የድነት (ደኅንነት) መሠረቱ የክርስቶስ ስለ ኃጢአተኞች መሞት ነው (ሮሜ 3፡21-31)

ጳውሎስ የወንጌል ገለጻውን ከክርስቶስ ሳይሆን ከሰዎች ኃጢአተኝነት እንደሚጀምር ከዚህ በፊት በነበረው ትምሕርታችን ተመልክተናል። ጳውሎስ መንፈሳዊና መልካም ሥነ ምግባራዊ ሕይወት ያላቸው የሚመስሉትን ጨምሮ ሰዎች ሁሉ ምን ያህል ልባቸው በክፋት እንደተሞላ እንዲያውቁ ይፈልጋል። ይህንንም ያደረገው ተስፋ እንዲቆርጡ ለማድረግ ሳይሆን፥ «እድን ዘንድ ምን ላድርግ?» የሚል ጥያቄ እንዲያነሡና ለድነት (ለደኅንነት) ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ነው።

ጳውሎስ ስለ ድነት (ደኅንነት) ባቀረበው ትምህርት ሁለተኛው ዐቢይ ደረጃ ቅዱሱ አምላክ ኃጢአተኛ ሰዎችን እንዴት «ጻድቅ ነህ» ብሎ እንደሚያውጅላቸው የሚያሳይ ነው።

የእግዚአብሔር ቃል የሌላቸው አሕዛብ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ከሆኑና የእግዚአብሔርን ሕግ ለመፈጸም የሚጥሩ አይሁዶች በአግባቡ ለመፈጸም ስለተሳናቸው ኃጢአተኞች ከሆኑ፥ የሰው ዘር ምን ተስፋ አለው? ሰው ሊድን የሚችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ ወንጌሉንና ሰው ሁሉ የሚድንበትን መንገድ ጠቅለል አድርጎ አቅርቧል።

ሀ. «ከእግዚአብሔር የሆነ ጽድቅ» ተብሎ የተጠራው ድነት (ደኅንነት) የሚመነጨው ሰዎች ለእግዚአብሔር ከሚያከናውኑት ተግባር ሳይሆን እግዚአብሔር ለሰዎች ከሚሠራው ሥራ ነው። መሠረታዊ የጽድቅ ግንዛቤ እግዚአብሔር ከመሠረተው መመዘኛ ጋር መስማማቱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን፥ እግዚአብሔር ሁልጊዜም ትክክለኛውን ተግባር የሚያከናውን ጻድቅ ሲሆን፥ የሰጠውን የተስፋ ቃል በሙሉ የሚፈጽምና የመሠረተውን ሥነ ምግባራዊ መመዘኛ የሚያሟላ ፍትሐዊ አምላክ ነው። የጻድቅነትን መመዘኛ የመሠረተው እግዚአብሔር ነው። ጻድቅ ፈራጅ እንደመሆኑ መጠን፥ ሰዎች እርሱ ከሰጣቸው ሕግጋትና መመዘኛዎች ጋር ተስማምተው ለመኖራቸው ወይም ላለመኖራቸው በኃላፊነት ይጠይቃቸዋል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ «ጻድቅ» የሚለው ቃል አያሌ የተለያዩ ትርጉሞችን ይሰጣል። ጻድቅ የሚለው ቃል ሰዎችን በሚያመለክትበት ጊዜ የሚከተሉትን አሳቦች ያሳያል።

  1. ከእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዛት ጋር የሚስማማ ሕይወት የሚመራ ሰው።
  2. በማኅበረሰቡ መካከል ሰዎች እርስ በርሳቸው ሰላማዊና ትክክለኛ ግንኙነት እንዲኖራቸው የሚያግዝ ሕይወት የሚኖር ሰው።
  3. ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት እንደሌለው የታወጀለት ሰው። ይህ ጽድቅ የእግዚአብሔር ስጦታ ሲሆን፥ እግዚአብሔር ስጦታውን በእምነት ወደ እርሱ ለሚመለሰው ይሰጠዋል። ጳውሎስ ከሮሜ 3፡21-26 ውስጥ የጠቀሰው የዚህን ጽድቅ ትርጉም ነው።

ጳውሎስ «የእግዚአብሔር ጻድቅ» የሚለው ግለሰቡ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት እንዳለው የሚያመለክተውን ሕጋዊ አዋጅ ነው። በሌላ አነጋገር ሰውዬው ድኖአል። ነገሩ ገንዘብ ሰርቆ በፖሊስ እንደመያዝ ዓይነት ነው። ፖሊሱ ሌባውን ወደ ዳኛው ያቀርበዋል። ዳኛው መረጃውን ተመልክቶ የጥፋተኝነት ውሳኔ በማስተላለፍ ብዙ ገንዘብ ይበይናል። ከዚያም ዳኛው ከራሱ ኪስ ገንዘቡን አውጥቶ በመክፈል ጥፋተኞች አለመሆናችንን በአደባባይ ለሕዝብ ይገልጻል። ጥፋተኞች አይደሉም ብሎ በመግለጹ ጥፋት እልፈጸማችሁም ማለቱ አይደለም። ነገር ግን የጥፋተኝነቱ ዋጋ እንደተከፈለና ከሕግ የሚፈለግ ቅጣት እንደማይኖር መግለጹ ነው። በመሆኑም፥ ሌባው ስርቆቱን እንዳልፈጸመ ያህል ይስተናገዳል።

ለ. ጥፋተኛ ያለመሆንና ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት የማድረግ ተግባር የሚመጣው «ከሕግ ውጭ» ነው። ይህ ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕግጋት በመጠበቅ ከእርሱ ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ለማድረግ በመሞክር የሚያመጡት አይደለም። ለምን? ምክንያቱም ሕጉን ያፈረስን ኃጢአተኞች ስለሆንን ነው።

ሐ. ይህ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት የማድረግ እወጃ አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ ሊያገኙ የሚችሉት ነው። የሚፈለገው ነገር ቢኖር የግለሰቡ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነው። እይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ ኃጢአተኞች እንደሆኑ ሁሉ፥ «ጻድቅ» ተብሎ የመጠራቱ የእግዚአብሔር ግሩም ስጦታም ለሰዎች ሁሉ ክፍት ነው። ይህም በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን እንዲያገኙና ከኃጢአት እንዲድኑ ያስችላቸዋል።

መ. የእግዚአብሔር ነፃ ስጦታ ጳውሎስ በምናቡ የፈጠረው ሳይሆን፥ «ሕግና ነቢያት» የተባለውን ብሉይ ኪዳንን ከመገንዘብ የመነጨ ነው።

ጳውሎስ «እምነት» የሚለውን ቃል እንዴት እንደሚጠቀም መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። የሚያድን እምነት ክርስቶስ ስለ እኛ በመስቀል ላይ እንደሞተ ማወቅ ብቻ ሳይሆን፥ ጠቅላላ ሕይወትን በሚለውጠው እውነት ላይ ሙሉ ለሙሉ መደገፍ ነው። በክርስቶስ ማመን ክርስቶስ በመስቀል ላይ ለኃጢአተኞች ሞቷል የሚለውን አእምሯዊ እምነትና አንድን ነገር በማድረግ የእግዚአብሔርን ሞገስ ለማግኘት አለመጣርን ያመለክታል። ሌሎች ሰብአዊ የድነት (ደኅንነት) መንገዶችን ትተን በእግዚአብሔር የድነት (ደኅንነት) መንገድ ላይ እንደገፋለን ማለት ነው።

ሠ. ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ካከናወነው ተግባር የተነሣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ ማግኘት ይቻላል። እግዚአብሔር አብ ክርስቶስን ወደ መስቀሉ ልኮታል። ክርስቶስ የስርየት መሥዋዕት ሆኖ ደሙን በማፍሰሱ እግዚአብሔር ለሰዎች ድነት (ደኅንነት) በር ከፍቷል። (የእግዚአብሔር የይቅርታ መርህ ሁልጊዜም አንዱን ሕይወት ለሌላው መሥዋዕት የማድረግ ነበር። የእንስሳት መሥዋዕት ስለ ሰው ሕይወት ሲባል የእንስሳት መሰጠት ነበር። የክርስቶስ መሥዋዕት ክርስቶስ ሕይወቱን ለሕይወታችን እንደሰጠ በመገንዘብ ላይ የተመሠረተ ነው።) አማኞች አሁን «ቤዛነትን» አግኝተዋል። ይህም ከኃጢአተኛነት በደል ወጥተው እግዚአብሔርን ለማገልገል ነፃ መሆናቸውን የሚያሳይ ሌላው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ነው። ዳኛው የኃጢአት ደመወዝ ሞት እንደሆነ አውጇል። ሁላችንም ኃጢአተኞች ስለሆንን መሞት እንዳለብን ያውጃል፡፡ ከዚያም እግዚአብሔር ፍጹም የሆነውን ልጁን በምትካችን እንዲሞት ይጠይቀዋል። ይህም ሞት ለኃጢአት የመሞትን ሕጋዊ መስፈርት ያሟላል። ይህ ክርስቶስ ስለ እኛ መሞቱን መቀበላችን እግዚአብሔርን ለማገልገል ነፃ ያወጣናል።

(ስርየት የሚለው ቃል «የእግዚአብሔርን የፍርድ ቁጣ የሚመልስ» ማለት ሲሆን። ቤዛነት የሚለው ቃል ደግሞ ጥንት ባሪያዎችን ከመግዛት ተግባር የመጣ ነው። ብዙውን ጊዜ ባሪያ የነበረ ሰው ለሽያጭ ወደ ገበያ ይወሰድ ነበር። ሰዎች ይገዟቸውና እንደባሪያ ይገለገሉባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ግን ከርኅራኄ የተነሣ አንዳንድ ሰዎች ባሪያዎችን ገዝተው ነፃ ያደርጓቸዋል። ከዚያ በኋላ ቀደም ሲል ባሪያዎች የነበሩት ሰዎች ለሌሎች መገዛታቸው ቀርቶ የራሳቸውን ምርጫ የማድረግና በፈለጉት መንገድ የመኖር ነጻነት ይኖራቸዋል። «ተቤዥተዋል» ማለት ነው። በብሉይና አዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ሰዎችን ከባርነት ሕይወታቸው «የሚገዛ» (ከግብጽ፥ ከኃጢአት፥ ከመከራ) እና የተፈጠሩለትን ዓላማ እንዲፈጽሙ የሚያደርግ ቤዛ እንደሆነ ተመልክቷል። የተፈጠሩትም ፈጣሪ አምላካቸውን እንዲያከብሩ ነው።

ረ. እግዚአብሔር አብ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚገኘውን የድነት (ደኅንነት) መንገድ ሲያዘጋጅ ጻድቅና አጽዳቂም ነበር። እንደ ቅዱስ ፈራጅ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ኃጢአተኝነት አሳንሶ ለመለካትና «ይቅር ብያችኋለሁ» ሊል አይችልም ነበር። እግዚአብሔር ቅዱስ ነው ሲባል የኃጢአተኝነት ዓመፅ መቀጣት አለበት ማለት ነው። ከአዳም ዘመን ጀምሮ የእግዚአብሔር ፍርድ «ኃጢአትን የሚሠራ እርሱ ይሙት» የሚል ነበር። በሌላ በኩል፥ እግዚአብሔር አብ አፍቃሪ፥ መሐሪና ቸር አምላክ ነው። ስለሆነም ከእርሱ ጋር ሊዛመዱ የሚፈልጉትን ሰዎች ለማዳን ይፈልጋል። ስለሆነም እግዚአብሔር ራሱ የድነትን (ደኅንነትን) መንገድ አዘጋጅቷል። በቅድስናውና በፍቅሩ፥ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞት የኃጢአታችንን ቅጣት እንዲከፍል አድርጓል። እግዚአብሔር ኃጢአትን በመቅጣቱ ጻድቅ ነበር። ይሁን እንጂ ሰዎችን ጻድቅ የሚያደርገውም እርሱ ራሱ ነበር። የኃጢአታችን ዋጋ ስለተከፈለ እግዚአብሔር «ከበደል ነፃ ናችሁ» ሊለን ይችላል።

ሰ. የእግዚአብሔርን የድነት (ደኅንነት) ስጦታ የምንቀበለው በሥራ ሳይሆን ክርስቶስ ለእኛ በመሞቱ ነው (ሮሜ 3፡27-31)። የእግዚአብሔርን የድነት (ደኅንነት) ስጦታ ለማግኘት በፍጹም መደገፍ ላይ የተመሠረተ እምነት ያስፈልጋል። እንደ ድነት (ደኅንነት) ተስፋችን ሆኖ ኢየሱስ በምትካችን መሞቱን ስናምን «አላጠፋህም» የሚለውን የእግዚአብሔር አዋጅ መቀበል እንችላለን። ይህም ሕግ ላላቸው አይሁዶችም ሆነ ሕግ ለሌላቸው አሕዛብ ሁሉ የሚሠራ ነው። የድነትን (ደኅንነትን) መንገድ ያዘጋጀው እግዚአብሔር በመሆኑ፥ ማንም ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ለመመሥረት ባከናወነው ተግባር በእግዚአብሔር ፊትም ሆነ በሌሎች ዘንድ ሊመካ አይችልም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሮሜ 3፡22-24 በቃልህ አጥና። ለ) ይህን ክፍል በመጠቀም ወንጌሉን በራስህ አገላለጽ ጠቅለል አድርገህ ግለጽ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “የድነት (ደኅንነት) መሠረቱ የክርስቶስ ስለ ኃጢአተኞች መሞት ነው (ሮሜ 3፡21-31)”

  1. Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

%d bloggers like this: