የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ታሪክ ጥናት

የውይይት ጥያቄ፥ የዓለምን፥ የኢትዮጵያንና የራስህንም ነገድ የሚመለከቱ ታሪኮችን ማወቅ ለምን ያስፈልጋል?

ሕይወታችን በሙሉ በታሪክ፥ ወይም ባለፈው ጊዜ በእኛ ሕይወት ውስጥ በተፈጸመውም ሆነ በዓለም ዙሪያ በመሆን ላይ ባሉት ክስተቶች ተጽእኖ ሥር ነው። ለምሳሌ፡- ኢጣሊያን፥ ሩሲያን፥ አሜሪካን፥ እንግሊዝን፥ ወዘተ ሳናውቅና ከኢትዮጵያ ጋር ስላላቸው ግንኙነት ሳንረዳ፥ አዲሲቷን ኢትዮጵያ መረዳት ያስቸግረናል። እነዚህ ሕዝቦች ሁሉ በኢትዮጵያ ላይ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተጽእኖ ስለነበራቸው ያ ተጽዕኖ አሁንም ድረስ ውጤት አለው። እንዲሁም ደግሞ የምኒልክን ወይም የኃይለ ሥላሴን መንግሥት ሥረ-መሠረት ሳናውቅ አዲሲቷን ኢትዮጵያን ለመረዳት አንችልም። ለእነዚህ የተለያዩ ሕዝቦችና አገሮች ያለን አመለካከት የተለያየ ቢሆንም፥ ሁሉም ግን በእኛ ላይ ያሳደሩት ተጽዕኖ አለ። ያለፉትን ክስተቶች የበለጠ በተረዳን ቁጥር በአሁኑ ጊዜ በአገራችን የሚደረገውን ነገር በተሻለ ሁኔታ እየተረዳን እንሄዳለን። 

መጽሐፍ ቅዱስን ስለመረዳትም ተመሳሳይ ነገር ማለት ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ መጽሐፍ ነው። በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተጻፉ ታሪኮች ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጸሙ የእውነተኛ ክስተቶች ታሪክ ነው። በዚያ ዘመን የነበሩ ታሪኮችንና የምድሪቱን ሁኔታ የበለጠ በተረዳን ቁጥር፥ መጽሐፍ ቅዱስን በተሻለ ሁኔታ እንረዳለን። ለምሳሌ በከነዓን ምድር ላይ የነበራቸውን ሚና ለመረዳት ስለ ግብፅ፥ ባቢሎን፥ ፋርስ፥ ሮም፥ ግሪክ ወዘተ ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው። የአይሁድና የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ከዓለም ታሪክ ጋር የተሳሰረ ነው። ይሁን እንጂ ከዓለም አመለካከት አንጻር አይሁድ በዓለም ታሪክ ውስጥ መጠነኛ ሚና ተጫውተዋል። ከእግዚአብሔር አመለካከት አንጻር ግን የታሪክ እምብርት ናቸው። እግዚአብሔር ስለመረጣቸው፥ መጽሐፍ ቅዱስን በእነርሱ በኩል ስለሰጠ፥ መሢሑ ኢየሱስ ክርስቶስን ወደዚህ ዓለም በእነርሱ በኩል ስለላከ ወዘተ. አይሁድ ከሌላው ሕዝብ ሁሉ ይልቅ እጅግ አስፈላጊ ሕዝብ ናቸው። ይህም ማለት አይሁድ በትውልዳቸው ከሌላ ዘር የተሻሉ ናቸው ማለት አይደለም። ነገር ግን ዓለምን በካህንነት እንዲያገለግሉ በእግዚአብሔር ተመርጠው ነበር፤ (ዘጸ. 19፡5-6)።

ብሉይ ኪዳን የዓለምን ሕዝቦች ታሪክ ለመናገር አይፈልግም። በግብፅና በመሰጴጦምያ ስለነበሩት አስደናቂ የሥልጣኔ ክስተቶች አያስተምርም፡፡ እነዚህን ሕዝቦች የሚጠቅሰው ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በነበራቸው ግንኙነት አንጻር ብቻ ነው። ብሉይ ኪዳን ከምዕራቡ ዓለምና ከመካከለኛው ምሥራቅ አስቀድሞ ስለታየው የቻይና ታላቅ ሥልጣኔ የሚናገረው ነገር የለም።

ብሉይ ኪዳን እጅግ ጥንታዊ መጽሐፍ ነው። በውስጡ የያዛቸው ታሪኮች ወደማይታወቅ ኋለኛ ዘመን ይሄዳሉ፤ ስለዚህ አንዳንድ ድርጊቶች የተፈጸሙበትን ዘመን መናገር አስቸጋሪ ነው። ለምሳሌ፡- ዓለም የተፈጠረችበትን አዳምና ሔዋን በምድር ላይ መኖር የጀመሩበትን ዘመን በትክክል መናገር የሚቻልበት መንገድ የለም፤ ነገር ግን በከርሰ-ምድር ጥናት አማካይነት እርግጠኛ ልንሆንባቸው የምንችል ድርጊቶች የተፈጸሙባቸው ዘመናትም አሉ። ለምሳሌ፡- አብዛኛዎቹ የእስራኤል ነገሥታት የነገሡበትን ጊዜ በአንድና በሁለት ዓመት ልዩነት መወሰን ይቻላል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የሚከተሉትን ሰዎች በታሪካዊ ቅደም ተከተል አስቀምጥ፡- ዳዊት፥ አዳምና ሔዋን፥ ሄኖክ፥ ኖኅ፥ ሳኦል፥ አብርሃም፥ ሰሎሞን። ለ) በብሉይ ኪዳን ታሪክ ውስጥ እጅግ ጠቃሚ ሚና የተጫወቱ ሌሎች የብሉይ ኪዳን ሰዎችን ጥቀስ።

የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ መንገዶች የታሪክን ዘመናት ይቆጥራሉ። ቻይናዎች የራሳቸው መንገድ አላቸው። አይሁድ ከፍጥረት ጀመረ ብለው የሚናገሩት የራሳቸው መንገድ አላቸው። ክርስቲያኖችም የራሳቸው መንገድ አላቸው። ዛሬ አብዛኛው የዓለም ሕዝብ የክርስቲያንን የቀን መቁጠሪያ ይከተላል። ክርስቲያኖች ታሪክን በሁለት ታላላቅ ዘመናት ይከፍሉታል። የመጀመሪያው ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት (ዓመተ ዓለም) ይባላል። ይህ ዘመን ከዓለም ፍጥረት ይጀምርና እስከ ክርስቶስ መወለድ ድረስ ይቀጥላል። ሁለተኛው ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያለው ሲሆን በአማርኛ ዓመተ ምሕረት (ዓ.ም.) ብለን እንጠራዋለን። (በእንግሊዝኛ ኤ.ዲ. ተብሎ ሲታወቅ የመጣውም ከላቲኑ «አኖ ዶሚኒ» ማለትም «የጌታችን ዓመት» ነው።) በክርስቲያኖች የቀን መቁጠሪያ ዓመቱ ወደ ኢየሱስ ልደት በቀረበ መጠን ቁጥሩ እየቀነሰ ይመጣል። ከክርስቶስ ልደት በኋላ ቁጥሩ እየጨመረ ይመጣል። የሚከተለውን መግለጫ ተመልከት፡-

አብርሃም (2000 ዓ.ዓ.) 

                  ዳዊት (1000 ዓ.ዓ.)

                                 ክርስቶስ (አልቦ ዜሮ (0) ዓ.ዓ.)

                                                          አሁን (2019 ዓ.ም.)

በብሉይ ኪዳን ዘመን ቁጥሩ እንዴት እያነሰ ይሄድ እንደነበር ወደ ክርስቶስ ደግሞ እየቀረበ እንደመጣ ከከላይ የቀረበወን ገለጻ ልብ በል። ከክርስቶስ በፊት በ2000 ዓመታት ገደማ የኖረው አብርሃም ከክርስቶስ ልደት በፊት 1000 ዓ.ዓ. ገደማ ከኖረው ከዳዊት ዘመን የበለጠ ቁጥር አለው። በሌላ አንጻር ስናየው ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደ ሁለት ሺህ አስራ ዘጠኝ ዓመታት አልፈዋል ማለት ነው።

በኢትዮጵያና በአውርጳ የዘመን አቆጣጠር መካከል ልዩነት የሚታየው ለምንድነው? ምክንያቱ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን ጊዜ በሚመለከት አለመግባባት በመኖሩ ነው። ሰዎች የክርስቲያንን የቀን መቁጠሪያ ይጠቀማሉ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ዘመን ቀን አቆጣጠርን ማንም አልጀመረም። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ መቼ እንደተወለደ ትክክለኛውን ጊዜ ሊያውቁ አልቻሉም። ምዕራባውያን አገሮች የተከተሉት ግሪጐሪ የተባለው ሰው የጀመረበትን የቀን አቆጣጠር ነበር። ይህም የቀን መቁጠሪያ በ1582 ዓ.ም. የጀመረ ሲሆን የግሪጐሪያን የቀን መቁጠሪያ በመባል ይታወቃል። ኢትዮጵያ ደግሞ ሌላ ቀን መቁጠሪያን ትጠቀማለች። ሁለቱም የቀን መቁጠሪያዎች አዲሱን ዘመን የሚጀምሩት ከኢየሱስ ልደት ቢሆንም፣ እነዚህ የቀን መቁጠሪያዎች በስምንት ዓመታት ይለያያሉ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ በተለያዩ ክፍለ ጊዜያት ይከፍላሉ። ቀጥሉ በብሉይ ኪዳን ያለውን የእስራኤል ታሪክ ባጭሩ እንመለከታለን።

፩. ከአይሁድ የእምነት አባቶች (ፓትሪያርኮች) በፊት የነበረው ዘመን (2500-2000 ዓ.ዓ.)

ከዘፍ. 1-11 የጥንት ታሪኮችን አጭር መግለጫ እንመለከታለን። ታሪኩ የሚጀምረው የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ከተፈጠሩበት አጠቃላይ ታሪክ አጀማመር ነው። እግዚአብሔር ዓለምን እንዲሁም አዳምንና ሔዋንን የፈጠረበትን ጊዜ የሚያውቅ ማንም የለም። በእነዚህ የኦሪት ዘፍጥረት 11 ምዕራፎች የብዙ ሺህ ዓመታት ታሪክ አጠር ባለ መልኩ ቀርቧል። የእነዚህ ምዕራፎች ዋና ዓላማ ዓለም እንዴት እንደተጀመረች፥ ኃጢአት በዓለም እንዴት እንደተስፋፋ እንዲሁም ከአዳም እስከ አብርሃም ያለውን የአይሁድ የዘር ሐረግ ለመከተል ነው። 

አይሁድ ሴማውያን ከተባሉ ዘሮች የተገኙ ነገዶች ወይም የሴም ዝርያ ናቸው። ሴማውያን በብዛት የሚኖሩት በመካከለኛው ምሥራቅ፥ በኤፍራጥስና በጤግሮስ ወንዞች መካከል በሚገኘውና መሰጴጦምይ በተባለው ሥፍራ ነው። የጥንት ሥልጣኔ የተጀመረው በዚያ ስፍራ ነው። ጽሑፍ፥ ሒሣብ፥ ሥነ ጥበብ፥ ሕግ፥ ሕክምና፥ ወዘተ በመጀመሪያ የተጀመረው በዚህ ስፍራ ነው። በ2100 ዓ.ዓ. ገደማ የመሰጴጦምያ ዋና ከተማ በደቡብ መሰጴጦምያ የምትገኘው የዑር ከተማ ነበረች። የደቡብ መሰጴጦምያን አብዛኛዎቹን ክፍሎች በሚቆጣጠር በአንድ ንጉሥ ሥር የምትገዛ ነበረች። ይህ ሁኔታ ባስገኘው ሰላም ምክንያት ለሥልጣኔ በፍጥነት ማደግ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። አብርሃምና አባቱ ካራን የመጡት ከዚህ ስፍራ እንደነበር እናያለን። አብርሃም የኖረበትን ትክክለኛ ዘመን ባናውቅም እንኳ፥ ዑርን ትቶ ወደ ከነዓን የሄደው በዚህ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ነው፡፡ 

ይህ ከተማ በሥልጣኔ ያደገና የላቀ እንደነበረ ማወቃችን፥ አብርሃም በሥልጣኔ እጅግ የበለፀገችውን አገር ትቶ ኋላ ቀር ወደ ሆነችው ወደ ከነዓን ለመሄድ ያደረገውን አስቸጋሪ ምርጫ ያሳየናል። እግዚአብሔር ሰውን ከአዲስ አበባ ወጥቶ በሐመር ባኮ፥ ወይም ራቅ ካሉ አካባቢዎች በአንዱ እንዲኖር የተናገረውን ያህል ነው። ምርጫው አስቸጋሪ ነበር። አብርሃም ያደረገውን በእምነት የመታዘዝ ከፍተኛ እርምጃ ያሳየናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዑርን ለቆ እንዲወጣ እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው ትእዛዝ አስቸጋሪ የነበረው ለምንድነው? ለ) ዛሬ እግዚአብሔር ለእኛ የሚሰጠን አስቸጋሪ የሆነ ተመሳሳይ ትእዛዝ ምንድነው? (ማቴ. 28፡19-20 ተመልከት)። ሐ) በአሁኑ ጊዜ የአብርሃም ምሳሌነት ለእኛ መልካም ትምህርት የሚሰጠን እንዴት ነው? 

፪. የአይሁድ የእምነት አባቶች (የፓትሪያርኮች) ዘመን (2000-1600 ዓ.ዓ.)

በእነዚህ ዓመታት የዑር ከተማ ኃይል ማሽቆልቆል ጀመረ። መሰጴጦምያ በአንድ ንጉሥ መገዛቷ ቀረና «የከተማ ግዛቶች» ወደሚባሉ ትናንሽ ክልሉች ተከፋፈለች። ይህም ማለት ዋና ዋናዎቹ ከተሞች በአካባቢያቸው ያሉ ክልሉችን ሁሉ መቆጣጠር ጀመሩ። በእያንዳንዱ ከተማም ንጉሥ ነበር። ይሁን እንጂ ሕዝቡ እንደ ቀድሞው ታላቅና ኃያላን አልነበሩም። ይህም በተለይ የከነዓንን ምድር በሚመለከት እውነት ነበር። እያንዳንዱ ከተማ በንጉሥ ቁጥጥር ሥር ነበር።

አብርሃም፥ ይስሐቅና ያዕቆብ በከነዓን ምድር ይኖሩ በነበሩበት ጊዜ ምድሪቱ በሕዝብ ብዛት አልተጨናነቀችም ነበር። ይህ ማለት ከተለያዩ ነገዶች ጋር ሳይጋጩ በነፃነት ይንቀሳቀሱ ነበር ማለት ነው።

በእነዚህ ዓመታት የግብፅ አገር በአካባቢው ባሉ አገሮች ላይ የነበራት የበላይነት እያየለ መጣ። የከነዓንን ምድር ክልል ከዕለት ወደ ዕለት እየተቆጣጠረች መጣች። እንደሚታወሰው አብርሃም፥ ያዕቆብና ዮሴፍ ግብፅን ጎብኝተዋል። በእነዚህ ዓመታት ዮሴፍ በግብፅ ውስጥ በይበልጥ ሁለተኛው ኃያል መሪ ሆኖ ነበር።

ከዘፍጥረት 12-50 ያሉት ታሪኮችና መጽሐፈ ኢዮብ በዚህ የታሪክ ክፍለ ጊዜ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። 

፫. ግብፅ እስከ ዘመነ መሳፍንት (1600-1200 ዓ.ዓ.) 

የግብፅ አገር ሥልጣኔ የጀመረው በ3100 ዓ.ዓ. ነው። ከ2700-2200 ዓ.ዓ. ባሉት ዘመናት ግብፅ እጅግ ኃያል ሆነች በከነዓንም ላይ በከፍተኛ ደረጃ የበላይ ሆነች። እስካሁን ድረስ በግብፅ የሚታዩት አንዳንዶቹ ትላልቅ ፒራሚዶች የተሠሩት በዚህ ጊዜ ነው።

ነገር ግን ከ1800-1600 ዓ.ዓ. ከሶርያና ከከነዓን የመጡ «ሐይክሰስ» የተባሉ ነገዶች ግብፅን ተቆጣጠሩ። ይህም የግብፅ ኃይል እየተዳከመ የመጣበት ጊዜ ነበር። በእነዚህ ዓመታት ነበር በግብፅ የነበሩ ከ70 የማይበልጡ አይሁድ እስከ ከ1 ሚሊዮን በላይ የሆኑት።

በ1600 ዓ.ዓ. አካባቢ ግብፆች ዓመፁና እንደገና የራሳቸውን አገር ማስተዳደር ጀመሩ። ግብፆች የምድራቸው አብዛኛውን ክፍል የወሰዱባቸውን «የውጭ አገር ዜጎች» ጠሏቸው። ስለዚህ የቻሏቸውን ባሪያዎች ሲያደርጉ፥ ሌሎቹን ከአገር አስወጧቸው። አይሁድ በግብፃውያን ባርነት ቀንበር ሥር የወደቁት በዚህ ዘመን ነበር። በዚህ ጊዜ ግብፃውያን ደቡብ ሱዳንን፥ ከነዓንን በሙሉ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያሉትን መንገዶች ያዙ። ግብፅ እንደገና ኃያል አገር ሆነች።

ነገር ግን በ1400 ዓ.ዓ. የግብፅ ኃይልና የበላይነት ማሽቆልቆል ጀመረ። በፍልስጥኤም ላይ የነበራቸውን አገዛዝ አጡ። ብዙዎቹ ምሁራን እንደሚያስቡት አይሁድ በግብፅ ከነበሩበት ግዞት ወጥተው ከነዓን በመድረስ የራሳቸውን አገር ያቋቋሙት በዚህ ጊዜ ነበር። ይህንን ከኦሪት ዘጸአት ጀምሮ እስከ መሳፍንት ባሉት ክፍሎች ውስጥ እናገኘዋለን። መጽሐፈ ሩት የተፈጸመውም በዚህ የታሪክ ወቅት ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔር የግብፅን ታሪክ በመቆጣጠር ለሕዝቡ ጥቅም ያዋለው እንዴት ነው? ከ1400-1200 ዓ.ዓ. ከነዓን የታላላቅ ኃያላን መንግሥታት የጦርነት ሜዳ ሆነች። በሰሜን በኩል ወደ ከነዓን ዘልቀው በመግባት ጥቃት የሚያደርሱ ኬጢያውያን በመባል የሚታወቁ ነገዶች ነበሩ። በደቡብ በኩል ግብፆች የከነዓንን ድንበር ተቆጣጥረው ለመቆየት ይዋጉ ነበር።

ከነዓን በጣም ጠቃሚ የነበረችው ለምንድነው? የተለያዩ ሁለት አህጉሮች መገናኛ ስለነበረች ነው:- በደቡብ በኩል አፍሪካ፥ በሰሜን ደግሞ እስያ፡፡ ከግብፅ ወደ መሰጴጦምያ የሚያልፉ ሁለት እጅግ ጠቃሚ የንግድ መሥመሮች ነበሩ። ከነዓን በስተምሥራቅ ያለው ምድረ በዳ ብቻ ስለሆነና በምዕራብ በኩል ደግሞ የሜዴትራኒያን ባሕር ስለነበር፥ ነጋዴዎች በደቡብ በኩል ካለው ከግብፅ ወደ ሰሜኑ መሰጴጦምያ ለመሄድ በከነዓን ማለፍ ግድ ሆኖባቸው ነበር፤ እነዚህን የንግድ መሥመሮች የተቆጣጠረ ማንኛውም ከፍል ባለጸጋ ሆነ፤ ስለዚህ ውሾች በአጥንት ላይ እንደሚጣሉ እነዚህ አገሮች በከነዓን ላይ የበላይ ለመሆን ይዋጉ ነበር።

በዚህ ጊዜ ነበር መሳፍንት በእስራኤል የገዙት። በመሳፍንት ክፍለ ዘመን ያለማቋረጥ የምናነበው እግዚአብሔር ረድቶአቸው ነፃ እስኪያወጣቸው ድረስ የተለያዩ ነገዶች እስራኤልን ይገዙ እንደ ነበር ነው።

በ1200 ዓ.ዓ. ግብፅ ኃይሏን አስተባበረችና ከነዓንን መቆጣጠር ጀመረች። ይህ ማለት በግብፆችና በኬጢያውያን መካከል ከፍተኛ ጦርነት ነበር ማለት ነው። ኬጢያውያን ተሸነፉ። ዳሩ ግን በጦርነቱ ጦስ በከነዓን ዙሪያ የነበሩ በርካታ ከተሞች ተደመሰሱ።

፬. የኋለኛው የመሳፍንት ዘመንና የሳኦል ዘመን (1200-1000 ዓ.ዓ.)

ግብፆች ኬጢያውያንን ቢያሸንፉም እንኳ ኃይላቸው ለረጅም ጊዜ አልቆየም። ኃይላችው ወዲያውኑ ያሽቆለቁል ጀመር። በውጤቱም በከነዓን ላይ የነበራቸውን አንዳንድ የበላይነት አጡ። በእነዚህ ዓመታት አንድ አዲስ ነገድ ወደ ከነዓን ምድር መግባት ጀመረ። ከሜዲትራኒያን ባሕር ደሴቶች የመጡ በመሆናቸው «የባሕር ሰዎች» በመባል ይታወቁ ነበር። ከባሕር ሰዎች መካከል አንዱ ቡድን ፍልስጥኤማውያን በመባል ይታወቁ ነበር። ከዘመነ መሳፍንት መጨረሻ ጀምሮ በዘመነ ነገሥታት ሁሉ ፍልስጥኤማውያን ዋናዎቹ የአይሁድ ጠላቶች ነበሩ። ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤላውያን የበለጠ በእውቀት የላቁ ነበሩ። በዚህ ዘመን ነበር የብረት መሣሪያዎችን የመሥራት ዘዴዎች ማወቅ የጀመሩት። 

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ሳሙ. 13፡19-23 አንብብ። ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን እንዲቆጣጠሩ ይህ እውቀት እንዴት ረዳቸው?

የመጨረሻዎቹ መሳፍንት ከነበሩት ከሳምሶንና ከሳሙኤል ጀምሮ እስከ ዳዊት መንገሥ ድረስ ፍልስጥኤማውያን አብዛኛውን እስራኤልን ይቆጣጠሩ ነበር። በእነዚህ ዓመታት ማንም እንደ ግብፅ ያለ ታላቅ መንግሥት ፍልስጥኤምን የገዛ አልነበረም። ይህ ዘመን የታየው በዘመነ መሳፍንት መጨረሻና በ1ኛ ሳሙኤል ላይ ነው።

* (ማሳሰቢያ፡- ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በእነዚህ ጳለስጢና፥ ጳለስጢናውያንና ፍልስጥኤማውያን የተባሉት የተለያዩ ስሞች የግንዛቤ ችግር አለ። ጳለስጢና የሚለው ስም ከሜዲትራኒያን ደሴቶች ፈልሰው ወደ ከነዓን ለመጡ ሰዎች የተሰጠ ነው። ፍልስጥኤማውያን የእስራኤልን ጠረፍ መቆጣጠር ከጀመሩ ወዲህ በግብፅና በመስጴጦምያ መካከል የነበረውን ዋናውን መንገድ ያዙ። በውጤቱም የአሕዛብ መንግሥታት ሕዝቦች ያለማቋረጥ ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ያደርጉ ነበር። ምድሪቱንም «የፍልስጥኤሞች» ምድር ወይም ጳለስጢና በመባል ተጠራች። ጳለስጢና በዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ ከግብፅ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያለው አገር በሙሉ የተለመደ መጠሪያ ሆኖአል። ስለዚህ ፍልስጥኤማውያን ከቀርጤስ ደሴት የመጡ አውሮጳውያንን ይመስላሉ። በአሁኑ ዘመን ያሉ ግን ፍልስጥኤማውያን ዐረቦች ናቸው፤ ስለዚህ ከቀድሞዎቹ ጋር አንድ ዓይነት አይደሉም። ከ700 ዓ.ም. በኋላ የዐረብ መንግሥታት እስራኤልን አሸንፈው በዚያ ይኖሩ ጀመር። እስራኤል በ1948 ዓ.ም. እንደገና የራሷን መንግሥት ስታቋቁም በዚያ የነበሩ አንዳንድ ዐረቦች ከዚያ ለቀቁ፤ ስለዚህ ፍልስጥኤማውያን በዘመናዊቷ እስራኤል ውስጥ የነበሩ አሁንም በእስራኤል ውስጥ በአንዳንድ ስፍራዎች ወይም ከእስራኤል ውጭ በስደት የሚኖሩ ዐረቦች ናቸው። የዘመናችን ፍልስጥኤማውያንና አይሁድ የሚያደርጉት ትግል እስራኤል የእኔ ነው የምትለውን ምድር፥ ፍልስጥኤማውያንም የእኛ ነው በማለታቸው ነው።) 

፭. የዊትና የሰሎሞን መንግሥት (ከ1000 – 900 ዓ.ዓ.)

የውይይት ጥያቄ፦ 1ኛ ነገሥት 4፡21-24 አንብብ። በሰሎሞን አመራር ጊዜ የእስራኤል መንግሥት ይዞታ ምን ያህል ነበር?

ግብፅ በፍልስጥኤም ላይ የነበራት ቁጥጥር እየቀነሰ ሲሄድና በመሰጴጦምያ አንድ ኃያል መንግሥት ባለመተካቱ፥ የእስራኤል መንግሥት ኃይል እየጨመረ ሊሄድ ቻለ። በዳዊት የጦር አመራር የእስራኤል መንግሥት በደቡብ በኩል እስከ ግብፅ፥ በሰሜን በኩል ደግሞ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ተስፋፋ። በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ 12 የተለያየ ነገድ ከመሆን በአንድ ንጉሥ የሚተዳደር አንድ ሕዝብ ሆነ። ዋና ከተማዋ ኢየሩሳሌምም ተገነባች።

ዳዊት ተዋግቶ የሕዝቡን የግዛት ዳርቻ ያሰፋ ሲሆን፥ ሰሎሞን ከአባቱ ወረሰ። በአብዛኛው የሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ሰላም የነበረ ሲሆን የአባቱን የዳዊትን ምድር በሚገባ ተቆጣጥሮ ነበር፤ ነገር ግን በሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ የተለያዩ መንግሥታት ዓመፅ እያየለበት ሄዶ ነበር። እርሱ ሲሞት አንድ የነበረው የእስራኤል መንግሥት ለሁለት ተከፈለ። የሰሜኑ መንግሥት «እስራኤል» ሲባል የደቡቡ «ይሁዳ» ተባለ።

ይህ ዘመን ለአይሁድ ሕዝብ «ወርቃማው ዘመን» በመባል ይታወቃል። ይህ ኃይላቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ዘመን ነበር። አስደናቂ የሆኑ አንዳንዶቹ ጽሑፎቻቸውም የተጻፉት በዚህ ጊዜ ነበር፤ በአይሁድ ታሪክ ከየትኛውም ጊዜ ይልቅ ሕዝቡ እግዚአብሔርን የተከተለበት ጊዜ ይህ ነበር። ምክንያቱም መሪዎቻቸው እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ነበሩ፤ ስለዚህ ዘመን በ2ኛ ሳሙኤል፥ 1ኛ ነገሥት 11ና 1ኛ ዜና፥ 2ኛ ዜና እስከ 9 ተጽፎ እናገኛለን። አብዛኛዎቹ የግጥምና የቅኔ መጻሕፍት (መዝሙረ ዳዊት፥ ምሳሌ፥ መክብብና መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን) የተጻፉት በዚህ ዘመን ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ የአንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ መንፈሳዊ ሕይወት በቤተ ክርቲያኒቱ አባሎች ሕይወት ላይ እንዴት ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል? 

፮. የሶርያውያን በኃይል መነሣት (900-800 ዓ.ዓ.)

ከሰሎሞን ሞት በኋላ ኃያል የነበረው የእስራኤል መንግሥት ተከፋፍሉ መውደቅ ጀመረ። በዳዊትና በሰሎሞን ጊዜ በእስራኤል ቁጥጥር ሥር የነበሩ ሶርያውያን (አራማውያን ተብለውም ይጠሩ ነበር) ሰሎሞን ከሞተ በኋላ ማመፅ ጀመሩ። ወዲያውኑ ዋና ከተማቸውን ደማስቆ በማድረግ ኃያል መንግሥታት ሆኑ። በእነዚህ ዓመታት ጳለስጢና ውስጥ ሶርያውያን ኃያላን በመሆን አብዛኛውን የእስራኤልን ምድር ተቆጣጠሩ።

ሁለቱ ታላላቅ ነቢያት ኤልያስና ኤልሳዕ ያገለገሉትም በእነዚህ ዓመታት ነበር። የእስራኤልና የይሁዳ መንግሥታት ታሪክ ከ1ኛ ነገሥት 12 – 2ኛ ነገሥት 14 ድረስ ይገኛል። በተጨማሪ በ2ኛ ዜና ምዕራፍ 10-27 ተጽፎ እናገኛለን። ትናንሽ መጻሕፍት ከጻፉ ነቢያት አንዳንዶቹም መጻሕፍቶቻቸውን የጻፉት በዚህ ዘመን ነው። 

፯. የአሦር ጊዜ (850-650 ዓ.ዓ.)

ሶርያ ኃያል መንግሥት መሆን በጀመረችበት ጊዜ በሰሜን በኩል ደግሞ ሌላ በጤግሮስ ወንዝ የነበረው መንግሥትም ኃያል ሆነ። ይህ መንግሥት የአሦር መንግሥት ነበር። አሦራውያን መስጴጦምያን ተቆጣጠሩና በደቡብ በኩል ያሉትን ሶርያውያንን መዋጋት ጀመሩ። በመጨረሻም ሶርያውያንና የእስራኤል የሰሜኑ መንግሥት በአሦራውያን ተሸነፉ። በ722 ዓ.ዓ. የእስራኤል መንግሥት ተሸነፈና ሕዝቡ በአሦራውያን ተማርከው በመስጴጦምያ ሁሉ ተበተኑ። አሦራውያን አብዛኛውን የይሁዳን መንግሥት ቢቆጣጠሩም እንኳ በሕዝቅያስ ምሪት እግዚአብሔር ይሁዳን ታደገና ኢየሩሳሌም በአሦራውያን እጅ እንዳትወድቅ አደረገ።

የዚህ ዘመን ታሪክ በ2ኛ ነገሥት 15-23ና 2ኛ ዜና 28-36፡4 ይገኛል። አንዳንዶቹ ትናንሽ የነቢያት መጻሕፍትና ኢሳይያስም የተጻፉት በዚህ ጊዜ ነው። 

፰. የባቢሎን መንግሥት የአገዛዝ ዘመን 650-550 ዓ.ዓ. 

በ650 ዓ.ዓ. ታላቁ የእሶር መንግሥት የተለያዩ ሕዝቦች ስለ ዓመፁበት መውደቅ ጀመረ። የአሦር መንግሥት በ612 ዓ.ዓ. በመስጴጦምያ ባቢሎን ተብሎ በሚጠራ መንግሥት ተሸነፈ። ባቢሎን ከአሦር ደቡብ በኤፍራጥስ ወንዝ አካባቢ የሚገኝ ነው። የባቢሎን መንግሥት በታላቁ መሪው በናቡከደነፆር በታላቅ ፍጥነት አድጎ ከባቢሎን ጀምሮ እስከ ግብፅ ያሉትን አካባቢዎች ተቆጣጠረ። ከ606-586 ዓ.ዓ. ሦስት ተከታታይ ዘመቻዎች ተደርጎው የደቡብ ይሁዳ መንግሥት ተሸነፈና ሕዝቡም በምርኮኛነት ተወሰደ።

2ኛ ነገሥት 24-25ና 2ኛ ዜና 36 ስለዚህ ዘመን ይናገራሉ። ከታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት አንዳንዶቹ፥ እንዲሁም ኤርምያስ፥ ሕዝቅኤልና ዳንኤል የተጻፉት በዚህ ጊዜ ነው። 

፱. የሜዶንና የፋርስ የአገዛዝ ዘመን 550-331 ዓ.ዓ. 

በ550 ዓ.ዓ. የሜዶንና የፋርስ መንግሥታት በባቢሎን መንግሥት ላይ ዓመፁና በ539 ዓ.ዓ. አሸነፏት። ባቢሎን ይዛው የነበረውን ምድር በሙሉ ተቆጣጠሩና በዛሬ ጊዜ ቱርክ እስከሚባለው እስከትንሹ እስያ ድረስ ተስፋፉ። በቁጥጥራቸው ሥር ካሉ መንግሥታት ጋር በሰላም ለመኖር ስለፈለጉ የሜዶንና የፋርስ መንግሥታት ባቢሎናውያንና አሦራውያን የማረካቸውን ሕዝቦች በሙሉ ወደየአገሮቻቸው እንዲሄዱና ቤተ መቅደሶቻቸውን እንዲሠሩ ፈቀዱላቸው። እንዲመለሱና ቤተ መቅደሳቸውን እንዲሠሩ ከተፈቀደላቸው መንግሥታት መካከል አንዱ የይሁዳ መንግሥት ነበር። በዘሩባቤል፥ በዕዝራና በነህምያ መሪነት ቤተ መቅደሱና የኢየሩሳሌም ቅጥሮች እንደገና ተሠሩ።

በብሉይ ኪዳን ውስጥ የምናነበው የመጨረሻው ኃያል መንግሥት ይህ ነው። እያንዳንዱን ታሪክ በመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ ውስጥ እናነባለን። የመጽሐፈ አስቴር ታሪክም የተፈጸመው በዚህ ጊዜ ነው። የሐጌ፥ የዘካርያስና የሚልክያስ መጻሕፍትም የተጻፉት የፋርስ መንግሥት በሥልጣን ላይ በነበረበት በ400 ዓ.ዓ. ነው።

ከዘመነ ብሉይ በኋላና በሁለቱ ኪዳኖች መካከል በነበረው ዘመን (400-0 ዓ.ዓ.)፣ አይሁድ ከ166-63 ዓ.ዓ. ለአጭር ጊዜ ነፃነት ከማግኘታቸው በስተቀር ብዙውን ጊዜ በሌላ ሕዝብ ቁጥጥር ሥር ኖረዋል። በ331 ዓ.ዓ. ሜዶንና ፋርስ በግሪክ መንግሥት እጅ ወደቁ። በኋላም የግሪክ መንግሥት በተራው ክርስቶስ በተወለደበትና የአዲስ ኪዳን ዘመን በተጀመረበት ጊዜ ጳለስጢናን ይቆጣጠር በነበረው በሮም መንግሥት እጅ ወደቀ።

የብሉይ ኪዳን የዓለምንና የእስራኤልን ታሪክ በምንመረምርበት ጊዜ በርካታ ነገሮችን ለማየት እንችላለን። እስራኤል በጣም ጠቃሚ የሆነችው በእግዚአብሔር እንጂ በሰው ዓይን እንዳልሆነ ማስታወስ አለብን። በአካባቢው ከነበሩ መንግሥታት ጋር ስትወዳደር ሁልጊዜ ከቁጥር የማትገባ ነበረች፤ ነገር ግን እስራኤል ለእግዚአብሔር በታዘዘች ጊዜ በአካባቢዋ ካሉ ሕዝቦች ሁሉ ይልቅ ብርቱ ነበረች። እግዚአብሔርን አልታዘዝም ስትልና በሕይወቷም ሆነ በአምልኮዋ አንዳንድ ነገሮችን ስትቀይጥ እግዚአብሔር ሊቀጣት ለአሕዛብ መንግሥታት አሳልፎ ይሰጣት ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ጉዳይ ቤተ ክርስቲያን ከዓለም ጋር በሚኖራት ግንኙነት አንፃርና እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚሠራበት መንገድ ጋር ያለው ተመሳሳይነት ምንድን ነው?

የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ በምናጠናበት ጊዜ አንድ ሌላ መሠረታዊ እውነት እናያለን። በዓለም ላይ ያሉ ክስተቶች የሚፈጸሙት ያለ እግዚአብሔር ቀጥተኛ ቁጥጥር ሳይሆን፥ ታሪክን በሙሉ የሚመራው እርሱ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። አንዳንድ ነገሥታትና መንግሥታትን የሚያስነሣ ደግሞም የሚጥል እርሱ ነው። በዘመናችን ሳይቀር በዓለምም ሆነ በአገራችን የሚፈጸሙትን ታሪኮችንና ክስተቶችን ሁሉ የሚቆጣጠር አምላካችን እንደሆነ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።

የውይይት ጥያቄ፥ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ይህ እውነት ክርስቲያኖችን እንዴት ያበረታታቸዋል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading