ሳኦል የእስራኤል ንጉሥ ይሆን ዘንድ ተመረጠ (1ኛ ሳሙ. 8-11)

ይህኛው የ1ኛ ሳሙኤል ክፍል ከዘመነ መሳፍንት ወደ ነገሥታት ዘመን የተደረገውን የሽግግር ጊዜ ያሳየናል። ሳሙኤል የመጨረሻው መስፍን ነበር። 

ሳሙኤል፥ ዕድሜው በገፋ ጊዜ የእስራኤልን ሕዝብ የመምራት ኃላፊነት ለልጆቹ ለማስተላለፍ አሰበ። 

ሆኖም እንደ ዔሊ ልጆቹን በሚገባ ስላላሳደገ፥ ሊያከብሩትና ሊታዘዙት አልቻሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሳሙኤል ልጆች የፖለቲካም ሆነ የመንፈሳዊ መሪ መሆናቸውን ሳይደግፍ ቀረ። ይልቁንም እግዚአብሔር የመጀመሪያውን የእስራኤል ንጉሥ ለመምረጥ ሳሙኤልን ተጠቀመበት።

የእስራኤል ሕዝብ የእግዚአብሔር ተወካይ ወደሆነው ወደ ሳሙኤል በመምጣት ንጉሥ ያነግሥላቸው ዘንድ ይጠይቁታል። ሕዝቡ ንጉሥ የፈለጉባቸው ሁለት ምክንያቶች ነበሩ። የመጀመሪያው፥ ልክ በአካባቢያቸው የሚኖሩ አሕዛብ ነገሥታት እንደነበሯቸው ሁሉ፥ እነርሱም ንጉሥ ይኖራቸው ዘንድ ፈለጉ። ምኞታቸው ልክ እንደቀረው ዓለም ለመሆን ነበርና እግዚአብሔር ንጉሣቸው እንደሆነ ዘነጉ። ለቃል ኪዳኑ በመታዘዝ ቢኖሩ ኖሮ ሰብአዊ ንጉሥ አያስፈልጋቸውም ነበር (1ኛ ሳሙ. 8፡5-7)። በሁለተኛ ደረጃ ንጉሥን የጠየቁበት ምክንያት ከጠላቶቻቸው ነፃ ያወጣቸው ዘንድ ነው (1ኛ ሳሙ. 8፡20)። 

ጥያቄአቸው ሳሙኤልን አስቆጣው። ያስቆጣውም ሕዝቡ እርሱንና ልጆቹን እንደ መሪ አለመቀበላቸው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር፥ ሕዝቡ ንጉሥ እንዳይሆን የናቁት እርሱን ሳይሆን እግዚአብሔርን እንደሆነ ለሳሙኤል አሳየው።

ሕዝቡ የጠየቁት ጥያቄ እግዚአብሔርን ደስ እንዳላሰኘውና በእርሱ ላይ እንደተደረገ ዓመፅ መቆጠሩ ግልጥ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ጥያቄአቸውን በመመለስ ንጉሥ ለመስጠት ለምን እንደተስማማ (1ኛ ሳሙ. 8፡7 22፤ 10፡9፤ 12፡12፥ 17) የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ተደንቀዋል። እስራኤል ንጉሥ ይኖራት ዘንድ በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ እንደነበረ ከመጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ እንመለከታለን። ከ800 ዓመታት በፊት ነገሥታት ከአብርሃም እንደሚወጡ ተናግሮ ነበር። እስራኤላውያን ወደ ከነዓን ከመግባታቸው ከ400 ዓመታት በፊት እግዚአብሔር ለሕዝቡ ስለ ንጉሥ ትምህርት ሰጣቸው (ዘዳ. 17)። 

የእግዚአብሔር ዕቅድ በሕዝቡ ላይ ራሱ እንደ ዋና ንጉሥ ሊነግሥና ምድራዊ ተወካይ የሚሆን ንጉሥ እንዲኖራቸው ለማድረግ ነበር። እስራኤላውያን፥ ንጉሥ እንዲሰጣቸው እግዚአብሔርን የጠየቁት ከተሳሳተ ዓላማ ነበር። ይህ ውስጣዊ ዓላማቸው የእግዚአብሔርን ንጉሥነት አለመቀበላቸውን የሚያሳይ ነበር። እግዚአብሔር በጥያቄአቸው ያልተደሰተበት ሦስት ምክንያቶች ነበሩት። አንደኛ፥ ሕዝቡ በጠላት እጅ የወደቁበት ብቸኛው ምክንያት ንጉሥ ስለሌላቸው እንደሆነ አድርገው ያቀረቡት የተሳሳተ አሉባልታ ነበር። በጠላቶቻቸው የተሸነፉበት እውነተኛ ምክንያት ኃጢአታቸው መሆኑን አውቀው በእግዚአብሔር ፊት ንስሐ የመግባት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ፈቃደኞች አልነበሩም። ሁለተኛ፥ ንጉሥ የፈለጉበት ውስጣዊ አነሣሽ ምክንያታቸው የተሳሳተ ነበር። እንደሌላው የዓለም ሕዝብ ለመሆን መፈለጋቸው ነበር፤ በመሠረቱ ግን ከሌላው የዓለም ሕዝብ ሊለዩ እንጂ ሊመሳሰሉ አይገባም ነበር። ሦስተኛ በጠላቶቻቸው ላይ ስለሚያገኙት ውጤታማነት በተሳሳተ መንገድ ዋስትናቸውን በእነርሱ ብጤ ሰው ላይ አደረጉ። ንጉሥ ቢኖራቸው በጠላቶቻቸው ላይ ድል እንደሚያገኙ አሰቡ። በጠላቶቻቸው ላይ ድልን የሚሰጥ እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ዘነጉ። ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ቢኖሩ እንደሚጠብቃቸው የገባላቸውን የተስፋ ቃል ረሱ። በመታዘዝ ለመኖር ስላልፈለጉ እግዚአብሔር እንደሚጠብቃቸው ማሰብ አልሆነላቸውም። ስለዚህ ንጉሥ ጠየቁ። 

ሕዝቡ ንጉሥ ያገኙ ዘንድ እግዚአብሔር ፈቀደ። ሆኖም ይህ ንጉሥ በአካባቢያቸው እንደሚኖሩ ሕዝቦች ያለ ንጉሥ እንዳልሆነ አሳያቸው። ይልቁንም የሕዝቡ መሪ ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ራሱን አስገዝቶ የሚኖር ሰው መሆን ነበረበት። በምድሪቱ እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት የሚኖረው ምድራዊው ንጉሥ ለሰማያዊው ንጉሥ ራሱን ሲያስገዛ ብቻ ነበር። በኋላ ሳኦል ለንጉሡ ለእግዚአብሔር ራሱን አላስገዛም በማለቱ ሰላም ጠፍቶ በጠላቶቻቸው እንደተሸነፉ እናያለን፤ ዳዊት ግን ራሱን ለእግዚአብሔር በማስገዛቱ የተከናወነለት መሪ ሆነ።

የውይይት ጥያቄ፥ በተሳሳተ ውስጣዊ አሳብ ተነሣስተን የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን በመምረጥ፥ እግዚአብሔርን የማያስከብር ድርጊት እንዴት መፈጸም እንችላለን? 

እግዚአብሔር ሳኦልን ለንጉሥነት እንዲመርጥ ሳሙኤልን ሲያዝ፥ ሳኦልን ደግሞ በሉዓላዊነቱ ወደ ሳሙኤል መራው። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር ሳኦልን በግሉ ቀብቶት ነበር፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ፥ በታላቅ ደስታ በተቀበሉት በሕዝቡ ሁሉ ፊት ንጉሥ መሆኑ ታወጀ። የሚገርመው ግን ሳኦል ከሳሙኤል ርቆ የሚኖረው 8 ኪሎ ሜትር ብቻ ሆኖ እያለ ሳሙኤልን አያውቀውም ነበር። ከመጀመሪያው ጀምሮ ሳኦል መንፈሳዊ ረሀብ አልታየበትም። ሳሙኤል በሠራው መሠዊያ አጠገብ እንኳ አምልኮ አልፈጸመም። ሳኦል በእስራኤል ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ በእግዚአብሔር እንደተመረጠ በሁለት መንገድ አሳይቶ ነበር። የመጀመሪያው፥ በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር ሆኖ ከነቢያት ጋር ትንቢት መናገርን መጀመሩ ነበር። ሁለተኛው ደግሞ፥ አሞናውያንን ለማሸነፍ መቻሉ ነበር። የሚያሳዝነው ግን የሳኦል ታሪክ በድል ሊቀጥል አለመቻሉ ነው። ሳኦል ለንጉሡ ለእግዚአብሔር ከመታዘዝ እንዴት እምቢ እንዳለና እግዚአብሔር እንደናቀው እንመለከታለን። 

ሳኦል፥ ንጉሥ ሆኖ በሚገባ ከተደላደለ በኋላ፥ ሳሙኤል በእስራኤል ሕዝብ ላይ የነበረውን የካህንነትና የነቢይነት አገልግሎት ቀጠለ፤ ነገር ግን የፖለቲካ መሪያቸው ሳኦል ሆነ። ስለዚህ ሳሙኤል የእስራኤልን ሕዝብ በአንድነት ሰበሰበ። በእግዚአብሔር ላይ የነበራቸውን ዓመፅና አጠቃላይ ታሪካቸውን አስታወሳቸው። እግዚአብሔር በኃጢአታቸው ምክንያት ለጠላቶቻቸው አሳልፎ በመስጠት እንደፈረደባቸው አስታወሳቸው። አሁን ንጉሥ በመፈለጋቸው ባሳዩት የተሳሳተ ዓላማ እግዚአብሔር ደስ አላመሰኘቱን ድንገተኛ ዝናብና የመብረቅ ነጎድጓድ በማውረድ አሳያቸው። እግዚአብሔር ሕዝቡ በእርሱ ላይ የነበራቸውን እምነት ለማደስ ሳሙኤልን ተጠቀመበት። ሳሙኤል እንደገና ከእግዚአብሔር እንዳይርቁና የውሸት አማልክትን እንዳያመልኩ አስታወሳቸው። በእግዚአብሔር ፊት በጸሎት ሊያቀርባቸውና የእግዚአብሔርን ቃል ያለማቋረጥ ሊያስተምራቸው ቃል ገባላቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከሳኦል ሹመት በኋላ፥ ሳሙኤል የቀጠለው የእግዚአብሔርን ቃል የማስተማርና የጸሎት አገልግሎት፥ አንድ መሪ ለሕዝቡ ሊያደርገው የሚገባ ከሁሉ የተሻለ አገልግሎት የሆነው እንዴት ነው? ለ) እነዚህ ሁለት አገልግሎቶች በሕይወትህ የሚታዩት እንዴት ነው? በእነዚህ ሁለት አገልግሎቶች መሻሻል ልታሳይ የምትችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “ሳኦል የእስራኤል ንጉሥ ይሆን ዘንድ ተመረጠ (1ኛ ሳሙ. 8-11)”

Leave a Reply

%d bloggers like this: