ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ (1ኛ ቆሮ.8፡1-6)

በመጀመሪያው መቶ ዓመት ይኖሩ ለነበሩ ክርስቲያኖች የጣዖት ጉዳይ ከባድ ችግር ያስከተለ ነበር፡፡ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሐዋርያውን ከጠየቁት ጥያቄዎች አንዱ ስለ ጣዖት ነበር። ስለ ጋብቻ ለጠየቁት ጥያቄ በቂ መልስ ከሰጠ በኋላ አሁን ወደ ሁለተኛው ጥያቄያቸው ዘወር ይላል። 

ለእነዚህ ክርስቲያኖች ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ በሁለት መንገድ ችግር አስከትሉባቸው ነበር፡፡ አንደኛው በየሄዱበት ግብዣ ያጋጥማቸዋል። ይህንንም ግብዣ የሕብረተሰቡ አባል የሆነ ሁሉ መካፈል ነበረበት። ካልተካፈሉ ከሕብረተሰቡ ጋር ከባድ የቅያሜ ግጭት ይደርስባቸው ነበር፡፡ 

ሁለተኛው ችግር በሥጋ ገበያ ሄደው የሚገዙት ሥጋ አስቀድዋ ለጣዖት የተሠዋ ነበር፡፡ እንደልማዳቸው የሕብረተሰቡ አባሎች ለጣዖት ከሠዉ በኋላ ሲሦው (⅓) ሊሰግዱ ለመጡት ይታደላል፤ ሲሦው ለካህኑ ይሰጣል። ካህኑ የተሰጠውን ስለማይጨርሰው የተረውን ገበያ አውጥቶ ይሸጣል። እንግዲህ በገበያ ያለው ሥጋ አስቀድሞ ለጣዖት ተሠውቶ ነበር ማለት ነው። 

ለዚህ ችግራቸው መፍትሄ እንዲነገራቸው ሐዋርያውን ይጠይቁታል። በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ያለው ውይይት ይህን ጥያቄ በመመርኮዝ ነበር፡፡

1ኛ ቆሮ.4፡1-6ን ካነበብህ በኋላ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ። 

ጥያቄ 3. በቁጥር 1 ላይ አለን የሚለው እውቀት ምን ዓይነት እውቀት ነው? 

ጥያቄ 4. ጣዖት ከንቱ ከሆነ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋስ? 

ጥያቄ 5. በቁጥር 6 ላይ እንደተጠቀሰው በአብና በወልድ መካከል ያለውን ዝምድና ሰፋ ባለ አነጋገር ግለጽ። 

ቁጥር 1:- ለጣዖት ስለተሠዋ ሥጋ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እውቀት ያላቸው መሆኑን ገልጸውለት ባላቸውም እውቀት የተመኩ ይመስላል። “ለጣዖት ስለተሠዋ ሥጋ ሁላችን እውቀት አለን” በማለት ስለዚህ ነገር እውቀት ያላቸው እነርሱ ብቻ እንዳልሆኑም ይገልጽላቸዋል። ይህ እውቀት ምን እንደሆነ ዝቅ ብሎ ይዘረዝራል፤ (ቁጥር 4)። 

አለን የተባለው የእውቀት ፍሬ ነገር ይህ ነው፤ አንድ አምላክ ብቻ ስላለ ጣዖት አምላክ አይዳለም፤ እንዲሁ ከንቱ ነገር ነው። ከንቱ ነገርም ስለሆነ ሰው በዚህ ነገር መጨነቅ አይገባውም። ስለዚህ ሰው ለከንቱ ነገር የተሠዋውን ቢበላ ምንም ጉዳት የለበትም እያሉ ነገሩን ይህን በመሰለ ግምገማ ውስጥ አስቀምጠውት ነበር። 

ቁጥር 2፡- ሆኖም በዚህ ግምገማቸው ላይ የዘነጉት ነገር እንዳለ ያስረዳቸዋል። ያም የዘነጉት ነገር ፍቅር ነው። «እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል»። ይህም ማለት ሰው እውቀት አለኝ ብሎ እውቀቱ የመሪውን ነገር ሁሉ ማድረግ አይገባውም። ያ የሚወስደው እርምጃ በሌሎች ላይ ምን ያስከትላል ብሉ ማመዛዘን ይኖርበታል፡፡ ካላመዛዘን ግን በእውቀቱ ትዕቢት አድሮበታል፤ ሥራውም ቤተ ክርስቲያንን የሚገነባ ሳይሆን የሚያፈርሳት ሆኖ ይገኛል። 

ቤተ ክርስቲያንን በማይገነባትና በሚያፈርሳት ሥራ መሠማራት አደገኛ እንደሆነ ሐዋርያው ቀደም ሲል ተናግሮአል ( 1ኛ ቆሮ.3፡17)። ነገር ግን ሰው በእውቀት ታብዮ ሳይሆን በፍቅር ተመርቶ ሲራመድ ቤተ ክርስቲያንን ይገነባል፤ «ፍቅር ግን ያንፃል።» 

ከዚህ በላይ ምንም እንኳ ሰው ብዙ እውቀት ያለው ቢሆንም ሊታወቅ የሚገባውን ገና አላወቀም፤ ሊያውቅም አይችልም። ስለዚህ የሰው እውቀት ሁልጊዜ ጎዶሎ ስለሆነ በእውቀቱ ላይ መደገፍ የለበትም። የቆሮንቶስ ሰዎች ያላቸው እውቀት በቂ አለመሆኑን ተገንዝበው በትህትናና በፍቅር መራመድ ይኖርባቸዋል፡፡ ትህትናና ፍቅር የሌለበት የእውቀት ምንጭ ከዲያብሎስ አንጂ ከእግዚአብሔር አይደለምና እውቀትን እንዴት እንደምንጠቀምበት ጥንቃቄ እናድግ፤ (ያዕ.3፡15)። 

ጥያቄ 6. የዛሬ ዘመን አማኞች በፍቅር ሳይሆን በእውቀት ብቻ ሲሠሩ የምናየው እንዴት ነው? በምሳሌ ግለጽ። 

ቁጥር 3፡- የፍቅር መጀመሪያው እግዚአብሔርን ማፍቀር ነው። እግዚአብሔርን ከምውደድ አንፃር እግዚአብሔር የወደዳቸውንም መውደድ እንችላለን፤ (1ኛ ዮሐ.4:20 እና 21)፡፡ የእውቀትም ጉዳይ በእግዚአብሔር መታወቅ ነው። ስለዚህ ሰው ስለ ራሱ ደስ መሰኘት ከወደደ በእግዚአብሔር በመታወቁ ብቻ ሊደሰት ይገባዋል፤ (ሉቃ. 10፡20-22)። 

በእግዚአብሔር መታወቅ ማለት ምን ማለት ነው? ከላይ ከሉቃስ ወንጌል እንዳገኘነው የእያንዳንዱ ክርስቲያን ስም በእግዚአብሔር መዝገብ ስለሰፈረ በእግዚአብሔር ታውቋል። ይህም እውቀት የሚንከባከብና የእኔ ነህ የሚል ፍቅር ነው። ቅዱስ ዳዊት ስለዚህ እውቀት ሲጽፍ እንዲህ ይላል፤ «እግዚአብሔር የጻድቃንን መንገድ ያውቃል፤ የኃጢዕን መንገድ ግን ትጠፋለች፤» (መዝ.22፡(23):6)። 

ቁጥር 4፡- ስለ ጣዖት አለን የተባለውን እውቀት ይጠቅሳል። ጣዖት ከንቱ እንደሆነ እናውቃለን። ከአንዱ አምላክ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም። 

ቁጥር 5-6፡- ምንም እንኳ ሰዎች የተለያዩ ነገሮችን አምላክና ጌታ አድርገው ቢሰግዱላቸውና ቢያገለግሏቸውም እኛ ግን አንድ አምላክ ብቻ እንዳለን እናውቃለን። ሌሎቹ ግን ከንቱ ነገሮች ብቻ ናቸው። 

ጥያቄ 7. በዛሬ ዘመን አንዳንድ ሰዎች ከእግዚአብሔር ሌላ አምላክ የሚያደርጉት ነገር ምንድነው?

ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን። ሁሉ ነገር ከአብ የመነጨ ነው፡፡ከዚያም ቀጥሎ “ነገር ሁሉ በእርሱ በኩል የሆነ እኛ በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን”፡፡ በማለት በአብና በወልድ መካከል ያለውን ዝምድና ይገልፃል። ሁሉ ነገር ከአብ ሲሆን፥ ሁሉ ነገር ደግሞ በወልድ በኩል (ወይም አማካይነት) ነው፡፡ ይህም ማለት እግዚአብሔር አብ ሥራውን ሁሉ (የመፍጠርንም የማዳንን ሥራ) የሠራው በእግዚአብሔር ወልድ በኩል ነው ማለት ነው። 

ጥያቄ 8. ይህንን እውነት የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ነን ለሚሉት እንዴት አንድንመልሳቸው ልንጠቀምበት እንችላለን?

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading