የ2ኛ ጴጥሮስ መግቢያ

ሸምገል ያለ ሰው ነበር። ከ30 ዓመት በፊት ነበር አንድ ክስተት ሕይወቱን የለወጠው፡፡ በአንድ ተራ ቀን ወንድሙ የእድሜ እኩያው ከሆነው ከክርስቶስ ጋር እንዲተዋወቅ ጠየቀው «መሲሁ ይሄ ነው» ሲል ነገረው። ለሚቀጥሉት ሦስት ተኩል ዓመታት ከመሢሑ ጋር በመጓዝ፥ በመነጋገር፥ ሕይወቱን በመመልከት፥ ሲሞትም እዛው በመገኘትና በትንሣኤውና በእርገቱ በመደነቅ አሳልፎአል። ይህን መልእክት በሚጽፍበት ጊዜ ብዙ ዘመናት ስላለፉ እርጅና ተጫጭኖታል። እናም እስር ቤት ባይገባም ክርስቶስ በቅርቡ እንደሚሞት ነግሮታል። ጴጥሮስ እንደ ጻፈው፥ «ሁልጊዜም በዚህ ማደሪያ ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ የሚገባኝ ይመስለኛል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ማደሪያዬ መለየቴ ፈጥኖ እንደሆነ አውቃለሁና» (2ኛ ጴጥ. 1፡13-14)። ብዙም ሳይቆይ ይህ አረጋዊ እንደ ጌታው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞቷል። ከመሞቱ በፊት ግን ጴጥሮስ እርሱን ያውቁትና ያከብሩት የነበሩ ክርስቲያኖች አንዳንድ ጠቃሚ እውነቶችን እንዲያውቁ ፈለገ። ከእነዚህም እውነቶች አንዱ ከክርስቶስ ጋር ባላቸው ሕይወት ክርስቲያኖች ማደግ እንዳለባቸው ነበር። ጴጥሮስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ ማደጉን አላቆመም። ነገር ግን በክርስቶስ እውቀትና ባህሪ ለማደግ ፈለገ «ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፥ በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም መምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ» (2ኛ ጴጥ. 1፡5-7)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በክርስቶስ ካመንህ ምን ያህል ጊዜ ሆነህ? ለ) ጴጥሮስ በዘረዘራቸው ባሕርያት በእያንዳንዳቸው እንዴት እያደግህ እንደ መጣህ ግለጽ። ያላደግህበት ባህሪ ካለህ ምክንያቱ ምንድን ነው? መንፈስ ቅዱስ ጴጥሮስ እንደተናገረው በመንፈሳዊ ሕይወትህ እንዲረዳህ ጊዜ ወስደህ ጸልይ!

የውይይት ጥያቄ፡– 2ኛ ጴጥሮስን ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። በመዝገበ ቃላት ውስጥ ስለ ጸሐፊው፥ ስለ እንባቢዎቹ፥ መልእክቱ ስለ ተጻፈበት ጊዜና ዓላማ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።

የ2ኛ ጴጥሮስ ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፡- 2ኛ ጴጥ. 1፡1-2 አንብብ። ሀ) ጸሐፊው ራሱን የሚገልጸው እንዴት ነው? ለማን እንደሚጽፍ ይናገራል?

የሁለተኛ ጴጥሮስ ጸሐፊ ራሱን፥ «የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ የሆነ ስምዖን ጴጥሮስ» ሲል ይገልጻል። ምንም እንኳን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሁሉ ይህን መጽሐፍ ማን እንደ ጻፈው የሚጠራጠሩ ሰዎች ቢኖሩና አንዳንድ ምሁራን ደግሞ ጴጥሮስ ይህን መልእክት እንዳልጻፈው ቢናገሩም፥ ጸሐፊው የተናገረውን ለመጠራጠር የሚያስችል በቂ መረጃ የለንም። ጸሐፊው ሐዋርያው ጴጥሮስ መሆኑ ክርስቶስ በተራራ ላይ መልኩን በለወጠ ጊዜ እንዳየው ከሚናገረው አሳብ ጋር ይጣጣማል (2ኛ ጴጥ. 1፡16-18፤ ማቴ. 17፡1-13)። እንዲሁም ደግሞ ጴጥሮስ ይህ ሁለተኛ መልእክቱ እንደሆነ ይናገራል (2ኛ ጴጥ. 3፡1)። ጸሐፊው በተጨማሪም፥ «የተወደደ ወንድማችን» (2ኛ ጴጥ. 3፡15) ሲል የገለጸው ጳውሎስ በኖረበት ዘመን እንደኖረ ይናገራል። ይህ ሁሉ ማስረጃ የዚህ መልእክት ጸሐፊ ሐዋርያው ጴጥሮስ መሆኑን ያመለክታል።

በ1ኛ ጴጥሮስና 2ኛ ጴጥሮስ መልእክቶች መካከል ያለውን የመግቢያ ልዩነት መመልከቱ አስገራሚ ነው። በ2ኛ ጴጥሮስ፥ ጴጥሮስ ራሱን በሙሉ ስሙ ስምዖን ጴጥሮስ ሲል ይጠራዋል። ስምዖን አይሁዳዊ ስሙ ሲሆን፥ ጴጥሮስ ደግሞ የግሪክ ስሙ ነበር። ይህንንም ስም የሰጠው ደግሞ ክርስቶስ ነበር። በ1ኛ ጴጥሮስ፥ ሐዋርያ መሆኑን ሲያመለክት በ2ኛ ጴጥሮስ ደግሞ ባሪያ የሚለውን ቃል ያክላል። ጴጥሮስ ክርስቲያኖች ሐዋርያነቱንና ከዚህ ጋር በተያያዘ በሐዋርያዊ ሥልጣኑ መልእክቱን እንደ ጻፈ መዘንጋት እንደሌለባቸው ተገንዝቦ ነበር። ከሁሉም በላይ ግን ጴጥሮስ ክርስቲያኖች ልክ እንዴት እርሱ ክርስቶስን ለማገልገል የሚፈልግ መሆኑን እንዲገነዘቡለት ይፈልጋል። ምናልባትም ጴጥሮስ ክርስቶስ በተያዘበት ሌሊት የነበሩትን ሁኔታዎች እያስታወሰ ይሆናል። እንደ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ሁሉ መሪና በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ ታላቅ መሆን ይፈልግ ነበር (ሉቃስ 22፡24-30)። እንደ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ሁሉ ጴጥሮስ ራሱን ዝቅ አድርጎ የሌሎችን ደቀ መዛሙርት እግር ለማጠብ አልፈለገም ነበር (ዮሐ 13፡1-17)። አሁን ከረጅም ጊዜ በኋላ ክርስቶስ ራሱን ዝቅ አድርጎ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበትን ሁኔታ ሲያስታውስ እንመለከታለን። እንዲሁም በክርስቶስ መንግሥት ሰው ታላቅ የሚሆነው ሌሎችን በማገልገል እንደሆነ የሚያስረዳውን የክርስቶስን ቃል አስታውሷል። በመሆኑም አሁን በሕይወቱ መጨረሻ ፥ ጴጥሮስ ሰዎች በሐዋርያነቱ ብቻ ሳይሆን በባሪያነቱ እንዲያስታውሱት ይፈልጋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እራሳቸውን ለሌሎች በሚያስተዋውቁበት ጊዜ ባላቸው ኃይል፥ ሥልጣን ወይም ትምህርት ላይ ትኩረት የሚሰጡት ለምንድን ነው? ለ) ብዙ መሪዎች እንደ ባሪያ ለመታወቅ የማይፈልጉት ለምንድን ነው? ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ራሳቸውን በቀዳሚነት እንደ ሽማግሌዎች ወይም መሪዎች ሳይሆን፥ እንደ ባሪያዎች ቢመለከቱ ባህሪያቸው እንዴት ይለወጣል?

ጴጥሮስ መልእክቱን የጻፈው ለማን ነው?

ጴጥሮስ መልእክቱን ለማን እንደሚጽፍ ሲገልጽ፥ «በአምላካችንና በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ካገኘነው ጋር የተስተካከለ የክብር እምነት ላገኛችሁት» ይላል። በሌላ አገላለጽ፥ ጴጥሮስ የሚጽፈው ለአማኞቹ ሁሉ ነበር። እነዚህ አማኞች እንደ ሰሜናዊ ትንሹ እስያ ባሉ የተወሰኑ አካባቢዎች የሚኖሩ አልነበሩም። ነገር ግን ይህ አጠቃላይ መልእክት በትንሹ እስያ ውስጥም ያሉትን አማኞች ያካትት ነበር። ምክንያቱም ጴጥሮስ ይህ ለእነርሱ የሚልከው ሁለተኛ መልእክት እንደሆነ ይናገራል። የመጀመሪያው መልእክት አንደኛ ጴጥሮስ ብለን የምንጠራው ነው (2ኛ ጴጥ. 3፡1)።

በዚህ አጭር መግቢያ ውስጥ ሁለት ጠቃሚ እውነቶችን ልንመለከት እንችላለን። በመጀመሪያ፥ ጴጥሮስ በአማኞች መካከል የደረጃ ልዩነቶችን ለመመልከት አልፈለገም። ምንም እንኳን እርሱ ክርስቶስን ያየና ሐዋርያዊ ሥልጣን ያለው ቢሆንም፥ በክርስቶስ የሚያምኑ ክርስቲያኖች ሁሉ ለእርሱ እኩል ነበሩ። በሮም ግዛት ውስጥ የተበተኑ አሕዛብ ክርስቲያኖች እምነት ልክ እንደ እርሱ እምነት ውድ ነበር። ሁለተኛ፥ ጴጥሮስ ስለ ክርስቶስ አምላክነት ግልጽ የሆኑትን ትምህርቶች ይሰጣል፡፡ ጴጥሮስ ክርስቶስን አምላክና አዳኝ ሲል ይጠራዋል።

2ኛ ጴጥሮስ የተጻፈበት ጊዜና ቦታ

የውይይት ጥያቄ፡– 2ኛ ጴጥ. 1፡12-15 አንብብ። ጴጥሮስ በቅርቡ ምን እንደሚደርስበት ይጠባበቃል?

ምንም እንኳን ጴጥሮስ የ2ኛ ጴጥሮስ መልእክትን በሚጽፍበት ጊዜ ገና እስር ቤት ውስጥ ባይገባም፥ ጴጥሮስ እንደሚሞት ያውቅ ነበር። ለዚህም ምክንያቱ ክርስቶስ በቅርቡ እንደሚሞት የገለጠለት መሆኑ ነው። 2ኛ ጴጥሮስ የተጻፈው ከ1ኛው የጴጥሮስ መልእክት በኋላ መሆኑ ግልጽ ነው (2ኛ ጴጥ. 3፡1)። ይሁንና፥ ከአንደኛው መልእክት በኋላ ሁለተኛው መልእክት ምን ያህል ዘግይቶ እንደ ተጻፈ አናውቅም። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚያመለክተው፥ ጴጥሮስ በሰማዕትነት የሞተው በኔሮ የስደት ዘመን ነበር። ኔሮ የሞተው 68 ዓ.ም ስለነበረ ጴጥሮስ ይህን መልእክት ከዚያ ቀደም ብሎ መጻፉ የተረጋገጠ ነው። በተለይ መልእክቱ 65-68 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የተጻፈ ይመስላል።

ጴጥሮስ ይህንን ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት የት እንደነበረ በትክክል ለማወቅ አይቻልም። ምናልባትም ከሮም ከተማ ለሁሉም አማኞች፥ በተለይም በትንሹ እስያ ለሚገኙ ክርስቲያኖች የጻፈ ይመስላል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: