የሉቃስ ወንጌል ልዩ ገጽታዎች

1. የሉቃስ ወንጌል ከወንጌላት ሁሉ የላቀ ሥነ ጽሑፋዊ ውበት አለው። መጽሐፉ የተጻፈው ጥልቅ የግሪክ ቋንቋ ክህሎት ባለው ሰው ነው።

2. ከሦስቱ ተመሳሳይ ወንጌላት መካከል ሉቃስ የተለየ ነው። የማቴዎስንና የማርቆስን አጠቃላይ ገጽታ ቢከተልም፣ ካቀረባቸው መረጃዎች መካከል 50 በመቶው ከማቴዎስና ማርቆስ የተለየ ነው።

3. ሉቃስ የታሪክ ባለሙያ እንደ መሆኑ መጠን፣ ሁኔታዎቹ የተፈጸሙበትን ትክክለኛ ጊዜ ይገልጻል። መጥምቁ ዮሐንስ መቼ አገልግሎቱን እንደ ጀመረ (ሉቃስ 3፡1-2)፣ የሮም ገዥዎች እነማን እንደሆኑና ሌሎችንም ነጥቦች ይገልጻል። ሉቃስ የክርስቶስን ሕይወት በግልጽ ታሪካዊ የጊዜ ቀመር ውስጥ አኑሮታል።

4. ሉቃስ ሌሎች ሰዎችንና መጻሕፍትን መረጃ አድርጎ እንደ ተጠቀመ ገልጾአል። ከእነዚህ መረጃዎች መካከል ማቴዎስና ማርቆስ ሊካተቱ ቢችሉም፣ ሌሎች እጅግ ብዙ የጽሑፍ መረጃዎችም ሳይኖሩ አይቀርም። መንፈስ ቅዱስ የትኞቹ የጽሑፍ መረጃዎች የመጽሐፍ ቅዱስ አካል መሆን እንዳለባቸው በጥንቃቄ መርጧል። ምክንያቱም ስለ ክርስቶስ የተነገሩ ታሪኮች ከሰው ወደ ሰው እየተላለፉ ሲሄዱ እውነተኝነት ሊጎድላቸው ይችላልና።

የውይይት ጥያቄ፡- ሉቃስ 2፡14፣32፣38 አንብብ፡፡ እነዚህ ምንባቦች የእግዚአብሔር የደኅንነት ዕቅድ ለሰዎች ሁሉ እንደሆነ የሚያስረዱት እንዴት ነው?

5. ሉቃስ፥ ወንጌሉ ሁሉን አቀፍ ባሕርይ እንዳለው በአጽንኦት ገልጾአል። ሉቃስ የኢየሱስን የዘር ሐረግ የጀመረው እንደ ማቴዎስ የአይሁዶች አባት ከነበረው ከአብርሃም ወይም ከዳዊት ሳይሆን፣ የመጀመሪያው ሰውና የሰው ልጆች ሁሉ አባት ከነበረው ከአዳም ነው (ሉቃስ 3፡38)። መላእክት የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ሲያውጁ፥ መልካሙ የምሥራች ለሰዎች ሁሉ እንደሆነ ተናግረዋል (ሉቃስ 2፡14)። አይሁዳዊው ስምዖን ኢየሱስ የአሕዛብ ብርሃን እንደሆነ መስክሯል (ሉቃስ 2፡32)። ሉቃስ ወደ ብሉይ ኪዳን በማመልከት፥ አሕዛብን የእውነተኛው እምነት መገለጫዎች ማብራሪያ አድርጎ ጠቅሷቸዋል ሉቃስ 4፡25-27 11፥31-32)። ኢየሱስ በደጉ ሳምራዊ አማካይነት ፍቅር ምን እንደሆነ ገልጾአል (ሉቃስ 10፡30-37)።

6. ሉቃስ ከየትኞቹም የወንጌል ጸሐፊዎች በላይ ስለ ኢየሱስ የልጅነት ጊዜ ዝርዝር ጉዳዮችን አቅርቧል። ቅድስት ማርያምን በተመለከተ ስለ ድንግል መውለድ ይተርክልናል። በተጨማሪም መጥምቁ ዮሐንስ ተምአራዊ በሆነ መንገድ እንደ ተወለደ፤ ኤልሳቤጥ ማርያምን እንደ ጎበኘች፣ እረኞች ሕጻኑን ኢየሱስን ለመጎብኘት እንደ መጡ፣ ኢየሱስ እንደ ተገረዘና ወደ ቤተ መቅደስ እንደ ተወሰደ፣ እንዲሁም በ12 ዓመት ዕድሜው በቤተ መቅደስ ውስጥ የሃይማኖት መሪዎችን እንዳስደነቃቸው ያስረዳል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሉቃስ 8፡1-3፤ 15፡8-10፤ 7፡11-15 አንብብ። ኢየሱስ ለሴቶች ያለውን አክብሮት ያሳያው እንዴት ነበር?

7. ሉቃስ ከሌሎቹ ወንጌላት በላይ ሴቶች በኢየሱስ አገልግሎት ውስጥ የነበራቸውን ልዩ ድርሻ ገልጾአል። ማቴዎስና ማርቆስ በአንድነት ስለ ሴቶች 49 ጊዜ የጠቀሱ ሲሆን፣ ሉቃስ ብቻውን 43 ጊዜ ጠቅሷል። ኢየሱስ ለሴቶች የነበረው ግምት በዘመኑ ከነበሩት ሁሉ የተለየ ነበር። ሉቃስ ሴቶች እንዴት ኢየሱስን ከሁሉም በተሻለ ሁኔታ ይረዱ እንደነበሩ ያስረዳል። ሕጻኑ ኢየሱስ ለሚያከናውነው ተግባር እግዚአብሔርን ያመሰገነችው ሴት ነበረች (ሉቃስ 2፡36-38)። ኢየሱስ ሴቶች የደቀ መዛሙርቱ ቡድን አባላት እንዲሆኑ ፈቅዷል። ዮሐና የተባለች ሴት የአንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ሚስት ነበረች (ሉቃስ 8፡1-3)። ኢየሱስ ከፈወሳት በኋላ የምቾት ኑሮዋን ትታ ከስፍራ ስፍራ የሚዞረውን የኢየሱስን ቡድን ተቀላቀለች። ኢየሱስን ከመውደዱና ከማክበርዋ የተነሣ ለአገልግሎቱ የገንዘብ ድጋፍ ታደርግ ነበር። ከሞተም በኋላ ተስፋ ቆርጣ ወደ ቤቷ ሳትመለስ፥ ከኢየሱስ መስቀል አጠገብ ቆይታለች። ከዚህም የተነሣ ባዶውን መቃብር ከተመለከቱት አንዷ ለመሆን በቅታለች። ኢየሱስ በሚናገራቸው ምሳሌዎች ውስጥ ሴቶችን ያካትት ነበር (ሉቃስ 13፡20-21፤ 15፡8-10)። ኢየሱስ ልጆቻቸውን ከሞት በማስነሣት ሉቃስ 7፡11-15)፣ ንስሐቸውንና ፍቅራቸውን በማክበር (ሉቃስ 7፡36-50)፣ በመፈወስ (ሉቃስ 13፡10-13) እና በመሳሰሉት ለሴቶች ርኅራኄን አሳይቷል።

8. በሁለቱም መጽሐፎቹ ውስጥ ሉቃስ በመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ላይ አጽንኦት ሰጥቷል። መንፈስ ቅዱስ ማርያም እንድትፀንስ አድርጓል። መጥምቁ ዮሐንስም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታል (ሉቃስ 1፡15)። ሌሎች እንደ ኤልሳቤጥ (ሉቃስ 1፡41)፣ ዘካርያስ (ሉቃስ 1፡67) እና ስምዖን (ሉቃስ 2፡25-27) የመሳሰሉ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሊናገሩ ችለዋል። የኢየሱስ ሕይወት ሙሉ በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ አመራር ሥር ነበር። በተጠመቀ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ከተሞላ በኋላ ወደ ምድረ በዳ ተወስዷል (ሉቃስ 4፡1)። ኢየሱስ በገሊላ ያከናወነው አገልግሎት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተደረገ ነበር (ሉቃስ 4፡14)። ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ደስታ ተሞልቶ ነበር (ሉቃስ 10፡21)። ኢየሱስ ለተከታዮቹ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ እንደሚሰጥ ቃል ገብቶላቸው ነበር ሉቃስ 11፡13፤ 12፡12)።

9. ማቴዎስ ኢየሱስ የእስራኤል ንጉሥ መሆኑን ሲያመለክት፥ ማርቆስ ደግሞ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ባሪያ መሆኑን ያስረዳል። ሉቃስ ደግሞ በኢየሱስ ሰብአዊነት ላይ በማተኮር ፍጹም ሰው መሆኑን አመልክቷል።

10. ሉቃስ ሰዎች እግዚአብሔርን ያመሰገኑባቸውን መዝሙራት (ቅኔዎች) በመጽሐፉ ውስጥ አካትቷል። ኤልሳቤጥ (ሉቃስ 1፡39-45)፣ ማርያም (ሉቃስ 1፡46-55)፣ ዘካርያስ (ሉቃስ 1፡67-79)፣ መላእክት (ሉቃስ 2፡13-14) እና ስምዖን (ሉቃስ 2፡28-32) የዘመሯቸውን መዝሙሮች በሉቃስ ወንጌል ውስጥ እናገኛለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሉቃስ 3፡21፤ 5፡16፤ 6፡12፣ 28፤ 9፡28-29፤ 11፡1፤ 22፡40-46፤ 23፡34፣ 46 አንብብ። ኢየሱስ እንደ ጸለየ የተነገረባቸውን የተለያዩ አጋጣሚዎች ዘርዝር።

11. ሉቃስ በኢየሱስ የጸሎት ሕይወት ላይ ትኩረት ሰጥቷል። እርሱም ሌሎች ያልጠቀሷቸውንና ኢየሱስ የጸለየባቸውን ሰባት ጊዜያት አመልክቷል። መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ የመጣውኢየሱስ እየጸለየ ባለበት ወቅት ነበር (ሉቃስ 3፡21)። ብዙውን ጊዜ ብቻውን ሆኖ ይጸልይ ነበር (ሉቃስ 5፡16)። ኢየሱስ አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ከመምረጡ በፊት ጸልዮአል (ሉቃስ 6፡12-13)። በጸለየበት ጊዜ መልኩ ተለውጦ ክብሩ ተገልጾአል (ሉቃስ 9፡29)። በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እንኳ ኢየሱስ ወደ እግዚአብሔር ጸልዮአል (ሉቃስ 23፡34፣ 46)።

12. ሉቃስ፥ ከኢየሱስ ምሳሌዎች ብዙዎቹን በመጽሐፉ ውስጥ አካትቷል። ከ22 ምሳሌዎች መካከል 17ቱ የሚገኙት በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ብቻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሉቃስ 1፡53፣ 4፡18፤ 6፡20፣ 24፤ 12፡16-21፤ 6፡19-31 አንብብ። ኢየሱስ ለድሆችና ለራስ ወዳድ ባለጠጎች ስለነበረው አመለካከት እነዚህ ጥቅሶች ምንን ያስተምራሉ?

13. ሉቃስ፥ ኢየሱስ ለድሆች የነበረውን ፍቅር ገልጾአል። የኢየሱስ ቤተሰቦች ድሆች በመሆናቸው፥ ለድሆች የተፈቀደውን መሥዋዕት ለማቅረብ ተገድደው ነበር (ሉቃስ 2፡24)። ኢየሱስ አገልግሎቱን በጀመረ ጊዜ ሉቃስ ይህ ለድሆች ወንጌልን መስበክ እንደሆነ አመልክቷል (ሉቃስ 4፡18)። ሉቃስ ለድሆች የሚሰጠውን ይህንኑ ልዩ ትኩረት ድሆችን ብፁዓን ብሎ በመጥራት (ሉቃስ 6፡20)፣ እግዚአብሔር ለድሆች የሚያስፈልጋቸውን እንደሚሰጣቸው (ሉቃስ 1፡53-54) ገልእል፣ እንዲሁም የለማኙን ታሪክ በማቅረብ (ሉቃስ 16፡19-31) በግልጽ አሳይቷል። በአንጻሩም፣ ሉቃስ ለሀብታሞች ብዙ ማስጠንቀቂያዎችን ይሰጣል። ማርያም ባለጠጎች ባዶ እጃቸውን እንደሚመለሱ ስትገልጽ (ሉቃስ 1፡53)፣ ኢየሱስ ለባለጠጎች ወዮላቸው ብሏል (ሉቃስ 6፡24)። ባለጠጎችን የሚቃወሙ አያሌ ምሳሌዎችም ቀርበዋል ሉቃስ 12፡16-21፤ 16፡19-31)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: