ይሁዳ 1:1-25

አብያተ ክርስቲያናት ከሚጋፈጧቸው ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች አንዱ ሁልጊዜም ከቤተ ክርስቲያን ውስጥም ሆነ ውጭ ሐሰተኛ ትምህርትን የሚያሰራጩ ሰዎች መኖራቸው ነው። ከዚህም የተነሣ፥ አማኞች ሁሌም ሐሰተኛ አሳቦችን ለመዋጋት በተጠንቀቅ ላይ መሆን አለባቸው። ሰዎች ሁሉ እውነትን እንዲያውቁና እንዲያስተምሩ እንፈልጋለን። ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የማይከሰትበት ጊዜ ሞልቷል። ሰዎች የሚፈልጉትን እንዲያምኑ ዝም ብለን ብንተው ደግሞ ዘላለምን በሚያሳልፉበት ሁኔታ ላይ ለውጥ ይከሰታል። ስለሆነም እውነት የሆነውንና ሐሰቱን ለማወቅና ለመተንተን ባለማቋረጥ መዋጋት ይኖርብናል። ይህ ብዙውን ጊዜ አስደሳች ሂደት አይደለም። ሰዎች በእውነት በምንጋፈጣቸው ጊዜ ደስተኞች አይሆኑም። ይሁዳ ግን እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ እንደሚቆጣጠር በማስገንዘብ አሳቡን ይጀምራል። እግዚአብሔር ጠርቶናል፤ በእኛ ላይ ያለው ፍቅርም የሚቀጥል ነው። እግዚአብሔር በእምነታችን እውነተኞች ሆነን እንድንኖርም ሊረዳን ዝግጁ ነው ማለት ነው። ይሁዳ አጭር መልእክቱን የሚያጠቃልለው በዚሁ ተመሳሳይ አሳብ ነው። እግዚአብሔር ልጆቹ ለቃሉ ታማኞች ሆነው እንዲኖሩ ሊጠብቃቸው ይችላል። በፍርድ ቀን በፊቱ በሚቀርቡበት ጊዜ እነዚህን ከሐሰት ጋር የሚታገሉትን ደካማ ልጆቹን ፍጹማን አድርጎ ያቆማቸዋል (ይሁዳ 24)። ስለሆነም ይሁዳ ዓይኖቻችን በሐሰተኛ አተማሪዎች ችግሮችና በአብያተ ክርስቲያኖቻችን ላይ ከሚያደርሱት አደጋ ላይ ሳይሆን በሕይወታችን ውስጥ ተግቶ በሚሠራውና በንጽሕና እንድንቆም በሚያስችለን በታላቁ አምላካችን ላይ እንድናሳርፍ ያስገነዝበናል።

ይሁዳ ይህን ደብዳቤ ለመጻፍ ሲቀመጥ ስለ ድነት (ደኅንነት) የሚናገር ነገረ መለኮታዊ ደብዳቤ ለመጻፍ ነበር ያሰበው። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል እያደገ ስለመጣው እውነትን ቸል ስለማለት ይጽፍ ዘንድ አነሣሣው። ምናልባትም ከስፍራ ስፍራ እየተጓዙ የሚያገለግሉ አስተማሪዎች በሮም ግዛት ሁሉ ውስጥ እየተዟዟሩ ከወንጌሉ እውነት ጋር የማይሄድ ትምህርት የሚያስፋፉ ይመስላል። እነዚህ ሰዎች እንደ ሰላዮች አማኞችን መስለው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሠርገው በመግባት ክርስቲያኖችን ወደ ስሕተት ይመሩ ነበር። ይሁዳ በትዕግሥት ከመጸለይ ይልቅ አማኞች እውነትን ለይተው እንዲያውቁና እነዚህን ሐሰተኛ ትምህርቶች እንዲከላከሉ ለማገዝ ይህንን መልእክት ለመጻፍ ተነሣሣ። ሐሰተኛ ትምህርቶች በትዕግሥት በመጠበቃችንና በመጸለያችን ብቻ ሊርቁ አይችሉም። በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ ግልጽ ትምህርት መቅረቡ የግድ አስፈላጊ ነው።

በአብያተ ክርስቲያን ዙሪያ ሐሰተኛ ትምህርቶች በሚከሰቱበት ጊዜ አማኞች በተለይም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? ይሁዳ እውነትን መከላከል እንዳለብን ይናገራል። እውነት ልንቀበለው ወይም ልንተወው የምንችለው ተራ የሰው አስተሳሰብ አይደለም። ነገር ግን በጥንቃቄ ተጠብቆ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፉ የኖረ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነው። ይህም እውነት የእግዚአብሔር እውነት ነው፥ ምክንያቱም እውነት የሆነውንና ያልሆነውን የሚለየው እርሱ ብቻ ነው። ሰዎች የተሳሳተ ነው ብለው በማሰባቸው ምክንያት የእግዚአብሔር እውነት አይለወጥም። አንድን ታላቅ ግንብ በእጃችን ብንደበድበው አይፈርስም። የእውነትም ግንብ ሰዎች እውነት አይደለም ስላሉ አይፈርስም። አንድ ሰው የእግዚአብሔርን ቃል፥ ይሄኛው የእግዚአብሔር ቃል አካል እውነት ነው፥ ይኼኛው ስሕተት ነው ቢል፥ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ፈራጅ ነኝ ማለቱ ነው። ይህ ደግሞ ስሕተት ነው። ያለን መብት እውነቱን መቀበል ወይም መተው ብቻ ነው። ለፍላጎታችን እንደሚስማማ አድርገን ልንገመግመው ወይም ልንለውጠው አንችልም። ይሁዳ ይህ እውነት ለቅዱሳን እንደ ተሰጠ ይናገራል። እንዳይጠፋ ወይም እንዳይሰረቅ በማሰብ ባንክ ውስጥ እንደምናስገባው ውድ ንብረት የወንጌል እውነትም ቤተ ክርስቲያን ሳትለውጠው ጠብቃ ታቆየው ዘንድ የተሰጣት ንብረት ነው።

ቤተ ክርስቲያንን ያውኩ የነበሩት ሐሰተኛ ትምህርቶች ምን ምን ነበሩ? ይሁዳ ሁለት ዓይነት ችግሮችን ይጠቅሳል። በመጀመሪያ፥ እነዚህ አስተማሪዎች «የእግዚአብሔር ጸጋ ማለት አማኞች እንደፈለጋቸው ሊኖሩ የሚችሉበት መብት ነው።» ብለው ያስቡ ነበር። ይህም ግልጽ ኃጢአትን ይጨምራል። ሁለተኛ፥ አስተማሪዎች ክርስቶስ በፍጹም አምላክ፥ ሉዓላዊና ጌታ መሆኑን ይክዱ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩትን አንዳንድ ሐሰተኛ ትምህርቶች ዘርዝር። ይሁዳና የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ከተጋፈጧቸው ሐሰተኛ ትምህርቶች ጋር የሚመሳሰሉትና የሚለያዩት እንዴት ነው? ለ) በእውነት ዳርቻ ውስጥ ባለ ለየት ያለ ትኩረት (ተቀባይነት ያለው) እና የእውነትን መሠረት በሚያናጋ ሐሰት (ተቀባይነት የሌለው) መካከል ያለውን ልዩነት እንዴት ማወቅ እንደሚቻል ግለጽ።

፩. ለሐሰተኛ አስተማሪዎች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ (ይሁዳ 5-16)

  1. እውነትን ያጣጣሉ ሰዎች ስለደረሰባቸው ቅጣት የተሰጡ ታሪካዊ ምሳሌዎች (ይሁዳ 5-7)

ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ እንዲያምጹ የሚያስተባብሩትን ግለሰቦች መቃወም አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? እውነትን ተግተን የምንከላከለው ለምንድን ነው? ይሁዳ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክን በመቃኘት ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጠናል። ሰዎች እውነትን ሳያውቁ ወይም ሳይታዘዙ በሚቀሩበት ጊዜ ምን ይከሰታል? ሁልጊዜም የእግዚአብሔር ፍርድ ይገለጣል። ይሁዳ አያሌ ምሳሌዎችን በአጭሩ አቅርቦልናል። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በብዙ ተአምራት ከግብጽ ምድር ቢያወጣቸውም በኋላ ያልታዘዙትንና ያላመኑበትን ሁሉ አጥፍቶአቸዋል። ሁለተኛ፥ መላእክት እግዚአብሔርን ባልታዘዙት ጊዜ ለዘላለም ታስረው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል። ይህም የመጨረሻውን ፍርድ ከእግዚአብሔር ዘንድ እስከሚቀበሉበት ቀን ድረስ የሚቀጥል ይሆናል። ይህ ከአዳምና ሔዋን ውድቀት በፊት የነበረውን የሰይጣንና የመላእክቶቹን ሁኔታ ወይም ደግሞ በይበልጥ በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ውስጥ የተጠቀሱትን መላእክት (የእግዚአብሔር ልጆች) የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ሦስተኛ፥ ሰዶምና ገሞራ በክፉ ባህሪያቸው ምክንያት ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። የእነዚህ ሰዎች በእሳት መጥፋት ዛሬ ወሲባዊ እርኩሰት እየፈጸሙ የሚኖሩ ሰዎች የሚጋፈጡትን የሲኦል እሳት በምሳሌነት የሚያሳይ ነው።

  1. በይሁዳ ዘመን እውነት የማይቀበሉ ሰዎች አኗኗር (ይሁዳ 8-16)

የሐሰተኛ አስተማሪዎች ባሕርያት ምን ምን ናቸው? በይሁዳ ዘመን የነበሩት የሐሰተኛ አስተማሪዎች ባሕርያት ምን ይመስሉ ነበር? እግዚአብሔር የሚፈርድባቸው በእነዚህ ባህሪዎቻቸው ሳቢያ ነበር። ይሁዳ፥ ዛሬ ሐሰተኛ አስተማሪዎችን ለመለየት የሚያግዙንን ብዙ ባሕርያት ይዘረዝራል። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ከሚከተሉት ባሕርያት በአንዱ ወይም ካአንድ በሚበዙት ራሳቸውን ይገልጣሉ።

ሀ) እንደ ሰዶምና ገሞራ በወሲባዊ እርኩሰት ሰውነታቸውን ያቆሽሻሉ።

ለ) ሐሰተኛ አስተማሪዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እግዚአብሔር የወሰነውን ሥልጣን ይንቃሉ። እነዚህ አስተማሪዎች ራሳቸውን ትክክለኞች፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ግን የተሳሳቱ አድርገው ይመለከታሉ። ስለ አከራካሪ ጉዳዮች ለመወያየት ፈቃደኞች አይደሉም። ውሸትን እንዳያስተምሩ ሲነገራቸው አይታዘዙም።

ሐ) ሰማያዊ አካላትን ይሳደባሉ። ይህ ምንን እንደሚያመለክት አናውቅም። ምናልባትም ሐሰተኛ አስተማሪዎች በሰይጣንና አጋንንቱ ወይም መላእክት ላይ የሚሳለቁ ይመስላል። ይህንንም የሚያደርጉት እንዳሻቸው ሊኖሩ እንደሚችሉና ሰይጣን ወይም መላእክት ምንም እንደማያደርጓቸው በመግለጽ ነበር። የመላእክት አለቃ የሆነው ሚካኤል እንኳን በራሱ ኃይል ሰይጣንን እንደማይረግምና በትሕትና ወደ እግዚአብሔር ኃይል እንደሚያመለክት ይሁዳ ይህን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆነ ታሪክ ጠቅሶ አስረድቷል። ምዕራባውያን ቀንዶችና ጭራ ያለው ቀይ ሰይጣን በፊልማቸው ውስጥ ይጠቀማሉ። ሰዎችን የሚዋጋበት ሹል ነገርም ይኖረዋል። የፊልም ሠሪዎቹ በዚህ ዓይነት በሰይጣን ላይ ይሳለቃሉ። ኃይል እንዳለው ጠላት ሳይሆን በአሳብ የተፈጠረ አድርገው ያቀርቡታል። በመላእክትም ላይ እንዲሁ ይሳለቃሉ። እግዚአብሔር በሰይጣንም ሆነ መላእክት ላይ እንዳንሳለቅ ያስጠነቅቀናል።

መ. ይሁዳ የሐሰተኛ አስተማሪዎችን ባሕሪ ለማሳየት ሦስት የብሉይ ኪዳን ምሳሌዎችን ጠቅሷል።

  1. እንደ ቃየል የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ላለመስማት ይመርጣሉ። ጥፋታቸውን አምነው ንስሐ ከመግባት ይልቅ ሰው  መግደልን ይመርጣሉ (ዘፍጥ. 4፡3-4)።
  2. እንደ በለዓም ለገንዘብ ካላቸው ፍቅር የተነሣ የእግዚአብሔርን ቃል ይጠመዝዛሉ። አልያም በእግዚአብሔር ቃል ዙሪያ በመሄድ የእግዚአብሔርን ሰው ወደ እርኩሰት ይመራሉ (ዘኁል. 31፡16-19 እንብብ)።
  3. እንደ ቆሬ እግዚአብሔር የሾማቸውን መሪዎች አንታዘዝም ይላሉ (ዘኁል16)።

ሠ. ይሁዳ በመቀጠል የሐሰተኛ አስተማሪዎችን ባህሪ በስድስት ምሳሌዎች ያብራራል።

1) ለኃጢአታቸው ይቅርታ ሳይጠይቁ በግድየለሽነት የጌታን ራት (የፍቅር ግብዣ) ይበላሉ።

2) ለራሳቸው እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ምእመናን የማይገዳቸው ራስ ወዳድ እረኞች (የቤተ ክርስቲያን መሪዎች) ናቸው።

3) ዝናብ እንደማያስገኝ ደመናዎች ብዙ ተስፋ ቢሰጡም፥ ምንም ነገር አያደርጉም።

4) ከሥር በስተቀር ፍሬ እንደሌለባቸው የበልግ ዛፎች መንፈሳዊ ፍሬ ያላቸው መስለው ሲታዩ፥ የስደት ወይም የመከራ ነፋስ በሚነፍስበት ጊዜ በቀላሉ ይነቀላሉ። ስደትን በመሸሽ ብዙውን ጊዜ ከቦታ ቦታ ይዘዋወራሉ። ይህም ዘላቂ ተግባር ወይም ፍሬ በአንድ አካባቢ እንዳያሳዩ ያደርጋቸዋል።

5) እንደ ኃይለኛ ማዕበል ባለማቋረጥ ሥራቸውና እምነታቸውን ስለሚለውጡ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ያነሣሣሉ። ባለማቋረጥ የሚጣደፉ ቢሆንም፥ በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር አይሆኑም። የተረጋጉና በሕይወታቸው የበሰሉ አይደሉም።

6) እንደ ተቅበዝባዥ ከዋክብት (ተወርዋሪ ከዋክብት) ደምቆ የሚታይ አስደናቂ አገልግሎት ቢኖራቸውም፥ ብዙም ሳይቆይ ይከስማል። እነዚህ ሰዎች ወደ መጨረሻ ፍርዳቸው እየተቃረቡ የሚሄዱ ናቸው።

ረ) ሐሰተኛ አስተማሪዎች ሁልጊዜም ያጉረመርማሉ። የሌሎችን ስሕተቶች ፈልፍለው ያወጣሉ። አገልግሎታቸው የሰዎችን ሕይወትና ዝና ያጠፋል እንጂ አይገነባም። ከራሳቸው በስተቀር ለማንም ስለማይገዳቸው፥ ሁልጊዜም እነርሱ የሚያስቡት ትክክል ይመስላቸዋል። ሐሰተኛ አስተማሪዎች ስለ እራሳቸው፥ ስለ መንፈሳዊነታቸው፥ ስለ ስጦታቸውና ስለ እውቀታቸው በትምክህት ይናገራሉ። ከሌሎች ጋር በሚነጋገሩበት ጊዜ ሁልጊዜም የራሳቸውን ተግባር ከፍ አድርገው በማሳየት ራሳቸውን ያንቆለጳጵሳሉ። (ይሁዳ እነዚህ ሰዎች ፈሪሃ እግዚአብሔር የራቃቸው መሆኑን በተደጋጋሚ እንደሚያመለክት ልብ ብለህ አስተውል። መንፈሳውያን መስሎ ለመታየት የሚጥሩ ሃይማኖተኞች ቢሆኑም እንደ እውነቱ ከሆነ በእግዚአብሔር ላይ ያምጹ ነበር።)

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ያጋጠሙህን የተለያዩ ሐሰተኛ አስተማሪዎች አስብ። የእነዚህን ሰዎች ሕይወት በይሁዳ መልእክት ውስጥ ከተገለጸው ጋር አነጻጽር። በሕይወታቸው ውስጥ የተመለከትካቸው ባሕርያት የትኞቹ ናቸው? ለ) በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ችግሮች የሚፈጥሩትን ሰዎች በምናገኝበት ጊዜ እነዚህን የሐሰተኛ አስተማሪዎች ባሕርያት ማስታወሱ ማን ከእግዚአብሔር ማን ደግሞ ከሰይጣን እንደሆነ ለመለየት እንዴት ያስችለናል?

ይሁዳ፥ እግዚአብሔር በእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ላይ ፍርዱን እንደሚገልጥ ይናገራል። አሁንም ይሁዳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተገኘ ሌላ ታሪክ ይጠቅሳል። ይህም ከመጽሐፈ ሄኖክ የተወሰደ ነው። እግዚአብሔር ሄኖክን ወደ ሰማይ ከመውሰዱ በፊት ሄኖክ እግዚአብሔር ከመላእክቱ ጋር እንደሚመለስ የተነበየ መሆኑን ይናገራል። በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር በሰዎች ሁሉ ላይ ፍርድን ይሰጣል። በእግዚአብሔር ላይ ያመጹት ክፉ ሰዎች የዘላለም ፍርድ ይቀበላሉ። ይሁዳ ለአማኞች ክርስቶስ በቶሎ እንደሚመለስ ያሳስባቸዋል። እርሱ በሚመለስበት ጊዜ ሰዎችን እንደየሥራቸው በመለየት ይፈርድባቸዋል። እውነትን በመጠምዘዝ ለራስ ወዳድነት ፍላጎቶቻቸው ባደሩት ላይ ፍርዱን ይገልጻል።

፪. የእግዚአብሔር ሕዝብ እንዴት መኖር እንዳለበት የሚያስገነዝብ ትምህርት (ይሁዳ 17-23)

ሐሰተኛ ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያን ላይ ጥቃት በሚሰነዝሩበት ጊዜ ተግተን እውነትን ልንጠብቅና ሐሰተኛ አስተማሪዎችን ልናጋልጥ እንደሚገባን ይሁዳ ያስገነዝበናል። እነዚህን ሐሰተኛ አስተማሪዎች ለይቶ ለማወቅ የአኗኗር ዘይቤአቸውን፥ ለሥልጣን ያላቸውን አመለካከትና ውዳሴ መፈለጋቸውን ማጤኑ ጠቃሚ ይሆናል። በተጨማሪም ይሁዳ፥ አማኞች በሐሰተኛ ትምህርቶች ሳይወሰዱ ቅዱሳንና ንጹሐን ሆነው ለመታየት ሊያደርጓቸው የሚገቧቸውን አንዳንድ አዎንታዊ ነገሮችን ይዘረዝራል።

  1. ሁልጊዜም ክርስቶስ በቶሎ እንደሚመለስ በማሰብ ከእርሱ ጋር ለመገናኘት ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን። ይህም በመንፈስ ቅዱስ እንድንሞላ ያግዘናል። መንፈስ ቅዱስ ወደ እውነት ሁሉ ይመራናል። ሐሰተኛ ትምህርቶችን ለመፈተንና ለማሸነፍ እንድንችልም ያግዘናል።
  2. አማኞች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ማደጋቸውን መቀጠል አለባቸው። ይህንንም የሚያደርጉት «ቅዱስ እምነት» የተባለውን በመከተል፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል በመኖር ነው።
  3. በመንፈስ የመጸለይ ልማድ ልናዳብር ይገባል። ይሁዳ ይህን ሲል በልሳን መጸለይን ወይም በሌሎች የመንፈስ ቅዱስን ቁጥጥር በሚያሳዩ መንገዶች መጸለይን ማመልከቱ አይደለም። ነገር ግን ሕይወታችንን ለእግዚአብሔር ቃል አሳልፈን በሰጠን ቁጥር መንፈስ ቅዱስ አሳባችንንና ጸሎታችንን እንደሚመራ ለመግለጽ ነው። ይህም ሲሆን ጸሎታችን በእውነት ላይ የተመሠረተ ይሆናል። መንፈሳዊ መስለው እየታዩ ዳሩ ግን በተግባራቸው ኃጢአተኞችና መንፈስ ቅዱስ የሌለባቸው መሆናቸውን እንደሚያሳዩ ሐሰተኛ አስተማሪዎች መሆን የለብንም።
  4. የክርስቶስን ዳግም ምጽአት በምንጠባበቅበት ጊዜ በእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ መሆን አለብን። በሁለንተናችን እግዚአብሔርን መውደዳችንን መቀጠል አለብን። እንዲሁም አማኞች እግዚአብሔር በሰጠን ፍቅር እርስ በርሳችን መዋደድ ይኖርብናል።
  5. የሰዎች ትምህርቶችና የተሳሳቱ ተግባራት እንዳያበላሹን እየተጠነቀቅን ሰዎችን ወደ እውነትና እግዚአብሔርን ወደ መምሰል ጎዳና ልንመልሳቸው ይገባል።

፫. አማኞችን ከውድቀት ለሚጠብቀው ታላቁ አምላክ የቀረበ ምስጋና (ይሁዳ 24-25)

ይሁዳ ሐሰተኛ ትምህርትን በጽኑ በማስጠንቀቅ መልእክቱን ያጠቃልላል። በቡራኬው፥ ይሁዳ አማኞች እግዚአብሔር ከእኛ እንዳልተለየና በሕይወታችን ውስጥ በትጋት እንደሚሠራ ይገልጻል። ለእውነት ታማኞች ሆነን እንድንቆም የሚረዳን እርሱ ነው። ኃጢአትን የምንቋቋምበት ኃይል የሚሰጠን እርሱ ነው። በክርስቶስ ፊት በምንቀርብበት ጊዜ ከኃፍረትና ሐዘን ይልቅ ታላቅ ደስታ ይጠብቀናል። በዚያን ጊዜ እንከን የለሽ ሆነን እንቀርባለን።

የውይይት ጥያቄ፡– ከይሁዳ መልእክት የተማርካቸውን ጠቃሚ እውነቶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: