ጳውሎስ ክርስቶስ የዐመፁ ሰው ሳይገለጽ እንደማይመለስና አማኞች በታማኝነት ሊመላለሱ እንደሚገባ ያስተምራል (2ኛ ተሰ. 2:1-17)

እንደዛሬው ዘመን ሁሉ በተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ መጨረሻው ዘመን ከፍተኛ ግራ የመጋባት ሁኔታ ነበር። ጳውሎስ የሁለተኛ ተሰሎንቄን መልእክት የጻፈበት ዋናው ምክንያት ይህንኑ ግራ መጋባት ለማስተካከል ነበር። በተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ መጨረሻው ዘመን እርስ በርሳቸው የሚጋጩና በአማኞች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን የሚያስከትሉ ሁለት ዓይነት ትምህርቶች የነበሩ ይመስላል። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ በቶሎ ይመጣል ብለው የሚያስቡ ወገኖች ነበሩ። ከዚህም የተነሣ ክርስቲያኖች ሥራ አቁመው ነበር። ሁለተኛ፥ ሌሎች ደግሞ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጣም እንደ ረፈደባቸው ያስተምሩ ነበር። ክርስቶስ ድሮውኑ ዳግም ተመልሶ እንደመጣና እነርሱ ግን ሊያገኙት እንዳልቻሉ ይናገሩ ነበር። እንዲያውም ከጳውሎስ እንደተጻፈ ተደርጎ የቀረበ ክርስቶስ አስቀድሞ መምጣቱን የሚገልጽ ደብዳቤ ደርሷቸው ነበር። እነዚህን ሁሉ ውዝግቦች ለማርገብ ጳውሎስ ስለ መጨረሻው ዘመን ጠቃሚ ትምህርቶችን ይሰጣል። ጳውሎስ ይህንኑ ትምህርት በሚሰጥበት ጊዜ በመጨረሻው ዘመን በሚከሰቱት መልእክቶች ላይ ያተኩራል። በዚህም ክርስቶስ ከዚህ በፊት ዳግም እንዳልተመለሰ ያብራራል። ከእነዚህም ምልክቶች እንዳንዶቹ ምን ምን ነበሩ?

ሀ) ጳውሎስ በመጨረሻው ዘመን ዐመፅ እንደሚበዛ ያስረዳል። እንደውም ጳውሎስ ይህንኑ ዘመን ዐመፅ ይለዋል። ይህም በዓለም ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በእግዚአብሔር ላይ ከፍተኛ ዐመፅ የሚቀሰቀስበት ዘመን መሆኑን ለማስረዳት ነው።

ለ) ይህ የዐመፅ ጊዜ፥ የዐመፅ ሰው ወይም የጥፋት ሰው ተብሎ በሚታወቀው ግለሰብ ይመራል። ይህ ሰው ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት መገለጥ ይኖርበታል። ጳውሎስ የዚህን ሰው ክፉ ባሕርያት በሦስት መንገዶች ያብራራል። በመጀመሪያ፥ በሥርዓት የለሽነት የተሞላ መሆኑን ያስረዳል። ይህ የዐመፅ ሰው የእግዚአብሔርን ሕግጋት ለማፈራረስ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል። ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር ቀድሞውኑ ፍጻሜውን ወስኗል። ይህ ሰው ለአጭር ጊዜ በዓለም ሁሉ ላይ ሥልጣን ሊኖረው ቢችልም፥ እግዚአብሔር ግን በመጨረሻው ያሸንፈውና ወደ ሲኦል ይሰድደዋል (ራእ. 19፡19-20 አንብብ)። ሦስተኛ፥ ይህ ዐመፀኛ ራሱን እንደ አምላክ በመቁጠር ሰዎች እንዲያመልኩት ያስገድዳቸዋል። እግዚአብሔርንም እንዲቃወሙት ያነሣሣቸዋል።

ምሁራን ይህ የዐመፅ ሰው ማን ይሆን በሚለው ጉዳይ ላይ እርስ በርሳቸው ይከራከራሉ። አንዳንዶች ጳውሎስ ክርስቶስ ከመመለሱ በፊት የሚታየውን የመጨረሻው ዘመን አስከፊ ሁኔታ በተምሳሌት እየተናገረ ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ጳውሎስ እንደ ኔሮ ወይም ዶሚቲያን ስላሉት ክፉ የሮም መሪዎች እየተናገረ ነው ይላሉ። እነዚህ ሰዎች ጳውሎስ መልእክቱን ከጻፈ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ በቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ያስከትሉ ነበር። ነገር ግን ጳውሎስ ስለ ሐሳዊ መሢሕ የሚናገር ይመስላል። ይህም በራእይ መጽሐፍ ውስጥ አውሬው የተባለው የመጨረሻ ው የዓለም ገዢ ነው (ራእ. 13)።

ጳውሎስ የዐመፀኝነት ምሥጢራዊ ኃይል ሁልጊዜም ይሠራ እንደነበር ይናገራል። ከእግዚአብሔር ጋር በመጣላት ሕዝቡን የሚያሳድዱ መሪዎች ሁልጊዜም ሲታዩ ኖረዋል። በመጨረሻው ዘመን ግን ልዩ የዐመፅ የታላቅ ክፋትና የስደት ጊዜ ይመጣል። ጳውሎስ የተሰሎንቄ አማኞች ክርስቶስ ሳናውቀው መጥቶ ተመልሷል ብለው እንዳይሠጉ ያሳስባቸዋል። ምክንያቱም ይህ ታላቅ የክፋት ጊዜ ገና አልደረሰምና። የተሰሎንቄ አማኞች ክርስቶስ መቼ እንደሚመጣ ወይም ደግሞ ቀድሞውኑ መጥቶ እንደሆነ እንዴት ልናውቅ እንችላለን ሲሉ ጳውሎስን ጠይቀውታል። ጳውሎስ በዓለም ሁሉ ላይ የሚገዛው ክፉ መሪ አለመገለጹ ክርስቶስ ዳግም እንደ ተመለሰ የሚያውቁበት አንደኛው መንገድ እንደሆነ ያስረዳል።

ሐ) ዐመፃን የሚከለክለው ገና አልተወሰደም። ነገር ግን ይህ ዐመፅን የሚከለክለው ማን ነው? አንዳንድ ምሁራን ይህ ዐመፅን የሚከለክለው እግዚአብሔር የሚቆጣጠረው የሰዎች መንግሥት እንደሆነ ያስባሉ። የሮም መንግሥት በጳውሎስ ዘመን የክፋትን ስርጭት ይቆጣጠር ነበር። የእኛም መንግሥታት በዘመናችን ውስጥ ያሉትን የክፋት ሥራዎች ይቆጣጠራሉ። በመጨረሻው ዘመን ግን ይህ የዐመፅ ሰው መንግሥታትን ሁሉ ስለሚቆጣጠር ማንም ክፋትን የመፈጸም ዓለም አቀፋዊ ኃይሉን ሊቀንስበት እይችልም። ይሁንና ጳውሎስ የሚናገረው ስለ መንፈስ ቅዱስ ይመስላል። እግዚአብሔር ለመንፈስ ቅዱስ በዓለም ውስጥ የሚሰራጨውን የክፋት ኃይል ለመቀነስ እገልግሎት የሰጠው ይመስላል። ስለሆነም ሐሳዊ መሢሕ ሥልጣን ከመያዙ በፊት የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ከዚህ ዓለም ይወሰዳል። ሌሎች ደግሞ ይህንኑ ሁኔታ ከአማኞች መነጠቅ ጋር በማዛመድ ዛሬ በአማኞች ልብ ውስጥ ያለው መንፈስ ቅዱስ ከእነርሱ ጋር እንደሚወሰድ ይናገራሉ። በዚያ የዐመፃ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ የሚሠራው ልክ በብሉይ ኪዳን ዘመን ይሠራ እንደነበረው ይሆናል። ሁሉንም የእግዚአብሔር ልጆች ከመሙላት ይልቅ በአንዳንድ ሰዎች ላይ ብቻ ይመጣል።

መ) ክርስቶስ በአፉ እስትንፋስ ሐሳዊ መሢሕን በማሸነፍ ኃይሉን ያስወግዳል። (ክርስቶስ ይህን የሚያደርገው በቃሉ ትእዛዝ ይሆናል)። ክርስቶስ ይህን የመጨረሻውን ክፉ የዓለም መሪ በመገለጡ ኃይል በቀላሉ ያሸንፈዋል።

ሠ) ሐሣዊው መሢሕ የሰይጣንን ኃይል በመላበስ ሁሉንም ዓይነት ተአምራት ይፈጽማል። በዚህም አምላክ መሆኑንና ሰዎች ሊያመልኩት እንደሚገባ ያሳምናቸዋል።

ረ) በመጨረሻው ዘመን ወንጌሉን ሊሰሙ ያልፈቀዱ ሰዎች የሐሳዊው መሢሕን ውሸት ያምናሉ። በመሆኑም ከሐሳዊው መሢሕ ጋር አብረው ይጠፋሉ።

በዚህ የዓመፅ ዘመን ክርስቲያኖች በምድር ላይ ይኖሩ ይሆን? ክርስቲያኖች ይህንን የክፋት ዘመን እንደሚጋፈጡና ለክርስቶስ በታማኝነት ጸንተው ሊያልፉ እንደሚገባ የሚናገሩ አያሌ ምሁራን አሉ። ነገር ግን መጀመሪያ ቤተ ክርስቲያን እንደምትነጠቅና በአፋቸው ክርስቲያኖች ነን የሚሉት ብቻ ከዐመፅ ሰው ጋር እንደሚጋፈጡ ያስተምራሉ። እነዚህ የአፍ ክርስቲያኖች ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ሳይነጠቁ የቀሩ ናቸው። ትክክለኛው አመለካከት እንግዲህ የትኛው ነው? ይህን ሁኔታ መወሰኑ አስቸጋሪ ነው። ምንም እንኳን በራእይ 6-19 እንደተገለጸው ይህንን በዚህ የዐመፅ ጊዜ ውስጥ ባንገባ ደስ ቢለንም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ጉዳዩን በግልጽ አያብራራም። ስለሆነም አማኞች በዚህ የመከራ ጊዜ ውስጥ ሊያልፉ ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን ተስፋችንና ትኩረታችን በዚህ የክፋት ዘመን ውስጥ አለመግባት ሳይሆን፥ ለክርስቶስ ታማኝ ሆኖ መጽናት ሊሆን ይገባል። በዚህ ጊዜ ክርስቶስ ከመከራ በፊት ቢወስደን ወይም ደግሞ በዚህ የክፋት ዘመን ውስጥ ሲያሳልፈን፥ ክርስቶስን በማስከበር በዘላለሙ መንግሥት በእርሱ እንሸለማለን።

ጳውሎስ ይህንን ክፍል የሚያጠናቅቀው የተሰሎንቄ አማኛች የክርስቶስን ምጽአት በሚጠባበቁበት ጊዜ እንዴት ሊመላለሱ እንደሚገባ በመምከር ነው። እግዚአብሔር እንደመረጣቸውና ሊቀድሳቸው በውስጣቸው እየሠራ መሆኑን በመገንዘብ ልበ ሙሉነት ሊሰማቸው ይገባ ነበር። እንዲሁም ከጳውሎስ የሰሙትን የወንጌል እውነት ጠብቀው በታማኝነት ሊኖሩ እንደሚገባ ያስረዳል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ ስለ መጨረሻው ዘመን የሚናገረው ትምህርት ክርስቶስ በዚህ ቀን ይመጣል ለሚሉ ሰዎች መልስ እንድንሰጥ የሚረዳን እንዴት ነው? ለ) ክርስቶስ የሚመጣበት ቀን ከመገመት ይልቅ እርሱ በሚመለስበት ጊዜ እንዳናፍር በሕይወታችን ምን ልናደርግ ይገባል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: