የቆላስይስ መልእክት በማን ተጻፈ፣ ለማን ተጻፈ፣ የተጻፈበት ዘመንና ቦታ

፩. የቆላስይስ መልእክት ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፡- ቆላ. 1፡1-2 አንብብ። ሀ) ጸሐፊው ማን ነው? ለ) ጸሐፊው ራሱን የሚገልጸው እንዴት ነው? ይህ ከፊልጵ. 1፡1 የሚለየው እንዴት ነው? ሐ) መልእክቱን የጻፈው ለማን ነው?

የውይይት ጥያቄ፡- ስለ ቆላስይስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ስለ መጽሐፉ ጸሐፊ፥ ስለ ከተማይቱ፥ ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱና ስለ መጽሐፉ የተሰጠውን ትምህርት ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።

ጳውሎስ የጻፈው ሦስተኛው «የእሥር ቤት መልእክት» የቆላስይስ መልእክት ነው። ጳውሎስ በዚህ መልእክት ውስጥ ስለ ራሱ ልማዳዊ ገለጻ አድርጓል። ለቆላስይስ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ሊሆን መብቃቱን ያስረዳል። የቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን ከጳውሎስ ጋር የቅርብ ግንኙነት ካላቸውና የጳውሎስን የሐዋርያነት ሥልጣን ከማይጠራጠሩ የፊልጵስዩስ አማኞች የተለየች ነበረች። ጳውሎስ ጎብኝቶ በማያውቃት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰርጎ በመግባት ላይ ያለውን የሐሰት ትምህርት ለመከላከል በመጣር ላይ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ስለ ሐሰት ትምህርቱ ለማስተማርና እውነትን ከሐሰት ለይቶ ለማሳየት እግዚአብሔር በሰጠው የሐዋርያነት ሥልጣኑ ላይ አጽንኦት አደረገ።

ጢሞቴዎስ አብሮት ስለነበረ ጳውሎስ የእርሱንም ስም ጠቅሷል። የመልእክቱ ጸሐፊ ግን ጳውሎስ እንጂ ጢሞቴዎስ አይደለም። አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ የጢሞቴዎስን ስም የጠቀሰው በዚያች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሆነ ወቅት ስላገለገለ ሊሆን ይችላል ይላሉ።

፪. መልእክቱ ለማን ተጻፈ?

ጳውሎስ በቆላስይስ ለሚገኙ ቅዱሳንና የታመኑ አማኞች እንደ ጻፈ ገልጾአል። ይህም መልእክቱ ሰቆላስይስ ከተማ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች እንደ ተጻፈ ያስረዳል።

የቆላስይስ ከተማ ከኤፌሶን በስተምሥራቅ 50 ኪሎ ሜትሮች ያህል ርቃ በእስያ ውስጥ ከሚያልፉ ዐበይት ጎዳናዎች በአንደኛው ላይ ትገኝ ነበር። (ከመጽሐፉ መጨረሻ ላይ ያለውን ካርታውን ተመልከት።) ቆላስይስ በፍርጊያ ግዛት ውስጥ እጅግ ከታወቁ ከተሞች አንዷ እንደነበረች ቢታወቅም፥ ጳውሎስ በኤፌሶን ውስጥ በሚሠራበት ወቅት ትንሽ ከተማ ነበረች። መጠኗ የቀነሰው በአካባቢዋ በስፋት ከሚከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ ሊሆን ይችላል። ከቆላስይስ በስተሰሜን ሰፊዋ የሎዶቅያ ከተማ ነበረች።

የቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደ ተመሠረተች አይታወቅም። ምናልባትም ይህ የሆነው ጳውሎስ ለሦስት ዓመታት ኤፌሶን ውስጥ ባገለገለበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም። በዚህ ጊዜ በእስያ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ ወንጌልን መስማታቸው ተገልጾአል (የሐዋ. 19፡10)። ጳውሎስ የቆላስይስንም ሆነ የሎዶቅያን ቤተ ክርስቲያን እንዳልጎበኘ ይናገራል (ቆላ. 2፡1)። ነገር ግን እነዚህ አብያተ ክርስቲያን የጳውሎስ አገልግሎት ተዘዋዋሪ ውጤቶች ነበሩ። ምናልባትም የቆላስይስ ሰዎች ለንግድ ወደ ኤፌሶን በመጡ ጊዜ የጳውሎስን ስብከት ሰምተው በክርስቶስ አምነው ይሆናል። ወደ አገራቸው ተመልሰው ለሌሎች በመመስከር ቤተ ክርስቲያን ሊመሠርቱ ችለው ይሆናል። ወይም ጳውሎስ ኤጳፍራ ወንጌሉን እንዳመጣላቸው ስለሚናገር (ቆላ. 1፡7)፤ ጳውሎስ ኤፌሶን ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሠርት ልኮት ይሆናል። ሌላው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ወደ ቆላስይስ ከተማ እንደ ላከውና እርሱም ኤጳፍራን ወደ ክርስቶስ እንደ መራው የሚያስረዳ ነው። ጳውሎስ የጢሞቴዎስን ስም ከመግቢያው ላይ የጠቀሰው በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ጳውሎስ በአካል ወደዚያ ባይሄድም፥ በቆላስይስ የሚኖሩትን ቁልፍ ክርስቲያኖች ያውቅ ነበር። ከመልእክቱ መጨረሻ ላይ ለተወሰኑ የቤተ ክርስቲያን አባላት ሰላምታ ያቀርባል (ቆላ. 4፡14-17)። ምናልባትም በኤፌሶን ውስጥ በነበረው እገልግሎቱ ሳቢያ ድነት (ደኅንነትን) በማግኘታቸው የቆላስይስና የሎዶቅያ አማኞች ጳውሎስን እንደ መንፈሳዊ አባታቸው ሳይመለከቱት አልቀሩም። ጳውሎስ አማኞቹ ያልተገረዙ መሆናቸውን ስለሚናገር (ቆላ. 2፡13)። አብዛኞቹ የቆላስይስ ምእመናን አሕዛብ ሳይሆኑ አይቀሩም።

፫. ቆላስይስ የተጻፈበት ዘመንና ቦታ

በቆላስይስና ኤፌሶን መካከል ካለው ተመሳሳይነት የተነሣ፥ ሁለቱም መልእክቶች በተመሳሳይ ጊዜ የተጻፉ መሆናቸውን መናገር ይቻላል። ጳውሎስ ይህን መልእክት በጻፈ ጊዜ በሮምና ቂሣርያ ወይም ኤፌሶን መታሠሩ ምሁራኑን ቢያከራክራቸውም፥ ትክክለኛ የሚመስለው ሮም ነበረ የሚለው ነው። (መልእክቱ ስለተጻፈበት ስፍራ በኤፌሶን ወይም በፊልጵስዩስ ውስጥ ከተሰጠው ማብራሪያ አንብብ።) የተጻፈበት ዘመን ምናልባትም ከ60-61 ዓ.ም. ይሆናል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: