ሃይማኖተኛ የሆኑ አይሁዶችም ኃጢአተኞች ናቸው (ሮሜ 2፡1-3፡8)

የውይይት ጥያቄ፡- ሮሜ 2፡1-3፡8 አንብብ። አይሁዶች (እና የትኛውም ሃይማኖተኛ ጥሩ ሰው) በቅዱስ አምላክ ፊት ኃጢአተኞች መሆናቸውን በራስህ ቃል በአጭሩ አስረዳ።

አይሁዶችና ሌሎች ጥሩ ሃይማኖተኛ ሰዎች ስለ አሕዛብ ኃጢአተኝነት በሚያነቡበት ጊዜ ኩራት ሳይሰማቸው አይቀርም። ጥቂት ሰዎች፥ «እኛ እንደ እነርሱ ክፉዎች አይደለንም። የእግዚአብሔርን ሕግጋት እናከብራለን። የወሲብ ኃጢአት አንፈጽምም። ማንንም አልገደልንም። ጣዖታትን እናመልክም። ስለዚህ እግዚአብሔር ሊቀበልን ይገባል» ብለው ያስቡ ነበር። በቀጣዩ ክፍል ጳውሎስ የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን በመጠበቃቸው የሚኩራሩትን ሃይማኖተኛ አይሁዶች ያናግራል።

ሀ. እግዚአብሔር ያለአድልዎና በእውነት የሚፈርድ ስለሆነ የሃይማኖት ሰዎች ከኩራት እንዲጠበቁ ጳውሎስ ያስጠነቅቃል (ሮሜ 2፡1-16)። የሃይማኖት ሰዎች ከክፉ ጣዖት አምላኪ አሕዛብ የሚሻሉ ሊመስል ይችላል። ጳውሎስ ግን የሃይማኖት ሰዎች እንኳ ኃጢአተኞች በመሆናቸው ለእግዚአብሔር ፍርድ እንደተጋለጡ በመግለጽ ያስጠነቅቃል። የሃይማኖት ሰዎች አምላክ እንደሌላቸው አሕዛብ ግልጽ ኃጢአት ላይፈጽሙ ቢችሉም፥ በልባቸው ተመሳሳይ ኃጢአት ይሠራሉ። ጳውሎስ የእግዚአብሔር ፍርድ በሦስት መርሆዎች ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ያስረዳል።

በመጀመሪያ፥ የእግዚአብሔር ፍርድ በእውነት ላይ የተመሠረተ ነው። እርሱ በሰው ሕይወት ውስጥ የሚፈጸመውን ነገር በትክክል ያውቃል (ሮሜ 2፡1-4)፡፡ የሃይማኖት ሰዎች ጥሩ ሰዎች መስለው ሰዎችን ሊያሞኙ ሲሞክሩም እንኳን፥ እግዚአብሔር የልባቸውን ኃጢአተኝነት ያውቃል። የሃይማኖት ሰዎች በግልጽ ኃጢአት ላይሠሩ፥ ጣዖት ላያመልኩ፥ ላይገድሉ፥ ወሲባዊ እርኩሰት ላይፈጽሙ ቢችሉም፥ ትዕቢትና የኃጢአት አሳብ ይኖርባቸዋል። ስለሆነም፥ ከእግዚአብሔር የቅድስና መመዘኛ አንጻር ሲታይ በተቀደሰው አምላክ ፊት ኃጢአተኞች ናቸው።

እግዚአብሔር በፍጥነት አልፈረደባቸውም ማለት ስለ ስውር ኃጢአታቸው ግድ የለውም ማለት አይደለም። ነገር ግን እግዚአብሔር በፍጥነት የማይፈርደው በደግነቱ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ ጊዜ ለመስጠት እንደሆነ ያመለክታል።

ሁለተኛ፥ የእግዚአብሔር ፍርድ በአድልዎ ላይ ያልተመሠረተ ነው (ሮሜ 2፡5-16)። ጳውሎስ የእግዚአብሔር ፍርድ በክፉ ተግባራቸው ላይ የተመሠረተ መሆኑን ተናግሯል። አይሁዶች የእግዚአብሔር የብሉይ ኪዳን ቤተሰብ አካል በመሆናቸው እግዚአብሔር ለእነርሱ የተለየ የፍርድ መመዘኛ እንዲጠቀም አያደርገውም። አይሁድም ቢሆኑ አሕዛብ እግዚአብሔር በእያንዳንዱ ሰው ላይ ፍርድን የሚሰጠው አድልዎ በሌለበት ሁኔታ በሥራቸው ላይ ተመሥርቶ ነው።

ጳውሎስ በዚህ ክፍል ሊያስተላልፍ የሚፈልገውን መልእክት መረዳቱ ጠቃሚ ነው። ከአዲስ ኪዳን ገለጻ ለመረዳት እንደሚቻለው፥ ሁሉም ሰው ኃጢአተኛ ስለሆነ ማንም ራሱን ሊያድን የሚችል የለም። ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን። ስለሆነም፥ ሁሉም መዳንን ያገኝ ዘንድ የእግዚአብሔር ጸጋ ያስፈልገዋል (ኤፌ. 2፡8-9)። በሌላ በኩል፥ ተግባራችን መዳን አለመዳናችንን ያሳያል። ድነትን (ደኅንነትን) አግኝተን አዲስ ፍጥረት ከሆንን (2ኛ ቆሮ. 5፡17)፥ ልባችንና ተግባራችን ይለወጣል።

በሮሜ 2፡12-16፥ ጳውሎስ አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ የእግዚአብሔርን ሕግ ሊታዘዙና በራሳቸው ጽድቅ ሊድኑ እንደሚችሉ እያስተማረ አይደለም። ጳውሎስ ወረድ ብሎ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት የሚመሩ አይሁዶች ኃጢአተኞች መሆናቸውን መግለጹ ይህንን አሳብ እንድንረዳ ያደርጋል። ጳውሎስ ሁለት ዓይነት የእግዚአብሔር ሕግጋት እንዳሉ አመልክቷል። እነዚህም ለአይሁዶች የተሰጠው የተጻፈ ሕግና በሰዎች ሁሉ ሕሊናና ልብ ውስጥ የተቀመጠው ያልተጻፈ ሕግ ናቸው። እግዚአብሔር የብሉይ ኪዳን ሕግጋት ባላቸው አይሁዶች ላይ የሚፈርደው እነዚያን የተጻፉ ሕግጋት በጠበቁበት ሁኔታ ላይ በመመሥረት ነው። ከሕሊና በስተቀር የተጻፈ ሕግ በሌላቸው አሕዛብ ላይ የሚፈርደው ግን በልባቸው ውስጥ የተጻፈውን ሕግ በጠበቁበት ሁኔታ ላይ በመመሥረት ነው። እግዚአብሔር አሕዛብ ሰምተው ለማያውቋቸው የተጻፉ ሕግጋት ተጠያቂ አያደርጋቸውም።

ነገር ግን አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ የተጻፉ ወይም ያልተጻፉ ሕግጋትን ሙሉ ለሙሉ ጠብቀው ከፍርድ ሊያመልጡ ይችላሉ? ጳውሎስ ወደ በኋላ እንደገለጸው፥ አሕዛብም ሆኑ አይሁድ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ሙሉ ለሙሉ ሊጠብቁ አይችሉም። ስለሆነም፥ ሰዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ስለሆኑ፥ ለመዳን ሌላ መፍትሔ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

ሦስተኛ፥ ጳውሎስ በኋላ እንዳመለከተው፥ እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያድነው ከክርስቶስ ጋር ባላቸው ግንኙነት ላይ በመመሥረት ነው (ሮሜ 3፡21-30)፡፡

ለ. አይሁዳዊ መሆን በእግዚአብሔር ዘንድ የተቀባይነትን ዋስትና አያስገኝም (ሮሜ 2፡17–3፡8)። ለብዙ ዓመታት ጳውሎስ ሃይማኖተኛ አይሁዳዊና ኵሩ ፈሪሳዊ ነበር። አይሁዶች የሚያስቡበትን መንገድ ያውቅ ነበር። 1) የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ በመሆናቸው፥ 2) የእግዚአብሔር የተጻፈ ቃል ያላቸውና 3) የተገረዙ በመሆናቸው ይኩራሩ ነበር። ይህ ኩራት ብዙውን ጊዜ አይሁዶች ኃጢአተኝነታቸውን እንዳያዩ ስላደረጋቸው፥ ወደ መንፈሳዊ ኩራትና በራስ ወደ መርካት መርቷቸዋል። ጳውሎስ የአይሁዶችን ኃጢአተኝነት ለማሳየት ሲል አይሁዶች በሚማረኩባቸው ሁለት ነገሮች ላይ ያተኩራል።

  1. የተጻፈ ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ቃል ማግኘት፡ ጳውሎስ ዋናው የእግዚአብሔርን ቃል መቀበል ሳይሆን ቃሉን መታዘዝ እንደሆነ ለአይሁዶች አስገንዝቧቸዋል። አይሁዶች የእግዚአብሔር ቃል ስላለን «ለዓይነ ሥውራን፥ በጨለማ ላሉት፥ ለሞኞችና፥ ሕፃን ለሆኑት» አሕዛብ «መሪዎች ነን» በሚል ተመክተው ይሆናል። ነገር ግን ሕይወታቸውን በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ከተጻፈው ጋር ሲያነጻጽሩት፥ የልባቸውን ክፋት ሊመለከቱ ይችሉ ነበር። አሥርቱ ትእዛዛት አይሁዶች እንዳይሰርቁና እንዳያመነዝሩ ያዛሉ። ነገር ግን አይሁዶች ከሌሎች ሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት (በተለይም በንግድ) ብዙውን ጊዜ ከማጭበርበርና ዝሙትን ከመፈጸም ወደኋላ አይሉም ነበር። አምልኮተ ጣዖትን እየተቃወሙ ቢሰብኩም፥ ዕድሉ በሚገጥማቸው ጊዜ ገንዘብ ከቤተ መቅደስ ወስደው ለራሳቸው ይጠቀማሉ። ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ቃል ቢኖራቸውም፥ አይሁዶች እግዚአብሔርን አያስከብሩም ነበር። በዚህ አኗኗራቸውም ዘላለማዊ ቃል ያልነበራቸው አሕዛብ በአምላካቸው ላይ እንዲሳለቁ አድርገዋል።

የውይይት ጥያቄ፡– የዘላለም ቃል አለን ብለን እየተመካን በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተጻፈውን እውነት ባለመታዘዝ የክርስቶስን ስም የምናሰድብባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

  1. መገረዝ፡ እግዚአብሔር አብርሃምና ልጆቹ፥ የእርሱ ሕዝብ እንደሆኑና ከእርሱ ጋር ልዩ ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውን ለማሳየት ውጫዊ ምልክት የሆነውን የግርዛትን ሥርዓት ሰጥቷቸዋል። አይሁዶች አንድ ሰው ሥጋዊ ግርዛትን እስከፈጸመ ድረስ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሚሆን ያምኑ ነበር። ዋናው የልብ ዝንባሌ እንደሆነና አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት በእምነትና በታዛዥነት እንደሚረጋገጥ ዘንግተው ነበር። ይህ ውስጣዊ ግርዛት ነው። አንድ አሕዛብ በሥጋ ባይገረዝም፥ እንደ አብርሃም በእምነትና በታዛዥነት ከእግዚአብሔር ጋር በመገናኘቱ የልብ ግርዛት ሊሆንለት ይችላል። ለእግዚአብሔር ዋናው ነገር ይሄ ነው እንጂ ውጫዊ የሆነ የሥጋ መገፈፍ አይደለም። እውነተኛ አይሁዳዊነትም የአንድ ነገድ አባልነት ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር በእምነት የመገናኘት ጉዳይ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- በሰው የልብ ሁኔታ ላይ ሳናተኩር በውጫዊ ሥርዓቶች (ለምሳሌ፥ ጥምቀት፥ አለመጠጣት) ላይ ልንመካ የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

ጳውሎስ በኢየሩሳሌም የነበሩት ብዙ አይሁዶች እንዳልተረዱት ሁሉ የሮም አይሁዶችም በተሳሳተ መልኩ እንዳይረዱት ሰግቶ ነበር። ጳውሎስ አይሁዳዊነታቸውን በመቃወም መገረዝና የእግዚአብሔርን ቃል መቀበል ምንም ጥቅም እንደሌለው የሚያስተምር መስሏቸው ነበር። ጳውሎስ ግን ሕግን እየተቃወመ አልነበረም። ፀረ-አይሁዳዊ ሆኖ አይሁዶች ቅርሳቸውን እንዲትዉ እያስተማረ አልነበረም።

ጳውሎስ አይሁዶች ሁለት ነገሮችን እንዲገነዘቡለት ይፈልግ ነበር። እነዚህን አሳቦች ወደ በኋላ በሰፊው ያብራራቸዋል። በመጀመሪያ፥ አንዳንድ አይሁዶች እምነትን አጥተው እግዚአብሔርን ባለመታዘዛቸው እግዚአብሔር ለአይሁዶች የሰጠውን አስደናቂ በረከት ለሌሎች ሊያስተላልፉ አልቻሉም። የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል አሁንም ቢሆን አይሁዶችን ጨምሮ ዓለምን ሁሉ የሚፈርድበት ፍጹማዊ መመዘኛው ነበር። ሁለተኛ፥ አይሁዶች እንደ አሕዛብ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ሙሉ በሙሉ ለመታዘዝ አለመቻላቸው ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል ወዳዘጋጀው የጽድቅ መስመር ሊመለሱ እንደሚገባ ያሳያል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “ሃይማኖተኛ የሆኑ አይሁዶችም ኃጢአተኞች ናቸው (ሮሜ 2፡1-3፡8)”

  1. Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

%d bloggers like this: