የ1ኛ ሳሙኤል መግቢያ

የአንድ ሕዝብ፥ ወይም የአንድ ቤተ ክርስቲያን መሪ በተራ ሰዎች ሥነ – ምግባርም ሆነ መንፈሳዊ ዝንባሌ ላይ የሚጫወተው ሚና በጣም ከፍተኛ ነው። መሪው ብልሹ ከሆነ፥ ከሥሩ የሚተዳደሩ ሰዎችም የተበላሹ ይሆናሉ። መሪው አምላክ የለሽ ከሆነ፥ ሕዝቡም አምላክ የለሽ ይሆናሉ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚሆነውም ልክ እንደዚሁ ነው። የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ ሕይወት ደረጃ የሚወስነው የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ ነው። መሪው ስግብግብ ከሆነ፥ ወይም ጠንካራ መንፈሳዊ ሰው ካልሆነ፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባሎችም ስግብግብና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የደከሙ ያይሆናሉ። የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ እግዚአብሔርን የሚፈራ የጸሎት ሰው፥ ደግሞም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ የእግዚአብሔርን ቃል የሚያጠና ሰው ከሆነ፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባሎችም የጸሎት ሰዎች፥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅና ለማድረግ የሚፈልጉ ይሆናሉ። በማንኛውም ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሕይወት ዝቅ ሲል፥ ብዙ ጊዜ ችግሩ ያለው ከቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ነው። የእግዚአብሔርን ፈቃድ በሙሉ ለማወቅና ለማድረግ ወሳኝ የሆኑ መልካም መንፈሳዊ መሪዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እስከሌሉ ድረስ ቤተ ክርስቲያኖቻችን ደካማና ውጤት የማያስገኙ ይሆናሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የአንድ አገር መሪ የሥነ-ምግባር ሕይወት፥ በሚመራው አገር የሥነ-ምግባር ሕይወት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? ለ) የአንዲት ቤተ ክርስቲያን መሪ ሥነ-ምግባርና መንፈሳዊ ሕይወት በአባላቱ ሥነ-ምግባርና መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? ሐ) ይህ ነገር በቤተ ክርስቲያን መሪ የሚሆኑ ሰዎችን በከፍተኛ ጥንቃቄ ስለመምረጥ የሚያስተምረን ምንድን ነው?

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ጢሞ. 3፡1-7 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሕይወት ውስጥ ሊያይ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ዘርዝር። እነዚህን ባሕርያት ለሦስት ክፈላቸው፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ጋር የሚያያዙትን፥ ከመሥራት ችሎታ ጋር የሚያያዙትንና ከሥነ-ምግባርና ከመንፈሳዊ ሕይወት ጋር የሚያያዙትን። ለ) ከእነዚህ ከሦስት ክፍሎች፥ በርካታ ባሕርያት ያሉት በየትኛው ሥር ነው? ሐ) እግዚአብሔር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ካለን እውቀትና ከመሥራት ችሎታችን በላይ ሥነ-ምግባርና በመንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ የሚያተኩረው ለምን ይመስልሃል? መ) የቤተ ክርስቲያን አባላት መሪዎቻቸውን በሚመርጡበት ጊዜ በአብዛኛው መመዘኛቸው ምንድን ነው? ሠ) እግዚአብሔርን ለሚፈራ አንድ መሪ እነዚህ መልካም ባሕርያት ናቸው ወይስ አይደሉም? ማብራሪያ ስጥ።

መጽሐፈ ሳሙኤል ስለ እግዚአብሔር ሕዝብ መሪዎች የሚናገር መጽሐፍ ነው። በተለይ የሚያተኩረው የእግዚአብሔርን ሕዝብ በመልካም አመራር ስላልመሩ ሰዎች ነው። ልጆቹን በሚገባ ለመቆጣጠር ባለመቻሉ ምክንያት የእግዚአብሔርን አምልኮ ያበላሸው ካህኑ ዔሊ ነበር። መልካምና እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ቢሆንም፥ ዳሩ ግን እንደ ዔሊ ልጆቹን መቆጣጠር ያልቻለ ሳሙኤል ነበር። በመጨረሻም ለእግዚአብሔር በሙላት ባለመታዘዙ ሕዝቡን ይመራ ዘንድ እግዚአብሔር የናቀውን የመጀመሪያውን ንጉሥ ሳኦልን እናያለን። ይህ መጽሐፍ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ መሪ ለሆንን ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕዝብ እንዴት መምራት እንዳለብንና እንዴትስ መምራት እንደሌለብን የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎችን ይሰጠናል። 

የመጽሐፉ ርእስ 

ቀደም ሲል በነበረው የዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ፥ መጽሐፈ ሳሙኤል ዛሬ በእጃችን እንዳለው 1ኛ እና 2ኛ ተብሉ የተከፈለ ሳይሆን፥ አንድ መጽሐፍ ነበር። ይህንን ታሪክ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሣ ለመጻፍ የፈለገ አንድ ጸሐፊ ያለ ይመስላል። በኋላ የዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን ወደ ግሪክ ቋንቋ ሲተረጎም (ሴፕቱዋጀንት የሚለው ትርጉም ማለት ነው) አንድ የነበረው ሳሙኤል፥ 1ኛ እና 2ኛ ሳሙኤል በመባል ለሁለት ተከፈለ። በዘመናችን ያሉ አብዛኛዎቹ መጽሐፍ ቅዱሶች አንድ ወጥ መጽሐፍ ከመሆን ይልቅ 1ኛና 2ኛ ሳሙኤል ተብለው የተከፈሉ ሁለት መጻሕፍት አሏቸው።

የ1ኛ እና 2ኛ ሳሙኤል ርዕስ የተሰጠው ታሪኩን በ1ኛ ሳሙኤል ከምናገኘው እግዚአብሔርን ከሚፈራ ከአንድ ሰው ነው። መጽሐፉ የተሰየመው ከመሳፍነት ወደ ነገሥታት ዘመን በነበረው የሽግግር ዘመን ይኖር በነበረ ሳሙኤል በተባለ ሰው ስም ነው። ሳሙኤል ካህን፥ ነቢይና ከዔሊ ጀምሮ እስከ መጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ፥ እስከ ሳኦል ድረስ በእስራኤል ላይ በመፍረድ ያገለገለ መስፍን ነበር። መጽሐፉ በሳሙኤል ስም የተሰየመው፥ ይህ ሰው በእስራኤል ታሪክ ውስጥ የሚቀጥለው ተከታይ የታሪክ ዘመን በሆነው፥ በሳኦል፥ በዳዊትና በሰለሞን መሪነት ሥር የነበረውን አንድ የተባበረ የእስራኤል መንግሥት ታሪክ ጀማሪ መሆኑን ዕብራውያን ስላመኑበት ስለተገነዘቡ ነበር። ሳሙኤል የነገሥታትን ዘመን ለማስተዋወቅ በእግዚአብሔር የተመረጠ መሪ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ «ሳሙኤል» የሚለውን ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ ተመልከት። የሳሙኤልን የሕይወት ታሪክ ባጭሩ ጻፍ። 

የ1ኛ እና የ2ኛ ሳሙኤል ጸሐፊ

የ1ኛና የ2ኛ ሳሙኤል መጻፍ በሁለት ደረጃዎች የተከናውነ ሳይሆን አይቀርም። አንደኛ፥ አንዳንድ ጸሐፊዎች የታሪክ መጻሕፍትን ወይም የነገሥታትን ዘገባ ድርጊቱ በተፈጸመበት ዘመን አካባቢ ጽፈዋል። ሁለተኛ፥ አንድ ያልታወቀ ጸሐፊ የተለያዩ የታሪክ መጻሕፍትን ከሰበሰበ በኋላ አንዳንድ ታሪኮችን መርጦ የአሁኖቹን የ1ኛ እና 2ኛ ሳሙኤል መጻሕፍት ጽፎአል። አንዳንድ ሰዎች የነቢዩ ናታን ልጅ የነበረውና የንጉሥ ሰሎሞን የግል አማካሪ ሆኖ የሠራው ዛቡድ መጽሐፈ ሳሙኤልን ጽፏል ብለው ይገምታሉ (1ኛ ነገሥ. 4፡5)፤ ነገር ግን ከሁሉም የሚሻለው የ1ኛና 2ኛ ሳሙኤል ጸሐፊ ማን እንደሆነ አይታወቅም ማለቱ ነው። ሳሙኤል ነው የጻፈው ለማለት አይቻልም፤ ምክንያቱም የ1ኛ ሳሙኤል መጨረሻ አካባቢና የ2ኛ ሳሙኤል ታሪክ በሙሉ የተፈጸመው እርሱ ከሞተ በኋላ በመሆኑ ነው።

ጸሐፊው ማንም ይሁን ማን፥ የዳዊትንና በጥንት ዘመን የተፈጸሙ ታሪካዊ ድርጊቶችን ሁሉ ለማወቅ የሚያስችሉ የቤተ መንግሥት መዛግብትን ለማግኘት የቻለ ሰው ነበር። ማለትም ስለ እነዚህ ጊዜያት የተጻፉ ነገሮችን ሁሉ ለማግኘት ዕድል የነበረው ሰው ነው። ቢያንስ ቢያንስ ያሻር የተባለውን መጽሐፍ እንደምንጭ ለመጠቀሙ እርግጠኞች ነን (2ኛ ሳሙ. 1፡18)። በዚያን ጊዜ ቢያንስ አራት መጻሕፍት እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል። እነርሱም የሳሙኤል፥ የናታን፥ የጋድና የንጉሥ ዳዊት መጻሕፍት በመባል የሚታወቁ ናቸው (1ኛ ዜና 27፡24)። «ስለ ይሁዳ መንግሥት» (1ኛ ሳሙ. 27፡6) ስለሚናገር፥ የመጽሐፈ ሳሙኤል ጸሐፊ ከሰሎሞን ሞት በኋላ የኖረ መሆን አለበት። ይህ ሐረግ «የይሁዳ መንግሥት የሚለው» ሰሎሞን ከሞተና መንግሥቱ ለሁለት ከተከፈለ በኋላ ብቻ አገልግሎት ላይ የዋለ አጠቃቀም ነው። መጽሐፈ ሳሙኤል የተጻፈበት ጊዜ የ1ኛና የ2ኛ ሳሙኤል ጸሐፊ ማን እንደሆነ ሰለማናውቅ፥ እነዚህ መጻሕፍት የተጻፉት መቼ እንደሆነም አናውቅም። ጸሐፊው ኦሪት ዘዳግምን የጻፈው ሰው ነው ብለው የሚያምኑ ሰዎች (ስለ ኦሪት ዘዳግም ታሪክ ከዚህ ቀደም የተሰጠውን አሳብ ተመልከት) መጽሐፉ የተጻፈው የይሁዳ ሕዝብ ከተማረኩ በኋላ ነው ይላሉ። ነገር ግን አብዛኛዎቹ ምሁራን መጽሐፉ የተጻፈው ከዚህ በጣም ቀደም ብሉ ነው ብለው ያምናሉ። 

ስለዚህ 1ኛ እና 2ኛ ሳሙኤል የተጻፈው፥ ሰሎሞን በ930 ዓ.ዓ. ከሞተና የእስራኤል መንግሥት ይሁዳና እስራኤል ተብሉ ለሁለት ከተከፈለ በኋላ ሳይሆን አይቀርም። 

የመጽሐፈ ሳሙኤል ታሪክ የተፈጸመበት ጊዜ ሥረ -መሠረት 

የ1ኛ እና 2ኛ ሳሙኤል ታሪክ በተፈጸመበት ጊዜ በደቡብ የሚገኘው የግብፅ መንግሥትም ሆነ፥ በሰሜን የሚገኘው የአሦር መንግሥት በጣም ጠንካራ አልነበሩም። ከነዓንን ከ1113-1074 ዓ.ዓ. የተቆጣጠሩት አሦራውያን፥ በአሦር በተነሣው ዓመፅ ምክንያት በከነዓን ላይ የነበራቸውን የመቆጣጠር ኃይል አጥተው ነበር። ውጤቱም የከነዓን ምድር በውጭ ኃይሎች አለ መገዛት ሆነ። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በከነዓን ምድር በተለያዩ መንግሥታትና በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል የሚካሄድ የማያቋርጥ ጦርነት ስለነበረ፥ እስራኤላውያን ቀስ በቀስ በከፍተኛ ደረጃ ምድሪቱን ተቆጣጠሩ።

የ1ኛ ሳሙኤል ታሪክ በተፈጸመበት ጊዜ የነበሩት ጠንካራ ሕዝቦች ፍልስጥኤማውያን ነበሩ። እንደምታስታውሰው፥ ፍልስጥኤማውያን «የባሕር ሰዎች» በመባል የሚታወቁ ከሜዲትራኒያን ባሕር ደሴቶች የመጡ ሰዎች ነበሩ። የፍልስጥኤም ምድር አምስት ከተሞች በነበራቸው አምስት የተለያዩ ክፍሎች የተከፈለ ነበር። እያንዳንዱም የራሱ ዋና ከተማ ነበረው። እነርሱም አዛጦን፥ ጋዛ፥ አስቀሉና፥ ጌትና አቃሮን በመባል የሚታወቁ ነበሩ (1ኛ ሳሙ. 6፡17)። እያንዳንዱ ከተማ ከሌሎች የፍልስጥኤም ከተሞች ተለይቶ ራሱን ችሎ በአንድ ጌታ ወይም ንጉሥ ይተዳደር ነበር። እነዚህ ከተሞች በመተባበር በአንድነት ይዋጉ የነበሩት የጋራ የሆነ ጠላታቸውን በጦርነት በሚገጥሙበት ጊዜ ብቻ ነበር። ፍልስጥኤማውያን ኃያል የሆኑበት ምሥጢር የእስራኤል ሕዝብ የማያውቀውን የብረት ሥራ ስለሚያውቁ ነበር (1ኛ ሳሙ. 13፡19-22)፤ ስለሆነም እስራኤላውያን ለብረት መሣሪያዎች (ለምሳሌ ማረሻ) በፍልስጥኤማውያን ላይ ይደገፉ ነበር፤ በዚህ ምክንያት ለውጊያ የሚሆን እንደሰይፍና የመሳሰሉት አልነበራቸውም፡፡ በዔሊ፥ በሳሙኤልና በሳኦል ዘመን የእስራኤላውያን ዋነኛ ጠላቶች ፍልስጥኤማውያን ነበሩ። እነርሱም አብዛኛውን የከነዓንን ምድር ተቆጣጥረው ነበር። ዳዊት እስኪነግስና እስራኤላዊያን የራሳቸውን የጦር መሣሪያ ማበጀት እስከሚማሩበት ጊዜ ድረስ የፍልስጥኤማውያንን ኃይል ለመበተን አልተቻለም ነበር። 

ፍልስጥኤማውያን እስራኤላውያንን መጨቆናቸውን እየቀጠሉ ስለሄዱ በዔሊና በሳሙኤል ዘመን ሁለት ነገሮች ተፈጸሙ። የመጀመሪያው የተለያዩ የእስራኤል ነገዶች የበለጠ መተባበር በመጀመራቸው፥ በመጨረሻ በአንድ ንጉሥ ወደ መመራት መራቸው። ይህ አንድነት የሆነው በሳኦል፥ በዳዊትና በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ነበር። ከሰሎሞን ሞት በኋላ መንግሥቱ ለሁለት ተከፈለችና የሰሜኑ መንግሥት እስራኤል የደቡቡ መንግሥት ይሁዳ ተባለ። ሁለተኛው፥ ነገዶቹ ሁሉ በአንድነት የሚተባበሩበትና ከጠላቶቻቸው ጥበቃን የሚያገኙበት ሁኔታ የሚፈጥር አንድ የተለየ ሰው ማለትም ንጉሥ አስፈለጋቸው (1ኛ ሳሙ. 8፡20)። 

ሊቋቋማቸው የሚችል አንዳችም ታላቅ መንግሥት በሌለበት በዳዊትና በሰሎሞን አመራር፥ የእስራኤል ሕዝብ ከግብፅ ድንበር ጀምሮ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያለውን ክልል በሙሉ በመቆጣጠር፥ እጅግ በጣም ሰፋ። ይህም እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው ተስፋ ክፍል ነበር (ዘፍ. 15፡18-21)።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠውን ተስፋ ለመፈጸም የዓለምን ክስተቶች የተቆጣጠረው እንዴት ነው? ለ) ከዚህ ነገር ስለ እግዚአብሔር ምን እንማራለን? ሐ) ይህ ዛሬ የሚያጽናናን እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

5 thoughts on “የ1ኛ ሳሙኤል መግቢያ”

  1. kebebe urgecha

    የ 1ጢሞ3:17 የሚል ያለ አይመስለኝም ።

    On Tue, Apr 21, 2020, 5:10 AM ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት wrote:

    > tsegaewnet posted: “የአንድ ሕዝብ፥ ወይም የአንድ ቤተ ክርስቲያን መሪ በተራ ሰዎች ሥነ – ምግባርም ሆነ
    > መንፈሳዊ ዝንባሌ ላይ የሚጫወተው ሚና በጣም ከፍተኛ ነው። መሪው ብልሹ ከሆነ፥ ከሥሩ የሚተዳደሩ ሰዎችም የተበላሹ
    > ይሆናሉ። መሪው አምላክ የለሽ ከሆነ፥ ሕዝቡም አምላክ የለሽ ይሆናሉ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚሆነውም ልክ እንደዚሁ
    > ነው። የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ ሕይወት ደረጃ የሚወስነው የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ ”
    >

    1. ወንድሜ ከበበ፣ ስለ አስተያየትህ እናመሰግናለን፡፡ ጥቅሱ መሆን የነበረበት 1ጢሞ3:1-7 ነው፡፡ ስለ ታይፒንግ ስህተቱ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ ጌታ ኢየሱስ ይባርክህ፡፡

    2. ወንድሜ ከበበ፣

      የወንጌል በድረ ገጽ አገልግሎት ዌብ ሳይት (https://ethiopiansite.com/) በርካታ መንፈሳዊ ጽሑፎችን የያዘ ሳይት ነው፡፡ በዌብ ሳይቱ ለአዳዲስ አማኞች የሚሆን የድነት (የደኅንነት) ትምሕርቶች፣ ለሰነበቱ አማኞች የሚሆን የደቀ መዝሙር ማሰልጠኛዎች፣ ብሉይ ኪዳን እና አዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጽሐፎችን ያካተተ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማቴሪያሎችን፣ ለተለያዩ መንፈሳዊ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ አጫጭር የጥናት ጽሑፎች፣ ወዘተ ተካተዋል፡፡ እንግዲህ እንደ ምርህ ሊንኮቹን በመጫን ጥናትህን ማካሄድ ትችላለህ፡፡

      የወንጌል በድረገጽ ዌብ ሳይት ተከታታይ (follower) ለመሆን የምትሻ ከሆነ የወንጌል በድረ-ገጽ አገልግሎት ዌብ ሣይት (https://ethiopiansite.com/) የፊት ገጽ ግርጌ ላይ በመሄድ፣ በስተቀኝ ባልው ክፍት ሣጥን ውስጥ የኢ-ሜይል አድራሻህን በመጻፍና “ድረ-ገጹን ይከታተሉ” የሚለውን ቁልፍ በመጫን የዌብ ሣይቱ ተከታይ (follower) መሆን ትችላለህ፡፡ ይህን ስታደርግ በዌብ ሣይቱ ላይ አዳዲስ ጽሑፎች ሲጫኑ፣ በኢ-ሜይል አድራሻህ የማንቂያ መልእክት (notification) የምታገኝ ይሆናል፡፡

      ከዚህ በተጨማሪ የግል ጥያቄዎች ቢኖርህ በሚከተለው ኢሜይል ልትልክልኝ ትችላለህ፣ በደስታ ለመርዳት ዝግጁ ነኝ (tsegaewnet@gmail.com)፡፡

      የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከአንተና ቤተሰብህ ጋር ይሁን። አሜን።

  2. ሰላም ወጌል በድህረ ገጽ የሚለቀቁት ትምህርቶች ጠቅመውኛል ተባረኩ አንዳንድ ቢገኝ

    1. ወንድሜ ሃብታሙ፣ ጊዜ ሰጥተህ ስለላክልኝ አበረታች መልዕክት እጅግ አመሰግናለው፡፡ በባረከኝ በረከት እግዚአብሔር መልሶ አንተንና ቤተሰብህን እንዲሁም አገልግሎትህን ይባርክልህ፡፡

      የወንጌል በድረ ገጽ አገልግሎት ዌብ ሳይት (https://ethiopiansite.com/) በርካታ መንፈሳዊ ጽሑፎችን የያዘ ሳይት ነው፡፡ በዌብ ሳይቱ ለአዳዲስ አማኞች የሚሆን የድነት (የደኅንነት) ትምሕርቶች፣ ለሰነበቱ አማኞች የሚሆን የደቀ መዝሙር ማሰልጠኛዎች፣ ብሉይ ኪዳን እና አዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጽሐፎችን ያካተተ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማቴሪያሎችን፣ ለተለያዩ መንፈሳዊ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ አጫጭር የጥናት ጽሑፎች፣ ወዘተ ተካተዋል፡፡ እንግዲህ እንደ ምርህ ሊንኮቹን በመጫን ጥናትህን ማካሄድ ትችላለህ፡፡

      የወንጌል በድረገጽ ዌብ ሳይት ተከታታይ (follower) ለመሆን የምትሻ ከሆነ የወንጌል በድረ-ገጽ አገልግሎት ዌብ ሣይት (https://ethiopiansite.com/) የፊት ገጽ ግርጌ ላይ በመሄድ፣ በስተቀኝ ባልው ክፍት ሣጥን ውስጥ የኢ-ሜይል አድራሻህን በመጻፍና “ድረ-ገጹን ይከታተሉ” የሚለውን ቁልፍ በመጫን የዌብ ሣይቱ ተከታይ (follower) መሆን ትችላለህ፡፡ ይህን ስታደርግ በዌብ ሣይቱ ላይ አዳዲስ ጽሑፎች ሲጫኑ፣ በኢ-ሜይል አድራሻህ የማንቂያ መልእክት (notification) የምታገኝ ይሆናል፡፡

      ከዚህ በተጨማሪ የግል ጥያቄዎች ቢኖርህ በሚከተለው ኢሜይል ልትልክልኝ ትችላለህ፣ በደስታ ለመርዳት ዝግጁ ነኝ (tsegaewnet@gmail.com)፡፡

      የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከአንተና ቤተሰብህ ጋር ይሁን። አሜን።

Leave a Reply to Habtamu DoriCancel reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading