ከክርስቶስም ጋር አብራ ትገዛለች። የሥጋዊ ውሱንነት፥ የምግብ፥ የቦታ፥ የመንግሥታዊ እና ሌሎች ችግሮች አይኖሩባትም። በሺህ ዓመቱ አገዛዝ ወቅት የቤተ ክርስቲያን ትክክለኛ መኖሪያ አዲሲቷ ኢየሩሳሌም ትሆናለች (ራእይ 21፡2፥ 9-10)።  መንፈሳዊ ባሕሪው  የሺህ ዓመቱ አገዛዝ ምድራዊ ነውና መንፈሳዊ ሊሆን አይችልም፣ የሚል እና ይችላል የሚል አከራካሪ አሳብ አለ። በመሠረቱ ግን በሁለቱ አሳቦች መካከል ግጭት ሊኖር ባልተገባ ነበር። ዛሬ በምድር የሚኖር ክርስቲያን መንፈሳዊነት ይጠበቅበታል። በሺህ ዓመቱ አገዛዝ ዘመንም እግዚአብሔር ምድራዊና መንፈሳዊ የሆነውን ነገር በማጋጠም በምድር ላይ የራሱን ክብር በሙላት ይገልጣል። መንግሥቱም ከፍተኛ መንፈሳዊነት ይታይበታል።  ከመንግሥቱ መንፈሳዊ ባሕርያት ውስጥ ጥቂቶቹ የሚከተሉት ይሆናሉ። ጽድቅ ያብብበታል (ኢሳ. 11፡3-5)፥ ሰላም ይሰፍናል (ኢሳ. 2፡4)፥ መንፈስ ቅዱስ ለየት ባለ መንገድ ይሠራል (ኢሳ. 61፡3፤ ኢዮብ 2፡28-29)፥ ሰይጣን ይታሠራል (ራእይ 20፡2-3)። አንዳንዶች በሺህ ዓመት ግዛት የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደገና ይሠራና የእንስሳት መሥዋዕት የሚቀርብበት የአምልኮ ስፍራ ይሆናል ብለው ያምናሉ። ሕዝቅኤል 40-46 ይህን የሚያመለክት ቢመስልም ክርስቶስ በምድር እስካለ ድረስ መሥዋዕቱ ምን ያደርጋል? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። በአገዛዙ ወቅት የሚኖረው መንፈሳዊ አምልኮ ምን እንደሚመስል ሙሉ በሙሉ መረዳቱ ስለሚሳነን፥ ዛሬ ለዚህ ጥያቄ መልስ አናገኝለት ይሆናል።  ማኅበራዊ ፍትሁ  ጽድቅና ፍትህ የሚነግሡበት ይሀ የሺህ ዓመት አምላካዊ አገዛዝ የማኅበራዊ ፍትህንም ይጨምራል። ፍርድ ቤቶች እንደተለመደው ስሕተት በተሞላበት የዓይን ምስክሮች ግንዛቤና ቃል ሳይሆን፥ በራሱ በክርስቶስ ሙሉ እውቀት በትክክል ይዳኛሉ (ኢሳ. 11፡3-5)። ማንኛውም ወንጀል ያለቅጣት አይታለፍም። ጭቆናም ጨርሶ አይፈቀድም፤ ለሕግ ማስፈጸሚያ የሚያስፈልገው ክፍያ በጣም ይቀንሳል። ሰላም በዓለም ስለሚሰፍን ወታደራዊ ወጪዎች ሁሉ ይሰረዛሉ።  መሬት እጅግ ፍሬያማ ትሆናለች (ኢሳ. 35፡1-2)፤ ምንም እንኳን ሺሁ ዓመት እስኪፈጸምና ሞት ለዘላለም እስኪሻር ድረስ ሙሉ በሙሉ ባይሰረዝም፥ ምድር በአዳም ኃጢአት ምክንያት የተጣለባት እርግማን ይነሳላታል (ዘፍጥ. 3፡17)። በቂ ዝናብ ኖሮ የምግብ አቅርቦት ስለሚጨምር፥ ታላቅ የብልጽግና ዘመን ይሆናል። የክርሰቶስም የጽድቅ አገዛዝ ለሰዎች ባመረቱት፣ ወይም በአገልግሎታቸው መጠን ተገቢውን ክፍያ ያስገኝላቸዋል። ሰላም በምድር ሰፍኖ ብልጽግናና ማኅበራዊ ፍትህ ይሰፍናል።  ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

የሺህ ዓመት ግዛት Read More »

የፍዳው ዘመን [Tribulation]

በመጽሐፍ ቅዱስ፥ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከሌሎች ትምህርቶች ይልቅ ስለ ፍጻው ዘመን በስፋት ተጽፎ እናገኛለን።  የጊዜው እርዝማኔ  ዘመኑ በትልቁ የዳንኤል ትንቢት ሰባኛ ሳምንት ይሆናል (ዳንኤል 9፡24-27)። የዚህም ግማሽ ጊዜ 42 ወራት ወይም 1260 ቀናት እንደሚሆን ተጠቅሷል (ራእይ 11፡2-3)። ምንም እንኳን በብዙ አገሮች ወራት የተለያዩ ቀናት ቢኖሯቸውም፥ በብሉይ ኪዳን ጊዜ (ዛሬ በኢትዮጵያም እንደሚታየው) አንድ ወር 30 ቀናትን መያዙ ይታወቃል (ዘፍጥ. 7፡11፥ 24፤ 8፡4፤ ዘኁል. 20፡29፤ ዘጸግ. 34፡8፤ 21፡13)። ይህ 7 ዓመት ለሁለት እኩል የሚከፈለው በዳንኤል 9፡27 መሠረት የሚደረገው ቃል ኪዳን ሲፈርስ ነው። ሁለቱም ክፍሎች ታላቅ ስደትና የደም መፍሰስ የሚታይባቸው ይሆናሉ።  የፍዳው ዘመን ልዩ ገጽታ  የፍዳ ዘመን ከዓለም ታሪክ ሁሉ ልዩ እንደሚሆን ጌታችን ተናግሯል (ማቴ. 24፡21)። እርግጥ ይህ ቃል ከተነገረ ወዲህ ብዙ አስከፊ ጊዜያቶች አልፈዋል። እንዲያውም ጌታ ራሱ ተከታዮቹን በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ብሏቸዋል (ዮሐ. 16፡33)። ታዲያ የሚመጣውን የፍዳ ዘመን እጅግ ልዩ የሚያደርገው ምን ይሆን?  የፍዳውን ዘመን፥ ዓለም ከዚህ በፊት ካያቸው መከራና ፍርዶች የተለየ የሚያደርጉት ሁለት ባሕርያት አሉ። በመጀመሪያ ፍዳው ዓለምን ሁሉ የሚያዳርስ እንጂ፥ በአንድ ቦታ የሚወሰን አይደለም (ራእይ 3፡10)። ስለሆነም በተለያዩ ቦታዎች ሰዎች በተናጠል የሚደርሱባቸው ስቃዮች የፍዳ ዘመንን መምጣት አያመለከቱም። ምክንያቱም መከራው በጊዜው በዓለም ሁሉ ነው የሚሆነው። የፍዳውን ዘመን ልዩ የሚያደርገው ሌላ ነገር፥ ሰዎች የዓለም ፍጻሜ መቅረቡን መረዳታቸው ብቻ ሳይሆን በሥራቸውም ሁሉ የሚመሰክሩ በመሆኑ ነው። በመጀመሪያ ፍርድ ወቅት ሰዎች ራሳቸውን በጎሬ፥ በዋሻ በተራሮች፥ ለመደበቅ ይፈልጉና በላያችን ውደቁ፥ በዙፋኑም ከተቀመጠው ፊት፥ ከበጉም ቁጣ ሰውሩን” ይላሉ (ራእይ 6፡16)። ሰዎች ስለ መጨረሻው ዘመን መቃረብ ብዙ ከማውራታቸው ጋር፥ አርማጌዶን የሚለውን ቃል እንደ ፍጻሜው ምልክት ይወስዱታል። ይሁን እንጂ ፍጻሜው መድረሱን የሚያምኑ መሆናቸውን በድርጊት አይገልጡም። ሕይወት ያለማቋረጥ እንደምትቀጥል በማመን የንግድ ልውውጥ፥ የገንዘብ ክምችትና የሕንፃዎች ግንባታ ያካሂዳሉ። የፍዳው ዘመን ሲመጣ ግን የሚያጓጓ ነገር አያዩምና ሰዎች ከሕይወት ሞትን ይመርጣሉ።  አገላለጡ  የመከራው ዘመን የሚጀምረው፥ የምዕራብ መንግሥታት ፌዴሬሽን መሪ የሆነው የዓመፅ ሰው ከአይሁዳውያን ጋር የትብብር ስምምነት ሲፈራረም ነው (ዳን. 9፡27)። በቤተ ክርስቲያን መነጠቅና በስምምነቱ መካከል ጊዜ ቢኖርም፥ መነጠቁ ግን ከዚያ ቀደም ብሉ ይፈጸማል፡፡ የሰባት ዓመቱ ጊዜ መቆጠር የሚጀምረው ልክ ይህ ስምምነት ሲፈረም ነው። በራእይ 6፣ 8፣ 9፣ 16 ሦስት ተከታታይ ፍርዶች ተጽፈዋል። ምናልባት አንዱ አንዱን እየለጠቀ በየተራ ይከናወኑ ይሆናል። እንዲያ ከሆነ በምዕራፍ 6 ላይ የተጠቀሱት የማኅተሙ ፍርዶች፥ በፍዳው ዘመን መጀመሪያ ዓመታት ላይ የሚከናወኑ ይሆናሉ። እነርሱም ጦርነትን፥ ረሃብን፥ ሞትን፥ መሥዋዕትነትንና በዓለም የተፈጥሮ ሚዛን መመሰቃቀልን ያካትታሉ።  ከዚህ ጊዜ ጥቂት ቀደም ብሉ አንዲት ዓለም አቀፋዊ ሐሰተኛ ቤተ ክርሰቲያን ገናና ትሆናለች (ራእይ 17፡3)፤ በዓለም መንግሥታት ላይም ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ታሳድራለች። ለዚህ ዓላማ በታተሙ ሰዎች ምስክርነትም ብዙ ሰዎች ይለወጣሉ (ራእይ 7)። አንዳንዶች ግን ስለ እውነተኛ እምነታቸው ወዲያውኑ ይሰዋሉ (ራእይ 6፡9-11)። ይህን ሁሉ ጌታ በደብረ ዘይት ስብከቱ ገልጦታል፥ (ማቴ. 24፡4-14፥ ስለ ፍርዱ ቁ. 6-7፣ ስለሚሰውት ቁ. 9፥ ስለ ምስክርነት ቁ. 14)።  በፍዳው ዘመን አጋማሽ ላይ አንዳንድ ታላላቅ ድርጊቶች ይከናወናሉ። ግብፅ በዓመፁ ሰው ሠራዊት ድል ትሆናለች (ዳን. 11፡40-43)። በፍዳ ዘመን መጨረሻ የሩቅ ምሥራቅ አገሮች አንድ ግንባር ይፈጥሩና ወደ ፍልስጥኤም ይዘምታሉ። ከሰሜን የሚነሳ ጎግ ማጎግ የተባለ ኃይል እስራኤልን ይወራል። ሆኖም በእግዚአብሔር መለኮታዊ ኃይል ይጠራረጋል (ሕዝ. 38-39)። ልክ በመካከሉ የዓምፁ ሰው ከእስራኤል ጋር የነበረውን ስምምነት ያፈርስና የእስራኤል ጠባቂ በመሆን ፋንታ፥ እንደ አምላክ እንዲመለክ ይፈልጋል (2ኛ ተሰ. 2፡4)። ዓለምን ሁሉ ድል ለማድረግ ይሻል። በዚህ ጊዜ የመጨረሻው የፍዳ ዘመን ስለሚቃረብ እግዚአብሔር ተመጨሪ የፍርድ ጽዋውን በምድር ላይ ያፈሳል። እነዚህ ሁሉ በራእይ 8-9 መለከቶችና በምዕራፍ 16 ጽዋዎች ተገልጠዋል። እነዚህ የተፈጥሮን ሚዛን የሚያመሰቃቅሉ ናቸው። ሰዎች የሚጠጡት ውኃ አይኖርም፥ ብዙዎች ይሞታሉ፥ ሰይጣናዊ ስደት ይነሳል፥ ሕመምና ቁስል፥ የከፋ መመሰቃቀል ይከሰታል። የዓመፅ ሰው ዓለምን ለመቆጣጠር ሲገሰግስ በስተምሥራቅ ከሚነሳው ጠላቱ ጋር ከፍልስጥኤም በስተሰሜን ከሚገኝ አርማጌዶን ላይ ጦርነት ይገጥማል። በጦርነቱ መካከል ጌታ ይገለጥና ጠላቶቹን ሁሉ ድል ያደርጋቸዋል። የዓመፅ ሰውና ሐሰተኛ ነቢያቱ ዘላለም ወደሚሰቃዩበት የእሳት ባሕር ይባላሉ። እንዲህ ያለው ጊዜ መኖሩ ለምን አስፈለገ? ቢያንስ ሁለት ምክንያቶች አሉ፡- መጀመሪያ የሰዎች በደል መቀጣት አለበት። እግዚአብሔር አሁን ስላለው ክፋት ምንም የሚያደርግ ባይመስልም፤ ቅጣቱን በግልጥ የሚሰነዝርበት ጊዜ ይምጣል። ሁለተኛው፥ ሰዎች ሁሉ በምንም እኳኋን ይሁን በምን በገሥታት ንጉሥና በጌቶች ጌታ ፊት መንበርከክ አለባቸው። ከዚህ ሁሉ ይድኑ ዘንድ አሁኑኑ በፈቃደኝነትና በእምነት ወደ ክርስቶስ በመቅረብ ድነትን (ደኅንነትን) መቀበል ይኖርባቸዋል። ይህን ባያደርጉ፣ ለድነት (ደኅንነት) ሳይሆን ለፍርድ ይሰግዱለታል። ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

የፍዳው ዘመን [Tribulation] Read More »

ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያሉ መሠረታዊ አመለካከቶች

ሰዎች ስለ ወደፊቱ ለማወቅ ያላቸው ጉጉት አብሯቸው የኖረ ሲሆን ብዙ ነቢያት (እውነተኞቹም ሆኑ ሐሰተኞቹ) ይህን የሰው ፍላጎት ለማርካት ጥረት አድርገዋል። መተንበይ አደገኛ ሥራ ነው ምክንያቱም ትንበያው ስሕተት በሆነ መጠን፥ በአገልግሎቱ መቀጠሉ አስቸጋሪ እየሆነ ይሄዳል። በብሉይ ኪዳን ዘመን አንድ ነቢይ በእግዚአብሔር ስም መናገር ካቃተው፥ ወይም የተናገረው ትንቢት ባይፈጸም ያለ ምሕረት ይወገር ነበር (ዘዳግ. 13፡1-11፥ 18፡20-22)። አልፎ አልፎ ትክክለኛ ነገር ያመለከቱ ሐሰተኛ ነቢያት ቢነሱም (ይህ ዛሬም እንደተከሰተ ነው)፥ መልእክታቸው ቀደም ሲል እግዚአብሔር ለሕዝቡ በሰጠው እውነተኛ ትንቢቶች ይመዘን ነበር። እነዚህም ነቢያት ሚዛን ካላነሱ ይወገሩ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ የተነገሩ ትንቢቶች በትክክል መፈጸማቸው ተረጋግጧል። ይህም ያልተፈጸሙ ትንቢቶች በጽሑፍ በሰፈረው መሠረት በትክክል እንደሚከናወኑ እርግጠኛ ያደርገናል።  የወደፊቱን ሁኔታ በሚመለከት ብዙዎች አይስማሙም። ከዚህም የተነሳ ትንቢትን በመተርጎም ረገድ በቤተ ክርስቲያን ሦስት መሠረታዊ አመለካከቶች አሉ። እነዚህም እግዚአብሔር ከአይሁዳውያን፥ በተለይ ከአብርሃም ጋር ከገባው ቃል ኪዳን ጋር የሚያያዙ ናቸው።  እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባው ቃል (ዘፍጥ. 12፡1-3) እየቆየ ሊረጋገጥና ይፋ ሊሆን ችሏል (ዘፍጥ. 13፡14-17፥ 15፡1-7፥ 17፡1-18)። አብርሃም በጊዜያዊና በመንፈሳዊ በረከቶች ሁሉ እንደሚባረክ በዚህ ቃል ኪዳን ተገልጧል። በዚህም መሠረት ርስት፥ ባሪያዎች፥ መንጋዎች፥ ብርና ወርቅ ማግኘቱ ሲታይ (ዘፍጥ. 13፡14-15፥ 17፤ 15፡7፣ 24፡34-35)፣ ከእግዚአብሔር ጋር ደስ የሚያሰኝ ኅብረት ስለነበረው የእግዚአብሔር ወዳጅ ተብሎ ለመጠራትም በቅቷል (ዘፍጥ. 18፡17፤ ያዕ. 2፡23)። እነዚህ ትንቢቶች ልክ በተነገሩት አኳኋን ተፈጽመዋል፡፡ ለአብርሃም ልጆችና ለእስራኤል ለራሷም በዚያ ቃል ኪዳን ተስፋ ተሰጥቷቸው ነበር። እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ከአብርሃም ልጆች ጋር እንደሚቀጥልና (ዘፍጥ. 17፡7)፣ ቁጥራቸው እንደ ባሕር አሸዋ የበዛ ታላቅ ሕዝብ እንደሚያደርጋቸው ተናግሯል (ዘፍጥ. 12፡2፥ 13፡16፥ 15፡5)። የሚደንቀው የአብርሃም ልጆች የሆኑት አይሁዳውያን ዛሬ የሚኖሩበት መሬት ዳርቻውና ክልሉ ቀደም ብሎ በተስፋ መገለጡና ለዘላለምም የነርሱ ርስት እንደሚሆን መነገሩ ነው (ዘፍጥ. 15፡18፣ 17፡8)።  ቃል ኪዳኑ ሌሎች ሕዝቦችን የሚጨምር ተስፋ ነበር። አብርሃምንና ልጆቹን የሚባርኩ እንደሚባረኩና፥ የሚረግሟቸው ደግሞ እንደሚረገሙ ተናግሯል። ይህ በአብርሃም የሕይወት ዘመን የተረጋገጠ ጉዳይ ነው (ዘፍጥ. 14፡12-20፥ 20፡2-18)። በእስራኤል ልጆች ልምምድ ውስጥ እንዲሁ (ዘዳግ. 30፡7፤ ኢሳ. 14፡12)፥ ትንቢቱ ወደፊት በሚጠበቀው የፍዳ ዘመንም ይሠራል (ማቴ. 25፡40)። የምድር ነገዶች ሁሉ በአብርሃም እንደሚባረኩ ተስፋ ነበር። እግዚአብሔርም በእስራኤል በኩል መጽሐፍ ቅዱስን በመስጠትና ከአብርሃም ዘር የሆነ ክርስቶስን በመላክ ቃሉን ፈጽሟል(ገላ. 3፡16)።  ለአብርሃም የተገባው የተስፋ ቃል አብዛኛው የተፈጸመ ለመሆኑ ሰዎች ሁሉ ይስማማሉ። የእስራኤልን ምድር በተመለከተ የተሰጠው የተስፋ ቃል ግን ሙሉ በሙሉ ተፈጽሟል ለማለት አይቻልም። የምድሪቱ ዳርቻ “ከግብፅ ወንዝ ጀምሮ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ” (ዘፍጥ. 15፡18) መሆኑ ተገልጧል። የምድሪቱ ምሥራቅ ዳርቻ የኤፍራጥስ ወንዝ እንደሚሆን ሰዎች ሁሉ ይስማማሉ። የግብፅ ወንዝ የተባለው የቱ ነው? ለሚለው ጥያቄ ነው የተለያየ መልስ ያላችው። አንዳንዶቹ ወንዝ የሚለው ቃል አባይን ያመለክታል ሲሉ፥ ሌሉቹ ደግሞ ዋደ ኤል አሪሽ የተባለውንና ከጋዛ እጅግም የማይርቀውን ወንዝ ይጠቅሳል ይላሉ። ከሁለቱም አመለካከት አቅጣጫ ሲታይ እስራኤል በታሪኳ እስከዛሬም ቢሆን እነዚህን ድንበሮች አልያዘችም፡፡ ለአብርሃም በተሰጠው ቃል ኪዳን ላይ የሚነሳው ሌላ ጥያቄ የተስፋው ቃል በታዛዥነት ላይ የተመሠረተ ነው፥ ወይስ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ይፈጸማል? የሚል ነው። ተስፋው በአይሁድ ታማኝነትና መልካምነት ላይ የተመሠረተ ከሆነ፣ ስለ ፍልስጥኤም የተባለው ነገር እና በቃል ኪዳኑ የተሰጠው በረከት ሁሉ ተሰርዟል ማለት ነው። ምክንያቱም የአይሁድ ሕዝብ ደግሞ ደጋግሞ ኃጢአት ሠርቷል። ተስፋው በእግዚአብሔር ታማኝነት ላይ የሚመሠረት ከሆነ ግን በሰው መታመን ወይም አለመታመን ሳይታገድ ይፈጸማል።  ቃል ኪዳኑ በቅድመ ሁኔታ ላይ ለመመሥረት ወይም ላለመመሥረቱ ጥያቄ መልስ የሚሆነን ነገር ስዘፍጥረት 15፡9-17 ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ ይህም እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ለማጽናት ያደረገው ተግባር ነው። በእነዚያ ጊዜያት ቃል ኪዳንን ለማጽናት የተለመደው መንገድ በመጀመሪያ እንስሳትን መሥዋዕት ማድረግ፥ ከዚያም እንስሳቱን ቆራርጦ መሬት ላይ ማስቀመጥ ነበር። በቃል ኪዳኑና በተለመደው አሠራር መሠረት ቢሆን ሁለቱ ተስማሚ ወገኖች በመሥዋዕቱ መካከል መሄድ ይገባቸው ነበር። በዚህ አሠራር ግን አሰገራሚና ልዩ ሁኔታ ታይቷል። እግዚአብሔርና አብርሃም በመሥዋዕቱ መካከል አልተመላለሱም። በዚያ ፈንታ እግዚአብሔር በአብርሃም ላይ ከባድ እንቅልፍ ጣለበትና ብቻውን በመሥዋዕቱ መካከል አለፈ። ይህ የሚያሳየን እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ብቻውን የሚጠብቅ መሆኑን ነው።  በተጨማሪም ቃል ኪዳኑ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅ፥ ለይስሐቅም ልጅ ለያዕቆብ፥ እንደገና ተረጋግጧል (ዘፍጥ. 26፡2-4፥ 28፡13-15)። በዚህ ጊዜ ሁሉ ለትንቢቱ ፍጻሜ ቅድመ ሁኔታ ያልተጠቀሰ ሲሆን፥ እግዚአብሔር ለአብርሃም ማረጋገጫውን ያጸናለት ያለ ቅድመ ሁኔታ የገባውን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ ብቻ ነው። ከዚህም ሌላ ቃል ኪዳኑ በተሰጠበትና ለይስሐቅ በተረጋገጠበት ጊዚ መካከል አብርሃም ኃጢአት ፈጽሞ ነበር። ታዲያ ቃል ኪዳኑ የታዛዥነት ቅድመ ሁኔታ ቢኖረው ኖሮ፥ በአብርሃም አለመታዘዝ ምክንያት በተሰረዘ ነበር (ዘፍጥ. 12፡10-20)። በትክክል ለመናገር ለቃል ኪዳኑ ተፈጻሚነት በአንዳንድ መለስተኛ ጉዳዮች ላይ ቅድመ ሁኔታዎች መኖራቸው ቢታይም፥ ለቃል ኪዳኑ አጠቃላይ ፍጻሜ ግን ግዴታ አልነበረም። በእስራኤል ታሪክ ውስጥ የተስፋይቱን ምድር ለጊዜውም ቢሆን፥ በከፊል ለመውረስ ታዛዥነት እግዚአብሔር የጠየቀው ግዴታ የነበረ ሲሆን፥ አለመታዘዝና ኃጢአት መፈጸምም የመበተንን ፍርድ ያስከትል ነበር (ዘዳግ. 28፡25፤ ኤር. 25፡11)። ይሁን እንጂ የቃል ኪዳኑ መጨረሻ በእግዚአብሔር ይከናወናል፤ እስራኤልም በመሢሁ በምትገዛበት ዘመን ወደ ፍጹም ታዛዥነት ትለወጣለች።  ለዳዊትና ለልጆቹም እግዚአብሔር እንደዚሁ “በዳዊታዊ ቃል ኪዳን” በጣም ጠቃሚ የሆኑ ቃል ኪዳኖች ገብቷል (2ኛ ሳሙ. 7፡12-16)። ቤተ መቅደሱን የሚገነባው ዳዊት ሳይሆን ልጁ ሰሎሞን መሆኑን ጠቅሶ፥ ዙፋኑና መንግሥት በዳዊት ዘር ለዘላለም እንደሚጸና ቃል ገብቷል፡፡ ክርስቶስ ከዳዊት ዘር ለመሆኑና የተስፋ ቃል ፈጻሚ ለመሆኑ ሰዎች ሁሉ ይስማማሉ፤ ምክንያቱም ሉቃስ 1፡32-33 ይህን ስለሚያረጋግጥ ነው። እነዚህ ንጉሡንና መንግሥቱን የተመለከቱ ተስፋዎች በብሉይ ኪዳን የተደጋገሙ ቢሆንም፥ ከሁሉም ጠንከር ያለው ኃይለ ቃል በመዝሙር 89 ላይ የተጠቀሰው ነው። በዚህ ሰፍራ ጌታ አለመታዘዝን እንደሚቀጣና፥ ቃል ኪዳኑም በምንም ሁኔታ እንደማይሻር ወይም እንደማይለወጥ በተጠናከረ ሁኔታ ተገልጧል (ቁ. 30-37)። ሌሎች ተመሳሳይ ቃሎች ኢሳ. 9፡6-7፤ ኤር. 23፡5- 6፤ ሕዝ. 37 ፡24-25፤ ሆሴእ 3፡4-5፤ 152 አሞጽ 9፡11 እና ዘካ. 14፡4-9 ናቸው። እነዚህን ሁሉ የሚፈጽማቸው ክርስቶስ ስለመሆኑ የትምህርተ-መለኮት ሰዎች ሁሉ ይስማማሉ። መቼ? ለሚለው ጥያቄ የሚሰጡት መልስ ግን ተመሳሳይ አይደለም። አሁን ክርስቶስ በሰማይ ባለው የዳዊት ዙፋን ነው የተቀመጠው? ወይስ ቤተ ክርስቲያን ናት መንግሥቱ? ወይስ ይህ ሁሉ የሚፈጸመው ክርስቶስ ወደፊት መንግሥቱን ምድር ላይ በሚመሠርትበትና በሚገዛበት ጊዜ ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልሶች ናቸው ስለ ወደፊቱ ሁኔታ ያሉትን አመለካከቶች የተለያዩ የሚያደርጓቸው። ስለ ሺሁ ዓመት አገዛዝ [Millenium/ሚሌኒየም] ያሉት ሦስት የተለያዩ አመለካከቶች የተመሠረቱት ለአብርሃምና ለዳዊት የተሰጧቸው ቃል ኪዳኖች ቅድመ ሁኔታዎች ነበሯቸውን? በሚለው ጥያቄ ላይ ነው።  የድህረ-ሺህ ዓመት አገዛዝ አመለካከት [Postmillennialism]  ይህ አመለካከት የሚያስተምረው የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ከሺህ ዓመቱ አገዛዝ በኋላ ይሆናል በማለት ነው። የዚህ አመለካከት አራማጆች በቤተ ክርስቲያን ጥረት በምድር ላይ ፍጹም የሆነ አገዛዝ ይመሠረታል በማለት ያስተምራሉ። በወርቃማው ዘመን የአብርሃምንና የዳዊትን ቃል ኪዳን የምትለማመደው ቤተ ክርስቲያን እንጂ እስራኤል አይደለችም ይላሉ። ይህ መንግሥት ምድራዊ ስለሚሆን “የቤተ ክርስቲያን መንግሥት” እንጂ የአይሁድ መንግሥት አይሆንም። ንጉሡ ክርስቶስም በምድር ላይ አይኖርም፤ የሚገዛው በሰዎች ልብ ውስጥ በማደር ሲሆን፥ ሺሁ ዓመት የአገዛዝ ዘመን ሲያበቃ ነው ወደ ምድር የሚመለሰው። በዚያን ጊዜም የሙታን አጠቃላይ ትንሣኤ ይሆንና፥ ለሰዎች ሁሉ ፍርድ ይሰጣል፤ ከዚያ በኋላ ነው ዘላለማዊ ሕይወት የሚጀመረው።  በድህረ-ሺህ ዓመት አገዛዝ እምነት ተከታዮች አመለካከት መሠረት፥ ለአብርሃም የተሰጠው ቃል ኪዳን የሚፈጸመው በቤተ ክርስቲያን በኩል ቢሆንም፥ አፈጻጸሙ ቃል በቃል በሚሰጠው ትርጉም መሠረት አይደለም። የአተረጓጎም ዘዴውም ትንቢቶቹን ምሳሌያዊ ትርጉም በመስጠት ነው። የአልቦ-ሺህ ዓመት አገዛዝ አመለካከት [Amillennialism]  ይህ አመለካከት ሺህ ዓመት የሚባል ነገር ጨርሶ የለም ብሎ ነው የሚያስተምረው። መንግሥት ቢኖር ያለው አሁን ነው፤ ይህም መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ላይ ያለው

ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያሉ መሠረታዊ አመለካከቶች Read More »

ቤተ ክርስቲያን መቼ ተጀመረች?

የሥነ-መለኮትን ትምህርት የሚከፋፍለው መሠረታዊ ጥያቄ፥ ቤተ ክርስቲያን መቼ ተጀመረች? የሚለው ነው። “የቃል ኪዳን ሥነ-መለኮት [Covenant Theolog/ኮቨናንት ቲያሎጂ] የተሰኘው የትምህርት ክፍል፣ ቤተ ክርስቲያን በብሉይ ኪዳን (በተለይ በአብርሃም) ተጀምራ ለዘላለም ቀጥላለች ይላል። በዚህ አመለካከትና ትምህርት መሠረት፥ ዓለም አቀፋዊቷ ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ የነበሩትን አማኞች ሁሉ ይዛለች (ቢያንስ ከአብርሃም) ጀምሮ። ሌሎች ቡድኖች ደግሞ ቤተ ክርስቲያን በመጥምቁ ዮሐንስ ጊዜ ተጀመረች ይላሉ። ለዚህም የሚያቀርቡት የመከራከሪያ ነጥብ ሰዎችን በማጥመቅ የመጀመሪያው ዮሐንስ ስለሆነና (ሌሎች የአይሁድ ጥምቀቶች ራስ በራስ ነበር የሚካሄዱት) ጥምቀት ቤተ ክርስቲያንን ከሌሎች ድርጅቶች የሚለያት መታወቂያ በመሆኑ ነው የሚል ነው። የሦስተኛው ቡድን አባላት ደግሞ፥ ቤተ ክርስቲያን በበዓለ አምሳ ዕለት የተጀመረች መሆኗን ያስተምሩና፥ አባላቷም ከዚያን ዕለት ጀምሮ እስካሁን ያሉት አማኞች ናቸው ይላሉ። ሌሎቹ ደግሞ፥ የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን፥ ጳውሎስ አገልግሎት ከጀመረ በኋላ ተመሠረተች ይላሉ (ይህም ጳውሎስ ጌታን ባወቀ ጊዜ፥ በመጀመሪያው ሐዋርያዊ ጉዞው፥ ወይም በሮሜ የመጀመሪያ እሥራቱ ሊሆን እንደሚችል ነው፡- ማለት በሐዋርያት ሥራ 9፡13 ወይም 28 መሠረት)። ከዚያ በፊት ግን (ከበዓለ አምሳ እስከ ሐዋ. 9፣ 13፥ ወይም 28) የነበረችው የአይሁድ ቤተ ክርስቲያን እንጂ፥ የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን አይደለችም ይላሉ። በእርግጥ ይህ እጅግ ወሳኝና የሚከፋፍል ጥያቄ ነው።  በዓለ አምሳ የቤተ ክርስቲያን መጀመሪያ ዕለት መሆኑን የሚከተሉት ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ።  1. ጌታ በማቴዎስ 16፡18 ላይ ቤተ ክርስቲያን ገና ወደፊት የምትመሠረት መሆኗን ተናገረ። በብሉይ ኪዳን ጊዜ ቤተ ክርስቲያን እንዳልነበረች ይህ ያሳያል።  2. የክርስቶስ ትንሣኤና ዕርገቱ ለቤተ ክርስቲያን ተግባራዊነት አስፈላጊ ነበሩ። የተመሠረተችው በትንሣኤው ላይ ነው (ኤፌ. 1፡19-20)። ለሥራዋም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ያስፈልጓት ነበር። ስጦታዎችን ይልክ ዘንድ ክርስቶስ ማረግ ነበረበት (ኤፈ. 4፡7-12)። ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው ከክርስቶስ ዕርገት በፊት ቢሆን ኖሮ ለተግባራዊነቷ አስፈላጊ የሆነው መሠረትና ኃይል ሊኖራት አይችልም ነበር። የቤተ ክርስቲያን ህልውናም ሆነ ተግባር የተመሠረተው በክርስቶስ ትንሣኤና ዕርገት ላይ መሆኑ ቤተ ክርስቲያንን እስካሁኑ ዘመን ድረስ ልዩ ያደርጋታል።  3. ቤተ ክርስቲያን በበዓለ አምሳ ዕለት መመሥረቷን የሚያረጋግጥልን ዋና ማስገንዘቢያ ግን የመንፈስ ቅዱስ የማጥመቅ ሥራ ነው። ጌታ ከማረጉ በፊት ይህ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ወደፊት የሚከናወን መሆኑን አመልክቷል (ሐዋ. 1፡5)። በበዓለ አምሳ ዕለትም ለመጀመሪያ ጊዜ ተከናወነ (በሐዋርያት ሥራ 2 ላይ ያለው ጽሑፍ ይህን አይልም፤ በሐዋርያት ሥራ 11፡15-16 ያለው ግን ይናገራል)። ይህ የመንፈስ ጥምቀት ሥራ ምን ያደርጋል? የዚህ መልስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 12፡13 ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህም እማኙን በክርስቶስ አካል ውስጥ የማኖር ተግባር ነው። ወደ ክርስቶስ አካል ለመግባት ይህ ብቸኛው መንገድ መሆኑ (በመንፈስ ቅዱስ የማጥመቅ ሥራ) እና እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በመጀመሪያ የተከናወነው በሰዓለ አምሳ ዕለት ስለሆነ ከዚህ ተነስተን የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን በበዓለ አምሳ ዕለት ተጀምራላች ወደሚለው ድምዳሜ ልንደርስ እንችላለን።  መቼ ነው ቤተክርስቲያን ከፍጻሜ የምትደርሰው?  የክርስቶስ አካል የሆነች ቤተ ክርስቲያን በበዓለ አምሳ ዕለት ከተጀመረች ፍጻሜዋ ጌታ ወደ ራሱ በሚጠራት ወይም በመነጠቅ ጊዜ ይሆናል። ይህ ማለት ግን፥ ከዚያ በኋላ የሚድኑ ሰዎች አይኖሩም ማለት አይደለም። ልክ ከበዓለ አምሳ በፊት የተዋጁ እስራኤላውያን እንደነበሩ ሁሉ፥ ከቤተ ክርስቲያን መነጠቅ በኋላም የሚዋጁ ይኖራሉ። ይህ በከራው ዘመን እና በሺህ ዓመት ግዛት፥ በሁለቱም ጊዜ ይሆናል። እነዚህ አማኞች ምንም እንኳን የተዋጁና በመንግሥተ ሰማያት ቦታ ያላቸው ቢሆንም፥ የክርስቶስ (የቤተ ክርስቲያን) አካል የሆኑ አይመስልም፡፡ በግልጥ እንደተነገረን ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም የመላእክት፥ የቤተ ክርስቲያን፥ የእግዚአብሔር፥ የኢየሱስ እና “የጻድቃን ነፍሳት” (የብሉይ ኪዳን ቅዱሳንን የሚያመለክት ይመስላል) መኖሪያ ነች። አሳቡ የሚያመለክተው የተለያዩ አማኝ ወገኖች በሰማይ እንደሚገኙ ነው። ፍጻሜውና መድረሻው አንድ ቢሆንም እንኳን፥ ልዩነቱ እንደተጠበቀ ይሆናል።  ጎልቶ የሚታየው ሌላ ጉዳይ ደግሞ፥ በመከራው ዘመንም ሆነ በሺህ ዓመቱ ግዛት ወቅት፥ የመንፈስ ቅዱስ የማጥመቅ ተግባር አለመጠቀሱ ነው። ይህም የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ፍጻሜ፥ የፍዳው ዘመን ከመጀመሩ በፊት እንደሚሆን ያመለክታል። ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን መቼ ተጀመረች? Read More »

ዓለም-አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን

ዓለም-አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን፡- ክርስቶስ ራሷ የሆነ፥ ከበዓለ-አምሳ ዕለት ጀምሮ እስከ መነጠቅ ድረስ ያሉ አማኞች ሁሉ አባላት የሆኑባት መንፈሳዊት አካል ነች። የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ስለሆነች ቤተ ክርስቲያኔ ብሏታል (ማቴ. 16፡18)። የመጀመሪያ መሪዎቿን አስተምሯል (ዮሐንስ 14-16)፤ ሊጀምራትና ኃይል ሊሰጣት በበዓለ አምሳ ዕለት መንፈስ ቅዱስን ልኮላታል (ሐዋ. 2፡33)። በትንሣኤውና በዕርገቱ የቤተ ክርስቲያኑ ማለት የአካሉ ራስ ሆኗል (ኤፈ. 1፡20-23)። ስጦታ ሰጥቷታል (ኤፈ. 4፡8-11)፤ ያለ ነውርና ነቀፋ የሆነች ሙሽራ እንድትሆንለት ያዘጋጃታል (ኤፌ. 5፡26-27)።  ክርስቶስ ስለ ቤተ ክርስቲያን በተናገረው ትንቢት ላይ የተለያዩ የትርጉም ችግሮች ተነስተዋል (ማቴ. 16፡18-19)። ከችግሮቹ አንዱ ቤተ ክርስቲያኑን የሚገነባበት አለት ምንድን ነው? (ቁ. 18) የሚል ነው። የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጴጥሮስ ራሱ ነው ትላለች። ይህ ግን የማይታመን ነው። ምክንያቱም ጴጥሮስ የሚለው ቃል ተባዕታይ ሲሆን፥ አለት የሚለው ቃል (በግሪክኛው አጠቃቀም) አንስታይ ጾታ በመሆኑ ነው። ቤተ ክርስቲያን የምትመሠረትበት አለት ክርስቶስ እንጂ፥ እርሱ አለመሆኑን ጴጥሮስ ራሱ ያረጋግጣል (1ኛ ጴጥ. 2፡4-8)። ይህም አለቱ ኢየሱስ ነው ለሚለው ትርጉም ድጋፍ ይሰጣል (1ኛ ቆሮ. 3፡11ንም ይመልከቱ)። ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን የሚሠራበት ድንጋይ ማለት ጴጥሮስ ክርስቶስ የተተነበየለት መሢህ ስለመሆኑ የተናገረው ቃል ሊሆንም ይችላል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን አባል የሚሆን ሰው የክርስቶስን መሢህነት ተቀብሏል።  ሌላው የትርጉም ችግር ደቀ መዛሙርቱ የተሰጣቸውን የማሠርና የመፍታት ሥልጣን ይመለከታል (ማቴ. 16፡19)። ደቀ መዛሙርቱ ሥልጣን የተሰጣቸው ነገሮች ላይ እንጂ በሰዎች ላይ እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ቃሉ “በምድር ያሠራችሁት ነገር በሰማያትም የታሠረ ነው” ይላል። ለመፍታትም እንዲሁ። በዮሐንስ 20፡23 ላይ ኃጢአትን ይቅር ስለማለትና ስላለማለት የተገለጠውን እንዲሁ በተመሳሳይ ሁኔታ ለመፍታት ይቻላል። በሁለቱም ጥቅሶች ውስጥ ያለው ቁም ነገር፥ ደቀ መዛሙርት ለማሠር ወይም ለመፍታት፥ ይቅር ለማለት ወይም ኃጢአትን ለመያዝ ሥልጣን አላቸው ማለት ሳይሆን፥ በሰማያት የሆነውንና የተከናወነውን ለማወጅ ወይም ለማረጋገጥ መቻላቸውን ለማሳየት ነው። እግዚአብሔር እነዚህን ነገሮች ይጀምራቸዋል፥ ሐዋርያት ደግሞ ለሰዎች ያውጇቸዋል። ምሳሌ ቢያስፈልግ፥ ሐዋርያቱ ቤተ ክርስቲያንን ስለማሠራቸው በሐዋርያት ሥራ 15 ላይ የተጠቀሰውን መመልከት ይቻላል። ኃጢአትን ይቅር ስለአለማለት ደግሞ ሐዋ. 5፡1-11 ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ምንም እንኳን የዛሬዎቹ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከቀድሞዎቹ ተመሳሳይ የሆነ ኀላፊነት ቢኖርባቸውም፥ ኀላፊነቶቹ ተሰጥተው የነበረው ለሐዋርያቶች ብቻ ነው።  የዓለም-አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ምሳሌዎች  በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያኑ መካከል ያለው ግንኙነት በአዲስ ኪዳን ውስጥ በአያሌ ምሳሌዎች ተገልጧል። ምሳሌዎቹ ዝርዝር ጥናት የሚያስፈልጋቸው ቢሆኑም፥ ጥቂቶቹን ብቻ ጠቅሰን እናልፋለን።  1. ክርስቶስ እረኛ፥ እኛ ደግሞ በጎቹ ነን (ዮሐንስ 10)። እርሱ ለእኛ ያለው ጥንቃቄና፥ የእኛ በእርሱ መጠበቅ መልእክት በዚህ ምሳሌ ይተላለፋል።  2. ከርስቶስ የወይን ግንድ ነው፥ እኛ ቅርንጫፎቹ ነን (ዮሐንስ 15)። ፍሬያማ የምንሆነው የሚያስፈልገንን ከግንዱ ስናገኝ ብቻ ነው።  3. ክርስቶስ የማእዘን ድንጋይ፥ እኛ የሕንጻው ላይ ድንጋዮች ነን (ኤፌ. 2፡19-21)። የማእዘን ድንጋይ ለሕንጻው ቅርፅ ሲሰጥ፣ የሚቀመጠውም አንድ ጊዜ ብቻ ነው።  4. ክርስቶስ ሊቀካህን ነው፥ እኛም የምንግሥቱ ካህናት ነን (1ኛ ጴጥ. 2)። እንደ ካህናት እኛነታችንን፣ ያለንንና፣ አገልግሎታችንን መሥዋዕት አድርገን መስጠት እንችላለን (ሮሜ 12፡፤ ዕብ. 13፡15-16)።  5. ክርስቶስ ራስ፥ እኛም የአካሉ ብልቶች ነን (1ኛ ቆሮ. 12)። እንደ ራስ እርሱ ይመራል፥ እንደ ብልቶች ደግሞ ከሞት የተነሣው ራስ በሚሰጠን መንፈሳዊ ስጦታ እርስ በእርሳችን መገልገል እንችላለን።  6. ክርስቶስ የመጨረሻው አዳም ነው፥ እኛ አዲስ ፍጥረታት ነን (1ኛ ቆሮ. 15፡45)። የትንሣኤውን ኃይልና ሕይወት እንካፈል ዘንድ የመጨረሻው አዳም በሆነው በክርስቶስ ውስጥ በእምነታችን አለን (ሮሜ3፡19)።  7. ክርስቶስ ሙሽራ፥ እኛ የእርሱ ሙሽሪት ነን (ኤፌ. 5፡25-33፤ ራእይ 19፡7-8)። በሙሽራውና ሙሽራይቱ መካከል ያለው የማያቋርጥ ፍቅርና ውህደት የዚህ ምሳሌ ዋና ዋና ነጥቦች ናቸው።  8. ክርስቶስ ወራሽ ነው፥ እኛም ከእርሱ ጋር ወራሾች ነን (ዕብ. 1፡23 ሮሜ 8፡17)። ዓለም እርሱነቱን በሚረዱበት ዕለት እኛም የክብሩ ተካፋዮች እንደምንሆን ይህ ቃል ዋስትናችን ነው።  9. ክርስቶስ የመጀመሪያ ፍሬ፥ እኛ መከር ነን (1ኛ ቆሮ. 15፡23)። ትንሣኤው ለእኛ ትንሣኤ ዋስትና ነው።  10. እርሱ ጌታ፣ እኛ ባሪያዎቹ ነን (ቁላ. 4፥ 1፤ 1ኛ ቆሮ. 7፡22)። ባሪያ የጌታውን ፈቃድ ይፈጽማል፤ በአንጻሩም ጌታ ለባሪያው የሚያስፈልገውን ያደርግለታል። ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

ዓለም-አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን Read More »

የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች ብዛት፥ ትርጉም እና ጥቅም በተመለከተ ብዙ ሲያከራክር ቆይቷል። በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ሥርዓቶች ብቻ የነበሩ ሲሆን፥ እነሱም ጥምቀትና የጌታ እራት ናቸው። ከዚያ በኋላ ግን ሌሎች ሥርዓቶች ተጨምረዋል። ዛሬ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን “ሳክራምንት” [Sacrament] የሚባሉ ሰባት ሥርዓቶች አሏት። በ1545 ዓ.ም. የትሬንት ጉባኤ ሳክራመንት “በእግዚአብሔር የታቀደ፣ አንዳንድ መለኮታዊ እውነቶችን የሚያሳየን ብቻ ሳይሆን ጸጋንም የሚሰጠን” እንደሆነ ጠቅሷል። ይህን ትምህርት በአጠቃላይ የምሥራቃዊ ቤተ ክርስቲያናትም ጭምር ተከትለውታል።  በ16ኛው ክፍለ ዘመን ከተሃድሶ ጊዜ በኋላ አብዛኞቹ የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያናት ሥርዓትን እንደሚከተለው ተርጉመውታል፡- “በክርስቶስ የታዘዘ፥ በቤተ ክርስቲያኑ በግልጥ የሚከናወን ሃይማኖታዊ ሥርዓት።” ይህ ጋብቻን ሊያጠፋ ይችላል፤ ምክንያቱም ጋብቻ ከክርስቶስ በፊት የተደነገገ በመሆኑ ነው። እንደ ፕሮቴስታንቶች አመለካከት፥ ሥርዓቶች፥ በሥርዓቱ የተካፈለ ሰው ጸጋን እንዲላበስ የሚያደርጉ ሳይሆኑ፥ እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገልንን ነገሮች የሚያስታውሱ ምሳሌዎች ብቻ ናቸው። ከዚህ ቀጥሎ በማንኛውም ክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነት ባላቸው ሁለት ሥርዓቶች ላይ እንወያያለን። የጌታ እራት። የተለያዩ ሰዎች ስለ ጌታ እራት የተለያየ ትርጉም አላቸው። የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች፥ ህብስቱና ወይኑ መልካቸውን ባይለውጡም፣ በትክክል የክርስቶስ አካልና ደም ይሆናሉ ብለው ያምናሉ። ይህ አመለካከት [“ትራንስብስታንሺዬሽን” /Transubstantiation] የሚባል ሲሆን፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነም ነው። ምክንያቱም የክርስቶስ ደምና ሥጋ ይህ ሥርዓት በተፈጸመ ቁጥር መሥዋዕት ሆኖ በመቅረቡ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በተቃራኒው የሚገልጠው የክርስቶስ ሞት ሙሉና በቂ፥ እንዲሁም ላንዴና ለሁልጊዜ የተፈጸመ መሆኑን ነው (ዕብ. 10፡101 9፡12)። ሉተራውያን ደግሞ ወይኑና ህብስቱ ለውጥ ባይኖራቸውም፥ ሰው ከቅዱስ ቁርባኑ በሚቋደስበት ጊዜ እውነተኛ የክርስቶስ ሥጋና ደም ይሆናሉ ይላሉ። ይህም “ካንሰብስታንቪዬሽን” [Consubstantiationa] ይባላል። ሌሎች ደግሞ ይበልጥ ትክክል የሚመስል አመላካከት ያቀርባሉ፡- የጌታ እራት ሥርዓት የሚዘከረው ለመታሰቢያነት ብቻ ነው (1ኛ ቆር. 11፡24-25 “ለመታሰቢያዬ”) ህብስቱም ሆነ ወይኑ አይለወጡም፤ ክርስቶስ ግን በአገልግሉቱ ወቅት በመካከላችን ይገኛል፤ ያም ቢሆን ከህብስቱና ከወይኑ ውስጥ አይደለም ይላሉ።  የጌታ እራት የተለያዩ ዓላማዎች አሉት፡- 1. የጌታችን ሕይወትና ሞት መታሰቢያ ነው። ህብስቱ ፍጹምና ቅዱስ ሕይወቱን ያመለክታል፤ ይህ ቅዱስ ሕይወት ለኃጢአት መሥዋዕትነት የበቃና ተቀባይነት ያለው ነው። ስለሆነም ህብስቱ ኃጢአታችንን በመስቀል ላይ የተሸከመውን የክርስቶስ አካል ያመለክታል (1ኛ ጴጥ. 2፡24)። ወይኑም ለኃጢአታችን ስርየት የፈሰሰውን ደም ይወክላል። ያ አካል ዳግመኛ ሲሰቀል ለማየትም ሆነ ደሙ ሲፈስ ለመመስከር ስለማንችል፥ የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት ለመታሰቢያነት ሲባል ብቻ የሚደረግ መሆኑን ማወቅ አለብን።  2. የጌታ እራት የወንጌልን እውነት የምናውጅበት ነው (1ኛ ቆሮ. 11፡26)።  3. የጌታን ዳግም ምጽአት በናፍቆት እንድንጠባበቅ ያሳስበናል፡፡ ይህን ሥርዓት የምናከብረው እስከዚያ ዕለት (ጌታ እስኪመጣ ድረስ ብቻ ይሆናል (1ኛ ቆሮ. 12፡26)።  4. እራቱ በክርስቶስ አካል ውስጥ ያለንን አንድነትና በዚህ አካል ውስጥ ካሉት አባላት ጋር ያለንን ኅብረት ያስታውሰናል(1ኛ ቆሮ. 10፡17)።  መቼ መቼ ነው የጌታ እራት መከበር ያለበት? አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በየሦስት ወሩ ሲያደርጉ፥ በተለምዶ ሥርዓቱን ለመፈጸም ካሰቡበት እሁድ በፊት ዮዝግጅት አገልግሎቶችን ያከናውናሉ። አንዳንዶች በየወሩ ሲያደርጉ፥ በየእሁዱም መደረግ አለበት የሚሉ አሉ። እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ የጌታን እራት መከበሪያ ጊዜ ለይቶ አይነግረንም። ከበዓለ አምሳ ሰኋላ የነበሩት የመጀመሪያ አማኞች በየቀኑ ያደርጉት የነበረ ይመስላል። ይህ ግን በየቀኑ በእያንዳንዱ ሰው ቤት ይከበር ነበር ማለት ሳይሆን፥ በኢየሩሳሌም ከተማ በአንድ ማዕከል መፈጸሙን ለማመልከት ነው (ሐዋ. 2፡46)። በጢሮአዳ (ሐዋ. 20፡6) እሁድ ዕለት ተደርጎ ነበር። ታዲያ አንዳንዶች ከጥቅሱ በመነሳት በየእሁዱ ተደርጓል ቢሉም፥ በዚህ ሁኔታ ስለመዘከሩ በግልጥ የተጻፈ መረጃ አናገኝም። የቱንም ያህል ቢደጋገም፥ አንዳንድ ጊዜ በምሽት ቢከናወን ተመራጭ ሊሆን ይችላል። እራት ስለሆነ ብቻ ሳይሆን፥ ጠዋት ጠዋት መምጣት የማይችሉ ምእመናንም እንዲካፈሉ ለማድረግም ነው። ይህ ሥርዓት ቤተ ክርስቲያን ከምታደርጋቸው ሌሎች ሥርዓቶች ይበልጥ ጠቃሚ ስለሆነ ሰፊ ጊዜ የሚሰጠው እንጂ፥ በችኮላ የሚከናወን ጕዳይ አይደለም።  ጥምቀት። የውኃ ጥምቀት ጉዳይ ሁለት ጥያቄዎች ያስነሳል። እነርሱም እንዴት ነው ጥምቀት መከናወን ያለበት? (አሠራሩ) እና በማን ላይ ነው መከናወን ያለበት? (አማኞች ብቻ ወይስ ሕፃናትም ጭምር) የሚሉ ናቸው። እነዚህን ጥያቄዎች ከመመለሳችን በፊት ግን የጥምቀትን ትርጉምና ጥቅም መግለጥ አስፈላጊ ይሆናል።  ማንኛውም የጥምቀት ትርጉም፥ ከክርስቲያን ጥምቀት ጋር ተያይዞ ብቻ ሳይሆን፥ ወደ ይሁዲነት የሚለወጡ ሰዎች የሚወስዱትን ጥምቀት፥ የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀትና በ1ኛ ቆሮንቶስ 10፡2 ላይ የተጠቀሰውን እንግዳ አሳብ ሳይቀር ማካተት አለበት። ብዙ ትርጉሞች የተመሠረቱት በውኃ ማጥለቅ በሚለው ቃል ላይ ነው። የጥምቀት ሥነ-መለኮታዊ ትርጉም ግን ከአንድ ማኅበር፥ ወይም መልእክት ወይም ልምድ ጋር አንድ መሆንና ኅብረት መመሥረትን ነው የሚያስገነዝበው።  የጥምቀት አፈጻጸም እስካሁን ያከራከረና ወደፊትም የሚያከራክር ጉዳይ ነው። በማጥለቅ ማጥመቅ አስፈላጊ አይደለም የሚሉ ክፍሎች የሚከተሉትን መከራከሪያ ሃሳቦች ያቀርባሉ፡፡ 1. “ባፕቲዞ” የሚለው የግሪክ ቃል ሁለተኛ ትርጉም አለው። ይኸውም “በአንድ ነገር፥ ወይም ተጽዕኖ ሥር መሆን” ማለት ነው። ስለዚህ ውኃውን በተጠማቂው ላይ ማፍሰስ፥ ወይም መርጨት፥ የሚሉት ቃላት ማጥለቅ ከሚለው በተሻለ ጥምቀት የሚለውን አሳብ ይገልጡታል።  2. ጥምቀት የመንፈስ ቅዱስን በአንድ ሰው ላይ መውረድ የሚያስረዳ ከሆነ፥ የውኃ ጥምቀትን አስመልክቶም ማፍሰስ ወይም መርጨት የሚሉት ቃላት ይበልጥ ይገልጡታል።  3. ለምሳሌ በሐዋርያት ሥራ 2፡41 እንደተጠቀሰው በውኃ ውስጥ ማጥለቅ የማይቻልበት ሁኔታ ያጋጥም ይሆናል (በጣም ብዙ ሰዎችን በማጥለቅ ማጥመቅ ያዳግታል)። በሐዋርያት ሥራ 8፡38 (በረሃ ውስጥ ያለው ውኃ ትንሽ ስለሆነ) እና ሐዋ. 10፡47 እና 16፡33 (በየቤቱ ለማጥለቅ በቂ ውኃ አለመገኘቱ፣ በማጥለቅ የማጥመቁን ተግባር የማይችል ባያደርገውም፥ ተግባራዊነቱ ያጠራጥራል)።  4. በዕብራውያን 9፡10 ጥምቀት የሚለው ቃል በብሉይ ኪዳን ያሉትን ብዙ ወጎች ስለሚጠቅስና ከነዚህም አንዱ መርጨት ስለሆነ፥ ቃሉ ማጥለቅ ማለት ብቻ አይሆንም።  5. ማጥለቅ ለሚለው ቃል ሌላ የማያጠራጥርና ግልጥ የሆነ የግሪክ ቃል አለ። ታዲያ ትክክለኛው የማጥመቅ አሠራር ማጥለቅ ከሆነ፥ ለምን ትክክለኛው የግሪክ ቃል አልተጠቀሰም?  በውኃ በመጥለቅ መጠመቅን የሚደግፉ ወገኖች ከሚያቀርቡዋቸው ማስረጃዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-  1. “ባፕቲዞ የሚለው የግሪክ ቃል የመጀመሪያ ትርጉም ማጥለቅ ነው።  2. “ወደ ውስጥ” እና “ወደ ውጭ” (ውኃ) የሚሉትን መስተዋድዶች በሚገባ ከተረዳን፥ ቃላቱ የሚያመለክቱት መጥለቅን ነው።  3. ወደ ይሁዲነት የገባ ሰው የሚጠመቀው በማጥለቅ ነበር (ጥምቀቱን የሚፈጽመው ግን ሌሎች ሳይሆኑ ሰውየው ራሱ ነበር)። ክርስቲያናዊው አሠራርም ያን የተከተለ መሆኑን ከዚህ እንረዳለን (በሌላ ሰው የሚከናወን ቢሆንም።  4. የማጥለቅ ጥምቀት፥ የጥምቀትን ጥቅም ማለትም የአሮጌውን ሕይወት ሞትና የአዲሱኝ ሕይወት ትንሣኤ በሚገባ የሚገልጥ አሠራር ነው (ሮሜ 6፡1-4)።  5. የማጥለቅ ጥምቀት በጥንት ቤተ ክርስቲያናት ይፈጸም የነበረ አሠራር ሲሆን፥ አያሌ የአዲስ ኪዳን ምሳሌዎችም ይህን ያዛሉ፥ ወይም ይፈቅዳሉ (በኢየሩሳሌም አካባቢ ባሉ የውኃ ጉድጓዶች ውስጥ ሊጠመቁ ይችላሉ)። ሦስት ሺህ ሰዎች በበዓለ አምሳ ዕለት በመጥለቅ ሊጠመቁ ይችሉ እንደነበር መገመት አያዳግትም።  6. የግሪኩ ቋንቋ ለማፍሰስና ለመርጨት የተለያዩ ቃላት አሉት፤ ይሁን እንጂ ጥምቀትን በማመልከት አገልግሎት ላይ አልዋሉም።  አንድ ሰው ይህን ሲመለከት ማጥለቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አሠራር ነው ለማለት ይገደድ ይሆናል። ማጥለቅ የየትኛዋም ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን አሠራር የነበረ ይመስላል። የቃሉ ተገቢ ትርጉምና በሥርዓቱ የሚተላለፈው መልእክት ማጥለቅን ያመለክታሉ። ከማጥለቅ ቀጥሉ በሥራ ላይ የሚውለው ማፍሰስ እንጂ መርጨት አልነበረም። ይህም በተግባር ይውል የነበረው፣ የታመሙና በመጥለቅ መጠመቅ የማይችሉ ሰዎችን ለማጥመቅ ነበር። ከዚህ በመነሳት ማፍስስ “የሕሙማን ጥምቀት” ይባላል። ሲፕርያን [Cyprian] የተባለ ሰው (200-257 ዓ.ም.) በመርጨት መጠመቅን በመደገፍ የመጀመሪያው ነበር። ይሁን እንጂ እሰከ አሥራ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ይህ ዓይነቱ አሠራር በስፋት አልተለመደም።  ሌላው ጥያቄ መጠመቅ ያለበት ማንነው? አማኞች ወይስ ሕጻናትም መጠመቅ ይችላሉ? የሚል ነው። የሕፃናትን ጥምቀት የሚደግፉ ወገኖች በእምነታቸው መሠረት የሚደረድሯቸው ነጥቦች፡-  1. የግርዘት ሥርዓት (በሕፃናት ላይ የሚደረግ መሆኑ ይታወቃል) እና የጥምቀት ሥርዓት ተመሳሳይ ናቸው። ግርዘት የአሮጌው ኪዳን የመጀመሪያ ሥርዓት ሲሆን፣ ጥምቀት ደግሞ የአዲሱ መጀመሪያ ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች Read More »