ክፍፍል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ (1ኛ ቆሮ. 1፡10-4፡21)

ጳውሎስ በመልእክቱ ውስጥ ያነሣው የመጀመሪያው ዐቢይ ጉዳይ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለተከሰተው ክፍፍል ነበር (1ኛ ቆሮ. 1-4)። ጳውሎስ ክፍፍል፥ በተለይም የተወሰኑ መሪዎችን በመከተል የሚፈጠር ክፍፍል የዓለምን ጥበብ እንደሚያሳይ፥ የአማኞችን አለመብሰል እንደሚያመለክትና የመሪነትን ጽንሰ አሳብ በተሳሳተ መንገድ መረዳታቸውን እንደሚያስረዳ ገልጾአል።

  1. ጳውሎስ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መከፋፈል መኖሩን ገለጸ (1ኛ ቆሮ. 1፡10-17)። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበው የመጨረሻው የክርስቶስ ጸሎት ስለ አማኞች አንድነት የቀረበ ነው (ዮሐ 17)። ጳውሎስ ጠንካራ እገላለጾችን በመጠቀም የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በሃሳብና በተግባር አንድነት በመመሥረት ይህንኑ ጸሎት እውን እንዲያደርጉ ጠይቋል። ይህ ግን ጳውሎስ ሰዎች ሁሉ በሁሉም ነገር ተመሳሳይ አሳብ እንዲይዙ መፈለጉን አያሳይም። ነገር ግን ጠቃሚ በሆነው ጉዳይ ላይ እንዲያተኩሩ፥ ማለትም አንድነትን ለመፍጠር እንዲቆርጡና አብረው እንዲሠሩ ይፈልጋል።

ክርስቲያኖች በተለያዩ ነገሮች ላይ ይከፋፈላሉ። አንዳንድ ጊዜ በአነስተኛ የአስተምህሮ ጉዳዮች፥ ሌላ ጊዜ ደግሞ በዘርና በጎሳ፥ ወይም አንዱ ቡድን ሌላውን በሆነ መንገድ በመጉዳቱ ምክንያት እንከፋፈላለን። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የተከፋፈሉበት ምክንያት የተለያዩ ታዋቂ መሪዎችን በሞዴልነት ለመከተል በመፈለጋቸው ነበር። (ይህም ሰዎች እንደ ሮናልዶ ዓይነቱን ስፖርተኛ ወይም እንደ ቦንኬ ዓይነቱን ሰባኪ ወይም የፈውስ አገልጋይ በቲፎዞነት ከሚከተሉበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው።) እነዚህ ክርስቲያኖች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታላቁ መሪ ማን እንደሆነና ማንን ለመከተል እንደሚፈልጉ ይከራከሩ ነበር። አንዳንዶች የቤተ ክርስቲያኖቻቸው መሥራችና ታላቅ የአሕዛብ ሐዋርያ የነበረውን ጳውሎስን ተከተሉ። ሌሎች ጳውሎስ በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው መጨረሻ ከቆሮንቶስ ከወጣ በኋላ መጥቶ ሲያገለግል የነበረውንና በአንደበተ ርቱዕነት የሚታወቀውን አጵሎስን ተከተሉት። የአይሁድ ክርስቲያኖች የቤተ ክርስቲያን መሥራችና የአይሁዶች ሐዋርያ የነበረውን ኬፋን (የጴጥሮስ አይሁዳዊ ስም) ተከተሉት። አንዳንድ ምሁራን ይህ ጴጥሮስ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለማገልገል እንደመጣ ያሳያል ይላሉ። በመጨረሻም፥ በጣም መንፈሳውያን ነን የሚሉት ደግሞ የክርስቶስ ተከታዮች መሆናቸውን ገለጹ።

የውይይት ጥያቄ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከከርስቶስ ይልቅ በሰብአዊ መሪ ላይ ሲያተኩሩ የተመለከትከው እንዴት ነው?

ጳውሎስ የትኛውንም ሰብአዊ መሪ መከተሉ ትክክል እንዳልሆነ ገልጾአል። የበለጠ የስብከት ስጦታ አለው የሚባለውን አገልጋይ ለማግኘት ከቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን መዟዟሩ ትክክል አይደለም። ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ የሚያመጣ ይመስል ታላቅ የፈውስ አገልጋይ በሄደበት ሁሉ መዞሩም ተገቢ አይሆንም። ይህንን በምናደርግበት ጊዜ ሰይጣን ዓይኖቻችንን ከክርስቶስ ላይ አንሥተን ኃጢአተኛ፥ ደካማና ፍጹም ባልሆነ የሰው ልጅ ላይ እንድናሳርፍ አድርጓል ማለት ነው። ጳውሎስ አሉታዊ ምላሽ የሚያስገኙ ጥያቄዎችን በማንሣት እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ትክክል አለመሆኑን ያሳያል። ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካልና አንድ ክፍል ነች። የክርስቶስ አካል እንዴት ሊከፋፈል ይችላል? ጳውሎስ ለኃጢአታቸው አልተሰቀለም ነበር። በእርሱ ስምም አልተጠመቁም ነበር (ጳውሎስ ሰዎች በእርሱ ስለመጠመቃቸው በትምክሕት እየተናገሩ ከክርስቶስ ይልቅ እርሱን እንዳይከተሉት በማሰብ ብዙዎችን ከማጥመቅ እንደ ተቆጠበ ገልጾአል። ይህም ዛሬ አንዳንድ ክርስቲያኖች በተሳሳተ መልኩ ከሚያስተምሩት በተቃራኒ ጳውሎስ የውኃ ጥምቀት ለድነት (ደኅንነት) አስፈላጊ ነው ብሎ እንዳላሰበ ያሳያል። እንደዚያ ዓይነት አመለካከት ቢኖረው ኖሮ፥ ወደ ክርስቶስ የመለሳቸውን ሰዎች በሙሉ ራሱ ባጠመቃቸው ነበር።)

መንፈሳዊ ስጦታ ባለው መሪ ላይ ትኩረት በምናደርግበት ጊዜ ሁሉ የሰውን ጥበብ ተከትለናል ማለት ነው። በዓለም የሚታየው ይኸው ነውና። በሰዎች ላይ በምናተኩርበት ጊዜ ደግሞ ከክርስቶስ መስቀል ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ ከመሻት እንታቀባለን።

  1. ስለ ዓለማዊ ጥበብና በክርስቶስ መስቀል በተገለጠው መንፈሳዊ ጥበብ መካከል ያለውን ልዩነት ጥርት አድርጎ አለማወቅ ክፍፍልን ያስከትላል (1ኛ ቆሮ. 1፡18-2፡16)። ስሕተት የሆነው ነገር እንደ አስፈላጊ ነገር አጽንኦት ሲሰጠው ዓለማዊ ጥበብ ይንጸባረቃል።

ሀ. ዓለማዊ ጥበብ በሰው አንደበተ ርቱዕነት ምክንያት፥ በማቅረብ ችሎታውና ሰዎችን የሚያስደስቱ ጥበቦችን በመጠቀም ብቃቱ ላይ ያተኩራል። ጳውሎስ ይህን «የሰው የቃል ጥበብ» ይለዋል (1ኛ ቆሮ. 1፡17)። ይህ ጥበብ በእውነት፥ በሚነገረው መልእክት፥ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በመስማማቱ ወይም እግዚአብሔር የሚፈልገውን በማብራራቱ ላይ እያተኩርም። ይህ ጥበብ የሚያተኩረው በንግግር ችሎታው፥ ሰዎችን ለመሳብና ስሜቶችን ለማነሣሣት በመቻሉ ላይ ነው።

ለ. ዓለማዊ ጥበብ የተማሩ ሰዎች በሚወዷቸው ነገሮች ላይ ያተኩራል፡፡ የተማሩትና የሠለጠኑት ግሪኮች እውቀታቸውን በሚያሳዩበት ጥበብ ላይ አጽንኦት ያደርጉ ነበር። ዛሬ ብዙ ሰዎች፥ «ምን ያህል እንደተማርህ አሳየን፤ አስደናቂ ቃላትን ተጠቀም፣ እንግሊዝኛም እየቀላቀልህ ተናገር፤ አሳቦችን ውስብስብ አድርግ» ሲሉ የዓለማዊ ጥበብን ዝንባሌ ያሳያሉ። ጳውሎስ አብዛኛው የዓለም የፍልስፍና ትምህርት ወንጌሉን እንደሚቃወምና የእግዚአብሔርን ጥበብ እንደማይቀበል አስረድቷል።

ሐ. ዓለማዊ ጥበብ ሰዎችን ለሚያስደንቁ ነገሮች ትኩረት ይሰጣል። አይሁዶች የታላቅነት ዐቢይ ማረጋገጫው ተአምር ማድረግ ነው ብለው ያስቡ ስለነበረ ሁልጊዜም ተአምራዊ ምልክቶችን ይፈልጉ ነበር። «ተአምር እሳየንና እንከተልሃለን። ተአምር አድርግና ወደ ስብሰባህ እንመጣለን።» ስለሆነም፥ ተአምራትን እንደሚያሳዩ ቃል የሚገቡና ሥጋዊ ጥቅም የሚሰጡ ሰዎች በአይሁዶች ዘንድ እጅግ ተወዳጆች ነበሩ። ይህ ከዛሬው ዘመን ጋር ይመሳሰላል?

የውይይት ጥያቄ፡- ዛሬ ክርስቲያኖች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በዚሁ ዓለማዊ ወጥመድ የሚጠመዱት እንዴት ነው?

የእግዚአብሔር ጥበብ ከዓለም የጥበብ ትምህርት ተቃራኒ ነው።

ሀ. የእግዚአብሔር ጥበብ በመስቀሉ ስብከት ላይ ያተኩራል። ዋናው ነገር የሰባኪው ማንነት ሳይሆን፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ መምጣቱና እውነት መሆኑ ነው።

ለ. መለኮታዊ ጥበብ ሰዎች እንደ ታላቅ ነገር ከሚመለከቱት ጋር ይቃረናል። ዓለም መስቀል የሽንፈት ስፍራ እንደሆነ ታስባለች። የነፍሰ ገዳዮች መቀጫ የሆነው መስቀል ለሰው ልጆች ችግሮች መፍትሔ የሚሆነው እንዴት ነው? እግዚአብሔር ግን በጥበቡ የሞትን መሣሪያ ወደ ሕይወት መሣሪያነት በመለወጥ የሰውን ልጆች የኃጢአት ዋጋ በከፈለበት ቦታ የእርሱ ልጆች የሚሆኑበትን መንገድ ከፍቷል።

ሐ የእግዚአብሔርን ጥበብ የሚረዳው ትሑቱ እንጂ ኩሩው አይደለም። ስለሆነም፥ ዝቅ ያሉ፥ ብዙ ትምህርት፥ ሀብት ወይም የዓለም ክብር የሌላቸው ሰዎች ናቸው ወንጌሉን ተረድተው የሚቀበሉት። የእግዚአብሔር መንግሥት በቀዳሚነት የተገነባው ዓለም በምትንቃቸው ሲሆን፥ ዓለም የምታከብራቸው ሰዎች የእግዚአብሔርን የድነት (ደኅንነት) መንገድ ለመቀበል ይቸገራሉ።

መ. የእግዚአብሔር ጥበብ ከሰዎች፥ በተለይም የፖለቲካ፥ የትምህርትና የኢኮኖሚ መሪዎች ከሆኑት ወገኖች የተሰወረ ነው። ብዙውን ጊዜ ወንጌሉ ትሕትናን እንዴት እንደሚጠይቅ ለመረዳት የሚቸገሩ ሲሆኑ፥ ያላቸውን በረከት ትተው ሙሉ ለሙሉ ወደ እግዚአብሔር ድነት (ደኅንነት) ለመመለስ ይፈተናሉ። ይህ ለመሪዎች ከባድ ነው። የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎች ክርስቶስ እንዲሰቀል የጠየቁት ለዚህ ነበር።

ሠ. በክርስቲያኖች ውስጥ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ፍላጎት፥ አሳብና አመለካከት ያውቃል። እውነተኛ መንፈሳዊነት ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን ለመንፈስ ቅዱስ የሚሰጡና እርሱም በሰዎች፥ በትምህርት ወይም በኃይልና በመሳሰሉት ላይ ሳይሆን በድነትና እግዚአብሔርን በማስከበር ላይ የሚያተኩረውን ጥበብ እንዲገልጥላቸው የሚፈቅዱት ብቻ ናቸው።

ረ. የእግዚአብሔር ጥበብ የመንፈሳዊ ጥበብ መለያ ነው። ክርስቲያኖች በሚጣሉበት ጊዜ ወይም ከክርስቶስ ይልቅ ሰዎችን በሚከተሉበት ወቅት የእግዚአብሔር ጥበብ እንደሌላቸው ያሳያል። መንፈሳዊ ብስለት ቢኖራቸው ዓለማዊ ጥበብ (ዓለም ዋጋ የምትሰጣቸው ነገሮች) ለዘላለማዊ መንግሥትና ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የሚስማማ ሕይወት እንዲመሩ ለማድረግ እንደማይጠቅም ባወቁ ነበር።

ሰ. የእግዚአብሔር ጥበብ ከትምህርት አይገኝም። ይህ እግዚአብሔር ለሰዎች የሚገልጠው ነው። ጳውሎስ ድነትን (ደኅንነትን) ያላገኙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ሊረዱ አይችሉም ማለቱ አይደለም። ያልዳነ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እንብቦ ቃላቱን ሊረዳ ቢችልም፥ እውነቱ ከሕይወቱ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ግን አያውቅም። የእግዚአብሔር ጥበብ፥ ትሑቱን ሲሸልም ኩሩውን ግን ይፈርድበታል፥ በእግዚአብሔር የሚታመነውን ሲያድን በራሱ የሚታመነውን ይኮንነዋል። መስቀሉ ድነትን (ደኅንነትን) እንዲያመጣ ሲያደርግ የሰው ፍልስፍናን አታላይነት ያሳያል፥ ሌሎችን ማገልገል እንደሚያስከብርና ራስን ማገልገል እንደሚያዋርድ ያሳያል።

ሸ. ዓለም ሞኝነትና ጥበብ የሆነውን እንደምታውቅ ብታስብም፥ ትክክል የሆነውንና ያልሆነውን፥ ዘላለማዊውንና በዚህ ዓለም ብቻ የተወሰነውን፥ እንዲሁም እውነተኛውንና እውነተኛ ያልሆነውን ጥበብ በግልጽ ሊረዱ የሚችሉት የእግዚአብሔር ጥበብ ያላቸው ብቻ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያውቁና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለመከተል የወሰኑ ሰዎች «የክርስቶስ ልብ» ስላላቸው፥ ጠቢባን ብቻ ሳይሆኑ ጠቅላላ ሕይወታቸውን እግዚአብሔርን ለማስከበርና ለዘላለማዊ ሕይወት በሚያዘጋጃቸው መልኩ የሚኖሩ ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከምታውቃቸው ሰዎች መካከል በዓለም ጠቢባን ላይባሉ ቢችሉም፥ በአኗኗራቸው መለኮታዊ ጥበብን የሚገልጹትን ሰዎች ዘርዝር። ለ) ሕይወታቸው በሌሎች ሰዎች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምንድን ነው?

ጳውሎስ ዘላለማዊ መፍትሔዎች የሚገኙት በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በመቀበል ብቻ መሆኑን ስለተገነዘበ፥ የሚከተሉትን ነጥቦች አስተላልፎአል።

1) ጳውሎስ ግሪኮችን ያስደነቀው አንደበተ ርቱዕነቱ የወንጌሉን መልእክት እንዳይሰውር በማሰብ በዚሁ ጉዳይ ላይ አጽንኦት ከማድረግ ተቆጥቧል (1ኛ ቆሮ. 2፡1-5)። መልእክቱን ቀለል አድርጎ አቅርቧል። አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ ይህን ሲል በአቴና የፈላስፋዎችን ትምህርት እየጠቀሰ በዓለም ጥበብ ለመናገር የሞከረበትን ሁኔታ እያስታወሰ ነበር ይላሉ። ይህ የማስተማር መንገድ ውጤታማ ሆኖ በአቴና ብዙ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ አላመጣም ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ በቆሮንቶስ የሚያባብል ቃል ሳይጠቀም ወንጌሉን በግልጽ ሰበከ። ኩሩና የተማሩ የአቴና ሰዎች ወንጌሉን ለመቀበል ቢቸገሩም፥ በቆሮንቶስ የሚገኙ ድሆች፥ ባሮችና ያልተማሩት ግን በቀላሉ ለማመን ችለዋል።

2) እግዚአብሔር መልእክቱን ለማጠናከር ተአምራትን ሠርቷል። እግዚአብሔር ዛሬም ተአምራትን ይሠራል። ነገር ግን እግዚአብሔር ተአምራትንና ፈውስን የሚያመጣበት ቀዳሚ ምክንያት ሰዎችን ለማስደነቅ ወይም ችግራቸውን ለመቅረፍ አይደለም። በዓለም ዙሪያ ብዙ ተከታይ ለማግኘትም አይደለም። የድነት (ደኅንነት) መልእክት ከእግዚአብሔር እንደመጣ ለማሳየት ነው። ጳውሎስ ሕዝቡ በእርሱ ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔርና በወንጌሉ ላይ እንዲያተኩር በመፈለጉ ተአምራትን በጥንቃቄ እንዳደረገ ገልጾአል (1ኛ ቆሮ. 2፡5)።

የውይይት ጥያቄ፡- ጳውሎስ ለርቱዕ አንደበትና ለተአምራት ካሳየው አመለካከት ምን እንማራለን?

3) የተለያዩ ሰዎችን ከመከተል የሚመጣው ክፍፍል መሪዎች እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች የሚያበረክቱትን የአገልግሎት ድርሻ በተሳሳተ መንገድ እንድንረዳ ያደርጋል (1ኛ ቆሮ. 3)። መንፈሳዊ መሆንህን ወይም አለመሆንህን እንዴት ታውቃለህ? በልሳን በመናገር ወይም ታላላቅ መንፈሳዊ ስጦታዎችን በመጠቀም ነውን? ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ስጦታዎች በሙሉ እንደነበሯቸው አስረድቷል። ነገር ግን መንፈሳዊ ብስለት ስላልነበራቸው ዓለማዊ ጥበብን ይከተሉ ነበር። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሃሳባቸውና ድርጊታቸው እንደ ዓለማዊያን ነበር። ሕይወታቸው በእግዚአብሔር ጥበብ የሚመራ አልነበረም። ዓለማዊነት ወይም የዓለምን ጥበብ መከተል ራሱን የሚገልጸው እንዴት ነው? ከዐበይት የመገለጫ መንገዶች አንዱ ክፍፍል ነው። በቆሮንቶስ ክፍፍሉን ያስከተለው መንፈሳዊ ስጦታ ስለነበራቸው መሪዎች በምእመናኑ ዘንድ የነበረው የተሳሳተ አመለካከት ነበር። ዛሬ ክፍፍሉን የሚያስከትለው ጎሰኝነት፥ ገንዘብ፥ ወዘተ. ሊሆን ይችላል። የችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ ክርስቶስ ብቻ ሆኖ ሳለ በሰብአዊ መሪዎች ላይ በምንደገፍበት ጊዜ፥ የዓለምን መንገዶች እንደምንከተል ማሳየታችን ነው።

እንግዲህ፥ ተሰጥዖ ያላቸውን መሪዎችና ክርስቲያኖች ሁሉ መረዳት ያለብን እንዴት ነው?

ሀ. እያንዳንዱ መሪ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ለመገንባት የሚያስችል ልዩ ክፍል የሰጠው አገልጋይ ብቻ ነው። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን ተካይ ነበር። እግዚአብሔር ጳውሎስ ወንጌል ወዳልተሰበከባቸው አካባቢዎች በመሄድ ስለ ክርስቶስ እንዲመሰክርና አብያተ ክርስቲያናት በሚባሉ ኅብረቶች እንዲያደራጃቸው ልኮት ነበር። አጵሎስ በእግዚአብሔር ቃል አማካኝነት ጳውሎስ የተከላቸውን አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲያጠጣ የተመረጠ ስጦታ የነበረው አስተማሪ ነበር።

ለ. ዘላቂ ፍሬ የሚያስገኘው የግለሰቡ ስጦታ ሳይሆን የእግዚአብሔር ሥራ ነው። አንድ ገበሬ ችግኙን ከመትከልና ውኃ ከማጠጣት በቀር የማሳደግ ችሎታ እንደሌለው ሁሉ፥ የትኛውም መሪ መንፈሳዊ ዕድገትን ሊያመጣ አይችልም። ይህን ሊያደርግ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር በዋናነት የሚሠራው በሰዎች አማካኝነት ነው። እኛ እግዚአብሔር የሚሠራብን መሣሪያዎች ነን። ለሰው ስጦታዎችን የሚሰጠውም ሆነ መንግሥቱን ለመገንባት የክርስቲያኖችን ሥራ የሚጠቀመው እግዚአብሔር ስለሆነ፥ ቀዳሚ ትኩረት የሚገባው ለሰዎች ሳይሆን ለእግዚአብሔር ነው። ማንኛውም ስጦታ ያለው መሪ (ሰባኪ፥ የፈውስ አገልጋይ) ከእግዚአብሔር በስጦታ የሚቀበለው እንጂ ከራሱ ጥረት የመነጨ አይደለም። ስለሆነም፥ በመሪው ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ ማተኮር እንዳለብን ልንገነዘብ ይገባል። (ይህ ከእኛ የበለጠ ስጦታ ባላቸው ሰዎች መቅናት እንደሌለብንም ያሳያል። ይህ እነርሱ በጥረታቸው ያገኙት ሳይሆን፤ የእኛን ስጦታ ከእግዚአብሔር እንደተቀበልን ሁሉ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተቀብለውታል።)

ሐ. እያንዳንዱ መሪ ከእግዚአብሔር ዘንድ ልዩ ጥሪ፥ ዓላማና ችሎታ አለው። እያንዳንዱ ግለሰብ መሪና እያንዳንዱ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር የተቀበላቸውን ችሎታዎች ለተጠቀመበት ሁኔታ በኃላፊነት ይጠየቃል። ዓላማው ስጦታውን የተቀበለውን ሰው ለማስከበር ሳይሆን፥ ቤተ ክርስቲያኒቱ አድጋ እግዚአብሔር ከሚፈልግበት ደረጃ እንድትደርስ ለማድረግ ነው። እያንዳንዱ ግለሰብ ቤተ ክርስቲያን እንድታድግ ለማገዝ የራሱን ድርሻ በጥንቃቄ ማበርከት አለበት።

መ. እያንዳንዱ ክርስቲያንና በተለይም መሪዎች የሚሠሩት የክርስቶስ ቤተ መቅደስ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን ለመገንባት የጋራ ዓላማ ነው። ስለሆነም፥ አንድ ክርስቲያን ከሌላው የበለጠ ክብር እንዳገኘ በማሰብ መቅናት ወይም ከሌላው ክርስቲያን ወይም መሪ የበለጠ ክብር ለማግኘት መወዳደር አያስፈልግም።

ሠ. ክርስቶስ እያንዳንዱን ክርስቲያን እግዚአብሔር በሰጠው ስጦታ አማካኝነት ለቤተ ክርስቲያን ግንባታ ስላበረከተው አስተዋጽኦ ይጠይቀዋል። እግዚአብሔር ፍርዱን የሚሰጠው በምን ላይ ተመሥርቶ ነው? ስለምንሠራ ብቻ ሳይሆን በግንባታው ወቅት ስለ አገልግሎታችን ባለን አመለካከትና በመነሻ አሳባችን ላይ በመመሥረት ነው። የቤተ ክርስቲያን አገልግሎታችን ጊዜያዊ (ገለባ፥ እንጨት፥ ሣር) ወይም ዘላቂ (ወርቅ፥ ብር፥ የከበረ ማዕድን) የሚሆነው በአመለካከታችንና በመነሣሻችን፥ እንዲሁም ለማን ክብር እንዳገለገልን በሚያመለክቱ መስፈርቶች ነው። ስለሆነም የዓለምን ጥበብ በመጠቀም ለሰው ከብር ከሠራን፥ ሥራችን ሁሉ ዋጋ ቢስና ሽልማትን የማያስገኝ ይሆናል። ነገር ግን እግዚአብሔርን ለማስከበርና መንግሥቱን ለመገንባት ባለን መሻት የምናከናውናቸው ነገሮች በዓለም ፊት ተደናቂነትን ቢያተርፉ ወይም ባያተርፉ፥ ትንሽ ወይም ትልቅ ቢሆኑ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሽልማትን ያስገኛሉ። ጳውሎስ ይህ ግምገማ ከእግዚአብሔር ዘንድ የምናገኘውን ሽልማት እንጂ ዘላለማዊ ደኅንነታችንን እንደማይነካ አመልክቷል።

ጳውሎስ ሁለት ዐበይት አሳቦችን በመግለጽ ይህንን ክፍል ደምድሟል። በመጀመሪያ፥ የአማኞች ሰውነት መንፈስ ቅዱስ የሚያድርበት የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆነ ገልጾአል። ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ በእያንዳንዱ አማኝ ሕይወት ውስጥ እንደሚያድር ከሚገልጸው 1ኛ ቆሮንቶስ 6፡19 በተቃራኒ፥ በዚህ ስፍራ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚገኙ የክርስቲያኖች ቡድን ነበር የሚናገረው። በቆሮንቶስ (ወይም በኢትዮጵያ፥ አዲስ አበባ ወይም በሆነች አጥቢያ) ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚገኝ የአማኞች አካል ውስጥ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ያድራል። ይህም እግዚአብሔር በምድረ በዳው ጉዞ ወቅት በመገናኛ ድንኳን ውስጥ፥ በሰሎሞን ዘመን ደግሞ በቤተ መቅደስ ውስጥ ካደረበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው። በመጣላታችን ምክንያት ቤተ ክርስቲያንን ከመገንባት ይልቅ የምናፈርስ ከሆነ፥ ከእግዚአብሔር ጋር እየተጣላን ስለሆነ ፍርድ ይጠብቀናል። በብሉይ ኪዳን በሕንፃ ውስጥ የነበረው እግዚአብሔር አሁን በአማኞች ማኅበረሰብ ውስጥ እንደሚኖር ጳውሎስ ገልጾአል። እኛም እርሱንና በማኅበረሰባችን ውስጥ የሚገኘውን የእርሱን ሕልውና ማክበር አለብን። የክርስቲያኖች መጣላት የእግዚአብሔርን ሕልውና ትርጉም አልባ ያደርገዋል። እንደ ዝሙት ሁሉ የእርስ በርስ ጠብም በሕዝቡ መካከል የሚኖረውን የእግዚአብሔርን ስም ያሰድበዋል።

ሁለተኛ፥ ጳውሎስ ነገሮችን በዓለም ጥበብ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ጥበብ እይታ እንዲመለከቱ አስጠንቅቋቸዋል። እንደ እግዚአብሔር መመዘኛ ጠቢብ መሆን ትሕትናን (ሞኝ መሆን) የሚያካትት ሲሆን፥ እንደ ጳውሎስ፥ እንደ አጵሎስ ወይም ጴጥሮስ ባሉት ልዩ ስጦታ ባላቸው መሪዎች ላይ አያተኩርም። መንፈሳዊ ጥበብ ክርስቶስን ብቻ በመገንዘብ አሳብን በሰማያዊው ነገር ላይ ሲያደርግ፥ አስፈላጊ የሚመስሉትን ምድራዊ ነገሮች ሁሉ ይጥላል። እንደ ድነት (ደኅንነት)፥ የእግዚአብሔር ልጅነት መንፈሳዊ በረከቶች፥ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ እንክብካቤ ያሉትን ወሳኝ ነገሮች እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል ሰጥቶናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከዚህ ክፍል ስለ መሪነት ምን ልንማር እንደምንችል ግለጽ። ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካለው የእግዚአብሔር ጥበብ ይልቅ የዓለምን ጥበብ ለአሳባችንና ለተግባራችን መሠረት አድርገን በምንጠቀምበት ጊዜ ችግሮች ስለመከሰታቸው ምን እንማራለን? ሐ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ስለሚገኙት ችግሮች የዘረዘርኸውን ተመልሰህ ከልስ፡፡

የውይይት ጥያቄ፡- እያንዳንዱ ችግር በመለኮታዊ ሳይሆን በዓለማዊ ጥበብ ላይ መመሥረቱን አሳይ። መ) እግዚአብሔር የሰጠህን ስጦታዎችና ኃላፊነቶች ዘርዝር። ሁሉንም በጸሎት ሆነህ መዝናቸው። እነዚህን ነገሮች የምታከናውናቸው ጊዜያዊ ጥቅሞችን በሚያመጣና እግዚአብሔርን በማያስከብር መንገድ (በእንጨት፥ በሣር፥ በገለባ) ነው? ወይስ በንጹሕ ልብ ለእግዚአብሔር ክብርን በሚያመጣ መልኩ (በወርቅ፥ በብርና በከበረ ድንጋይ ነው)?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: