የጳውሎስ የማጠቃለያ ማበረታቻ እና የስንብት ሰላምታ (2ኛ ጢሞ. 4፡1-22)

ጳውሎስ ጢሞቴዎስ የእግዚአብሔር ታማኝ አገልጋይ ሆኖ ሊኖር ስለሚችልበት መንገድ የማጠቃለያ ማበረታቻ ይሰጠዋል (2ኛ ጢሞ. 4፡1-5)።

ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን መሪ ተግባር ምን መሆን እንዳለበት ጠቅለል አድርጎ በመግለጽ ለጢሞቴዎስ ያቀረበውን ምክር ይደመድማል። ጢሞቴዎስ እግዚአብሔር ሕይወቱን እየተመለከተ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልገው ነበር። አንድ ቀን ደግሞ በሕያዋንና በሙታን ላይ በሚፈርድ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ይቀርባል። አንድ መሪ ምን ማድረግ እንዳለበት፥ እንዴት መምራት እንዳለበት ወይም የስኬታማ አመራር ምሥጢሮች ምን ምን እንደሆኑ የሚያብራሩ ብዙ ሊቆች አሉ። ምንም እንኳ የእነዚህ ሊቃውንት ምክር ጠቃሚ ቢሆንም፥ ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ እጅግ ጠቃሚ እውነቶችን ዘርዝሯል።

ሀ) መሪ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት። ጊዜው አመቺ ሆኖ ሰዎች ስብከቱን በሚሰሙበት ጊዜ (በጊዜውም) ወይም ጊዜው አስቸጋሪ ሲሆንና ሰዎች ስብከቱን በማይቀበሉበት ጊዜ (አለጊዜውም)፥ ሕዝቡን የማረም፥ የመገሠጽና የማበረታታት ተግባሩን ማከናወን አለበት። ዘለቄታዊ ውጤት የሚያመጣው የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው። ከዘመኑ የአመራር ሊቃውንት የሚመጡ ምክሮች ወይም ፈውሶችና ተአምራት የእግዚአብሔርን ቃል ያህል ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ አይችሉም። የእግዚአብሔርን ቃል ማስተማር አስፈላጊ ከሚሆንባቸው ምክንያቶች አንዱ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት እየቀረበ በሚመጣበት ጊዜ፥ ብዙ ሰዎች እውነትን ለመስማት የማይፈልጉ መሆናቸው ነው። ሰዎች የሚሰሙት የሚፈልጉትን ስብከት ብቻ ይሆናል። እነዚህም ሰባኪዎች ሕዝቡ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉ ሳይሆን ጊዜያዊ ስሜታቸውን በሚኮረኩሩ ነገሮች ላይ ያተኩራሉ።

ለ) መሪ በተለዋዋጭ ጊዜያትና ሁኔታዎች ግር መሰኘት ወይም መፍራት የለበትም። ሁሉንም ተቋቁሞ በርጋታ መመላለስ ይኖርበታል።

ሐ) መሪ እግዚአብሔር እንዲያልፍ በሚጠይቀው መከራ ሁሉ ውስጥ ማለፍ አለበት። የመሪነት ጎዳና ቀላል አይደለም። ከቤተ ክርስቲያንም ሆነ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ችግሮች ይገጥሙታል። ነገር ግን በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ እግዚአብሔር ሁልጊዜም ከልጆቹ ጋር ነው።

መ) መሪ ዓይኖቹን ከእግዚአብሔር በተቀበላቸው ኃላፊነት ላይ ማኖር አለበት። መሪ በቀላሉ ዓላማውን ሊስትና እግዚአብሔር ያልጠራውን አገልግሎት ለማከናወን ሊሯሯጥ ይችላል። ነገር ግን መሪ እግዚአብሔር የሰጠውን ስጦታ ተጠቅሞ ዓላማውን ማከናወኑ ወሳኝ ነው። ጢሞቴዎስ ለጠፉት ወንጌልን እየሰበከና የወንጌላዊነት ተግባሩን እየተወጣ ቤተ ክርስቲያንን የመገንባት ተግባሩን ማከናወን ነበረበት። ጢሞቴዎስ በአንድ ቦታ መቀመጥ የሚገባው መጋቢ ሳይሆን፥ ለጠፉት የመመስከርና የተዳከሙትን አብያተ ክርስቲያናት የማጠንከር ጸጋ የተሰጠው አገልጋይ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር ምን ዓይነት ስጦታዎች ወይም ጥሪ የሰጠህ ይመስልሃል? ለ) ይህንኑ ተግባር እንዴት እያከናወንህ ነው? ሐ) እግዚአብሔር የሰጠህን ስጦታና ጥሪ ትቶ ወደ ሌላ አገልግሎት መግባት የሚያስከትላቸው ፈተናዎች ምን ምንድን ናቸው? መ) ጳውሎስ ከላይ ያቀረባቸው ትእዛዛት እግዚአብሔር ከእያንዳንዱ መሪ ሕይወት የሚፈልገውን አገልግሎት የሚገልጹት እንዴት ነው?

ጳውሎስ እየቀረበ ስላለው ሞቱ በመግለጽ ጢሞቴዎስ ወደ እርሱ እንዲመጣ ይጠይቃል። ለወዳጆቹም ሰላምታ ይልካል (2ኛ ጢሞ. 4፡6-22)።

ጳውሎስ ይህንን ደብዳቤ ያጠቃለለው የቅርብ ጓደኛውና መንፈሳዊ ልጁ ለነበረው ጢሞቴዎስ የሚሞትበት ጊዜ እንደቀረበ በመግለጽ ነው። ቀደም ሲል ከፍርድ ችሎቱ ሲቀርብ ወዳጆቹ ሁሉ ትተውት ራቁ። ፍርዱም በጳውሎስ ላይ እየጠነከረ መጣ። ነገር ግን ጳውሎስ መራር ከመሆን ይልቅ፥ እግዚአብሔር በቅርብ እንደረዳውና ወንጌሉን ለማሰራጨት እንዳስቻለው ገልጾል። ጳውሎስ ለጊዜው ከአንበሳ አፍ ድኖ ነበር። ይህ ተምሳሌታዊ አገላለጽ የሚያመለክተው ጳውሎስ በቅርቡ እንደሚገደል ነው። ምክንያቱም የሮም ዜግነት ያላቸው ሰዎች በአንበሶች ተበልተው እንዲሞቱ አይደረግም ነበር።

አሁን ግን ጳውሎስ የሞትን ፍርድ ወደሚቀበልበት ችሎት እየቀረበ ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ የራሱን ሕይወት ይገመግማል። ጳውሎስ ራሱን የተመለከተው እንደ ሰማዕት ወይም አሳዛኝ ሁኔታ እንደሚደርስበት ሰው አልነበረም። ይልቁንም ራሱን እንደ መጠጥ መሥዋዕት ይቆጥረዋል። በብሉይ ኪዳን ዘመን ከእንስሳት መሥዋዕት ጋር ከመሠዊያው ሥር የሚፈስ የወይን መሥዋዕት ይቀርብ ነበር። ይህም አይሁዶች እግዚአብሔር ለሰጣቸው በረከት ምሥጋና የሚያቀርቡበት መንገድ ነበር (ዘኁል. 15፡1-12፥ 28፡7፥ 24)። ጳውሎስ ሕይወቱ ለሚወደው ክርስቶስ የቀረበ መሥዋዕት መሆኑን ተመለከተ። ክርስቶስ ደግሞ ለሰዎች ሕይወቱን የሰጠ ዋንኛው መሥዋዕት ነበር። ጳውሎስ በሕይወት ቢኖር ኖሮ ሕይወቱ ሕያው መሥዋዕት ይሆን ነበር (ሮሜ 12፡1-2)። ሲሞት ደግሞ ሕይወቱን ለክርስቶስ በፍቅርና በምስጋና መልሶ ያስረክበዋል። እናም የመሥዋዕትነት ሞት ይሞታል። ጳውሎስ ሕይወቱንና መንፈሳዊ ሩጫውን መለስ ብሎ ሲመለከት፥ ለክርስቶስ ታማኝ ሆኖ መልካሙን ሩጫ ስለሮጠ እግዚአብሔርን ያመሰግናል። ጳውሎስ ወደፊት አሻግሮ በሚመለከትበት ጊዜ ክርስቶስ የጽድቅን አክሊል እንደሚሸልመው ያውቅ ነበር። በጥንት ዘመን አትሌቶች በስፖርት አሸናፊ በሚሆኑበት ጊዜ ከወይንና ከአበባ የተሠራ አክሊል በራሳቸው ላይ ይደረግላቸው ነበር። ነገር ግን መንፈሳዊ ሩጫ ለሚሮጡ ሰዎች ጳውሎስ የተሻለ ሽልማት እንደሚሰጣቸው ይናገራል። ይህም የጽድቅ አክሊል ነው። ጳውሎስ በችሎት ፊት ቀርቦ ሞት እንደሚፈረድበት ቢያውቅም፥ ሞቱ ሽንፈት ሳይሆን እግዚአብሔር ወደ መንግሥተ ሰማይ ሊወስደው የተጠቀመበት መንገድ መሆኑን ተረድቷል። ጳውሎስ ከመሞቱ በፊት ጢሞቴዎስና ዮሐንስ ማርቆስ ወደ ሮም መጥተው ከእርሱና ከሉቃስ ጋር እንዲገናኙ ይፈልጋል። ጢሞቴዎስ በርኖሱን ይዞላት እንዲመጣ ጠይቋል። ይህም ከእስር ቤቱ ብርድ ይከላከለው ነበር። በተጨማሪም የብራና መጽሐፉን (ምናልባትም መጽሐፍ ቅዱሱን እንዲያመጣለትም ጠይቆታል።)

ጳውሎስ ስለ አንዳንድ የሥራ ጓደኞቹም ጽፎአል። ከጳውሎስና ጢሞቴዎስ ጋር ሲሠራ የቆየው (ቆላ. 4፡14) ዴማስ ከፍርሃት ወይም ከክፉ እሳብ የተነሣ ጳውሎስን ትቶ ወደ ቤቱ ተመልሷል። ቲቶና ቄርቂስን እንዲሁ ወደ ሌላ ስፍራ ሄደዋል። እነርሱ የሄዱት ምናልባት ለአገልግሎት ይሆናል። ኤርስጦስ ጳውሎስ ወዳለበት ወደ ሮም ሊመጣ አልቻለም። ነገር ግን በቆሮንቶስ ማገልገሉን ቀጠለ። ሌላው የእነጳውሎስ የአገልግሎት ጓደኛ ጥሮፊሞስን ታሞ በሚሊጢን ቀረ።

ጳውሎስ በጢሞቴዎስ በኩል ለአንዳንድ ልዩ ጓደኞቹ ሰላምታ በመላክ ይህንን መልእክት ይፈጽማል። እነዚህም አቂላ፥ ጵርስቅላና የሄኔሲፎሩ ቤተሰቦች ናቸው። እንዲሁም ጳውሎስ ከእርሱ ጋር የነበሩት ጥቂት ክርስቲያኖች ለጢሞቴዎስ ያስተላለፉትን ሰላምታ አቅርቧል።

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) የመጨረሻዎቹ የጳውሎስ ቀናት የምንሞትበት ጊዜ በሚቃረብበት ወቅት ሊኖረን ስለሚገባው አመለካከት መልካም ምሳሌዎች የሚሆኑት እንዴት ነው። ለ) የጳውሎስ የመጨረሻው መልእክት ከሆነው የ2ኛ ጢሞቴዎስ ውስጥ ለመንፈሳዊ ሩጫ መሠረታዊ የሆኑትን ትምህርቶች ዘርዝር። ሐ) ከዚህ መልእክት የተፈተነ አገልጋይ ስለመሆን ምን እንማራለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d