የአብርሃም ታሪክ (ዘፍጥረት 12-24)

ዛሬ የኦሪት ዘፍጥረትን ሁለተኛ ዋና ክፍል ማጥናት እንጀምራለን። ዘፍጥረት በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች እንደሚመደብ መመልከታችንን ታስታውሳለህ። ዘፍ. 1-11 የሚያተኩረው ከእስራኤል አባቶች በፊት በነበረው ዘመን ላይ ሲሆን፥ ዘፍ. 12-50 ደግሞ አራቱን የእስራኤል ዋና ዋና አባቶች ታሪክ ያሳየናል። እነርሱም፡- አብርሃም፥ ይስሐቅ፥ ያዕቆብና ዮሴፍ ናቸው። በዛሬው ትምህርታችን የአይሁድ ሕዝብና በእግዚአብሔር ላይ እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች ሁሉ አባት የሆነውን የአብርሃምን ታሪክ እንመለከታለን። በዓለም ታሪክ ውስጥ እንደ አብርሃም እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ሰዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው። አይሁድም ሆኑ ዐረቦች ሁለቱም በሥጋ አባታችን አብርሃም ነው ይላሉ። እንዲሁም ክርስቲያኖችም አብርሃም መንፈሳዊ አባታችን ነው ይላሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘፍ. 12-24 አንብብ። ሀ) ከዘፍ. 12፡1-3) እግዚአብሔር ለአብርሃም ተስፋ የሰጠውን ሰባት በረከቶች ዘርዝር። ለ) በዘፍ. 15 እና 17 ወዘተ እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠውን ተጨማሪ የተስፋ ቃላት ዘርዝር። ሐ) እነዚህ ቃል ኪዳኖች በብሉይ ወይም በአዲስ ኪዳን የተፈጸሙት እንዴት ነው? መ) አብርሃም በሕይወት ዘመኑ የሄደባቸውን ከተማዎች ወይም ቦታዎች ዘርዝር። ሠ) የአብርሃምን ሕይወት በአጭሩ አጠቃለህ አቅርብ። በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት እንዴት እንደገለጸ አስረዳ። በእምነት ስላልተራመደባቸው ጊዜያት ግለጥ ወዘተ። ረ) አብርሃም በእምነት የመኖር ጥሩ ምሳሌ የሆነው ለምንድን ነው? ሰ) የራስህን የእምነት ጉዞ ከአብርሃም ሕይወት የእምነት ጉዞ ጋር አወዳድረህ የሚመሳሰልባቸውንና የሚለያይባቸውን ነገሮች ጥቀስ።

ዘፍጥረት 11ን ባጠናንበት ጊዜ ከአብርሃም ቤተሰብ ጋር ተዋውቀናል። የአብርሃም ታሪክ የሚጀምረው በመስጴጦምያ በዑር ከተማ ነው። ዑር በመስጴጦምያ ከሚገኙ ታላላቅ ከተሞች አንዷ ስትሆን፥ የከፍተኛ ሥልጣኔ ማዕከልም ነበረች። ደግሞም ዑር የጣዖት አምልኮ ማዕከል ነበረች፤ ምክንያቱም ሰዎቹ የጨረቃን አምላክ ያመልኩ ነበርና ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ኢያሱ 24፡2-3 አንብብ። በእነዚህ ቁጥሮች በዑር ስለ ነበረው የአብርሃም ቤተሰብ ሃይማኖታዊ ሕይወት የተጻፈው ምንድን ነው?

ስለ አብርሃም ቤተሰብ ምንም የተለየ ነገር አልነበረም። በዑር እንደነበሩ ሰዎች የአብርሃም አባት ታራና ቤተሰቡም የጨረቃና የከዋክብት አማልክትን የሚያመልኩ ይመስላል። ዳሩ ግን እግዚአብሔር ሉዓላዊ በሆነው ምርጫው የሥልጣኔና የሃይማኖት ብልሹነት ይታይባት የነበረችውን የዑር ከተማ ትቶ ሁሉንም ነገር እንደ አዲስ ወደሚጀምርበት ምድር እንዲሄድ አብርሃምን ጠራው።

የአብርሃምን ሕይወት ለመረዳት የኦሪት ዘፍጥረትን የመጀመሪያ ክፍል ማስታወስ አለብን። እግዚአብሔር የአሠራር መንገዱን የለወጠበት ምክንያት ምንድን ነው? ከሰዎች ሁሉ ጋር በእኩልነት ከመሥራት ይልቅ ከአንድ ሰውና ከአንድ ሕዝብ ጋር ለመሥራት ለምን መረጠ? መልሱ ያለው በዘፍጥረት የመጀመሪያ 11 ምዕራፎች ውስጥ ነው።

በአብርሃም ዘመን የዓለም ሁሉ መሠረታዊ ባሕርይ በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ እንደነበር ታስታውሳለህ። እንዲከተሉት ለማድረግ እግዚአብሔር ለብዙ ዓመታት ከሰዎች ሁሉ ጋር ለመሥራት ሞክሯል። አሁንም በቀረው የብሉይ ኪዳን ክፍል እግዚአብሔር ዘዴውን ለወጠ። እግዚአብሔር አንድ ሰውና አንድ አነስተኛ ሕዝብ ለዓለም ብርሃን እንዲሆኑ ወሰነ። እግዚአብሔር ከሰዎች ሁሉ ጋር ሊኖረው የሚፈልገውን ግንኙነት በምሳሌነት እንዲያሳዩ የተመረጡ ነበሩ። ሌሎች ሕዝቦች እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር ያለውን ልዩ ኅብረት እንዲመለከቱና ይህ ኅብረት በመንፈሳዊና በሥጋዊ መንገድ የሚያስገኘውን ሽልማት (በረከት) እንዲያዩ ዐቅዶ ነበር። እነዚህ ሕዝቦች ይህን ኅብረት አይተው ከእግዚአብሔር ጋር ወዳለው ልዩ ኅብረት እንዲመጡ የእግዚአብሔር አሳብ ነበር። እስራኤላውያን በዓለም ላይ የእግዚአብሔር ተወካዮች ነበሩ።

የሚያሳዝነው ግን የብሉይ ኪዳን ታሪክ እስራኤል ይህን ኃላፊነቷን መፈጸም አቅቷት መውደቋን የሚያሳይ መሆኑ ነው። በእግዚአብሔር ላይ ዓመፀች። ከዓለም ከመለየት ይልቅ እንደ ዓለም ተመላለሰች። እግዚአብሔር ዓለምን ለእርሱ ትማርክለት ዘንድ ያሰበውን ዕቅድ ልታሟላ ስላልቻለች፥ ሥራውን ከቤተ ክርስቲያን ጋር በሚሠራበት በአዲስ ኪዳን ዘመን ለጊዜው ገለል ተደረገች።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለእስራኤል የነበረው ዓላማ ዛሬ እግዚአብሔር እኛ እንድሆን ከሚፈልገው ነገር ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ለ) እስራኤል በወደቀችበት መንገድ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ጊዜ የምትወድቀው እንዴት ነው? ሐ) አንተና ቤተ ክርስቲያንህ በኅብረተሰቡ ውስጥ ይህንን ዓላማ የምታሟሉት እንዴት ነው?

በአዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር የግንኙነት መስመር ተለውጦአል። ከዓለም ጋር በስፋት አልሠራም። ከአንድ ሕዝብም ጋር አልሠራም። ይልቁን ከተለያዩ ሕዝቦች መካከል ራሳቸውን ከዓለም ከለዩ ሰዎች ጋር መሥራት ጀመረ። ይህችም ቤተ ክርስቲያን ናት። ክርስቲያኖች የእርሱ ብርሃን እንዲሆኑና ለዓለም እንዲመሰክሩ ነበር። በሕይወታቸው በሚታየው ለውጥ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥትና ቤተሰብ ሊስቡ ያስፈልግ ነበር። የእርሱ ልጆች ነን ብለን ከምናስበው፥ ከእኛ እግዚአብሔር የሚፈልገው ይህንን ነው። ይህንን ዓላማ ለሕይወታችን እያሳካን ነውን?

ሀ) ከላይ የተጠቀሰውን የቤተ ክርስቲያን ዓላማ አንተና ቤተ ክርስቲያንህ የምታሟሉባቸውን መንገዶች ጥቀስ። ለ) የተሻለ «የዓለም ብርሃንና ጨው» (ማቴ. 5፡13-16) ለመሆን እንድትችሉ አሁን ከምትሠሩበት መንገድ በተለየ ሁኔታ ልታከናውኑ የምትችሏቸውን አንዳንድ ነገሮች ዘርዝሩ።

እግዚአብሔር በመጀመሪያ ዑርን እንዲለቅ የጠራው ታራን ይሁን ወይም አብርሃምን የምናውቀው ነገር የለም። ጥሪው የመጣው ግን ለአብርሃም ሳይሆን አይቀርም። አብርሃምም በዕድሜ የገፋ አባቱንና የወንድሙን ልጅ ሎጥን ከራሱ ጋር ይዞ ወጣ። የአብርሃም ወንድም የሆነው ናኮር ለጊዜው በዑር የቆየ ቢሆንም በኋላ ግን ወደኖረበት ወደ ካራን ሄደ። አብርሃምና ሣራ፥ ታራና ሎጥ ወደ ከነዓን ለመሄድ 1000 ኪሎ ሜትር ያህል ከተጓዙ በኋላ ወደ ካራን ከተማ ደረሱ። ወደ ከነዓን በሚወስደው መንገድ ላይ የነበረችው የመጨረሻዋ ዋና ከተማ ካራን ነበረች። ከግብፅ በመነሣት በከነዓን በኩል ወደ መስጴጦምያ በሚወስደው መንገድ ላይ ነበረች። ደግሞም የጨረቃ አምላክ የሚመለክባት ከተማ ነበረች። ታራ ምናልባት በእድሜ ስለገፋ፥ ወይም የለመደውን ባሕልና ሃይማኖትን ትቶ ለመሄድ ባለመፈለጉ ከአብርሃም ጋር በካራን ሰፈረ። በዚህ ስፍራ የኖሩት ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ አይታወቅም፤ ነገር ግን ከታራ ሞት በኋላ አብርሃም የእግዚአብሔርን ጥሪ እንደገና ተቀበለና ወደ ከነዓን ሄደ። 

የአብርሃም መጠራት 

ዘፍጥ. 12፡1-3 በመጽሐፍ ቅዱሳችን ከሚገኙ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ክፍሎች አንዱ ነው። በብሉይና በአዲስ ኪዳን የነበረው የእግዚአብሔር ዕቅድ የተሠራበት መሠረት ነው። በእግዚአብሔርና በአብርሃም መካከል ለተደረገው ቃል ኪዳንም መሠረት ነው። አብርሃም በሕይወት እስከ ኖረበት ዘመን ድረስ እግዚአብሔር በመጀመሪያ በሰጠው የተስፋ ቃል ላይ በየጊዜው ይጨመርለት ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አብርሃምን መጀመሪያ ሲጣራው የሰጠው ሰባት ተስፋዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኙ ተስፋዎች ሁሉ መሠረት ናቸው። 

ከዚህ በታች እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባውን ሰባት የተስፋ ቃሎች እንዴት እንደፈጸመ እናያለን። 

ለአብርሃም የተሰጡ ተስፋዎች              የተስፋዎቹ መፈጸም 

«ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ።»              የእስራኤል ሕዝብ

(«እባርክሃለሁ።»                             አብርሃም ባለጠጋ ሆነ።

«ስምህን አከብረዋለሁ፡፡»                  አይሁድ፥ ዐረቦችና ክርስቲያኖች ሁሉም አብርሃምን እንደ

                                                 አባታቸው ያከብሩታል።

«በረከትም ትሆናለህ።»                    በአብርሃምና በዘሩ መጽሐፍ ቅዱስ ተጻፈ፤ ጌታ ኢየሱስ

                                                ተወለደ፥ ድነት ወደ ዓለም መጣ።

(«የሚባርኩህን እባርካለሁ፡፡»)          በዘመናት ሁሉ አይሁድን የሚባርኩ ሰዎችንና መንግሥታትን

                                                እግዚአብሔር ባርኮአቸዋል።

«የሚረግሙህን እረግማለሁ።»           በመናት ሁሉ አይሁድን የሚያሳድዱ ሰዎችንና መንግሥታትን

                                                እግዚአብሔር በተራው አጥፍቷቸዋል። (ምሳሌ፡- ባቢሎን፣ አሦር) 

«የምድር ነገዶች ሁሉ ባንተ ይባረካሉ።» በአብርሃምና በዘሩ ዓለም ሁሉ ተባርኳል። ይህ በተለይ እውን የሆነው እግዚአብሔር እራሱን ለዓለም የገለጠው በአይሁድ በኩል ስለሆነና የዓለም ሁሉ አዳኙ ክርስተስ አይሁዳዊ ስለሆነ ነው።

እግዚአብሔር አብርሃምን ሲጠራው ይጠብቃቸው ዘንድ ሦስት ትእዛዛትን ሰጥቶታል፡- 1) የሚኖርበትን ምድር ትቶ ይወጣ ዘንድ፥ 2) የአባቱን ቤተሰብ ትቶ ይወጣ ዘንድ፥ 3) እግዚአብሔር ወደሚያሳየው ምድር ይሄድ ዘንድ ነበሩ። አብርሃም የለመደውንና የሚያውቀውን ነገር ሁሉ ትቶ ወደማያውቀውና እንግዳ ወደሆነ ስፍራ ለመሄድ ትልቅ የእምነት እርምጃ ወሰደ። አብርሃም ግን ይህንን ትእዛዝ ሙሉ በሙሉ አልጠበቀም። የአባቱን ቤተሰብ ሁሉ ትቶ እንደመሄድ የወንድሙ ልጅ የሆነውን ሎጥን ይዞ ወጣ። አብርሃም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በከፊል መጠበቁ በኋላ በሕይወቱ ላይ ትልቅ ችግር አስከተለበት። ይህም የወንድሙ ልጅ የሆነው ሎጥ ከሌሎች ነገሥታት ጋር ወደ ጦርነት እንዲሄድ ያደረገው የቤተሰብ ክፍፍል ማስከተሉ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር በከፊል ብቻ እንዴት ልንታዘዘው እንደምንችል ምሳሌ ስጥ።

የአብርሃም ሕይወት በምድር ላይ ለሚኖረን የእምነት ጉዞ ጥሩ ምሳሌ ነው። ማንም ሰው እግዚአብሔርን ፍጹም በሆነ መንገድ መታዘዝ አይችልም። በሕይወታችን ዘመን እግዚአብሔርን የምንታዘዝባቸው ጊዜያት እንዳሉ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ የማንታመንባቸውና ለእርሱ የማንታዘዝባቸው ጊዜያትም አሉ። ስለ አብርሃም ሕይወት በዘፍጥረት የጥናት መጽሐፍ ውስጥ የበለጠ ማጥናት ትችላለህ። ቀጥሉ ግን ልናስታውሳቸው የሚገባን አጠቃላይ ነገሮች ብቻ ቀርበዋል። 

፩. እግዚአብሔር አስቀድሞ ለአብርሃም በሰጠው ተስፋ በምንም ቅድመ ሁኔታ ላይ ያልተመሠረተ ቃል ኪዳን ገባለት። 

ሀ. እግዚአብሔር ከግብፅ ጀምሮ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያለውን ምድር በሙሉ ለአብርሃምና ለዘሩ እንደሚሰጥ ቃል ገባለት፤ (ዘፍጥ. 15፡ 18)።

ለ. እግዚአብሔር አብርሃምን የብዙ ሕዝብ አባት፥ ሣራን ደግሞ የብዙ ሕዝብ እናት አደርጋችኋለሁ አላቸው፤ (ዘፍጥ. 17፡5፥ 15-16)። እግዚአብሔር፥ «ታላቅ አባት» የሚል ትርጉም የነበረውን አብራም የሚለውን የመጀመሪያ ስሙን «የብዙ ሕዝብ አባት» የሚል ትርጉም ወዳለው ወደ አብርሃም ቀየረው። የሚስቱንም ስም ከሦራ ወደ ሣራ ቀየረው። ትርጉሙም «ልዕልት» ማለት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር የሰውን ስም ሲቀይር፥ ሰው ከእርሱ ጋር አዲስ ግንኙነት ጀመረ ማለት ነው። 

ሐ. እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ለማድረግ የተለመደውን ባሕላዊ መንገድ በመጠቀም ማረጋገጫ ሰጠ (ዘፍጥ. 15)። በጥንት ዘመን ሰዎች ሃይማኖታዊ በሆነ ወይም በሌላ ሥነ-ሥርዓት ቃል ኪዳን ወይም ስምምነት ሲያደርጉ አንድ እንስሳን በማረድ ሥጋውን በትክክል ሁለት ቦታ ቅርጫ ይከፍሉት ነበር። ከዚያ በኋላ ቃል ኪዳኑን የፈጸሙት ሁለት ወገኖች በተከፋፈሉት ቅርጫ መሃል ይራመዱ ነበር። ይህን የሚያደርጉትም የቃል ኪዳን ስምምነታቸውን ቢያጥፉ፥ እነርሱም እንዲገደሉ መስማማታቸውን ለመግለጽ ነበር። አብርሃም ያንን በግልጽ በማየት በእምነቱ ይበረታ ዘንድ፥ እግዚአብሔር የተለመደ ቃል ኪዳን ምልክት ሰጠው፤ ነገር ግን አንድን ነገር ማስተዋል አስፈላጊ ነው። በቃል ኪዳን ምልክት ማድረጊያው መካከል የተረማመደው እግዚአብሔር ብቻ ነበር። ለምን? ምክንያቱም ይህ ቃል ኪዳን በምንም ቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ አልነበረምና ነው። ይህንን ቃል ኪዳን ይፈጽም ዘንድ አብርሃም እንዲያደርገው የተጠየቀው አንዳችም ነገር አልነበረም። ይልቁንም የቃል ኪዳኑ መፈጸም የተመሠረተው እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ በመጠበቁ ላይ ነበር። 

መ. ነገሥታት ከአብርሃም ዝርያ እንደሚነሡ እግዚአብሔር ተስፋ ሰጥቶ ነበር፤ (ዘፍጥ. 17፡6)። ይህም የሚያመለክተው ዳዊትንና ልጆቹን በተለይ ደግሞ ለአብርሃም በጣም አስፈላጊ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ነበር።

ሠ. እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለአይሁድ በአጠቃላይ ከእርሱ ጋር ልዩ የሆነ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን የሚያመለክት የሚታይ ምልክት ሰጣቸው (ዘፍጥ. 17)። ይህ ምልክት የእያንዳንዱ ወንድ ልጅ መገረዝ ነበር። በሥጋ አይሁድ የሆነ ማንኛውም ሰው አልገረዝም ቢል በእግዚአብሔርና በአብርሃም ልጆች መካከል በተደረገው ቃል ኪዳን አይታቀፍም ማለት ነው፤ ስለዚህም የአብርሃም እምነት ስላልነበረው እውነተኛ አይሁዳዊ አልነበረም ማለት ነው። 

፪. አብርሃምን ያጋጠመው አደጋ የቃል ኪዳኑን መፈጸም ሊያሰናክለው የሚችል ነበር

ሀ. የአብርሃም የወንድም ልጅ የሆነው ሎጥ የፈጠረው አደጋ። 

 1. የአብርሃም ብቸኛ ዘመድ የሆነው ሎጥ ወራሹ ነበር (ዘፍጥ. 13-14)፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ዕቅድ የአብርሃምን ርስት የራሱ ልጅ እንዲወርሰው ነበር። ቃል ኪዳኑ በሎጥ ምክንያት በሁለት መንገዶች አደጋ ላይ ወድቋል። በመጀመሪያ፥ ሎጥ የአብርሃም ወራሽ ነበር። የአብርሃም ርስት ልጁ ወዳልሆነው ወደ ሌላ ሰው ያልፋልን? አብርሃም ልጅ ቢኖረውም እንኳ ወራሹ ማን ይሆናል በሚለው ጥያቄ ውስጥ አከራካሪ ነገር ሊኖር ይችላልን? ነገር ግን ሎጥ የተስፋይቱን ምድር በተወ ጊዜ የአብርሃም ወራሽ የመሆኑ ነገር ቀረ። ሁለተኛው እግዚአብሔር እንደሚያወርሰው ለአብርሃም ተስፋ ሰጥቶት ነበር። ሎጥ የከነዓንን ምድር ለመውረስ ይመርጣልን? ሎጥ የፈለገው ምቹ የሆነ ምድርን ነበር። ከሁሉ የተሻለውን ምድር ለአጎቱ ለአብርሃም ሊለቅለት ሲገባ፥ እጅግ በጣም ጥሩ የመሰለውን ነገር ግን፥ እጅግ ክፉ የነበረውን የሰዶምን ምድር መረጠ። ስለዚህ ሎጥ የተስፋይቱን ምድር ከነዓንን ተወ። በራስ ወዳድነት ያደረገው ምርጫ ከእግዚአብሔር የበረከት ስፍራ ውጭ አደረገው። ለሁለተኛ ጊዜ እግዚአብሔር የከነዓንን ምድር ለአብርሃም ቃል ገባለት። ደግሞም ዝርያዎቹ ሊቆጠሩ እስከማይችሉ ድረስ እንደሚበዙ ተስፋ ሰጠው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሥጋዊ ክርስቲያን መላ ሕይወቱን ለእግዚአብሔር አስገዝቶ አልኖርም በሚልበት ጊዜ የሚመርጠው ምርጫ ከሎጥ ምርጫ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? 

 1. ሎጥ በሰዶም ሲኖር ሳለ በሰሜን ነገሥታት ተማረከና ቃል ኪዳኑን አደጋ ላይ ጣለው። በአብርሃም ዘመን፥ በከነዓን ምድር በርካታ የከተማ መንግሥታት ነበሩ። ገናና የሆነችው ከተማም በአካባቢዋ ያለውን ምድር ሁሉ ትማርክና በማስገበር ትገዛ ነበር። የዚያች ከተማ መሪም ንጉሥ ተብሎ ይጠራ ነበር። ይህ ታሪክ በተፈጸመ ጊዜ ሎጥ ወደ ሰዶም ምድር ተንቀሳቀሰ። በመሐሉ በሙት ባሕር በስተደቡብ መጨረሻ አካባቢ እንደ ነበሩ በሚገመቱ በሰዶምና ገሞራ ከተሞችና በኤላም፥ በጎኢምና እላሳር (በመስጴጦምያ የሚገኙ) ከተሞች መካከል በተደረገው ትግል ሎጥም ተማርኮ ተወሰደ። በዚህ ጊዜ ሰዶምና ገሞራ በሰሜን ነገሥታት እጅ የወደቁ ቢሆንም ዓምፀው ግብር አንከፍልም አሉ፤ ስለዚህ የሰሜን ነገሥታት የደቡብ ነገሥታትን ለመቅጣት መጡ። ደቡቦቹ ተሸነፉና ሎጥን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በምርኮ ተወሰዱ። አብርሃምም የወንድሙ ልጅ መማረኩን በሰማ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎችን በሙሉ (318 ወንዶች)፥ በከነዓን ምድር ከሚኖሩ አንዳንድ መሪዎች ጋር ይዞ ሄዶ የሰሜን ነገሥታትን በማጥቃት አሸነፋቸው። አብርሃም እነዚህን ነገሥታት ለመውጋት በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ተጓዘ። ሎጥን ለማዳን ሲል ሕይወቱን አደጋ ላይ ጣለ። ይህም እግዚአብሔር በአብርሃም በኩል ሊጀምረው የነበረውን የተመረጠ ሕዝብን የማዘጋጀት ዕቅድ ሊያበላሽ ይችል ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አብርሃምን ጠብቆ ድልን አጎናጸፈው። 

የውይይት ጥያቄ ፥ ሎጥ ከአብርሃም ምርጥ የሆነውን መሬት ቢወሰድበትም አብርሃም ቸር ነበር። ከዚህ ምን እንማራለን?

ሙሴ ይህንን ታሪክ ለምን ጻፈው? የሎጥን የሞኝነት ምርጫ በማሳየት፥ ራስ ወዳድነት ክርስቲያንን እንዴት ችግር ውስጥ ሊከተው እንደሚችል ለማሳየት ሊሆን ይችላል። በተጨማሪ ወደ ከነዓን ለመግባት በዝግጅት ላይ ያሉትን እስራኤላውያንን ለማበረታታትም ሊሆን ይችላል። አብርሃም ከእርሱ ጋር የነበሩት ጥቂት ቢሆኑም እንኳ እግዚአብሔር ግን ከእርሱ ጋር ስለነበር ታላቅ ኃይልን ለማሸነፍ ቻለ። እስራኤላውያን ወደ ከነዓን ምድር ሊገቡ በተዘጋጁ ጊዜ ቁጥራቸው ከጠላቶቻቸው ቁጥር ያነሰ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ስለሆነ በቁጥር እጅግ ጥቂት ቢሆኑም እንኳ በርካታ የሆኑትን የእግዚአብሔር ጠላቶቻችን አሸንፈዋል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬ በጠላቶቻቸው ብዛት የተዋጡት ክርስቲያኖች ይህ እንዴት ያበረታታቸዋል? 

 1. የሎጥ በሰዶምና ገሞራ ላይ ከመጣው ፍርድ ማምለጥ በቃል ኪዳኑ ላይ ትልቅ አደጋ ሊፈጥር የሚችል ነበር፤ (ዘፍጥ. 18-19)። ሎጥ የሰዶምን ኑሮ ስለወደደ ወደ ከተማይቱ ገባ። እግዚአብሔር በከተማይቱ ላይ በመፍረድ ሊያጠፋት ባሰበ ጊዜ ወደ ወዳጁ ወደ አብርሃም በመምጣት ዕቅዱን ገለጠለት (ዘፍጥ. 18)። አብርሃም ስለ ከተማይቱ እግዚአብሔርን አጥብቆ ለመነ፤ ነገር ግን አሥር ጻድቃን እንኳ ስላልተገኙባት እግዚአብሔር ከተማይቱን አጠፋት። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ለአብርሃም ብሉ ሎጥንና ሁለቱን ሴቶች ልጆቹን አዳናቸው። ሎጥ ወደ ከነዓን ተመልሶ የአብርሃም ወራሽ ሆነን? የለም፤ ሎጥ ወደ ከነዓን ከመመለስ ይልቅ በዋሻ ውስጥ መኖርን መርጦ እምቢ አለ።

የሎጥ ታሪክ ለሥጋዊ ክርስቲያን ጥሩ ምሳሌ ነው። ሎጥ ከአብርሃም ጋር በሰላም ቢኖር ኖሮ ከአብርሃም ጋር የእግዚአብሔርን የበረከት ፍሬ በሙሉ በተካፈለ ነበር። በረከቶቹ ግን በአብርሃምና በሎጥ መካከል አለመስማማትን አስከተሉ። በረከቶቹ ወደ ራስ ወዳድነት መሩት። ሎጥ ለሥጋዊና ለጊዜያዊ ጥቅም ሲል ከምድሪቱ ምርጥ ነው ብሉ ያሰበውን ነገር መረጠ። ይህ ምርጫው በነገሥታት እንዲማረክ፥ በመጨረሻም ሚስቱን፥ ንብረቱንና ሀብቱን ሁሉ እንዲያጣ ምክንያት እንደሚሆን አልተገነዘበም። ከሴት ልጆቹ ጋር ኃጢአት በማድረግ የእግዚአብሔርና የእስራኤላውያን ጠላቶች የሆኑ ሕዝቦች የተገኙባቸውን ልጆች ወለደ። የሎጥ ልጆች የሆኑት ሞዓብና ዓሞን፥ ሞዓባውያንና ዓሞናውያን የተባሉ ሁለት ሕዝቦች ሲሆኑ እነርሱም በብሉይ ኪዳን ዘመን ከእስራኤላውያን ጋር ያለማቋረጥ ይዋጉ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔርን ደስ እያሰኙ ከመኖር ይልቅ እራሳችንን ደስ እያሰኘን የመኖርን ውጤት ምንነት ከሎጥ ታሪክ ምን እንማራለን?

ለ. የአብርሃም ሎሌ ኤሊዔዘር በቃል ኪዳኑ ፍጻሜ ላይ የፈጠረው አደጋ፡- (ዘፍጥረት 15) 

በጥንት ዘመን አንድ ሰው ምንም ልጆች ከሌሉት ከሎሌዎቹ አንዱን ወራሽ አድርጎ ይሾመው ነበር። አብርሃም ለዚህ ጉዳይ የሾመው ተወዳጅ አገልጋዩ የነበረውን የደማስቆውን ሰው ኤሊዔዘርን ሳይሆን አይቀርም። የአብርሃም ፍላጎት ግን ከጉልበቱ የወጣው ልጁ እንዲወርሰው ነበር።

ከአብርሃም ታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም አስፈላጊው ክፍል ዘፍጥረት 15 ነው። በዚህ ታሪክ ውስጥ እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን አደሰ። እጅግ ጠቃሚ በሆነው በዚህ ታሪክ ውስጥ የሚከተሉትን ነገሮች ተመልከት፡-

 1. እግዚአብሔር ለአብርሃም በርካታ ተስፋዎችን በመስጠት ቃል ኪዳኑን ጀመረ።

ሀ. እግዚአብሔር ለአብርሃም ልጆቹ በሰማይ እንዳሉ ከዋክብት እንደሚበዙ የተስፋ ቃል ገባለት። 

ለ. ከግብፅ ጀምሮ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያለው የከነዓን ምድር በሙሉ ለአብርሃም ዝርያዎች ተሰጠ። 

 1. አብርሃም ለእግዚአብሔር በእምነት መልስ ሰጠ። ዘፍጥ. 15፡6 እንዲህ ይላል፡- «አብራምም በእግዚአብሔር አመነ፥ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት።» አብርሃም የዳነው እንዴት ነበር? አንዳንድ ታላላቅ ነገሮችን ስላደረገ ነውን? ስለተገረዘ ነውን? አይደለም። እግዚአብሔር አብርሃምን የተቀበለውና ጻድቅ ብሎ የጠራው የገባውን የተስፋ ቃሉን ስላመነ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬ ለድነት (ደኅንነት) ከሚፈለግብን ነገር ጋር ይህ እንዴት ይመሳሰላል? (ሮሜ 4፡1-25 ተመልከት)።

ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን የአብርሃምን እምነት በመውሰድ፥ እኛም የምንድነው ወይም ጻድቃን ተብለን የምንቆጠረው በምንሠራው መልካም ሥራ (ለድሆች በመስጠት፥ ባለመጠጣት፥ ዝሙትን ባለማድረግ ወዘተ) ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባለን እምነት ብቻ እንደሆነ ለመግለጽ ተጠቅሞበታል።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ትምህርት ወደ መንግሥተ ሰማያት የምንገባው በምንሠራችው መልካም ተግባራት፥ ማለትም በጥምቀት፥ ለድሆች በመስጠት፥ በመጾም ወዘተ ነው ብለው ከሚያስተምሩ ሰዎች የሚለየው እንዴት ነው?

፫. እግዚአብሔር ስለ አብርሃም ዝርያዎች የወደፊት ጉዳይ ተንብዮአል።

እግዚአብሔር እስራኤላውያን ወደፊት መጻተኞች እንደሚሆኑ (በተስፋ የእነርሱ ብትሆንም እንኳ በከነዓን ውስጥ ምድር እንደማይኖራችው) እና ለ400 ዓመታት በባርነት እንደሚቆዩ ለአብርሃም ተናገረ። በሙሴ ዘመን የነበሩ እስራኤላውያን ይህንን ትንቢት በማወቃቸው ይበረታቱ ነበር፤ ምክንያቱም 400 ዓመታት እየተጠናቀቁ መሆናቸውን ቆጥረው ለመድረስ ይችሉ ነበር።

** (ማስታወሻ፡- እግዚአብሔር አሞራውያን የኃጢአታቸው ጽዋ ስላልሞላ በጸጋው የንስሐ ጊዜ እንደሰጣቸው ይናገር ነበር። አሞራውያን ከኃጢአታችው ይመለሱ ዘንድ እግዚአብሔር ለ400 ዓመታት በትዕግሥት ጠበቃቸው። አሞራውያን የከነዓናውያን ሌላ ስም ነው። እነርሱ ግን ከመመለስ ፈንታ በክፋታቸው እጅግ እየባሱ ሄዱ። ስለዚህ በመጽሐፈ ኢያሱ የእግዚአብሔር ፍርድ በአሞራውያን ላይ ይፈጸም ዘንድ እስራኤላውያን መሣሪያ ሆኑ። ሙሉ በሙሉ እንዲያጠፏቸውም ታዘዙ።)

ሐ. በቃል ኪዳኑ ፍጻሜ ላይ እስማኤል የፈጠረው አደጋ፡- (ዘፍጥ.16፤ 21፡8-21)

ከአብርሃምና ከባሪያይቱ ከአጋር የተወለደው እስማኤል እግዚአብሔር ከአብርሃምና ከሣራ ሊያስገኘው ያቀደውን ተአምራዊ ልጅ የመወለድ ዕቅድ ሊያበላሸው ነበር። እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ የሚሠራ መሆኑን በማመን ፈንታ አብርሃም በራሱ መንገድ የራሱን ልጅ በማዘጋጀት እግዚአብሔርን ሊረዳው ሞከረ። በዚያን ዘመን ሰው ከገዛ ሚስቱ ልጅ ማግኘት ካልቻለ ባሪያውን በመገናኘት ልጅ ይወልድ ነበር። በዚህ ዓይነት የተገኘውም ልጅ የልጅነት ሙሉ መብት በማግኘት ወራሽ ይሆን ነበር። አብርሃም ይህ ድርጊቱ የሚያስከትልበትን ኃዘን አልተገነዘበም ነበር። በቤቱ ውስጥ በሣራና በአጋር መካከል ጠብን ፈጠረ። ይህም ማለት የሚወደውን ልጁን እስማኤልን ከቤት ማባረር ነበረበት ማለት ነው። በኋላም በታሪክ እንደምናገኘው፥ የእስማኤል ዝርያዎች የሆኑት ዐረቦች፥ የአብርሃም ልጅ፥ የይስሐቅ ዝርያዎች የሆኑት የአይሁድ ክፉ ጠላቶች ሆኑ።

የውይይት ጥያቄ፥ የራሳችንን አሳብ ወይም መንገድ በመጠቀምና አንድ ነገር በማድረግ እግዚአብሔርን ለመርዳት ስለመሞከር ይህ ምን ያስተምረናል?

መ. አብርሃም እግዚአብሔር ሕይወቱን ለመጠበቅ እንደሚችል አላምንም በማለቱ በቃል ኪዳኑ ላይ የተፈጠረ አደጋ፡-

አብርሃም ታላቅ የእምነት ሰው ቢሆንም፥ ሊወጣው ያልቻለው ደካማ ነጥብ በሕይወቱ ነበር። ይህም ደካማ ነጥብ እግዚአብሔር ሕይወቱን እንደሚጠብቅ ሊታመንበት አለመቻሉ ነበር። በመጀመሪያ አብርሃምና ሣራ ወደ ግብፅ በወረዱ ጊዜ የተፈጸመ ታሪክ ነው (ዘፍጥ. 12፡ 10-20)። አብርሃም ወደ ግብፅ ይወርድ ዘንድ እግዚአብሔርን ስለመጠየቁ ምንም ማረጋገጫ የለንም። በእግዚአብሔር ላይ እምነት በማጣቱ ሕይወቱን ለመጠበቅ በከፊል ሲዋሽ እናየዋለን። ሣራን ለማግባት ሲሉ ይገድሉኛል ብሎ ስለፈራ ለግብፃውያን እኅቱ እንደሆነች ነገራቸው። ሣራ የአብርሃም አባት ከሌላ ሚስት የወለዳት ስለ ነበረች (ዘፍ. 20፡12) ይህ ማለቱ በከፊል እውነት ነው። ሣራ ሚስት እንድትሆነው ወደ ፈርዖን ቤት ተወሰደች። ይህ የሚያሳየው አብርሃም በእግዚአብሔር ላይ እምነት ማጣቱን ብቻ ሳይሆን፥ ቃል ኪዳኑን አደጋ ላይ እንደጣለው ነው። ፈርዖን ሣራን በሚስትነት ቢያስቀራት ኖሮ ለአብርሃም ከሣራ የሚገኝ ልጅና ሕዝብ ሊኖር አይችልም ነበር። እግዚአብሔር በዚህ መካከል ጣልቃ ሊገባና ሣራን ከፈርዖን እጅ ሊያድናት ይገባ ነበር። ይህም አብርሃም በእግዚአብሔር ላይ እምነት ያልጣለበት የመጀመሪያ ጊዜ ነበር።

ከብዙ ዓመታት በኋላ፥ አብርሃም በጌራራ ንጉሥ በአቤሜሌክ ፊት ይህንኑ ስሕተት ደገመው (ዘፍጥ. 20)። አብርሃም ስሕተቱን የሠራው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከሣራ ልጅ እንደሚያገኝ እግዚአብሔር ቃል ከገባለት ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነበር። ይስሐቅ ከመወለዱ ጥቂት ቀደም ብሎ ሰይጣን ወደ አብርሃም ያመጣው ፈተና ነበር። ወደ ጌራራ ንጉሥ ዘንድ በሄደ ጊዜ ሣራ እኅቱ መሆንዋን ለሰዎቹ ነገራቸው። ይህም ንጉሡ ሣራን ሚስቱ አድርጎ ሊወስዳት ፈለገ። እግዚአብሔር ሣራ የአብርሃም ሚስት መሆንዋን ለንጉሡ በመንገርና በማስጠንቀቅ ቃል ኪዳኑን ከአደጋ ጠበቀው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬስ እግዚአብሔር እንደሚጠብቀን በእርሱ በማመን ፈንታ፥ የራሳችንን ሕይወት ወይም ፍላጎታችንን ለመጠበቅ በመሞከር እነዚህን የመሰሉ ተመሳሳይ ፈተናዎች እንዴት እንጋፈጣቸዋለን?

ሠ. ለወራሹ፥ ለይስሐቅ ተገቢ የሆነች ሚስት ያለማግኘት አደጋ፥ (ዘፍጥ. 24) የአብርሃም የዘር ሐረግ እንዲቀጥል ይስሐቅ ሊያገባና ልጆችን ሊወልድ ይገባው ነበር፤ ነገር ግን ከአብርሃም አጠገብ ይኖሩ የነበሩት ሰዎች ሁሉ በአንዱ እውነተኛ አምላክ የማያምኑ ከነዓናውያን ነበሩ፤ ስለዚህ ይስሐቅ በካራን ካሉ ዘመዶቹ ዘንድ ማግኘት ነበረበት። ምናልባት ይስሐቅ የካራንን ምድር ወዶ ሊቀር ይችላል የሚል ፍርሃት ስለ ነበረው አብርሃም ይስሐቅን ወደዚያ መላክ አልፈለገም። በሌላ በኩል ደግሞ በሰለጠነ ከተማ (በካራ) የኖረች ሴት፥ የነበረችበትን አገር ትታ የማታውቀውን ሰው ለማግባት በመቶ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ተጉዛ ትመጣለች ብሎ ማሰብም የሚያጠራጥር ነበር፤ ነገር ግን አብርሃም እግዚአብሔር ለልጁ ለይስሐቅ ትክክለኛዋን ሚስት ሊሰጠው እንደሚችል አመነ። አብርሃም አገልጋዩን ላከ፤ እግዚአብሔር ሥራውን ስለ ሠራ ርብቃ ወደ ከነዓን ለመምጣትና የይስሐቅ ሚስት ለመሆን ተስማማች።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይስሐቅ የማታምን ሴት እንዳያገባ አብርሃም ያደረገው ጥንቃቄ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ለ) የገዛ ሚስቶቻችንንም ሆነ የልጆቻችንን ሚስቶች በጥንቃቄ ስለመምረጥ ይህ ታሪክ የሚያስተምረን ነገር ምንድን ነው? ሐ) የማይቻል በሚመስል ሁኔታ ውስጥ እንኳ እግዚአብሔር ትክክለኛ የትዳር ጓደኛ ሊሰጠን ስለመቻሉ ይህ ታሪክ ምን ያስተምረናል?

በአብርሃም ሕይወት ውስጥ ጠቃሚ የሆኑ ሌሎች በርካታ ታሪኮችም አሉ፡፡ በተለይ ደግሞ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ተምሳሌት የሆኑ ሁለት ታሪኮች አሉ፡-

 1. አብርሃም፥ የወንድሙን ልጅ ሎጥን ማርከው ወስደው የነበሩትን የሰሜን ነገሥታት አሸንፎ በሚመለስበት ጊዜ ከአንድ ልዩ ሰው ጋር ተገናኝቶ ነበር። ይህ ሰው በኋላ ኢየሩሳሌም የተባለችው የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅ ነበር። አብርሃም ከጦርነቱ ምርኮ ከሆነው ሁሉ አንድ አሥረኛውን (አሥራት) ለዚህ ንጉሥ ሰጠው። ንጉሡም አብርሃምን ባረከው አከበረውም፤ (ዘፍጥ. 14፡17-24)። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዕብ. 6፡20-7፡24 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ቁጥሮች መልከ ጼዴቅን ይመስላል የተባለለት ማን ነው? ለ) ከመልከ ጼዴቅ ጋር የሚመሳሰለው በምንድን ነው? 

ስለ መልከ ጼዴቅ የምናውቀው ብዙ ነግር ባይኖርም፥ ወደ ዕብራውያን ሰዎች የተላከው መልእክት እርሱ የክርስቶስ ተምሳሌት ነው ይላል። «ተምሳሌት» በመጽሐፍ ቅዱሳችን የሚሰጠው ትርጉም አንድ የተለየ ድርጊት ወይም ሰው ወደፊት ስለሚመጣ ሰው ወይም ስለሚፈጸም ድርጊት ግልጽ የሆነ ምሳሌነት የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ፡- የእስራኤል ሕዝብ ከግብፅ ነፃ የመውጣት ታሪክ ከኃጢአት ነፃ የመውጣት ምሳሌ ነው። አዳም የሁለተኛው አዳም፥ የክርስቶስ ምሳሌ ነው (ሮሜ 5፡14)። በዚሁ ዓይነት፥ መልከ ጼዴቅም የሊቀ ካህናችን፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ተምሳሌት ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ መልከ ጸዴቅ ንጉሥም ሊቀ ካህንም ነው። መልከ ጼዴቅ ልክ እንደማንኛችንም ሰው በመሆኑ፥ የተወለደና የሞተ ቢሆንም፥ መቼ እንደተወለደና መቼ እንደሞተ ኦሪት ዘፍጥረት የሚያመለክተው አንዳችም ነገር የለም። ኢየሱስ ክርስቶስም፥ እንደ እግዚአብሔር ልጅ መጀመሪያና መጨረሻ የለውም። እርሱና የሊቀ ካህንነቱ ሥራ ዘላለማዊ ነው።

 1. ይስሐቅ የ15 ዓመት ወጣት በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር አብርሃምን ከእርሱና ከልጁ የላቀ ማንን እንደሚወድ ለማረጋገጥ ፈተነው። አንድ ልጁን ይዞ በሞርያም ተራራ እንዲሠዋለት እግዚአብሔር አብርሃምን አዘዘው (ዘፍ. 22) 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ለአብርሃም ይህንን ፈተና የሰጠው ለምን ይመስልሃል? ለ) ዛሬም ለእኛ ሊሰጠን የሚችለውን ተመሳሳይ የፈተና ዓይነት ጥቀስ።

አብርሃም ይህን ፈተና አልፎአል። ብዙ ኪሎ ሜትሮች ተጉዞ ወደ ሞርያም ተራራ በደረሰና ልጁን ለመሠዋት ቢላውን ባነሣ ጊዜ እግዚአብሔር በይስሐቅ ምትክ የሚሠዋ በግ ሰጠው።

ይህ በብዙ መንገድ የክርስቶስ ኢየሱስ ተምሳሌት ነው። ይስሐቅ የአብርሃም ብቸኛ ወይም ልዩ ልጅ እንደሆነ፣ ኢየሱስ ክርስቶስም የእግዚአብሔር አንድያ ልጁ ነው፤ (ዮሐ. 3፡16)። አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ይሠዋ ዘንድ እንደሰጠ፥ እግዚአብሔር አብም ልጁን ኢየሱስን ለዓለም ኃጢአት መሥዋዕት አድርጎ ሰጠ። ይህም ቢሆን እንኳ በሁለቱ ታሪኮች መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ። እግዚአብሔር አብርሃምን፥ ልጁን እንዲሠዋ የከለከለው ሲሆን፥ የገዛ ልጁ በመስቀል ላይ እንዲሞት ግን ፈቅዷል። አብርሃም ልጁን ለመሠዋት የወሰደው ወደ ሞርያም ማለትም ወደ ጽዮን ተራራ ሲሆን፥ ኢየሱስ ለኃጢአታችን የሞተውም በሞርያም ወይም በጽዮን ተራራ ነው። ይስሐቅ ወጣት ልጅ እንደመሆኑ መጠን አባቱ መሥዋዕት አድርጎ እንዳያቀርበው መከላከል እና እምቢ ማለት ሲችል፥ በጸጥታ በመታዘዝ ለመሠዋት እንደፈቀደ ሁሉ፥ ኢየሱስም እግዚአብሔር አብ ይሠዋ ዘንድ ለወሰነው ውሳኔ በፈቃደኝነት ታዘዘ። በገዛ ፈቃዱ ሕይወቱን ሰጠ።

 1. «የእግዚአብሔር መልአክ» መታየት። በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱሳችን፥ በብሉይ ኪዳን፡- «የጌታ መልአክ» ተብሎ የተጠራ ልዩ የሆነ መልአክ መኖሩን መለየት አስቸጋሪ ነው። ይህ መልአክ በዘፍጥረት፥ በዘጸአት፥ በዘኁልቁ፥ በ1ኛና በ2ኛ ሳሙኤል፥ በ1ኛና በ2ኛ ነገሥት እንዲሁም በ1ኛና በ2ኛ ዜና መዋዕል ውስጥ ተጠቅሷል። በኦሪት ዘፍጥረት ይህ መልአክ ከአጋር (ዘፍጥ. 16፡7-14፤ 21፡16-20)። ከአብርሃም (ዘፍጥ. 18፤ 22፡ 10-18) እና ከያዕቆብ (ዘፍጥ. 31፡11-13) እንደተገናኘ ተጠቅሷል። ይህ ልዩ የጌታ መልአክ ማን ነው? ስለዚህ መልአክ የተጠቀሱትን የተለያዩ ጥቅሶች ስንመረምር ወደሚከተሉት እውነቶች እንደርሳለን፡ –

ሀ. የጌታ መልአክ ከእግዚአብሔር የተለየ ነው። ይህን ስንል የጌታ መልአክ ስለ እግዚአብሔር ስለሚናገር እርሱ ከእግዚአብሔር የተለየ ሰብዕና አለው ማለታችን ነው።

ለ. የጌታ መልአክ ከእግዚአብሔር እንደሆነ ተጠቅሷል። ለምሳሌ፣ አጋር ከጌታ መልአክ ጋር ከተነጋገረች በኋላ እግዚአብሔርን አየሁት አለች፤ (ዘፍጥ. 16፡10)።

ሐ. ይህ የጌታ መልአክ ይታያል ደግሞም ወዲያውኑ ይሰወራል። ግለሰቦች ወይም የእስራኤል ሕዝብ የእርሱ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው በተወሰኑ ጊዜያት ይታይና ተግባሩን ከፈጸመ በኋላ ይሄዳል። 

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን፥ ይህ መልአክ በእግዚአብሔር ተልኮ የአንዳንድ ሰዎችን ወይም የእስራኤልን ሕዝብ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ የሚረዳ አንድ ልዩ መልአክ ነው ብለው ያስባሉ። እግዚአብሔር ተብሎ የተጠራውም እንደ እግዚአብሔር መልእክተኛ ሆኖ የሚመጣና የእግዚአብሔር ተወካይ መሆኑ የታወቀ ስለሆነ ነው ይላሉ። ሌሉች የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ደግሞ ይህ መልአክ እግዚአብሔር ነው፤ እንዲያውም በአዲስ ኪዳን ሥጋ ከመልበሱ በፊት በብሉይ ኪዳን የተጠቀሰውን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ያመለክታል ይላሉ። ዘላለማዊ የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን በሥራ ላይ እንደነበረና በምድር ላይ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ለሰዎች እየተገለጠ ይሰወር እንደነበር የሚያመለክት ይመስላል።

የአብርሃም ሕይወት የጊዜ ቅደም ተከተል 

በአብርሃም ሕይወት በጣም ዋና ዋና የሆኑ ታሪካዊ ድርጊቶች 

 1. አብርሃም በ2166 ዓ.ዓ. አካባቢ ተወለደ 
 2. አብርሃም ካራንን ትቶ ወደ ከነዓን ተጓዘ – 75 ዓመት 
 3. የእስማኤል መወለድ – 86 ዓመት 
 4. እግዚአብሔር የግዝረትን ቃል ኪዳንና የይስሐቅን መወለድ ተስፋ ሰጠው – 99ዓመት 
 5. የይስሐቅ መወለድ – 100 ዓመት 
 6. የአብርሃም ይስሐቅን ለመሠዋት ማቅረብ – በግምት ወደ 115 ዓመት ይሆናል 
 7. አብርሃም በ1991 ዓ.ዓ. አካባቢ ሞተ – 175 ዓመት

ከአብርሃም ጋር የተገባው ቃል ኪዳን ለብሉይ ኪዳን ታሪክ ያለው አስፈላጊነት፡

የአብርሃምን ሕይወት ጠቃሚነትና በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ደጋግመን ብንገልጠውም አጥጋቢ አይሆንም። እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን ብሉይ ኪዳንን የምንረዳበትና የእስራኤልን ሕዝብ አስፈላጊነት የምንመዝንበት መሠረት ነው። ትንቢትን የምንረዳበት መሠረትም ነው። ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር ከአብርሃም በኋላም ከእስራኤል ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን በምንም ቅድመ ሁኔታ ላይ ያልተመሠረተ ነው ብለን ካመንን፥ ወደ ፊት ለእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር ቃል ኪዳኖቹን ያከብራል። ቃል ኪዳኖቹ በቅድመ ሁኔታዎች ላይ እንደተመሠረቱ አድርገን ወይም የሚፈጸሙት በመንፈሳዊ ትርጓሜ በክርስቲያኖችና በቤተ ክርስቲያን ብቻ ነው ብለን ካመንን እስራኤል ከእንግዲህ ወዲህ በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ስፍራ የላትም ማለታችን ነው።

እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ያደረጋቸው እነዚህ የተስፋ ቃላት የብሉይ ኪዳኖች ታሪኮች የተመሠረቱባቸው መሠረቶች ናቸው። የአብርሃምን ሕይወት ለማጥናት በርከት ያለ ጊዜ የወሰድነው ለዚህ ነው። 

የብሉይ ኪዳን ታሪክ የተመሠረተው ከአብርሃም ጋር በተደረገ ቃል ኪዳን ላይ ነው። በቃል ኪዳኑ ውስጥ የብሉይ ኪዳንን ታሪክ እንደምሶሶ ሆነው የሚደግፉ ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ነበሩ። የመጀመሪያው፥ አይሁድ የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ መሆናቸው ነው። ከሌላው ሕዝብ ጋር ካለው ከየትኛውም ዓይነት ቃል ኪዳን በተለየ ሁኔታ እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ቃል ኪዳን አለው። ሁለተኛው፥ የከነዓን ምድር ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአይሁድ እንደተሰጣቸው የተገባ ተስፋ መኖሩ ነው። ሦስተኛው፥ ደግሞ ከአብርሃም ዘር ነገሥታት እንደሚነሡ የተሰጠው ተስፋ ነው። በኋላ እንደምናየው፥ እነዚህ ነገሥታት የሚመጡት ከይሁዳ ዘር በተለይ ደግሞ ከዳዊት ዝርያ ነው። 

እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ስለገባው ቃል ኪዳን ልንመለከታቸው የሚገቡ ሌሎች ሁለት እውነቶች አሉ። 1) እግዚአብሔር አሕዛብ በሙሉ በዘሩ እንደሚባረኩ ለአብርሃም ተስፋ ሰጥቶት ነበር። ይህ በረከት በተለያየ መልክ መጣ። እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጅ ለመግለጥ አይሁድን ተጠቀመ። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉ የተጻፈው በአይሁድ ስለሆነ ነው። የሚያምኑትን ሁሉ የሚያድነው ጌታ ኢየሱስ በትውልዱ አይሁዳዊ ነው። 2) አብርሃም የእውነተኛ አማኞች ሁሉ አባት ነው። እንደ አብርሃም በእግዚአብሔር የሚያምኑ ሁሉ እግዚአብሔር ጻድቃን አድርጎ ይቀበላቸዋል። ከዚያም የአብርሃም መንፈሳዊ ልጆች ይሆናሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ የአብርሃም መንፈሳዊ ልጅ የሆንከው መቼ ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: