ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ (1ኛ ቆሮ.8:7-13) 

ጥያቄ 9. በቁጥር 7 ላይ በሁሉ ዘንድ አይገኝም የሚለው እውቀት ምን ዓይነት እውቀት ነው? 

ጥያቄ 10. በቁጥር 9 ላይ የተጠቀሰው መብት ምንድነው? 

ጥያቄ 11. በቁጥር 10 ላይ «ሕሊናው አይታነጽበትምን› ማለቱ ምን ማለቱ ነው? 

ቁጥር 7:- «ይህ እውቀት በሁሉ ዘንድ የለም»። ጣዖት ከንቱ አንደሆነ ሁሉ ክርስቲያኖች አያውቁም። በቁጥር 1 ላይ «ሁላችን እናውቃለን» ካለው ጋር ይህ ንገገሩ ሊጋጭ አይገባም። በቁጥር 1 ላይ ይህ እውቀት በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መካከል ብቻ ሳይሆን በሁሉም አገር ክርስቲያኖች ዘንድ ይገኛል ማለቱ ሲሆን በቁጥር 7 ደግሞ ይህ እውቀት በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ባሉ በእያንዳንዳቸው ክርስቲያኖች ዘንድ አይገኝም ማለቱ ነው። 

ጣዖት ከንቱ መሆኑን ስላልተገነዘቡና ጣዖትን ለብዙ ገዜ ከማምለክ የተነሣ አእምሮአቸው በጣዖት አምልኮ አስተሳሰብ ስለተጠምደ በጣዖት ነገር በቀላሉ ይረክሳሉ። ጣዖት ከንቱ ነገር መሆኑን የተገነዘበ ሰው ለጣዖት የተሠዋውን ቢበላ ምንም አይሆንም። ግን ጣዖት አንድ ኃይል አለው የሚል ልማድ ያለው ሰው ለጣዖት ከተሰዋው ሥጋ ቢበላ ሕሊናው ይረክሳል። 

የሕሊና መርክስ ማለት ለጣዖት የተሠዋውን በሚበላበት ጊዜ ለጣዖት ኃይል መስጠት የለምደ ደካማ አእምሮ ስላለው የተከለከለ ጣዖትን ያመለከ በምስሎት ሕሊናው ይወቅሰዋል፡፡ ይህ የሕሊና ወቀሳ የሕሊና መርከስ ይባላል። ይህ እግዚአብሔርን ያስቀይመዋል እያለ ግን ደፍሮ ያን ሥራ ቢፈጽም በእውነትም እግዚአብሔርን ያስቀይማል። የሕሊና መርከስ እንግዲህ “በእምነት ያልሆነ ሁሉ ኃጢአት ነው” ከሚለው አስተሳሰብ ጋር ይወራረሳል፤ (ሮሜ 14:20):

ጥያቄ 12. በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ በአንድ ነገር ላይ ይህ ተፈቅዷል፤ ይህ አልተፈቀደም ብለው በሃሳብ የሚለያዩ ሰዎች አሉን? ካሉስ የሚለያዩበት ሃሳብ ምንድነው? ጥያቄአቸው ከቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ጥያቄ ጋር ይመሳሰላል ወይስ ይለያያል? 

ቁጥር 8፡- ጣዖት ከንቱ ስለሆነ ለጣዖት የተሠዋም በራሱ እንዲሁ ተራ ምግብ ከመሆን ሌላ ኃይል የለውም። ምግብም በሃይማኖት በኩል በራሱ ምንም ዋጋ የለውም። ሰው በመብል ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብም ከእግዚአብሔር ሊርቅም አይችልም። “ብንበላም ባንበላም ምንም አይተርፈንም”። 

ቁጥር 9፡- ስለምንበላው “ይህ እግዚአብሔርን ያስቀይም ይሆን?” አያሉ አለመጨነቅ ትልቅ የክርስቲያን ነፃነት ነው። ነገር ግን እውቀት የጎዳላቸው ክርስቲያኖች ይህን ነፃነት ገና አልተጎናጸፉም። በዚህም ምክንያት “ደካሞች” ተብለዋል። እንግዲህ መብል በራሱ ጉዳትም ጥቅምም ከሌለው፥ በመብልም ምክንያት ወንድም የሚሰናከል ከሆነ አለመብላትን በመምረጥ ነጻነታችንን በፍቅር ማሰር አለብን። ስለዚህ ማየት ያለብን ነፃነታችንን ብቻ ሳይሆን ያ ነፃነታችን በወንድማችን ላይ ሊያስከትል የሚችለውንም ጭምር መሆን አለበት። ይህም በእውቀት ሳይሆን በፍቅር መመላለስ ማለት ነው። «እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንፃል።» 

ቁጥር 10፡- በዚህ ቁጥር ላይ አንድ እውቀት ያለው ክርስቲያን እውቀቱን ያለ ፍቅር ሥራ ላይ ካዋለው የሚያደርሰውን በደል ሐዋርያው ይዘረዝራል፡፡ አንድ ሰው «ጣዖት ከንቱ ነው፤ ስለዚህ ለጣዖትም የተሠዋ አንዲሁ ተራ ምግብ ስለሆነ ብበላው ምንም አይጎዳኝም» ብሎ በጣዖት ቤት ቁጭ ብሎ ለጣዖት የተሰዋውን ሥጋ ይበላል። ነገር ግን ይህ እውቀት የሌለው ደካማ አማኝ ደግሞ ይህን አይቶ “አይ ይኸው እከሌ እንኳ በጣዖት ገበታ ይሳተፋል፤ ስለዚህ እኔም ልሳተፍ” ይልና ይሳተፋል፡፡ በቂ እውቀትም ስለሌለው «አይ ከጣዖት ማዕድ በመካፈሌ አምላክን አስቀየምሁ» አያለ የሕሊና ክስ ያስጨንቀዋል። ግን ደግሞ መልሶ «አይ ግድየለም እከሌስ በልቶ የለ?» እያለ በራሱ እምነት ሳይሆን ሰውን ብቻ በማየት በአምላኩ ፊት ይደፍራል፡፡ ይህ እንደዚህ ሕሊናውን መጣሱ እየተደጋገመ ሲመጣ ወደ ሌላም ኃጢአት በመንሸራተት በእምነቱ ይሰናከላል። ለዚህ ሁሉ  መነሻና የመሰናከያ አለት የሆነበት ያ ያለፍቅር በእውቀቱ የተመካው ክርስቲያን ወንድም ነው፡፡

«ሕሊናው አይታነጽበትምን?» ማለት ይህን ለጣዖት የተሠዋ ምግብ በእውቀት ሳይሆን በአምልኮት ለመብላት ይደፍራል ወይም ያን ለማድረግ ይገነባል ማለት ነው። የማይገባውን እርምጃ በድፍረትና በድንቁርና ይወስዳል፡፡ይህን ለማለት “ገነባ” የሚለው ቃል ተመራጭ አይደለም። ይህን ቃል ሐዋርያው የተጠቀመው ምናልባት በአሽሙር መልክ ሳይሆን አይቀርም። ምናልባት የቆሮንቶስ አማኞች ደካሞችን በእውቀት በመገንባት ሳይሆን በእርምጃ ለመገንባት ይሞክሩና የተባለውን ጉዳት በወንድማቸው ላይ አድርሰው ይሆናል። ስለዚህ ሐዋርያው በአጭር አነጋር «አዎ እንዲህ ወንድምህን እያሰናከልህ ትገነባዋለህ፤» ማለቱ ይሆናል። 

ቁጥር 11-12:- ፍቅር በሌለው እውቀት ሰው እንዲህ ወንድሙን ሊጎዳ ይችላል። ይህም ወንድም ክርስቶስ የሞተለት ስለሆነ ይህን በደል ያደረሰው ሰው ሰውን ብቻ ሳይሆን ክርስቶስን እንደበደለ ይታያል፡፡ ስለዚህ ሰው እርምጃውን በእውቀት ሚዛን ላይ ብቻ ሳይሆን በፍቅር ሚዛንም ላይ ማስቀመጥ አለበት። ፍቅርም ለሰው ብቻ ሳይሆን ለክርስቶስም የተሰነዘረ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። 

ጥያቄ 13. በዚህ ዘመን በእውቀታችን ብቻ ሳይሆን በፍቅር ሚዛን ላይ መታየት ያለባቸው ነገሮች ምን ዓይነት ናቸው? 

በዚህ ክፍል ውስጥ «ይጠፋል» የሚለው ቃል በግሪኩ የወደፊት ግሥ ሳይሆን የአሁን ግሥ ነው። ስለዚህ ጥፋቱ በዘላለም ኩነኔ ሳይሆን በአሁኑ ዘመን የሚደርስበትን ጉዳት ነው የሚያመለክተው፡፡ መጥፋት ማለትም በእምነቱ ተሰነካክሉ የክርስትና ሕይወቱ ይበላሻል ማለቱ ነው እንጂ የዘላለም ኩነኔ ይደርስበታል ማለቱ አይደለም። ሐዋርያው አንድ ክርስቲያን ከዳነ በኋላ የማይጠፋ የደህንነት ዋስትና እንዳለው አስተምሮአል (ፊልጵ.1:6)። 

ቁጥር 13፡- ሐዋርያው ክርስቲያኖች ማድረግ ያለባቸውን እርሱም ሊያደርግ የተዘጋጀ መሆኑን ያውጃል። “ወንድሜን እንዳላሰናክል” ማለት የወንድሙን ሕሊና እንዳያረክስ ማለቱ ነው፡፡

እዚህ ላይ ማሰናከል የሚለውን ቃል “ማስቀየም” ወይም “ቅር ማሰኘት” ከሚለው ሃሳብ ጋር ማደባለቅ የለብንም። በወንጌል እምነት የሌሉ ሰዎች ክርስቲያኖች በሚያደርጓቸው አንዳንድ ነገሮች ቅር መሰኘታቸው ወይም መቀየማቸው አይቀርም። ቃሉን በደንብ እንገንዘበው፡፡ 1ኛ / «ወንድምህን» ነው የሚለው፤ 2ኛ / ደካማን ወንድም ወደ ሕሊና ማርከስ አንምራ ነው እንጂ የሚለው በወንጌል ብርሃን መራመድ በማይፈልጉ ሰዎች ድንቁርና ታሰሩ አይደለም የሚለው። 

ጥያቂ 14. ላላመኑት የምናሳየው የሕይወታችን ምስክርነት እና የደካማውን አማኝ ሕሊና መጠበቅ በምን ይመሳሰላል? በምንስ ይለያያል?

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading