የታሪካዊ መጻሕፍት መግቢያ

በዚህ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት መክፈቻ ጥናታችን እስካሁን ድረስ የመጀመሪያውን ክፍል ፔንታቱክን ተመልክተናል። ፔንታቱክ፡- ዘፍጥረት፥ ዘጸአት፥ ዘሌዋውያን ዘኁልቁና ዘዳግም የሚባሉ አምስት መጻሕፍትን ይዞአል። ከታሪካቸው አንጻር፥ እነዚህ መጻሕፍት የሚናገሩት ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት እስከተዘጋጁበት ጊዜ ድረስ ያለውን ሁኔታ ነው። የፍጥረት መጀመሪያ መቼ እንደነበር ምንም የምናውቀው ነገር ባይኖርም፥ የፔንታቱክ ታሪክ ግን በ1400 ዓ.ዓ. ገደማ ያበቃል።

አይሁድ እነዚህን የብሉይ ኪዳን የመጀመሪያ አምስት መጻሕፍት ልዩና በታሪካቸው ውስጥ ለተሰጡት የእግዚአብሔር መገለጦች ሁሉ መሠረታዊ እንደሆኑ ያምናሉ። ስለዚህ ከሌሎቹ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ አብልጠው፥ እነዚህን አምስት መጻሕፍት ያከብራሉ።

የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሁለተኛ ዋና ክፍል «ታሪካዊ መጻሕፍት» በመባል የሚታወቁ ሲሆን፥ እነዚህም ከመጽሐፈ ኢያሱ ጀምሮ እስከ መጽሐፈ አስቴር ያሉት 12 መጻሕፍት ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- አሥራ ሁለቱን የታሪክ መጻሕፍት በዝርዝር አቅርበ።

እነዚህ የታሪክ መጻሕፍት ከሙሴ ሞት ጀምሮ እስከ አስቴር ድረስ ያለውን የእስራኤል ታሪክ የሚናገሩ ናቸው። ስለዚህ ከ1400 ዓ.ዓ. – 430 ዓ.ዓ. ያለውን የ1000 ዓመታት ጊዜ ያካትታሉ። እነዚህ 12 መጻሕፍት የቀሩትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ታሪክ በሙሉ የሚያካትቱ ናቸው። የቀሩት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ማለትም የግጥምና የቅኔ እንዲሁም የትንቢት መጻሕፍት በእነዚህ 12 መጻሕፍት የታሪክ ዘመን ውስጥ የሚጠቃለሉ ናቸው። የተጻፉትም በእነዚህ ታሪካዊ ወቅቶች ነው፡፡

አይሁድ የታሪክ መጻሕፍትን በሁለት የተለያዩ ዓበይት ክፍሎች ይከፍሉአቸዋል። ከመጽሐፈ ኢያሱ እስከ 2ኛ ነገሥት ያሉ መጻሕፍትን «የቀድሞ ነቢያት» መጻሕፍት ብለው ይጠሯቸው ነበር። ይህም የሚያመለክተው አይሁድ እነዚህን መጻሕፍት የሚያዩአቸው እንደ ታሪክ መጻሕፍት ብቻ ሳይሆን፥ የቀድሞዎቹ ነቢያት የሠሩበት ጊዜም እንደሆነ ጭምር ነው። ከመጽሐፈ ሩት ጀምሮ እስከ መጽሐፈ አስቴር ድረስ ያሉትን መጻሕፍት ደግሞ «ጽሑፎች» ብለው የሚጠሩአቸው የአንድ ትልቅ ክፍል አካል አድርገው በመቁጠር ነው።

እነዚህ አሥራ ሁለት የታሪክ መጻሕፍት በሊቃውንት መካከል ከፍተኛ የሆኑ አወዛጋቢና አከራካሪ ነገሮችን ፈጥረዋል። አንዳንድ ምሁራን እነዚህ መጻሕፍት በእስራኤል ታሪክ ውስጥ እጅግ ዘግይተው የተጻፉ ናቸው ብለው ያስባሉ። ከመጽሐፈ ኢያሱ እስከ 2ኛ ነገሥት ያሉት መጻሕፍት የተጻፉት እንዲያውም ከኦሪት ዘዳግም ጋር በአንድነት ስለሆነ፥ «የዘዳግም ታሪክ» በመባል ይታወቃሉ ይላሉ። ከመጽሐፈ ኢያሱ እስከ 2ኛ ነገሥት ያሉት መጻሕፍት ዋና ዓላማ በኦሪት ዘዳግም እስራኤላውያን ባለማመናቸው ምክንያት ፍርድ እንደሚጠብቃቸው የተነገረው ትንቢት በአይሁድ ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ፍጻሜ ግግኘቱን ለማሳየት ነው ብለው ያምናሉ።

የታሪክ መጻሕፍት በሙሉ የተጻፉት በአንድ ጸሐፊ መሆኑን መገመት በጣም አጠራጣሪ ቢሆንም፥ በጥልቀት ስንመለከታቸው ግን የታሪክ መጻሕፍቱ የእስራኤልን ታሪክ የተመለከቱት እግዚአብሔር ለዚህ ሕዝብ በሲና ተራራ ከሰጠው ቃል ኪዳን አንጻር ለመሆኑ ግልጥ ይሆናል። የታሪክ መጻሕፍትን የጻፉት የተለያዩ ጸሐፊዎች፥ የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ እግዚአብሔር በኦሪት ዘዳግም የሰጠውን ተስፋና ቃል ኪዳን እንዴት እንደፈጸመ የሚናገር ታሪክ መሆኑን ተገንዝበው ነበር። የእግዚአብሔር ሕዝብ ለቃል ኪዳኑ በሚታዘዙበት ጊዜ እግዚአብሔር ያከብራቸውና ይባርካቸው እንደ ነበር ያሳያሉ፤ ነገር ግን እስራኤላውያን በታሪካቸው ሁሉ ያጋጠሟቸው ችግሮች ቃል ኪዳኑን ለመታዘዝ ፈቃደኞች ያለመሆናቸው ውጤቶች እንደነበሩም ያመለክታሉ። የታሪክ መጻሕፍት ጸሐፊዎች ሊያሳዩን የፈለጉት ነገር እስራኤላውያን በርካታ ችግሮች እንደገጠሟቸውና በመጨረሻም የጠፉትና ወደ ምርኮ የተወሰዱት ለምን እንደሆነ ነው። ይህ የሆነው እግዚአብሔር ሕዝቡን መጠበቅ አቅቶት ሳይሆን፥ የኃጢአት ውጤት መሆኑን ለመግለጽ በመፈለጋቸው ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ጊዜ፥ የበረከት እጦት በኃጢአት ላይ የተሰጠ ፍርድ ውጤት መሆኑን መረዳት አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) አማኞች በእግዚአብሔር ፊት የተቀደሰ ሕይወት ለመኖር እንዲጠነቀቁ ለማድረግ ይህ እንዴት ይረዳል?

የታሪካዊ መጻሕፍት ጸሐፊዎች 

በታሪክ መጻሕፍት ሁሉ የሚታዩ የጋራ የሆኑ ዋና ሐሳቦች ቢኖሩም እንኳ መጻሕፍቱ በተለያዩ ሰዎች ተጽፈው በኋላ የተቀናበሩ ሳይሆኑ አይቀሩም። መጽሐፈ ኢያሱ፥ መሳፍንትና ሩት የተጻፉት የእስራኤል መንግሥት በተባበረ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። 1ኛ ና 2ኛ ሳሙኤል የተጻፉት ደግሞ በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት፥ ወይም የእስራኤል መንግሥት ለሁለት ከተከፈለ በኋላ ሳይሆን አይቀርም። ከ1ኛ ነገሥት እስከ መጽሐፈ ዕዝራ ድረስ ያሉ መጻሕፍት ደግሞ አይሁድ ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ የተጻፉ ናቸው። እነዚህ መጻሕፍት በተጻፉ ጊዜ ጸሐፊዎቹ ያኔ በነበሩት ሌሎች ታሪካዊ መጻሕፍት ተጠቅመው እንደጻፉ ይታመናል። እነዚያ መጻሕፍት ግን የእግዚአብሔር ቃል ስላልሆኑ፥ አንዳቸውም እስካሁን ድረስ አልቆዩም።

የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ዐበይት ክፍሎች 

የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ በሚከተሉት ዋና ዋና ጊዜያት ሊከፈል ይችላል፡-

  1. የእስራኤል ሕዝብ መመሥረት (ዘፍጥረት 12 – ዘዳግም መጨረሻ)፡- ይህ የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ የሚናገረው፥ ጅማሬያቸው እንዴት እንደሆነና የተስፋይቱን ምድር ወርረው ለመውረስ እስከተዘጋጁበት ጊዜ ድረስ ታላቅ ሕዝብ ወደ መሆን እንዳደጉ ነው። ዘመኑም ከ2100 ዓ.ዓ. እስከ 1400 ዓ.ዓ. ያለውን ጊዜ የሚያካትት ሲሆን፥ የእነዚህን ዓመታት ታሪክ በዚህ መጽሐፍ የመጀመሪያ ስድስት ምዕራፎች ውስጥ አጥንተነዋል።
  2. የተስፋይቱን ምድር መውረርና መውረስ (ኢያሱ)፡- የዚህ ዘመን ታሪክ የሚያሳየን የእስራኤል ሕዝብ የተስፋይቱን ምድር እንዴት እንደወረሩና ድል በማድረግ እንደወረሱ ነው፤ ዘመኑም ከ1400-1375 ዓ.ዓ. ነው።
  3. ዘመነ መሳፍንት (ከመጽሐፈ መሳፍንት – 1ኛ ሳሙኤል 8)፡- ይህ ዘመን ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው በተደጋጋሚ በተለያዩ ጠላቶች ስለ መሽነፋቸው በሚተርክ ዘገባ የተሞላ ከመሆኑ በስተቀር፥ ስለ ዘመኑ እምብዛም የምናውቀው ነገር የለም። መሳፍንት፥ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ከጠላቶቻቸው ያርፉ ዘንድ የሚያስነሣቸው ጊዚያዊ መሪዎች ነበሩ። ዘመነ መሳፍንት ከ1375 – 1050 ዓ.ዓ. ማለትም ሳኦል ንጉሥ እስከሆነበት ድረስ ያለው ጊዜ ነው። 
  4. የተባበረው የእስራኤል መንግሥት ዘመን (1ኛ ሳሙኤል 9 – 1ኛ ነገሥት 11፣ 1ኛ ዜና – 2ኛ ዜና 9)፡- ይህ ዘመን የእስራኤል ሕዝብ እንደ ታላቅ ሕዝብ የነበሩበት ዘመን ነው። ይህ ዘመን የመጀመሪያዎቹ ሦስት የእስራኤል ነገሥታት- ሳኦል፥ ዳዊትና፥ ሰሎሞን እያንዳንዳቸው 40 ዓመታት እስራኤልን የገዙበት ዘመን ነበር። በዚህ ክፍለ ዘመን ዋናው ትኩረት የነበረው በዳዊት ላይ ነው። በሙሉ ልቡ እግዚአብሔርን በመውደድና በእስራኤል ጠላቶች ላይ ድል በማድረግ ብዙ ነገሥታትን ለማንበርከክ እግዚአብሔር የተጠቀመበት ሰው፥ እንደ ዳዊት ያለ ታላቅ ንጉሥ እስራኤላውያን አይተው አያውቁም። ይህ የተባበረው የእስራኤል መንግሥት ዘመን ከ1050 – 930 ዓ.ዓ. ማለትም ከሰሎሞን ሞት በኋላ ሕዝቡ እስከተከፈለበት ድረስ የሚዘልቅ ነበር።
  5. የተከፋፈለው መንግሥት ዘመን (1ኛ ነገሥት 12 – 2ኛ ነገሥት 25፤ 2ኛ ዜና 10-36)፡- ከሰሎሞን ሞት በኋላ የእስራኤል ሕዝብ በሁለት መንግሥታት ተከፈለ። የሰሜኑ መንግሥት እስራኤል ተብሎ የተጠራ ሲሆን፥ የቆየውም ከ930 – 722 ዓ.ዓ ማለትም መንግሥቱ በአሦራውያን እጅ ወድቆ ሕዝቡ ወደ ምርኮ እስከተወሰዱበት ድረስ ነበር። የደቡቡ መንግሥት ደግሞ ይሁዳ ተብሎ የተጠራ ሲሆን፥ ከ930 – 586 ዓ.ዓ. ማለትም መንግሥቱ ፈርሶ በባቢሎናውያን ወደ ምርኮ እስከተወሰደበት ድረስ ቆይቷል።
  6. የምርኮ ዘመን (ሕዝቅኤልና ዳንኤል)፡- መጽሐፍ ቅዱስ ስለ 70ው ዓመት የምርኮ ዘመን የሚናገረው በጣም ጥቂት ነገር ነው፤ (586-536 ዓ.ዓ.)። እንደ እውነቱ ከሆነ፥ የይሁዳ ሕዝብ በምርኮ የቆየው ለ50 ዓመታት ብቻ ነው። ሰባው ዓመት የሚያመለክተው የመጀመሪያዎቹ የይሁዳ ሕዝብ ወደ ምርኮ ከሄዱበት ከ606 – 539 ዓ.ዓ. ማለት አይሁድ ወደ ከነዓን እስከተመለሱበት ድረስ ያለውን ጊዜ፤ ወይም ቤተ መቅደሱ ከፈረሰበት ከ 586 ዓ.ዓ ጀምሮ እንደገና እስከታደሰበት እስከ 516 ዓ.ዓ ድረስ ነው። 
  7. የይሁዳ መንግሥት ሕዝብ ከምርኮ መመለስ (ዕዝራና አስቴር)፡- በ536 ዓ.ዓ. የፋርስ መንግሥት የእስራኤልን ሕዝብ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ፈቀደ። የይሁዳ ሕዝብ በዘሩባቤል፥ በዕዝራና በነህምያ መሪነት እንደገና የራሳቸውን አስተዳደር መሠረቱ እንጂ የነበራቸውን ሉዓላዊነት ግን መልሰው አላገኙትም። በፋርስ ታላቅ መንግሥት ውስጥ እንደ አንድ ጠቅላይ ግዛት ነበሩ። ይህ ዘመን ከ536-400 ዓ.ዓ. ድረስ ቆይቷል። ከ400 ዓ.ዓ. በኋላ ያለውን ታሪክ ከብሉይ ኪዳን ውስጥ አናገኘውም። የብሉይ ኪዳን ታሪክ በሙሉ የሚናገረው እስከዚህ ዘመን ድረስ ስላለው ሁኔታ ብቻ ነው። በአዲስ ኪዳን መጀመሪያ ላይ የምናገኘው መጥምቁ ዮሐንስ እስኪመጣ ድረስ የእግዚአብሔርን ቃል የተናገረ የመጨረሻው ነቢይ ሚልክያስ

ነበር።

  1. 400 የጸጥታ ዓመታት፡- ከ400 ዓ.ዓ. ጀምሮ ክርስቶስ እስከመጣበት እስከ 4 ዓ.ዓ. ድረስ ስለነበረው ዘመን የሚናገር የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የለም። አንዳንዶቹ የአዋልድ መጻሕፍት በዚህ ጊዜ ስለተፈጸሙት አንዳንድ ጉዳዮች ይናገራሉ። እነዚህ ዓመታት በመለኮታዊ መንገድ፥ በእግዚአብሔር መንፈስ በመመራት ቃሉን ያስተላለፈ አንድም ነቢይ ስለ ሌለ፥ 400 የጸጥታ ዓመታት በመባል ይታወቃሉ።

መጽሐፍ ቅዱሳዊ የታሪክ አመለካከት

ታሪክን ስለምንረዳበት መንገድ የተለያዩ ባሕሎችና የተለያዩ አመለካከቶች አሉ። ታሪክን የምንረዳበት መንገድ ዛሬ በዘመናችንና በዙሪያችን የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ለመረዳትና ለመተርጎም ወሳኝ ነው። ቀጥሉ ሰዎች ታሪክን የሚረዱባቸውን ሦስት ዋና ዋና መንገዶች እንመለከታለን፡-

  1. ጣዖት አምላኪዎች ታሪክን የሚመለከቱበት መንገድ፡- በጥንት ዘመንም ሆነ ዛሬ በአብዛኛው የዓለም ክፍል (አፍሪካ፥ እስያ፥ ደቡብ አሜሪካ) ሰዎች ታሪክን የሚረዱት ሰው ሊቆጣጠረው የማይችል፥ የማያቋርጥ ክስተት ሂደት እንደሆነ አድርገው ነው። ይህ አመለካከት በዓለም ላይ ለሚፈጸሙ ድርጊቶች ምክንያቶቹ ልንታመንባቸው የማንችል ጣዖታት ናቸው የሚል ዝንባሌ አለው። አንድ ጊዜ በረከትን በሌላ ጊዜ ደግሞ ጥፋትን ያመጣሉ። ይህንን የሚያደርጉበት ግልጽ የሆነ መንገድ የለም፡፡ ይልቁንም እኛ ሰዎች እንደመሆናችን በእነርሱ ምሕረት ሥር እንገኛለን። ስለዚህ ለጉዳዩ ከመገዛትና እንደ ሙስሊሞች «አላህ ከፈቀደ» ከማለት በስተቀር ምንም ምርጫ የለንም። ልናደርግ የምንችለው ብቸኛው ነገር፥ አማልክትን ደስ የሚያሰኛቸውን መልካም ተግባራት ለመፈጸም መሞከር ነው። እኛ ለእነርሱ መልካም ከሆንን እነርሱም መልካም ሊሆኑልን ይችላሉ ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። በዚህ አመለካከት ታሪክን መጻፍ፥ ሰዎች ስለ ስኬታማነታቸው እንዲመኩ ከማድረግ ሌላ የሚፈይደው ነገር በጣም ትንሽ ነው። ታሪክ በሥልጣን ላይ ላሉ ሰዎች መግዛት መብታቸው መሆኑን የማረጋገጥ መሣሪያ ይሆናል ወዘተ።
  2. ዓለማዊው የምዕራባውያን አመለካከት፡- ዛሬ በትምህርት ቤት የምንማረው ታሪክ የተመሠረተው በሌላ ዓይነት የታሪክ አመለካከት ላይ ነው። ይህ አመለካከት በተለይ በአውሮጳና በሰሜን አሜሪካ ድጋፍ ያለው ሲሆን፥ ታሪክ በምድር ላይ የሚፈጸሙ ክስተቶች ዘገባ ነው ይላል። እንደዚህ አመለካከት፥ ታሪክ የሚወሰነው በእግዚአብሔር ሳይሆን በሰው ብቻ ነው። ታሪክን የምናጠናው፥ ሰው የሠራውን ስሕተት በማየትና ባለፈው ጊዜ ከተፈጸሙ ድርጊቶች ልምድ በመውሰድ በምድር ላይ ለራሳችን የተሻለ ሕይወት ለመኖር ነው። ይህ የታሪክ አመለካከት፥ ለተአምራትም ሆነ ለእግዚአብሔር ቦታ የለውም። በምድር ላይ የሚፈጸሙ ነገሮች፥ ጥፋቶችም ሆኑ ጦርነቶች ሁሉ በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት ለመፈጸማቸው አንዳችም መረጃ የለም፤ በተፈጥሮ የሚሆኑ ናቸው ይላሉ። በዚህ የታሪክ አመለካከት፥ ምን እንደተፈጸመ መመዝገብና ማስቀመጥ ከሁሉ የበለጠ አስፈላጊ ነገር ነው። ከዚያም ታሪክ አዋቂዎች ክስተቱ የተፈጸመው በምን ምክንያት እንደሆነ ይመረምራሉ። 
  3. መጽሐፍ ቅዱስ ታሪክን የሚመለከትበት መንገድ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እግዚአብሔር በሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚሠራው ሥራ ውጤት ነው በማለት ያስተምረናል። በምድር ላይ የሚፈጸሙ ነገሮች ሁሉ በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር ያሉ ናቸው። ከመጀመሪያው አመለካከት በተቃራኒ፥ እግዚአብሔር ግልጽ የሆነ ዕቅድ እንዳለውና በምድር ላይ የሚፈጸሙ ነገሮች ሁሉ የዚያ ዕቅድ አካል ናቸው በማለት ያስተምረናል። የእግዚአብሔር ዕቅድ መጀመሪያ የነበረው (የፍጥረታት መፈጠር ታሪክ) እና ወደ መጨረሻውም (የዘላለማዊ መንግሥት) እያዘገመ ያለው ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በምድር ላይ የሚፈጸሙ ነገሮች በሙሉ በእግዚአብሒር ቁጥጥር ሥር እንደሆነ ያምኑ ነበር። ስለዚህ ታሪክን በሚጽፉበት ጊዜ፥ ያተኮሩት በክስተቶች ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ ነበር። የታሪክ መጻሕፍት ዓላማ እግዚአብሔር የገባውን ቃል ኪዳን ለመፈጸም በታሪክ ውስጥ እንዴት እንደሚሠራ ማሳየት ነው። ጸሐፊዎቹ ጽሑፎቻቸውን የሚያነቡ ሰዎች እግዚአብሔር የፈጸመውን ድርጊት ለምን በዚያ መልክ እንደፈጸመውና በሕዝብ ላይ ለምን እንደፈረደ እንዲረዱላቸው ይፈልጉ ነበር። እግዚአብሔር ታሪክን ወደ አንድ ትልቅ ዓላማ በመምራት ላይ እንደሆነ ግልጽ ቢሆንም፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ ተግባር እርሱ የሚሰጣቸውን ምላሽ የሚወስን እንደነበር አስተምረዋል። ድርቅ፥ የመሬት መንቀጥቀጥ፥ ሕዝብና መሪዎች በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር መሆናቸው በግልጽ ሰፍሮአል፡፡ እግዚአብሔር ታሪክን እየመራና እየሠራ የታሪክ የመጨረሻ ማጠቃለያ ወደሆነው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መመሥረት እያቃረበው ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህ ሦስት የታሪክ አመለካከቶች ተግባራዊ ሆነው ያየህባቸውን ምሳሌዎች ጥቀስ። ለ) እነዚህ የታሪክ አመለካከቶች እያንዳንዳቸው ዛሬ በዓለም ላይ ባለን አመለካከት ላይ እንዴት ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ግለጽ። ሐ) በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በምናልፍበት ጊዜ፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊው የታሪክ አመለካከት የሚያበረታታን እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “የታሪካዊ መጻሕፍት መግቢያ”

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading