የኢየሱስ ተከታዮች እንደ መሆናችን እንዴት መመላለስ እንዳለብን (ዕብ.13፡1-25)

ጸሐፊው አይሁዳውያን ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን የሚያስከብር ሕይወት ለመኖር ሊያደርጉ የሚገዷቸውን አንዳንድ ነጥቦች በመዘርዘር መልእክቱን ያጠቃልላል። እነዚህ ትምህርቶች ሩጫችንን በሚገባ እንዳንሮጥ የሚከተሉት መሰናክሎች ወይም ኃጢአቶች በመንፈሳዊ ሩጫችን ውስጥ መኖር አለመኖራቸውን ለማረጋገጥ ደግመን ደጋግመን የምንመለከታቸው ነገሮች ናቸው።

ሀ) በክርስቶስ ወንድሞቻችሁና እኅቶቻችሁን ውደዱ።

ለ) ምንም ያህል ስደት ቢበዛም፥ እማኞችን በእንግድነት ለመቀበል ትጉ።

ሐ) በኢየሱስ በማመናቸው ምክንያት የታሰሩትን ወገኖች አትርሷቸው።

መ) የጋብቻ ሕይወታችሁን ጠብቁ። የወሲብ ሕይወታችሁ ንጹሕ ይሁን። እግዚአብሔር ከሚጠላቸው ኃጢአቶች አንዱ ከትዳር ውጭ የሚፈጸም የግብረ ሥጋ ግንኙነት ነው።

ወ) የገንዘብ ፍቅር ሕይወታችሁን እንዳይቆጣጠር ተጠንቀቁ። እግዚአብሔር በሰጣችሁ መርካትን ተማሩ። ሁልጊዜም ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት አትጣሩ። ሁኔታችሁ ምንም ዓይነት ቢሆን፥ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንደሆነና እንደሚረዳችሁ ተገንዘቡ።

ረ) መንፈሳዊ ሕይወታችሁን የመጠበቅ አስቸጋሪ አገልግሎት የሚወጡትን የቤተ ክርስቲያን መሪዎቻችሁን አክብሩ።

ሰ) ራሳችሁን ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ጠብቁ። በውጫዊ ሕጎችና ደንቦች ላይ ትኩረት አትስጡ። ነገር ግን ከኢየሱስ ጋር ያላችሁን ግንኙነት እንደ መሠዊያ ቁጠሩ። ይህም ተምሳሌታዊ ሲሆን፥ የማያምኑ ሰዎች ከእርሱ መንፈሳዊ ምግብ ሊያገኙ አይችሉም ነበር። (ይህ ከኢየሱስ ጋር ኅብረት የማድረጋችን መሠዊያ የብሉይ ኪዳን ካህናት ከእንስሳት መሥዋዕቶች ወስደው ለመብላት ከነበራቸው ዕድል የሚሻል ነው። ዘሌዋ. 7፡28-34)።

ሸ) ለክርስቶስ ስም ስደትና ውርደትን ለመቀበል ፈቃደኞች ሁኑ። በብሉይ ኪዳን ዘመን የኃጢአት መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ ኃጢአት የፈጸሙት ሰዎች በሚሠዋው እንስሳ ላይ እጆቻቸውን ይጭኑ ነበር። እንስሳው ከታረደ በኋላ፥ ሥጋው በመሠዊያው ላይ ይቃጠላል። ቆዳውና የሆድ ዕቃው ግን ከከተማ ውጭ ተወስዶ ይቃጠሳል (ዘሌዋ. 4፡1-12)። የዕብራውያን ጸሐፊ፥ ይህ በኢየሱስ ላይ የተፈጸመውን ሁኔታ የሚያብራራ መሆኑን ይናገራል። ክርስቶስ የተሰቀለው ከኢየሩሳሌም ከተማ ውጭ ነበር። የአይሁድ ክርስቲኖችም ተመሳሳይ ምርጫ ማድረግ ነበረባቸው። ሰዎችን ለማስደሰት ከሌሎች አይሁዶች ጋር ተባብረው አሕዛብ ክርስቲያኖችን ለማሳደድና ስደትን ፈርተው ክርስቶስን ለመተው በመወሰን፥ በከተማይቱ ውስጥ ለመቆየት ይመርጣሉ? ወይስ የመስቀሉን ስደት የሚያስከትልባቸው ቢሆንም እንኳን ከማኅበረሰቡ ወጥተው ከክርስቶስ ጋር ይተባበራሉ? ከከተማይቱ ወጥተው ከክርስቶስ ጋር የሚተባበሩና ስደትን የሚቀበሉ ሰዎች የተሻለች የመንግሥተ ሰማይ ከተማ እንደ ተዘጋጀችላቸው ያውቃሉ።

ቀ) ሁኔታዎች ያሻቸውን ቅርጽ ቢይዙም እግዚአብሔርን ማመስገናችሁን ቀጥሉ። ከእንግዲህ ወዲህ የእንስሳት መሥዋዕቶች አያስፈልጉንም። አሁን ለእግዚአብሔር ከምናቀርባቸው መሥዋዕቶች አንዱ ምስጋና ነው።

በ) ለሌሎች መልካም ማድረጋችሁን ቀጥሉ። እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ሌላኛው መሥዋዕት ይኼ ነውና።

ተ) ከእግዚአብሔር ሥልጣንን ለተቀበሉና በእግዚአብሔር ፊት ለነፍሳችሁ ተጠያቂዎች ለሆኑት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ተገዙ። በዚህም አገልግሎታቸው ከትግል ይልቅ ደስታ እንዲሆን አድርጉ። ይህም የኋላ ኋላ እናንተኑ ይጠቅማችኋል። ምክንያቱም ደስ በሚሰኙበት ጊዜ የተሻለ አገልግሎት ሊሰጧችሁ ይችላሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህን በሕይወታችን ውስጥ ልንለማመዳቸው የሚገቡንን ነገሮችን ከልስ። እነዚህ ነገሮች ጠቃሚ የሆኑት ለምንድን ነው? በዚህ ክፍል ውስጥ ከተሰጡት ትእዛዛት አንጻር ሕይወትህን ገምግም። ጸሐፊው በዚህ ክፍል ውስጥ ከቀረበው ትምህርት ጋር የሚዛመድ ሕይወት ትመራ ዘንድ በሕይወትህ ውስጥ ሊለወጥ የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

ማጠቃለያ (ዕብ. 13፡18-25)

ጸሐፊው አንባቢያኑ በጸሎት እንዲያግዙት በመጸለይ መልእክቱን ይደመድማል። በቅርቡ ከጢሞቴዎስ ጋር መጥቶ እንደሚጎበኛቸው ይነግራቸዋል። ከኢጣሊያ የሆኑት ወደሚያቀርቡትም ሰላምታ ያልፋል፡፡

ጸሐፊው ለእነዚህ አይሁዳውያን አማኞችና ለእኛ በሚሰጠው ቡራኬ ትምህርቱን ያጠቃልላል። ሀ) የሰላም ምንጭና ኢየሱስን ከሞት ያስነሣው እግዚአብሔር አብና ለ) የእግዚአብሔር በጎች እረኛ የሆነው ስለ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኘውን ሕይወት እንድንኖር በውስጣችን እንዲሠሩና እርሱን ለማገልገል ብቁዎች እንድንሆን እንዲያስችሉን ይጠይቃል።

የውይይት ጥያቄ፡- ዕብ. 13፡20-21 አንብብ። እግዚአብሔር ለራስህ ሳይሆን ለራሱ ክብር በሕይወትህ ውስጥ እንዲሠራ ጠይቀው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

3 thoughts on “የኢየሱስ ተከታዮች እንደ መሆናችን እንዴት መመላለስ እንዳለብን (ዕብ.13፡1-25)”

 1. እንዴት ነህ ወንድሜ አንድ ትያቄ ልጠይቅህ ስላልገባኝ ነው ፡፡ ለምንድን ነው እምነት ሲኖረንና ስንታዘዝ እነዚ ሁሉ
  የሚሆኑብን ታዲያ እግዚይብሄር ከእኛ ጋር መሆኑስ በምን ይታወቃል፡፡

  7 እምነትና ታዛዥነት በእግዚአብሔር ልጆች ላይ ሊያስከትላቸው የሚችላቸውን ሁሉ ይምረጡ፡፡ *

  0/1

  ከስቃይና ጉዳት ነጻ የሆነ የእረፍት ሕይወት

  ሥቃይ

  የጓደኞችና ጎረቤቶች መሳለቂያ መሆን

  እስራት

  ሞት

  ድህነት

  Correct answer

  ሥቃይ

  የጓደኞችና ጎረቤቶች መሳለቂያ መሆን

  እስራት

  ሞት

  ድህነት

  On Mon, May 13, 2019 at 5:56 PM ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት wrote:

  > tsegaewnet posted: “ጸሐፊው አይሁዳውያን ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን የሚያስከብር ሕይወት ለመኖር ሊያደርጉ
  > የሚገዷቸውን አንዳንድ ነጥቦች በመዘርዘር መልእክቱን ያጠቃልላል። እነዚህ ትምህርቶች ሩጫችንን በሚገባ እንዳንሮጥ
  > የሚከተሉት መሰናክሎች ወይም ኃጢአቶች በመንፈሳዊ ሩጫችን ውስጥ መኖር አለመኖራቸውን ለማረጋገጥ ደግመን ደጋግመን
  > የምንመለከታቸው ነገሮች ናቸው። ሀ) በክርስቶስ ወንድሞቻችሁና እኅቶቻችሁን ውደዱ። ለ”
  >

  1. ወንድሜ ጥያቄህን ለዝግጅት ክፍላችን ስለላክህ እናመስገናለን፡፡ ጥያቄህን፣ “በእምነት እየተመላለስን ለምን ክፉ ነገሮች እንዲገጥሙን እግዚአብሔር ይፈቅዳል?” እና “ከእግዚአብሔር ጋር አብረን መሆናችን በምን ይታወቃል?” በሚል በሁለት ከፍሎ ማየቱ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም፡፡

   በእምነት እየተመላለስን ለምን ክፉ ነገሮች እንዲገጥሙን እግዚአብሔር ይፈቅዳል?
   ለዚህ ጥያቄ በቂና ሙሉ ምላሽ ማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱሳችን ክፉ ወይም አስቸጋሪ ነገሮች እንዲደርሱብን ለምን እግዚአብሔር እንደሚፈቅድ መጠነኛ ፍንጮች ይሰጠናል፡፡ ከእስራኤል ሕዝብ ጉዞ አንጻር ይህን ጥያቄ ለመመለስ እንሞክር፡፡ አጭርና ጥቂት ቀናት ብቻ የሚፈጅ መንገድ እያለ እግዚአብሔር እስራኤላውያን ለምን ለ40 አመታት በምድረበዳ ለምን መራቸው? መልሱ እነሆ፣ “አምላክህ እግዚአብሔር ትእዛዞቹን መጠበቅህንና በልብህ ያለውን ለማወቅ፣ ትሑት ሊያደርግህና ሊፈትንህ በእነዚህ አርባ ዓመታት በዚህ ምድረ በዳ ጒዞህ ሁሉ እንዴት እንደ መራህ አስታውስ።ዘዳ 8፡2”

   እውነተኛውን ማንነታችንን የምናውቀው (ማለትም ድካማንንን/ጥንካሬያችንን፣ ወዘተ) በአስቸጋሪ ወይም ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ስናልፍ ብቻ ነው፡፡ እውነተኛ ማንነታችንን ማወቃችን ደግሞ የሚያስፈልገንን/የጎደለንን አውቀን እውነተኛ የእርዳታ ጥሪ ለማቅረብ ያስችለናል፡፡ ውድቀት/ሃጢአት አይኖቻችንን አሳውሮታል፣ ሕሊናችንን አደንዝዞታል፣ እውቀታችንን በክሎታል፣ ወዘተ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ስለራሳችን ያለን ግንዛቤ የተዛባ ቢሆን አያስገርምም፡፡ እናም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ስናልፍ ከተኛንበት መንፈሳዊ እንቅልፍ እንነቃለን፣ እውነተኛ የልብ ሃሳቦቻችንን፣ አነሳሽ ምክኛቶቻችንን፣ ዝንባሌዎቻችንን እና ፍላጎቶቻችንን እናውቃለን፣ የጎደለንን እንረዳለን፣ ድካማችንን እናስተውላለን፣ እርዳታ ወደምናገኝበት ስፍራ እንጠጋለን፣ መፍትሄውን/መድሃኒቱን ለማግኘት እውነተኛ ጥረት እናደርጋለን፡፡

   ፈተናዎች ወይም አስቸጋሪ ነገሮች ያለንበትን እውነተኛ ሁኔታ ከማሳበቃቸው በተጨማሪ ለመፍትሄው እንድንተጋም ያነሳሱናል፡፡ ለአብነት፣ በራሱ አይንና መመዘኛ ትሁት የሆነ የመሰለው ሰው፣ ትህትናውን በሚፈተን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዲያልፍ ተደርጎ ትህትናው የውሸት እንደሆነ መረዳት ቢችል፣ በመጀመሪያ እውነተኛ ማንነቱን ያውቃል (የሃሰት ጭንብሉን ይወልቃል) በመቀጠልም ትህትናን ሊሰጥ የሚችለውን አምላክ ብብርቱ ፍላጎትና እንባ ይጠይቃል፡፡ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ይሉሃል ይህ ነው፡፡ አንድ ሰው ትሕትናን በሚፈትኑ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲያልፍ ሳይደረግ ስለትህትናው በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ ትህትናን ሳይቀበል ደግሞ የእግዚአብሔርን ጸጋ በሙላት ማግኘት አይችልም (ያዕ 4፡6፣ 1ጴጥ 5፡5፣ ምሳሌ 3፡34)፡፡ እግዚአብሔርን “ለምን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንድንገባ ፈቀድክ?” ስንለው ከአስቸጋሪዎቹ ሁኔታዎች በስተጀርባ ያሉትን እነዚህን ስጦታዎች ማስተዋል ስለማንችል ነው፡፡ አንድ ሕጻን የአባቱን ቅጣት እንደሚያማርር ማለት ነው፡፡ ልጁ በሕጻንነቱ ዘመን ያላስተዋለውን የቅጣት አስፈላጊነት ሲጎለምስ እንደሚያስተውለው ሁሉ እኛም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንድናልፍ ለምን እግዚአብሔር እንደፈቀደ የምናስተውለው ብዙ ጊዜ ዘግይተን ነው፤ ምናልባትም ጭራሽ ላናስተውለውም እንችላለን፡፡

   አይምሮአዊ እውቀት በራሱ ተግባራዊ እውቀት ሊሆን እንደማይችል ሁሉ ያልተፈተነ መታዘዝ፣ እውነተኛ መታዘዝ ሊባል አይችልም፡፡ አብርሃም ልጁን ለእግዚአብሔር መሰዋት አድርጎ ለማቅረብ “እሺ” ማለቱ ብቻ በቂ አልነበረም፡፡ ያ “እሺታ” በተግባር መፈተን ነበረበት፡፡ ያ ፈተና ደግሞ እጅግ አስቸጋሪ እና አስጨናቂ መሆኑን ማንም ወላጅ የሆነ ሰው ሁሉ መገመት ይችላል፡፡ አብርሃም ልጁ ላይ ቢላ እስኪያነሳ ድረስ እግዚአብሔር ዝም ያለው በአብርሃም ልብ ውስጥ ያለው መታዘዝ (እግዚአብሔርን መፍራት) በግልጽ ይታወቅ ዘንድ ነበር፡፡ “በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፥ አንዳችም አታድርግበት፤ አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደ ሆንህ አሁን አውቄአለሁ አለ።(ዘፍ 22፡12)”፡፡ እግዚአብሔርን መታዘዛችን ሳይፈተን መታዘዙ ከእውቀት ያለፈ ስለመሆኑ ሊረጋገጥ አይቻልም፡፡ የፈተና አይነቶቹ ደግሞ ብዙ መልክ ሊኖራቸው ይችላል፣ (ሥቃይ፣ የጓደኞችና ጎረቤቶች መሳለቂያ መሆን፣ እስራት፣ ሞት፣ ድህነት፣ ወዘተ)፡፡

   ከእግዚአብሔር ጋር አብረን መሆናችን በምን ይታወቃል?
   ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖች፣ አማኝ ከእግዚአብሔር (ከመንፈስ ቅዱስ) ጋር ያለውን ጤናማ ግንኙነት የሚለኩበት መሣሪያ የተሳሳተ ነው፡፡ ለአብነት፣ የተሻለ ደሞዝ፣ ጥሩ መኖሪያ ቤት፣ ልጆች፣ አካላዊ ጤና፣ ፣ ወዘተ ያሉት አማኝ ይህ የሆነለት ከእግዚአብሔር ጋር መልካም ግንኙነት ስላለው እንደሆነና እነዚህ የጎደሉት ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር በትክክለኛ መንገድ ላይ እየሄደ አለመሆኑን ያሳያል ሲሉ ይደመጣል፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት መለኪያዎች ከእግዚአብሔር ጋር መሆናችንን የሚያሳዩ ከሆነ ወንጌልን ለባለጠጎች መስበካችንን አላስፈላጊ አያደርገውም ወይ? ከዚህ በተጨማሪስ እግዚአብሔር የለም የሚሉ ኢአማኒያንን ጨምሮ በእስልምና፣ በቡድሃ፣ ወዘተ ቤተ እምነቶች ስር ያሉ እና ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች የሚያሟሉ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር በመልካም መንገድ ላይ እየተጓዙ ያሉ ሰዎች ናቸው ወይ? መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ መመዘኛዎቹ የተሳሳቱ ናቸው፡፡

   ሁላችን በእድገት ላይ ያለን ነን፡፡ ሁላችን በግንባታ ላይ ያለን መንፈሳዊ ሕንጻዎች ነን፡፡ እናም ከሕወታችን ፍጹም ነገር መጠበቅ ስላለንበት ሁኔታ በትክክል ካለመገንዘብ የሚመጣ ነው፡፡ ሕይወታችን በብዙ ውጣ ውረድ የተሞላች ናት፡፡ መውደቅና መነሳት፣ መድከምና መበርታት፣ መሳቅ እና ማዘን የሕይወቶቻችን መገለጫዎች ናቸው፡፡ እናም ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ ስለመጓዝ ስናወራ፣ ከሃጢአት ፈጽሞ ነጻ የሆነ ሕይወት ወይም አልጋ በአልጋ ስለሆነ መንገድ እያወራን ስላለመሆኑ መጀመሪያ ግንዛቤ መውሰድ ጠቃሚ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር አብረን መሆናችንን ፍንጭ የሚሰጡ አንዳንድ ነገሮች ከዚህ በታች ቀርበዋል፦

   የማንንም እርዳታ ከመጠየቃችን በፊት አስቀድመን ፈጣሪያችንን በጸሎት እንጠይቃለን፣ “አቤቱ፥ በመልካሙ ጊዜ ጸሎቴ ወደ አንተ ነው፤ አቤቱ፥ በምሕረትህ ብዛት በማዳንህም እውነት አድምጠኝ።” (መዝ 69፡13)

   የእግዚአብሔርን ቃል ለማንበብና ለማጥናት ረሃብ ይኖረናል፣ “ከአፉ ከወጣው ትእዛዝ አልራቅሁም፣ የአንደበቱን ቃል ከእለት እንጀራዬ አብልጬ ይዣለሁ፡፡” (ኢዮብ 23፡12 አ.መ.ት.)

   ስለውጫዊው ሳይሆን ስለውስጣዊው የልብ ዝንባሌያችን እና ምኞቶቻችን ከፍተኛ ትኩረት እንሰጣለን፣ “በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን?” (2ቆሮ 13፡5)

   በአለም ካሉትን አለማዊ ነገሮች እለት እለት እየራቅን እንሄዳለን፣ “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።” (ሮሜ 12፡2)

   በቀላሉ አንበሳጭም፣ “በነፍስህ ለቍጣ ችኩል አትሁን፥ ቍጣ በሰነፍ ብብት ያርፋልና።” (መክ 7፡9)

   በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ስናልፍ ከመስጋት ይልቅ በእርሱ ተስፋ እናደርጋለን፣ “ለእግዚአብሔር ተገዛ ተስፋም አድርገው። መንገድም በቀናችለትና ጥመትን በሚያደርግ ሰው አትቅና።” (መዝ 37፡7)

   እንዚህም ነገሮች ቢሆኑ በሕይወታችን የሚቋረጡበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል፡፡ ያ ማለት በጊዚያዊነት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለን ሕብረት ታውኳል ማለት እንጂ ድነታችንን አጥተናል ማለት አይደለም፡፡ ይህን ለማደስ ንስሃ መግባትና ትጋታችንን መቀጠል ነው፡፡ ትግሉ እና ውጣ ውረዱ እስከ ሕይወታችን ዘመን ፍጻሜ የሚቀጥል ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን አንድ መርሳት የሌለብን ነገር አለ፡፡ ተስፋችንም ሆነ መተማመናችን በእኛ ጥረትና ትጋት ላይ ሳይሆን በእርሱ ጸጋ ላይ መሆን አለበት፡፡ በእኛ የጀመረውን መልካም ሥራ እስኪፈጽም ድረስ ከእኛ ጋር እንደሚሆን የተናገረውን ተስፋ አምነን በትእግስት ሩጫችንን እንሮጣለን ፡፡ “በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤” (ፊል 1፡6)

  2. ወንድሜ፣ ለጥያቄህ ተጨማሪ ምላሽ ይሰጣል ብዬ ያመንኩትን ሊንክ አቅርቤልሃለው፡፡ የጽሁፉ ርዕስ “መከራና የእግዚአብሔር ሉአላዊነት” ይላል፡፡ ተጨማሪ ጥያቄ ካለህ ከመጽፍ ወደኋላ እንዳትል፡፡ እግዚአብሔር ይባርክህ፡፡ https://ethiopiansite.com/2018/05/30/%E1%88%98%E1%8A%A8%E1%88%AB%E1%8A%93-%E1%8B%A8%E1%8A%A5%E1%8C%8D%E1%8B%9A%E1%8A%A0%E1%89%A5%E1%88%94%E1%88%AD-%E1%88%89%E1%8A%A0%E1%88%8B%E1%8B%8A%E1%8A%90%E1%89%B5/

Leave a Reply

%d bloggers like this: