ወደ አብ የሚያደርሰው መንገድ (ዮሐ. 14፡1-14)

ደምሴ ሥራ የሌለው ክርስቲያን ነው፤ እርሱና ቤተሰቡ በልተው የሚያድሩት ምግብ ለመግዛት የሚያስችል በቂ ገንዘብ የሚያገኘው አልፎ አልፎ ነው። የሚረዳው ዘመድ እንኳ አልነበረም። «ለነገ እንዳልጨነቅ እግዚአብሔር ለምን በቂ ገንዘብ አይሰጠኝም?» ሲል ያስባል። «ሥራ የማገኘው እንዴት ነው? ለኑሮ የሚያስፈልገንን ገንዘብ የማገኘው ከየት ነው?» ብታመም የምታክመው በምኔ ነው? በማለት ስለ ወደፊት ኑሮው እጅግ ይጨነቃል። «ብሞትስ፣ ባለቤቴንና ልጆቼን ማን ይንከባከባቸዋል?» እነዚህ አሳቦች ውስጡን ሰርስረው ለጭንቀት ዳረጉት።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ፍርሃትና ጭንቀት አሳባችንን በቀላሉ የሚቆጣጠሩት ለምንድን ነው? ለ) ዮሐ 14፡1-4 እና ዕብ 11፡10፥ 16 አንብብ። እነዚህን ምንባቦች ከሕይወታችን ጋር ብናዛምድ ጭንቀትን እንድናሸንፍ እንዴት ይረዱናል?

ጭንቀት የሚመነጨው ካለማመን ነው። «ምግብና ልብስ ከየት እናገኝ ይሆን?» እያልን የምንጨነቅ ከሆነ፥ ክርስቶስ በየዕለቱ የሚያስፈልገንን ነገር ለማሟላት የገባልንን ቃል ዘንግተናል ማለት ነው (ማቴ. 6፡25-34)። ስለወደፊቱ የምንጨነቅ ከሆነ፥ ክርስቶስ «የነገ» ጌታ እንደ ሆነ ዘንግተናል ማለት ነው። ስለ ጤንነታችን የምንጨነቅ ከሆነ፥ ክርስቶስ ታላቁ ሐኪም እንደ ሆነ ረስተናል ማለት ነው። እንዲሁም፥ ስለ ቤተሰቦቻችን የምንጨነቅ ከሆን፥ ክርስቶስ እኛ ከምንወዳቸው በላይ እንደሚወዳቸውና አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደሚያደርግላቸው ዘንግተናል ማለት ነው። ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ ተለይቷቸው እንደሚሄድ ባወቁ ጊዜ በጣም ተጨነቁ። ከሦስት ዓመት በላይ ከክርስቶስ ጋር ኖረዋል። ሥራቸውንም ትተው ነበር። በዚህ ላይ ድሆች ነበሩ። ወደፊት ምን ይገጥማቸዋል? ያለ ክርስቶስ የሕይወትን ማዕበል እንዴት ይቋቋሙታል? ስለሆነም፥ ክርስቶስ በአካል ከእነርሱ ጋር በማይኖርበት ጊዜ የወደፊት ሕይወታቸው እንዴት እንደሚሆን የተለያዩ እውነቶችን በመንገር ያጽናናቸዋል።

ዮሐንስ 14-17 ኢየሱስ፥ ደቀ መዛሙርቱ ስለ እርሱ፥ ስለ መንፈስ ቅዱስና ስለ ደቀ መዝሙርነት ሕይወት እንዲነዘቡ የሚፈልጋቸውን አንዳንድ አጠቃላይና እጅግ ጠቃሚ እውነቶችን አካትቶ ይዟል።

  1. ኢየሱስ ለተከታዮቹ ዘላለማዊ የመኖሪያ ስፍራ እንደሚያዘጋጅ ቃል ገባ (ዮሐ 14፡1-4)

ምን ጊዜም ቢሆን መለያየት ሥቃይ አለበት። ክርስቶስ ወደ ሰማይ ተመልሶ መሄዱ በደቀ መዛሙርቱ ላይ የመለየትን ሥቃይና ጥርጣሬ እንዳያስከትልባቸው በማሰብ የተለያዩ እውነቶችን አስተማራቸው። እነዚህ እውነቶች እያንዳንዱ ክርስቲያን ዛሬ ሊያውቃቸውና ከሕይወቱ ጋር ሊያዛምዳቸው የሚገቡ ናቸው። የክርስቶስ ተከታዮች በብርቱ መከራና ሥቃይ መካከል በተስፋ ሊኖሩ የሚችሉት እንዴት ነው? ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ሁለት ዐበይት እውነቶችን አስጨብጧል፡-

ሀ. ደቀ መዛሙርቱ ሁልጊዜ በእግዚአብሔርና በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት አጽንተው መያዝ አለባቸው። እምነት እንዴት እንደሚሠራ ባናውቅም፥ እግዚአብሔር በሰጠው ቃል ላይ ተመሥርቶ መኖር ነው። የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃሎች በማወቅና በእነዚህ ቃሎች ላይ የተመሠረተ ሕይወት ለመምራት በመቁረጥ፥ ተስፋችንን አጽንተን እንይዛለን። ተስፋ ቆርጠን የምንጨነቀው ዓይኖቻችንን ከእግዚአብሔር ላይ ስናነሣ፥ የተስፋ ቃሎቹን ስንረሳና ፍጹም የተስፋ ቃሎቹን ከሕይወታችን ጋር ሳናዛምድ ስንቀር ነው።

ለ. የክርስቶስ ተከታዮች ዓይናቸውን በዘላለሙ ተስፋ ላይ ማድረግ አለባቸው። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን እንደማይተዋቸው፥ በሰማይም እነርሱ የሚኖሩበትን ስፍራ እንደሚያዘጋጅላቸው ቃል ገብቶላቸዋል። ስለሆነም፥ በእግዚአብሔር አብ መንፈሳዊ ቤት፥ ኢየሱስ ለተከታዮቹ ሁሉ የመኖሪያ ስፍራ ያዘጋጅላቸዋል። ሕዝቡ ሁሉ ወደ እርሱ ዘንድ ሲሄዱ በአንድ ትልቅ ቤት ውስጥ እንደማይታጎሩና በዘላለሙ ስፍራ እግዚአብሔር ለልጆቹ ለእያንዳንዳቸው የተለየ ስፍራ እንደሚያዘጋጅላቸው ከክርስቶስ ትምህርት መገንዘብ ይቻላል።

የውይይት ጥያቄ፡- ዓይናችንን በዘላለሙ ተስፋ ላይ ማድረጋችን በእምነታችን ጸንተን እንድንቆም የሚረዳን እንዴት ነው?

  1. በኢየሱስ ማመን ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ መንገድ ነው (ዮሐ 14፡5-14)

መንገድ ወደምንፈልግበት ስፍራ እንድንደርስ ስለሚረዳን፥ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ነገር ግን ትክክለኛው መንገድ የትኛው እንደ ሆነ ማወቅ አለብን። ደቀ መዛሙርቱ ወደ እግዚአብሔር አብና በሰማይ ወደሚገኘው ወደ ዘላለማዊ ቤታቸው በሚያደርሰው ትክክለኛው መንገድ ላይ እየተጓዙ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ፈልገው ነበር። ክርስቶስም ብርቱ በሆኑ ቃላት የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷቸዋል፡-

ሀ. ኢየሱስ «እኔ መንገድ፥ እውነትና ሕይወት ነኝ፤’ በእኔ በቀር ማንም ወደ አብ ሊመጣ አይችልም» አላቸው (ዮሐ 14፡6)። ይህ ክርስቶስ የተናገረው ስድስተኛው «እኔ ነኝ» የሚለው ዐረፍተ ነገር ነው። በዚህ ንግግሩ ኢየሱስ ወሳኝ አሳቦችን ሰንዝሯል፤ ወደ ሰማይ እናደርሳለን የሚሉ ሰው ሠራሽ መንገዶች እንዳሉ ቢገልጽም፥ ሁሉም ግን እውነተኛ መንገዶች እንዳልሆኑ አመልክቷል። በራሳቸው መንገድ ወደ ሰማይ ለመድረስ የሚጥሩ ሰዎች፥ ካሰቡት ሊደርሱ አይችሉም። በመሐመድ፥ በቡድሃ ወይም በተከታዮቻቸው የሚያምኑ ሰዎች፥ መንግሥተ ሰማይ ሊገቡ አይችሉም። ማንም ሰው ወደ እግዚአብሔር ሊደርስ የሚችለው በክርስቶስ በማመን ብቻ ነው። ምንም እንኳ ዛሬ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰው መንገድ አንድ ብቻ ነው የሚለው አሳብ በዓለም ላይ ተወዳጅነት ባይኖረውም፥ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን ግን ይህንን ሐቅ ነው። ይህ ክርስቲያኖች በራሳቸው ያመጡት አሳብ ሳይሆን፥ ክርስቶስ ራሱ የተናገረው ነው። ክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰው ብቸኛው መንገድ እርሱ ራሱ እንደ ሆነ ተናግሯል። ክርስቶስ እውነትን ሁሉ የያዘ አምላክ በመሆኑ፥ እውነት የሆነውን አሳብ ማስተማር ብቻ ሳይሆን፥ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ እውነተኛ መንገድም ነው። እንዲሁም፥ መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ሕይወትን የሚቆጣጠረው ክርስቶስ ነው። ስለሆነም፥ የዘላለም ሕይወት የሚገኘው በክርስቶስ አማካይነት ብቻ ነው።

ለ. ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ ትክክለኛ እንደራሴ ነው። ወደ ክርስቶስ መመልከት፥ ወደ እግዚአብሔር እንደ መመልከት ያህል ነው። ኃይላቸው፥ ባሕርያቸውና ዓላማቸውም አንድ ነው። ክርስቶስ ፈቃዱን ለአብ ስላስገዛ፥ አብ የነገረውን ብቻ ተግባራዊ ያደርጋል፤ ደግሞም ከእርሱ ጋር በፍጹም ስምምነት ስለሚሠራ፥ የአንዱ ሥራ የሌላውም ነው። (ማስታወሻ፡የሥላሴን ሕልውና የካዱና «ኢየሱስን ብቻ» እናመልካለን የሚሉ ተከታዮች እንደሚያስተምሩት በዚህ ክፍል ክርስቶስ ከአብ ጋር አንድ አካል መሆኑን እየገለጸ አይደለም። የተለያዩ አካላት መሆናቸው በዚህም ሆነ በሌሎች ክፍሎች ግልጽ ነው። ዮሐንስ የሚናገረው ግን በመካከላቸው ስላለው ፍጹም ስምምነትና የጋራ አንድነት ነው። እግዚአብሔር አብና እግዚአብሔር ወልድ ድርጊቶችን ሁሉ በጋራ ተስማምተው ያከናውናሉ።)

ሐ. የክርስቶስ ተከታዮች ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት በማድረግ ደስ ይሰኛሉ። እነርሱም ክርስቶስ ካደረጋቸው ነገሮች የበለጠ እንደሚያደርጉ ገልጾአል። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነው? ኢየሱስ እንዲህ ሲል እኔ ካደረግሁት ተአምር የበለጠ ታደርጋላችሁ ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። እርሱ ለማለት የፈለገው ግን፥ እኔ ካገለገልሁት ሕዝብ የበለጠ ቁጥር ያለውን ሕዝብ ታገለግላላችሁ ማለቱ ነው። ክርስቶስ በሥጋዊ አካል ስለ ተወሰነ፥ በአንድ ጊዜ በብዙ ቦታዎች ላይ ለመገኘት አይችልም ነበር። ስለሆነም፥ የሚያገለግለው የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ ነበር። ነገር ግን የክርስቶስ ተከታዮች በሕይወታቸው ውስጥ ካለው መንፈስ ቅዱስ የተነሣ ብዙ ሰዎችን ለመድረስ ይችላሉ። የክርስቶስ ተከታዮች በዓለም ሁሉ ሲሰራጩ፥ በክርስቶስ ኃይል ብዙ ተአምራትን ይሠራሉ። በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሳይወሰኑ እስከ ምድር ዳርም ይደርሳሉ። ተአምራቱም አሁን ተግባራዊ በመሆን ላይ ናቸው። ከሁሉም የሚልቀው ተአምር የክርስቶስ ተአምር ይሆናል። ይህም የክርስቶስ ተከታዮች የእግዚአብሔር መሣሪያዎች ሆነው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ መንፈሳዊ ጎዳና መመለሳቸው ነው።

ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ያለውን ዓይነት የኃይል ምንጭ ሊኖራቸው ይችላል። በክርስቶስ አማካይነት ከእግዚአብሔር አብ ጋር ኅብረት ልናደርግ እንችላለን። ልጆቹ እንደ መሆናችን መጠን፥ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ካለንና ክርስቶስ እንዳደረገው ፈቃዳችንን ለእግዚአብሔር ፈቃድ የምናስገዛ ከሆነ፥ እግዚአብሔር የምንጠይቀውን ሁሉ ለእኛና በእኛ አማካይነት ተግባራዊ ያደርጋል። ይህ እውነት የሚሆነው ፈቃዳችንን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ስናስገዛና የምንጸልይባቸው ነገሮች እግዚአብሔር እንዲከናወኑ የሚፈልጋቸው ሲሆኑ ብቻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እንዳንድ ሰዎች ልመናችን ምንም ይሁን ምን፥ ትክክልም ይሁን ስሕተት፥ እግዚአብሔር ጸሎታችንን ሁሉ ለመመለስ ቃል ገብቶልናል ይላሉ። ይህ የተስፋ ቃል ምን ማለት ይመስልሃል? ለ) ጸሎቱ ላልተመለሰለት ሰው ምን ምላሽ ትሰጠዋለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: