ማርክ ትዌይን፥ «በጥሩ ምሳሌ መማረክን የመሰለ ከባድ ነገር የለም» ሲል ጽፏል። ምናልባትም ስለጥሩ ምሳሌ ሊሰማን የሚችል ቅሬታ ቢኖር፥ በምሳሌው ውስጥ የተገለጠውን ዓይነት መልካም ባሕርይ በዚህ ሕይወታችን ውስጥ ልንለማመድ ባለመቻላችን መሆን አለበት። በትልቅ ሰው መደነቅ እኛን ሊያነሳሳን ይችላል፤ ነገር ግን እኛን ትልቅ ለመሆን አያስችለንም። በእኛ ሕይወት ሰውየው ካልገባና ችሎታውን ካላካፈለን፥ እኛ ወደ እርሱ ከፍ ያለ የሥራ ውጤት መድረስ አንችልም። ላይ ላዩን ሲያዩት እንደ ምሳሌው ለመሆን ቀላል ይመስላል፤ ዳሩ ግን ባለ በሌለው ውስጣዊ ኃይላችን መጠቀም በግድ ያሻናል።
ጳውሎስ፥ የትሑት አእምሮን ልምምድ በማስመልከት ኢየሱስ ክርስቶስን ታላቁ ምሳሌ በማድረግ አቅርቦልናል። እኛም አንብበነው በእርሱ አሳብ እንስማማ ይሆናል፤ ነገር ግን ትልቁ ጥያቄ፥ «ወደ ልምምድ የምንሸጋገረው እንዴት ነው?» የሚለው ነው። ሌላው ጥያቄ ደግሞ «ደካማው የሰው ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጸመውን ለመፈጸም እንደ ምን ተስፋ ለማድረግ ይችላል?» የሚል ነው። ይህን ለመሞከር እንኳን ጨርሶ የማይቻል ይመስላል። እኛ ግን ትሕትናን ለመለማመድና ለማሳደግ፥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመምሰል በድፍረት በመነሳሳት በኩራት እየታበይን ነው።
እንደ እውነቱ ይህን ለማሟላት ያን ያህል አስቸጋሪ አይደለም። ጳውሎስ የማይቻለውን «ዘላችሁ ከከዋክብት ላይ ድረሱ» ሲል አልጠየቀንም። እርግጥ የእኛ ግብ ከዚህም የበለጠ ነውና በበኩላችንም በዚያው መጠን ጥረት ልናደርግ ይገባናል። ጳውሎስም የሚያሳስበን በትሑት አእምሮ በመመራት እንዴት የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ልናሟላ እንደምንችልና በእርሱም ፈለግ መጓዝ እንደሚኖርብን ነው። «በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና» (2፡13)። በማስመሰል ሳይሆን ግን ሥጋችንን በመልበሱ «ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል»(ገላ. 2፡20) ለማለት እንድንችል ነው። የክርስትና ሕይወት ገባ ወጣ ወይንም የሚፈራረቅ አይደለም። በምትኩ በማይቃረን ሁኔታ «በውስጣችንና በውጪም» የሚሠራ ኃይል ነው። እግዚኣብሔር ከውስጥ ይሠራል እኛ ደግሞ ከውጭ እንሠራለን። ትሕትና የተሞላ አእምሮን የምናሳድገው እግዚአብሔር ለእኛ በመለኮታዊ መንገድ ለሚያዘጋጅልን ነገሮች ምላሽ በመስጠት ነው።
- ለመፈጸም ዓላማ አለን (2፡12፥ 14-16)
«የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ» (ቁ. 12) ማለት «ለራሳችሁ መዳን ሥሩ» ማለት አይደለም። መጀመሪያ ነገር፥ ጳውሎስ ሲጽፍ በቅድሚያ «ቅዱሳን» (1፡1) ለሆኑ ሰዎች ነው፥ ይህም ማለት እነርሱ በክርስቶስ አምነዋልና ለራሱ የለያቸው ናቸው። «ፈጸመ» የሚለው ግሥ የያዘው ትርጉም «ሥራን ሙሉ በሙሉ አከናወነ» ወይም በሒሳብ ቋንቋ ቀመሩን በትክክል አስቀመጠ እንደማለት ነው። በጳውሎስ ጊዜ ቃሉን «ለማዕድን ሥራ» ይጠቀሙበት ነበር። ይኸውም የተለያዩ ማዕድናትን ከአፈርና ከድንጋይ ውስጥ አንጥሮ ማውጣትን ያመለክታል። እንደዚሁም «በእርሻ ሥራ» ላይ ብዙ መከር ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ለመግለጥ ያገለግል ነበር። የእግዚአብሔር ፍላጎት እኛ ክርስቶስን ለመምሰል በምናደርገው ጥረት ከግብ እንድንድረስ ነው። «የልጁን መልክ እንዲመስሉ» (ሮሜ 8፡29)። በሕይወት ውስጥ ችግሮች አሉ፥ ግን እግዚአብሔር «እንድንወጣቸው» ይረዳናል። የእኛ ሕይወት እንደ ማዕድኑና እንደ እርሻው በከፍተኛ ሊበለጽግ የሚችል ነው፥ እና እርሱም ይህን እንድንፈጽም ሊረዳን ይፈልጋል።
ሲንዲ ከዩኒቨርስቲ ከቤተሰቦችዋ ጋር በዓልን ለማሳለፍ ቤት ስትደርስ የተደሰተች አትመስልም። ወላጆችዋ ያልተለመደ ባሕሪዋን አውቀዋል፤ ግን እርሷ እራሷ ችግሯን እስክታካፍላቸው ድረስ ይጠብቋታል። ከእራት በኋላ እንዲህ ሆነ።
«እናቴ፥ አባቴ ሆይ፤ እስቲ አንድ ነገር ልነግራችሁ እፈልጋለሁ፤ ግን እንድታዝኑብኝ አልፈልግም» አለች። «በልብሽ ያለውን ንገሪን» ብሎ አባቷ አደፋፈራት፤ «እኛ እንረዳሻለን፥ ምንም ነገር ይሁን ካንቺ ጋር ስለ ችግሩ እንጸልያለን»። «መቼም እንደምታስታውሱት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለሁ ነርስ እንደምሆን ብዙ ጊዜ አወራ ነበር፤ ምክንያቱ እናቴ ነርስ ስለሆነች እና እናንተም የእርሷን ፈለግ እንደምከተል ሳትገምቱ ባለመቅረታችሁ ነው። ነገር ግን በዚህ ዓላማዬ ለመቀጠል አልቻልኩም። ጌታ ነርስ እንድሆን አልፈለገም» አለቻቸው።
እናቷ ፈገግ ብላ የሲንዲን እጅ ያዘችና «ውዴ፥ አባትሽና እኔ የምንፈልገው የእግዚአብሔር ፈቃድ በሕይወትሽ ውስጥ እንዲመራሽ ነው። ከዚህ ውጭ ሌላ ነገር ብትሠሪ ግን ሁላችንም አንደሰትም።» አለቻት።
ሲንዲ የወሰደችው የድፍረት እርምጃ ነበር። ይኸውም የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመጠበቅ ለራሷ መዳን ለመሥራት ፈለገች፡ የራሷን ክርስትና ሕይወት ተከተለች እንጂ ሌላ ሰው እንድትሆን የመከራትን ለመሆን አልፈለገችም። ክርስቲያን የመሆን አንዱ አስደናቂ ነገር እግዚአብሔር በእኛ ሕይወት ያለውን ፈቃድ ለማወቅ መቻላችንና ፈቃዱን ለክብሩ ሲል እንድንፈጽመው እንደሚረዳን መገንዘባችን ነው (ኤፌ. 2፡10)። እግዚአብሔር በምንም ነገር የማይወሰን ፈጣሪ አምላክ ነው። ሁለት አበቦች አንድ አይደሉም፥ ሁለት የሱፍ ዘለላዎች አንድ አይደሉም፤ ታዲያ ሁለት ክርስቲያኖች ለምን አንድ መሆን ይገባቸዋል? ሁላችንም ክርስቶስን መምሰል አለብን፥ ግን እኛ ደግሞ ራሳችንን መሆን አለብን።
«የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ» የሚለው ሐረግ ምናልባት በተለይ በፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላለው ልዩ ችግር የተጻፈ መረጃ ይሆናል፤ ዓረፍተ-ነገሩ ግን ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ይሠራል። እኛ የሌሎች ሰዎች ቅጂ መሆን አይገባንም። በተለይም የታላላቅ ክርስቲያኖች ግልባጮች መሆን አይገባንም። እኛ መከተል ያለብን በሕይወታቸው ውስጥ የምናየውን የክርስቶስ ባሕርያት ብቻ ነው። «እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ» (1ኛ ቆሮ. 11፡1)። እያንዳንዱ «ታላቅና ቅዱስ ነኝ ባይ» ደካማ ጎን አለው፤ እና ውሉ አድሮ ተስፋ ሊያስቆርጠን ይችላል። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ፈጽሞ ለውድቀት አይዳርገንም።
በቁጥር 14 እና 15 ውስጥ ጳውሎስ የአማኝን ሕይወት በዓለም ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ያነጻጽራል። ያልዳኑ ሰዎች ያማርራሉ፥ በሌሉች ላይ አቃቂር ለማውጣት ይጥራሉ፤ ክርስቲያኖች ግን በደስታ ይሞላሉ። በዙሪያችን ያለው ኅብረተሰብ «የተወሳሰበና የተዛባ» ነው። ክርስቲያኖች ግን ቀጥ ብለው ይቆማሉ ምክንያቱም ሕይወታቸው የሚለካው በእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ነው። እርሱም ፍጹም መለኪያ ነው። ዓለም ጨለማ ነው ክርስቲያኖች ግን እንደ ደማቅ ብርሃን ይበራሉ። ዓለም የምትሰጠው ምንም ነገር የላትም፥ ክርስቲያን ግን በክርስቶስ በማመን የሕይወት ቃል የሆነውን የደኅንነት መልእክት ይሠጣል። በሌላ አነጋገር እግዚአብሔር በእኛ ሕይወት ሊያሟላ የሚፈልገውን እንዲሠራ ከፈቀድንለት፥ እኛም በተራችን በዓለም ውስጥ ተስፋ ለቆረጡትና ክርስቶስ ለሚያስፈልጋቸው ምስክሮች እንሆናለን። እነዚህ ባሕሪያትን ከኢየሱስ ጋር ስናነጻጽር እርሱ በዚህ ፍጹም ባልሆነ ዓለም ፍጹም የሆነ ኑሮ እንደኖረ እናያለን።
ከልብ ልናጤነው የሚገባው ነገር ደግሞ ይህ ግብ «በዚህ በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል» እንኳን ሊሳካ መቻሉን ነው። ጳውሎስ ከምንኖርበት ዓለም ተገልለን፥ ሕይወታችንን ሙሉ በምነና እንድናውለው አይመክረንም። እንደ እውነቱ ክርስቶስን ይበልጥ መምሰል የምንጀምረው በዕለት ኑሮአችን ላይ ችግሮች ሲገጥሙንና ፈተናዎችን በድል ስንወጣ ብቻ ነው። ፈሪሳውያን በጣም የተለዩ እና ከእውነት የራቁ ከመሆናቸውም፥ የራሳቸው የሆነ ሰው-ሰራሽ ጽድቅ በማስፋፋት እግዚአብሔር እንዲኖራቸው ከሚፈልገው ጽድቅ የራቁ ነበሩ። በመሆኑም ፈሪሳውያን ሃይማኖታቸውን በግዳጅ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ይጥራሉ። እናም በሰዎች ላይ ባርነትን ይጭናሉ (ማቴ. 23 አንብብ)። ኢየሱስን የሰቀሉበትም ምክንያት ይህንን ዓይነት ሃይማኖት በመቃወም በድፍረት ስለተናገረ ነው። የእግዚአብሔርን ዓላማ በሕይወታችን ለመፈጸም የምንችለው ራሳችንን ከዓለም በማግለል ሳይሆን ሌሎችን በማገልገል ነው።
- የምንቀበለው ኃይል አለ (2፡13)
ጳውሎስ የጻፈው መመሪያ፥ እግዚአብሔር በእኛ ተጠቅሞ ከመሥራቱ በፊት በእኛ ውስጥ መሥራት አለበት የሚል ነው። ይህ መመሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምናገኛቸው እንደ ሙሴ፥ ዳዊት፥ ሐዋርያት እና ሌሎች ሰዎች ሕይወት ውስጥ እንደሠራ እናያለን። እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው ሊፈጽመው ያለ ልዩ ዓላማ አለው። በመሆኑም እያንዳንዱ ሰው ልዩ ነው እንጂ አንዱ ሌላውን ሰው ሊሆን አይችልም። ለምሳሌ እግዚአብሔር ሙሴን የእስራኤልን ሕዝብ ወዳዘጋጀው ቦታ እንዲመራ ለማዘጋጀት ለአርባ ዓመታት ታግሦ ጠብቋል። ሙሴ በእነዚያ አርባ ዓመታት የበጎች እረኛ በመሆን ቢያገለግልም እግዚአብሔር በእርሱ ውስጥ ይሠራ ነበር። ዝግጅቱም እግዚአብሔር በእርሱ አማካይነት የሚሠራበት ቀን እስከሚደርስ ነበር። እግዚአብሔርም ከሥራው ይበልጥ በሠራተኛው ይደሰታል። ሠራተኛው ትክክለኛ ሰው እስከሆነ፥ ሥራውም የሰመረ ይሆናል።
በጣም ብዙ ክርስቲያኖች በውስጣቸው ባለው ኃይል ገፋፊነት ሳይሆን ከውጪ በሚያድርባቸው ተጽዕኖ የተነሳ ለእግዚአብሔር ይታዘዛሉ። ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ሰዎችን ሲያስጠነቅቅ እርሱ ከእነርሱ ጋር ባይሆንም፥ ትልቁ ቁም ነገር ግን እግዚአብሔርን ለመታዘዝና ለማስደሰት ፍላጎት እንዲኖራቸው መሆኑን ገልጦላቸዋል (1፡27፤ 2፡12)። ሕይወታቸውን በጳውሎስ ላይ መመሥረት አይችሉም። ምክንያቱም እርሱ ከእነርሱ ጋር ለሁልጊዜም አብሯቸው የሚቆይ ባለመሆኑ ነው። በመሪዎች ለውጥ ምክንያት አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች ሲደክሙ ወይም ሲፈርሱ ሳይ አዝናለሁ። ሰዎችን የማስደሰት ፍላጎት አለን፥ እንደዚሁም የሌሎችን አድናቆት ለማግኘትም ስንል ብቻ ለእግዚአብሔር የምንታዘዝበት ጊዜ አለ፤ ነገር ግን ልቦናችንን ለእግዚአብሔር ኃይል በምናስገዛበት ጊዜ መታዘዝ ደስታ እንጂ ትግል አይሆንብንም።
በእኛ ውስጥ የሚሠራው ኃይል የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው (ዮሐ. 14፡16-17፥ 26፤ ሐዋ. 1፡8፤ 1ኛ ቆሮ. 6፡19-20)። በቁጥር 13 ውስጥ «ሥራ» የሚለው ቃል የመነጨው «ኃይል» ከሚለው ቃል ነው። የእግዚአብሔር አምላካዊ ኃይል በእኛ ውስጥ እና ከእኛም አልፎ የሚሠራ ነው። በምድር በሚያገለግልበት ጊዜ ለክርስቶስ ኃይል የሰጠው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ለእኛም ኃይልን ሰጥቶናል፤ ነገር ግን እኛ በደንብ መለየት ያለብን ነገር የሥጋን ፈቃድና (ሮሜ 7፡5)፥ የሰይጣንን ሥራ (ኤፌ. 2፡2፤ 2ኛ ተሰ. 2፡7) ነው፤ ምክንያቱም ሁለቱም በሥራ ላይ በመሆናቸው ነው። በክርስቶስ ሞት፥ በትንሳኤውና በዳግም መምጣቱ ምክንያት የእግዚአብሔርን አምላካዊ ኃይል በፈለግን ጊዜ ልናገኘው የምንችለው ነው (ኤፌ. 1፡18-23)። ኃይሉ በቅርባችን አለ፥ ነገር ግን እንዴት ነው እኛ የምንጠቀምበት? እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በሕይወታችን ውስጥ ለመሥራት የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች ምንድን ናቸው? ለዚህ ሦስት «መሣሪያዎች» አሉት እነርሱም የእግዚአብሔር ቃል፥ ጸሎትና መከራ ናቸው።
የእግዚአብሔር ቃል፡- «ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን» (1ኛ ተሰ. 2፡13)።
የእግዚአብሔር መለኮታዊ ኃይል በሕይወታችን የሚሞላው በመንፈስ በተሞላው ቃሉ በኩል ነው። ዓለምን ለመፍጠር ያገለገለው ያ ቃል በግል ሕይወታችን ውስጥ መለኮታዊ ኃይል ማስረፅ ይችላል። ሆኖም ግን ቃሉን አክብረን የመያዝ ኃላፊነት አለብን፥ የሰዎችን ቃል በምንመዝንበት መንገድ ልንመራመረው አይገባም። የእግዚአብሔር ቃል ልዩ ነው፤ መንፈስን የሚያነሳሳ፥ ሥልጣን ያለው፥ የማይሳሳት ነው። ለቃሉ ዋጋ ካልሰጠነው፥ የእግዚአብሔር ኃይል በሕይወታችን ውስጥ ጐልቶ አይታይም።
ለዚህም ቃሉን ለራሳችን መገንዘብ አለብን – «መቀበል»። ይህም ማለት፥ ብዙ ማዳመጥ፥ ይልቁንም ማንበብና፥ ማጥናት ማለት ነው። የእግዚአብሔርን ቃል «መቀበል» ማለት በደስታ ተቀብሎ፥ በልቡናችን ውስጥ ቀርፆ መያዝ ነው። ምግብ ለሰብዓዊ ሰውነታችን የሚያስፈልገውን ያህል የእግዚአብሔር እውነት ደግሞ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን የሚያስፈልገው ነው።
በመጨረሻም፥ ቃሉን ከሕይወታችን ማዛመድ አለብን፤ ቃሉም የሚሠራው «በሚያምኑት» ውስጥ ብቻ ነው። የእግዚአብሔርን ቃል በምናምንበት ጊዜ፥ እንሠራበታለን፥ ያን ጊዜ የእግዚአብሔር ኃይል በሕይወታችን ይታያል። በሉቃስ 1፡37 ውስጥ መልአኩ ለማርያም ቃል ሲገባ «ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና» ብሎአል። የእግዚአብሔር ቃል በውስጡ የሚሠራ ኃይል አለው እና እምነትም ይህን ኃይል በግልጥ ያሳየዋል።
ይህ እውነት በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ሲሠራ እናያለን። ሽባውን ሰው እጁን እንዲዘረጋ አዘዘው እና ልክ እንዳዘዘው እጁን የመዘርጋት ኃይል አግኝቶ ተፈወሰ (ማቴ. 12፡13)። ጴጥሮስን በውኃ ላይ ወደ እርሱ እንዲመጣ አዘዘው፥ ትእዛዙም ጴጥሮስን እስከተማመነ ድረስ በውኃው ላይ ለመራመድ አስቻለው (ማቴ. 14፡22-33)። የእግዚአብሔርን ተስፋ ቃል ኪዳን ማመን የእግዚአብሔርን ኃይል እንዲታይ ያደርጋል። ትእዛዙ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ የሚያስችል ነው። መንፈስ ቅዱስ በቃሉ ውስጥ ለእኛ ያለውን ተስፋ ጽፏል፥ ደግሞም እነዚህን ተስፋዎች ለመጠበቅ እምነትን ሰጥቶናል። «እግዚአብሔር ለሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ አዎን ማለት በእርሱ ነውና ስለዚህ ለእግዚአብሔር ስለ ክብሩ በእኛ የሚነገረው አሜን በእርሱ ደግሞ ነው» (2ኛ ቆሮ. 1፡20)።
ጸሎት – የእግዚአብሔር ኃይል በእኛ እንዲሠራ እስከፈለግን፥ በየቀኑ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የተወሰነ ጊዜ ማሳለፍ አለብን፤ እንደዚሁም መጸለይም አለብን። ምክንያቱም እግዚአብሔር በልጆቹ ሕይወት ለመሥራት የሚጠቀምበት ሁለተኛው «መሣሪያ» ጸሎት በመሆኑ ነው። «እንግዲህ በእኛ እንደሚሠራው ኃይል መጠን ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ ለሚቻለው» (ኤፌ. 3፡20)። መንፈስ ቅዱስና የምንጸልየው ጸሎት በሕይወታችን በጣም የተቀራረቡ ናቸው (ሮሜ 8፡26-27፤ ዘካ. 12፡10)። በሐዋርያት ሥራ ውስጥ እንደተገለጸው ጸሉት ከእግዚአብሔር የተለገሰን የመንፈሳዊ ኃይል ምንጭ ነው። (1፡14፥ 4፡23-31፥ 12፡5፥ 12)፥ እና የእግዚአብሔር ቃልና ጸሎት አብረው ይሄዳሉ (ሐዋ. 6፡4)። አንድ ክርስቲያን ለጸሎት የተወሰነ ጊዜ እስካልመደበ እግዚኣብሔር በእርሱ ውስጥ እና በእርሱ በኩል ሊሠራ አይችልም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እና በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እግዚአብሔር የሚጠቀምባቸው ሰዎች የጸሎት ሰዎች ነበሩ።
መከራ፡- የእግዚአብሔር ሦስተኛ «መሣሪያ» መከራ ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ ለክርስቶስ ክብር መከራን በሚቀበሉ ሰዎች ሕይወት ውስጥ በልዩ መንገድ ይሠራል (1ኛ ጴጥ. 4፡12-19)። «በእሳት መፈተን» በውስጣችን ዋጋ የሌለውን የማቃጠል ኃይል አለው እና ለአማኙ ክርስቶስን እንዲያገለግል ኃይልን ያስገኝለታል። ጳውሎስ እራሱ የእግዚአብሔርን ኃይል በፊልጵስዩስ እስር ቤት ውስጥ ተለማምዷል። ይህን የተለማመደው በተደበደበበት ጊዜ እና ከግንድ ጋር በተጠረቀበት ጊዜ ነው። በመከራ ውስጥ ቢሆንም እንኳን እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግን ነበር (ሐዋ. 16፡19-33)። የእርሱ «በእሳት መፈተን» ደግሞ ለወህኒ ጠባቂው ምሕረት ለማድረግ አስቻለው። ለሰውየው እምነት ምክንያት የሆነው የመሬት መንቀጥቀጡ አልነበረም። እንዲያውም የመሬት መንቀጥቀጡ ሰውየው እራሱን ወደ መግደል ሳይገፋፋው አልቀረውም። ለመጽናናት ያበቃው «እንደሱ አታድርግ! ሁላችንም ከዚህ አለን» የሚለው የጳውሎስ የሚያደፋፍር ቃል ነበር። የሰውን ልብ የሚሰብር እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ነበር ሰውየውን በጳውሎስ ፊት ተደፍቶ እንዴት ልድን እችላለሁ? ብሎ እንዲጠይቅ ያደረገው።
የእግዚአብሔር ቃል፥ ጸሎት፥ እና መከራ እግዚአብሔር በሕይወታችን የሚጠቀምባቸው «መሣሪያዎች» ናቸው። ልክ የኤሌክትሪክ ኃይል በሽቦ ውስጥ ማለፍ እንዳለበት መንፈስ ቅዱስም እግዚአብሔር በፈቀደው መንገድ ይሠራል። ክርስቲያን ቃሉን ስለሚያነብና ስለሚጸልይ በይበልጥ ክርስቶስን ይመስላል፥ ክርስቶስን በመሰለ ቁጥር ደግሞ ያልዳነው ዓለም እርሱን ይቃወማል። ይህም በየእለቱ «በመከራው መካፈል» (ፊልጽ. 3፡10) ነውና አማኙን ወደ ቃሉና ወደ ጸሎት እንዲመለስ ይገፋፋዋል። ሦስቱም «መሣሪያዎች» በአንድ ላይ የሚሠሩት ክርስቶስን ለማክበር የሚያስፈልገውን መንፈሳዊ ኃይል ለመስጠት ነው።
እኛ ትሑት አእምሮንና አብሮት የሚሄደውን ደስታ ለመቀናጀት እስከፈለግን፥ ልናማሏው የሚገባን ግዴታም እንዳለ መገንዘብ አለብን (የእግዚአብሔር ዕቅድ በሕይወታችን ውስጥ ይሠራል)፤ የምንቀበለውም ኃይል (መንፈስ ቅዱስ) እና የምናምነውም ተስፋ አለን።
- የምናምነው ተስፋ አለ (2፡16-18)
ተስፋው ምንድን ነው? ደስታ የሚመጣው ከመገዛት ነው። በዓለም ፍልስፍና ግን ደስታን የሚያስገኘው ጠብ አጫሪነት ነው፤ የሚፈልጉትን ለማግኘት ከሁሉ ሰው ጋር መጣላት የግድ ነው፥ በዚህም ደግሞ የሚደሰቱ የሚመስላቸው አሉ። የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ብቻ ይህ የዓለም ፍልስፍና ትክክል ያለመሆኑን ሊያረጋግጥልን በቂ ነው። እርሱ በሰይፍም ሆነ ወይም በሌላ የጦር መሣሪያ አንድም ጊዜ አልተጠቀመም፤ ሆኖም በታሪክ ውስጥ ካሉት ሁሉ ታላቅ የሆነውን ጦርነት አሸንፏል፤ ይኸውም ውጊያው ከኃጢአት፥ ከሞት እና ከሲኦል ጋር ነበር። ፍቅሩን በመግለጽ ጥላቻን አሸነፈ። ውሸትን በእውነት አስወገደ። እራሱን ለአባቱ አስገዝቶ ነበረና ድል አድራጊ ሆነ፤ እና እናንተና እኔም ተስፋውን ለማመን መድፈር አለብን። «ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል» (ሉቃ. 14፡1)። «በመንፈስ ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ስለሆነች ደስ ይበላቸው» (ማቴ. 5፡3 አዲሱ መደበኛ ትርጉም)።
በትሑት አእምሮ ለሚመራውና ራሱንም ለዚህ ለሚያስገዛው ሰው ድርብ ደስታ አለው። ይኸውም ከምድራዊ ሕይወቱ በኋላ የሚቀዳጀው ደስታ (ቁ. 16) እና እዚሁና አሁኑኑ የሚያገኘው ደስታ (ቁ. 17-18) ናቸው። በክርስቶስ ቀን (1፡6፥ 10 ተመልከት) እግዚአብሔር ለእርሱ ታማኝ የሆኑትን ይሸልማል። «የጌታ ደስታ» የሽልማቱ አንዱ ክፍል ይሆናል (ማቴ. 25፡21)። ታማኝ ክርስቲያን በምድር ላይ ያሉ መከራዎች በሰማይ ወደ ክብር እንደሚለወጡ መገንዘብ አለበት። ሥራዎቹ በእርሱ ዘንድ ከንቱ እንደማይቀሩ ያውቃል (1ኛ ቆሮ. 15፡58)። አዳኛችንን በመስቀል ላይ መከራውን እንዲታገስ የረዳው በፊቱ ይህን ዓይነቱ ተስፋና ከፊቱ ይታየው የነበረው ደስታ ነበር (ዕብ. 12፡1-2)።
ሆኖም ግን እኛ የትሑት አእምሮን ደስታ መለማመድ ለመጀመር፥ የክርስቶስን መመለስ መጠበቅ የለብንም። ደስታውን አሁኑኑ ልንለማመደው የምንችለው ሲሆን (ቁ. 17-18)፥ የሚገኘው ግን በመሥዋዕትና በአገልግሎት በኩል ይሆናል። ጳውሎስ በሁለቱ ጥቅሶች ውስጥ ስለ መሥዋዕት የተናገረው የሚያስደንቅ ነው። ጳውሎስ ደስታ እና ደስ ይበላችሁ በሚሉት ቃላት ከመጠቀሙም በላይ ደጋግሟቸዋል። አብዛኛው ሰው ሐዘንን ከመከራ ጋር ያዛምዳል፤ ነገር ግን ጳውሎስ መከራንና መሥዋዕትን በክርስቶስ ለሚገኘው ጥልቅ ደስታ በር ከፋቾች አድርጎ አቅርቧቸዋል።
በቁጥር 17 ጳውሎስ የራሱን የመሥዋዕት ልምምድ የመጠጥ ቁርባን ከሚያቀርበው ካህን ጋር ሲያነጻጽረው እንመለከታለን (ዘኁ. 15፡1-10)። ጳውሎስን የሚጠብቀው ፍርድ እርሱን የመቃወምና ለሞት ቅጣት የሚያደርሰው ሊሆን ይችላል፤ ይህ ግን የጳውሎስን ደስታ ሊገፍፈው አልቻለም። ሞቱን በፈቃደኝነት የሚቀበለው መሥዋዕትነት ነው። ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያኑ የሚፈጽመው የካህንነት አገልግሉት በመሆኑ ለእርሱ ደስታ ይሰጠዋል። «መሥዋዕትና አገልግሎት» የትሑት አእምሮ ምልክቶች ናቸው (2፡7-8፥ 21-23፡ 30)፥ እና ትሑት አእምሮ በመከራ መሀል እንኳን ደስታን ይለማመዳል።
ባለ ትሑት አእምሮ ለመሆን፥ የማያወላውል እምነት ሊኖረን ይገባል። የእግዚአብሔር ተስፋዎች እውነት መሆናቸውን ማመን አለብን። በጳውሎስ ሕይወት እንደሠራ በእኛም ሕይወት ውስጥ ይሠራል። እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ በቃሉ በጸሉት፥ እና በመከራ ይሠራል። ቃሉን በተቀበልነውና ባመንንበት መጠን የእግዚአብሔር ዓላማ በእኛ ውስጥ ይፈጸማል። ሕይወት አሳዛኝ በሆኑ «ውጣ ውረዶች» የተሞላ አይደለም። እንዲያውም በተመሳሳይ ጊዜ «ከውስጥም ከውጪም» የደስታ ስሜት ሊያጎናጽፈን የሚችል ነው። እግዚአብሔር በውስጥ ይሠራል። እኛ በውጭ እንሠራለን። ምሳሌነቱን ከክርስቶስ፥ ኃይልንም ከመንፈስ ቅዱስ የምንቀዳጀው ይሆናል። ውጤቱም ደስታ ነው!
ምንጭ፣ ጽሑፍ በ ዋረን ደብልዩ ዌርዝቢ፣ ትርጉም በመስፍን ታዬ፣ እርማት በ ዓብይ ደምሴ