የመንፈሳዊ ስጦታዎች በተለይም በልሳን የመናገር ዓላማ ምንድን ነው? (1ኛ ቆሮ. 12፡1-14፡25)

አንዳንድ አማኞች፣ «ደካማ የምንሆንበት ምክንያት በቂ መንፈሳዊ ስጦታዎች ስለሌሉን ነው። ሁሉም ክርስቲያኖች ሊያገኙት የሚገባው እጅግ ጠቃሚ ስጦታ በልሳን መናገር ነው። መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያኑ ውስጥ እንዳለ የሚታወቀው በልሳን ሲናገር ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሰዎች በልሳን ስለሚናገሩና ብዙ ተአምራት ስለሚፈጸሙ መነቃቃትን እንዳገኘን እናውቃለን።» ይላሉ። ለመሆኑ እንዲህ ዓይነት አባባሎች እውነት ናቸው?

መንፈሳዊ ስጦታዎች ጠቃሚዎች ናቸው። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች እንዲያውቁ የፈለገውም ለዚህ ነው (1ኛ ቆሮ. 12፡1)። ነገር ግን መንፈሳዊ ስጦታዎች አንድ ግለሰብ ወይም ቤተ ክርስቲያን በሳል መሆናቸውን አያሳዩም። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ምንም የጸጋ ስጦታ እንዳልጎዳላቸው ቢናገርም፥ መንፈሳዊ ብስለት እንዳልነበራቸው ገልጾአል (1ኛ ቆሮ. 3፡1-4)። ክፍፍል፥ ቅንዓትና ሌሎችም ኃጢአቶች ቤተ ክርስቲያኒቱን አጨናንቀው ነበር። እንዲያውም ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ይህን ረዥም ትምህርት ያቀረበው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ስጦታዎች ላይ በነበሯቸው የተሳሳቱ ግዛቤዎች ሳቢያ ይከፋፈሉ ስለነበረ ነው። የተቀረውን የአዲስ ኪዳን ክፍል በጥንቃቄ ብንመረምር፥ መንፈሳዊ ስጦታዎች በሌሎች ጥቂት ስፍራዎች ብቻ እንደተዘረዘሩ እንረዳለን (ሮሜ 12፡4-7፤ ኤፌ. 4፡11-13፤ 1ኛ ጴጥ. 4፡10-11)። ይህም መንፈሳዊ ስጦታዎች የአዲስ ኪዳን ቀዳሚ ትኩረቶች እንዳልሆኑ ያስረዳናል። በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ ውስጥ በአጽንኦት የተገለጸው የመንፈስ ፍሬ ነው (ገላ. 5፡22-23)። ይህም ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ እንድነት፥ ተስፋ፥ ትዕግሥት፥ የመሳሰሉት የሚገኙበት ነው። ይህም እውነተኛ መንፈሳዊነት በቀዳሚነት ራሱን የሚገልጸው በመንፈሳዊ ስጦታዎች ሳይሆን በመንፈሳዊ ባሕርያት እንደሆነ ያሳያል።

የውይይት ጥያቄ፡- አንዳንድ ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ መንፈሳዊ መነቃቃት እንዳለ ይናገራሉ። አስደሳች አምልኮ፥ የልሳን ስጦታና አስደናቂ ተአምራት ከወትሮው በበለጠ እንደሚታዩ ያስረዳሉ። ሀ) ይህ ሰዎች ከበፊት ይልቅ መንፈሳዊ ብስለትን እንደተላበሱ የሚያሳይ ይመስልሃል? መልስህን አብራራ። ለ) የመንፈስ ፍሬ (ገላ. 5፡22-23ን አንብብ።) ከበፊት የበለጠ የሚታይ ይመስልሃል ? መልስህን አብራራ።

የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ 12ን አንብብ። ሀ) ጳውሎስ በዚህ ክፍል ያተኮረባቸውን የመንፈሳዊ ስጦታዎች መርሆዎች ዘርዝሩ። ለ) ከእነዚህ መርሆዎች ዛሬ አንዳንድ ሰዎች ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ከሚያስቡት እሳብ ጋር የሚጋጩት የትኞቹ ናቸው?

ችግሩ፡- የቆሮንቶስ አማኞች በአንዳንድ የጸጋ ስጦታዎች፥ በተለይም በልሳን አጠቃቀም ላይ በአሳብ የተከፋፈሉ ይመስላል። አንዳንድ ክርስቲያኖች በልሳን መናገር እጅግ በጣም ጠቃሚ ስጦታ ነው ብለው አሰቡ። እንዳንድ ክርስቲያኖች፥ «እውነተኛ ሰዎች ሁሉ በልሳን ይናገራሉ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ሰዎች በልሳን መናገራቸው የሌሎችን አምልኮ ቢረብሽም እንኳ የተሻለ ነው» ይሉ ነበር። እነዚህ ሰዎች ጳውሎስ ክርስቲያኖች ሁሉ በልሳን እንዲናገሩ ያበረታታላቸው ዘንድ ፈለጉ። ሌሎች ክርስቲያኖች ደግሞ ብዙ ሕዝብ በሚያመልክበት ስፍራ በልሳን መናገሩ አስፈላጊ እንዳልሆነ በመግለጽ እጥብቀው ተቃወሙ። በልሳን የሚናገሩ ሰዎች ጉባኤውን ከሚያውኩ በቀር ምንም ጥቅም እንደሌለው አስረዱ። ስለሆነም፥ ጳውሎስ በልሳን የሚናገሩትን ሰዎች እንዲከለክል ፈለጉ። «የመንፈሳዊ ስጦታዎች ዓላማ ምንድን ነው? ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት አምልኮ ውስጥ (በተለይ ልሳንን) እንዴት ልንጠቀም ይገባል?» ሲሉ ጠየቁት። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በሰጠው ምላሽ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ብቻ ሳይሆን፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው ፍቅር፥ አንድነትና መተሳሰብ ጠቃሚ ትምህርት ሰጥቷል።

መፍትሔው፡- ምንም እንኳ ጳውሎስ ብዙ ሕዝብ በሚገኝበት አምልኮ ውስጥ ልሳንን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ዝርዝር መመሪያዎችን ባይሰጥም (1ኛ ቆሮ. 14)፥ መንፈሳዊ ስጦታዎችን መጠቀም ስለሚያስፈልግባቸው ምክንያቶችና ስጦታዎቹን በምንጠቀምበት ጊዜ ሊኖረን ስለሚገቡ አመለካከቶች አጽንኦት ሰጥቶ አብራርቷል። ቀጣዩ ጳውሎስ የሰጠው ትምህርት ጭማቂ ነው።

ሀ. በልሳን መናገር የአንድን ሰው መንፈሳዊነት አያረጋግጥም (1ኛ ቆሮ. 12፡1-3)። በዚህ ክፍል የጳውሎስን ምክንያት መረዳቱ አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ጳውሎስ በልሳን ከሚናገሩ ሰዎች አንዳንዶቹ አረማውያን በነበሩ ጊዜ (በተለይ ጠንቋዮቹ) በልሳን ይናገሩ እንደነበረ እያስታወሳቸው ይሆናል። ስለሆነም በልሳን መናገር በራሱ የመንፈሳዊነት ምልክት ሊሆን አይችልም። ክርስቲያን የሆኑትም ያልሆኑትም በልሳን ሊናገሩ ይችላሉ። እንግዲህ፥ የአንድ ሰው ልሳን ከእግዚአብሔር ወይም ከሰይጣን መሆኑን እንዴት እናውቃለን? ጳውሎስ የክርስቶስን ጌትነት በልቡ የሚያምንና በሕይወቱ የሚያረጋግጥ ማንኛውም ክርስቲያን በሰይጣን ቁጥጥር ሊናገር እንደማይችል ገልጾአል።

ይህን መፈተኛ ለመረዳት፥ የጳውሎስን ዘመን ባሕል መረዳት አለብን። ዛሬ ሰዎች ስለ ትርጉሙ ብዙም ሳያውቁ መስቀልን የውበት ትምህርት አድርገው ይጠቀማሉ። ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች ሳይቀሩ ኢየሱስ ጌታ ነው ሊሉ ይችላሉ። በጳውሎስ ዘመን ግን አንድ አይሁዳዊ የሆነ ሰው ኢየሱስ የብሉይ ኪዳን አምላክ የሆነው ያህዌ ነው ቢል፥ አይሁዶች ለፈጸመው የስድብ ኃጢአት በድንጋይ ወግረው ይገድሉት ነበር። አንድ አሕዛብ ኢየሱስ ጌታ ነው ቢል፥ ማኅበረሰቡ የተሰቀለው ኢየሱስ ጌታ ነው በማለቱ ከማኅበራቸው ያስወጡት ነበር። ዛሬ ለሙስሊሞች በክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነት ማመን የሚከብደውን ያህል ያን ጊዜ ለሰዎች በክርስቶስ ማመኑ አስቸጋሪ ነበር። ስለሆነም፥ በክርስቶስ ላይ ላላቸው እምነት ለመሞት የሚመርጡ ሰዎች እግዚአብሔር በልባቸው ውስጥ ለውጥ ያመጣባቸው ብቻ መሆናቸውን ገልጾአል። እንደነዚህ ዓይነት አማኞች በልሳን በሚናገሩበት ጊዜ የስጦታው ምንጭ መንፈስ ቅዱስ ለመሆኑ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ጳውሎስ አጽንኦት የሰጠው በሚናገራቸው ቃላት ላይ ሳይሆን፥ ግለሰቡ በሕይወቱ ክፍሎች ሁሉ በክርስቶስ አገዛዝ ሥር ስለመኖሩ ነው። ግለሰቡ ለክርስቶስ የማይገዛና ፍቅርን የማያሳይ ከሆነ፥ በልሳን የመናገርን ኃይል የሰጠው ሰይጣን ሊሆን እንደሚችል የመጠራጠር መብት አለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አኗኗራቸው ክርስቶስ የሕይወታቸው ጌታ መሆኑን የሚመሰክርላቸው ክርስቲያኖች በልሳን ሲናገሩ ሰምተሃል? ለክርስቶስ እንደሚገዙ በምን ታውቃለህ? የዚህ ዓይነቱ ልሳን ምንጭ ማን ነው? ለ) ለክርስቶስ ተገዝተውና ታዘው እንደሚኖሩ ሕይወታቸው የማይመሰክርላቸው ክርስቲያኖች በልሳን ሲናገሩ ሰምተሃል? ለክርስቶስ አለመገዛታቸውን እንዴት ታረጋግጣለህ? የልሳናቸው ምንጭ ማን ነው?

ለ. ከአንዱ አሀዱ–ሥሉስ አምላክ የሚመጡ የተለያዩ ስጦታዎች (አገልግሎቶችና አሠራሮችም ተብለዋል) አሉ (1ኛ ቆሮ. 12፡4-6)። ጳውሎስ እንዴት በሁለት ቃላቶች ላይ እንደሚያተኩር አጢን። ጳውሎስ «ልዩ ልዩ» በሚለው ሐረግ ላይ በማተኮር የተለያዩ ስጦታዎች መኖራቸውን ያሳያል። ይህም እንደ ልሳን ካለው አንድ ስጦታ ይልቅ እግዚአብሔር በሚሰጣቸው ስጦታዎች ሁሉ ላይ አጽንኦት መስጠት እንዳለብን ያመለክታል። እንዲሁም፥ እነዚህ የተለያዩ ስጦታዎች ከእግዚአብሔር (ከአንድ ምንጭ) እንደሚመጡ ለማሳየት «አንድ» በሚል ቃል ላይ ትኩረት አድርጓል። ስለሆነም፤ በልሳን የመናገር ስጦታ ያለው ሰው ሌላ ዓይነት ስጦታ ካለው ሰው ይልቅ መንፈስ ቅዱስ በበለጠ ሁኔታ ይኖርበታል ማለት አይደለም።

ሐ. እያንዳንዱ ክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ለጋራ ጥቅም ይሰጠዋል። ይህም በክርስቲያኑ ሕይወት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ያሳያል (1ኛ ቆሮ. 12፡7)። የእያንዳንዱ መንፈሳዊ ስጦታ ዓላማ የጋራ ጥቅም ነው። ስጦታው የሚሰጠው ለግለሰቡ የግል ጥቅም ሳይሆን፥ ለቤተ ክርስቲያን ነው። መንፈሳዊ ስጦታ መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዱ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲያገለግል የሚሰጠው ችሎታ ነው።

መ. መንፈስ ቅዱስ ለተለያዩ ሰዎች የተለያዩ ስጦታዎችን ይሰጣል (1ኛ ቆሮ. 12፡8-10)። አንዳንድ ክርስቲያኖች የተወሰኑ መንፈሳዊ ስጦታዎች ብቻ እንዳሉ ቢያስቡም፥ በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ የተገለጹት የመንፈሳዊ ስጦታዎች ዝርዝሮች አንድ ዓይነት አይደሉም። ይህም መንፈስ ቅዱስ ሊሰጥ የሚችላቸው የተለያዩ ስጦታዎች እንዳሉ ያሳያል። መንፈስ ቅዱስ በልሳን መናገርን ለሁሉም አማኞች አይሰጥም። ይህ አንድ ስጦታ ብቻ ሲሆን፥ መንፈስ ቅዱስ ለተለያዩ ሰዎች የሚሰጣቸው የተለያዩ ስጦታዎች አሉ።

ሠ. ማን የትኛውን ስጦታ እንደሚቀበል የሚወስነው መንፈስ ቅዱስ ነው (1ኛ ቆሮ. 12፡1)። መንፈሳዊ ስጦታን የሚሰጠን መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ፥ ሌሎች ከእኛ ይበልጥ አስደናቂ ስጦታ የተቀበሉ በሚመስልበት ጊዜ የመቅናት መብት የለንም። እንደ እኛ አስደናቂ የሆኑ ስጦታዎች የሌላቸውንም ቁልቁል ልንመለከትና ልንንቃቸው አይገባም። ስጦታውን የሚወስነው ተቀባዩ ሳይሆን፥ እንደ ዓላማውና እንደ ምርጫው የሚሰጠው መንፈስ ቅዱስ ነው።

ረ. ሰውነት አብረው ከሚሠሩ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች እንደተዋቀረ ሁሉ፥ ቤተ ክርስቲያንም ለክርስቶስ አካል ጥቅም በሚሠሩ የተለያዩ ስጦታዎች ባሏቸው ሰዎች ተዋቅራለች (1ኛ ቆሮ. 12፡12-26)። ይህ አሳብ ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን ያስተምራል። በመጀመሪያ፥ እያንዳንዱ ክርስቲያን ስጦታውን በሚገባ ካልተጠቀመ ቤተ ክርስቲያን ትዳከማለች። ሁለተኛ፥ እያንዳንዱ መንፈሳዊ ስጦታ ዋጋ ሊሰጠው እንደሚገባና አንዱ መንፈሳዊ ስጦታ ከሌላው እንደሚበልጥ ሁሉ ከፍ ከፍ መደረግ እንደሌለበት ያሳያል። ሦስተኛ፥ እጅግ አስደናቂ ያልሆኑ ወይም ጎልተው የማይታዩ ስጦታዎች መከበር እንዳለባቸው ያሳያል።

ሰ. የበለጠ ጠቀሜታ ያላቸው አንዳንድ መንፈሳዊ ስጦታዎች አሉ። ስለሆነም፥ ሐዋርያት፥ ነቢያት፥ አስተማሪዎች በቀዳሚነት ተዘርዝረዋል (1ኛ ቆር. 12፡27-28፥ 31)። ጳውሎስ በልሳን መናገር ከወሳኝ መንፈሳዊ ስጦታዎች አንዱ እንዳልሆነ ለማሳየት በዝርዝሩ ውስጥ ከወደ መጨረሻው አካባቢ ጠቅሶታል።

ሸ. ሁሉም ስጦታዎች ያሉት ክርስቲያን የለም (1ኛ ቆሮ. 12፡29-30)። ጳውሎስ ሰዎች ሁሉ ሐዋርያት ወይም ነቢያት እንዳልሆኑ ሁሉ፥ ሁሉም በልሳን እንደማይናገሩ ገልጾአል። የትኞቹም ስጦታዎች ለሁሉም ሰው አይሰጡም፤ ሁሉም ስጦታዎች ያሉትም ክርስቲያን የለም።

የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 13ን አንብብ። ሀ) ጳውሎስ ይህን ከሁሉም የሚሻል መንገድ ያለው ለምን ይመስልሃል? ለ) በልሳን እንደ መናገር ባሉት ጉዳዮች በአሳብ በምንለያይበት ጊዜ ጳውሎስ በዚህ ስፍራ የገለጻቸው መርሆዎች እንዴት ሊመሩን ይገባል?

ቀ. ከመንፈሳዊ ስጦታዎች «እጅግ የሚሻለው መንገድ» እርስ በርሳችን መዋደዳችን ነው (1ኛ ቆሮ. 12፡31-13፡13)። እንደ ልሳን፥ ትንቢት፥ እውቀት ወይም ተአምር የመሥራት እምነት ያሉ እጅግ አስደናቂ ስጦታዎችን እንኳ ለሌሎች የማሰብንና የማፍቀርን መርህ ሳንከተል በተሳሳተ አመለካከት ከሥራ ላይ ልናውላቸው እንችላለን። እነዚህን ስጦታዎች በራስ ወዳድነት፥ ለግል ክብር ወይም በሚያውክ መንገድ በምንጠቀምበት ጊዜ፥ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡት ጥቅም ካለመኖሩም በላይ የአጥፊነትን ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።

የፍቅር መንገድ ከሁሉም የሚሻለው ለምንድን ነው? ጳውሎስ ፍቅርን የገለጸው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚካሄዱ አለመስማማቶች አንጻር ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተለያዩ ክርስቲያኖች ስለ ልሳን የተለያዩ አመለካከቶችን ይዘው ሳሉ አንድነትን ልንጠብቅ የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ ለዚህ ችግር መፍትሔው ፍቅር እንደሆነ አስረድቷል። የተለያዩ አመለካከቶች በሚኖሩበት ጊዜ አንዱ ወገን ሌላውን መታገሥ አለበት። አንደኛው ወገን ከሌላው የበለጠ መንፈሳዊ መሆኑን ለማሳየት ሊሞክር፥ ሊሳደብና አመለካከቱን በግድ ለመጫን ሊጥር አይገባም። ነገር ግን እርስ በርሳቸው ለመረዳዳት፥ ለመከባበርና አንድነትን ለመጠበቅ በልዩነቶቻቸው ላይ በእውነተኝነት ሊወያዩ ይገባል።

ፍቅር ዘላቂ ስለሆነ ከሁሉም ይልቃል። ለዘላለም የሚዘልቀው ፍቅር ብቻ ነው። ልሳን አንድ ቀን ያበቃል። ሁሉንም ነገር ልናውቅ ስለማንችል፥ ትንቢትና እውቀት ሁልጊዜም ከፊል ብቻ ናቸው። ከመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የማንረዳቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ስለሆነም፥ የራሳቸውን መንገድ የሚሹትን ሕፃናት ሳንመስል ሁሉንም ነገር ለማወቅ አለመቻላችንን በትሕትና ተቀብለን ለሌሎች ፍቅርና አቀባበልን ልናሳይ ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የተከሰተውን የአሳብ እለመግባባት በምሳሌነት በመውሰድ፥ በ1ኛ ቆሮንቶስ 13 የተገለጸው ዓይነት ፍቅር ለችግሩ መፍትሔ በመስጠት ሰዎች እንዳይጎዱና የክርስቶስም ስም እንዳይሰደብ ሊያደርግ የሚችልበትን መንገድ አብራራ።

የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 14ን አንብብ። ሀ) ሦስት ዓምዶች ያሉት ሠንጠረዥ ሥራ። የመጀመሪያውን ዓምድ «በልሳን መናገር» ብለህ ሰይም። ሁለተኛውን «ትንቢትን መናገር» ብለህ ሰይምና በሦስተኛው ዓምድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ዘርዝር። ይህን ክፍል በምታነብበት ጊዜ፥ ጳውሎስ ስለ ልሳን የገለጸውን በመጀመሪያው ዓምድ፥ ስለ ትንቢት የገለጻውን በሁለተኛው ዓምድ፥ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በሦስተኛው ዓምድ ጻፍ። ለ) ጳውሎስ ትንቢትን መናገር ከልሳን እንደሚሻል በመግለጽ ያቀረባቸውን ነጥቦች ጠቅለል አድርገህ ጻፍ። ሐ) ከዚህ ክፍል የምንመለከታቸው የጉባዔ አምልኮ አንዳንድ ጠቃሚ መርሆዎች ምን ምንድን ናቸው?

በ. ክርስቲያኖች የሚበልጡትን የጸጋ ስጦታዎች እንዲፈልጉ ተበረታተዋል (1ኛ ቆሮ. 14፡1-25)። አብዛኞቹ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በልሳን የመናገር ጉጉት ነበራቸው። ይህ የመንፈሳዊ ብስለትና በመንፈስ ቅዱስ የመሞላት ትልቅ ምልክት ነው ብለው ያስቡ ነበር። መንፈስ ቅዱስ በበዓለ ኀምሳ ዕለት ራሱን የገለጻው በዚህ መንገድ አይደለምን? የሚል ክርክር አንሥተው ነበር። ጳውሎስ ግን ልሳን መንፈሳዊ ስጦታ መሆኑን ሳይክድ ከአንዳንድ ስጦታዎች ጋር ሲነጻጸር ልሳን አነስተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጾአል።

የሚበልጠው ስጦታ የትኛው ነው? መንፈሳዊ ስጦታዎች የተሰጡት ጠቅላላዪቱን ቤተ ክርስቲያን ለመገንባት እንጂ ለግል ጥቅም ስላልሆነ፥ የሚበልጠው መንፈሳዊ ስጦታ ጠቅላላዪቱ ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ብስለት እንድታድግና ምሉዕ እንድትሆን የሚረዳት ነው። ስለሆነም፥ የሚበልጠው መንፈሳዊ ስጦታ ቤተ ክርስቲያንን ለክርስቶስ በምታቀርበው አምልኮ፥ ክርስቶስን በመምሰል፥ ክርስቲያኖችንና ዓለምን በማገልገሉ ረገድ የተሟላ ተግባር እንድታከናውን የሚረዳትና ዳሩ ግን አሁን የሚጎድላት ስጦታ ነው። በመሆኑም፥ ቤተ ክርስቲያን ጥሩ አስተማሪ እያላት ወንጌላዊ ከሌላት፥ የሚበልጠው ስጦታ የወንጌል ስርጭት ይሆናል። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን አስተማሪ ሳይኖራት ወንጌላዊ ካላት የሚበልጠው ስጦታ ማስተማር ይሆናል። ጳውሎስ ትንቢት ከሁሉም የሚበልጥ ስጦታ ነው ማለቱ አይደለም። ቀደም ብሎ ትንቢት ከሁሉም እንደሚበልጥ ገልጾአል።

ጳውሎስ የተወሰኑ ስጦታዎች ከልሳን በላይ ለቤተ ክርስቲያን አስፈላጊዎች መሆናቸውን ለማብራራት ትንቢትንና ልሳንን አነጻጽሯል። አብዛኞቻችን ትንቢት የወደፊቱን ክስተት መተንበይ ነው ብለን እናስባለን። የትንቢት ስጦታ መሠረታዊ አሳብ ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚስማማ መልእክት ከእግዚአብሔር ተቀብሎ ለቤተ ክርስቲያን ማስተማርን ያሳያል። አንዳንድ ጊዜ መልእክቱ ወደፊት ከሚከሰቱ ነገሮች ጋር ሊዛመድ ይችላል። ብዙውን ጊዜ ግን መልእክቱ በወቅቱ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች የሚያገለግል ነው።

የጳውሎስ ትኩረት ስጦታዎችን ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው የአምልኮ ስፍራዎች የመጠቀሙ ሁኔታ እንደሆነ ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። ሕዝባዊ አምልኮ መንፈሳዊነታችንን የምናሳይበት ወይም በግላዊ በረከቶቻችን ላይ የምናተኩርበት አይደለም። ሕዝባዊ አምልኮ ምእመናን በጋራ የሚያካሂዱት ሲሆን፥ ዓላማውም የሁሉም መታነጽና መካፈል ነው። ጳውሎስ ስለ ግል አምልኮ አላነሣም። ጳውሎስ በዚህ ክፍል ልሳንን ከትንቢት ጋር እንደሚከተለው ያነጻጽሯል።

  1. አንድ ሰው በልሳን በሚናገርበት ጊዜ ለሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር ይናገራል። አንድ ሰው ትንቢት በሚናገርበት ጊዜ የእግዚአብሔርን መልእክት ለሰዎች ይናገራል።
  2. አንድ ሰው በልሳን በሚናገርበት ጊዜ አሳቡን የሚረዳው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ለሌሎች ሰዎች ግን ልሳን ካልተቃኘ የሙዚቃ መሣሪያ እንደሚወጣ ድምፅ ሁሉ የማይታወቅ ነው። አንድ ሰው ትንቢትን በሚናገርበት ጊዜ ግን ሰዎች የሚረዱትን ቋንቋ ይጠቀማል።
  3. አንድ ሰው በማይተረጎም ልሳን በሚናገርበት ጊዜ እርሱም ሆነ ጉባኤው የሚነገረውን ቃል ስለማይሰማ ሊታነጽ አይችልም። ሊባረክም ሆነ ሊማር አይችልም። ነገር ግን ትንቢትን በሚናገርበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ሌሎችን እንዲያበረታታና እንዲያጽናና ይጠቀምበታል።
  4. አንድ ሰው በልሳን በሚናገርበት ጊዜ በመንፈሱ ከእግዚአብሔር ጋር በመገናኘቱ ምክንያት ሊታነጽና ሊባረክ የሚችለው ራሱ ብቻ ነው። በትንቢት ሲናገር ግን ራሱም ጉባኤውም ይታነጻል።
  5. በልሳን መናገር መልካምና የተፈቀደ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ እንኳን፥ ብዙ ሰዎችን ስለሚጠቅም ትንቢትን መናገሩ የተሻለ ነው።
  6. በልሳን መናገር ለአሕዛብ ምልክት ሲሆን፥ ትንቢትን መናገር ግን ለአማኞች ምልክት ነው። ይህን አሳብ መረዳቱ አስቸጋሪ ነው። ጳውሎስ እግዚአብሔር በአይሁዶች ላይ በመፍረድ ወደ ባቢሎንና አሦር እንደሚሰዳቸው የተናገረበትን የራእይ 28፡11-12 ክፍል ይጠቅሳል። አይሁዶች ተማርከው በሚሄዱበት ጊዜ ከዚህ በፊት የማያውቁትን የአሦርና የባቢሎንን ቋንቋዎች ይሰሙ ዘንድ ተገድደው ነበር። ነገር ግን ባዕድ ቋንቋዎችን መስማቱ እስራኤላውያን ከኃጢአታቸው ተጸጽተው ንስሐ እንዲገቡ አላደረጋቸውም ነበር። ይሁንና ይህ በሌሎች ቋንቋዎች የሚናገሩ አሕዛብ ስለ እግዚአብሔር እንዲሰሙ አድርጓል። በሐዋርያት ሥራ 2 ሐዋርያት በልሳን በተናገሩ ጊዜም ተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጽሟል። ሐዋርያት በልሳን የተናገሩት በቀዳሚነት ለሰሚዎቹ ጥቅም ይመስላል። ይህ ከዓለም ዙሪያ ለተሰባሰቡ የማያምኑ ሰዎች ወንጌሉ ለእነርሱ መምጣቱን የሚያሳይ ምልክት ነበር። ሌሎች ምሁራን ጳውሎስ ይህን ሲል በብሉይ ኪዳን ባዕድ ቋንቋዎችን መስማት ለአይሁዶች የፍርድ ምልክት እንደሆነ ሁሉ፥ ዛሬም የማያምኑ ሰዎች የማይረዱትን ልሳን በሚሰሙበት ጊዜ አምነው ካልዳኑ ፍርድ እንደሚጠብቃቸው እየተገነዘቡ መሆኑን ማመልከቱ እንደሆነ ይናገራሉ።

ትንቢት ግን አማኞችን በእግዚአብሔር ቃል ለማነጽ ያገለግላል። ነገር ግን የማያምኑ ሰዎች እንኳ ትንቢትን በሚሰሙበት ጊዜ የእግዚአብሔርን ሥራ በመመልከት ይወቀሳሉ። ጳውሎስ በጉባኤ ላይ በልሳን ካልተናገርን የሚሉ ሰዎች የሕፃናትን ዓይነት ተግባር እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጾአል። እነዚህ ሰዎች በቀዳሚነት ለራሳቸውና ለራሳቸው መንፈሳዊ በረከት ትኩረት በመስጠታቸው የተሳሳተ አነሣሽ ምክንያት ነበራቸው ወይም ደግሞ ስጦታቸውን ለማሳየት ይፈልጉ ነበር። ለሌሎች ጥቅምና ዕድገት አስተዋጽኦ ለማድረግ ወይም ለማያምኑ ሰዎች መልካም ምስክርነትን ለመስጠት ፍላጎት አልነበራቸውም።

  1. በልሳን መናገር ንግግሩን በማይሰሙ ክርስቲያኖችና እንደ ሰከሩ ወይም እንዳበዱ በሚያስቡ ዓለማውያን ጭምር ግራ መጋባትን ያስከትላል። ትንቢትን መናገር ለክርስቲያኖች ጠቃሚ ትምህርትን ሲሰጥ፥ ዓለማውያንን ወደ ንስሐ ይመራል።

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) ብዙ ሰዎች በልሳን መናገር የሚፈልጉት ለምንድን ነው? ሰዎች በልሳን የሚናገሩባቸው መልካምና መልካም ያልሆኑ አነሣሽ ምክንያቶች ምን ምንድን ናቸው? ለ) በልሳን ላይ የሚያተኩሩ ሰዎች እንደ አስተዳደር፥ ልግስና፡ አገልግሎት፥ ትምህርት፥ ላሉት ለሌሎች የጸጋ ስጦታዎች አጽንኦት የማይሰጡት ለምንድን ነው? ሐ) ሰዎች በአስደናቂ የጸጋ ስጦታዎች ላይ እንዲያተኩሩ የሚያደርጋቸው አነሣሽ ምክንያት ምን ይመስልሃል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: