ሁሉም ሰው ኃጢአተኛ ስለሆነ ደኅንነትን ማግኘት ይኖርበታል (ሮሜ 3፡9-20)

የውይይት ጥያቄ፡– ሮሜ 3፡9-20 አንብብ። ሀ) ጳውሎስ ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኞች ስለመሆናቸው የሚሰጠው መደምደሚያ ምንድን ነው? ለ) ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ከማመናቸው በፊት ይህን እውነት ማወቅ ያለባቸው ለምን ይመስልሃል?

ጳውሎስ ስለ ሰዎች ኃጢአተኝነት ያቀረበውን የመጀመሪያውን ክፍል ትምህርት በግልጽ አሳብ አጠቃሎታል። ይህም ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኞች ናቸው የሚል ነው። የተጻፈ የእግዚአብሔር ሕግ ባይኖራቸውም እንኳን፥ አሕዛብ ሁሉ ኃጢአተኞች ናቸው። አይሁድም ኃጢአተኛች ናቸው። በምድር ላይ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በሰው ሕሊና ውስጥ የተጻፈውን የእግዚአብሔርን ሕግ ሙሉ በሙሉ የጠበቀ ሰው ስለሌለ፥ በእግዚአብሔር ፊት በጥረቱ ጻድቅ ተብሎ ሊጠራ የሚችል ሰው የለም። የእግዚአብሔር ሕግ አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ ኃጢአተኞች መሆናቸውን ለማስገንዘብ ይረዳል። (ጳውሎስ ሕጉ የተሰጠው ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ የሚሆኑበትን መንገድ ለማስገኘት ሳይሆን፥ ሰዎች የእግዚአብሔርን ጸጋና ምሕረት ይቀበሉ ዘንድ ኃጢአተኝነታቸውን ለማሳየት መሆኑን አመልክቷል) መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎችም ከኃጢአት የጸዱ አይደሉም። ስለሆነም፥ ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት «ኃጢአተኛ» የሚል የፍርድ ውሳኔ ይሰጣቸዋል።

ዛሬ ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ዘላለማዊ ፍርድ ሊቀበሉ የሚገባቸው ኃጢአተኞች የመሆናቸውን እውነት እየዘነጋን በመልካምነታቸው ላይ እናተኩራለን። ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ሲመጡና ስለ ክርስቶስ ስንመሰክርላቸው፥ ክርስቶስ በሚሰጣቸው በረከት ላይ አጽንኦት እናደርጋለን። «በክርስቶስ ስታምን የዘላለምን ሕይወት ታገኛለህ፥ ትፈወሳለህ፥ ትባረካለህ» እንላለን። ይህም ሰዎች ከእግዚአብሔር አንድ ነገር ለማግኘት ብለው የሚከተሉትን የራስወዳድነት ክርስትና ያበረታታል። እንዲህ ዓይነት ክርስቲያኖች ለኃጢአታቸው ካለማፈራቸውም በላይ፥ ክርስቶስ እነርሱን ከዘላለማዊ ሞት ለመታደግ በመስቀል ላይ ስለመሞቱ አክብሮት የላቸውም።

ጳውሎስ በእግዚአብሔር ፊት ምን ያህል ኃጢአተኞች እንደሆንን በመግለጽ ወንጌሉን ያብራራል፡፡ የእግዚአብሔርን ምሕረትና ጸጋ ልንፈልግ የምንችለው በጻድቅ አምላክ ፊት ዘላለማዊ ፍርድ ሊቀበሉ የሚገባቸው ኃጢአተኞች መሆናችንን ስንገነዘብ ብቻ ነው። እግዚአብሔር ከኃጢአተኝነታችን እንዳዳነንና ልጆቹ እንዳደረገን በመገንዘብ ለዘላለም ልናመሰግን የምንችለው በዚህ ጊዜ ብቻ ነው። ከዚህ በኋላ በራሳችን ብቃት ላይ የነበረን ሰብአዊ ኩራት ስፍራውን ይለቅቃል። በምትኩም ልጁን ስለሰጠን እግዚአብሔርን እያመሰገንን እርሱን የሚያስከብርና ምስጋናችንን የሚገልጽ ሕይወት ለመኖር ከልባችን እንነሣሣለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ጳውሎስ በሮሜ ያደረገውን ምሳሌነት በመከተል ወንጌሉን ብንሰብክ፥ የእሑድ ቀን የነፍሳት ጥሪያችን እንዴት ይለወጥ ይሆን? ለ) በሰዎች ጥሩነት ወይም ክርስቲያን በመሆን በሚያገኙት ነገር ላይ ሳይሆን በክፋታቸው ላይ ብናተኩር፥ ሰዎች በክርስቶስና በእግዚአብሔር ላይ ያላቸው አመለካከት እንዴት የሚለወጥ ይመስልሃል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “ሁሉም ሰው ኃጢአተኛ ስለሆነ ደኅንነትን ማግኘት ይኖርበታል (ሮሜ 3፡9-20)”

  1. Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading