የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሮሜ 1 አንብብ። የሮሜ መልእክት ጸሐፊ ነኝ የሚለው ማን ነው? ስለ ራሱ የሰጣቸው ሦስት ገለጻዎች ምንድን ናቸው? እነዚህ ገለጻዎች ስለ ጳውሎለ ምን ያስተምሩናል? ለ) ሮሜን ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብና ስለ ጸሐፊው፥ መልእክቱ ስለተጻፈላቸው ሰዎች፥ መልእክቱ ስለተጻፈበት ዘመን፥ ወዘተ… የሚገልጹትን እውነቶች ጠቅለል አድርህ ጻፍ። ሐ) እግዚአብሔር ሕይወትህን ለመለወጥ የተጠቀመባቸውን የሮሜ መልእክት እውነቶች ዘርዝር።
ቀደም ብለን እንደተመለከትነው፥ የጥንት ዘመን ደብዳቤዎች ብዙውን ጊዜ የሚጀምሩት በጸሐፊው ስም ነበር። ስለሆነም፥ ይህ ደብዳቤ የሚጀምረው ጸሐፊው ጳውሎስ መሆኑን ለሮሜ ቤተ ክርስቲያን በመግለጽ ነው። ጳውሎስ ራሱን በሦስት መንገዶች ገልጾአል።
- የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ፡- በግሪኩ ቋንቋ «ባሪያ» የሚለውን ቃል ለመግለጽ ሀ) እስከ ሞት ድረስ የጌታው ንብረት የሆነ ባሪያ፥ ወይም፥ ለ) ከፍቅር የተነሣ ጌታውን በማገልገል ሊቀጥል የመረጠን ባሪያ ሊያመለክት ይችላል። የሮም ዜጎች ነፃ በመሆናቸው ይኮሩ ነበር። በጳውሎስ ዘመን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በባርነት ይኖሩ የነበረ ሲሆን፥ አብዛኞቹ የሌላ ሰው ንብረት መሆንን ይጠሉ ነበር። ጳውሎስ ሮማዊ ዜግነት ያለው ነፃ ሰው መሆኑን ቢያውቅም፥ ራሱን እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ አድርጎ ይመለከት ነበር። ጳውሎስ የክርስቶስ ንብረት የሆነው በፍጥረት መብት ብቻ ሳይሆን በክርስቶስ ደም የተገዛ በመሆኑ ጭምር ነው (1ኛ ቆሮ. 6፡20)። ይህ እውነት ጳውሎስን በጣም ስላስደነቀው ለኩሩ ሮማውያን ባሪያን የመጀመሪያ መግለጫው አድርጎ አቅርቧል። ጳውሎስ ክርስቶስን ለመከተል ስለመረጠ ሕይወቱ በሙሉ ለክርስቶስ ፈቃድ ተገዝቷል። ጌታውን በታዛዥነት መከተሉ በድንጋይ እንዲወገር፥ የመርከብ መሰበር አደጋ እንዲደርሰበት፥ እንዲሰደድ፥ እንዲገረፍና እንዲታሰር አድርጎታል። ነገር ግን ይህ የሚያሳስበው ጉዳይ አልነበረም። ምክንያቱም ጳውሎስ ክርስቶስ የሕይወቱ ጌታ ከሆነ፥ እግዚአብሔር በሕይወቱ ላይ የፈለገውን ጉዳይ የመፈጸምና ወደፈለገው ስፍራ የመላክ መብት እንደነበረው ተረድቶ ነበር። ለጳ ውሎስ ዋናው ጉዳይ የራሱን መብትና ነጻነት ማስጠበቅ ሳይሆን ከጌታው ጋር መልካም ግንኙነት ማድረግ ነበር።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለሌላ ሰው ባሪያ የመሆንን አሳብ የምንቃወመው ለምንድን ነው? ለ) እንደ ጳውሎስ የክርስቶስ ባሪያ እንደሆንህ የምታስብ ብትሆን ሕይወትህ እንዴት ይለወጣል? ሐ) ብዙ ክርስቲያኖች የክርስቶስ ባሪያ ነን ብለው የሚያስቡ ይመስልሃል? መልስህን አብራራ።
- ሐዋርያ፡- ከሞላ ጎደል በሁሉም መልእክቶቹ ውስጥ፥ ጳውሎስ ሐዋርያነቱን ይገልጻል። ይህም ስለ ሐዋርያነቱ መግለጹ ለእርሱ በጣም አስፈላጊ እንደነበረ ያሳያል። ሐዋርያው «ክርስቶስ እርሱን እንዲወክል የላከው ሰው» የሚል ፍች አለው። በአዲስ ኪዳን ሁለት የሐዋርያነት ደረጃዎች ነበሩ። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ በተለየ ሁኔታ የመረጣቸውና ለሦስት ዓመታት የተከተሉት 12ቱ ሐዋርያት ነበሩ። እነዚህ ሐዋርያት ወንጌሉን ወደ ዓለም የመውሰድ ብቻ ሳይሆን፥ የቤተ ክርስቲያን ቃል እቀባይ የመሆንና የቀድሞዪቱን ቤተ ክርስቲያን እምነቶች የመወሰን ሥልጣን ነበራቸው። ሁለተኛ፥ ሌሎችም ሐዋርያት ተብለው የተጠሩ ነበሩ (ሮሜ 16፡7 አንብብ)። እነዚህን ሰዎች ለሐዋርያነት ያበቋቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ እምብዛም የተገለጸ ነገር አናገኝም። አንዳንድ ምሁራን እነዚህ ሰዎች ቀደም ሲል ወንጌል ባልተሰበከባቸው አካባቢዎች አብያተ ክርስቲያናትን የተከሉ ናቸው ይላሉ።
እንግዲህ፥ ጳውሎስ የትኛው ዓይነት ሐዋርያ ነበር? ጳውሎስ ክርስቶስ መርጦ ከላካቸው 12 ሐዋርያት ጋር ራሱን እኩል አድርጎ እንደተመለከተ ግልጽ ነው። 12ቱ ሐዋርያት በቀዳሚነት ለአይሁድ አብያተ ክርስቲያናት ሲላኩ፥ ጳውሎስ ክርስቶስ በደማስቆ መንገድ ላይ ተገልጦ የአሕዛብ ሐዋርያ አድርጎ እንደ ሾመው ያምን ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ የጻፈው በዚህ ልዩ የሐዋርያነት ሥልጣን ነው። የጥንቱ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር ይህን ሥልጣን እንደሰጠው እንድትገነዘብና መልእክቶቹን ከክርስቶስ እንደመጡ ያህል በጥንቃቄ እንዲቀበሉ አሳስቧቸዋል። ከሮሜ መልእክት በስተጀርባ ጳውሎስ፥ አሕዛብ የወንጌሉን እውነት እንዲረዱ በእግዚአብሔር ፊት ኃላፊነት እንዳለበት ተሰምቶት ያገለግል ነበር።
ዛሬ የ12ቱን ሐዋርያትና የጳውሎስን ያህል ሐዋርያዊ ሥልጣን እንዳላቸው የሚናገሩ ሰዎች አሉ። ነገር ግን ይህ ለ12ቱና ለጳውሎስ የተሰጠው ሥልጣን ለሌሎች ሊተላለፍ እንደሚችል የሚያመለክት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃ የለም። ካቶሊኮች ከሚያምኑት በተቃራኒ፥ የጴጥሮስ ሥልጣን (ማቴ. 16፡7-19) ወደ ሌላ የቤተ ክርስቲያን መሪ እንደሚተላለፍ የሚያመለክት እሳብ የለም። በቀድሞዪቱ ቤተ ክርስቲያን ጽሑፎች ውስጥ ለሐዋርያነትና ለሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በተሰጡት ሥልጣናት መካከል ግልጽ ልዩነት ተደርጓል። ዛሬ ሐዋርያት አሉ ቢባል፥ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን እንዲመሠርቱ ያነሣሣቸውን ሁለተኛ ዓይነት ሐዋርያት መሆን አለባቸው።
- ለእግዚአብሔር ወንጌል ተለየ፡- የሮሜ መልእክት በወንጌሉ ላይ ያተኩራል። ጳውሎስ እግዚአብሔር የክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ ዓላማ እንደመረጠው ለሮሜ ሰዎች አብራርቷል። ምንም እንኳ ሁላችንም ስለ ክርስቶስ እንድንመሰክር የታዘዝን ቢሆንም፥ ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያንና በዓለም ከነበሩት ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር እርሱን እንደመረጠው ተረድቶ ነበር። እግዚአብሔር ጳውሎስን የመረጠው ለአንድ ዓላማ ማለትም ወንጌሉን ለአሕዛብ እንዲሰብክ ነበር። ጳውሎስ ሐዋርያ ሆኖ ለጠፉት ወንጌልን መስበኩ ሥራ ብቻ ሳይሆን ግዴታም እንደሆነ ተረድቶ ነበር። እግዚአብሔር ከሌሎች ክርስቲያኖች ሁሉ ለይቶ በመምረጥ ይህንን ሥራ ሰጥቶታል። እግዚአብሔር ጳውሎስ ይህንን ተግባር እንዲያከናውን ኃላፊነት የሰጠው ሲሆን፥ አንድ ቀን ምን ያህል ሥራውን በብቃት እንደተወጣ ፍርዱን ይሰጠዋል፡፡
እግዚአብሔር አንድን መሪ በወንጌላዊነት፥ በሰባኪነት ወይም በአስተማሪነት አገልግሎት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጠቀም ከተፈለገ፥ ግለሰቡ እግዚአብሔር ለተወሰነ አገልግሎት እንደጠራው መረዳት አለበት። በሕዝብ መመረጡ ወይም በደመወዝ መቀጠሩ ብቻ በቂ አይደለም። ነገር ግን በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ ካሉት ሰዎች ሁሉ መካከል እግዚአብሔር እንደመረጣቸውና ልዩ አገልግሎት እንደሰጣቸው መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ከዚያም እግዚአብሔር አገልግሎቱን ስላካሄዱበት ሁኔታ በኃላፊነት ይጠይቃቸዋል።
የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ወንጌላውያን፥ መጋቢያንና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በእግዚአብሔር ለመጠራታቸው እርግጠኞች ከሆኑ አገልግሎታቸው እንዴት የሚለወጥ ይመስልሃል? ለ) አብዛኞቹ መሪዎች የሚያገለግሉት እግዚአብሔር ጠርቶኛል በሚል እምነት ነው ወይስ አይደለም? መልስህን አብራራ። ሐ) ቤተ ክርስቲያን ሥራ የሚፈልጉትን ሳይሆን እግዚአብሔር ጠርቶኛል ብለው የሚያስቡትን አገልጋዮች ስለመምረጧ አስፈላጊነት ምን አሳብ ትሰጣለህ?
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር እያንዳንዱን አማኝ ለዓላማ እንደጠራው ያስተምራል። ነጋዴ፥ የቤት እመቤት፥ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ ቢሆን፥ እያንዳንዱን ሰው መርጦ ባለበት ስፍራ ላይ የሚያስቀምጣቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ ግለሰቡን ከዚያ ስፍራ ላይ ያስቀመጠው የራሱ ምርጫ ወይም መንግሥት ሳይሆን እግዚአብሔር በመሆኑ፥ ሁለት እውነቶችን ልናስታውስ ይገባል። በመጀመሪያ፥ በሥራችን የምንችለውን ሁሉ ማከናወን አለብን ምክንያቱም የምንሠራው ለራሳችን፥ ለመንግሥት ወይም ለሌላ ሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር ነው። ሁለተኛ፥ በዚያ የተቀመጥነው መንፈሳዊ ብርሃንን ለማብራት ነው። አንድ ቀን ክርስቶስ የጠራንን ዓላማ ስለመፈጸም አለመፈጸማችን በፊቱ ቆመን ምላሽ እንሰጣለን። ሥራችንን ያከናወንበት ሁኔታ ይመዘናል። ፈሪሃ እግዚአብሔር በሌለው ዓለም ውስጥ እንደ ክርስቲያኖች በብርሃን የተመላለስንበትም ሁኔታ ይመዘናል (1ኛ ቆሮ. 3፡11-15)።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሙሉ ጊዜያቸውን በአገልግሎት ላይ የሚያውሉና ዓለማዊ ሥራ ላይ የተሰማሩ ክርስቲያኖች ሁሉ እግዚአብሔር በተለየ መንገድ እንደጠራቸውና እነዚህን ኃላፊነቶች እንደሰጣቸው ቢያምኑ፥ ለሥራና ለአገልግሎት ያለን አመለካከት እንዴት የሚለወጥ ይመስልሃል? ለ) በአሁኑ ሰዓት የት እንደምትሠራና ለቤተ ክርስቲያንም የምትሰጠውን አገልግሎት ገምግም። የምትሠራውና የምታገለግለው እግዚአብሔር ጠርቶኛል በሚል እምነት ነው? አሁን በክርስቶስ ፊት ለመመዘን ብትቆም፥ የትኛው ክፍል የሚያስደስተው ይመስልሃል? የትኛውስ ያሳዝነዋል? ሐ) እግዚአብሔር የተጠራህለትን ልዩ ዓላማ እንዲገልጽልህ በጸሎት ጠይቀው። ሥራውን ለክብሩ የምታከናውንበትን ኃይል እንዲሰጥህ ጠይቀው።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)
Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት