የመጽሐፈ ኢያሱ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ መዝ. (91)፡1-16 አንብብ። ሀ) በጠላቶቻችን ላይ ስለምንቀዳጀው ድል በዚህ ስፍራ የተሰጡ ተስፋዎች ምንድን ናቸው? ለ) እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ድል የሰጠህን አንዳንድ ጠላቶች ጥቀስ። ሐ) እግዚአብሔር፥ ቤተ ክርስቲያንህ በእነርሱ ላይ ድል እንድትጎናጸፍ ያደረጋትን አንዳንድ ችግሮችንና ጠላቶችን ጥቀስ።

መጽሐፈ ኢያሱ በእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላቶች ላይ ስለተገኘ ድል የሚናገር መጽሐፍ ነው። ዛሬም እኛ ድልን እንዴት እንደምናገኝ የሚያስተምረን መጽሐፍ ነው። ድልን የምናገኘው ለእግዚአብሔር ስንታዘዝ፥ በተቀደሰ ሕይወትና በእግዚአብሔር ላይ ባለን እምነት ስንመላለስ ብቻ ነው። ይህ መጽሐፍ ዛሬም ለእኛ የሚሆን በጣም አስፈላጊ መልእክት አለው። እግዚአብሔር እያንዳንዳችን ኃጢአትን፥ ሰይጣንን ወዘተ. ድል በማድረግ እንድንኖር ይፈልጋል። ቤተ ክርስቲያን እንደ መሆናችንም እግዚአብሔር በድል እንድንኖር ይፈልጋል። መጽሐፈ ኢያሱ በግልም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ደረጃ በድል እንዴት እንደምንመላለስና የእግዚአብሔርን ጠላቶች ሁሉ እንደምናሸንፍ ሊያስተምረን ይችላል።

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ መጽሐፈ ኢያሱና ስለ ኢያሱ ሕይወት ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ሀ) ስለ ኢያሱ ማንነት የተጠቀሱትን ነገሮች በሙሉ ዘርዝር። ለ) የመጽሐፈ ኢያሱ ጸሐፊ ማን ነው?

የመጽሐፈ ኢያሱ ጸሐፊና የተጻፈበት ጊዜ

መጽሐፈ ኢያሱን የጻፈው ማን ነው? የሚለው ጥያቄ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራንን አከራክሮአል። መጽሐፉን የጻፈው ማን ነው? የሚለውን ጥያቄ በሚመለከት ሦስት የተለያዩ አሳቦች አሉ፡- 

  1. አንዳንዶች መጽሐፈ ኢያሱ የተጻፈው በታሪኩ ውስጥ የሚገኙ ድርጊቶች ከተፈጸሙ ከ800 ዓመታት በኋላ ነው፤ የተጻፈውም ኦሪት ዘዳግምንና እስከ 2ኛ ነገሥት ያሉትን ሌሎች የታሪክ መጻሕፍትን በጻፈው ሰው ነው ይላሉ። ሆኖም በመጽሐፈ ኢያሱ ውስጥ የተሰጡትን ታሪካዊ ዘገባዎች ከተመለከትን መጽሐፈ ኢያሱ የተጻፈው ከዳዊት በፊት እንደሆነ ግልጥ ነው። ለምሳሌ፡- ኢየሩሳለም አልተወረረችም ነበር። 
  2. አንዳንዶች መጽሐፉን የጻፈው ኢያሱ ነው ይላሉ፤ ይህም ስለ ሞቱ ከሚናገረው ክፍል በቀር መጽሐፉን በሙሉ የጻፈው ኢያሱ ነው የሚለው የአይሁድ አመለካከት ነው። ከመጽሐፈ ኢያሱ 18:8 ና 24፡25-26 እንደምንመለከተው፥ ኢያሱ አንዳንድ ነገሮችን ጽፎአል። ስለ ጦርነቶቹና ስለ ተካሄደባቸው ስፍራዎች ከሚሰጠው ገለጻ አንፃር፥ ጸሐፊው ድርጊቱ ሲፈጸም በዓይኑ ያየ ሰው ይመስላል። ይሁን እንጂ ጸሐፊው ኢያሱ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አይናገርም። መጽሐፉን የጻፈው ኢያሱ እንደሆነ የሚናገር ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የለም።
  3. ከኢያሱ ዘመን በኋላ፥ ምናልባትም በሳሙኤል ጊዜ መጽሐፈ ኢያሱ ተጽፎ፥ ወይም ተቀናብሮ ይሆናል። በመጽሐፈ ኢያሱ ውስጥ የመጽሐፉ የመጨረሻ ቅንብር የተከናወነው ኢያሱ ከሞተ ከብዙ ጊዜ በኋላ መሆኑን የሚጠቁም፥ «እስከዚህ ቀን ድረስም» የሚል ቃል ከ12 ጊዜ በላይ ተጠቅሶአል።

ስለዚህ የመጽሐፈ ኢያሱ ጸሐፊ አይታወቅም፥ ነገር ግን የመጸሐፉ ሥራ የተጠናቀቀው በዳዊት ጊዜ በ1000 ዓ.ዓ. ነው ማለቱ ይሻላል።

ከነዓንን የመውረር ታሪካዊ ሥረ – መሠረት 

  1. ከነዓንን ለመቆጣጠር የተደረገ ጦርነት ከፔንታቱክ መጽሐፍ ጥናታችን እንዳየነው፥ የከነዓን ምድር ተፎካካሪ የሆኑ መንግሥታት ጦር ሜዳ ነበረች። ከ2000 – 1780 ዓ.ዓ. በአብርሃም ጊዜ ከነዓን በግብፅ ግዛት ሥር ነበረች። የግብፅ ኃይል በደከመና በቀነሰ ጊዜ በሐይክሶሳውያን ተውግታ ድል ሆነችና ከ1780-1550 ዓ.ዓ. በቁጥጥራቸው ሥር ሆነች። ግብፃውያን ሐይክሶሳውያንን አስወጥተው እንደገና ገናና መንግሥት ሆኑና አይሁድን በባርነት ገዟቸው። በ1440 ዓ.ዓ. አካባቢ የግብፃውያን ኃይል ቀነሰና እግዚአብሔር አይሁዳውያንን ከግብፅ ኃይል ነጻ አደረጋቸው። በዚህ ጊዜ ግብፃውያን በከነዓን ላይ የነበራቸውን የበላይነት አጡ።

በ1460 ዓ.ዓ. ከጳለስጢና በስተሰሜን እጅግ ራቅ ብሎ (በአሁኑ ዘመን ቱርክ በሚባለው ስፍራ) ሌላ ሕዝብ ተነሣ። ይህ ሕዝብ ኬጢያዊ ይባል ነበር። ይህ ሕዝብ ግብፅን አሸነፈና በሰሜን ከነዓን ላይ ጊዜያዊ የሆነ የበላይነት አገኘ። በዚሁ ጊዜ የአሦር መንግሥት ተነሣ ይህችን የተስፋ ምድር ለመውረስ የሚዋጉ ሦስት ትላልቅ መንግሥታት ስለነበሩ፥ በከነዓን ውስጥ የሚደረጉ በርካታ ጦርነቶች ቢኖሩም፥ ከነዓንን የተቆጣጠረ አንድም መንግሥት አልነበረም። ይህ ጦርነት ኬጢያውያን ከተደመሰሱ በኋላ ግብፅ በከነዓን ላይ እንደገና የበላይነትን እስከተቀዳጀችበት እስከ 1280 ዓ.ዓ. ድረስ ቀጠለ።

ይህም ማለት እግዚአብሔር እስራኤልን ነፃ ለማውጣትና ለአብርሃም በገባው ቃል መሠረት፥ የከነዓንን ምድር ለመስጠት በተዘጋጀበት ጊዜ፥ ግብፅ በኃይሏ እንድትዳከም ሁኔታዎችን አመቻችቶ ነበር። በኋላም በ1300 ዓ.ዓ. በመሳፍንት ዘመን በመጽሐፉ ውስጥ ባይጠቀስም እንኳ ግብፅ እንደገና ኃያል አገር በመሆን ከነዓንን ተቆጣጥራ ነበር።

የዓለምን ታሪክ በምናጠናበትና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በምናወዳድርበት ጊዜ እግዚአብሔር በታሪክ ሁሉ አይሁዳውያን ከምርኮ ነፃ የሚወጡበትን መንገድ ለማዘጋጀትና ከነዓንን እንዲወርሱ ለማድረግ እንደሠራ በመገንዘብ እንደነቃለን። አይሁዳውያን ከባርነት ነፃ ለመውጣት የቻሉት ግብፃውያን በዚያን ጊዜ ደክመው ስለነበር ነው። ሦስት መንግሥታት ከነዓንን ለመውረስ በመታገል ላይ ስለነበሩ አንድ ታላቅና የታወቀ ኃይል የከነዓንን ምድር ለመቆጣጠር አልቻለም፤ ስለዚህ እስራኤላውያን እንደ ግብፅ፥ ኬጢያውያንና አሶራውያን ያሉ ታላላቅ መንግሥታት ጣልቃ ሳይገቡ ወረራ በማካሄድና ድል በማድረግ የከነዓንን ምድር ለመውረስ በቅተዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር በሕዝብ ሁሉ ላይ ተቆጣጣሪ እንደሆነና ይህንም በማድረጉ ለሕዝቡ ያለውን ዓላማ ለመፈጸም እንደሚሠራ ይህ ክፍል ምን ያስተምረናል? ለ) ይህንን መረዳት ዛሬ ለእኛ የሚሰጠው መጽናናት ምንድን ነው?

የከነዓናውያን የፖለቲካ መዋቅር

ከነዓን በአንድ ንጉሥ ሥር ተጠቃልላ የምትተዳደር ምድር አልነበረችም። ይህም ራሱ ምድሪቱን ለመውረር ቀላል አድርጎታል። ከነዓን የምትተዳደረው «የከተማ ግዛቶች» በመባል ይታወቁ በነበሩ ትናንሽ መንግሥታት ነበር። ይህም ማለት በአካባቢው ያለው መሬት በአንዲት ሰፊና ትልቅ ከተማ ሥር ሆኖ በንጉሥ ይገዛ ነበር ማለት ነው። በመሆኑም የንጉሡ ሥልጣን በአካባቢያቸው ላለው ምድር ብቻ ነበር። እነዚህ ከተሞች በጠላቶቻቸውና በወራሪ ዘላኖች እንዳይደፈሩ በትላልቅ ቅጥሮች የተከበቡ ነበሩ። እነዚህ የከተማ ግዛቶች ብዙ ጊዜ በውጭ ኃይል ቁጥጥር ሥር የሆኑና ለእነዚህ ኃይላት የሚገብሩ ነበሩ። እነዚህ ትናንሽ የከተማ ግዛቶች ጠላቶች ሊያጠቋቸው በሚመጡበት ጊዜ፥ በቃል ኪዳን ይተባበሩና የጠላቶቻቸውን ጥቃት ለመመከት ይታገሉ ነበር። ይህ ሁሉ በመጽሐፈ ኢያሱ ውስጥ ተንጸባርቆአል። የከነዓን ምድር አቀማመጥ አገሪቱ አንድ ሆና በአንድ ንጉሥ እንድትተዳደር የማያስችላት ስለነበረና ብዙ ጊዜ እንደ ግብፅ ባሉ ውጫዊ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ስለነበረች ለተፈጸመው ታሪካዊ ሁኔታ በዚህ መልክ ተደራጅታ ነበር።

በዚህ ሳይቀር የእግዚአብሔርን እጅ እናያለን። አንድ የሆነና የተባበረ መንግሥት ስላልነበረ ለኢያሱና ለእግዚአብሔር ሕዝብ ትናንሽ ከተሞችን ወይም የትናንሽ ከተሞችን ኅብረት ለማጥቃት ቀላል ነበር። በመጽሐፈ ኢያሱ ጥናታችን፥ ኢያሱ ምድሪቱን በአጠቃላይ ለመውረስ ሦስት ዋና ዋና የከተማ ግዛት ፌዴራላዊ ኅብረቶችን ብቻ ማሸነፍ እንደነበረበት እናያለን። 

ከነዓን ለዓለም የነበራት አስፈላጊነት

የከነዓን ምድር ብዙ ሕዝብ ያልነበረባት ብትሆንም ለቀረው ዓለም በጣም ተፈላጊ ነበረች። አስፈላጊነቷ በነበራት ሀብት አልነበረም። አስፈላጊነቷ የሦስት ክፍለ ዓለማት፡- የአውሮፓ፥ የአፍሪካና የእስያ መገናኛ ስለነበረች ነው። ስለዚህ የበርካታ ንግዶች መተላለፊያ ነበረች። የዚህ ዓይነት የንግድ መተላለፊያ ስለነበረችና ጠቃሚ የወደብ አገልግሎት ስለ ነበራት ለመካከለኛው ምሥራቅ ኢኮኖሚ ካላት ጠቀሜታ አንፃር፥ ትላልቅ መንግሥታት እርሷን ለመቆጣጠር ይዋጉ ነበር።

የከነዓናውያን ሃይማኖት

የውይይት ጥያቄ፥ ዘፍ. 15፡16 አንብብ። በዚህ ስፍራ እግዚአብሔር የአሞራውያን ኃጢአት ምንድን ነው ይላል? (አሞራውያን የሚለው ስም የከነዓናውያን ሌላ ስም ነው)።

በቅርብ ዓመታት የከርሰ ምድር ተመራማሪዎች ስለ ከነዓናውያን ጥንታዊ ማምለኪያ ስፍራዎች በርካታ ነገሮችን አግኝተዋል። የከነዓናውያን ሃይማኖት እጅግ የተበላሸ በመሆኑ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት እንደነበር አረጋግጠዋል። ሃይማኖታቸው በርካታ አማልክት ያሉት ብቻ ሳይሆን በብዙ የፍትወተ ሥጋ ኃጢአት ላይ የተመሠረተ፥ ወንዶችና ሴቶች በማምለኪያ ስፍራዎች በግልሙትና የተጠመዱበት፣ ፍትወተ ሥጋ ከእንስሳት ጋር ሁሉ የሚፈጸምበት ሃይማኖት ነበር። ልጆቻቸውንም ለጣዖቶቻቸው ይሠዉ ነበር።

ከነዓናውያን ከ70 የሚበልጡ የተለያዩ ተባዕትና እንስት አማልክት እንደነበሩ ያምኑ ነበር። እነዚህ ሁሉ የሁለት ዋና ዋና አማልክት – ኤል እና አሼራህ የሚባሉ ልጆች እንደሆኑ ያምኑ ነበር። ኤል ዋና አለቃ የሆነው አምላክ ሲሆን፥ ስሙ አይሁድ የእግዚአብሔር ስም አድርገው ይጠቀሙበት ለነበረው ኤሎሂም መሠረት ነው። ይህን አምላክ ብዙ ጊዜ ከኮርማ ወይም በሬ ምስል ጋር ያያይዙት ነበር። የሚስቱ ስም አሴራ ነበር፤ (2ኛ ነገሥት 21፡7 አዲሱን የአማርኛ ትርጉም ተመልከት)። ከልጆቻቸው ዋና ከነበሩት መካከል አንዱ በአል ሲሆን የስሙ ትርጉምም ጌታ ማለት ነው። እርሱ የሌሎቹ አማልክት ሁሉ ጌታ ሲሆን ሰማይና ምድርን፥ ዝናብን፥ ወዘተ ይቆጣጠር ነበር። ሁለት ሚስቶች አግብቶ ነበር። አንደኛዋ የጦርነት አምላክ የነበረችው «እኅቱ» አናት ነበረች። ሁለተኛዋ ሚስቱ ደግሞ «አሽቶሪዝ» ተብላ የምትጠራው የምሽት ኮከብ አምላክ የነበረችዋ ናት። «ሞት» የተባለው የሞት አምላክ ሲሆን፥ የበአል ጠላት ነበር። «ዮምም» የባሕር አምላክ የነበረና ከበአል ጋር ተጣልቶ የተሸነፈ ነው። «ሞሌክ» የአሞን አምላክ ሲሆን ብዙ ጊዜ ሰውን ከመሠዋት ጋር ይያያዝ ነበር። እነዚህ ከነዓናውያን ያመልኩአቸው ከነበሩ አማልክት ጥቂቶቹ ናቸው።

እግዚአብሔር አንድ ቀን የአሞራውያን ወይም የከነዓናውያን የኃጢአት ጽዋ ሲሞላ የሚፈርድበት ጊዜ እንደሚመጣ ለአብርሃም ተናግሮ ነበር። ያ የፍርድ ጊዜ እስራኤላውያን ወደ ከነዓን ለመግባት ወረራ ባካሄዱ ጊዜ ተፈጸመ።

አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሔር ከነዓናውያንን ሙሉ በሙሉ እንዲያጠፉ እስራኤላውያንን አዝዞአቸው ነበር የሚለውን ትእዛዝ ለመቀበል ይቸገራሉ (ዘዳ. 7፡16፤ 20፡17-18 ተመልከት)። ይህ ቅን ፍርድ አይደለም ብለው ያስባሉ። ነገር ግን አራት ነገሮችን በቀጥታ ማስታወስ ይገባናል፡-

1) እግዚአብሔር በፈለገው መንገድ በኃጢአትና በኃጢአተኞች ላይ የመፍረድ መብት አለው። በበሽታ ወይም በሞት ሊቀጣ ይችላል። ደግሞም ሌሎች ሰዎችን በመቅጫ መሣሪያነት ሊጠቀም ይችላል። እግዚአብሔር በምሕረቱ ለከነዓናውያን ከኃጢአታቸው ንስሐ ገብተው እንዲመለሱ 400 ዓመታት ሰጥቶአቸው ነበር። ይህንን ዕድል ለመጠቀም ስላልፈቀዱ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን የፍርድ መሣሪያው አድርጎ ተጠቀመባቸውና የከነዓናውያንን ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆቻቸውን ሁሉ እንዲያጠፉ አዘዛቸው።

2) ከነዓናውያን ይህንን ፍርድ በራሳቸው ላይ ያመጡት፣ በእግዚአብሔርና እርሱ በልባቸው ባኖረላቸው ሕግጋት ላይ በግልጽ ስላመፁ ነው። ልባቸውን በእግዚአብሔር ላይ አደነደኑ (ኢያ. 11፡18-20)።

3) እግዚአብሔር፥ ከነዓናውያንን በሙሉ እንዲያጠፏቸው እስራኤላውያንን ያዘዘው አይሁድን ወደ ጣዖት አምልኮ እንዳይመልሱ ነበር፤ (ዘዳግ. 20፡16-17)። ይህንን ባለማድረጋቸው፥ ወዲያውኑ ከነዓናውያን እስራኤላውያንን ሲያስኮበልሉና የብልሹ ምግባሮቻቸው ሰለባዎች ሊያደርጉአቸው እንመለከታለን። እንዲያውም በመጨረሻ እስራኤላውያን ከእነርሱ ብሰው በመገኘታቸው እግዚአብሔር እንደፈረደባቸው እንመለከታለን፤ (2ኛ ነገሥት 21፡9)።

4) የከነዓን ምድር የእግዚአብሔር እንጂ የከነዓናውያን አይደለም። ስለዚህ እግዚአብሔር ለፈለገው ሰው ሊሰጠው መብቱ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ነገሥት 17፡7-23፤ 21፡9ን አንብብ። ሀ) እስራኤላውያን የሠሩትን ኃጢአትና የተፈረደባቸውን ፍርድ ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር ኃጢአትን ስለ መጥላቱ ይህ ነገር ምን ያስተምረናል? ሐ) ኃጢአትን እንዴት መጥላት እንዳለብንና በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ እንዳይስፋፋ እንዴት መጠበቅ እንዳለብን ከዚህ ምን እንማራለን? መ) ኃጢአት እንዳይስፋፋ ቤተ ክርስቲያንህ ልታደርግ ትችላለች ብለህ የምታስባቸውን ነገሮች ዘርዝር።

ምሁራን የመጽሐፈ ኢያሱ ታሪክ እጅግ አከራክሮአቸዋል። በተለይ ደግሞ የታሪኩን በትክክል መመዝገብ የሚጠራጠሩ አሉ። የሚከራከሩባቸውም ዋና ዋና ሐሳቦች ሦስት ናቸው፡

  1. የእስራኤል ሕዝብ ከነዓንን መቼ እንደወረሩ፡- መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚያሳየው የእስራኤል ሕዝብ ወደ ከነዓን የገቡት በ1400 ዓ.ዓ. ነበር። ሐሳባቸውን በከርሰ ምድር (አርኪዮሎጂ) ጥናት ላይ የመሠረቱ አዋቂዎች እስራኤላውያን ወደ ከነዓን ምድር የገቡት ብዙ ቆይተው ወደ 1250 ዓ.ዓ. ገደማ ነው ይላሉ።
  2. የእስራኤል ሕዝብ ከነዓንን ወርረው ምድሪቱን በአጠቃላይ የያዙት ምንኛ ፈጥነው ነው፡- ሌሎች ምሁራን ከነዓንን የመውረርና የመያዝ ነገር ቀስ በቀስ በብዙ ክፍለ-ዘመናት የተፈጸመ ስለሆነ እስራኤላውያንም ምድሪቱን የወረሱት ቀስ በቀስ ነው ይላሉ። ጥቂት ምሁራን ደግሞ እስራኤላውያን 600000 ተዋጊ ሰዎች ቢኖሯቸው ኖሮ ማንም ሊቋቋማቸው እስከማይችል ድረስ በአጭር ጊዜ ምድሪቱን ሊወርሱ ይችሉ ነበር ይላሉ። ሌሎቹ ደግሞ እስራኤላውያን ምድሪቱን ለመውረስ ችግር ገጥሟቸው ነበርና፥ ይህን ያህል ተዋጊ ኃይል አልነበራቸውም፤ በማለት ከነዓንን ለመያዝ በቁጥርና በኃይል እስኪያድጉ ድረስ ብዙ ዓመታት ፈጅቶባቸዋል ይላሉ።

ከነዓንን በጦርነት የመውረርና የመያዝ ተግባር ልክ በመጽሐፈ ኢያሱ እንደተጻፈው በአጭር ጊዜ በ1400 ዓ.ዓ. የተፈጸመ ነው የሚለውን አቋም መያዝ ከሁሉም የተሻለ ነው።

  1. በጣም የተለያዩና እርስ በርስ የሚጋጩ ሆነው የሚታዩ ቢመስሉም፥ መጽሐፈ ኢያሱና መሳፍንት እርስ በርስ የተያያዙት እንዴት ነው? አንዳንድ ምሁራን መጽሐፈ ኢያሱና መሳፍንት እርስ በርስ የሚቃረኑ ናቸው ይላሉ። መጽሐፈ ኢያሱ የሚያስተምረው፡- እስራኤላውያን ከነዓንን እንደወረሩና እንደተቆጣጠሩ ነው፤ መጽሐፈ መሳፍንት ግን ምድሪቱን ለመቆጣጠር እንዳልቻሉ ያሳያል ይላሉ።

ነገር ግን እነዚህን መጻሕፍት በጥልቀት ስናጠና በመካከላቸው ምንም ቅራኔ እንደሌለ እንገነዘባለን። መጽሐፈ ኢያሱ አብዛኛው የከነዓን ምድር እንደተወረረና እንደተያዘ ቢናገርም (ኢያ. 11፡23፤ 21፡43-45)፣ አንዳንድ የምድሪቱ ክፍሎች አለመያዛቸውንም አይሸሽግም፤ (ኢያ. 13፡1-6፤ 23፡4-5፥ 13)። ሁለቱ መጻሕፍት ሁለት የተለያዩ ዓላማዎች አሏቸው። መጽሐፈ ኢያሱ የሚናገረው፣ እግዚአብሔር የተስፋ ቃሉን እንዴት እንደፈጸመና ለእስራኤላውያን በጠላቶቻቸው ላይ እንዴት ድል እንደሰጣቸው ነው። በኢያሱ ዘመን መጨረሻ ምድሪቱ በሙሉ በእስራኤል ቁጥጥር ሥር ሆና ነበር፤ ዋና ዋና የተባሉ ጠላቶችም ተሸንፈው ነበር። ነገር ግን በምድሪቱ የነበሩት ጠላቶቻቸውን ሁሉ ለማስወጣት ሳያቋርጡ መታገልና መዋጋት የእስራኤላውያን ኃላፊነት ነበር። መጽሐፈ መሳፍንት የሚያሳየው ግን እግዚአብሔር እስራኤላውያን በጠላቶቻቸው ሁሉ ላይ ድል የሰጣቸው ቢሆንም፥ መዋጋታቸውን አቁመው ምድሪቱ ላይ ሰፍረው ቁጭ እንዳሉ ነው። ምድሪቱን ሁሉ ለመያዝ ሙከራ ባለማድረጋቸው፥ እግዚአብሔር የድል ክንዱን ከእነርሱ ላይ አነሣ። ስለዚህ በጠላቶቻቸው ላይ ድልን ለማግኘት አልቻሉም። አይሁድ በቀረው ታሪካቸው በሙሉ ባገኙት ድል ለመቀጠል ባለመዋጋታቸውና እግዚአብሔር በመራቸው መሠረት ጠላቶቻቸውን በሙሉ ባለማጥፋታቸው ችግር ውስጥ ገብተው እናያቸዋለን።

የውይይት ጥያቄ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በከፊል ስለ መታዘዝ ከዚህ የምናገኘው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው?

የመጽሐፈ ኢያሱ አስተዋጽኦ 

የሚከተለውን የመጽሐፈ ኢያሱን አስተዋጽኦ አጥና፡-

  1. የእስራኤላውያን ወደ ከነዓን መግባት (ኢያሱ 1-4)
  2. እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን እንደ አሸነፉ (ኢያሱ 5-12)

ሀ. ጠላቶቻቸውን ለማሸነፍ ያደረጉት ዝግጅት (ኢያሱ 5) 

ለ. በከነዓን መካከለኛ ክፍል ባሉ ጠላቶች ላይ የተደረገ ዘመቻ (ኢያሱ 6-8) 

ሐ. በደቡብ ከነዓን በሚገኙ ጠላቶች ላይ የተደረገ ዘመቻ (ኢያሱ 9-10) 

መ. በሰሜን ከነዓን በሚገኙ ጠላቶች ላይ የተደረገ ዘመቻ (ኢያሱ 11) 

ሠ. በእስራኤላውያን የተሸነፉ ጠላቶች ዝርዝር ማጠቃለያ (ኢያሱ 12) 

  1. የምድሪቱ ለልዩ ልዩ የእስራኤል ነገዶች መከፋፈል (ኢያሱ 13-21) 
  2. ኢያሱ ለተለያዩ ነገዶች ያደረገው የስንብት ንግግር (ኢያሱ 22-24)

ኢያሱ የእስራኤል ሕዝብ መሪ 

በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኙ ታላላቅ የእምነት ሰዎችን ያህል ስለ ኢያሱ የተነገረ ባይሆንም፥ ኢያሱ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ነበር። ኢያሱ ከኤፍሬም ነገድ ሲሆን የመጀመሪያ ስሙ አውሴ ነበር፤ ትርጉሙም «ድነት (ደኅንነት)» ማለት ነው፤ (ዘኁ. 13፡8)። በኋላ ሙሴ ስሙን ኢያሱ አለው፤ ትርጉሙም «ጌታ ያድናል» ማለት ነው።

ማስታወሻ፡- «ኢየሱስ» የሚለው ስም ኢያሱ (ጆሽዋ) ከሚለው የተወሰደ የግሪክ ስም ነው፤ ስለዚህ ኢየሱስ በአራማይክ ቋንቋ ኢያሱ ተባለ።

ኢያሱ በግብፅ፥ በባርነት ያደገ ሰው ነው። እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ ከወጡ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ የእስራኤል ጦር አዛዥ ስለሆነ፥ አንዳንድ ሰዎች የአንድ የግብፅ የጦር መሪ ባሪያ የነበረ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ፤ (ዘጸ. 17፡8-13)። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ ሲያወጣ የተመለከተ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በእግዚአብሔር ላይ ዓምዖ አያውቅም። በ40 ዓመታቱ የምድረ በዳ ጉዞም የሙሴ ረዳት እንዲሆን ተመርጦ ነበር። ከሙሴ ጋር ወደ ሲና ተራራ ወጥቶ ነበር። ሙሴ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ካየ ወዲህ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አብሮት የነበረው ኢያሱ ለእግዚአብሔር ያለውን ታላቅ ፍቅር ለማሳየት በእግዚአብሔር ፊት ቆየ፤ (ዘጸ. 33፡11)። ከ12 ነገዶች የተመረጡ ምድሪቱን እንዲሰልሉ በተላኩ ጊዜ፥ ኢያሱ የኤፍሬምን ነገድ ወክሎ ሄደ፤ ከካሌብም ጋር በመሆን የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ማመንና ወደ ምድሪቱ መግባት እንዳለባቸው ተናገረ፤ በውጤቱም እግዚአብሔር እምነቱን አከበረና ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደሚገባ ነገረው። እግዚአብሔር ሙሴን፥ ከእርሱ ቀጥሎ የሚመጣ መሪ አድርጎ ኢያሱን እንዲመርጠው ተናገረ። በኃይልም አስታጠቀው፤ (ዘዳ. 31፡14)። በኢያሱ መሪነት እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ወደ ከነዓን ምድር መራቸው። በከነዓናውያን ላይም ድልን ሰጣቸው። ኢያሱ የእስራኤልን ሕዝብ የመራው ከ25-30 ዓመታት ለሚደርስ ጊዜ ሲሆን፥ በመጨረሻም ሲሞት በኤፍሬም ምድር ተቀበረ። ኢያሱ ከመሞቱ በፊት በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል የነበረውን ቃል ኪዳን አደሰ። ለእግዚአብሔር የነበረው ፍቅር ለእስራኤላውያን ባቀረበው ምርጫ ታውቋል፡- «የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን» አላቸው (ኢያ. 24፡15)።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደመሆናችን፥ ዛሬ እግዚአብሔር ከእኛ ስለሚፈልገው ነገር የኢያሱ ሕይወት መልካም ምሳሌ የሆነው እንዴት ነው? ለ) ከኢያሱ ሕይወት ውስጥ ከምታየው ባሕርይ በሕይወትህ ልታያቸው የምትፈልጋቸውን ነገሮች ዘርዝር።

የመጽሐፈ ኢያሱ ርእሰ 

መጽሐፉ፥ መጽሐፈ ኢያሱ ወልደነዌ የሚለውን ስም ያገኘው በውስጡ ዋና ገጸ ባሕርይ ሆኖ ከቀረበውና የእስራኤል ሕዝብ መሪ ከሆነው ከኢያሱ ነው። ከሙሴ ሞት በኋላ፥ እግዚአብሔር ኢያሱን መረጠውና የከነዓንን ምድር ድል በመንሣት የእስራኤልን ሕዝብ እንዲመራ በኃይል አስታጠቀው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: