የ1ኛ ነገሥት መግቢያ

የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሁለተኛ ዋና ክፍል የሆኑትን 12ቱን የታሪክ መጻሕፍት እያጠናን ነበር። እነዚህ መጻሕፍት ከኢያሱ እስከ አስቴር ያሉት ናቸው። እስካሁን ድረስ፥ የእስራኤል ሕዝብ በኃጢአት ምክንያት ለብዙ ዓመታት ከታገሉ በኋላ ወደ ታላቅና ኃያል መንግሥት እንዴት እንዳደጉ ተመልክተናል፤ ነገር ግን በዳዊት ወታደራዊ አመራር የእስራኤል ሕዝብና መንግሥት ወደ ከፍተኛ ስኬታማነት ደረሰ። እንዲሁም ዳዊት ከእስራኤል ታላላቅ የሃይማኖት መሪዎችም አንዱ ነበር። አብዛኛዎቹ የታሪክ መጻሕፍት የዳዊትን ታሪክ ይነግሩናል።

1ኛና 2ኛ ነገሥት ስለ ሰሉሞን ዘመነ መንግሥት አጭር መግለጫ ከሰጡ በኋላ፥ የሰሜኑ የእስራኤል መንግሥትና የደቡቡ የይሁዳ መንግሥት ወደ ምርኮ እስከሄዱበት ጊዜ ድረስ ያለውን የእስራኤል መንግሥት አወዳደቅ ይነግረናል። ከሰሎሞን ሞት ጋር ታላቁ የእስራኤል መንግሥት እንደገና ወደዚያ ኃያልነት ሊመለስ በማይችልበት ሁኔታ እየወደቀ ሄደ። እስራኤል ልክ እንዳለፈው ጊዜ ገናና ልትሆን የምትችለው፥ በመሢሑ የወደፊት መሪነት ብቻ ነው።

1ኛና 2ኛ ነገሥት፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ በተከታታይ በሚያምፁበት ጊዜ ስለሚያገኛቸው ቅጣት ይነግሩናል። በራእይ 3፡15፣ 19 ኢየሱስ የሎዶቅያን ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ሲል አስጠንቅቆአል፡«በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆን መልካም በሆነ ነበር»። እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው። … እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ»። የእስራኤል ሕዝብ ለእግዚአብሔር በነበራቸው አምልኮ ሲበላሹ እግዚአብሔር ይቀጣቸው ዘንድ ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ሰጣቸው። ከ70 ዓመታት በኋላ ከምርኮ የተመለሱት ጥቂት አይሁድ ብቻ ነበሩ። እነዚህ መጻሕፍት ዛሬ ለእኛ ብርቱ ማስጠንቀቂያ ይሆናል። ክርስቲያኖች ዓለምን ከመሰልንና ለእግዚአብሔር የማንጠቅም ከሆንን፥ እግዚአብሔር ለዚህ ዓለም ፍርድ ይተወናል። ይህ የሥነ -ሥርዓት እርምጃ ስደት ሊሆን ይችላል። ወይም ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆኑ ጥቂት ቅሬታዎችን ብቻ አስቀርቶ፥ ቤተ ክርስቲያንን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ሊሆን ይችላል። የሉዶቅያ ቤተ ክርስቲያን ንስሐ በመግባት ወደ ኢየሱስ አልተመለሰችም ነበር። ስለዚህ ዛሬ የሉዶቅያ ቤተ ክርስቲያን ሕልውናዋ የለም። ወደ ሎዶቅያ ብንሄድ፥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተደምስሳ በቦታው መስጊድ ተሠርቶበት እናገኛለን። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬ በዚህ ዘመን ያለን ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስን ለመውደድና ለእርሱም ለመታዘዝ በገባነው ቃል መጽናት እንዳለብን ይህ እንዴት ብርቱ ማስጠንቀቂያ ይሆነናል? ለ) ቤተ ክርስቲያን ወይም አንድ ክርስቲያን ለብ በሚልበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር የሥነ- ሥርዓት እርምጃ የሚወስደው እንዴት እንደሆነ የተመለከትከውን ግለጥ። የመጽሐፈ ነገሥት ርዕስ እንደ 1ኛና 2ኛ ሳሙኤል 1ኛና 2ኛ ነገሥትም በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ መጽሐፍ ነበሩ። ይህ አንድ መጽሐፍ ከዳዊት ሞት ጀምሮ የተከፋፈለው መንግሥት ወደ ምርኮ እስከተወሰደበት ጊዜ ድረስ ያለውን የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ይሸፍናል። ይህ ማለት በ1ኛና በ2ኛ ነገሥት ውስጥ ያለው የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ከ970-586 ዓ.ዓ. ድረስ ያለው ታሪክ ነው። 

የዕብራይስጡ የብሉይ ኪዳን ክፍል ወደ ግሪክ ሴፕቱዋጀንት ትርጉም ሲተረጎም፥ መጽሐፈ ነገሥት በጣም ረጅም ስለሆነ፥ በሁለት መጻሕፍት ተከፈለና 1ኛና 2ኛ ነገሥት ተባለ። የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ የሴፕቱዋጀንትን ትርጉም የተከተለ ነው። መጽሐፉ «ነገሥት» የተባለው፥ በእነዚህ ሁለት መጻሕፍት አማካይነት ከዳዊት ሞት ጀምሮ በእስራኤል ላይ በመጨረሻ እስከነገሠው ንጉሥ እስከ ሴዴቅያስ ድረስ ያሉትን የተለያዩ ነገሥታት አጫጭር ታሪኮችን ስለያዘ ነው። 

ምሁራን መጽሐፈ ሳሙኤል ከመጽሐፈ ነገሥት ጋር ያለውን ቅርበትና ግንኙነት ለብዙ ጊዜያት ተገንዝበውት ነበር። በእርግጥ የላቲን መጽሐፍ ቅዱስ፥ ለመጽሐፈ ሳሙኤልና ነገሥት 1፥ 2፥ 3 ና 4 ነገሥት የሚሉ ስሞች ሰጥቶአቸዋል። እነዚህ መጻሕፍት በአንድነት ከሳኦል ጀምሮ እስከ ሴዴቅያስ ድረስ የእስራኤል ነገሥታት ስለነበሩበት ዘመን ያለውን ታሪክ ይነግሩናል። 

የመጽሐፈ ነገሥት ጸሐፊ የመጽሐፈ ነገሥት ጸሐፊ ማን እንደሆነ የምናውቅበት አንዳችም መንገድ የለም። ይህ መጽሐፍ እንዴት እንደተጻፈ የሚናገሩ ሁለት ዋና ዋና ፅንሰ ሐሳቦች አሉ፡-

  1. የተለመደው ባሕላዊ አመለካከት፥ የኢየሩሳሌምን ውድቀት በዓይኖቹ ያየ ሰው መጽሐፈ ነገሥትን ጽፎታል የሚል ነው። ይህ ነገር እውነት ይሁን ውሸት በምንም መንገድ ልናረጋግጠው አንችልም። የአይሁድ አፈታሪክ 1ኛ እና 2ኛ ነገሥትን ኤርምያስ ጽፎታል ይላል፤ ምክንያቱም 2ኛ ነገሥት 24-25 የትንቢተ ኤርምያስ 52 ተመሳሳይ በመሆናቸው ነው።
  2. ኦሪት ዘዳግማዊ አመለካከት ያላቸው ምሁራን ደግሞ፥ መጽሐፈ ነገሥት ሕዝቡ ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ ቆይቶ በአይሁድ ታሪክ ውስጥ ሰዎች በቡድን የጻፉት ነው ይላሉ። መጽሐፉን የጻፉት ከዳዊት ዘር የሆነውን ንግሥና ለመደገፍ፥ በአምልኮ ወቅት የንጽሕናን አስፈላጊነት ለመናገር፥ የነቢያትን ትንቢቶች ፍጻሜ ለማሳየትና በተለይም ደግሞ በኦሪት ዘዳግም ውስጥ ያሉትን በረከቶችና እርግማኖች በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ እንዴት እንደተፈጸሙ ለማሳየት ነው። 

መጽሐፈ ነገሥትን ከተለያዩ መጻሕፍት ያጠናቀረው አንድ ሰው እንደ ነበር ማመን ከሁሉ የተሻለው መንገድ ነው። ይህ ያልታወቀ ጸሐፊ መጽሐፈ ነገሥትን ከ586-539 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ አጠናቅቆታል። የመጨረሻውን መጽሐፈ ነገሥት ለመጻፍ ጸሐፊው ሌሎች ጽሑፎችንና መጻሕፍትን በመረጃ ምንጭነት መጠቀሙ ግልጥ ነው። በእርግጠኝነት የምንጠቅሳቸው ቢያንስ ሦስት መጻሕፍት አሉ፡- የሰሎሞን የታሪክ መጽሐፍ (1ኛ ነገ. 11፡ 41)፥ 17 ጊዜ የተጠቀሰው የእስራኤል የነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ (ለምሳሌ 1ኛ ነገ. 14፡19)፥ እንዲሁም 15 ጊዜ የተጠቀሰው የይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ (ለምሳሌ 1ኛ ነገ. 15፡23) ናቸው። እነዚህ መጻሕፍት የመጽሐፈ ነገሥት ጸሐፊ በመረጃነት የተጠቀመባቸው የቤተ መንግሥት ታሪኮች ሳይሆኑ አይቀሩም። 

አንዳንድ ምሁራን መጽሐፈ ነገሥትን የጻፈው ከእስራኤል ነቢያት አንዱ ነው፤ ስለዚህም ነው በነቢያት ሥራዎች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ባሕላዊ መጻሕፍትን የሚጠቀመው ይላሉ። ከመጽሐፍ ቅዱስ አንደምናውቀው፣ ነቢያት የጻፉት የትንቢትን መጻሕፍት ብቻ ሳይሆን፥ የታሪክንም መጻሕፍት ነው (ለምሳሌ፡- 1ኛ ዜና 29፡29፤ 2ኛ ዜና 9፡29፤ 20፡34፤ 26፡22)።

** 2ኛ ነገሥት 25፡ 22-30 የመጽሐፈ ነገሥት ዋና ክፍል በሚጻፍበት ጊዜ ሳይሆን ኋላ የተጨመረ ይመስላል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: