የአምልኮ መርሖዎች (ማቴ. 6፡1-18)

ዮሐንስ የአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መጋቢ ነበር። እርሱም በጸሎቱ የታወቀ አገልጋይ ነበር። በየእሑዱ «ሃሌሉያ» እያለ ረዥም ጸሎት ያቀርባል። ዮሐንስ በረዥም ጸሎቱ መንፈሳዊነቱን ለሰዎች እንደሚያሳይ ያስብ ነበር። ብዙነሽ ክርስቲያን ነጋዴ ነበረች። አንድ ቀን ቤተ ክርስቲያኗ ለአዲስ የሕንጻ ግንባታ ገንዘብ ታሰባስብ ነበር። ብዙነሽ መሪው በምእመናኑ ፊት እያንዳንዱ ሰው የሰጠውን የገንዘብ ልክ እንደሚናገር ታውቅ ነበር። ስለሆነም ትክክለኛውን ጊዜ ጠብቃ ብዙ ስጦታ ይዛ ገባች። ለእግዚአብሔር ብዙ ገንዘብ ለመስጠት ሰዎችን ማስደነቅ መቻሏ ያስደስታታል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) መንፈሳዊ ነገሮችን በራስ ወዳድነት አመለካከት ማድረግ የሚቀልለው እንዴት ነው? ለ) መንፈሳዊ የሚመስሉ ነገሮችን የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ባለን ፍላጎት ልናደርግ የምንችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

ኤርምያስ በ17፡9 ላይ የሰው ልብ ክፉና ተንኮለኛ ማንም የማያውቀው እንደሆነ ይናገራል። በልባችን እራሳችንን ከምናታልልባቸው እጅግ አደገኛ መንገዶች አንዱ አምልኮ ነው። የሐሰት አምልኮ ሊመጣ የሚችለው የውሸት ጣዖት በማምለክ ወይም በኢየሱስ ክርስቶስ ባለማመን ብቻ አይደለም። ለእግዚአብሔር ሕዝብ፥ በምናከናውናቸው የአምልኮ ተግባራት ሁሉ የሐሰት አምልኮ መፈጸሙ ቀላል ነው። ስለሆነም ክርስቶስ የተሳሳተ አመለካከት በሚኖረን ጊዜ፥ ሊከሰቱ የሚችሉትን የተለመዱ የአምልኮ ተግባራት ገልጾአል። እነዚህ ምሳሌዎች ብቻ ናቸው። ለሌሎች መንፈሳዊ መስለን ለመታየት በምንፈልጋቸው ጊዜያት ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ማምለክ አቁመናል ማለት ነው። በኳየር (በኅብረ ዝማሬ) ውስጥ የምንዘምረው የኳየር ልብሳችንን ለማሳየት፥ ዓይኖቻችንን በመጨፈን ወደ ሰማይ በማየትና በመወዛውዝ መንፈሳዊነታችንን ለማሳወቅ፥ ወይም ሃሌሉያ እያልን በመጮህ የሕዝቡን ስሜት ለማነሣሣት ከሆነ፥ እነዚህ ሁሉ ነገሮች የማይጠቅሙ ይሆናሉ። እውነተኛ አምልኮ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የልባችን መግለጫ ነው። ከዚህ ውጭ የምናደርገው ሁሉ የሐሰት አምልኮ ነው።

በክርስቶስ ዘመን ሌሎችን ለማስገረም የሚካሄዱ የአምልኮ ተግባራት በፈሪሳውያን ሕይወት ውስጥ ይታዩ ነበር። አለባበላቸው፥ በሕዝቡ ፊት የነበራቸው አክብሮትን ሰዎች ልብ ብለው እንዲያዩዋቸው መፈለጋቸው ሁሉ አምልኳቸው እንዲበላሽ አድርገዋል። ክርስቶስ እነዚህን አደጋዎች በመረዳት፥ ደቀ መዛሙርቱ አምልኳቸው ተቀባይነትን እንዲያገኝና ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው «ምጽዋታችሁን» በፊታቸው እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ ያለዚያ በሰማያት ባለው አባታችሁ ፊት ዋጋ የላችሁም።» ሲል አስጠነቀቃቸው ክርስቶስ «ምጽዋታችሁን» ሲል በእግዚአብሔር ፊት «ትክክለኛ ነገሮችን» እንድናደርግ ማሳሰቡ ነው።

  1. ለድሆች በመመጽወት ማምለክ (ማቴ. 6፡1-4)። ለድሆች መስጠት እግዚኣብሔር ከልጆቹ ሁሉ የሚጠብቀው ተግባር ነው። የወንጌል አማኝ ክርስቲያኖች፥ ሌሎች ወገኖች የሚሰጡበትን ምክንያት በመንቀፍ የሕይወት ማዕበል ለሚያንገላታቸው ወገኖች ርኅራኄን ማሳየት ኣቁመዋል። ነገር ግን ከመስጠት የሚበልጠው በምንሰጥበት ጊዜ በልባችን ውስጥ ያለው አመለካከት ነው። በመስጠት ዙሪያ አራት አመለካከቶች ይንጸባረቃሉ።

በመጀመሪያ፥ «ለድሃ ብሰጥ እግዚአብሔር እኔን ወደ መንግሥተ ሰማይ ያስገባኛል፤ ኃጢአቴንም ይሰርዝልኛል» የሚል አመለካከት አለ። አንድ መልካም ነገር በማድረግ ኃጢአታችንን ልናስወግድ ወይም ወደ መንግሥተ ሰማይ ልንገባ አንችልም። አንድ ሰው የኃጢአትን ይቅርታ አግኝቶ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን ሊያገኝ የሚችለው፥ የእግዚአብሔርን ይቅርታ በመጠየቅና በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው።

ሁለተኛው፥ በመስጠት እግዚአብሔር ሀብታም እንዲያደርገን ለማስገደድ እንችላለን ብለው የሚያስቡ ሰዎች ኣሉ። «ለእግዚኣብሔር ብዙ ገንዘብ ስጠው። ይህም እግዚአብሔር ከሰጠኸው የበለጠ እንዲመልስልህ ያደርገዋል። ለእግዚአብሔር 100 ብር ብትሰጠው፥ እርሱ 1000 ብር ይሰጥሃል። ብዙ ከሰጠኸው ሀብታም ትሆናለህ።» እግዚአብሔር በትክክለኛ አመለካከት ከሰጠነው ይባርከናል። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር የሚሰጠን የበረከት ተስፋ የግድ በምድር ላይ ብዙ ገንዘብ የምናገኝበት ሳይሆን፥ በመንግሥተ ሰማይ የምንቀበለው ነው። ከእግዚአብሔር ዘንድ እንድ ነገር ለማግኘት ተብሎ የሚደረግ ስጦታ የራስ ወዳድነት ተግባር ነው። ይህ በርኅራኄ ሳይሆን አንድን ነገር በአጸፋው ለማግኘት የሚደረግ ጥረት በመሆኑ፥ እግዚአብሔር የሚያከብረው ዓይነት ስጦታ ኣይደለም።

ሦስተኛው፥ «ሌሎች አይተው በችሮታዩ ሊያመሰግኑኝ በሚችሉበት መንገድ ለድሃ መስጠት አለብኝ» የሚሉ ሰዎች አሉ። ይህ የርኅራኄ መግለጫ ሳይሆን፥ በሌሎች ፊት ታዋቂ ለመሆን የሚደረግ ስጦታ ነው። ክርስቶስ የዚህ ዓይነቱ መስጠት የሰዎችን ምስጋና ከማስከተል ያለፈ፥ ሌላ ማዕረግ እንደማያስገኝ ተናግሯል። ይህ እግዚአብሔርን የማያስደስት በመሆኑ፥ ከእርሱ ዘንድ ምንም ምሥጋና አያስገኝም። ፈሪሳውያን የሚያደርጉት ይህንኑ ነበር። በቤተ መቅደስ ገንዘብ በሚሰጡበት ጊዜ ሕዝቡ ምን ያህል እንደሰጡ እንዲያውቁላቸው ይፈልጉ ነበር። እንዲያውም አንዳንዶች ሰዎች እንዲያዩላቸው መለከት እየነፉ ይሰበስቧቸው ነበር።

አራተኛው፥ ከርኅራኄና እግዚአብሔርን ከመታዘዝ የተነሣ ለተጎዱ ሰዎች የሚበረከት ስጦታም አለ። ይህ ስጦታ በሚለገስበት ጊዜ ተመልካች ስለመኖር አለመኖሩ ሳንጨነቅ የምናደርገው ነው። መንፈሳዊ ልብ ለእውቅና አይጣደፍም። ስሙ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ መጠራት አለመጠራቱም አይጨነቅም። ክርስቶስ በመስጠት ጊዜ የሚከሰተውን አደጋ በማጤኑ፥ ቀኝ እጃችን የሚሰጠውን ግራው እንደማያውቅ ያህል በምሥጢር እንድናደርገው እዝዞናል። እግዚአብሔርን የሚያስደስተው የዚህ ዓይነቱ ልግስና ብቻ ነው። እግዚአብሔር ትልቅ ግምት የሚሰጠው የዚህ ዓይነቱን ልግስና ብቻ ነው። አንዳንድ ጊዜ እርሱን እንድናገለግለው በምድር ብዙ ሀብት በመስጠት ቢባርከንም፥ ከሁሉም የሚበልጠው በሰማይ የሚገኘው በረከት ነው። (አሁንም ቢሆን በሰማይ ትልቅ ስጦታ ለማግኘት ስንል፥ በራስ ወዳድነት ዓላማ አለመስጠታችንን ማረጋገጥ አለብን። እግዚአብሔር ከሰው ምንም ነገር ለማግኘት ሳይሆን፥ ከፍቅሩና ከርኅራኄው የተነሣ እንደሚሰጥ፥ የእኛም ስጦታ ከርኅራኄ ልብ ሊመነጭ ይገባል።)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች በእነዚህ አራት መንገዶች ሊሰጡ ስለሚችሉባቸው መንገዶች ግለጽ። ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ሰዎችን ወደ ተሳሳቱ አቅጣጫዎች ሊመሩ የሚችሉ እንዳንድ ልምምዶች ምንድን ናቸው? ሐ) ምእመናን እግዚአብሔርንና ሰዎችን በመውደዳቸው ምክንያት፥ ከራስ ወዳድነት በጠራ መንፈስ በልግስና እንዲሰጡ ለማገዝ፥ ሊለወጥ የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

  1. አምልኮ በጸሎት (ማቴ. 6፡5-15)። ጸሎት ከተሳሳቱ አነሣሽ ምክንያቶች ሊመነጭ ይችላል? ክርስቶስ፥ «አዎን» ብሏል። ክርስቲያኖች የአምልኮ ግብዝነታቸውን ከሚያሳዩባቸው ዐበይት መንገዶች ኣንዱ ጸሎት ነው። ክርስቶስ ካስተማራቸው ዐበይት የአምልኮ ተግባራት አንዱ ጸሎት ነው። ብዙ ሰባኪዎች ሰዎችን ለማስደሰት ሲሉ ረዥም በሆኑ ወይም በስሜት ጸሎቶች ይጠቀማሉ። እንዲሁም ለስብከት የጸሎት ጊዜን ይጠቀማሉ። ጸሎት ከሰዎች ጋር ሳይሆን፥ ከእግዚአብሔር ጋር የምንነጋገርበት መሣሪያ ነው። ሌሎች መሪዎች የተወሰኑ ቃላትን በመደጋገም መንፈሳዊነታቸውን ለማሳየት ይፈልጋሉ። አንዳንዶች የእግዚአብሔርን ወይም የክርስቶስን ስሞች ይደጋግማሉ። ሌሎች ደግሞ ሃሌሉያ የሚለውን ቃል ይደጋግማሉ።

በኢየሱስ ዘመን ፈሪሳውያን መንፈሳዊነታቸውን በጸሎት ለማሳየት ይፈልጉ ነበር። ስለሆነም በአምልኮ ዕለት ወደ ምኩራብ ገብተው ከፊት በመቀመጥ ረዥም ጸሎቶችን ያቀርባሉ። ያም ባይሆን ሕዝብ ወደሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ሄደው ሁሉም ሰው እስኪሰማቸው ድረስ፥ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ይጸልያሉ። ክርስቶስ፥ «ይኼ ምን እርባና ኣለው?» ሲል ነቅፎአቸዋል። ብድራታቸው የእግዚአብሔር ሳይሆን፥ የሰዎች አድናቆት ነበር።

የኢየሱስ ተከታዮች የሆኑ የጸሎት አመለካከት ፍጹም የተለየ ሊሆን ይገባል። ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር የምናደርገው ንግግር ስለሆነ፥ የሰዎች መኖር አለመኖር ሊያሳስበን አይገባም። (ክርስቶስ በኅብረት መጸለይ የለብንም ኣላለም። ክርስቶስም ሆነ ሐዋርያት ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበባቸው ስፍራዎች ጸልየዋል። ነገር ግን ክርስቶስ በሕዝብ ፊት በምንጸልይበት ጊዜ አመለካከታችን ትክክለኛ መሆን እንዳለበት አስገንዝቧል። ኢየሱስ ተከታዮቹ በትክክለኛ መንገድ እንዲጸልዩ የተወሰኑ መመሪያዎችን ሰጥቷቸዋል።

ሀ. ክርስቶስ ጸሎትን ከተሳሳቱ አነሣሽ ምክንያቶች ለመጠበቅ፥ አብዛኛውን ጸሎታችንን እግዚአብሔር ብቻ በሚሰማባቸው ስውር ስፍራዎች እንድናደርግ አስተምሮናል። እግዚአብሔር ከመናገራችን በፊት ጸሎታችንን ስለሚያውቅ፥ ስለ ጸሎታችን መናገሩ የግድ አስፈላጊ አይደለም። ጮክ ብሎ መጸለዩ ተጨማሪ በረከት አያስገኝም። ጮክ ብለን መጸለያችን እግዚአብሔር በተሻለ ሁኔታ እንዲያደምጠን አያደርገውም። እግዚአብሔር ደንቆሮ ስላልሆነ መጮኽ አያስፈልገንም። ጮክ ብለን የምንጸልይ ከሆነ፥ አነሣሽ ምክንያታችንን መመርመር ይኖርብናል። ክርስቶስ ከእርሱ ጋር ከተነጋገርን፥ ለጸሎታችን መልስ እንደሚሰጠን ተናግሯል።

ለ. ጸሎት በቃላት አማካኝነት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ነው። ስለሆነም ቀጥተኛ የሆነ አነጋገር ለጸሎት ተስማሚ ነው። ክርስቶስ ቀጥተኛ ከሆነ የጸሎት ቃላት ውጪ ሳይታሰቡ የሚወረወሩ ቃላት ለጸሎት ሊያገለግሉ እንደማይገባ አስጠንቅቋል። ስሙን በመደጋገማችን ወይም ሃሌሉያ እያልን በመጮኻችን ብቻ እግዚአብሔር ጸሎታችንን በተሻለ ሁኔታ እያደምጥም። ይህንን የምናደርግ ከሆነ፥ «ለምንድን ነው የማደርገው?» ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። ያለልማድ የምንጠቀምባቸው ቃላት ብዙውን ጊዜ ለሌሎች እንደምንጸልይ ወይም ሳናስብ በልማድ እንደምንጸልይ ያሳያሉ።

ሐ. ረዥም ጸሎት የግድ አፈላጊ አይደለም። ክርስቶስ ብዙ ቃላት መደጋገም እንደማያስፈልግ ገልጾኣል። ብዙ በጸለይን ቁጥር ትክክለኛ ጸሎት እናደርጋለንን? አናደርግም። ጥርት ባለ ሁኔታ እግዚአብሔርን የሚያመሰግንና ለእግዚአብሔር ለመናገር የምንፈልጋቸውን ነገሮች የሚገልጽልን የሁለት ደቂቃ ጸሎት በቂ ነው። በተለይ በሌሎች ሰዎች ፊት ረጅም ጸሎት የምንጸልይ ከሆነ፥ ለሰዎች ሳይሆን ለእግዚኣብሔር እየጸለይን መሆናችንን በልባችን መመርመር አለብን።

የውይይት ጥያቄ፡- ኢየሱስ ፈሪሳውያንን ባስጠነቀቀባቸው በእነዚህ መንገዶች የጸለይህባቸውን ሁኔታዎች ግለጽ።

እነዚህ ደቀ መዛሙርት ጸሎት ምን እንደሆነ በትክክል እንዲረዱ ለማገዝ፥ ክርስቶስ የጸሎት መመሪያ ሰጥቷቸዋል። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ያስተማረው የአባታችን ጸሎት፥ (እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የደቀ መዛሙርት ጸሎት) ቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ፕሮግራም ለመፈጸም እንድትጠቀምበት አልነበሩም። ጸሎቱ የተሰጠው እንዴት ልንጸልይ እንደሚገባን ለማሳየት ነበር። በዚህ ጸሎት ውስጥ አስፈላጊው ነገር በውስጡ የተጻፉት ቃላት ሳይሆኑ፥ በቃላቱ ውስጥ የተካተቱት አመለካከቶች ናቸው። በዚህ የጸሎት መመሪያ በመጠቀም ብዙ ነገሮችን ልንማር እንችላለን።

ሀ. የጸሎት መሠረቱ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት መረዳት ስለ መሆኑ። አይሁዶች እግዚአብሔርን «አባታችን» ብለው ሊጠሩት አይችሉም ነበር። እንዲያውም ከክርስቶስ በፊት ማንም ሰው እግዚአብሔርን አባ አባት በሚል ዓይነት የግል መጠሪያ መጥራቱን የሚያመለክት መረጃ አልተገኘም። («አባ» የሚለው የአማርኛ ቃል አባትነትን የሚያመለክት ብቻ ሳይሆን፥ የፍቅርም መግለጫ ነው – ልክ ትንሽ ልጅ «አባዬ» እያለ እንደሚጠራው) ማለት ነው። ለአይሁዶች እግዚአብሔር የሩቅ አምላክ ነበር። እርሱ እጅግ ቅዱስ አምላክ በመሆኑ፥ በጸሎት ውስጥ ስሙን ለመጥራት የሚደፍር አልነበረም። ክርስቶስ ግን እግዚአብሔር ያን ያህል ሩቅ እንዳልሆነና ጸሎታችውን ለመስማት እንደሚፈልግ ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯል። እግዚአብሔር ልጁ ኣንዳች ነገር በፍቅርና በመተማመን ቢጠይቀው እንደሚፈቅድ ሰብአዊ ኣባት ይመስላል።

ለ የጸሉት አነሣሽ ምክንያት የእግዚአብሔር ክብር ነው። ከእግዚአብሔር አንድን ነገር ለመቀበል ጸሎትን ለራስ ወዳድነት ዓላማ ከመጠቀም ይልቅ፥ የእግዚአብሔርን ክብር ልንሻ እንደሚገባን ክርስቶስ አስተምሯል። እግዚአብሔር በሕይወታችን፥ በቤተ ክርስቲያናችንና በዓለማችን እንዲከበር ልንሻ ይገባል። እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ልጅ የሚጸልየው ጸሎት ሁሉ እግዚአብሔርን የማክበር ፍላጎት ሊያንጸባርቅ ይገባል።

ሒ ራእያችን የእግዚአብሔር መንግሥት መስፋት መሆን ኣለበት። እግዚአብሔር በሰማይ ሆኖ በፍጹማዊ ሥልጣኑ ስለሚገዛ፥ አልታዘዝህም የሚለው ማንም የለም። ወደ እግዚአብሔር የሚጸልየው ግለሰብ ቁጥጥሩ ምድርንም እንደሚያካትት መገንዘብ ይኖርበታል። የእግዚአብሔር ግዛት በሚጸልየው ግለሰብ ልብ፥ በቤተ ክርስቲያንና በዓለም ጉዳዮች ሁሉ ላይ መስፋፋት አለበት። ክፋትና ዓመፅ ባለበት ሁሉ እግዚአብሔር የክርስቶስን አገዛዝ እንደሚያመጣ ሊናፈቅ ይገባል።

መ. በጸሎት የራስ ወዳድነት አመለካከትን ልናንጸባርቅ አይገባም። ጸሎት የራስ ወዳድነት አመለካከትን ሊያንጸባርቅ ስለማይገባ፥ መሠረታዊ ያልሆኑትን ነገሮች ከእግዚአብሔር ልንጠይቅ አይገባም። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ያስተማራቸው ለሕይወት መሠረታዊ የሆነውን ዕለታዊ እንጀራ እንዲጠይቁ ነበር። የጸሎት ድፍረታችን የሚመጣው ከእግዚአብሔር አባታዊ ፍቅር ነው። ለሕይወት መሠረታዊና አስፈላጊ ነገሮችን በምንጠይቅበት ጊዜ አነሣሽ ምክንያቱ የእግዚአብሔር ክብር ሊሆን ይገባል። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የጸሎት ጥያቄያችንን እንደሚመልስ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።

ሠ. የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሆነ ሰው፥ በእግዚአብሔርና በሰዎች ፊት በንጽሕና መመላለስን ይሻል። ኃጢኣትን በምንሠራበት ጊዜ፥ የእግዚአብሔርን ይቅርታ በመጠየቅ ሕይወታችንን እናጠራለን። ከሰዎችም ጋር በስምምነት ለመኖር እንፈልጋለን። የሚበድሉንን ይቅር ማለት አለብን። ይህ አስፈላጊ ጉዳይ በመሆኑ፥ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ይቅርታ እኛ ሌሎችን ይቅር ለማለት ባለን ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ሁለት ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ተናግሯል። የበደለንን ሰው ይቅር ለማለት የማንፈልግ ከሆነ፥ በልባችን ውስጥ መራርነት እንዳለ ግልጽ ነው። ስለሆነም እግዚአብሔር ይቅር አይለንም። ከእግዚአብሔር ጋር የቀረበ ግንኙነት ከሌለን፥ ጸሎታችን መልስ ስለ ማግኘቱ ድፍረት ሊኖረን አይችልም። በጸሎታችን ልንገፋ ብንችልም፥ እግዚአብሔር አይሰማንም።

ኣንድ ሰው የሌሎችን በደል ይቅር ለማለት የሚችለው፥ እግዚኣብሔር የራሱን ኃጢአት ይቅር በማለት ያሳየውን ምሕረት ሲረዳ ብቻ ነው። የልቡን ኃጢአተኛነትና ከእግዚአብሔርም ፍርድ እንጂ በረከትን መቀበል እንደማይገባው ሲገነዝብ ሌሎችን ይቅር ይላል። ሌሎችን ይቅር ለማለት አለመፍቀድ፥ በልባችን ውስጥ ትዕቢት መኖሩንና ከሌሎች እንደምንበልጥ ማሰባችንን ያሳያል።

ረ. ልባችንንና የኃጢኣት ዝንባሌውን ለማወቅ መፈለግ አለብን። ስለሆነም በፈተና ጊዜ እግዚአብሔር እንዲረዳን እንጠይቀዋለን። ይሄኛው የጸሎት ምሳሌ አካል በምሑራኑ ዘንድ ብዙ ክርክሮችን አስነሥቷል።

በመጀመሪያ፥ «ፈተና» የሚለው ቃል በግሪክ ሁለት ትርጉሞች አሉት። ይህ ቃል ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር እምነታችንን ለመፈተንና ለማሳደግ የሚጠቀምባቸውን መከራዎችና ችግሮች ያመለክታል። ወይም ደግሞ ሰውን በኃጢአት ለመጣል የሚደረገውን የሰይጣን ፈተና ሊያመለክት ይችላል። እግዚኣብሔር ኃጢአትን እንድናደርግ እንደማይፈትነን በያዕቆብ 1፡13 ላይ በግልጽ ስለሚታይ፥ እዚህ ላይ የቀረበው ጸሎት እግዚአብሔር በቀጥታ ወደ ኃጢአት እንዳይመራን የሚጠይቅ ሊሆን አይችልም። ነገር ግን እግዚአብሔር የሰይጣንን ጥቃት በመከላከል ከኃጢአት እንዲጠብቀን ለመለመን የቀረበ ጸሎት ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ይህ ጸሎት እግዚኣብሔር በመከራው ጊዜ ኢየሱስን ከመስቀሉ የመከራ መንገድ እንዲያድነው እንደ ለመነ ሁሉ የምናቀርበው ጸሎት ይሆናል።

(ማስታወሻ፡- በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ክርስቶስ፥ «ፈቃድህ ቢሆን» ብሏል። ምንም እንኳ ይህ የጸሎት መንፈስ ቢሆንም፥ የጸሎት ኣመለካከታችን ግን መገዛትን ያካተተ መሆን አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር የምንፈልገውን ይሰጠን ዘንድ እንድናዝዘው አይፈቅድልንም። ሁልጊዜ እንደ ፍጡራን ሁሉ ከፈጣሪያችን ጋር ያለን ግንኙነት፥ የመገዛትንና የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲፈጸም የመፈለግን ስሜት ማንጸባረቅ አለበት። ስለሆነም፥ የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ስለማናውቅ ለነገሮች በምንጸልይበት ጊዜ፥ ሁልጊዜ ልመናችን፥ «ጸሎቴ እንደ ዕቅድህ ከሆነ» ማለት አለበት።)

ሁለተኛው፥ «ማዳን» የሚለውም ቃል ሁለት ፍቺዎች ስላሉት አከራክሯል። ይህ ቃል ማንኛውም ዓይነት ክፋትና መከራ ወደ እኛ እንዳይመጣ መከልከልን ሊያመለክት ይችላል። እንደዚሁም «በመከራ ጊዜ በሰላም ጠብቀን» ማለትም ይሆናል። በ1ኛ ቆሮ. 10፡13 ላይ እግዚኣብሔር ሁልጊዜ የሚያጋጥሙንን ችግሮችና ፈተናዎች የምንጋፈጥበት ኃይል እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል። በተጨማሪም እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ ለክርስቲያኖች ለበጎ እንደሚያደርግ ይናገራል (ሮሜ 8፡28)። ስለሆነም ክርስቶስ ችግሮቻችንን እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንድንቀበልና ፈተናውን እንድናልፍ ይፈልጋል። ከዚህም በስተቀር ከእግዚአብሔር ዘንድ የተፈለገውን ትምህርት እስክናገኝ ድረስ በእምነታችን እንድንጸና የሚያስፈልገንን ኃይል ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔርን እንድንማጠን ያሳስበናል።

ሦስተኛው፥ «ክፉ» የሚለው ቃል ምን ትርጉም ኣለው? በግሪኩ ይህ ቃል «ክፉ» ወይም «ክፉው» ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። በመሆኑም ቃሉ ኃጢአትን ወይም ኃጢአትን እንድንሠራ የሚፈትነንን ሰይጣንን ሊያመለክት ይችላል። ስለሆነም ይህ ጸሎት ድክመታችንን በመናዘዝ፥ ሰይጣን እንድንፈጽም ከሚፈልገው ኃጢአት ለመራቅ ኃይልን የምንጠይቅበት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የጸሎታችን ክፍሎች ሊሆኑ የሚገባቸውን መንፈሳዊ መርሖዎች ዘርዝር። ለ) ከእነዚህ መርሖዎች ብዙውን ጊዜ በጸሎትህ ውስጥ የማትጠቀምበት መርሕ የትኛው ነው? ሐ) ከእነዚህ መርሖዎች ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የማይጠቀሙባቸው የትኞቹ ናቸው?

እንደምታስታውሰው፣ «መንግሥት ያንተ ነውና፥ ኃይል ምስጋና ክብርም ለዘላለሙ አሜን» ስለሚለው የመጨረሻው የጸሎቱ ክፍል፥ ማብራሪያ አልሰጠንም። ለዚህ ምክንያቱ ምሑራን ይህ በመጀመሪያው ጽሑፍ ውስጥ የሌለና በኋላ በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ የተጨመረ መሆኑን በማመናቸው ነው። ምሑራን የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ጸሎት ወደ ዝማሬ እንደ ለወጠችና በራእይ 5፡13 መሠረት ጸሎቱን ሲጨርሱ ይህንን ሐረግ እንደጨመሩበት ያምናሉ።

  1. በጾም አማካይነት ስለ ማምለክ (ማቴ. 6፡16-18)። ሰዎች ለተለያዩ ምክንያቶች ይጾማሉ። አንዳንዶች የቤተ ክርስቲያናቸውን ትእዛዝ ለማክበር ሲሉ በሳምንት ለተወሰኑ ቀናት ይጾማሉ። (ለምሳሌ፥ ፈሪሳውያን ሰኞና ሐሙስ ቀን ሲጾሙ፥ የኦርቶዶክስ አማኞች ደግሞ ረቡዕና ዓርብ ይጾማሉ።) ሌሎች ደግሞ የተወሰኑ ምግቦችን ትተው የተቀሩትን እየተመገቡ ይጾማሉ። ሌሎች ደግሞ (ሙስሊሞች በረመዳን ጾም እንደሚያደርጉት) በተወሰኑ ሃይማኖታዊ በዓላት ወቅት አንዳንድ ምግቦችን አይበሉም፥ ጨርሰው ምንም ዓይነት ምግብ የማይበሉበት ጊዜ አለ። ክርስቶስ ስለ እነዚህ ጾሞች የተናገረው ነገር አልነበረም።

ኣይሁዶች ሦስት ዓይነት አጽዋማት (ጾሞች) ነበሯቸው። በመጀመሪያ፥ የመታሰቢያ ጸሎት ነበር። አይሁዶች አሳዛኝ ታሪኮችን ወይም እግዚአብሔር በተለየ መንገድ ለእነርሱ የሠራባቸውን ጊዜ እያስታወሱ ከምግብ ርቀው የሚያከብሯቸው በዓላት ነበሩ። (ለምሳሌ፥ የስርየት ቀን።) ሁለተኛው፥ እንደ ፈሪሳውያን ያሉ አንዳንድ አይሁዶች በተወሰኑ የሳምንት ቀናት ውስጥ አይመገቡም ነበር። መጀመሪያ ይህ ጾም የታቀደው በእነዚህ ቀናት በጸሎትና በአምልኮ ላይ እንዲያተኩሩ ለማገዝ ነበር። በኋላ ይህ ወደ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ተለወጠ። ሦስተኛው፥ አይሁዶች ከምግብ ርቀው በግላቸው ይጾሙ ነበር። የግል ጾሞች ዓላማ ግለሰቡ በጸሎት ላይ እንዲያተኩር ለማገዝ ነበር (አስ. 4፡16)። ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው በጉዳዩ ላይ ለማተኮር የሚጸልየው ችግር በሚከሰትበት ጊዜ ነበር። ይሁንና ይህንን ጸሎት ልማድ አድርገው ሥጋቸውን እንደሚያሸንፉና ፈሪሳውያን እንደሆኑ ለማሳየት የሚሞክሩ ወገኖች ነበሩ።

ብዙ ፈሪሳውያን የተሳሳተ የጾም አመለካከት ነበራቸው። በጸሎት ላይ መሆናቸውን ለሰዎች ለማሳየት ሲሉ የተወሰኑ ልብሶችን ይለብሱ ነበር። እንዲሁም ፊታቸውን ከመታጠብ ይቆጠቡና እንዲህ ዓይነት ብዙ ተግባራትን ያከናውኑ ነበር። ፈሪሳውያን ጹዋሚነታቸውን ሰዎች አይተው በመንፈሳዊነታቸው እንዲያከብሩዋቸው ይፈልጉ ነበር።

ክርስቶስ በቀዳሚነት የጠቀሰው ይህንኑ ሦስተኛውን ግላዊ የጸሎት ዓይነት ነበር። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲጾሙ ቢያበረታታም፥ የግል ጸሎት በሚይዙበት ጊዜ፥ ትክክለኛ አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚገባ ሳያስጠነቅቃቸው አላለፈም። መንፈሳዊነታችንን ለማሳየት ስንል ልንጾም አይገባንም። በምንጾምበት ትክክለኛ ምክንያት ላይ ለማተኮር እንችል ዘንድ፥ ስለ ጾማችን ማወጅ ሳያስፈልገን በስውር መጾም አለብን (ለምሳሌ፥ ልዩ ልብሳችንን ሳንለብስና ፊታችንን ሳናኮማትር) ለሌሎች መንፈሳዊነታችንን ሳናሳይ በምንጸልይበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ልባዊ ጸሎታችንን እንደሚያዳምጥ ልንተማመን እንችላለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ አማኞች የሚጸልዩት ለምንድን ነው? ለ) ይህ ጾም ትርጉም የሌለው ልማድ ሊሆን የሚችልበትን ሁኔታ በምሳሌዎች አስረዳ። ሐ) እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በጾም ሊጠቀም የሚችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎችን ለማስደሰት ወይም ለመታወቅ ሲባል የሚደረጉ ሌሎች የአምልኮ ተግባራትን ዘርዝር። ለ) ለእግዚኣብሔር ብቻ በሚቀርብና ሰዎችን ለማስደሰት በሚካሄድ ኣምልኮ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: