የአሕዛብ ሐዋርያ የነበረው ጳውሎስ ከማንኛውም ጸሐፊ በላይ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን እንዲጽፍ እግዚአብሔር ተጠቅሞበታል (ጳውሎስ ከሌሎቹ ጸሐፊዎች የሚበልጠው በጻፈው ቁም ነገር ብዛት ሳይሆን በጻፈው መጻሕፍት ብዛት ነው።) የቀድሞዪቱ ቤተ ክርስቲያን የጳውሎስን 13 መጻሕፍት በመሰብሰብ ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ቀጥሎ አስቀምጣቸዋለች። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መጻሕፍቱን ለምን በዚህ መልክ እንዲቀመጡ እንዳደረጓቸው አናውቅም። መጻሕፍቱ የተቀመጡት ጳውሎስ በጻፋቸው የጊዜ ቅደም ተከተል አይደለም። ምናልባትም ዋናው መስፈርት የገጹ ብዛት ሳይሆን አይቀርም። የመጀመሪያዎቹ ሦስት መጻሕፍት (ሮሜ፥ 1ኛ ና 2ኛ ቆሮንቶስ) ጳውሎስ ከጻፋቸው መልእክቶች ከፍተኛ የገጽ ብዛት ያላቸው ናቸው። ሮሜ ከጳውሎስ ረዣዥም መልእክቶች የመጀመሪያው ሆኖ የቀረበው የድነትን (የደኅንነትን) መንገድ በማብራራት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ የተነሣ ሳይሆን አይቀርም። ገላትያ ከቆሮንቶስ ቀጥሎ የተጻፈው ጳውሎስ የሐሰት ትምህርትን በመከላከል ከጻፋቸው የመጀመሪያ መልእክቶች አንዱ በመሆኑ ነው። ቀጣዮቹ መልእክቶች «የእስር ቤት መልእክቶች» (ኤፌሶን፥ ፊልጵስዩስና ቆላስይስ) በመባል ይታወቃሉ። እነዚህ ጳውሎስ በሮም ታስሮ የጻፋቸው መልእክቶች ስለ ክርስቶስ የጠለቀ ትምህርት ይሰጣሉ። ከዚያም የክርስቶስ ዳግም ምጽእት ጉዳይ ግራ ላገባቸው የተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን የተጻፉት ሁለት አጫጭር መልእክቶች ቀርበዋል። የመጨረሻዎቹ አራት መልእክቶች ከጳውሎስ ጋር ቀረቤታ ለነበራቸው ሦስት ግለሰቦች የተጻፉ ናቸው። ሁለቱ መልእክቶች የተጻፉት የጳውሎስ ወጣት ሠልጣኝና የሥራ ተባባሪ ለነበረው ለጢሞቴዎስ ነው። ጢሞቴዎስ በሁለተኛውና ሦስተኛው የጳውሎስ የሚሲዮናዊነት አገልግሎት ላይ ተሳትፎአል። ሌላው የጳውሎስ ረዳት የነበረው ቲቶ አንድ መልእክት የተጻፈለት ሲሆን፥ የመልእክቱም አሳብ በቀርጤስ ቤተ ክርስቲያንን በእምነቷ እንዴት እንደሚገነባ የሚያሳይ ነበር። የመጨረሻውና ከጳውሎስ መልእክቶች ሁሉ የሚያጥረው ፊልሞና ለተባለ የባሪያ አሳዳሪ ክርስቲያን የተጻፈ ነበር። የተጻፈውም በእስር ቤት መልእክቶች በተጻፉበት ጊዜ ነበር።
የጳውሎስን መልእክቶች በጥንቃቄ በማጥናት የሚከተሉትን እውነቶች ልንመለከት እንችላለን።
ሀ. ጳውሎስ የጻፋቸው መልእክቶች ሁሉ በአዲስ ኪዳን ውስጥ አልተካተቱም። ቢያንስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የጻፈው አንድ መልእክት አልታተመም። ምሁራን ይህንን ወደ ቆሮንቶስ ተልኮ የጠፋው መልእክት ብለው ይጠሩታል። መንፈስ ቅዱስ ይህ መልእክት በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንዲካተት ስላልፈቀደ እንዲጠፋ ሆኗል።
ለ. ከእነዚህ መልእክቶች አብዛኞቹ የተላኩት በሮም ግዛት ሁሉ በሚገኙ ከተሞች ለተበተኑት አብያተ ክርስቲያናት ነበር። ጳውሎስ የእነዚህን አብያተ ክርስቲያናት የእምነት ችግሮችን ለማስወገድ በመሻት ነበር የጻፈላቸው። መጻሕፍቱ የተሰየሙት አብያተ ክርስቲያናቱ በነበሩባቸው ከተሞች ስም ነው።
ሐ. የኤፌሶን መልእክት በትንሹ እስያ ለነበሩት አብያተ ክርስቲያኑ ሁሉ የተዘጋጀ ይመስላል። በኤፌሶን 1፡1 ላይ «ኤፌሶን» ተብሎ የተጠቀሰው ቃል በብዙ ጥንታዊ መዛግብት ውስጥ አይገኝም።
መ. አብዛኞቹ የጳውሎስ መልእክቶችና ምናልባትም ሌሎችም መልእክቶች ጸሐፊው እየተናገረ ሌላ ሰው የጻፋቸው ናቸው። በመሆኑም ጳውሎስ የሮሜን መልእክት በሚጽፍበት ጊዜ ጠርጢዮስ በጸሐፊነት እንዳገለገለው (ሮሜ 16፡22) እና ጴጥሮስም 1ኛ ጴጥሮስን በሚጽፍበት ጊዜ ሲላስ እንደጻፈለት እንመለከታለን (1ኛ ጴጥ. 5፡12)።
ሠ. የጳውሎስ መልእክቶች በሁለት ዐበይት ክፍሎች ተከፍለው የሚዘጋጁ ይመስላል። የመጀመሪያው ክፍል፥ ጳውሎስ ቁልፍ የወንጌል እውነቶችን የሚያብራራበት «ነገረ መለኮታዊ» ገለጻ ነው። አንዳንድ መልእክቶች (ቆላስይስ) በክርስቶስ ማንነት ላይ ሲያተኩሩ፥ ሌሎች (ሮሜ፥ ገላትያ) በድነት (በደኅንነት) መንገድ ላይ ያተኩራሉ። ሁለተኛው ክፍል፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ እርሱን በሚያስከብር መልኩ እንዴት ሊመላለሱ እንደሚገባቸው የሚያሳይ «ሥነ ምግባራዊ» መልእክት ነው። ጳውሎስ እውነቱን ማወቁ ብቻ በቂ እንዳልሆነና እውነተኛ የእግዚአብሔር ተከታዮች እውነቱን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው አመልክቷል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እውነቱን አምኖ ስለ ክርስቶስ መዘመር ክርስቶስን በሚያስከብር መንገድ ከመኖር ይልቅ ቀላል የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) ክርስቶስን በሚያስከብርና በእርሱ ላይ ያለህ እምነት እውነተኛ መሆኑን በሚያሳይ መልኩ ለመኖር እየጣርህ መሆንህን የሚያሳዩ ምሳሌዎች ስጥ።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)
Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት