በእምነትና ስለ እግዚአብሔር ባል እውቀት ማደግ (2ኛ ጴጥ. 1፡1-21)

ስለሺ እግዚአብሔርን የሚወድ ወንድም ነበር። እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ በሽምግልና አገልግሎት በብዙ መንገዶች ተጠቅሞበታል። ይሁንና፥ ስለሺ ሁልጊዜም ለእግዚአብሔር የሚቀና ሰው አልነበረም። ከአሥር ዓመታት አካባቢ በፊት፥ ለእግዚአብሔር የነበረው ፍቅር እየቀዘቀዘ እንዲሄድ አድርጓል። አንድ ሌሊት ከሚስቱ ጋር ብዙ ከተጨቃጨቁ በኋላ፥ ወደ ቡና ቤት ሄዶ ጠጥቶ ከሰከረ በኋላም እዚያው ከአንዲት ሴተኛ አዳሪ ጋር አብሮ አደረ። በኋላም መንፈስ ቅዱስ ስለፈጸመው ኃጢአት ስለ ወቀሰው ኃጢአቱን ለእግዚአብሔር እና ለሚስቱ ተናዝዞ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሕይወቱን በጥንቃቄ ይመራ ጀመር። ከብዙ ዓመታት በኋላ ስለሺ ይታመም ጀመር። ሐኪም ባዘዘለት መድኃኒት ለጊዜው ሻል አለው። ከቆይታ በኋላ ግን በሽታው እያየለበት ሄደ። ክብደቱም እየቀነሰ ይሄድ ጀመር። አንድ ቀን ለምርመራ ወደ ሐኪም ቤት ሄዶ ከተመረመረ በኋላ ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ ሳለ ከነርሶች አንዷ፥ «ይሄ ምስኪን ሰውዬ ኤድስ አለበት። ሞቱ ተቃርቧል ማለት ነው» ስትል ሰማ። ስለ እርሱ እንደምትናገር በተገነዘበ ጊዜ እጅግ ደነገጠ። ስለሺ እግዚአብሔር እንዲፈውሰው ቢጸልይም መልስ አላገኘም። የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንዲጸልዩለት ጠየቀ በተጨማሪም፥ ሰዎችን በመፈወስ ወደሚታወቅ አንድ አገልጋይ ሄዶ ተጸለየለት። እግዚአብሔር ግን አልፈወሰውም፡፡ አንድ ቀን መንፈስ ቅዱስ የአንድ ዓመት እድሜ ብቻ እንዳለው በመግለጽ አስጠነቀቀው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንተ በስለሺ ቦታ ብትሆን ኖሮ ራስህንና ቤተሰቦችህን ለሞት ለማዘጋጀት በመጨረሻው ዓመትህ በምን ምን ጉዳዮች ላይ ትኩረት ታደርግ ነበር? ለ) በቅርቡ እንደምትሞት ማወቅህ ለገንዘብ፥ ለጥሩ ቤትና ለመማር የሚኖርህን አመለካከት የሚቀይረው እንዴት ነው?

እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ መቼ እንደምንሞት አይነግረንም። ነገር ግን አንድ ቀን እንደምንሞት እና እንደዚሁም በቂ ዝግጅት ማድረግ እንዳለብን ያስጠነቅቀናል። ሞት በሚቃረብበት ጊዜ ሰዎች ስለ ገንዘብ፥ ጥሩ ቤት ወይም መኪና ስለ መግዛት አያስቡም። ስለ ትምህርትም አያስቡም። ስለሺ ሊሞት እንደ ተቃረበ ሚስቱን እርሱ በሌለበት ዓለም ውስጥ ለመኖር እንዴት እንደሚያዘጋጃት ያስብ ጀመር። ለልጆቹ በሕይወት አስፈላጊ ስለሆኑት ጉዳዮች ሊያስተምራቸው ፈለገ። እንደ እርሱ በኤድስ ለታመሙት እና የዘላለምን ሕይወት ሳያገኙ ለሚሞቱ ሰዎች እንዴት ወንጌልን እንደሚያደርስላቸው አሰበ። በዚህ ጊዜ የዘላለም ሕይወት በዚህ ምድር ካለው ነገር ሁሉ በላይ ዋጋ ያለው መሆኑን ተገነዘበ።

ጴጥሮስ ይህን የ2ኛ ጴጥሮስ መልእክት የጻፈበት ዓላማ ክርስቲያኖች ዓለም ከምታጋንናቸው ጊዜያዊ ነገር ርቀው ዘላለማዊ እሴት ባላቸው ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩ ለማበረታታት ነው። ይህንንም ለማድረግ ጴጥሮስ የተጠቀመው ስለ ሞት መጻፍ ሳይሆን፥ በጌታ ቀን ላይ አጽንኦት መስጠት ነበር። «የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል» አለ። «በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምጽ ያልፋሉ። የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኩሳት ይቀልጣል። ምድርም በእርሷ ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁ እና እያስቸኮላችሁ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርን በመምሰል እንደምን ልትሆኑ ይገባችኋል» ማናችንም ክርስቶስ መቼ እንደሚመለስ አናውቅም። ነገር ግን በየትኛውም ጊዜ ሊመለስ እንደሚችል ከተገነዘብን፥ የዛሬውን አኗኗራችንን እንለውጣለን። ለክርስቶስ ዳግም ምጽአት ተዘጋጅተሃል?

የውይይት ጥያቄ፡- 2ኛ ጴጥ. 1፡3 አንብብ። ሀ) ጴጥሮስ በመንፈሳዊ ጉዞአችን ስለማደግ ምን ይላል? እነዚህ ምዕራፎች ስለ ሐሰተኛ ትምህርትና ስለ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ምን ይላሉ? ሐ) ጴጥሮስ ስለ መጨረሻው ዘመን እና ክርስቶስ በየትኛው ጊዜ ሊመለስ እንደሚችል እየተገነዘቡ ስለ መኖር ምን ይላል?

ስለሺ ወደ ሞት በተቃረበ ጊዜ ስለ ልጆቹ መንፈሳዊ እድገት በጽኑ እንዳሰበ ሁሉ፥ ጴጥሮስም እንዲሁ ሞቱ ሲቃረብ ስለ መንፈሳዊ ልጆቹ እና መንፈሳዊ እድገታቸው በጥልቀት ያስብ ጀመር። በዚህ ሁለተኛ መልእክቱ በእምነታቸው ለመብሰል ምን ሊያደርጉ እንደሚገባ ይመክራቸዋል። ጴጥሮስን ያሳሰበው የመጀመሪያው ነገር በእውቀት እና በመንፈሳዊነት ማደግ መቀጠላቸው ነበር። ጴጥሮስ እነዚህ ሁለት ነገሮች አብረው እንደሚሄዱ ተገንዝቧል። አንድ ሰው በእውቀት ካላደገ በመንፈሳዊነትም ሊያድግ አይችልም። ሰዎች በእውቀት ማደግ የሚያስፈልጋቸው በመንፈሳዊነት እንዲያድጉ ነው። ይህ እውነት በ2ኛ ጴጥሮስ የመጀመሪያው ክፍል ውስጥ ተመልክቷል።

  1. መግቢያ (2ኛ ጴጥ. 1፡1-2) ጴጥሮስ በዚህ መግቢያው መንፈሳዊ ልጆቹ በሕይወታቸው እንዲያድጉ መፈለጉን ገልጾአል። ጴጥሮስ ከውድ እምነታቸው የተነሣ በጽድቅ የሚመላለሱ በመሆናቸው ደስ መሰኘቱን ከገለጸ በኋላ፥ ጸጋና ሰላም እንዲኖራቸው ይጸልያል። ለመሆኑ አማኝ ጸጋና ሰላምን የሚያገኘው እንዴት ነው? ጴጥሮስ እግዚአብሔርን እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ መሆኑን ይናገራል። ስለ እግዚአብሔር ባለን እውቀት እና ከክርስቶስ ጋር ባለን ቅርበት እያደግን ስንሄድ በሕይወታችን የእግዚአብሔርን ጸጋ እንለማመዳለን። በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም ሳይቀር የእርሱ ሰላም አእምሯችንን ይሞላዋል።
  2. እማኞች በክርስቶስ ያላቸውን እምነት ለማረጋገጥ በመንፈሳዊ ባህሪ ማደግ ይኖርባቸዋል (2ኛ ጴጥ. 1፡3-11)

ድነት (ደኅንነት) የሚጀምረው በእውቀት ነው። በክርስቶስ ልናምን የምንችለው ማንነቱን እና ለእኛ የሚያደርገውን ነገር ካወቅን በኋላ ብቻ ነው። ይህ ስለ ክርስቶስ ያለን እውቀት ወደ ግንኙነት፥ ወይም ክርስቶስን ወደ ማወቅ ያድጋል። ይህም ከጓደኞቻችን ጋር ብዙ ጊዜ ባሳለፍን እና ስለ እነርሱ ብዙ ባወቅን መጠን የጠለቀ ወዳጅነት እንደምንመሠርት ማለት ነው። ጴጥሮስ እግዚአብሔር አብን እና ኢየሱስ ክርስቶስን ከማወቃችን እና ግንኙነት ከመመሥረታችን የሚፈልቁትን አያሌ ውጤቶች ይዘረዝራል። በመጀመሪያ ድነት (ደኅንነት) በእግዚአብሔር እይታ መነጽር ምን እንደሆነ ይገልጻል። ከዚያም በክርስቶስ ባመንን ጊዜ እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታዎች ይዘረዝራል። እግዚአብሔር እርሱን በሚያስከብር መንገድ ለመኖር የማያስፈልጉንን ነገሮች ለእኛ ለማስተላለፍ መለኮታዊ ኃይሉን ይጠቀማል።

ሀ) እግዚአብሔር መለኮታዊ ባህሪን ለመስጠት እርሱን እንድንመስል ያደርጋል።

ለ) እግዚአብሔር በክፉ ምኞቶች ምክንያት በዓለም ከተከሰተው ጥፋት ነፃ እንድንሆን ያደርጋል። ከእንግዲህ ኃጢአትን ለማድረግ የኃጢአት ባህሪያችን እስረኞች አይደለንም። ነገር ግን ከክፉ ተመልሰን እግዚአብሔርን ለማገልገል ነፃ ወጥተናል።

ጴጥሮስ በድነት (ደኅንነት) ጊዜ እግዚአብሔር ምን እንዳደረገልን ከገለጸልን በኋላ፥ ልጆቹ ከሆንን በኋላ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ ያስረዳል። እግዚአብሔር በቀዳሚነት ከእኛ የሚፈልገው እንደ መጠጥ ማቆም፥ ፊልም አለማየት ወይም ሰዎች መንፈሳዊነትን ይገልጻሉ ብለው የሚያስቧቸውን ነገሮች ማድረጋችንን አይደለም። ነገር ግን ጴጥሮስ፥ ባሕሪያችን መለወጥ እንዳለበት ይናገራል። እንደ ጠንካራ ሰንሰለት መንፈሳዊ ባሕሪ ከብዙ የተለያዩ ባሕርያት የተገነባ ነው። ጴጥሮስ የዚህን ሰንሰለት የተለያዩ መገጣጠሚያዎች በመመልከት እያንዳንዱ መገጣጠሚያ ጠንካራ እና እያደገ የሚሄድ ሊሆን እንደሚገባ ያስጠነቅቃል። እነዚህም የመንፈሳዊ ባህሪ መገጣጠሚያዎች እምነት፥ በጎነት፥ እውቀት፥ ራስን መግዛት፥ ጽናት፥ እግዚአብሔርን መምሰል፥ የወንድማማች መዋደድና ፍቅር ናቸው። የእግዚአብሔር ባህሪ በውስጣችን ስላለ እና የእርሱ ልጆች ስለሆንን፥ እነዚህ ነገሮች የባህሪያችን መገለጫዎች ሊሆኑ ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ስምንት ባሕርያት የክርስቲያን ሕይወት ክፍሎች መሆናቸው ለምን አስፈላጊ እንደሚሆን ግለጽ? ለ) ከእነዚህ ባሕርያት አንዱ ቢጓደል ወደ ሕይወታችን ወይም ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ሊመጡ የሚችሉትን ችግሮች ዘርዝር። ሐ) ከእነዚህ ባሕርያት የግልህ ለማድረግ የሚያስቸግርህ የትኛው ነው? መ) በእነዚህ ስምንት ባሕርያት ለማደግ ምን እያደረግህ ነው?

በእነዚህ ባሕርያት እያደገ የሚሄድ ሕይወት ውጤቱ ምን ይሆናል? ጴጥሮስ ሁለት ነገሮችን ይዘረዝራል። በመጀመሪያ፥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ውጤታማ ሰዎች እንደምንሆን ይናገራል። በሌላ አገላለጽ፥ ተግባራችንም ሆነ አኗኗራችን እግዚአብሔርን የሚያስደስትም ሆነ የሚያስከብር ይሆናል። ሁለተኛ፥ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን የሚያሳይ ውስጣዊ ማረጋገጫ ይኖረናል። በራሳችን ሕይወት ውስጥ የተከሰተውን ለውጥ በመመልከት እምነታችን እውነተኛ መሆኑን እና የእርሱን ባሕሪ የተላበስን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን እንረዳለን። ጴጥሮስ «መመረጣችሁን እና መጠራታችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ» ሲል ይህን ማለቱ ነበር።

  1. አማኞች ከመንፈስ ቅዱስ የሚመጡትን የእግዚአብሔር ቃል እውነቶች ማስታወስ አለባቸው (2ኛ ጴጥ. 1፡12-21)

ሰዎች ድግግሞሽ የመማር ቁልፍ ነው ሲሉ እንሰማለን። ጴጥሮስ ሊሞት እንደተቃረበ ስለተገነዘበ ለእማኞች ቀደም ሲል የሰሟቸውን እውነቶች በድጋሚ ሊያሳስባቸው ይፈልጋል። ለአማኞች ብዙውን ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚቃረኑ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረቶች የሚያዛቡትን አዳዲስ እና አስገራሚ አሳቦች መከተል ቀላል ነው። እነዚህ አዳዲስ አሳቦች ይመጣሉ ይሄዳሉ። (ለምሳሌ፡ በተወሰኑ መንፈሳዊ ስጦታዎች ላይ፥ ወይም በተወሰነ የአምልኮ ስልት ላይ ትኩረት ማድረግ፥ ወዘተ. . . )። ነገር ግን አማኞች በፍጹም የማይለወጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ካላወቁና አጥብቀው ካልያዙ፥ ሕይወታቸው በውዝግብ የተሞላ ይሆናል።

ለመሆኑ እውነት የሆነውን እና ያልሆነውን እንዴት ነው ማወቅ የምንችለው? በየጊዜው የተለያዩ ትምህርቶች ይመጣሉ። እነዚህ ትምህርቶች ከእግዚአብሔር መሆናቸውን የምንገመግመው እንዴት ነው? ልክ እንደ ዛሬው ዘመን፥ የጴጥሮስ ዘመነኞችም በብልሃት የተፈጠረ ተረት ተጽዕኖ አሳድሮባቸው ነበር። እነዚህ ተረቶች (ታሪኮች) ክርስቲያኖችን ያስገርሙ እና ያደናግሩ ነበር። እነዚህ ትምህርቶች የተሳሳቱ ነበሩ? ጴጥሮስ ከእግዚአብሔር የሆኑትን ነገሮችና ከእግዚአብሔር ያልሆኑትን ለመለየት የሚቻልባቸውን ሁለት የመረጃ ምንጮች ይጠቁማል። በመጀመሪያ፥ የዓይን ምስክሮችን ይጠቅሳል። ጴጥሮስ ይህን ሲል እራሱን እና ሌሎች ሐዋርያትን ማመልከቱ ነበር። እራሱ ጴጥሮስ ክርስቶስ በተራራው ላይ ሲለወጥ ክብሩን እና ኃይሉን ለማየት በቅቷል። የእግዚአብሔር አብ ድምጽ ክርስቶስ ልጁ እንደሆነ ሲናገር ሰምቷል። እነዚህ ታሪኮች እና ትምህርቶች ዛሬ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ይገኛሉ። እውነትን የምናውቀው ከእግዚአብሔር ቃል እንጂ ከዝነኛ ሰዎች ወይም ከሌሎች ሃይማኖቶች አይደለም። ሁለተኛ፥ የብሉይ ኪዳን ነቢያቶችን ይጠቅሳል። ብሉይ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ልብ ውስጥ ከመሥራቱ የተነሣ የተገኘ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ለእምነታችን ብቸኛ የሥልጣን መሠረት ብሉይ ኪዳን እና አዲስ ኪዳን መሆኑን አጥብቀን መገንዘብ ያለብን እነዚህ መጻሕፍት የመንፈስ ቅዱስ የሥራ ውጤቶች በመሆናቸው ነው። እግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስን የእውነት መመዘኛ አድርጎ ሰጥቶናል። ሌሎች እምነቶች፥ ኃይማኖቶች እና ልምምዶች ሁሉ የሚገመገሙት በመጽሐፍ ቅዱስ ነው። ለአማኞች ሁሉ በተለይም ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተነገረውን መገንዘብ አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው። ይህ ካልሆነ ለእውነት መሠረት አድርገን የምንወስደው፥ የምናስበውን፥ የሚሰማንን ስሜት፥ ከሰዎች የሰማነውን ወይም ቀደም ሲል ያከናወነውን ብቻ ይሆናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጠና ማግኘታቸው አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ቤተ ክርስቲያን መሪዎቿና መምህሮቿ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያውቁ ምን ልታደርግ ትችላለች?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: