ጳውሎስ ድነት (ደኅንነት) ሕግጋትን በመጠበቅ ሳይሆን በክርስቶስ በማመን እንደሚገኝ አብራራ (ገላ. 3፡1-4፡31)

የውይይት ጥያቄ፡- ገላ. 3-4 አንብብ። ድነት (ደኅንነት) በእምነት ብቻ መሆኑን እንዴት እንደምናውቅ ጳውሎስ ያቀረበውን ክርክር ጠቅለል አድርገህ ግለጽ።

ብዙውን ጊዜ በክርስቶስ አዳኝነት ላይ በሚደገፉና ሥራቸው ለደኅንነታቸው አስተዋጽዖ እንዳለው በሚተማመኑ ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ሁለቱም የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን ሊጠብቁ ይችላሉ። ሁለቱም መጠጥ ላይጠጡ፥ ተገቢ ልብሶችን ሊለብሱ፥ ግብረገባዊ ሕይወት ሊመሩ፥ ወዘተ… ይችላሉ። በሁለቱ መካከል ቀዳሚ ልዩነት የሚታየው ከመነሣሻ ምክንያታቸው ወይም ለድነት (ደኅንነት) በሚያምኑት ነገር ላይ ነው። በክርስቶስ ብቻና በነፃ የድነት (ደኅንነት) ስጦታ የሚያምነው ሰው በክርስቶስና በክርስቶስ የመስቀል ሞት ላይ ያተኩራል። ጳውሎስ «በፊታችሁ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተስሎ ነበር» ሲል ይህን ለማለት ነበር (ገላ. 3፡1)። በክርስቶስ ላይ በምናተኩርበት ጊዜ ኃጢአተኝነታችንና አዳኝ እንደሚያስፈልገን እንረዳለን። በምናከናውናቸው ተግባራት ድነትን (ደኅንነትን) ልናገኝ እንደማንችል እንገነዘባለን። እግዚአብሔር በቃሉ ውስጥ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ በመመሥረት ወደ ክርስቶስና ወደ ማዳኑ እንመለሳለን።

ነገር ግን ድነት (ደኅንነት) ክርስቶስን በማመንና በመልካም ሥራ አማካኝነት እንደሚገኝ ካመንን ትኩረታችን በሥራችን ላይ ይሆናል። ለምሳሌ፥ «ለመዳን በክርስቶስ ማመን አለብህ። እንዲሁም ቢራ መጠጣትህንና ጫት መቃምህን ልታቆምና ሁለተኛ ሚስትህን ልትፈታ ይገባል» በምንልበት ጊዜ የምንመሰክርላቸው ሰዎች አጽንኦት የሚሰጡት ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት በሚያሟሏቸው ቅድመ-ሁኔታዎች ወይም ሥራዎች እንጂ በክርስቶስ ላይ አይሆንም። ስለሆነም በወንጌሉ ላይ ሌላ ነገር ጨምረናል ማለት ነው። አዳዲስ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ይቀበላቸው ዘንድ በተወሰነ መንገድ እንዲለብሱ በምንናገርበት ጊዜ በክርስቶስ ከማመን ይልቅ በተግባሮቻችን ላይ ወደ ማመኑ ተመልሰናል ማለት ነው። ሰዎች ከልባቸው፥ የክርስቶስ ሞት ጠቃሚ ቢሆንም በቂ አይደለም፤ በትጋት እንደምከተለው ለማሳየትና ያድነኝ ዘንድ ድጋፉን ለማግኘት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ አንድ ተግባር መፈጸም አለብኝ እንዲሉ እንገፋፋቸዋለን። ዓይኖቻችን ወደ ራሳችን ይመለሱና በክርስቶስ ላይ ማተኮራችን ይቀራል። ጳውሎስ ይህ አመለካከት ወንጌሉን እንደበረዘ ገልጾአል። ይህ የገላትያ ሰዎች ስውር የእምነት ለውጥ አንድ ጠንቋይ የደገመባቸው ይመስል ነበር። ስለሆነም ጳውሎስ ድነት (ደኅንነት) የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን በመጠበቅ ሳይሆን በክርስቶስ ላይ በሚጣል እምነት መሆኑን ለማብራራት የተለያዩ ማረጋገጫዎችን ይሰጣል።

ድነት (ደኅንነት) በእምነት እንደሚገኝ የሚያስረዳ የገላትያ ክርስቲያኖች የሕይወት ገጠመኝ ማረጋገጫ (ገላ. 3፡1-5)

ሀ. የገላትያ ክርስቲያኖች ድነትን ባገኙ ጊዜ የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት ሳይጠብቁ ነፃ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ተቀብለዋል። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር እነርሱን ለመቀበልና ለማዳን የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን እንዲጠብቁ እንዳልጠየቃቸው ግልጽ ነበር። ሕግጋትን ጠብቆ እግዚአብሔርን ለማስደሰት አሁን ከእምነት መመለሱ እግዚአብሔር ካዳናቸው መንገድ የሚቃረን ተግባር ነበር።

ለ. የገላትያ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ተአምራት የተለማመዱት በእግዚአብሔር ባመኑ ጊዜ እንጂ ሕግጋትን በጠበቁ ጊዜ አልነበረም። ስለሆነም፥ እነዚህ ተአምራት ሕግጋትን ሳይጠብቁ እግዚአብሔር እንደተቀበላቸው ያሳያሉ።

ሐ. ሕግጋትን ከመጠበቃቸው በፊት እውነተኛ ክርስቲያኖች ካልነበሩ፥ በክርስቶስ በማመናቸው ምክንያት የተቀበሏቸው ስደቶች ሁሉ ከንቱ ይሆናሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዘፍጥ. 15፡1-6 እንብብ። እግዚአብሔር ለአብርሃም ምን ምን የተስፋ ቃሎችን ሰጠው? እግዚአብሔር ያከበረውና እንደ ጽድቅ የቆጠረው የአብርሃም ምላሽ ምን ነበር? አብርሃም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሆኖ ለመታየት የሚያከናውናቸው የተግባር ዝርዝርች ነበሩ? ለ) ዘፍጥ. 12፡1-3 አንብብ። እግዚአብሔር ለአብርሃም ምን ምን የተስፋ ቃሉችን ሰጠ? ከእነዚህ የተስፋ ቃሎች ዛሬ አሕዛብ የሆንነውን ሰዎች የሚመለከቱት የትኞቹ ናቸው?

ድነት (ደኅንነት) በእምነት እንደሚገኝ የሚያስረዳ የብሉይ ኪዳን ማረጋገጫ (ገላ. 3፡6-4፡31)

ሀ. መጽሐፍ ቅዱስ የአይሁዶች አባት የሆነው አብርሃም እግዚአብሔርን በማመኑ እንደ ጸደቀ ወይም ተቀባይነትን እንዳገኘ ይናገራል (ገላ. 3፡6-9)። ይህ የሆነው ሕግ ከመሰጠቱና ከሙሴ በፊት ነበር። እግዚአብሔር አብርሃም ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት ሕግጋትን እንዲጠብቅ አልጠየቀውም።

ጳውሎስ የአብርሃምን ምሳሌነት በመጠቀም ሁለት ጠቃሚ ትምህርቶችን አስተላልፎአል። በመጀመሪያ፥ አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ጽድቅ የሚለውን ትክክለኛ ግንኙነት የመሠረተው ለእግዚአብሔር አንድን ነገር በማድረግ ወይም የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት በመጠበቁ አልነበረም። ነገር ግን እግዚአብሔር የተስፋ ቃል ሰጠው። አብርሃም ያንን የተስፋ ቃል በማመኑ እግዚአብሔር እንደ ጽድቅ ቆጠረለት። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ በአዲስ ኪዳን የተስፋ ቃሎች ላይ ተመሥረተን በክርስቶስ በምናምንበት ጊዜ የክርስቶስን ጽድቅ ተቀብለን ድነትን (ደኅንነትን) እናገኛለን። እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው መልካምን ሥራ ሳይሆን በእምነት ምላሽ እንድንሰጥ ነው።

ሁለተኛ፥ ጳውሎስ የአሕዛብ ክርስቲያኖች በሥጋ ከአይሁድ እንደ ተወለዱ ሰዎች ሁሉ የአብርሃም ልጆች መሆናቸውን ለማስተማር ይፈልጋል። ለዚህም ምክንያቱ አብርሃም ከመገረዙ ወይም አይሁዳዊ ከመሆኑና በእግዚአብሔር ከመጠራቱ በፊት አሕዛብን ጨምሮ የሰው ልጆች በሙሉ በአብርሃም በኩል እንደሚባረኩ ቃል መግባቱ ነው። ስለሆነም፥ በክርስቶስ የሚያምኑ አሕዛብ የእግዚአብሔር በረከት ተቀባዮች ሲሆኑ፥ በክርስቶስ እንደሚያምኑ አይሁዶች ሁሉ የአብርሃም ልጆች ናቸው።

ለ. ብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔርን ሕግጋት በሙሉ የማይጠብቅ ሰው የተረገመ ነው ይላል (ገላ. 3፡10-14፤ በተጨማሪም ዘዳግ. 27፡26ን አንብብ)። የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን ሁሉ ሙሉ በሙሉ ሊጠብቁ እንደማይችሉ አይሁዶች ራሳቸው ያምናሉ። ማንም ሰው የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን ሙሉ በሙሉ መጠበቅ ስለማይችል ማንም ሰው ሕግጋትን በመጠበቅ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኝ አይችልም። ይልቁንም «የተረገሙ» በመሆናቸው ሌላ የድነት (ደኅንነት) መንገድ ያስፈልጋቸዋል። ይህ የድነት (ደኅንነት) መንገድ ደግሞ አንዱን በሌላ በመተካት የሚፈጸም ነው። (በብሉይ ኪዳን የይቅርታው መንገድ ለኃጢአተኛ ሰው ሕይወት የእንስሳት መሥዋዕት በመተካት ነበር።) ኃጢአት የሌለው ክርስቶስ በመስቀል ላይ በእኛ ምትክ ሲሞት፥ ኃጢአታችንን ተሸክሞ «ተረግሟል»። የክርስቶስ መረገም በእንጨት ላይ የሚሞት ሰው ሁሉ እርጉም ነው ከሚለው የብሉይ ኪዳን ቃል ጋር የሚታይ ነው። በእንጨት ላይ መሞቱ ሌላ የድነት (ደኅንነት) መንገድ ከፍቷል። ይህ አዲሱ መንገድ በመስቀል ላይ የተፈጸመ ሥራውን በማመን የሚገኝ ነው። በዚህ መሠረት እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባለት የተስፋ ቃሎች በክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀል ሞት የእኛው ይሆናሉ። እግዚአብሔር ለሁሉም ክርስቲያን የሚሰጠው መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የዚህን የተስፋ ቃል ፍጻሜ ያሳያል። በዚህ እምነት ላይ አንዳች ተግባር መጨመር የክርስቶስን ሞት ትርጉም-አልባ ያደርገዋል። እግዚአብሔርን ለማስደሰት ሕግጋትን መጠበቅ የእምነት መንገድ ወይም እግዚአብሔርን ለድነት የማመን ተቃራኒ ነው። ማንም ሰው ለድነት (ደኅንነት) በክርስቶስ እያመነ በተመሳሳይ ጊዜ ለደኅንነቱ ሊሠራ አይችልም። የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት ሙሉ በሙሉ ለመጠበቅ የቻለ አንድም ሰው ስለሌላ፥ ለድነት (ደኅንነት) ሕግጋትን መጠበቁ መረገም ነው።

ሐ. ጳውሎስ በእምነት የመዳንን መንገድ ከቃል ኪዳን ወይም ከኑዛዜ ጋር በማነጻጸር ያብራራል (ገላ. 3፡15-18) ምናልባትም ጳውሎስ አንድ አባት ለልጆቹ ሀብቱን ስለሚከፋፍልበት ሕጋዊ ኑዛዜ እያሰበ ይሆናል። አንድ ሰው ከመሞቱ በፊት ኑዛዜውን በፈለገ ጊዜ ሊለውጥ ይችላል። ከሞተ በኋላ ግን የመጨረሻ ኑዛዜው የጸና ይሆናል። ከዚያ በኋላ ማንም ሰው ኑዛዜውን አሻሽሎ ሊጽፍ አይችልም። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ አብርሃም ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር እንደገና በመደራደር የቃል ኪዳኑን ወይም የኑዛዜውን ቅድመ-ሁኔታዎች ሊለውጥ አይችልም። ስለሆነም፥ አብርሃም ከሞተ ከ430 ዓመታት በኋላ የተሰጠው ሕግ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር የገባውን በእምነት የመዳን የተስፋ ቃል ሊለውጠው አይችልም። እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባው የበረከት ተስፋ ቃል የአብርሃም «ዘር» ወደሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ተላልፎአል። እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው የተስፋ ቃል ሙሉ ለሙሉ የሚፈጸመው በሕግ ሳይሆን በክርስቶስ ብቻ ነው።

መ. ጳውሎስ በእግዚአብሔር ዕቅዶች የሕግ ዓላማ ምን እንደነበረ ያብራራል (ገላ. 3፡19-25)

ጳውሎስ ቀደም ሲል ስለ ሕግ ያቀረባቸው አስተያየቶች በአይሁዶች ዘንድ ብዙ ጥያቄዎችን አስነሥቷል። «በእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች ማመን በቂ ከነበረ እግዚአብሔር ለምን ሕግን ሰጠ? ሕግ ጥቅም አልነበረውም ማለት ነው? ወይስ ሕጉ የእግዚአብሔር የእምነት መንገድ ተቃራኒ ነበር? ጳውሎስ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የሕግን ጠቀሜታና እግዚአብሔር ሕግን የሰጠበትን ዓላማ አብራርቷል።

በመጀመሪያ፥ ሕጉ እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው የተስፋ ቃል ፍጻሜ የሆነው «ዘር» ወይም ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ ለሰው ልጆች የተሰጠ ጊዜያዊ ስጦታ ነበር (ገላ. 3፡19-20)። የተሰጠውም ከሰዎች መተላለፍ የተነሣ ነበር። ይህ ሐረግ ሁለት ፍችዎችን ሊሰጥ ይችላል። 1) ሕጉ የክፋትን መስፋፋት ለመገደብ እግዚአብሔር የተጠቀመበት መሣሪያ ነበር። ወይም 2) ሕጉ የተሰጠው ለክርስቶስ መምጣት በማዘጋጀት የሰዎችን ልብ ኃጢአተኝነትና ዓመፅ እንዲገልጥ ነበር።

ጳውሎስ ሕጉን ሰዎች የሰብአዊ ተፈጥሯቸውን ክፋት በሙሉ ተግባራዊ እንዳያደርጉ ከሚቆጣጠር የወኅኒ ጠባቂ ጋር ያነጻጽረዋል። እንዲሁም፥ በክርስቶስ በማመን የእግዚአብሔርን ልጅነት ሙሉ መብቶች እስኪጎናጻፉ ድረስ የኃጢአት ተፈጥሯቸው የበለጠ ክፋትን እንዳይፈጽሙ ከምትከላከል የልጆች ሞግዚት ጋር ያመሳስለዋል። የሕግ ጠቀሜታ ክርስቶስ እስኪመጣና በመስቀል ላይ በመሞት የኃጢአትን ቅጣት እስኪከፍልና ሰዎችን ከኃጢአት ተፈጥሮ ቁጥጥር ነፃ እስኪያወጣቸው ድረስ የሚሠራ ጊዜያዊ ነበር። የብሉይ ኪዳን ሕግጋት የእግዚአብሔርን ባሕርይ ለመግለጥ ቢረዱንም በክርስቶስ ካመንን በኋላ የበለጠ ክፋት ከመፈጸም በሞግዚትነት እንዲጠብቁን አንሻም። ብቁ የሚያደርገን መንፈስ ቅዱስ አለን።

ጳውሎስ በዚህ ስፍራ «ኃጢአት»ን ሳይሆን «መተላለፍ»ን የጠቀሰው ሆን ብሎ ነው። መተላለፍ የሚታወቀውን የእግዚአብሔር ትእዛዝ መጣስ ነው፥ ኃጢአት እግዚአብሔር የሰጠውን መመዘኛ ለማሟላት አለመቻል ነው። ይህም የተሳሳተ ተግባር በመፈጸም ወይም እግዚአብሔር የሚፈልገውን መልካም ተግባር ባለመፈጸም የሚገለጥ ነው (ለምሳሌ፥ ችግር የገጠመውን ሰው አለመርዳት)። በሮሜ 4፡15 ጳውሎስ ግልጽ ትእዛዝ እስኪመጣ ድረስ መተላለፍ እንዳልነበረ ገልጾአል። የእግዚአብሔርን ሕግጋት መተላለፋችንንና ከዚህም የተነሣ ኃጢአተኞች መሆናችንን ያወቅነው ሕግ በተሰጠ ጊዜ ነበር። እንዲያውም የእግዚአብሔርን ሕግጋት በምናውቅበት ጊዜ ሕግጋቱ ከኃጢአት ተፈጥሯችን ጋር በመሥራት የበለጠ ኃጢአት እንድንፈጽም ያደርጉናል (ሮሜ 7፡7-18)። ስለሆነም በሲና ተራራ ላይ የተሰጠው ሕግ በጣም ጠቃሚ ዓላማ ነበረው። የሰው ልጅ ምን ያህል ኃጢአተኛና የእግዚአብሔር ጸጋና ይቅርታ የሚያሻው እንደሆነ አሳይቷል።

ሁለተኛ፥ ጳውሎስ፥ «ሕጉ የበለጠ ኃጢአት እንድፈጽም ካደረገኝ ክፉ አይደለምን?» ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል (ገላ. 3፡21-25)። ጳውሎስ ሕጉ መልካም እንደሆነ አበክሮ ይናገራል። አንድ ሰው ሕጉን መቶ በመቶ ለመፈጻም ቢችል ጽድቅን ሊያገኝ ይችል ነበር። ይህ በእርግጥ የማይቻል ነበር። ስለሆነም፥ መልካም የሆነው ሁለተኛው መንገድ ነበር። ይኸውም አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ የኃጢአት ባሕርያቸው እስረኞች በመሆናቸው የእግዚአብሔርን ድነት (ደኅንነት) በመልካም ሥራቸው ሊያገኙ የማይችሉ መሆናቸውን በማሳየት ሕጉ ሌላ የድነት (ደኅንነት) መንገድ እንዲፈልጉ አድርጓቸዋል። በሥራቸው እግዚአብሔርን ለማስደሰት መጣራቸውን አቁመው በእምነት ወደ ክርስቶስ እንዲመለሱና ብቸኛው የድነት ተስፋቸው በመሆን በመስቀል ላይ ያከናወነላቸውን ተግባር እንዲቀበሉ ረድቷቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለአማኞች ደንቦችንና ሕግጋትን ግልጽ ማድረግ በኃጢአት እንዳይወድቁ የሞግዚትነት ተግባር መፈጸምን የሚመስለው እንዴት ነው? ይህ አንዳንድ ጊዜ ጠቃሚ የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) ሰይጣን ይህንን ሁኔታ በመጠቀም ሰዎች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው በተሳሳቱ ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩ የሚያደርገው እንዴት ነው? ሐ) ግልጽ ደንቦችን መስጠትን ያህል ቀላል ባይሆንም፥ ሰዎች ከውጫዊ ተግባራት ይልቅ ለእግዚአብሔርና ለሌሎች ሰዎች ባላቸው ፍቅር ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ የበለጠ ጠቃሚ የሚሆነው እንዴት ነው? መ) ቤተ ክርስቲያንህ ምእመናን ለእግዚአብሔርና ለእርስ በርሳቸው ልባዊ ፍቅር ከማሳየታቸው ይልቅ በውጫዊ ተግባራት ላይ እንዲያተኩሩ የምታደርግ ይመስልሃል? መልስህን አብራራ። እንዲህ ከሆነ፥ ይህን ከውስጣዊ አመለካከቶች ይልቅ በውጫዊ ባሕርይ ላይ የማተኮር ሁኔታ ለመለወጥ ምን ሃሳብ ታቀርባለህ?

ሠ. ጳውሎስ የሕጉ ጊዜያዊ ሞግዚትነት እንዳበቃና በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች «የእግዚአብሔር ልጆች» እንደሆኑ ገልጾአል (ገላ. 3፡26-4፡7)

በገላትያ 3፡24፥ ጳውሎስ ሕጉ አንድ ልጅ አዋቂ እስኪሆን ድረስ የሚንከባከብ አገልጋይ እንደሆነ አስረድቷል። ይህንኑ አሳብ በገላትያ 4፡1-3 ይቀጥላል። ሕጻን ልጅ ወላጆቹ የደነገጉለት ዕድሜ እስኪደርስ ድረስ ሕጋዊ መብቶችና ውርስ የመቀበል ዕድል ስለሌለው ብዙም ከባሪያ አይሻልም።

ክርስቶስ መጥቶ ለኃጢአታችን ከሞተና እኛም ለደኅንነታችን በእርሱ ካመንን በኋላ ወደ ሙሉ አዋቂነት ደረጃ በመቀየር የእግዚአብሔርን በረከቶች ወርሰን ደስ እንሰኛለን። «ክርስቶስን ለብሰናል»፥ ይህም ክርስቶስ የሚያመጣቸውን የድነትና የአዲስ ባሕርይ በረከቶች እንዳገኘን ያመለክታል። ከዚህም የተነሣ አሁን እንደ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን ደስ እንሰኛለን። አይሁዶች ወይም አሕዛብ፥ ወንዶች ወይም ሴቶች፥ ባሪያዎች ወይም ነፃ ሰዎች ይህንን ይቅርታ ሊያገኙ የሚችሉት በክርስቶስ በማመን ስለሆነ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ የጎላ፥ የምጣኔ ሀብት ወይም የፆታ ልዩነት የለም። ሁሉም በእኩል ደረጃ የእግዚአብሔር ልጆች ሲሆኑ፥ ሁሉም የበሰሉና በእኩል ደረጃ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃሎች የሚቀበሉ ይሆናሉ።

እንደ እግዚአብሔር ልጆች ከምንቀበላቸው ውርሶች አንደኛው መንፈስ ቅዱስ ነው። ይህ መንፈስ ቅዱስ በልባችን ውስጥ በማደር የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ይመሰክራል። ከእግዚአብሔር አብ ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዲኖረን ስለሚያደርግ፥ እግዚአብሔርን «አባ አባት» ብለን ልንጠራው እንችላለን። «አባ» የሚለው ቃል ልጆች አባታቸውን የሚጠሩበት የጥልቅ ፍቅርና ኅብረት ምልክት ነው።

ረ. ጳውሎስ ልጆች እንደ ባሪያዎች ሊኖሩ እንደማይችሉ ይገልጻል (ገላ. 4፡8-20)

የአሕዛብ ክርስቲያኖች በክርስቶስ በማመን የእግዚአብሔር ልጆች ከመሆናቸው በፊት የሐሰተኛ ጣዖታት ባሪያዎች ነበሩ። ይህም አይሁዶች የሕግ አጥባቂ ሃይማኖት ባሪያዎች እንደነበሩ ዓይነት ነው። ባመኑ ጊዜ ግን ነፃ ወጥተው የእግዚአብሔር ቤተሰብና ወራሾች ሆነዋል። ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ መመለስና የተወሰኑ በዓላትንና ሌሎች የአይሁድ የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን («ደካማ ሕጎችን») በመጠበቅ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት መሞከር ወደ ባርነት መመለስ ነበር።

ጳውሎስ የገላትያ ክርስቲያኖች መጀመሪያ ወንጌሉን በመሰከረላቸው ጊዜ እንዴት እንደ ወደዱት እንዲያስታውሱ ይለምናቸዋል። በዚያን ጊዜ ጳውሎስ ታሞ የነበረ ቢሆንም፥ የገላትያ ክርስቲያኖች ግን ይህ ሳይገድበው ወንጌሉን ስላመጣላቸው ይወዱትና ይሰሙት የነበረ ይመስላል። አንዳንድ ምሁራን “ዓይኖቻችሁን ለማውጣት ፈቃደኞች ነበራችሁ” የሚለውን አሳብ በመጠቀም ጳውሎስ የዓይን ሕመም እንደነበረበት ይናገራሉ። ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች የነበረውን ጥልቅ ፍቅር በመግለጽ፥ የወንጌሉን እውነቶች ለማካፈልና የአመለካከታቸውን ለውጥ ለማየት እንደሚመኝ ያስረዳል።

ሰ. ጳውሎስ የአጋርንና የሣራን የብሉይ ኪዳን ታሪኮች በመጠቀም ስለ ሕግና ጸጋ ያብራራል (ገላ. 4፡21-31)

ጳውሎስ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ለማስደሰት የሕግን መንገድ እንደማይከተሉና የአብርሃምን አርአያነት እንደሚከተሉ በመግለጽ ክርክሩን ይቋጫል። ጳውሎስ ለዚህ ማብራሪያ የአይሁዶችን አተረጓጎም በመከተል የአጋርንና የእስማኤልን ባርነትና የሣራንና ይስሐቅን የተስፋ ቃል ልጅነት ያስረዳል። ጳውሎስ በዚህ ክፍል ውስጥ ያደረገውን ንጽጽር አጢን።

– አጋር፥ የሴት ባሪያ – ሣራ፥ ነፃ

– እስማኤል በተፈጥሯዊ መንገድ የተወለደ – ይስሐቅ በልዕለ ተፈጥሯዊ መንገድ ተወለደ

– አሮጌው ቃል ኪዳን – አዲሱ ቃል ኪዳን

– ምድራዊት ኢየሩሳሌም – ሰማያዊት ኢየሩሳሌም

– ይሁዳ – ክርስትና

አብርሃም ሁለት ዋነኛ ልጆችን ወልዷል። የመጀመሪያው እስማኤል የተወለደው ከባሪያይቱ አጋር ነበር፡፡ እስማኤል በአብርሃምና በአጋር መካከል በተደረገው ተፈጥሯዊ ግንኙነት የተወለደ በመሆኑ ልደቱ ተአምራዊ አልነበረም። አጋር ባሪያ ስለነበረች ከእርሷ የተወለደው እስማኤልም ባሪያ ነበር። አጋርና ልጁ ከአብርሃም ከተለዩ በኋላ ሕጉ በተሰጠበት በሲና ተራራ አካባቢ ኖረዋል። ሕጉ አሮጌ ኪዳን በመሆኑ እንደ አጋርና እስማኤል አይሁዶችን በባርነት ገዝቷል። ሕጉ ሰዎችን በባርነት የሚገዛውና በሥራ ላይ ያተኮረ የይሁዳ ሃይማኖት እንደሚገኝበት የኢየሩሳሌም ከተማ ነበር። ጳውሎስ አጋርና እስማኤል ሰዎች ሕግጋትን በመጠበቅ ለመዳን ያደረጉትን ጥረት እንደሚያሳዩ ገልጾአል። በሲና ተራራ የተሰጠውን የብሉይ ኪዳን ሕግ ይወክላሉ። እንዲሁም የእግዚአብሔርን ድነት (ደኅንነት) ለማግኘት ጥረት የሚደረግበትን ምድራዊ የሆነውን የአይሁዶች የአምልኮ ሥርዓት ያመለክታሉ።

ሁለተኛው ልጅ የሆነው ይስሐቅ እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለሣራ በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት የተወለደ የተአምር ልጅ ነበር። ይስሐቅ ነፃና የአብርሃም ወራሽ ነበር። እንዲሁም አብርሃም የይስሐቅን መወለድ በእምነት እንደ ተቀበለ ሁሉ፥ አንድ ሰው ድነትን (ደኅንነትን) በእምነት የሚቀበልበት የአዲሱ ኪዳን ተምሳሌት ነበር። ይስሐቅ የሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ተምሳሌት ነው። ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም እግዚአብሔር በክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉ ተስፋ የሰጣት ስፍራ ነች።

ጳውሎስ በእነዚህ ሁለት ታሪኮች መካከል ክርስቶስን በእምነት በመቀበልና ሕግጋትን ለመጠበቅ በመሞከር መካከል ያሉትን ምስስሎች ተመልክቷል። ወደ ኋላ ተመልሶ ሕግን መከተል አብርሃም ከባሪያይቱ የወለደውን እስማኤልን እንደ መሆን ነበር። ይህ የበረከት ሳይሆን የባርነት ስፍራ ነበር። በክርስቶስ ማመን ቀን የነጻነት፥ የተስፋ፥ የተአምራዊ ልደትና የመንግሥተ ሰማይ ወራሽነት መንገድ ነበር። በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች የሣራ ልጆች ሲሆኑ፥ እንደ ይስሐቅ በተአምር የተወለዱ የድነትና የመንግሥተ ሰማይ የተስፋ ቃሎች ወራሾች ናቸው።

ለመሆኑ በተፈጥሯዊ መንገድ የተወለደው እስማኤል በልዕለ ተፈጥሯዊ መንገድ የተወለደውን ይስሐቅን ያስተናገደው እንዴት ነበር? እስማኤል ይስሐቅን የማሳደድና የመሳለቅ ተግባር ፈጽሞበታል። በተመሳሳይ ሁኔታ የሕግ ወይም የዓለማዊ ሥርዓቶች ባሪያ የሆኑት ሰዎች የገላትያን ክርስቲያኖች ያሳድዱ ነበር። የገላትያ ክርስቲያኖች አሮጌውን የሕግ ሥርዓት እንዲከተሉ የሚገፋፉአቸውን ሰዎች ምን ማድረግ ያስፈልጋቸው ነበር? አብርሃም እስማኤልን እንዳባረረው ሁሉ፥ እነርሱም እነዚህን ሰዎች ከክርስቲያኖች ኅብረት ማባረር ያስፈልጋቸው ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች የእግዚእብሔርን ሞገስ፥ ይቅርታና ድነት (ደኅንነት) ለማግኘት የሚሞክሩባቸውን አንዳንድ መንገዶች ግለጽ። ለ) ይህ ባርነት የሚሆነው እንዴት ነው? ሐ) ፍርድ የሚገባቸው ኃጢአተኞች መሆናቸውን ተገንዝበው ወደ ክርስቶስ በሚመለሱና አንድን ተግባር በመፈጸም የእግዚአብሔርን ተቀባይነት ለማግኘት በሚሞክሩ ሰዎች መካከል ያለው የአመለካከት ልዩነት ምንድን ነው? መ) ይህ የነጻነት መንገድ የሚሆነው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: