ጳውሎስ አማኞች የክርስቶስን ምጽአት በሚጠባበቁበት ጊዜ ትጉሕ ሠራተኞች ሆነው ሊመላለሱ እንደሚገባ ያስተምራል (2ኛ ተሰ. 3:1-18)

ጳውሎስ ይህን አጭር የሁለተኛ ተሰሎንቄ መልእክት የሚያጠቃልለው የተሰሎንቄ አማኞች አንዳንድ ነገሮችን እንዲፈጽሙ በመጠየቅ ነው። እነዚህም ነገሮች ክርስቲያኖች የክርስቶስን ምጽአት በሚጠባበቁበት ጊዜ ስሙን በሚያስከብር መንገድ እንዲኖሩ የሚያግዙአቸው ናቸው።

1) አማኞች ጳውሎስ ወንጌልን በስፋት እንዲያሰራጭ በጸሎት ሊደግፉት ይገባ ነበር። ክፉ ሰዎች በተለይም የሐሰት አስተማሪዎች የወንጌሉን ዘር እንዳያጠፉ መጸለይ ይገባቸው ነበር። ጳውሎስ እግዚአብሔር የተሰሎንቄን አማኞች ከእነዚህ ክፉ ሰዎችና ከሐሰተኛ ትምህርታቸው እንደሚጠብቃቸው እርግጠኛ መሆኑን ይናገራል። እኛም በአገራችንና በዓለም ሁሉ ወንጌሉ በስፋት እንዲሰራጭ በዋናነት ልንጸልይ ይገባል።

2) ጳውሎስ ክርስቲያኖች ሥራ በመፍታታቸው በጽኑ እያስጠነቀቀ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ያሳስባቸዋል። የተሰሎንቄ አማኞች የእርሱን ምሳሌነት በመከተል ተግተው እንዲሠሩ ይመክራቸዋል። ቤተ ክርስቲያን ሊሠሩ በማይፈቅዱት ሰዎች ላይ ቅጣት እንድትጥልና ማንኛውም አማኝ ከእነርሱ ጋር ኅብረት እንዳያደርግ አዟል። ክርስቶስ መቼ እንደሚመለስ በትክክል ስለማናውቅ ተግተን እየሠራን፥ ስለ ወደፊቱ እያቀድን፥ ልጆቻችንን እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እያሳደግን፥ ወዘተ… ጤናማ ሕይወት መኖራችንን መቀጠል ይኖርብናል። እንዲሁም እግዚአብሔርን የሚያስከብር የተቀደሰ ሕይወት መኖር ይገባናል። በዚህ ዓይነት የምንመላለስ ከሆነ ክርስቶስ ዛሬ፥ ነገ፥ ከአምስት ዓመታት በኋላ ወይም ከአንድ ሺህ ዓመታት በኋላ ቢመለስ፥ እርሱን በሚያስከብር መንገድ ባለመኖራችን ለኃፍረት አንጋለጥም።

ጳውሎስ ከስደትና የሐሰት ትምህርት ጫና ባሻገር ልባቸውን የሚሞላ የእግዚአብሔር ሰላም እንዲኖራቸው በመመኘት ይህንን መልእክት ያጠናቅቃል። ከዚያም በመልእክቱ ላይ የእርሱ መሆኑን የሚያረጋግጥ ስሙን ይጽፋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ከ2ኛ ተሰሎንቄ መጽሐፍ ጠቃሚ ትምህርቶችን ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: