መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ 

ልክ እንደ መጽሐፈ ሳሙኤል፥ ነገሥትና ዜና መዋዕል መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያም በዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን አንድ መጽሐፍ ነበሩ። ዕዝራና ነህምያ በጊዚያቸው የተፈጸመውን ድርጊት እየተከታተሉ ራሳቸው የመዘገቡት ቢመስልም፥ ብዙ ምሁራን የሚስማሙት ጽሑፎቹን የሰበሰባቸውና ወደ አንድ መጽሐፍ በማጠቃለል ያቃናቸው ሌላ ሰው እንደሆነ ነው።

የዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ በኋላ ወደ ግሪክ ቋንቋ ሲተረጎም፥ ተርጓሚዎቹ አንድ የነበረውን መጽሐፍ ለሁለት ከፈሉት። በግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ሁለት መጻሕፍት 1ኛና 2ኛ ዕዝራ በመባል ይታወቃሉ። በኋላ የእነዚህ መጻሕፍት ርዕስ የመጀመሪያው ዕዝራ፥ ሁለተኛው ደግሞ ነህምያ ተብሎ ተሰየመ። እነዚህን ስያሜዎች ያገኙት በመጻሕፍቱ ውስጥ ባሉት ዋና ገጸ ባሕርያት በዕዝራና በነህምያ ነው።

የመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ ጸሐፊዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ በማን እንደተጻፉና እንዴት እንደተጻፉ ያላቸው አመለካከት የተለያየ ነው። የአብዛኛዎቹ አስተሳሰብ ዕዝራና ነህምያን የጻፈው ዜና መዋዕልን የጻፈው ሰው ነው የሚል ነው። ይህንንም ያሉበት ምክንያት የመጽሐፈ ዜና መዋዕል አጨራረስና የመጽሐፈ ዕዝራ አጀማመር ተመሳሳይ በመሆኑ ነው። በተጨማሪ በአጻጻፍ ስልቱም ተመሳሳይነት እናገኛለን።

ሌሎች ምሁራን ደግሞ መጻሕፍቱ ብዙ ተመሳሳይነት ቢኖራቸውም፥ የተጻፉት ግን በተለያዩ ጸሐፊዎች ለመሆኑ የሚያሳምኑ በቂ ልዩነቶች እናገኛለን ይላሉ።

ምሁራን መጽሐፈ ዕዝራንና ነህምያን ያቀናበረው ሰው የተጠቀመባቸው ሦስት የተለያዩ ምንጮች አሉ ይላሉ። በመጀመሪያ፣ ዕዝራ በእርሱ ዘመን ስለተፈጸሙት ክስተቶች ዘግቧል። ሁለተኛ፥ ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች እንዴት እንደሠራ ዘግቧል። ሦስተኛ ደግሞ፥ በሼሺባዛር (ዘሩባቤል) መሪነት አይሁዶች በመጀመሪያ እንዴት ወደ ኢየሩሳሌም እንደተመለሱ የሚናገር የተለየ ዘገባ ነበር። መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያን በአንድ ላይ እንዲሆኑ ያደረገው ሰው ከሦስት የታሪክ ምንጮች በማሰባሰብ በአንድ መጽሐፍ እንዲጠቃለል አድርጓል።

ጸሐፊው ዕዝራ በእርሱ ስም የተሰየመውን የመጀመሪያ መጽሐፍ ጽፎ ሊሆን ይችላል። በፋርስ መንግሥት ውስጥ ሥልጣን የነበረው ሰው ስለነበር፥ አይሁድ ወደ ይሁዳ እንዲመለሱ የተፈቀደበትን ማዘዣ ቅጂና ሌሎች የቤተ መንግሥት መዛግብት ቅጂዎች ኖረውት ሊሆን ይችላል። ከዚህም የተነሣ አይሁድ እንዴት ወደ ምድራቸው እንደተመለሱና ዕዝራ ከስንት ዓመታት በኋላ በምድሪቱ መንፈሳዊ መነቃቃትን እንደመራ አጭር መግለጫ ጽፎ ሊሆን ይችላል። መጽሐፈ ነህምያ የተጻፈው በነህምያ ሊሆን ይችላል። መጻሕፍቱ ባላቸው ተመሳሳይነት ምክንያት፥ የመጨረሻው ሰው መጠነኛ ለውጦችን አድርጎ ወደ አንድ መጽሐፍ አዋሕዶአቸው ሊሆን ይችላል። መጽሐፈ ዕዝራ ከሌዊ ነገድ በሆነ፥ ከምርኮ በኋላ በእስራኤላውያን ታሪክ ውስጥ ታላቅ ሚና በተጫወተና ትልቅ ስፍራ በነበረው ዕዝራ በተባለ ጸሐፊ ስም ተሰይሟል። ዕዝራ የተወለደው በምርኮ ምድር ነበር። ያደገውም በባቢሎን ነበር። ለዕዝራ የእግዚአብሔርን ሕግ ስላስተማሩት፥ ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። ዕዝራ በባቢሎን ምድር እስራኤላውያንንና የብሉይ ኪዳን ሕግን የሚያውቅ ዝነኛ ሰው እየሆነ እንደመጣ ይመስላል። አንዳንድ ምሁራን ዕዝራ በፋርስ መንግሥት ውስጥ የአይሁድ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ እንደተሾመ ይገምታሉ። የፋርስ ንጉሥ ከነበረው ከአርጤክስስ ጋር ግንኙነት የነበረውም ለዚህ ነበር። በ538 ዓ.ዓ. ሕዝቡ በዘሩባቤል መሪነት ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሱ ዕዝራ ያልተመለሰበትን ምክንያት አናውቅም። ምናልባት በጣም ወጣት ስለነበረ ይሆናል። በ458 ዓ.ዓ. ግን ዕዝራ ወደ ኢየሩሳሌም ለመመለስ ከፋርስ ንጉሥ ፈቃድ አገኘ። ንጉሡ ከቤተ መንግሥቱ ገንዘብ እንዲጠቀም ለዕዝራ ፈቃድ ሰጠው። ዕዝራ አንዳንድ ሌዋውያን ከእርሱ ጋር እንዲመለሱ በማሳመን፥ በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚደረገውን አምልኮ በመምራት ይረዱት ዘንድ አደረገ።

ዕዝራ ወደ እስራኤል ከተመለሰ በኋላ በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ታላቅ ሚናን ተጫወተ። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር ዕዝራን ሁለት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ለመምራት ተጠቀመበት (ዕዝራ 9-10፤ ነህ. 8-9)። ሁለተኛ፥ ዕዝራ የእግዚአብሔርን ሕግ በጥንቃቄ በማጥናት የታወቀ ሰው ነበር። ለዚህ ነው አይሁድ በሕግ ሥራና እውቀት «የተካኑ» የሃይማኖት መሪዎች አባት አድርገው የሚቆጥሩት። በአዲስ ኪዳን የተጠቀሱት የፈሪሳውያንና የጸሐፍት አባት ነበር። በዕዝራ ዘመን ከምርኮ የተመለሱ አብዛኛዎቹ አይሁዳውያን የራሳቸው የሆነውንና መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን የዕብራይስጥን ቋንቋ ስለማያውቁ ዕዝራና ሌሎች ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለእነርሱ ለመተርጎም ተገድደው ነበር። አብዛኛዎቹ አይሁድ የባቢሎንና የፋርስ የንግድ ቋንቋ የነበረውን አራማይክን ብቻ ያውቁ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት የመጠቁ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉ፥ በዚህ ሁኔታ በሚገባ የሠለጠኑ ሰዎችን ስም ዝርዝር።

መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ የተጻፉበት ጊዜ 

የመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ ጸሐፊ ማን እንደሆነ ስለማናውቅ የተጻፉበትንም ጊዜ በእርግጠኝነት ማወቅ አንችልም። በመጽሐፉ ውስጥ የተገለጡ ድርጊቶች የተፈጸሙት ከ538-420 ዓ.ዓ. ባለው ዘመን ነበር፤ ስለዚህ መጽሐፉ በ400 ዓ.ዓ. አካባቢ ተጠናቅቆ ሳይጻፍ እንዳልቀረ መገመት ይቻላል።

የመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ ሥረ – መሠረት 

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ዜና 36፡15-19 አንብብ። ሀ) የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስና ቅጥሮች ምን ሆኑ? ለ) የይሁዳ ሕዝብና ንጉሡስ ምን ሆኑ?

እንደምታስታውሰው በ2ኛ ነገሥትና በ2ኛ ዜና መጨረሻ ላይ የይሁዳ ሕዝብ በባቢሎናውያን መማረካቸውን ተመልክተናል። ቤተ መቅደሱና የኢየሩሳሌም ከተማም ተደምስሰዋል። ንጉሡም ተገድሉ ሕዝቡ ተማረኩ። ይህ ሁሉ የሆነው በ586 ዓ.ዓ. ነበር። ዋና ዋና የሆኑ ምርኮዎች የተፈጸሙት ሦስት ጊዜ ብቻ ቢሆንም፥ የባቢሎን ንጉሥ አይሁዳውያንን በምርኮ የወሰደው አራት ጊዜ ይመስላል። በመጀመሪያ፥ ዳንኤልና ሌሎች በምርኮ የተጋዙት በ605 ዓ.ዓ. ሲሆን፥ ሁለተኛ፥ ሕዝቅኤልና ንጉሡ ኢዮአኪን የተጋዙት በ597 ዓ.ዓ. ነበር። ሦስተኛ፥ በ586 ዓ.ዓ. ቤተ መቅደሱ የፈረሰበትና አብዛኛውን ሕዝብ የሚመለከት ዋናው ምርኮ ተፈጸመ፤ ነገር ግን ሌላ አራተኛ መማረክም በ582 የነበረ ይመስላል (ኤር. 52፡30)። የቀሩት አንዳንድ እስራኤላውያን ወደ ግብፅ ሸሽተው ሄዱ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: