የክርስቶስ ሐዋርያት (1ኛ ቆሮ. 4:1-21)

ለወንጌል ሥራ ቅንዓት ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ብዙውን ጊዜ ለወንጌል አገልጋዮች በቂ እንክብካቤ አያሳዩም። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ወንጌላውያንን እንድንከባከብ አጥብቆ ያስተምረናል። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ተገቢውን እንክብካቤ ስላላደረገችለት የወቀሳ ደብዳቤ ይጽፍላቸዋል። የእኛስ ቤተ ክርስቲያን ለወንጌላውያን ያላት እንክብካቤ እንዴት ነው? የዓለም ጥበብ የሚታየው ለሰዎች ወይም ለአንድ ሰው በሚሰጠው ክብር ነው። የእግዚአብሔር ጥበብ ግን ክብርን የሚሰጠው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው። 

1ኛ ቆሮንቶስ 4ን አንብብ። 

ጥያቄ 8. «ሎሌ» በሚለው ቃልና ‹መጋቢ» በሚለው ቃል መካከል ያለውን ልዩነት ግለጽ። 

ጥያቄ 9. በቁጥር 4 ላይ በዚህ አልጸድቅም እኔን የሚፈርድ ጌታ ነው» ሲል ሐዋርያው ምን ማለቱ ነው? 

ጥያቄ 10. በቁጥር 6 ላይ ‹ስል አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ (እንዳትታበዩ)» ማለቱ ምን ማለቱ ነው? 

ጥያቄ 11. ከቁጥር 8 እስከ 13 ያለው ክፍል በግልጽ የሮሮ አፃፃፍ ነው። የጽሑፉን ጠቅላላ ሀሳብ በአጭሩ ግለጽ። 

ጥያቄ 12. በቁጥር 15ና 16 ላይ በወንጌል ወልጄአችኋለሁና እንግዲህ እኔን የምትመስሉ ሁኑ” ሲል በምን እርሱን እንዲመስሉ ነው የሚጠይቃቸው? 

ከቁጥር 1-5 ያለው ክፍል ከላይ የጠቀሳቸውን ነጥቦች ይከተላል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስና ባልደረቦቹ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሲያገለግሉ ተጠሪነታቸው ለሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር መሆኑን ይገልጻል፡፡ ስለሆነም በምንፈሳዊ ሠራተኛች ዘንድ ታማኝ ሆና መገኘት አስፈላጊ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በራሱ ላይ እንኳ መፍረድ እንደማይችል ይናገራል፡፡ ጳውሎስ ሰው እንደመሆኑ ሊታለል እንደሚችል ያውቅ ነበር። ስለዚህም እንኳን በሰዎች ላይ ቀርቶ በራሱ ላይ ለመፍረድ የማይችል መሆኑን ተረድቶ ነበር። የቆሮንቶስም ክርስቲያና በሠራተኞች ላይ ከመፍረድ እንዲጠበቁ ያስጠነቅቃቸዋል። 

ጳውሎስ ስለራሱና ስላባልደረቦቹ የእግዚአብሔር ሎሌና የእግዚአብሔር መጋቢ የሚሉትን ቃላት ይናገራል። በመጽሐፉ ሎሌ የሚባለው ተራ አሽከር ሲሆን መጋቢ ደግሞ በሎሌዎች ላይ የተሾመ የሎሌዎች ተቆጣጣሪ አሽከር ነው፡፡ ስለዚህ ሎሌም ሆነ መጋቢ ሁለቱም የእግዚአብሔር ባሮች እንጂ ባለቤቶች ስላልሆኑ ባንዱም መመካት የለብንም። ለቀጠራቸው ለእግዚአብሔር መልስ የሚሰጡ ተጠሪነታቸውም ለእግዚአብሔር የሆነ አገልጋዮች ናቸው። 

በቁጥር 6 ላይ የአማርኛ ስህተት አለ፤ ‹እንዳይታበዩ» የሚለው «እንዳትታበዩ» ብሎ መነበብ አለበት። በቁጥር 6 እና 7 ላይ ሐዋርያው ክርስቲያኖች በሠራተኞች ላይ መመካት እንደሌለባቸው ይናገራል። የጠቀሰው ምሳሌ «ከተጻፈው አትለፍ» የሚለው ጥቅስ በብሉይ ኪዳን የትም ቦታ ተጽፎ አይገኝም፤ ምናልባት በዘመኑ በኅብረተሰቡ የታወቀ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። አገልጋዮች እግዚአብሔር በሰጣቸው ስጦታ ስለሚያገለገሉ ተገልጋዮች በአገልጋዮች ችሎታ መመካት የለባቸውም። 

ጥያቁ 13. አንዳንድ ሰዎች ወይም አገልጋዮች በችሎታቸው የሚመኩ አሉ? መመካታቸውን የሚገልጹት እንዴት ነው? 

ከቁጥር 8-13 ያለው ክፍል በአሽሙር መልክ የቀረበ የጳውሎስ ወቀሳ ነው። ሀሳቡን በዝርዝር ለማግኘት እንድንችል ቁጥር በቁጥር እንመለከተዋለን። 

ቁጥር 8፡- የቆሮንቶስ ክርስቲያናት በዓለማዊ አስተሳሰብ ውስጥ ስላሉ በወንጌል ምክንያት እየተሰደዱ የሚናቁትን የወንጌልን አገልጋዮች ይንቁ ስለነበር ጳውሎስ «ነገሣችኋል» በማለት ያሸሟጥጣቸዋል። በእርግጥ የነገሡ ከሆነ ከወንጌል አገልጋዮች ጋር አብረው በነገሡ፤ ማለት አሁን ለክርስቶስ ወንጌል ታማኝ ሆነው ከአገልጋዮች ጋር በመሰለፍ በዓለማውያን ቢናቁና በኋላ በወቅቱ ከወንጌል አገልጋዮች ጋር አብረው ቢነገሡ ይሻላል ይላቸዋል። 

ቁጥር 9፡- ሐዋርያት የወንጌል ሥራ ቀደምተኞች ስለሆኑ ዓለም በስደትና በማንቋሸሽም ቀደምት አድርጋቸዋለች፡፡ በዘመኑ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ወደ ሞታቸው ሲነዱ በሰልፍ ታጅበው ሟቾቹ ከሰልፉ መጨረሻ ተደርገው በሕዝብ ይንጓጠጡ ነበር። ሐዋርያው ያን ምሳሌ ወስዶ ሐዋርያት በዓለም ብቻ ሳይሆን በመላእክት እንኳ እየታዩ በውርደት ቦታ እግዚአብሔር እንዳስቀመጣቸው ይናገራል (መላእክት የሰዎችን ሕይወት ታዛቢ ለመሆናቸው የሚያስረዱ የሚከተሉትን ጥቅሶቶ ተመልከት፤ (1ኛ ቆሮ.11:10፤ 1ኛ ጢሞ.3:16፤ 5፡21፤ 1ኛ ጴጥ.1:12)። እንግዲህ የአሸሙሩ አቅጣጫ ይግባን። መንፈሳዊ አባቶች የሆኑት ሐዋርያት እንዲህ ተዋርደው ሳሉ ምእመናኑ ግን በትዕቢት ተነፍተው አገልጋዮችን ቢያንገዋልሉ ምን ያህል መጥፎ ነገር እንደሆነ ለቀሮንቶስ ክርስቲያኖች ያስረዳቸዋል፡፡

ከቁጥር 10-13፡- የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በኩራት አገልጋዮችን ሲያንገዋልሉ አገልጋዮች ግን ለክርስቲያኖች ሲሉ በብዙ ውርደትና መከራ ውስጥ አሉ። ይህ ክፍል ቤተ ክርስቲያንን ለወንጌል አገልጋዮች ተገቢ እንክብካቤ እንድታደርግ በጥብቅ ተግሣጽ ይናገራታል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይህን ተግሣጽ መስማትና ወንጌላውያንን እንደቃሉ መሠረት ልትንከባከብ ይገባታል። 

ቁጥር 14፡- ሐዋርያው ነገሩን ለማለሳለስ በፍቅር ብቻ ተገዶ ይህን ወቀሳ እንዳቀረበላቸው ያሳስባቸዋል። 

ቁጥር 15፡- ለመጀመሪያ ጊዜ ወንጌልን የሰበከላቸው ጳውሎስ ስለሆነ በክርስቶስ አባታቸው መሆኑን ያስታውሳቸዋል፤ ስለሆነም በግልጽ ሊወቅሳቸው ይችላል። እንዲያውም ከሱ በኋላ መጥተው ካገለገሏቸው ሞግዚቶች ይልቅ ይቀርባቸዋል። ይህ አነጋገሩ በተለይ እርሱን አንፈልግም ያሉትን ክርስቲያናት በጣም ሊገስጻቸው ይገባል። 

ቁጥር 16፡- ልጅ አባቱን መምሰል እንደሚገባው የእርሱን ምሳሌ እንጂ የዓለምን ምሳሌ መምሰል የለባቸውም፤ 1ኛ ቆሮ.1:1 1ኛ ተሰ.1:6፤ ሮሜ 12:1 እና 2። የጳውሎስን የክርስትና አኗኗር በሚገባ ተረድተው እርሱን እንዲመስሉ ስለ እርሱ ሕይወት የሚያውቀውን ጢሞቴዎስን ይልክላቸዋል። ጳውሎስ በስብከት ብቻ ሳይሆን በኑሮውም ያስተምር ስለነበር እኛም የዘመኑ ወንጌላውያን አርአያ የሆነ ሕይወት ሊኖረን ይገባል። 

ከቁጥር 18-21:- ጳውሎስ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ተቃዋሚዎች በተነሡበት ጊዜ አፍር ወይም በመቀየም አኩርፎ ከቤተ ክርስቲያኑ የማይቀር መሆኑን በግልጽ ያውጃል። የጌታ አገልጋይ ነገሮች በጠራ መንገድ እንዲታዩ መጣር አለበት። 

ጥያቄ 14. በአሁኑ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ለአገልጋዮችዋ ትክክለኛ እንክብካቤ ምን እያደረገች ነው?

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading